የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከጥቅምት 5-11

4ኛ ትምህርት

Oct 15–21




የብሉይ ኪዳኑ ተስፋ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢዮብ 19፡25-27፣ 1 ጢሞ. 6፡16፣ መዝ. 49፣ መዝ. 71፣ ኢሳ. 26፡14፣19፣ ዳንኤል 12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፥ የተስፋን ቃል የተቀበለው፦ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው።” (ዕብ. 11፡17-19)

የ ብሉይ ኪዳን ተስፋ የተመሠረተው ነፍስ አትሞትም በሚለው የግሪክ ሃሳቦች ላይ ሳይሆን ስለ ሙታን የመጨረሻ ትንሣኤ በሚያስተምረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ ነው። ነገር ግን ከአሁን በኋላ የማይኖር፣ አመድ ሆኖ የተቃጠለ ወይም በሌላ መንገድ የጠፋ የሰው አካል እንዴት እንደገና ወደ ሕይወት ሊመጣ ይችላል? ምናልባትም ለብዙ መቶ ዘመናት አልፎ ተርፎም ለሺህ ዓመታት በሞት ያለፈ ሰው ማንነቱን መልሶ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች የሕይወትን ምስጢር እንድናሰላስል ያደርጉናል።

እኛ በሕይወት ሆነን እግዚአብሔር በየዕለቱ በቸርነቱ በሚሰጠን ሕይወት እየተደሰትን ነው። ከተፈጥሮ በላይ የሆነውን የሕይወትን አመጣጥ ለመረዳት ሳንጀምር፣ እግዚአብሔር በመጀመሪያ በቃሉ ኃይል ሕይወትን ካለመኖር ወደ መኖር እንዳመጣ እናውቃለን (ዘፍ. 1፣ መዝ. 33፡6፣ 9)። ታዲያ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሕይወትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከምንም ነገር መፍጠር ከቻለ የሰውን ሕይወት እንደገና የመፍጠር እና የቀድሞ ማንነቱን የመመለስ ችሎታውን ለምን እንጠራጠራለን? በዚህ ሳምንት በኢዮብ፣ በአንዳንድ የመዝሙረ ዳዊት ክፍሎች፣ በነቢዩ ኢሳይያስ እና በዳንኤል ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ስለ መጨረሻው ትንሣኤ የሚናገሩት ሐሳቦች በብሉይ ኪዳን ዘመናት እንዴት እንደነበሩ እናመለከታለን። *ለጥቅምት 12 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 6
Oct 16

እግዚአብሔርን አየዋለሁ


ኢዮብ 19፡25-27ን ከዮሐንስ 1፡18 እና 1 ጢሞ. 6፡16 ጋር ያነፃፅሩ። ኢዮብ እግዚአብሔርን ለማየት ሲጠባበቅ የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?



ህይወት ፍትሃዊ አይደለችም። ይህንን የምናየው በተለይ “መልካም ሰዎች” ሲሰቃዩ እና “ዓመፀኞች” ሲበለጽጉ ስናይ ነው (መዝ. 73፡12-17፣ ሚል. 3፡1418ን ይመልከቱ)። ለምሳሌ፣ ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበትና ቅን” እና “እግዚአብሔርን የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ነበር” (ኢዮብ 1፡1)። ያም ሆኖ ሰይጣን በተለያዩ አስጨናቂ መንገዶች እንዲያስጨንቀው አምላክ ፈቅዶለታል። ከአካላዊው አንፃር ሰውነቱ በሚያሠቃይ ሕመም ተበላሽቷል (ኢዮብ 2፡1-8)። ከቁስ አንፃር፣ ከብቶቹን እና ንብረቶቹን በብዛት አጥቷል (ኢዮብ 1፡13-17)።

በቤተሰቡ ውስጥ፣ አገልጋዮቹን አልፎ ተርፎም የራሱን ልጆች አጥቷል (ኢዮብ 1፡16፣18)። ከስሜት አንፃር እርሱ የገጠመው ነገር ንስሐ ባልገባባቸው ኃጢአቶች ምክንያት እንደሆነ በሚከሱ ጓደኞች ተከቧል (ኢዮ. 4፡1-5፣27፣ ኢዮብ 8፡1-22፣ ኢዮብ 11፡1-20)። ሚስቱም እንኳ እንዲህ ብላለች:- “እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት።” (ኢዮብ 2፡9)። ኢዮብ በአምላክና በሰይጣን መካከል እየተካሄደ በነበረው ዓለም ዓቀፋዊ ጦርነት ዋና ማዕከል እንደነበር አልተገነዘበም። በእነዚያ ተጋድሎዎች ተጨንቆ፣ ኢዮብ በመወለዱ ተጸጸተ እናም ባልወለድ ብሎ ተመኘ (ኢዮብ 3፡1-26)።

ነገር ግን፣ ለእግዚአብሔር ያለው በሁኔታ ያልተመሰረተ ታማኝነት በጥሩ ሁኔታ የተገለጸው “ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤” (ኢዮብ 13፡15) በሚሉት ቃላት ነው። በቅርቡ ሕይወቱ እንደሚጠፋ በማሰብ እንኳ ሞት የመጨረሻው እንደማይሆን አምኗል። በጠንካራ እምነት ምንም እንኳን ቢሞትም፣ አዳኙ አንድ ቀን እንደሚቆምለትና እሱም ኢዮብ ራሱ እግዚአብሔርን በሥጋው እንደሚያየው ተናግሯል (ኢዮ. 19፡25-27)። “ይህ የማያሻማ የትንሣኤ ፍንጭ ነው።”- The SDA Bible Commentary, vol. 3, p. 549

በእንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! በበሽታና በሥቃይ፣ በኢኮኖሚ ውድቀት፣ በማኅበራዊ ነቀፋና በስሜት መፈራረስ የተከበበው ኢዮብ አሁንም ከሞት የሚነሳበትንና የሚወደውን አዳኙን የሚያይበትን ቀን ሊጠብቅ ችሏል። እንዲያውም ኢዮብ ስለ ትንሣኤ የተናገረው ሐሳብ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ማርታ ለኢየሱስ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “[አልዓዛር] በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ” (ዮሐንስ 11:24)። ምንም እንኳ ከኢዮብ በተቃራኒ ማርታ ወዲያው ለእምነቷ ጠንካራ ማስረጃ ቢሰጣትም ኢዮብ ልክ እንደ ማርታ ይህን የተስፋ ቃል በእምነት መናገር ነበረበት። በአስቸጋሪ የህይወት ኢፍትሃዊነት ውስጥ እንኳን እግዚአብሔርን መታመንን የምንማረው እንዴት ነው?

ጥቅምት 7
Oct 17

ከመቃብር ኃይል


መዝሙር 49ን ያንብቡ። መዝሙረኛው ያለማስተማመኛ ከሚጠፉት በተቃራኒ በመጨረሻ ከሞት እንደሚነሳ እርግጠኛ እንዲሆን ያደረገው ምንድነው?



መዝሙር 49 “በሀብታቸው ስለሚታመኑ በሀብታቸውም ብዛት ስለሚመኩ” (መዝ. 49፡6) “ምድራቸውን በስማቸው ስለሚጠሩ” (መዝ. 49፡11) እና እራሳቸውን ለመባረክ ብቻ ስለሚኖሩ (መዝ. 49፡18) ስለ ሞኞች የተሳሳተ እምነት ይናገራል።)፣ ። ቤታቸውና ክብራቸው ለዘላለም እንደሚኖር ሆነው ይኖራሉ (መዝ. 49፡11፣17)። ሰነፎች ግን ክብራቸው እንደሚጠፋና እንደ አውሬም እንደሚጠፉ ይረሳሉ (መዝ. 49፡12)። “እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው፥ እረኛቸውም ሞት ነው፤ . . . ውበታቸውም ከመኖሪያቸው ተለይታ በሲኦል ትፈርሳለች።” ( መዝ. 49:14)።

ኢዮብ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንደተናገረው፣ “ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፤’ (ኢዮብ 1፡21፣ 1 ጢሞ. 6፡7)። መዝሙረኛው ደግሞ ሞኞችም ሆኑ ጠቢባን “ሀብታቸውን ለሌሎች ትተው” (መዝ. 49:10) እንደሚሞቱ ተናግሯል። በሞኞቹና(በሰነፎቹ) በጠቢባኑ መካከል ግን ከፍተኛ ልዩነት አለ። በአንድ በኩል በራሱ ጊዜያዊ ንብረቶችና ስኬቶች ዋስትና ለማግኘት ቢሞክርም የሚጠፋው ሞኝ አለ። በአንጻሩ ጠቢቡ ከሰዎች እይታና ከመቃብር ባሻገር እግዚአብሔር ያዘጋጀለትን የክብር ዋጋ ያያል (1ጴጥ. 1፡4)። ይህን ግንዛቤ በአእምሮው ይዞ መዝሙረኛው በልበ ሙሉነት እንዲህ ሊል ይችላል፣ “ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል።” (መዝ. 49፡ 15)።

ከብሉይ ኪዳኑ ተስፋ ጋር በሚስማማ መልኩ፣ ይህ አባባል መዝሙረኛው ልክ ሲሞት ነፍሱ ወዲያው ወደ ሰማይ እንደምትበር የሚያመለክት አይደለም። መዝሙረኛው በመቃብር ውስጥ ለዘላለም እንደማይኖር መናገሩ ነው። እግዚአብሔር ከሞት የሚቤዥበት እና ወደ ሰማያዊ ፍርድ ቤት የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል። አሁንም ስለወደፊቱ ትንሣኤ እርግጠኝነት ተገልጧል፣ ይህም ለአሁኑ ሕይወት ተስፋን፣ ዋስትናንና ትርጉምን ያመጣል። ስለዚህ በዚህች አጭር ህይወት ውስጥ ሞኞች ለራሳቸው ሊሰበስቡ ከሚችሉት በላይ ጠቢቡ የበለጠ ክብር ያለው እና ዘላለማዊ ሽልማትን ያገኛል።

እርስዎ በራሳቸው ሃብት እና ስኬት የሚታመኑትን ሰዎች ሞኝነት ለማየት የቻሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ነበሩ? አይናችንን በመስቀሉ ላይ ማድረግ ተመሳሳይ ስህተት ውስጥ እንዳንወድቅ የሚጠብቀን እንዴት ነው?

ጥቅምት 8
Oct 18

ከምድር ጥልቅ


መዝሙር 71ን ያንብቡ። መዝሙረኛው “ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው?



በመዝሙር 49 ላይ በሀብቱ ከሚታመን ሰነፍ ከያዘው የውሸት ዋስትና በተቃራኒ የትንሣኤ ተስፋን የሚገልፅ ልብ የሚነካ መግለጫ አግኝተናል። በመዝሙር 71 መዝሙረኛው እግዚአብሔር ትቶታል በሚሉ ጠላቶች እና የሐሰት ከሳሾች ተከቦ ሳለ ከእግዚአብሔር ዘንድ ደህንነትን እና ተስፋን ይፈልጋል (መዝ. 71፡10-11)። መዝሙረኛው በፈተናዎቹ ውስጥ ሆኖም አምላክ በቀደሙት ጊዜያት እንዴት እንደተንከባከበው በማስታወስ መጽናኛና ማረጋገጫ አገኘ። በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር ከመወለዱ ጀምሮ እንደደገፈው እና እንዲያውም ከእናቱ ማኅፀን እንዳወጣው ተረድቷል (መዝ. 71፡6)። ከዚያም፣ እግዚአብሔር ከልጅነቱ ጀምሮ እንዳስተማረው አምኗል (መዝ. 71፡17)።

እግዚአብሔር ዓለቱና ምሽጉ እንደ ሆነ እርግጠኛ ሆኖ፣ መዝሙረኛው፣ “በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ።” (መዝ. 71፡3) “በእርጅና ጊዜ አትጣለኝ; ኃይሌ ባለቀ ጊዜ አትተወኝ” (መዝ. 71፡9)። “አምላኬ ሆይ ከእኔ አትራቅ። አምላኬ ሆይ እኔን ለመርዳት ፍጠን!” (መዝ. 71:12)። ከዚያም መዝሙረኛው አክሎ፣ “ታላቅና ከባድ መከራን ያሳየኸኝ አንተ እንደገና ሕያው ታደርገኛለህ፣ ከምድር ጥልቅም ታወጣኛለህ” (መዝ. 71፡20)።

“ከምድር ጥልቅ” የሚለው አገላለጽ የመዝሙረኛው የወደፊት ትንሣኤ ቀጥተኛ ፍንጭ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን አውዱ ምድር የዋጠችውን ያክል መዝሙረኛውን ጥልቅ የመንፈስ ጭንቀት እንደያዘው የሚናገር ዘይቤያዊ መግለጫ መሆኑን የሚደግፍ ይመስላል (ከመዝ. 88:6 እና መዝ. 130:1 ጋር ያስተያዩት)። ስለዚህ “በዋነኛነት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፣ ነገር ግን ስለ አካላዊ ትንሣኤ የሚጠቁም ፍንጭ ነው” ልንል እንችላለን። Andrews Study Bible note on Ps. 71:20።

በመጨረሻ፣ ልንረዳው የሚገባው ነገር፣ ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ እግዚአብሔር በዚያ አለ፣ እሱ ያስባል፣ እና በመጨረሻም፣ ተስፋችን በዚህ ህይወት ውስጥ ሳይሆን በሚመጣው ህይወት ውስጥ የሚገኝ አለመሆኑን ነው—ከእኛ በኋላ በኢየሱስ ውስጥ ያለን የዘላለም ህይወት በዳግም ምጽአቱ ትንሣኤ ነዉ። ሁላችንም አንዳንድ አስፈሪ የተስፋ መቁረጥ ጊዜያት አሳልፈናል። ነገር ግን ጌታ ከዚህ በፊት ከእኛ ጋር በነበረባቸው መንገዶች ላይ ማተኮር በእምነት ወደፊት ለመግጠም እና እርሱ ሩቅ በሚመስልበት ጊዜ እንድንተማመን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 9
Oct 19

“ሙታንህ በሕይወት ይኖራሉ”


ኢሳይያስ 26:14 እና 19ን ያንብቡ። ለዘላለም በሚጠፉት (ኢሳ. 26:14፣ ሚል. 4:1⁠) እና የዘላለም ሕይወት በሚያገኙት (ኢሳ. 26:19) መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?



የኢሳይያስ መጽሐፍ በእግዚአብሔር ታላቅነትና በእኛ ደካማነት መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ያሳያል (ኢሳይያስ 40ን ይመልከቱ)። እንደሚደርቅ ሣር እንደሚረግፍ አበባ ብንሆንም የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል (ኢሳ. 40፡6-8)። እኛ ኃጢአተኞች ብንሆንም የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ ለሰው ልጆች ሁሉ ነው፤ ይህ ፀጋም ውጤታማ የሚሆነው ቃል ኪዳኑን የራሳቸው በሚያደርጉት እና ሰንበትን በሚጠብቁት አሕዛብም ጭምር ላይ ነው (ኢሳይያስ 56)።

በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የትንሣኤ ተስፋ በከፍተኛ ሁኔታ ተነግሯል። ቀደም ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሳኤው የተነገሩት ኃሳቦች ከግለሰብ አንጻር (ኢዮ. 19፡25-27፣ መዝ. 49፡15፣ መዝ. 71፡20) ቢሆኑም ነቢዩ ኢሳይያስ ግን ትንሳኤው ራሱንና አማኞችን ሁሉ እንደሚያጠቃልል ተናግሯል (ኢሳ. 26:19)። ኢሳይያስ 26 የኃጢአንንና የጻድቃንን የተለያየ እጣ ፈንታ ያነጻጽራል። በአንድ በኩል ክፉዎች ሞተው ይቆያሉ፤ ቢያንስ እስከ “ሁለተኛው ሞት” ድረስ (ራዕ. 21፡8) ወደ መኖር አይመጡም። ፈጽመው ይጠፋሉ፤ መታሰቢያቸውም ሁሉ ለዘላለም ይጠፋል (ኢሳ. 26፡14)። ይህ ክፍል ከሞት በኋላ በሕይወት የሚተርፉ ነፍሳት ወይም መናፍስት እንደሌሉ የሚያስተምረውን ትምህርት ያጎላል። በሌላ ቦታ ላይ በኋላ ስለሚመጣው የክፉዎች የመጨረሻ ጥፋት ሲናገር ክፉዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚቃጠሉ “ሥርንና ቅርንጫፍንም”(ሚል. 4፡1) እንደማይቀርላቸው ተናግሯል ።

በሌላ በኩል ደግሞ የሞቱት ጻድቃን የተባረከ ዋጋቸውን ለመቀበል ከሞት ይነሣሉ። ኢሳይያስ 25 ጌታ አምላክ “ሞትን ለዘላለም እንደሚውጥ” እንዲሁም “እንባን ሁሉ እንደሚያብስ” (ኢሳ. 25፡8) ተናግሯል። በኢሳይያስ 26 ላይ የሚከተለውን ቃል እናገኛለን፡- “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።” ( ኢሳ. 26:19)። ከሞት የተነሱት ጻድቃን ሁሉ ጌታ ለሰዎች ሁሉ በሚያዘጋጀው አስደሳች በዓል ላይ ይሳተፋሉ (ኢሳ. 25፡ 6)። የመጨረሻው ትንሳኤ በሁሉም ዘመናት ያሉ ጻድቃንን ሁሉ በክርስቶስ አስቀድመው የሞቱትን ወዳጆችዎን ጨምሮ በአንድ ላይ ይሰበስባል።

መሞታችን ለእኛ የሁሉም ነገር ፍጻሜ ቢሆን፣ ለማንም ምንም ማለት ባይሆን፣ ምንም ዓይነት ተስፋ፣ ዋስትና ባይኖረን ብለው ያስቡ። እና ከዚያ ይባስ ብሎ እኛን የሚያውቅ ሁሉ ይጠፋል፤ ብዙም ሳይቆይ እኛ በጭራሽ እንዳልኖርን እና ህይወታችን ምንም ትርጉም እንደሌለው ይሆናል። ይህ እጣ ፈንታ እኛ ካለን ተስፋ ጋር እንዴት ይቃረናል?

ጥቅምት 10
Oct 20

በምድር ትቢያ ውስጥ ያንቀላፉት


እንደምናየው፣ አዲስ ኪዳን ስለ ሙታን ትንሣኤ ብዙ ይናገራል። ቀደም ሲል እንዳየነውም የሙታን ትንሳኤ ኃሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥም የተገለጠ ነው። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ሰዎች እኛ እንዳለን የመጨረሻው ትንሣኤ ተስፋ ነበራቸው። በኢየሱስ ዘመን ትኖር የነበረችው ማርታ ይህ ተስፋ ነበራት (ዮሐንስ 11፡24)። በዚያን ጊዜም ቢሆን አይሁዳውያን በመጨረሻ ስለሚኖረው ትንሣኤ የተወሰነ እውቀት እንደነበራቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምንም እንኳ ሁሉም ባያምኑም (የሐዋ. ሥራ 23:8)። ዳንኤል 12ን ያንብቡ። በዚህ ታላቅ ነቢይ ጽሑፎች ውስጥ ምን የትንሣኤ ተስፋ አለ?



ዳንኤል 12፡1 ማንነቱ ብዙ ክርክር የተደረገበትን “ታላቁን አለቃ” ሚካኤልን ያመለክታል። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉት እያንዳንዱ ታላላቅ ራእይ በክርስቶስና በመንግሥቱ መገለጥ ስለሚጠናቀቁ፣ ይህን ክፍል በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆን አለበት። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ተመሳሳዩን መለኮታዊ አካል “የሠራዊቱ አለቃ” (ዳን. 8፡11)፣ “የመኳንንቱ አለቃ” (ዳን. 8፡25)፣ “አለቃው መሲሕ” (ዳን. 9:25)፣ እና በመጨረሻም “ታላቁ አለቃ ሚካኤል” (ዳን. 12፡1) በማለት ሲገልፅ እንመለከታለን። ስለዚህ ሚካኤልንም ክርስቶስን ልንለው ይገባል።

እስካሁን ያየናቸው የብሉይ ኪዳን ንባቦች (ኢዮ. 19፡25-27፣ መዝ. 49፡15፣ መዝ. 71፡20፣ ኢሳ. 26፡19) ሁሉም ስለ ጻድቃን ትንሣኤ ይናገራሉ። ዳንኤል 12 ግን ስለ ጻድቃንና ዓመፀኞች ትንሣኤ ይናገራል። ሚካኤል ሲነሳ፣ “በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፣ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና” (ዳን. 12፡2)። ብዙዎች ይህ ጥቅስ ታማኝ እና ታማኝ ስላልሆኑ አንዳንድ ሰዎች፣ በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ስለሚኖረው ልዩ ትንሣኤ እንደሚናገር አድርገው ይመለከቱታል።

“መቃብሮች ተከፈቱ፤ እና ‘በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች... ነቅተዋል፣ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ውርደት።’ (ዳንኤል 12፡2) በሦስተኛው መልአክ መልእክት አምነው የሞቱ ሁሉ ሕጉን ከጠበቁት ጋር የእግዚአብሔርን የሰላም ቃል ኪዳን ለመስማት ከመቃብር በክብር ይወጣሉ። “የወጉትም”(ራእይ 1:7)፣ በክርስቶስ ላይ በደረሰው ስቃይ ያፌዙበት፣ እውነቱንና ሕዝቡን በኃይል የተቃወሙት፣ በክብሩ እንዲያዩትና በታማኞችና በታዛዦች ላይ የሚሆነውን ክብር ለማየት ተነሥተዋል።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ. 637.

ጥቅምት 11
Oct 21


ተጨማሪ ሀሳብ


ነቢያትና ነገስታት ከሚለው መጽሐፍ ላይ “የወደፊቱ ክብር ራዕዮች” የሚል ርዕስ ያለውን ክፍል ከገፅ 722-733 ድረስ ያንብቡ። ዘመናዊ ሳይንስ ሁሉም ቁስ አካል በአተሞች የተዋቀረ መሆኑን ያስተምራል፤ አተሞቹ እራሳቸው ደግሞ ኳርክ እና ሌፕተን ከሚባሉ ሁለት ትናንሽ ቅንጣቶች የተሠሩ ናቸው። እነዚህም የቁሶች ሁሉ ግብዓቶች ናቸው ተብሎ ይታመናል። እንግዲያውስ በቁሳዊው ዓለም ኳርክ እና ሌፕተን ከሆኑ፣ ያን ዓለም የፈጠረውና የሚደግፈው አምላክ እኛን የሚያስነሣንበት ጊዜ ሲደርስ ኳርኮችንና ሌፕተኖችን እንደገና ማዋቀር አይችልም? በእግዚአብሔር መኖር የማያምነው በርትራንድ ራስል በትንሣኤ ላይ እያፌዘ፣ ሰው በላዎች የበሏቸው ሰዎችስ ምን ይሆናሉ ብሎ ጠየቀ፤ ምክንያቱም ሰውነታቸው በአሁኑ ጊዜ የሰው ሥጋ የሚበሉ ሰዎች ሰውነት ውስጥ ነው፣ እናም በትንሣኤስ ማን ምን ይደርሰዋል? ነገር ግን ጌታ በቀላሉ በየትኛውም ቦታ የሚገኙትን ኳርኮችን እና ሌፕቶኖችን ወስዶ ስለእያንዳንዳችን ባለው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ከእነዚያ ኳርኮች እና ሌፕቶኖች መልሶ ሊገነባን ይችላል ብለን ብናስብስ? እሱ የእኛን ኦሪጅናል አይፈልግም፤ ከየትኛውም ሊሠራን ይችላል።

ወይም ቃል ብቻ ተናግሮ አዲስ ኳርኮችን እና ሌፕቶኖችን ወደ መኖር ካመጣ በኋላ ከዚያ መቀጠል ይችላል። እንዴትም ቢያደርግ አጽናፈ ሰማይን የፈጠረው አምላክ በትንሳኤ ቀን እንደሚያደርግ ቃል እንደገባው እንደገና ሊፈጥረን ይችላል። “ሕይወት ሰጪው በደሙ የገዛቸውን በመጀመሪያው ትንሳኤ ይጠራቸዋል፤ እናም እስከዚያች የድል ሰዓት ድረስ፣ የመጨረሻው መለከት እስኪነፋ እና ሰፊው ሰራዊት ወደ ዘላለማዊ ድል እስከሚወጣ ድረስ፣ ያንቀላፉት ቅዱሳን ሁሉ በደህና ይጠበቃሉ፤ እግዚአብሔር ስማቸውን የሚያወቃቸው እንደ ውድ ዕንቁ ተጠብቀዋል። በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በውስጣቸው ባደረው በአዳኙ ኃይል እና የመለኮታዊ ተፈጥሮ ተካፋዮች በመሆናቸው ከሞት ወጥተዋል።”— Ellen G. White Comments፣ The SDA Bible Commentary፣ Vol. 4, ገጽ. 1143.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ወደ 2 ትሪሊዮን የሚጠጉ እያንዳንዳቸው በብዙ ቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ከዋክብት የተሠሩ ጋላክሲዎች አሉ ተብሎ ይገመታል። በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ያሉት ፕላኔቶች በፀሐይ እንደሚዞሩ እነዚህንም ከዋክብት ፕላኔቶች ይዞሯቸዋል። እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ከዋክብት የፈጠረው ብቻ ሳይሆን የሚደግፋቸውንና በስም የሚያውቀውን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ኃይል ያሰላስሉ(መዝ. 147፡4)። ይህ አስደናቂ እውነታ አምላካችን ሙታንን እንደሚያስነሳ ባያረጋግጥም ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለውና እንደ ትንሣኤ ያለ ነገር ከአቅሙ በላይ የማይሆንበትን ምክንያት የሚገልፅልን እንዴት ነው?

2. ዕብራውያን 11 በጥንት ዘመን የነበሩ “የእምነት ጀግኖች” ተብለው የሚጠሩት ታማኝነት እና ከፊታቸው የሚጠብቁትን አጉልቶ ያሳያል። ይህ ምዕራፍ ከኢየሱስ ትንሣኤ በፊትም ቢሆን በብሉይ ኪዳን የነበሩ ገፀ-ባሕርያት ስለነበራቸው ተስፋ ያለንን ግንዛቤ እንዴት ሊያበለጽግ ይችላል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL