የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘኁ. 20:1–13፣ ዘዳ. 31:2፣ ዘዳ. 34:4፣ ዘዳ. 34:1–12፣ ይሁዳ 9፣ 1ቆሮ. 15:13–22።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል እንኳ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ፣ ‘ጌታ ይገስጽህ!’ አለው እንጂ የስድብ ቃል በመናገር ሊከሰው አልደፈረም” (ይሁዳ 9)።
በ
ዚህ ሩብ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንደተመለከትነው--ሟች
የሆነው ሙሴ የዘዳግም መጽሐፍ ዋንኛ አካል ነው። ሕይወቱ፣ ባህሪው
እና መልእክቶቹ በመጽሐፉ በግዝፈት ተንሰራፍተዋል። ምንም እንኳ
የዘዳግም መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር እና እርሱ ለእስራኤል ሕዝቦች ስላለው
ፍቅር የሚያወሳ ቢሆንም፤ እግዚአብሔር ያንን ፍቅር ለመግለጽና ለሕዝቡ
ለእስራኤል ለመናገር ሙሴን በተደጋጋሚ ተጠቅሞበታል።
አሁን ወደ ሩብ ዓመቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን መጨረሻና የዘዳግም
መጽሐፍ መደምደሚያ መምጣታችን፤ ወደ ሙሴ ሕይወት ማብቂያም
(ቢያንስ በዚህ ምድር ሕይወቱ) እንዲሁ ያደርሰናል።
“ብቻውን መሞት እንደነበረበት የተረዳው ሙሴ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት
ማንኛውም ምድራዊ ጓደኛ እንዲያገለግለው አልተፈቀደም ነበር። ከፊቱ
የነበረው ሁኔታ ምስጢራዊነትና አስፈሪነት የሙሴን ልብ አኮማትሮት ነበር።
የሙሴ ፍላጎትም ሆነ ሕይወት ለሕዝቡ ጥንቃቄ ከማድረግና እነርሱን ከማፍቀር
ጋር የተሳሳረ ስለነበር ከዚህ ትስስር መለያየት ለእርሱ ከባድ ፈተና ነበር። ነገር
ግን በእግዚአብሔር ስለ መታመን የተማረው ሙሴ ያለምንም ማንገራገርና
ጥያቄ እራሱንና ሕዝቡን ለአምላካዊው ፍቅርና ምህረት አስገዛ።” (የኃይማኖት
አባቶች እና ነቢያት፡ ክፍል፡2 ገጽ፡112)
የሙሴ ሕይወትና አገልግሎት የእግዚአብሔርን ባህሪ አብልጦ ገልጦ እንዳሳየ
ሁሉ፤ በተመሳሳይ ሞቱ እና ትንሣኤውም ይህንኑ ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳ የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ የመቅበዝበዛቸው ዘመን ተደጋሚ ክህደት ቢፈጽሙም፣ እግዚአብሔር ግን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በታምር ሰጥቷቸዋል። ይህ ለእነርሱ የማይገባቸው ዓይነት (ብዙውን ጊዜ በዚያው የጸኑ) ቢሆኑም የእግዚአብሔር ጸጋ ወደ እነርሱ ይፈስ ነበር። እነሆ እኛም ዛሬ የእርሱ ጸጋ ተቀባዮች ብንሆንም፣ በተመሳሳይ አብልጦ የሚገባን ዓይነት ሰዎች ግን አይደለንም። ለነገሩ የተገባን ቢሆን ኖሮ ጸጋ ባላስፈለገን ነበር--አይደል? እንዲሁም ጌታ በታምር በምድረ በዳ ከሰጣቸው የተትረፈረፈ ምግብ በተጨማሪ ሌላው የጸጋው መገለጫ ውሃ ነበር። ውሃ ባያገኙ ኖሮ በተለይ በዚያ ደረቅ፣ ሞቃትና ባድማ ምድረ በዳ በፍጥነት ባለቁ ነበር። ጳውሎስ ይህን ተሞክሯቸውን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፡ “ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ፣ ዐለት ክርስቶስ ነበር” (1ቆሮ. 10፡4)። “በጉዟቸው ወቅት በሚፈልጉበት ቦታ ሁሉ ውሃ ከአለት እየፈለቀ በሰፈራቸው አጠገብ ይገኝ ነበር።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ክፍል፡2 ገጽ፡42) ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘኁ. 20፡1-13። በዚህ ስፍራ ምን ተከሰተ? ሙሴ ላደረገው ነገር ጌታ የወሰነበትን ቅጣት እንዴት እንረዳለን?
በአንድ በኩል የሙሴን ብስጭት ለማየትና ለመረዳት ብዙም አይከብድም።
ጌታ እነዚያን ሁሉ ምልክቶች፣ ታምራትና ድንቅ ማዳን ካደረገላቸው በኋላ፤
እነሆ አሁን በተስፋይቱ ምድር ድንበር ደርሰዋል። ከዚያስ ምን ተከሰተ?
በድንገት የውሃ እጥረት በመከሰቱ በሙሴ እና በአሮን ላይ ማሤር ጀመሩ።
ጌታ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ውሃ ይሰጣቸው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን
ያን ማድረግ አልቻለም ማለት ነው? ይችላል! እርሱ ያን ማድረግ የማይሳነው
አምላክ እንደመሆኑ አሁንም ሊሰጣቸው ተዘጋጅቶ ነበር።
ሆኖም፣ ሙሴ ዐለቱን ከአንዴም ሁለቴ እየመታ የተናገራቸውን ቃላት
ልብ ይበሉ፡ “ ‘እናንተ ዓመፀኞች አሁን ስሙ! ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ
ውሃ ማውጣት አለብን?’ ” (ዘኁ. 20፡10)። ሙሴ “ዓመፀኞች” ብሎ ሕዝቡን
በመጥራት ንግግሩን የጀመረበት ድምጸት ውስጥ የነበረውን ቁጣ ማንም
ሊያስተውል ይችላል።
በእርግጥ የቁጣው መጥፎነት እንዳለ ሆኖ፤ የሚስተዋል ቢሆንም እንኳ፣
ችግሩ ራሱ ቁጣው ብቻ አልነበረም --ነገር ግን እርሱ ወይም ማንኛውም ሰብዓዊ
ፍጡር ከዐለት ውሃ ማፍለቅ ይችል ይመስል “ ‘ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ
ማውጣት አለብን?’ ” ብሎ መናገሩ ነበር። በቁጣው ውስጥ እንዲህ ዓይነት
ታምር ሊያደርግ የሚችለው በመካከላቸው የሚሠራው የእግዚአብሔር ኃይል
ብቻ መሆኑን የዘነጋ ይመስላል። እርሱም ሆነ መላው ሕዝብ ያን ሊያውቅ
የተገባ ነበር።
ቁጣው ትክክል ነበር ብለን ብናምን እንኳ፣ በቁጣ ስሜት
ውስጥ ስንሆን በተደጋሚ በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ምን
ይስተዋላል? ያልሆነ ነገር ከመናገራችንና ከማድረጋችን በፊት
ትክክለኛውን ነገር እንናገር እና እናደርግ ዘንድ ቆም ማለት፣
መጸለይና የእግዚአብሔርን ኃይል መፈለግ መማር የምንችለው
እንዴት ነው?
ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ ዘኁ. 20፡12-13። ሙሴ ባደረገው ነገር ምክንያት ወደ ፊት መቀጠል አለመቻሉን አስመልክቶ ጌታ የሰጠው ምክንያት ምን ነበር? በተጨማሪ ያንብቡ፡ ዘዳ. 31፡ 2፣ 34፡4።
በጥቅሱ መሠረት ሙሴ የእግዚአብሔርን ቦታ ለመውሰድ ካደረገው ሙከራ በተጨማሪ የከፋ ነገር ያሳየ ሲሆን፤ ይኸውም እንደ ሙሴ ዓይነቱ ሰው ይቅርታ ሊደረግለት የማይችለውን እምነተ-ቢስነት ማሳየቱ ነበር። እርሱ ማለት-ከሚቃጠለው ቁጥቋጦ (ዘፀ. 3፡2-16) አንስቶ ከሌሎች በተለየ ከእግዚአብሔር ጋር አስገራሚ ተሞክሮ የነበረው ቢሆንም፤ ጥቅሱ እንደሚነግረን ሙሴን በእኔ አላመንክም (1962 ትርጉም) ማለቱ እምነተ ቢስነቱን ማሳየቱን ተከትሎ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርገህ” ሳታከብረኝ ቀረህ ይለዋል። በሌላ አነጋገር ከሕዝቡ ክህደት ጎን ለጎን ሙሴ ተረጋግቶ እምነቱን በሚገልጥና በእግዚአብሔር ላይ ያለውን መታመን በሚያሳይ መልኩ ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ኖሮ፤ ጌታን በሕዝቡ ፊት ባከበረው--የእውነተኛ እምነት እና መታዘዝ ምሳሌ በሆናቸውም ነበር። በተጨማሪም ሙሴ ጌታ በተለይ እንዲታዘዝ የነገረውን ነገር እንዴት እንዳልታዘዘ ልብ ይበሉ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘኁ. 20፡8። ጌታ ምን አድርግ ሲል ነበር ለሙሴ የነገረው? ሙሴ በተባለው ምትክ ምን አደረገ (ዘኁ. 20፡ 9-11)?
ሙሴ “ልክ እንደ ታዘዘው” በትሩን መውሰዱ በቁ. 9 ቀርቧል። እስከዚህ ድረስ እጅግ መልካም ነበር። ነገር ግን በቁ. 10 እንደ ቀረበው ዐለቱን ተናግሮ ውሃው እንዲፈልቅና አስደናቂው የእግዚአብሔር ኃይል እንዲገለጥ በማድረግ ፋንታ ሙሴ በበትሩ መታው--አንዴ ሳይሆን ሁለቴ። ዐለትን በበትር መትቶ ውሃ እንዲፈልቅ ማድረግ ታምር ቢሆንም፤ ነገር ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ዐለትን ተናግሮ ውሃ እንዲፈልቅ የማድረግ ያህል ታምራት ግን አይሆንም። ሙሴ ካለፈባቸው እነዚያ ሁሉ ሁናቴዎች አኳያ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያሳለፈው ፍርድ ላይ ላዩን ሲያዩት በጣም የተጋነነ ሊመስል ይችላል። አዎ፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር አልፎ እንዲገባ አልተፈቀደለትም ነበር። በአንድ ጥድፊያ የተሞላው ሁናቴ ለተፈጸመ ድርጊት፣ ከረጅም ዘመን አንስቶ ሲጠብቅ የኖረውን ነገር ለምን ተከለከለ--ብለው ብዙዎች ይህ ታሪክ በተነገረ ቁጥር ይብሰለሰላሉ። የእስራኤል ልጆች በሙሴ ላይ ከደረሰው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት የነበረባቸው ይመስሎታል?
ምስኪኑ ሙሴ ይህን ሁሉ መንገድ ተጉዞ በእነዚያ አስቸጋሪ ሆናቴዎች ካለፈ በኋላ፤ በመጨረሻ እግዚአብሔር ከብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” (ዘፍ. 12፡7) ብሎ ለአብርሃም የሰጠውን የተስፋ ቃል ፍጻሜ ሳያይ ቀረ፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 34፡1-12። ሙሴ ላይ ምን ደረሰ? እርሱ የተለየ ሰው እንደ ነበር አስመልክቶ ጌታ ስለ ሙሴ ምን አለ?
“ሙሴ በበለጸገችው የግብፅ ግዛት ከነበረው ማዕረግና ደረጃ ለቅቆ ዕጣ
ፈንታውን ከእግዚአብሔር ምርጥ ህዝቦች ጋር ካደረገበት ጊዜ አንስቶ
ያለፈበትን የችግርና የእንግልት ሕይወት አስታወሰ። በእረኝነት የዮቶርን መንጋ
ሲጠብቅ ያሳለፋቸው
ረጅም ዘመናት፣ በሚቃጠለው ቁጥቋጦ የተገለጠው የእግዚአብሔር መልአክና
እስራኤልን ነጻ ለማውጣት የነበረው የግል ጥሪ ወደ አእምሮው መጡ።
እስራኤልን ነፃ ለማውጣት ስለ ሕዝቡ የተገለጸው ኃያሉ የእግዚአብሔር
ተአምራት እንዲሁም በረጅሙ የመቅበዝበዝና የአመጻ ዘመን የነበረው
ትዕግሥትና ይቅር ባይነትን አስታወሰ። እግዚአብሔር ለእነርሱ ብዙ ነገር
ቢያደርግም፣ ሙሴ ቢጸልይና ብርቱ ሥራ ቢሠራም --ግብፅን ለቅቀው
ሲወጡ ከነበሩት ጎልማሶች ሁለቱ ብቻ ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው ወደ
ተስፋይቱ ምድር መግባት ቻሉ። ሙሴ የድካሙን ውጤትና ፈተና የበዛበትን
የመሥዋእትነት ሕይወቱን ሲገመግም ከንቱ ሆኖ ታየው።” (የኃይማኖት
አባቶችና ነቢያት፡ ክፍል 2፣ ገጽ 113-114)
ዘዳ. 34፡4 አንድ በጣም አስደሳች ነገር ይናገራል፡ “ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና
ለያዕቆብ፣ ለዘሮቻችሁ እሰጣለሁ ብዬ በመሓላ ቀል የገባሁላቸው ምድር
ይህች ናት።” ጌታ ይህችን ምድር ለአባቶቻቸው እና ለልጆቻቸው እንደሚሰጥ
በተደጋጋሚ ቃል በቃል የተናገረውን አሁን ደግሞ በድጋሚ ለሙሴ እየነገረው
ነበር።
በተጨማሪ ጌታ “ ‘በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ነገር ግን ወደዚያ
አትሻገርም’ ” (ዘዳ. 34፡4) ብሎት ነበር። ሙሴ ከቆመበት ድንበር ሆኖ
በተፈጥሮአዊ ዐይኖቹ ጌታ የጠቆመውን ከሞዓብ እስከ ዳን እና ንፍታሌም
ወዘተ ያለውን ሁሉ ማየት የሚችልበት ሁናቴ ሊኖር አይችልም። ኤለን
ኋይት ይህን ጉዳይ ግልጽ ታደርገዋለች፡ ሙሴ ልዕለ ተፈጥሮ በሆነ መገለጥ
የተመለከተው ምድሪቱን ብቻ ሳይሆን፤ ነገር ግን ምድሪቱን ከወረሱ በኋላ
የሚኖረውን ሁኔታ ጭምር ነበር።
በአንድ በኩል ጌታ ጉዳዩን እየነካካና የሙሴን ሆድ እያባባ ያለ ይመስላል፡
እንደሚገባው ብትታዘዘኝ ኖሮ አንተም በዚህ መሆን ትችል ነበር። ከዚያ ሁሉ
ውጣ ውረድ ባሻገር፣ እንደውም ከሙሴ ስህተት በኋላም እንኳ--እግዚአብሔር
ከአባቶቻቸው እና ከራሳቸው እስራኤላውያን ጋር የገባውን ኪዳን በታማኝነት
እንደሚጠብቅ ለሙሴ እያሳየው ነበር። ቀጠል አድርገን እንደምንመለከተው
ይህ የጌታ ታማኝና ኅፀፅ የማያጣው አገልጋዩ የተሻለ ነገር ይጠብቀዋል።
“እግዚአብሔር እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በሞዓብ ምድር ሞተ። በሞዓብ ምድር በቤተ ፌጎር ፊት ለፊት ባለው ሸለቆ ቀበረው፤ ይሁን እንጂ መቃብሩ የት እንደ ሆነ እስከ ዛሬ ማንም አያውቅም።” (ዘዳ. 34፡5-6)። እንግዲህ--የእስራኤል ሕዝብ ሕይወት ማዕከል፣ መልእክቶቹ እስከ ዛሬ ሕያው ሆነው የሚነበቡ፣ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለዛሬው የአይሁድ ምኩራብ ወሳኝ የነበረው ሰው፣ ከላይ በቀረቡት ጥቂት ጥቅሶች በተገለጸው መሠረት--ሞተ። ሙሴ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ሕዝቡም አዘነ--በቃ ይኸው ነበር። በራእይ መጽሐፍ የቀረበው መርኅ በዚህ ስፍራ ተግባራዊ መሆን ይችላል፡ “ ‘ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ ሆነው የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው።” መንፈስም፤ “ ‘አዎ ሥራቸው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ያርፋሉ’ ይላል” (ራእ. 14፡13)። የሆነው ሆኖ የሙሴ ሞት በሙሴ የሕይወት ታሪክ የመጨረሻው ምዕራፍ አይደለም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ይሁዳ 9። በዚህ ስፍራ ምን እየሆነ ነው? በኋለኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የሙሴን ገጽታ ለማብራራት እንዴት ይረዳል?
ምንም እንኳ በጨረፍታ ብቻ ቢነገረንም፣ ነገር ግን በዚህ ስፍራ የቀረበው
ትዕይንት እጅግ አስደናቂ ነው። ሚካኤል ማለትም ክርስቶስ ራሱ በሙሴ ሥጋ
ዙሪያ ተሟግቷል። ለመሆኑ እንዴት በሥጋው ዙሪያ ሙግት ተነሣ? ሙሴ
ኃጢአተኛ እንደ ነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሲጀመር ለእግዚአብሔር
ይገባ የነበረውን ክብር ለራሱ የወሰደበት የመጨረሻው ኃጢአቱ--ራሱን
ሉሲፈርን ከሰማይ እንዲወረወር ካደረገው፡ “ ‘ከደመናዎችም ከፍታ በላይ
ዐርጋለሁ፤ ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ’ ” (ኢሳ. 14፡14) ጋር ተመሳሳይ
ኃጢአት ነበር። ክርስቶስ ይህን የትንሣኤ ተስፋ ቃል ለሙሴ ይገባዋል ማለቱ
በሥጋው ላይ ክርክር እንዳስነሣ ይታመናል።
ነገር ግን ክርስቶስ ሕጉን ለጣሰ እንደ ሙሴ ዓይነቱ ኃጢአተኛ ይህን ማድረግ
የሚችለው እንዴት ነው? መልስ መሆን የሚችለው በእርግጥ መስቀሉ ብቻ
ነው። ሁሉም የእንስሳት መሥዋእቶች ወደፊት ገቢራዊ የሚሆነውን የክርስቶስ
ሞት ያመላክቱ እንደነበር ሁሉ፤ ጌታም አሁን ወደ መስቀሉ በመመልከት
የሙሴ አካል የትንሣኤ ባለቤትነት ይገባዋል ሲል ተከራከረ። “ሙሴ በሠራው
ኃጢአት ምክንያት በሰይጣን ኃይል ስር ወደቀ። የእርሱ ሥራ የሞት እስረኛ
ቢያደርገውም፤ ነገር ግን በአዳኙ ማዕረግና ስም የማይሞት ሆኖ ተነሳ። ሙሴ
በክብር ከመቃብር ተነስቶ ከአዳኙ ጋር ሽቅብ ወደ እግዚአብሔር ከተማ
ወጣ።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ክፍል 2 ገጽ፡ 120)።
ይህ ሙሴ ከመስቀሉ በፊት እንኳ ሕያው ሆኖ የተነሣበት ታሪክ፤
የደኅንነት ዕቅድ ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው እንድናስተውል
እንዴት ይረዳናል?
ጉዳዩን በአዲስ ኪዳን ከምናገኘው ተጨማሪ ብርሃን አኳያ ስንመለከተው የሙሴ ከተስፋይቱ ምድር መገለል እንደውም ከቅጣት አኳያ የሚታይ አይመስልም። ከምድራዊቷ ከነዓን እና ከኋለኛዋ ምድዊ የሩሳሌም (በታሪኳ የጦርነት፣ የወረራና የሥቃይ ስፍራ ሆና የኖረችው) ይልቅ “ሰማያዊዋ የሩሳሌም” (ዕብ. 12፡22) እነሆ ዛሬም የእርሱ መኖሪያ ናት። እጅግ የተሻለ መኖሪያ ስፍራ! የሙታንን ትንሣኤ አስመልክቶ የቀረበው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሙሴ ነው። ሔኖክ ሞትን ሳያይ ወደ ሰማይ የተወሰደ ሲሆን (ዘፍ. 5፡ 24) ኤልያስም በተመሳሳይ ሞትን ሳይቀምስ አርጓል (2ነገሥ. 2፡11)። ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው መልእክት እንደምንረዳው ከመቃብር ተነሥቶ የዘላለም ሕይወት ባለቤት ለመሆን፣ ሙሴ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ሙሴ ለምን ያህል ጊዜ እንዳንቀላፋ ባናውቅም፣ ነገር ግን ይህ ምንም ለውጥ አያመጣም። ዐይኖቹ አንዴ በሞት ከተጨፈኑ በኋላ ለሦስት ሰዓት ይቆይ ወይም ለሦስት መቶ ዓመታት ለእርሱ ተመሳሳይ ነበር። እንዲሁም ከምድር ታሪክ አንስቶ በሞት ላንቀላፉ ሁሉ ስሜቱ አንድ ዓይነት ነው። በሞት ጥላ ያላንቀላፉ ሰዎች የቱንም ያህል ዘመን በመቃብር ቢቆዩ፣ የቆይታቸው ተሞክሮ ከሙሴ የተለየ አይሆንም። ዐይኖቻችን አንዴ በሞት ከተጨፈኑ በኋላ በቀጣይ የምናውቀው ነገር--የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ወይም አሳዛኙን የመጨረሻ ፍርድ ይሆናል (ራእ. 20፡7-15)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 15፡13-22። በዚህ ስፍራ የምናገኘው ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው? የጳውሎስ መልእክት ትርጉም ሊሰጥ የሚችለው--በክርስቶስ ያንቀላፉ በመቃብር የሚቆዩት እስከ ትንሣኤ መሆኑን ከተረዳን ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?
የትንሣኤ ተስፋ ከሌለን፤ አንዳችም ተስፋ የምናደርገው ነገር አይኖረንም። የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛ ዋስትና ነው። ለእኛ በመስቀል ላይ የመሥዋእት በግ ሆኖ በመሞት እና ከሙታን በመነሣት “የኃጢአት መንጻት” (ዕብ. 1፡3) አስገኘልን። እርሱ ከሞት በትንሣኤ የተነሣ እንደ መሆኑ፣ ለወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ከሞት መነሣት የመጀመሪያ ምሳሌ ከሆነው ከሙሴ ጋር እነሆ እኛም ይህ የትንሣኤው ዋስትና አለን። ክርስቶስ ወደፊት በሚያደርገው ነገር ሙሴ እንደተነሣ ሁሉ፤ ክርስቶስ ባደረገው ነገር ደግሞ እኛም እንነሣለን። በመሆኑም በሙሴ ታሪክ የጽድቅ በእምነት ምሳሌ ማግኘት የምንችል ሲሆን፤ ይኸውም ታማኝ በሆነና በእግዚአብሔር የሚመካ ሕይወት ውስጥ የሚገለጥ እምነት ነው--መጨረሻ ላይ መደናቀፍ ቢገጥመውም እንኳ። እንዲሁም በአጠቃላይ የዘዳግም መጽሐፍ ሙሴ ለእግዚአብሔርን ሕዝብ ተመሳሳይ የታማኝነት ጥሪ ለማቅረብ ይጥር እንደነበር ማየት እንችላለን። እነርሱ ለተሰጣቸው ጸጋ ምላሽ መስጠት እንደነበረባቸው ሁሉ--እኛ በተስፋይቱ ምድር ድንበር የምንገኝም ተመሳሳይ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል። ዛሬ ታማኝ እንድንሆን ጥሪ እያቀረበልን የሚገኘው ያው እግዚአብሔር አምላክ አይደለምን? ሙሴ በዘዳግም አስቀድሞ ያስጠነቀቀውን ተመሳሳይ ስህተቶች እኛም መልሰን እንዳንሠራ ምን ማድረግ እንችላለን?
““ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” ብለው በንዴት ሲጮኹ --ሰዎች እንደመሆናቸው ከሰብዓዊ ጉድለትና ስሜታዊነት ሊወጡ ባይችሉም እራሳቸውን በእግዚአብሔር ቦታ አስቀመጡ። በሕዝቡ ተከታታይ አመፅና ማጉረምረም የተሰላቸው ሙሴ ኃያል ረዳቱን መመልከት ተስኖት ያለ መለኮታዊው እርዳታ በሰብዓዊ ድክመቱ ችግሩን እንዲጋፈጥ ተተወ። በንጽህና የተመላለሰ፣ ጠንካራና እራስ ወዳድ ያልሆነው ሙሴ፤ አገልግሎቱ ወደ ፍጻሜ የተቃረበበት ሰዓት ላይ ሽንፈት ገጠመው። እግዚአብሔር ሊከብርና ከፍ ከፍ ሊደረግ ሲገባ በእስራኤል ማኅበረሰብ ፊት ክብሩ ተዋረደ።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ክፍል 2 ገጽ፡ 49) “ሙሴ ወደ ሰማይ ካረገው ኤልያስ ጋር በመሆን በመለወጥ ተራራ ላይ ተገኝቶ ነበር። እንደ ብርሃን ተሸካሚና ከአብ ለልጁ ክብር መገለጫ ሆነው ተልከው ነበር። በዚህም ሙሴ ከብዙ ክፍለ ዘመናት አስቀድሞ የጸለየው ጸሎት በስተመጨረሻ ፍጻሜ አገኘ። “በመልካሙ ተራራ” ላይ ቆሞ እስራኤል የሚወርሰውን ምድር ተመለከተ፤ እስራኤልን ማዕከል ላደረገ ተስፋ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስክር ሆነ። ይህ እንግዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እግዚአብሔር ላከበረው ሟች ሰው የተገለጠ የመጨረሻው ራእይ ነበር። (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ክፍል 2 ገጽ፡ 121) የመወያያ ጥያቄዎች፡ 1.በአንድ በኩል አዎ--ሙሴ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በትንሣኤ ወደ ሰማይ ተወስዷል። ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት ምስኪኑ ሙሴ (እንደምንገምተው) እዚህ ምድር ላይ እየሆነ የነበረውን እጅግ አሳዛኝ ትዕይንት ይመለከታል። አብዛኞቻችን ቢያንስ በምድር እየተካሄደ ያለው ፍልሚያ ካበቃ በኋላ በዳግም ምጽአቱ በትንሣኤ መነሣታችን ምን ያህል እድለኞች ያደርገናል! ታዲያ ይህ ሙሴ ካጋጠመው የበለጠ በረከት የሚሆነው በምን መንገድ ነው? 2.አዲስ ኪዳን አብልጦ በብሉይ ኪዳን ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም፤ የሙሴን ሞት እና በቀጣይ ገቢራዊ የሆነውን የትንሣኤውን ታሪክ አስመልክቶ ግን ከብሉይ ኪዳን አልፎ በመጓዝ በእርግጥም ሰፋ ያለ አዲስ ብርሃን የሚፈነጥቅልን እንዴት ነው? 3.ሙሴ በቁጣ ዐለቱን መምታቱን ጨምሮ ያለው የሕይወት ታሪኩ ከሕጉ ተግባራት ጎን ለጎን በእምነት ስለ መኖር እና በእምነት ስለ መዳን እንዴት ምሳሌ ይሆነናል? 4.በክፍል ውስጥ በዘመኑ መጨረሻ ገቢራዊ እንደሚሆን በተሰጠው የዳግም ምጽአቱ ተስፋ ዙሪያ ተወያዩ። ይህ የተስፋ ቃል የተስፋችን ሁሉ ወሳኝ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? እንዲሁም በዚህ ዙሪያ ማለትም ከሞት እንደሚያስነሣን በእግዚአብሔር ላይ መተማመን ከቻልን፣ ስለ ሌላው ማንኛውም ነገር በእርሱ መታመን መቻል የለብንምን? ለነገሩ እርሱ ያን ለእኛ ማድረግ ከቻለ ምን ማድረግ ይሳነዋል? የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ ማሳሰቢያ የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡ በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡ ድርጅቱ