የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከጥር 14-20

5ኛ ትምህርት

Jan 22-Jan 28




እረፍት ሰጪው ኢየሱስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። ዘፍ.15፡13-21፤ ዕብ.3፡ 12-19፤ ዕብ.4፡6-11፤ ዕብ.4፡1፤3፤5፤10፤ዘዳ.5፡12-15፤ዕብ.4፡8-11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ“እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል።” (ዕብ. 4፡9)

በ ዕብራውያን 1 እና 2 ኢየሱስ እንደ ንጉስና እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ነጻ አውጪ ሆኖ ተነግሯል። ዕብራውያን 3 እና 4 ደግሞ ኢየሱስን እረፍት ሰጪ አድርጎ ያስተዋውቀናል። ይህን አካሄድ የምንረዳው ዳዊታዊው ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለዚያ ንጉስና ለህዝቡ ከጠላቶቻቸው እረፍት እንደሚሰጣቸው መናገሩን ስናስታውስ ነው(2 ሳሙ.7፡10-11)። ይህ እረፍት ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ስለተቀመጠ ለኛ ሆኖልናል። የዕብራውያን መልዕክት ያ እረፍት የእግዚአብሔር እረፍት እንደሆነና የሰንበት ዕረፍት እንደሆነ ይገልጸዋል(ዕብ.4፡1-11)። ይህንን እረፍት የሠራው እግዚአብሔር ነው፤ስለዚህ የርሱ ነው፤ነገር ግን ለአዳምና ሄዋን ተላልፎ ተሰጠ። የመጀመሪያው ሰንበት ፍጹም ካደረገው ጋር ፍጽምናን መለማመድ ነበር። እግዚአብሔር ስለ ሰንበት ዕረፍት ተስፋ ሰጥቷል ምክንያቱም እውነተኛ የሰንበት አጠባበቅ እግዚአብሔር ያንን ፍጹም የሆነ ሁኔታ ይመልሳል የሚለውን ተስፋ ስለሚያጠቃልል ነው።

ሰንበትን ስንጠብቅ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥርና በመስቀል ላይ ሲዋጀን ፍጹም ሥራን እንደሰራ እናስታውሳለን(እናስባለን)። እውነተኛ የሰንበት አጠባቅ ግን ከማስታወስ ተግባር በላይ ነው። በዚህች በተበላሸች ዓለም እግዚአብሔር የሰጠውን የወደፊቱን ተስፋ የምናጣጥምበት ነው። የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለጥር 21 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥር 15
Jan 23

መሬት እንደ ማረፊያ ቦታ


ዘፍ.15፡13-21ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል ምን ነበር?



እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ሲያወጣ ወደ ከነዓን አምጥቶ ሊያሳርፋቸው ነበር(ዘጸ.33፡14፤ኢያሱ.1፡13)። የከነዓን ምድር አባታቸው አብርሃም የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምቶ ከሀገሩ ስለወጣ እግዚአብሔር ቃል የገባለት ምድር ነበረች(ዘፍ.11፡31፤12፡4)። እግዚአብሔር ያንን ምድር ለእስራኤላውያኑ የሰጠው ይዘውት እንዲቀመጡ ብቻ አልነበረም። እግዚአብሔር ወደራሱ እያመጣቸው ነበር(ዘጸ.19፡4)። እግዚአብሔር ያለ ከልካይ ከርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነትን የሚያጣጥሙበትን ቦታ ነው ሊሰጣቸው የፈለገው።በዚያም ውስጥ እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነና እርሱ የሰጣቸውን ለዓለም እንዲመሰክሩ ነበር። ልክ እንደ ፍጥረት ሳምንቷ ሰንበት የከነዓን ምድር ከአዳኛቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነትንና የርሱን መልካምነት እንዲያጣጥሙ የተሰጠች ቦታ ነበረች።

በዘዳግም 12፡1-14 ላይ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሲናገራቸው ወደ እረፍቱ የሚገቡት ወደዚያች መሬት ሲገቡ ብቻ ሳይሆን ምድሪቱን ከጣኦት አምልኮ ሲያጸዷት ነው። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በነርሱ መካከል የሚኖርበት እርሱ የመረጠውን ስፍራ ያሳያቸዋል። ዘጸ.20፡8-11ንና ዘዳ.5፡12-15ን ያንብቡ። ሰንበት የሚገልጻቸው (የሚያሳስባቸው) ሁለት ነገሮች ምንድናቸው? እነርሱስ የሚገናኙት እንዴት ነው?



እግዚአብሔር ሰንበትን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከመውጣት ጋር አገናኝቶታል። ሰንበት እስራኤላውያኑ ፍጥረትንና ከግብጽ ነጻ መውጣትን እንዲያስታውሱበት አዟቸዋል። ፍጥረትና መቤዠት በሰንበት ትዕዛዝ ውስጥ ሁለቱም ተካተዋል። ራሳችንን እንዳልፈጠርን ሁሉ ራሳችንን መቤዠት(ማዳን) አንችልም። ይህ እግዚአብሔር ብቻ ሊያደርገው የሚችለው ሲሆን በማረፍ ለመኖራችን ብቻ ሳይሆን ለመዳናችንም በርሱ ላይ እንደምንደገፍ እንናገራለን። ሰንበትን መጠበቅ መዳን በእምነት ብቻ እንደሆነ የሚናር ኃይለኛ መግለጫ ነው። ሰንበትን መጠበቅ ለመኖራችን ብቻ ሳይሆን ለመዳናችን ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መደገፋችንን የሚያሳየን እንዴት ነው?

ጥር 16
Jan 24

ባለማመናቸው ምክንያት


ዕብራውያን 3፡12-19ን ያንብቡ። የእስራኤል ሕዝብ ተስፋ ወደተገባው እረፍት መግባት ያልቻሉት ለምን ነበር?



አሳዛኙ ታሪክ ከግብፅ ነፃ የወጡት ህዝብ እግዚአብሔር ተስፋ ወደሰጣቸው እረፍት አልገቡም። እስራኤላውያኑ ወደ ተስፋይቱ ምድር ድንበር፣ ቃዴስ በርኔ ሲደርሱ የሚያስፈልጋቸውን እምነት አጡ። ዘሁልቅ 13 እና 14 እንደሚገልፅልን ምድሪቱን ሊሰልሉ የሄዱት ሰላዮች “ስለ ሰለሉአት ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች አወሩ፤” (ዘሁ. 13፡32)። ምድሪቱ መልካም እንደሆነች አወሩ ነገር ግን ነዋሪዎቹ ኃያላን፣ ከተሞቻቸውም የተጠናከሩ ስለሆኑ መውረስ እንደማይችሉ ተናገሩ።

ኢያሱና ካሌብ ምድሪቱ መልካም ነች በሚለው ቢስማሙም ነዋሪዎቿ ጠንካራና ከተማይቱም የተጠናከረች በሚለው ግን አልተስማሙም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው ወደ ምድሪቱም ያገባናል አሉ (ዘሁልቅ 14፡7-9)። እግዚአብሔር ግብፅን በመቅሰፍት ሲመታ (ዘፀ. 7-12)፣ የፈርኦንን ሠራዊት በቀይ ባህር ሲያሰጥም (ዘፀ. 14)፣ ከሰማይ መናን ሲያወርድ (ዘፀ. 16)፣ ከዐለት ውሃን ሲያፈልቅ (ዘፀ. 17)፣ ከነርሱ ጋር በቀጣይነት መሆኑን በደመና(ዘፀ. 40፡36-38) ያዩት ሕዝብ አሁን በርሱ ላይ መተማመን አልቻሉም።

የእግዚአብሔርን ኃይል በግልፅ ያዩት ህዝብ ያለማመን ምሳሌዎች መሆናቸው አሳዛኝ ምፀት ነው(ነህ. 9፡15-17፣ መዝ. 106፡24-26፣ 1 ቆሮ. 10፡5-10)። እግዚአብሔር ከሰው ግምት በላይ የሆኑ ስጦታዎችን ለልጆቹ ተስፋ ገብቷል። በፀጋ ላይ የተመሠረቱትና በእምነት ብቻ የሚገኙት ለዚያ ነው። ዕብራውያን 4፡2 እንደሚገልፀው እስራኤላውያኑ የተሰጣቸው ተስፋ “ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።” (በሌላ ትርጉም ፡- አልጠቀማቸውም ምክንያቱም የታዘዙትን ሰዎች እምነት ስላልተካፈሉ ይላል)።

እስራኤል እንደ ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ድንበሮች ተጓዘ። ሕዝቡ ስለ ምድሪቱ የሚጋጭ ዘገባ ሲሰሙ እምነት ከሌላቸው ጋር ተባበሩ። እምነትም ሆነ አለማመን ተላላፊ ናቸው። የእብራውያን መልዕክት ለአንባብያኑ ተመካከሩ (ዕብ. 3፡13)፣ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ተነቃቁ” ዕብ. 10፡24 የሚለን እና “የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው እንድንተያይ” (ዕብ. 12፡15) የሚመክረን ለዚያ ነው። ዛሬ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደ ሕዝብ እየተጓዝን ነው፤ አብረውን በመንገድ ለሚጓዙትም ኃላፊነት አለብን። የሌሎች አማኞች እምነት እንዲበረታ ማድረግ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? የሌሎቹን እምነት የሚያዳክም ነገር አለመናገር ወይም ተግባር አለመፈፀም የምንችለው እንዴት ነው?

ጥር 17
Jan 25

ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ


ዕብራውያን 4፡6-11ን ያንብቡ። በዚህ አንቀፅ ውስጥ የእግዚአብሔር ጥሪ ምንድነው?



በበረሃ የተጓዘው ሕዝብ ወደ እረፍት ለመግባት አለመቻላቸው እግዚአብሔር በነርሱ መካከል እንዳይሠራ አላገደውም። እግዚአብሔር እነርሱ ባይታመኑበትም እርሱ ግን በታማኝነቱ ቀጠለ (2 ጢሞ. 2፡13)። ስለዚህ ጳውሎስ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔር ተስፋ “ቀርቶልናል”(አሁንም አለ) ይላል (ዕብ. 4፡1፣ 6፣ 9)። ካታሌፖና አፖሌፖ የሚሉ የግሪክ ቃላት የሚጠቀም ሲሆን ትርጉማቸውም ተስፋው ተረስቷል ወይም “ተትቷል” የሚል ነው። ወደ እረፍቱ ለመግባት የተደረገው ጥሪ በዳዊት ጊዜ መደገሙ (መዝሙር 95ን ጠቅሶ ዕብ. 4፡6-7) ተስፋውን የራሳቸው እንዳላደረጉትና ያኔም ተስፋው እንዳለ የሚያሳይ ነው። እንደውም ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮ እረፍቱ ነበር ይላል።

ዛሬም እግዚአብሔር ወደ እረፍቱ እንድንገባ ይጠራናል። “ዛሬ” የሚለው ፅንሰ ኃሳብ ትርጉምን ያዘለ ነው። እግዚአብሔር ለነርሱ ታማኝ እንደነበር ሕዝቡ እንዲያስታውሱ “ዛሬ” ብሎ ይጠራቸዋል(ዘዳ. 11፡2-7)። “ዛሬ” ደግሞ ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆን የምንወስንበት ጊዜ ነው (ዘዳ. 5፡1-3)። ይህ ውሳኔ ወደ ሌላ ጊዜ ሊተላለፍ አይችልም። በተመሳሳይ “ዛሬ” የሚለው ውሳኔ የምንወስንበት ዕድል የተሰጠን ጊዜ ነው፤ እንዲሁም ልክ በዘመናት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆነው አደገኛ ማስጠንቀቂያም ነው።

በዕብራውያን መልዕክት “ዛሬ” የሚለው ጽንሰ ኃሳብ የእግዚአብሔር ተስፋዎች የሚፈፀምበት የጊዜ ወሰን ነው። ይህንን ወሰን “እኔ ዛሬ ወልጄሃለው” (ዕብ. 1፡ 5) በማለት በእግዚአብሔር ተስፋዎች መሠረት(2 ሳሙ. 7፡8-16) ኢየሱስን ገዢ በማድረግ ተጀምሯል። ስለዚህ የኢየሱስ መክበር ለኛ አዲስ የበረከቶችና የእድሎችን ዘመን ከፍቶልናል። ኢየሱስ ጠላቶቹን ድል ነስቷል(ዕብ. 2፡14-16) እንዲሁም አዲስን ኪዳን አስጀምሯል(ዕብ. 8-10)። ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ቀርበን(ዕብ. 4፡14-16፣ ዕብ. 10፡19-23) በመንፈሳዊ መስዋዕቶችና በምስጋና በፊቱ መደሰት እንችላለን (ዕብ. 12፡28፣ ዕብ. 13፡10-16)። “ዛሬ” ተብሎ የተሰጠው ጥሪ እግዚአብሔር ለኛ ታማኝ ስለመሆኑና ሳንዘገይ አሁኑኑ ጥሪውን እንድንቀበል የሚያስፈልገንን ምክንያት ሁሉ እንደሰጠን እንድናውቅ ይጋብዘናል።

ለሌላ ጊዜ የማናሳድራቸው ዛሬ ማድረግ ያለብን ምን ምን አይነት መንፈሳዊ ውሳኔዎችን መወሰን ይገባናል? ያኔውኑ ማድረግ እያለባችሁ የዘገያችሁባቸው ያለፉ የህይወታችሁ ክስተቶች ምን ነበሩ?

ጥር 18
Jan 26

ወደ እረፍቱ መግባት


ዕብራውያን 3፡11ንና ዕብራውያን 4፡1፣ 3፣5፣10ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እንድንገባ የጠራንን ዕረፍት የገለፀበት መንገድ ምንድነው።



እግዚአብሔር ዝም ብለን እንድናርፍ አልጠራንም። ወደ እርሱ እረፍት እንድንገባ ጋብዞናል። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ “እረፍት” የሚለው ቃል በከነዓን ምድር “እረፍት” ማግኘትን(ዘዳ. 3፡20)፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚገኝበት በቤተመቅደሱ ውስጥ ማረፍን(2 ዜና 6፡41) ወይም እግዚአብሔርና እስራኤላውያን በሰንበት ቀን ከስራቸው “እረፍት” ማግኘታቸውን(ዘፀ. 20፡11) የሚገልጽ ነው። ነገር ግን አሁን ጌታ ወደ እረፍቱ እንዲገቡ እየጠራቸው ነው። ዕብራውያን 4፡9-11፣16ን የተጠራነው? ያንብቡ ምን ለማድረግ ነው



የሰንበት ዕረፍት እግዚአብሔር የፍጥረትን(ዘፍ. 2፡1-3፣ ዘፀ. 20፡8-11) ወይም የማዳኑን(ዘዳ. 5፡12-15) ሥራ መጨረሱን የሚያሳስብ ነው። በተመሳሳይ በሰማዩ ቤተ መቅደስ የኢየሱስ መክበር ለኛ መዳን ሲል ፍፁም መስዋዕት አቅርቦ መጨረሱን ያበስራል (ዕብ. 10፡12-14)። ልብ እንበል፣ እግዚአብሔር የሚያርፈው የኛን ህልውናና ደህንነት ሲያረጋግጥ ነው። በፍጥረት ዓለምን ፈጥሮ ሲጨርስ አረፈ። ከዚያም እግዚአብሔር በመቅደሱ ያረፈው ለአብርሃም ተስፋ የሰጠውን ምድር ለመውረስ በተደረገ ትግል ውስጥ ዳዊት ሲያሸንፍና “እስራኤል በሰላም ሲሆን” ነበር(1 ነገ. 4፡21-25፣ ዘፀ.15፡ 18-21፣ ዘዳ. 11፡24፣ 2 ሳሙ. 8፡1-14)። እግዚአብሔር ለራሱ ቤት እንዲሠራ የፈቀደው የእስራኤል ሕዝብና ንጉሱ የራሳቸው ቤት ከኖራቸው በኋላ ነበር።

እግዚአብሔር ለኛ ቃል የገባውና የማያዳግመው እረፍት ታላቁ ተጋድሎ ካለቀ በኋላ በሚፈጥረው አዲሱ ዓለም ውስጥ የሚሆነው ነው። የእብራውያን መልዕክት “እግዚአብሔር የሠራትና የፈጠራት ከተማ. . .” ዕብ. 11፡10 እንዲሁም “ሰማያዊ መኖሪያ” (ዕብ. 11፡14-16) ብሎ ይጠራታል። ማለትም እግዚአብሔር በመጀመሪያ በፍጥረት ለሰው ልጆች ሰጥቶ የነበረውን ገዢነትና ክብር ወደ ቦታው መመለስ ማለት ነው(ዕብ. 2፡5-8፣ ዕብ. 12፡28)። የእርሱ እረፍት ነው። ሰላም የሚኖርባት ፍጹም ቦታ ብቻ አይደለችም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ዙፋን በአዲሲቱ ሰማይና ምድር የሚሆንባት ሰንበት ነች። አሁን ወደ እረፍቱ መግባት የምንችለው እንዴት ነው? ማለትም በእምነት፣ በራሳችን ሳይሆን በክርስቶስ ባገኘነው መዳን እርግጠኛ በመሆን ማረፍ የምንችለው እንዴት ነው?

ጥር 19
Jan 27

የአዲስ ፍጥረት ቅምሻ


ዘጸዓት 20፡8-11፤ዘዳግም 5፡12-15 እና ዕብራውያን 4፡8-11ን ያነጻጽሩ። የሰንበት እረፍትን በተመለከተ ምን አይነት ልዩነቶችን አገኛችሁ?



ቀደም ብለን እንደተመለከትነው እነዚህ በዘጸዓትና በዘዳግም የሚገኙ ጥቅሶች ወደኋላ እንድንመለከት ይጋብዙናል። እግዚአብሔር በፍጥረትና በመቤዠት ያጠናቀቀውን ስራ እያሰብን በሰንበት እንድንደሰት ይመክሩናል። ዕብራውያን 4፡9-11 ግን ወደፊት እንድናይ ይጋብዘናል። ከፊት ለፊታችን እግዚአብሔር የሰንበትን እረፍት እንዳዘጋጀ ይነግረናል። ሰንበትን ለመጠበቅ አዲስ ገጽን ያመላክተናል።የሰንበት ዕረፍት ያለፉትን የእግዚአብሔር ድሎች ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለወደፊቱ የሰጠንን ተስፋዎችም ያሳስበናል።

ሰንበትን የመጠበቅ የወደፊት ገጽታ ሁሌም የነበረ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን የተረሳ ነው። ከውድቀት በኋላ እግዚአብሔር በመሲሁ አማካኝነት አንድ ቀን ፍጥረትን ወደነበረበት እንደሚመልስ የሰጠውን ተስፋ ያመላክታል። ሰንበትን በመጠበቅ ውስጥ የመቤዠታችንን ነገር እንድናስብ ያዘዘን ሰንበት በአዲስ ፍጥረት ውስጥ የመቤዠት ፍጻሜን ስለምታሳይ ነው። ሰንበትን መጠበቅ በዚህች ፍጹም ባልሆነች ዓለም ውስጥ የሰማይ ቅምሻ ነው። በአይሁድ ባህል ውስጥ ይህ ግልጽ ነበረ። “Life of Adam and Eve,” The Old Testament Pseudepigrapha, by James H. Charlesworth, p. 18።

ከ100 እስከ 200 ዓ.ም የተጻፈ ጽሁፍ እንደሚነግረን ሰባተኛው ቀን የትንሳኤና የመጪው ዘመን እረፍት ምልክት ነው። Jacob Neusner, The Mishnah, a New Translation (New Haven: Yale University Press, 1988), p. 873.። አካቢ የተባለ የአይሁድ መምህር እንደፃፈው ደግሞ “እስራኤል ስሙ ለተባረከው ቅዱስ አምላክ “ትዕዛዛቱን ከታዘዝን ሽልማታችን ምንድነው?” አሉት፤እርሱም “የሚመጣው ዓለም” አላቸው። እነርሱም “ምሳሌ የሚሆን ነገር ስጠን” አሉት። እርሱም ሰንበትን አሳያቸው።” Theodore Friedman, “The Sabbath Anticipation of Redemption,” Judaism: A Quarterly Journal, vol. 16, pp. 443, 444

ሰንበት ደስታንና ምስጋናን ማጣጣሚያ ጊዜ ነው። ሰንበትን ስንጠብቅ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃላት እንደምናምንና የርሱን የጸጋ ስጦታ እንደምንቀበል እናሳያለን። ሰንበት ህያውና የሚሰራ ዕምነትን የሚያሳይ ነው። ተግባራት የሚገልጹትን ያክል በመሄድ፣ምናልባትም ሰንበትን መጠበቅ በእርሱ በማመን በጸጋ መዳናችንን ሙሉ በሙሉ የምንገልጽበት ነው። በስራ ከመጽደቅ በተቃራኒ ሰንበትን መጠበቅ በእምነት መዳን የሚለውን ጽንሰ ኃሳብ ማስተዋላችንን መግለጽ የሚችለው እንዴት ነው? በሰንበት ማረፍ በጸጋ የመዳን መግለጫ የሆነው እንዴት ነው?

ጥር 20
Jan 28


ተጨማሪ ሀሳብ


ጳውሎስ በዕብራውያን መልዕክቱ ውስጥ እግዚአብሔር ለሰጠን ፀጋ ምልክት እንዲሆን እሁድን ሳይሆን የሰንበት እረፍትን መጠቀሙ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። በዚህ መልኩ የሰንበት ዕረፍት መቀመጡ ሰንበት በአማኞች ዘንድ ይከበር እንደነበር ያሳያል። ሆኖም ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቤተክርስትያን ለውጥ እንደተካሄደ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እናገኛለን። ሰንበትን መጠበቅ እንደ መዳን ምልክት መታየቱ ቀርቶ የብሉይ ኪዳንና ወደ አይሁዳዊነት ልማድ የመመለስ ምልክት ሆኖ በመቅረብ መወገድ እንዳለበት መታሰብ ተጀመረ።

ሰንበትን መጠበቅ “አይሁዳዊ” ከመሆን ጋር እኩል ሆነ። ለምሳሌ የአንፆኪያው ኢግናሽየስ (በ110 ዓ.ም. አካባቢ) እንደጠቀሰው ፡- “እንደ ቀድሞው ስርዓት የኖሩት አዲስ ተስፋን አግኝተዋል። ከአሁን በኋላ ሰንበትን ሳይሆን ህይወታችን በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ከክርስቶስ ጋር የተነሳችበትን የጌታን ቀን ያከብራሉ። Jacques B. Doukhan, Israel and the Church: Two Voices for the Same God (Peabody, MA: Hendrickson Publishers, 2002), p. 42. በተመሳሳይ ማርሲዮን ደግሞ ተከታዮቹ አይሁዶችን ለመቃወም በሰንበት እንዲፆሙ አዟቸው ነበር። ቪክቶሪነስ ደግሞ የአይሁድን ሰንበት እንደጠበቀ መታሰብን አልፈለገም ነበር (Israel and the Church, pp. 41– 45)። ሰንበትን መጠበቅ በፀጋ የመዳን ምልክት ተብሎ መታሰቡ ስለቀረ ነው በክርስትን ቤተክርስትያን ውስጥ ውድቀትን ያመጣው።

“በክርስቶስ ውስጥ መኖር በእረፍት ውስጥ መኖር ነው። የመፈንደቅ ስሜት ላይኖር ቢችልም በመተማመን ግን ማረፍ ሊኖር ይገባል። ተስፋችሁ በራሳችሁ ሳይሆን በክርስቶስ ነው። የእኛ ድካም ከእርሱ ብርታት፣ አላዋቂነታች ከእርሱ ጥበብ፣ ልፍስፍስነታችን ከእርሱ ዘላለማዊ ኃይል ጋር ተቆራኝቶአል። ስለዚህም መመልከትና አእምሯችን ማተኮር ያለበት በራሳችን ነገር ላይ ሳይሆን በክርስቶስ ላይ ነው። አእምሯችን የእርሱን ፍቅር፣ የባህሪውን ውበትና ፍጽምና ያስብ። ነፍስ ልታሰላስለው የሚገባ ርዕስ ቢኖር፣ የክርስቶስን ራስን መካድ፣ ትህትናውን፣ ንጽህናውን፣ ቅድስናውን እንደዚሁም ወደር የለሽ ፍቅሩን ሊሆን ይገባል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገጽ 65፣66 (በአማርኛው)


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሰንበትን በመጠበቅና በእምነት መጽደቅ ምን ግንኙነት አላቸው?

2.በእውነተኛ የሰንበት አጠባበቅና ህግን ጠብቆ ለመዳን በሚሆን ሰንበት አጠባበቅ መካከል ምን ልዩነት አለ? በራሳችን የሰንበት አጠባበቅ ውስጥ ልዩነቱን ማወቅና ማጣጣም የምንችለው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL