የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በፈተና ውስጥ ከክርስቶስ ጋር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከሐምሌ 9-15

4ኛ ትምህርት

Jul 16 - Jul 22




የአንጥረኛውን ፊት ማየት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ 5:16, 1 ቆሮ 4:9, ኤፌ 3:10, ኢዮ 23:1-10, ማቴ 25:1-12, ዳን 12:1-10, ኤፌ 4:11-16ን አንብቡ።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን። ( 2 ቆሮ 3፡18).

ኤ ሚ ከርሚካኤል የሚባል ሰው ጥቂት የልጆችን ቡድን በህንድ ወደሚገኘው የወርቅ አንጥረኛ ቤት ወሰዳቸው። በከሰል እሳት መካከል ትንሽ የጣሪያ ቆርቆሮ አለ። በዚያ የቆርቆሮ ቁራጭ ላይ የጨው፣ተምሪነደ የሚባል የጥንት ምስራቃውያን አገር ይበቅል የነበረ ዛፍ ፍሬ፣ እና የብሎኬት ስብርባሪ አቧራ ቅልቅል ነበር። በነዚህ ቅልቅሎች ውስጥ ተቀብሮ የነበረው ወርቅ ነበር። እሳቱ ቅልቅሎቹን ሲያቃጥል ወርቁ ንጹህ ይሆናል። አንጥረኛውም ወርቁን በመቆንጠጫ ከእሳቱ ውስጥ ያወጣውና ንጹህ ካልሆነ ፣ እንደገና ሌላ ውህዶች ውስጥ አድርጎ እሳት ውስጥ ይከተዋል። በማንኛውም ጊዜ ወርቁ እንደገና በእሳት ሲደረግ የእሳቱ ኃይል እንዲጨምር ይደረጋል። ከዚያም የጎብኝዎቹ ቡድን ፣‹‹ ወርቁ መንጻቱን በምን ታውቃለህ ?”ብለው ጥያቄ ጠየቁት፣ እርሱም ሲመልስ ‹‹ ፊቴን በውርቁ ላይ ማየት ስትል ነው።›› አላቸው። ” Amy Carmichael, Learning of God (Fort Washington, PA: Christian Literature Crusade, 1989), p. 50. እግዚአብሄር እንደወርቅ እንድንነጻና፣ እርሱን ወደ መምሰል እንድንደርስ፣ እኛን ሊያጠራን ይፈልጋል። ያ እጅግ አስገራሚ የእግዚአብሔር ግብ ነው፣ እንዲያውም በጣም የሚያስገርም የሚሆነው፣ ክርስቶስን የመምሰል ባህሪይ በእኛ የሚቀረጸው በፈተና እሳት ውስጥ ስናልፍ ብቻ መሆኑ ነው።

ሳምንቱን በአጭሩ፡ መከራ፣ በማጽዳት (ክርስቲያኖችን በማጥራት) ስራ ውስጥ ያለው ሚና ምንድነው? ይህንን ሁሉ ከታላቁ ተጋድሎ አንጻር የምናስተውለው እንዴት ነው? *የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሐምሌ 16 ሰንበት ይዘጋጁ ሐምሌ 16

ሐምሌ 10
July 17

“በእርሱ አምሳል”


“ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ ፣ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና” (ሮሜ 8:29)። መጀመርያ እግዚአብሔር በአምሳሉ ፈጠረን። ( ዘፍ 1፡ 27 ) ። ነገር ግን ያ አምሳል በኃጢአት ምክንያት ተበላሸ።

በሰብዓዊ ዘር ላይ የእግዚአብሔርን አምሳል መበላሸት ማየት የምንችለው በምን በምን መንገዶች ነው?



ይህ ግልጽ ነው። እኛ ሁላችንም በኃጢአት ተበላሽተናል። ሮሜ 3፡ 10-19። ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ሀሳብ ጥንት ወደ ነበርንበት ሁኔታ መመለስ ነው። የዛሬው ጥቅሳችን የሚገጥመው ከዚህ ጋር ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ራሳቸውን የሰጡ ሁሉ የልጁን መልክ እንዲመስሉ እግዚአብሔር ያቀደውን የሚገልጽ ነው። (ሮሜ 8፡29)

ነገር ግን ሌላ እይታ አለ። ‹‹የእግዚአብሔር አምሳል በሰው ውስጥ እንደገና እንዲፈጠር ነው። የእርሱን ህዝብ ባህሪይ ፍጹም በማድረግ የእግዚአብሄር ክብር፣ የጌታችን ክብር፣ አብረው ይሰራሉ›› ኤሌን ዋይት የዘመናት ምኞት ገጽ 671።

ኤለን ዋይት ከላይ ባለው ጥቅስ የተናገረችውን እንዴት ያስተውሉታል እዮ 1፣ ማቴ 5፡15 1 ቆሮ 4፡9 ኤፌ 3፡10 በተጨማሪ መልከቱ።



እንደ ክርስቲያን፣ በዓለማት(ፈለክ) ድራማ መካከል መሆናችንን አንረሳዉም። በክርስቶስና በሰይጣን መከከል ያለው ታላቁ ተጋድሎ በሁላችን ዙሪያ ከጥንት ጀምሮ እስከአሁን እየተካሄደ ነው። የውጊያው ብዙ መልክ እና መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ፣ ብዙዎቹ ነገሮች ድብቅ ቢሆኑም ፣ እናም በዚህ ድራማ ፣ በህይወታችን ለክርስቶስ ክብር ለማምጣት ሁሉን የምንተው መሆናችንን እናስተውላለን::

በትልቅ ስታድየም ውስጥ እንዳለን እናስብ። በአንዱ የተመልካቾች መቀመጫ ለይ ለክርስቶስ ታማኝ የሆኑ ሰማያዊ አካላት ተቀምጠዋል። በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ከሰይጣን ጋር የወደቁ ተቀምጠዋል። ላለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ተጫውተው ከሆነ፣ ህይዎትዎ የትኛው ጎራ ነው የተሻለ የሚያስደስተው። መልስዎ ስለ ህይወትዎ የሚናገረው ምንድነው?

ሐምሌ 11
July 18

እምነት፣ በሚያነጻው እሳት ውስጥ


ውጊያ ውስጥ መሆን አንድ ነገር ነው ፤ በዚያው ውጊያ ውስጥ ተሳታፊ ኃይሎችን ለማየት አለመቻል ሌላ ነገር ነው። ክርስቲያኖች የምንዋጋው ይህንን ዓይነት ውጊያ ነው። ተዋጊ ኃይላት እንዳሉ በህይወታችን እናውቃለን፤ ሆኖም ‹‹ በማይታየው›› በእርሱ በመታመን በእምነት ወደ ፊት እንገፋለን፡ (እብ 11፡27) ኢዮ 23:1-10ን ያንብቡ። የኢዮብ ትግል ሁኔታ ምን ይመስላል? ማየት ያልቻለው ምንድነው? በተቃራኒው ደግሞ መከራው ብዙ ቢሆንም በእምነት የተቀበላቸው ነገሮች ምንድናቸው?



አስቸጋሪ በሆነ ፈተና መካከል እንኳ፣ ኢዮብ ጌታን ታመነ። ምንም ቢሆን ፣ ኢዮብ ጸና። ጸንቶ እንዲቆይ ካደረገው ነገር አንዱ ወርቅ ነው። የወርቅ ሜዳልያ አይደለም፤ ይልቁንም፣ የወደፊቱን አርቆ በተመለከተ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር በመጣበቅ ቢጸና፣ ከፈተናው ውስጥ እንደ ወርቅ ነጥሮ ሊወጣ እንደሚችል ተገንዝቧል። ከመጋረጃው በስተጀርባ እየሆነ ስለነበረው እኛ ስለማናውቀው ጉዳይ ኢዮብ ምን ያህል ያውቅ ነበር? ከእርሱ ምንም ያህል የተደበቀ ቢሆንም፣ እርሱ ግን በመከራው እሳት ውስጥ ጸና። እሳቱን ትፈራለህ? ነገሮች የሚፈጥሩት ሙቀት ያስጨንቅሃል?

ምናልባት የእግዚአብሔር ፈተናዎች ለመግለጽ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ችግሩ ምናልባት አዲስ ስራን መልመድ ወይም አዲስ ቤት መልመድ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በሥራ ቦታ ያለውን ሸካራ የሆነ የአመራር ፣ ወይም በራስዎ ቤተሰብ ውስጥ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። ህመም ወይም ገንዘብ ማጣት ሊሆን ይችላል። ለማስተዋል ከባድ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ግን አንተን ለማንጻት እና የእርሱን ምስል በውስጥህ ለመቅረጽ ይጠቀምበታል።

በዚህ ስፍራ እንደ ወርቅ መንጠሩ ለኢዮብ ፤ በአንድ ነገር ላይ ዓይኑን መትከሉ ፣ ከመከራው እንዲወጣ ጠቅሞት ነበር። ይህ ለኢዮብ ባህሪይ፣ የሚያነጻውን የመከራና የፈተና እውነታዎች በትክክል የተረዳ ስለመሆኑ ኃይለኛ የሆነ ምስክርነት ነው። በተጨማሪ ደግሞ እነዚህን ፈተናዎች ባያስተውላቸውም፣ ፈተናዎች ለማንጻት እንደሚሆኑ ተረድቷል። በእርሰዎ ተሞክሮ ፈተናዎች እንዴት ያነጻሉ? ከመከራ ሌላ ለማንጻት የሚሆኑ መንገዶች ምንድናቸው?

ሐምሌ 12
July 19

የክርስቶስ የመጨረሻ ቃላት


ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ሊሞት ተቃርቧል። እንደ ማቴዎስ ወንጌል ዘገባ፣ የኢየሱስ የመጨረሻ እራት ጊዜ ለደቀመ-ዛሙርቱ፣ ስለ አስርቱ ቆነጃጅት ደናግላን፣ ስለ በጎችና ፍየሎች በምሳሌ በማስተማር ነበር ያሳለፈው። ይህ ምሳሌ የክርስቶስን ዳግም ምጻት ስንጠባበቅ ከሚኖረን አኗኗር ጋር የተቆራኘ ታሪክ ነው።

በአስሮቹ ቆነጃጅት ምሳሌ (ማቴ 25:1-12) ብዙዎች ማብራሪያ አስተያየት የሰጡ ሰዎች ዘይቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚወክል ተናግረዋል። ኤለን ዋይትም በዚህ ትስማማለች፣ በተጨማሪ ይህ ዘይት ባህሪያችንን የሚወክል ሆኖ ማንም ሊሰጠን የማይችለው ነው።

ምሳሌውን ያንብቡ። የታሪኩ ትርጉም የሚለወጠው በየትኛው መንገድ ነው፣ ዘይቱን እንደ መንፈስ ቅዱስ በመውሰድ ወይስ እንደ ክርስቶስ ባህሪይ ሲወስዱት? የዚህ ታሪክ እንደምታ ለእርስዎ ምንድነው? ዘይቱ መንፈስ ቅዱስን ወይስ ክርስቶስን የሚመስል ባህሪይ? መንፈስ ቅዱስ: ______________________________________________________________



ባህሪይ:______________________________________________________________________



በማቴ 25፡31-46 ያለውን የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ያንብቡ። በጎቹንና ፍየሎቹን ለመለየት ጥቅም ላይ የዋሉት መመዘኛዎች ምንድናቸው?



ንጉሱ በጎቹንና ፍየሎቹን የሚለየው ሥራቸውንና ባህሪያቸውን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ልብ በል። በዚህ ስፍራ ምንም እንኳ ክርስቶስ እያስተማረ ያለው ደህንነት በሥራ ባይሆንም፣ የባህሪይ ዕድገት በድነት ዕቅድ እንዴት አስፈላጊ እንደሆነና በእውነት በክርስቶስ የዳኑት ባህሪዩን በህይወታቸው እንደሚያነጸባርቁ እንመለከታለን።

ባህሪይ ማለት እንደ ግለሰብ በጨለማ ውስጥ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ነው። ማንም በማያይበት ጊዜ እርስዎ ምን ዓይነት ሰው ነዎት? ይህ እርስዎ ማምጣት ስላለብዎት ለውጥ ምን ይነግርዎታል?

ሐምሌ 13
July 20

“ጠቢባን”


ትናንትና ባህሪይ የክርስቶስን ምጻት ለሚጠባበቁት አስፈላጊ እንደሆነ ተመልክተናል። ዛሬ በተለየ ሁኔታ ባህሪይ በክርስቶስ ምጻት ወቅት በህይወት ለሚኖሩት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንመለከታለን። ዳን 12፡1-10ን ያንብቡ። የታሪኩ አውድ ምንድነው? የትኛውን ዘመን የምድር ታሪክ ነው የሚወክለው? በጣም አስፈላጊ የሆነው፣ በዚህ ጊዜ ስለሚኖረው የእግዚአብሔር ህዝብ ባህሪይ ይህ ጥቅስ ምን ያሳየናል? ከኃጢአተኞች በተቃራኒ የተሰጣቸው ባህሪ ምን ይመስላል? ራዕይ 22፡11ን ያንብቡ።



ዳንኤል ከክርስቶስ ምጻት በፊት ከማንኛውም ዘመን ጋር የማይወዳደር የጭንቀት ጊዜ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። በዳን 12፡3፣10 በዚህ ጊዜ ጻድቃንና ኃጥአተኞች እንዴት እንደሚሆኑ ተነግሯል። ክፉዎች‹‹ ክፉ ያደርጋሉ›› (ዳን 12፡10) በተቃራኒው በቁጥር 3 ላይ ጻድቃን ደምቀው ያበራሉ ምናልባትም ነጽተው ዕድፍ አልባ ሆነዋል። በዚህ የመከራ ጊዜ ህዝብ ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚያ ድረስ ያልነበረ ” (ዳን 12:1):: በአንጻሩ ኃጢአተኞች ‹‹አያስተውሉም›› ፣ ጻድቃን ግን ‹‹ጥበበኞች›› ናቸው።

ምን ተረዱ? ሂሳብ፣ሳይንስ ወይስ ከፍተኛ ትችት? ምሳሌ 1፤7 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ::ምናልባትም፣ በዚህ አውድ ፣ ‹‹ጠቢባን›› ጠቢብ የተባሉት የማጠቃለያው ሁኔታ ማስተዋል ስላላቸው ልሆን ይችላል፣ እርሱም የመከራ ጊዜው ይሆናል። እነርሱ በሚያስደንቅ ነገር አይወሰዱም፣ ከሚያጠኑት የእግዚአብሔር ቃል ይህ እንደሚመጣ ያውቁታል። እና በጣም አስፈላጊው፣ እነርሱ ይህንን የመከራ ጊዜ ባህሪያቸውን ለማንጻት የመጣ መሆኑን በማወቅ ፈቅደው ይጠብቃሉ፣ በአንጻሩ ደግሞ፣ ኃጢአተኞች፣ በአመጻቸው የበለጠ እየገፉበት ይሄዳሉ። እዚህ የተሰጠን ወሳኙ ነጥብ፣ ሰዎች በመንጻትና በመጥራት ሂደት ውስጥ መሆናቸው ነው።

ምንም እንኳ እነዚህን ጥቅሶች በመጨረሻው ዘመን አውድ ያየናቸው ቢሆንም ፣ በአሁኑ ጊዜ ለእኛ ይህ የማንጻት እና የማጥራት ሂደት ምን እንደሚመስል የበለጠ እንድንረዳ ምን መሰረታዊ ሥርዓቶችን መረዳት እንችላለን?





ሐምሌ 14
July 21

ባህሪይና ማህበረሰብ


እንዲህ የሚል መዝሙር አለ ፡- ‹‹እኔ ደንጊያ ነኝ፣ እኔ ደሴት ነኝ›› ለብቻ ለመቆም እንደዚህ አስበው ያውቃሉ? ሰዎች እንዲህ ስሉ ሰምተው ይሆናል ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር ያለኝ ግኑኝነት የግል ጉዳዬ ነው፣ ስለዚህ ነገር ከማንም ጋር መነጋገር አልፈልግም››

ኤፌ 4:11-16ን ያንብቡ። እዚህ ስፍራ ጳውሎስ የሚያነሳው ሀሳብ ምንድነው? ለማህበረሰቡ እየሰጠው ያለው ሚና ምንድነው?



ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ፣ ቤተክርስቲያንን የሚገልጸው እንደ አካል ነው። ክርስቶስ ራስ ሲሆን ህዝቦቹ ሌላው አካል ናቸው። አፌሶን 4:13ን ስታነቡ ይህን በሚመስል ማህበረሰብ ውስጥ የመኖርን ዋነኛ ዓላማ፡እርሱም‹‹ የክርስቶስን ሙላት›› ለመለማመድ ነው። ለዚህም አንዳችን ለሌላችን እናስፈልጋለን!

ለብቻ ክርስቲያን መሆን ይቻላል። በእርግጥ፣ ለብዙ ዘመናት እየተሰደቡ ፣ እየተሰደዱ እና በብዙ መከራ ውስጥ እያለፉ ስለነበር ለብቻቸው መቆም ብዙውን ጊዜ ግድ ይል እንደነበር እናውቃለን። ሰዎች በዙሪያቸው ከከበቧቸውና ከሚገዳደሯቸው ነገሮች አኳያ ተጨፍልቀው አለመቅረታቸው ታላቅ የፈጣሪ ኃይል ማሳያ ነው። ነገር ግን ፣ ይህ እውነት ቢሆንም፣ ጳውሎስ አንድ እውነት ላይ ትልቅ ትኩረት ያደርጋል። ይህም የክርስቶስን እውነት ልናንጸባርቅ የምንችለው እርስ በርሳችን በህብረት ስንሆን ብቻ ነው። በኤፌሶን 4 ፡11- 16 ጳውሎስ፣ በእኛ በክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ የክርስቶስ ሙላት ከመገለጡ በፊት ምን መሆን አለበት ይላል?



የክርስቶስን ሙላት የሚያንጸባርቅ አንድ ማህበረሰብ እና አንድ ግለሰብ የሚያሳዩት ልዩነት ምንድነው። የዚህ መገለጫ በታላቁ ተጋድሎ አውድ ምንድነው? ኤፌ 3፡ 10ን ያንብቡ።



በግል ወይም ከእንግዳ ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ጥሩ መሆን ቀላል ነው፣ ነገር ግን በማትወዷቸው ሰዎች እና በትክክል የምታውቋቸው ሰዎች ባሉበት መልካም መሆን በእርግጥ ከባድ ነው። ይህ ማለት ለእነዚህ ሰዎች ጻጋንና ቸርነትን ስናሳያቸው፣ ስለ እውነትእና ስለ ክርስቶስ ማንም ሊቋቋመው የማይችለውን ምስክርነት እናሳያለን ማለት ነው።

ሐምሌ 15
July 22


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ዋይት “እግዚአብሄር የስጋን ልብ ሊሰጠን ቃል ገብቷል” ገጽ 100, የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች በሚለው “ሙሽራውን ለመገናኘት” ገጽ 405–421, የክርስቶስ ማስተማሪያ ; “የመከራ ጊዜ”በሚለው ገጽ 613–634 ያለውን ያንብቡ።

“ለሰው ልጆች ከተሰጡት ስራዎች ሁሉ እጅግ ወሳኝ የሆነው ባህርይን መገንባት ነው፣ እናም የዚህ ትምህርት ጥናት እንደ አሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆነበት ዘመን አልነበረም። የትኛውም ዘመን ላይ የነበረ ትውልድ እንደዚህ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲፈጽም አልተጠራም፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች እንደዚህ እንደ ዛሬው ዓይነት አደጋ ተጋርጦባቸው አያውቅም ። ስነ- ትምህርት ገጽ 225። “በሰነፎች ደናግላን ምሳሌ ላይ ፣ ሰናፎቹ ደናግላን ዘይትን

እንደሚለምኑ እና የለመኑትን ዘይት ማግኘት አለመቻላቸው ተገልጻል። ይህ በመከራ ጊዜ በክርስቶስ ፊት ሊያቆም የሚችል ባህሪይ ያልተለማመዱ ሰዎች ምሳሌ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ልክ ወደ ጎረቤት ሄዶ እባክህን ባህሪይህን አውሰኝ ከልሆነ መጥፋቴ ነው እንደ ማለት ነው። እነዚያ ጠቢባን መብራታቸው ሊጠፋ ላሉት ዘይት ሊያመጡላቸው አይችሉም። ባህሪይ ከአንዱ ወደ ሌለው የሚተላለፍ ጉዳይ አይደለም። የሚሸጥ ወይም የሚገዛ ነገርም አይደለም፣ የሚወረስ እንጂ። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ግለሰብ በተሰጠው የምህረት ዘመን የጽድቅ ባህሪይን እንዲያገኝ እድል ሰጥቶታል፣ ነገር ግን አንድ ሰው ለሌላው ሰው ፣ ከታላቁ መምህር የተማረውን በፈተና ውስጥ በትዕግስት የሚያልፍበትንና በከባድ ልምምድ ያሳደገውን፣ እና የአለማመንን ተራሮች የሚያፈርስበትን ባህሪዩን ለሌሎች እንዲሰጥ አይጠይቀውም።—Ellen G. White, The Youth’s Instructor, Jan. 16, 1896.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ‹‹የባህሪይ ግንባታ›› ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን እንዴት ማድረግ ትችላለህ? በቤተክርስቲያንዎ ማህበረሰብ እና በግል ህይወትዎ የባህሪይ ግንባታ ምን ያህል ቅድሚያ ይሰጠዋል ?

2.የሀሙስ ቀን ትምህርት፣ በክርስቲያን ህይወት ውስጥ የማህበረሰብን ሚና ተናግሯል። የእርሰዎ አጥቢያ ቤተክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካል እየሰራች ያለችው እንዴት ነው? በማህበረሰቡ ዘንድ ክርስቶስን እየወከሉ ያሉት እንዴት ነው? እንደ ክፍል፣ ምን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ይወያዩ።

3. ምንም አንኳ የዳንነው በክርስቶስ ባለን እምነት ብቻ ቢሆንም እንደ ክፍል፣ ባህሪይን መገንባት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ተነጋገሩ። የሚያድነን የእርሱ ፍጹም የሆነ ባህሪና ጽድቅ ከሆነ ፣ ታዲያ የባህሪይ ግንባታ ምን ያደርግልናል?

4. ከልጅነቷ ጀምሮ ድዳ እና እውር የነበረችው ሄሌን ኬሌር እንዲህ ስትል ጽፋለች “ባህሪይን እንዲሁ ዝም ብሎና ቀላል በሆነ ሁኔታ ማሳደግ አይቻልም። ነፍስ የምትጠነክረው፣ ዓላማ በግልጽ ልታይ የሚችለው፣ጉጉት ከግብ የሚደርሰው እና ወደ ስኬት የሚደረሰው በፈተናና በመከራ ልምምድ ብቻ ነው። 5. በባህሪይ ፣ በመከራ እና በታላቁ ተጋድሎ መካከል ያለውን ዝምድና ተወያዩበት።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL