የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከህዳር 4-10

8ኛ ትምህርት

Nov 13-Nov 19




ህይወት መምረጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 2:8-9፣ ሮሜ 6:23፣ 1ዮሐ. 5:12፣ ዘዳ. 30:1–20፣ ሮሜ 10:6–10፣ ዘዳ. 4:19፣ ራእ. 14:6–12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳ. 30፡19)

ታ ሪኩ በጣም አሳዛኝ ነው። አንዲት የ22 ዓመት ለግላጋ ወጣት ከተደረገላት የሕክምና ምርመራ በኋላ ለህልፈት የሚዳርግ የአእምሮ ዕጢ እንዳለባት ተነገራት። ምንም እንኳ የህክምና ሳይንሱ ግስጋሴ አስደናቂ ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ ነገር ግን ያ ቁርጥ ቀን እስኪመጣ የወጣቷን ሥቃይ ከማራዘም ውጪ ሌላ ምንም ነገር ማድረግ አልተቻለም። ሆኖም ወጣቷ “ሳንዲ” ግን መሞት አልፈለገችም። ስለዚህ እቅድ አወጣች። ከሞተች በኋላ የአእምሮ ህዋሶቿን ጠብቆ ማቆየት ይቻል ዘንድ ጭንቅላቷ በፈሳሽ ናይትሮጂን ሳጥን ውስጥ ተከትቶ በቀዝቃዛ በረዶ ቤት ይቀመጣል። በዚያ ሁኔታ ቴክኖሎጂው በቂ ግስጋሴ ላይ እስኪደርስ ለቀጣዮቹ ሃምሳ፣ መቶ ወይም ሺህ ዓመታት ይቆያል። በዚያን ጊዜ ከኒውራል መስመሮች ጋር የተሳሰረው አእምሮዋ ኮምፒውተር ላይ መጫን ይችላል። አዎ--ሳንዲ ምናልባት ለዘላለም “መኖር” ትችል ይሆናል።

ታሪኩን አሳዛኝ የሚያደርገው የወጣቷ ያለ ዕድሜዋ ሞት አፋፍ ላይ መድረስ ሳይሆን፣ የህይወትን ተስፋ ያስቀመጠችበት መንገድ ነው። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ሳንዲ በሕይወት መኖር ፈልጋለች። ነገር ግን የመረጠችው መንገድ በስተ መጨረሻ ሊሠራ የማይችል ዓይነት ነበር። በዚህ ሳምንት የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ ጥናታችንን ስንቀጥል፣ የህይወት ምርጫንና ሕይወትን እንድንመርጥ የተሰጠንን ዕድል የምንመለከት ሲሆን፤ ይኸውም ሕይወትን በጸጋው ከሰጠውና ደግፎ ከያዘው--እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የመምረጥ ዐውድ አኳያ ይሆናል።

ህዳር 5
Nov 4

የሕይወት ዛፍ


ማናችንም ብንሆን በዚህ ምድር እንድንኖር ተጠይቀን አልመጣንም--አይደል? የት እና መቼ መወለድ እንዳብን፣ ወላጆቻችን እነ ማን መሆን እንዳለባቸው አልመረጥንም። የአዳምና ሔዋን ጉዳይም ከተቀረው ሰብአዊ ፍጡር ጋር ተመሳሳይ ነበር። አንዷ ቅንጣት ቅጠል፣ ግዙፉ ቋጥኝ ወይም ተራራ በእግዚአብሔር እንዲፈጠሩ አልመረጡም። እኛ እንደ ሰው ፍጥረት ብቻ አይደለንም (ቋጥኝም ፍጥረት ነው)፣ ደግሞም ሕይወት ያለን ብቻ አይደለንም (አሜባም ህይወት አለው) ነገር ግን ነጻ የመምረጥ ችሎታ እንዳለው ባለ አእምሮ ፍጡር፣ ሕይወት በእግዚአብሔር አምሳልተሰጥቶናል።

አሁንም--በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተሠራና የመምረጥ ነጻነት እንዳለው ባለ አእምሮ ፍጡር፣ ወደ ሕይወት ለመምጣት አልመረጥንም። በእርግጥ በሕይወት መኖር የመቀጠል ምርጫን እግዚአብሔር በእጃችን ሰጥቶናል። ይኸውም በየሱስ እና በመስቀል ላይ ሞቱ-- በእርሱ ህይወት እንዲኖረን፣ የዘላለማዊ ህይወት ባለቤት ለመሆን መምረጥ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡8-9፣ 15-17፣ ዘፍ. 3፡22-23። አዳም መፈጠሩን ተከትሎ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ሁለት አማራጮችን አቀረበለት?



“በኤደን መካከል ፍሬው ሕይወትን የማቆየት ኃይል የነበረው የሕይወት ዛፍ ነበር። አዳም ለእግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ቢቀጥል ኖሮ ያለ ገደብ ወደዚህ ዛፍ መድረስና ለዘላለም መኖር ይችል ነበር። ነገር ግን ኃጢአት በሠራ ጊዜ ከህይወት ዛፍ ተጋሪነት ተነጠለ እና ለሞት ተገዢ ሆነ። ‘ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ’ የሚለው መለኮታዊ ፍርድ የህይወት ፍጻሜን ያመለክታል”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 532, 533. ስለዚህ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት አማራጮችን ያስቀምጥልናል። አንደኛው አስቀድሞውኑ ሊኖረን ይገባ የነበረው ዘላለማዊ ህይወት ሲሆን፣ ሁለተኛው ዘላለማዊ ሞት ወይም መጀመሪያ ከመጣንበት አስቀድሞ ወደ ነበረው ምንምነት መመለስ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ያለመሞት ባህሪ ወራሽ ያደርጋል ሲል የጠቀሰው “የሕይወት ዛፍ” በመጀመሪያው እና እንደገና ደግሞ በመጨረሻው (በኦሪት ዘፍጥረት እና በራእይ ዮሐንስ) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መቅረቡ አስደሳች ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡7 እና ራእ. 22፡2፣ 14። ምንም እንኳ ወደ ህይወት ዛፍ መድረስ እንችል የነበረ ቢሆንም፣ በኃጢአት ምክንያት ያን ዕድል አጣን። ሆኖም ለየሱስ እና ለደኅንነት ዕቅድ ምስጋና ይግባውና ውሎ አድሮ በመጨረሻ የኃጢአት ችግር ሲያከትም፣ መጀመሪያ ተዘጋጅቶልን እንደ ነበረው--ህይወትን የመረጡና የተዋጁ ወደ ህይወት ዛፍ መድረስ ይችላሉ። ያስቡበት፡ የዕለት ከዕለት ምርጫችን ምንድን ነው--ህይወት ወይስ ሞት?





ህዳር 6
Nov 5

መሃል ሰፋሪ የለም


በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ከሁለት ምርጫዎች መካከል አንዱን የምንመርጥበት አግባብ ቀርቦ እንመለከታለን። እነሆ ሁለት ምርጫዎች ቀርበውልናል። ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ። በጥቅሶቹ ምን ዓይነት ሁለት አማራጮች በግልጽ ተጠቅሰዋል? አማራጮቹ የቀረቡበትስ መንድ ምን ይመስላል? ዮሐ. 3:16____________________________________________________



ዘፍ. 7:22, 23_________________________________________________



ሮሜ 6:23____________________________________________________



ሮሜ 8:6_____________________________________________________



1ዮሐ. 5:12___________________________________________________



ማቴ. 7: 24 – 27_______________________________________________



በመጨረሻ ለእኛ ለሰው ልጆች የመሃል ሰፋሪ ቦታ የለም። ታላቁ ውዝግብ ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ኃጢአት፣ ሰይጣን፣ ክፋት፣ አለመታዘዝና ዐመጻ ይወገዳሉ። ይህ ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር ገና በመጀመሪያ፣ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ እያንዳንዱ ሰው፣ በግለሰብ ደረጃ የታቀደለት የዘላለም ህይወት ባለቤት ይሆናል ወይም ዘላለማዊውን ሞት ይጋፈጣል፡ “እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኃይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ተሰ. 1፡ 9)። ከዚህ ውጪ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርብልን ሌላ አማራጭ የለም። የእኛ መጨረሻ የትኛው ነው? መልሱ ውሎ አድሮ በየግል ውሳኔያችን ላይ የተመሠረተ ይሆናል። እነሆ ከፊታችን የሕይወት ወይም የሞት ምርጫ ቀርቧል።

ከዘላለማዊው ህይወት ወይም ከዘላማዊው ሞት ዐውድ አኳያ-ሲኦል ሰዎች ለዘላለም በእሳት ሲቃጠሉና ሲሠቃዩ የሚኖሩበት ስፍራ አለመሆኑን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አብልጦ የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው? የጠፉ ሰዎች ራሳቸውን በሚያውቁበት ሁኔታ ለዘላለም እየተሠቃዩ ይኖራሉ የሚለው አስተምህሮ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን ይናገራል?

ህዳር 7
Nov 6

ህይወት እና መልካም፣ ሞት እና ክፉ፣ በረከትና እርግማን


በኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ መጨረሻ አካባቢ፣ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ባይታዘዝና ቃል ኪዳኑን ቢያፈርስ ምን ሊደርስበት እንደሚችል የሚያትት ረጅም ንግግር ቀርቧል። ዘዳ. 30--ህዝቡ ባለመታዘዝ ተሰናክሎ የግዞት ቅጣት ቢቀበል እንኳ፣ እግዚአብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚመልሳቸው በሰጠው የተስፋ ቃል ይጀምራል። ይኸውም ንስሐ ገብተው ከክፉ መንገዳቸው ከተመለሱ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 30፡15-20። ለጥንት እስራኤላውያን የቀረቡላቸው አማራጮች ምንድን ናቸው? አማራጮቹ በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች የተመለከትናቸውን ነጥቦች እንዴት ያንጸባርቃሉ?



የጌታ መልእክት በጣም ግልጽ ነው፡ ጌታ ከሁለት አንዱን እንዲመርጡ-አማራጭ ያቀረበላቸው ሲሆን፣ ለአዳም እና ሔዋን ያደረገውም ይህንኑ ነበር። ለነገሩ በዘዳ. 30፡15 የቀረቡት “መልካም” (ቶቭ) ወይም “ክፉ” (ራኣ) የዕብራይስጥ ቃላት፤ በዘፍጥረት መጽሐፍ “መልካም” (ቶቭ) እና “ክፉ” (ራኣ) ስለሚያሳውቀው ዛፍ ከቀረቡት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁሉ በዚህ ስፍራም ለመሃል ሰፋሪ የተተወ ሦስተኛ አማራጭ የለም። ጌታን አገልግለው የህይወት ባለቤት መሆን ወይም ሞትን መምረጥ። በተመሳሳይ ይህ ለእኛም ይሠራል። ህይወት፣ በጎነት፣ በረከት ከምን ጋር ይቃረናል? ከሞት፣ ከክፉ እና ከእርግማን ጋር። በመጨረሻ እግዚአብሔር ለእነዚህ ሕዝቦች ሊሰጣቸው የሚችለው አንዱን ብቻ ነው--ህይወት፣ በጎነት እና በረከት--ብሎ አንድ ሰው ሊሞግት ይችላል። ነገር ግን ፊታቸውን ከእርሱ የሚመልሱ ከሆነ የእርሱን ልዩ ከለላ ማግኘታቸው ስለሚያከትም፣ እነዚህ መጥፎ ነገሮች ተፈጥሯዊ ውጤቶች ይሆናሉ።

እነዚህ አማራጮች ለሕዝቡ ቀርበው እንደ ነበር እንረዳለን። እንዲሁም የተሟላ የመምረጥ ነጻነት ባለቤት እንደነበሩም በጣም ግልጽ ነው። እነዚህና ሌሎች ብዙዎች የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ከተቀደሰው የመምረጥ ነጻነት ውጪ ትርጉም ሊሰጡ አይችሉም። ጌታ በተጨባጭ ያላቸው ይህን ነበር፡ እንግዲህ በሰጠኋችሁ የመምረጥ ነጻነት ተጠቅማችሁ ህይወትን ምረጡ፣ በረከትን ምረጡ፣ መልካም የሆነውን እንጂ ሞትን፣ ክፉውንና ርግማንን አትምረጡ።

ትክክለኛው ምርጫ የቱ እንደሆነ ለማስተዋል በጣም ግልጽ ይመስላል-አይደል? ደግሞም ምን እንደ ተከሰተ እናውቃለን። ታላቁ ውዝግብ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ ዛሬም በተጨባጭ አለ። ራሳችንን ለጌታ ቀድሰን ሰጥተን ህይወትን ካልመረጥንና ምርጫው የሚያካትታቸውን ሁሉ የራሳችን ማድረግ ካልቻልን፣ ሊከሰት ስለሚችለውን ነገር ከእስራኤል ምሳሌ መማር ይኖርብናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 30፡20። በፍቅር እና በመታዘዝ መካከል ያለውን ግንኙነት ልብ ይበሉ። እስራኤል ለጌታ ታማኝ ለመሆን ምን ማድረግ አለበት? እነዚህ ተመሳሳይ መርኅዎች ዛሬ ለእኛም ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉት እንዴት ነው?





ህዳር 8
Nov 7

ለእናንተ በጣም አስቸጋሪ አይደለም


ሕዝቡ ንስሐ ገብቶ ከክፉ መንገዱ ቢመለስ ምን ሊከሰት እንደሚችል በመናገር ዘዳ. ምዕ. 30 ይጀምራል። እንዴት ያሉ ድንቅ ተስፋዎች ተሰጧቸው! ቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 30፡1-10። ምንም እንኳ ይህ የሚናገረው ባይታዘዙ ሊደርስባቸው ስለሚችለው ነገር ቢሆንም፣ ከእግዚአብሔር የተሰጧቸው የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? ይህ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ምን ያስተምረናል?



በእርግጥ ይህን መስማታቸው አጽናንቷቸው እንደነበር ለመገመት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ዋናው ነጥብ--እግዚአብሔር ካዘዛቸው ቢያፈነግጡ ምንም አይደል የሚል አልነበረም። ጌታ ለማንም ቢሆን ርካሽ ጸጋ አያቀርብም። ማንኛውም ነገር ቢሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር ሊያሳያቸው ይገባ ነበር። በምላሹ፣ እርሱ አድርጉ ያላቸውን እየታዘዙ የፍቅር አጸፋ በመስጠት መግለጽ ነበረባቸው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 30፡11-14። ጌታ ምን እያላቸው ነው? በእነዚህ ጥቅሶች የቀረበው መሠረታዊ የተስፋ ቃል ምንድን ነው? ተመሳሳይ ተስፋ የሚያንጸባርቁ ምን ዓይነት የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ወደ አእምሮዎ ሊመጡ ይችላሉ?



በዚህ ውብ ቋንቋ እና የማያወላዳ አመክንዮ በመቀጠል የቀረበውን ጥሪ ይመልከቱ። ጌታ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ከባድ ነገር እንዲያደርጉ እየጠየቃቸው አልነበረም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያስተውሉ ዘንድ በጣም አስቸጋሪ ወይም ውስብስብ አልነበረም። ከአቅማቸው በላይ--እንደ ሰማይ የራቀ ወይም እንደ ባህር የጠለቀ፣ ፍጹም የማይደረስበት አልነበረም። “ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው” (ዘዳ. 30፡14)።

ስለዚህ ላለመታዘዝ ሊቀርብ የሚችል ማመካኛ የለም። “ትእዛዛቱ ሁሉ የሚቻሉ ናቸው”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 333. ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ ጥቅሶች የተወሰኑትን በክርስቶስ ከመዳን ዐውድ ባሰፈረው መልእክቱ ጠቅሷል። ማለትም ጳውሎስ በጽድቅ በእምነት ምሳሌ ማጣቀሻነት አስቀምጧቸዋል (ሮሜ 10፡6-10)። በዘዳግም ከተጠቀሱት ከእነዚህ ጥቅሶች በመቀጠል የእስራኤል ልጆች የህይወት ወይም የሞት፣ የበረከት ወይም የእርግማን ምርጫ ቀርቦላቸዋል። በጸጋ እና በእምነት ህይወትን ከመረጡ፣ የራሳቸው ያደርጓታል። ይህ ከዛሬው የተለየ ነው?





ህዳር 9
Nov 8

የአምልኮ ጥያቄ


በጌታ እና በእስራኤል መካከል የነበረው የኪዳናዊ ግንኙነት አስኳል አምልኮ ነበር። በዙሪያቸው ከነበረው ዓለም የተለዩ ያደረጋቸው ከሐሰተኞቹ የአረማውያን የወንድና ሴት አማልክት በተቃራኒ እንደ ሕዝብ እነርሱን፣ እውነተኛውን አምላክ ብቻ ማምለካቸው ነበር። “ ‘ “እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም” ’ ” (ዘዳ. 32፡39)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡19፣ ዘዳ. 8፡19፣ ዘዳ፣ 11፡16፣ ዘዳ. 30፡17። በጥቅሶቹ በጋራ የቀረበው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ማስጠንቀቂያው ለእስራኤል ሕዝብ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያትስ?



በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት፣ እንደ ዛሬው ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በአብዛኛው ከእምነታቸው ጋር ከሚቃረኑ ደንቦች፣ ልማድና ወጎች እንዲሁም ጽንሰ ሀሳቦች የተነጠለ ባህልና ከባቢ ሁኔታ ውስጥ ኖረዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሌም ቢሆን ዓለማዊ መንገዶች፣ ጣኦቶች እና “አማልክት” የአምልኳቸው አካል እንዳይሆኑ ተጠብቀው መኖር ነበረባቸው። “ቀናተኛ” (ዘዳ. 4፡24፣ ዘዳ. 5፡9፣ ዘዳ. 6፡15) አምላክ የሆነው እግዚአብሔር-እርሱ ብቻ ፈጣሪያችንና አዳኛችን በመሆኑ አምልኳችን ይገባዋል። በዚህም ላይ እንደምንመለከተው መሃል ሰፋሪ ሦስተኛ አማራጭ የለም። ህይወት፣ በጎነት እና በረከት የሚሰጠንን ጌታ እናመልካለን ወይም ክፉ፣ እርግማን እና ሞት ለሚያስከትለው እንሰግዳለን።

ጥቅሶቹን ካነበቡ በኋላ አምልኮ በቀረበበት ጥያቄ ዙሪያ ትኩረት ያድርጉ፡ ራእ. 13፡1-15። ከዚያም እነዚህን ጥቅሶች ከራእ. 14፡6-12 ጋር ያነጻጽሩ። በዘዳግም መጽሐፍ ስለ ሐሰት አምልኮ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ በሚያንጸባርቅ መልኩ በራእይ (እንዲሁም በሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች) እየተከሰተ ያለው ምንድን ነው?



ዐውደ ሀሳቡ የቱንም ያህል የተለየ ቢሆንም፣ ርዕሰ ጉዳዩ ግን ያው ተመሳሳይ ነው፡ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በማምለክ የህይወት ባለቤት ይሆናሉ። ወይስ--በግልጽ ወይም በስውር፣ ወይም ደግሞ ሁለቱንም ባካተተ መልኩ የተሸረበ ተንኮል ተጽእኖ ስር ወድቀው ከእርሱና ከፊቱ ይርቃሉ? መልሱ ውሎ አድሮ በእያንዳንዱ ግለሰብ ልብ የሚገኝ ይሆናል። እግዚአብሔር የጥንት እስራኤላውያን እንዲከተሉት እንዳላስገደዳቸው ሁሉ እኛንም አያስገድደንም። በራእ. 13 እንደምንመለከተው፣ ኃይል አውሬው እና የእርሱ ምስል የሚጠቀሙት መንገድ ይሆናል። በተቃራኒው እግዚአብሔር የሚሠራው በፍቅር ነው።

ለየሱስ የነበረንን ታማኝነት እጅግ በረቀቀ ተንኮል አጥተን ለሌላ አማልክት መገዛት ስለ አለመቻላችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?





ህዳር 1
Oct 31


ተጨማሪ ሀሳብ


ዛሬም ቢሆን ሁላችንም የመምረጥ ኃይል ተሰጥቶናል። እዚህ ላይ የቀረበው ወሳኝ ቃል ምርጫ ነው። አንዳንድ የክርስትና ተቋማት-ሰዎች ገና ከመወለዳቸው በፊት እግዚአብሔር አንዳንዶቹ እንዲጠፉ ብሎም በገሃነም እሳት ለዘላለም ሲቃጠሉ እንዲኖሩ አስቀድሞ ወስኗል ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ--ሕይወት ወይም ሞት፣ በረከት ወይም እርግማን፣ መልካም ወይም ክፉ የመምረጣችንን ውጤት እንጋፈጣለን ሲል ያስተምራል። የአንድ ሰው የተሳሳተ ምርጫ--ሞትና ዘላለማዊ ጥፋት ቢያስከትልም እንኳ ማለቂያ ለሌለው ዘመን በእሳት በባሕር ሲቃጠል አለመኖሩን ማወቅ መልካም ነው።

“ ‘የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።’ (ሮሜ 6፡23)። ሕይወት የጻድቃን ርስት ሲሆን ሞት ደግሞ የኃጥአን ድርሻ ነው። ሙሴ፡ ‘እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ’ (ዘዳ. 30፡15) ሲል በእስራኤል ፊት ያውጃል። በእነዚህ ጥቅሶች የተወሳው ሞት በአዳም ላይ የተነገረው አይደለም። ምክንያቱም የሰው ልጆች በሙሉ የእርሱን መተላለፍ ቅጣት ይቀበላሉ። ይልቁንም ከዘላለማዊው ሕይወት ጋር በንጽጽር የቀረበው ‘ሁለተኛው ሞት’ ነው።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 544.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በማክሰኞ ትምህርት በቀረበው ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ተነጋገሩ። ዛሬ ሰዎች ባለመታዘዛቸው ምክንያት እግዚአብሔር በቀጥታ እየቀጣቸው ይገኛል ወይስ ሕግ ሲጣስ የሚከተለው ዓይነት መዘዝ ይደርስባቸዋል--ወይስ ሁለቱም ይገጥማቸዋል? ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንዴት እናስተውለዋለን?

2.በዛሬው ጥናት የተመለከትነው የኤለን ኋይት ጽሑፍ ኃጢአትን ለማሸነፍ ስለምናገኘው የእግዚአብሔር ኃይል ምን ያስተምረናል?

3.ጳውሎስ ከዘዳ. 30፡11-14 በመጥቀስ ሮሜ 10፡1-10 ያሰፈረውን መልእክት ያንብቡ። ሕግን በመጠበቅ ጽድቅ እና ደኅንነት ለማግኘት ከሚደረግ ሩጫ በተቃራኒ በየሱስ ስለሚገኘው ጽድቅ በእምነት ያብራራል። እነዚህን ጥቅሶች ከዘዳግም መጽሐፍ ለምን የጠቀሳቸው ይመስሎታል? ለሚከተለው ጥቅስ የተለየ አጽንኦት ይስጡ፡ “የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና” (ሮሜ 10፡10)። ጳውሎስ ለማንሣት የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?

4.ካልተጠነቀቁ በቀር የገዛ ባህልዎ፣ ማኅበረሰብዎ እና ሕዝብዎ ወደ ሐሰተኛ አምልኮ ሊመራዎ የሚችሉባቸው መንገዶች የተኞቹ ናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL