የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ኢሳይያስ፡ “ሕዝቤን አጽናኑ”


1ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከጥር 29 – የካቲት 5

7ኛ ትምህርት

Feb 06 - Feb 12




የአሦራውያን ሽንፈት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 36:1፣ ኢሳ. 36:2–20፣ ኢሳ. 36:21–37:20፣ ኢሳ. 37:21–38፣ ኢሳ. 38-39.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “‘በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል’ ” (ኢሳ. 37፡16)።

አ ንድ ሰውነቱ የከሳ አባት ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር በባዶ እግሩ ይራመዳል። ሌላ ቤተሰብ ደግሞ ያለውን ንብረት በበሬ በሚጎተት ጋሪ ጭኖአል። በጋሪው ላይ ሁለት ሴቶች የተቀመጡ ሲሆን፤ አንድ ሌላ ሰው በሬዎቹን ይስባል። ከእነዚህ የባሱ ጋሪ የሌላቸው የምስኪን፣ ምስኪኖች ደግሞ ያላቸውን ንብረት በትከሻቸው ተሸክመው ጉዞአቸውን ቀጥለዋል። ወታደሮች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ከርቀት የሚወነጨፍ ከባድ አሎሎ የከተማዋን መግቢያ በር ይደበድባል። ከዚህ ጎን ለጎን ቀስተኞች መግቢያ በሩን በሚከላከሉ ወታደሮች ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት አፋፍመዋል። ምድር ቁና ሆናለች፣ ሞት እና ጥፋት በከፍተኛ ደረጃ ነግሦአል።

ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ--በዙፋኑ የተሰየመ ግርማ ሞገስ ያለው ንጉሥ ምርኮ እና ምርኮኞችን ይቀበላል። አንዳንዶቹ ምርኮኞች እጆቻቸውን ከፍ አድርገው፣ ሌሎች ተንበርክከው ወይም ቁጢጥ ብለው ምህረት እንዲያደርግላቸው ይማጸኑታል። “የዓለም ንጉሥ ሰናክሬም፣ የአሦር ንጉሥ፤ በናምዱ ዙፋን ተቀምጧል፤ የለኪሶ ከተማ ምርኮም በፊቱ አልፏል” የሚሉ ንጉሡን የተመለከቱ መግለጫዎች በስፋት መደመጣቸውን ቀጥለዋል።”—John Malcolm Russell, The Writing on the Wall (Winona Lake, Indiana: Eisenbrauns, 1999), pp. 137, 138.

በአንድ ወቅት የሰናክሬምን “ተቀናቃኝ የለሽ ቤተ መንግሥት” ግድግዳዎች ያስጌጡ እነዚህ ተከታታይነት ያላቸው ሥዕሎች ዛሬ በብሪታንያ ሙዚየም ውስጥ ይገኛሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስላጋጠማቸው መከራ የሚናገሩ እንዴት ድንቅ ታሪክ ይዘዋል!

ጥር 30
Feb 07

ስምምነት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ልዩ ፍላጎቶች (ኢሳ. 36፡1)


በይሁዳ ላይ ምን ደረሰ? 2 ነገሥ. 18:13፣ 2ዜና 32:1፣ ኢሳ. 36:1።



እምነት የለሹ አካዝ ሲሞት እና ታማኝ ልጁ ሕዝቅያስ እርሱን ሲተካው፣ ሕዝቅያስ ሙሉ በሙሉ ነፃነቱን ያጣውን መንግሥት ወረሰ። ከሶርያና ሰሜን እስራኤል የጦር ኪዳን ስምምነት ወረራ ለማምለጥ የአሦርን እርዳታ የገዛችው ይሁዳ፤ በግብር መልክ ለአሦር “የከለላ ክፍያ” እየፈጸመች ለመቀጠል ተገድዳ ነበር (2ዜና 28፡1621)። የአሦር ንጉሥ ዳግማዊ ሳርጎን ሩቅ አገር ላይ በተደረገ ዓውደ ውጊያ ሲሞት፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ707 ሰናክሬም በእርሱ እግር ዙፋን ላይ ቢቀመጥም አሦር ደካማ ሆና ታየች። በአሦር በኩል ያሉ ማስረጃዎችም ሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደሚጠቁሙት፤ ሕዝቅያስ በቀጣናው በነበሩ አነስተኛ ነገዶች መሃል ጠብ አጫሪ ርምጃ ወስዶ ቀንደኛ ጸረ አሦር የነውጥ መሪ የሚያደርገውን ይህን አጋጣሚ ለማመጽ ተጠቀመበት (2ነገሥ. 18፡7)።

ሕዝቅያስ የወቅቱን የአሦር ብርቱ የውጊያ ብቃት ዝቅ አድርጎ መመልከቱ አሳዛኝ ክስተት ነበር። ሰናክሬም ከክርስቶስ ልደት በፊት 701 ላይ ሌሎች የግዛቱን አካላት እንዳንበረከከ፤ አውዳሚ ኃይል ተጠቅሞ በሶርያ ፍልስጥኤም ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጸመ፤ ይሁዳን ወርሮ የተመሸጉትን ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው። ሕዝቅያስ ከአሦር ጋር ለመጋጠም የተዘጋጀው እንዴት ነበር? 2ዜና. 32:1–8



ሰናክሬም ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ ማሴሩን ሕዝቅያስ ባየ ጊዜ ከአሦር ጋር ለመጋጠም የሚያስችለውን ሰፊ ዝግጅት አደረገ። ምሽጎቹን አጠናከረ፣ ሠራዊቱን ከቀድሞው በበለጠ አስታጥቆ አደራጀ፤ እንዲሁም የየሩሳሌምን የውሃ አቅርቦት ደህንነት አጠናከረ (2ነገሥ. 20፡20፣ 2ዜና 32፡30)። ሕዝቅያስ ለከበባው ባደረገው ዝግጅት ስለ ሠራው አስገራሚ የሰሊሆም የውሃ ማለፊያ ቦይ ተጽፎ እናገኛለን። ወታደራዊ እና ድርጅታዊ አመራር አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፤ ሕዝቅያስ በዚህ አስፈሪ ጊዜ የሕዝቡን የሞራል ልዕልና ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መንፈሳዊ አመራር ሰጥቶአል። “ነገር ግን የይሁዳ ንጉሥ ጠላትን ለመቋቋም የበኩሉን ዝግጅት ለማድረግ ቁርጠኝነት ነበረው። ሰብዓዊ ብልሃትና ጉልበት ሊያከናውን የሚችለውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፤ ሠራዊቱን ሰብስቦ ደፋር እንዲሆኑ አበረታታቸው።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 351.

ሕዝቅያስ አብልጦ በጌታ እስከታመነ ድረስ በራሱ በኩል ያን ሁሉ ጥረት ማድረግ ለምን አስፈለገው? ለመሆኑ ተግባሩ እምነቱን ይቃረን ነበር? በትክክል ውጤታማ ኃይል ከሚሰጠው ከእግዚአብሔር ጋር ስለ መተባበር--ፊልጵ. 2፡12-13 ይመልከቱ።

የካቲት 1
Feb 08

ሐሰትን እንደ እውነት ለማሳመን የሚደረግ የቅስቀሳ ወሬ (ፕሮፓጋንዳ)፡ ኢሳ. 36፡2-20


የአሦር ገዥዎች ጨካኝ ብቻ ሳይሆኑ ብልሃተኞችም ነበሩ። ግባቸው ሐብት ማካበትና ኃይል ማደራጀት እንጂ ጥፋት ብቻ አልነበረም (ኢሳ. 10፡ 13-14)። የተከበበው ሕዝብ እጁን እንዲሰጥ ማሳመን ከቻሉ፤ ከተማውን በኃይል ለመውሰድ ለምን ሀብታቸውን ያባክናሉ? ስለዚህ ሰናክሬም ለኪሶን ከብቦ ከያዘው ሰራዊት ጋር ሰፍሮ፤ የሩሳሌምን በፕሮፓጋንዳ ለመውሰድ ከፍተኛ የጦር አዛዡን ወደዚያው ላከው። የጦር አዛዡ ይሁዳን ለማስፈራራት የተጠቀማቸው መሞገቻ ሀሳቦች ምን ነበሩ? ኢሳ. 36:2–20፣ 2ነገሥ. 18:17–35፣ 2ዜና 32:9–19።



የጦር አዛዡ አንዳንድ ብርቱ መሞገቻ ነጥቦችን አንስቶ ነበር። ግብፅ ደካማና የማይተማመኑባት ስለሆነች በእርሷ መታመን አትችልም። ሕዝቅያስ በመላው ይሁዳ የነበሩትን ማምለኪያ ኮረብቶችና መሠዊያዎች ከስፍራቸው አስወግዶ ሕዝቡ በየሩሳሌም መሠዊያ አምልኮ እንዲያቀርብ በመንገር ጌታን ስላሳዘነው በእርሱ መተማመን አትችልም። ጌታ በእርግጠኝነት የቆመው በአሦር በኩል ስለሆነ ሰናክሬም ይሁዳን እንዲያጠፋ ነግሮታል። ደግሞስ 2,000 ፈረሰኞችን ለመቋቋም የሚያስችል በቂ የሰለጠኑ ወታደሮች እንኳን የታለህ።

የሚበላና የሚጠጣ ከማግኘት የሚያግዳችሁን ይህን ከበባ ለማስወገድ አሁኑኑ እጃችሁን ብትሰጡ በእንክብካቤ ትያዛላችሁ። ሕዝቅያስ ሊያድናችሁ አይችልም። በአሦር ድል የሆኑ የሌሎች አገሮች አማልክት ሕዝቦቻቸውን መታደግ እንዳልቻሉ ሁሉ፤ የእናንተም አምላክ እንደማያድናችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። የጦር አዛዡ የተናገረው እውነት ነበር?



አዛዡ ከተናገረው መሃል አብዛኛው እውነት ከመሆኑ አኳያ ያቀረባቸው የሙግት ሀሳቦች አሳማኝ ነበሩ። እንዲሁም ሁለት ያልተነገሩ የሙግት ነጥቦች ድጋፍ ሆነውት ነበር። አንደኛ--አሦራውያን ጠንካራ ምሽጎች በነበሯትና እነርሱን ለመቋቋም በደፈረችው ከተማ ላይ የተከሰተውን ይፋ ካደረጉበት 48 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቀት ከነበረው ከለኪሶ አዛዡ መምጣቱ። ሁለተኛ--ብርቱና አስተማማኝ የአሦር ሰራዊት አብሮት መሆኑ (ኢሳ. 36፡2)። ከሦርያ ጋር የገጠሙ ሌሎች ሰራዊቶችና ከተሞች ዕጣ ፈንታ ምን እንደ ነበር መገንዘብ (የሰሜን እስራኤል ዋና ከተማ ሰማሪያን ጨምሮ፡ 2ነገሥ. 18:9-10) ከሰብዓዊ ዐይን አኳያ የሩሳሌም እንድትጠፋ የተፈረደባት ለመሆኗ ማንም ይሁዳዊ የሚጠራጠርበት ምክንያት ማግኘት አይችልም (ኢሳ. 10፡8-11)።

ሕዝቅያስ በየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ አንድ ብቻ ማዕከላዊ የአምልኮ ስፍራ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ፤ መሥዋእት ይቀርብባቸው የነበሩ የተለያዩ ስፍራዎችን አጥፍቷል። ስለዚህ የጦር አዛዡ የተናገረው ትክክል ነበር (2ነገሥ. 18፡4፣ 2ዜና፡ 31፡1)። ነገር ግን ይህ ተሐድሶ ለሕዝቡ ብቸኛ ተስፋ የነበረውን ጌታ አስቀይሞት ይሆን? ሊያድናቸውስ ይቻለዋል? የዚህ ጥያቄ መልስ ለእግዚአብሔር የተተወ ነበር! በሰው አስተሳሰብ ሲታይ ሁሉም እንዳይሆን መስሎ የታየበት ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞዎት ያውቃል? የነበረዎት ብቸኛው አማራጭ ምን ነበር? ፈቃደኛ ከሆኑ እንዴት እንደ ተቋቋሙትና የመጨረሻው ውጤት ምን እንደነበር የሚያሳይ ተሞክሮዎን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ለማካፈል ይዘጋጁ።

የካቲት 2
Feb 09

የተናወጠ ግን ያልተተወ (ኢሳ. 36፡21-37፡20)


አፈ ጮሌው የጦር መሪ በሕዝቅያስ እና ባለሟሎቹ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነበር? 2ነገሥ. 18:37–19:4፣ ኢሳ. 36:21–37:4።



ክፉኛ የተናወጠውና በጭንቀት የተዋጠው ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፤ አባቱ ምክረ ሀሳቡን ችላ ብሎ የነበረውን የነቢዩን ኢሳይያስ የምልጃ ጸሎት በትህትና ሻተ። እግዚአብሔር ሕዝቅያስን ያበረታታው እንዴት ነበር? ኢሳ. 37፡ 5-7።



መልእክቱ አጭር ቢሆንም በቂ ነበር። እግዚአብሔር ከህዝቡ ጎን ነበር። ሰናክሬም በይሁዳ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚያደናቅፍ ወሬ እንደሚሰማ ኢሳይያስ ተንብዮአል። ይህ ወዲያውኑ ተፈጸመ። ጊዜያዊ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢሰማውም፤ ነገር ግን በምንም ዓይነት ወደ ኋላ ላለማለት የወሰነው ሰናክሬም ሕዝቅያስን የሚያስፈራሪ መልእክት ላከበት፡ “‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልህ… የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን?’ ” (ኢሳ. 37፡10፣12፣ 2ዜና 32፡17)

በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ በቀጥታ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ደብዳቤውን “ ‘በኪሩቤል ላይ’ ” በሚቀመጥ (ኢሳ. 37:14–16) በሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። የሕዝቅያስ ጸሎት የሩሳሌም ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷን እንዴት ያሳያል? ኢሳ. 37:15–20



ሰናክሬም በሕዝቅያስ ጠንካራ መከላከያ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝሯል፡ በአምላኩ ባለው እምነት ላይ። ሕዝቅያስ የደረሰበትን ተጽእኖ በመንገር ፋንታ ይህ አምላክ ማንነቱን እንዲገልጥ ለመጠየቅ በእግዚአብሔር ፊት ቀረበ “ ‘የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ’ ” (ኢሳ. 37:20)። የሕዝቅያስን ልመና በጸሎት መንፈስ ያንብቡ (ኢሳ. 37፡15-20)። በየትኞቹ ነገሮች ላይ ያተኩራል? በግላዊ ችግሮቻችን ውስጥ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንድንችል፤ ብርታትና ጥንካሬ የሚሰጠን ምን ዓይነት መርኅ በዚህ ጸሎት ውስጥ እናያለን?

የካቲት 3
Feb 10

ቀሪው ታሪክ (ኢሳ. 37፡21-38)


ሰናክሬም እንደገለጸውና በዜና መዋዕሎቹ እንደተዘገበው አርባ ስድስት የተመሸጉ ከተሞችን ወሰደ፣ የሩሳሌምን ከበበ እንዲሁም ይሁዲው ሕዝቅያስ “በሽቦ ጎጆ እንደ ተቆለፈባት ወፍ በንጉሣዊ መኖሪያው፣ በየሩሳሌም እስረኛ ሆነ”—James B. Pritchard, editor, Ancient Near Eastern Texts Relating to the Old Testament (Princeton, New Jersey: Princeton University Press, 1969), p. 288. ለራሱ የነበረው ከፍተኛ አመለካከት--ቅጥያ ለሆነው ፕሮፓጋንዳው ፍቅር ቢኖረውም፤ የሩሳሌምን መውሰዱን በጽሑፍም ሆነ በሥዕል አልጠቀሰም። በሰው አስተሳሰብና ዕይታ አኳያ ሕዝቅያስ የማይበገር ኃይል ባለቤት በሆነው ሰናክሬም ላይ ማመጹ ታላቅ ስህተት ነበር። በአሦር ላይ የሚነሱ አመጸኞች አጭር የህይወት ዘመን እና አሰቃቂ ሞት ይጠብቃቸው ነበር።

ምሑራን እንደሚሉት--ምንም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ባይኖረንም በወቅቱ ታምራዊ ክስተት መፈጸሙን አምነን ለመቀበል እንገደዳለን። ሰናክሬም በዚያ “ተቀናቃኝ የሌለው ቤተ መንግሥት” ግድግዳዎች ላይ ያኖራቸው እፎይታ አመላካች ቁልምም ሥዕሎች በለኪሶ ያገኘውን ስኬት በግልጽ ማሳየታቸው፤ የደረሰበትን ሀፍረት አሳንሰው ገጽታውን ለመገንባት በመሣሪያነት የዋሉ ያስመስላቸዋል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ፤ እነዚህ ሥዕሎች ይልቁንም ያሳዩ የነበረው የሩሳሌምን ነበር! ሰናክሬም የተቀረውን ታሪኩን በዜና መዋዕሉ ባይናገርም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይነግረናል። የተቀረውስ ታሪክ? ኢሳ. 37 21-37 ።



የነገሥታት ንጉሥን በጥፊ ለመማታት (ኢሳ. 37፡23) በደፈረው ልበ ደንዳናው የአሦር ንጉሥ ላይ ቁጣው የነደደው አምላክ፤ ሕዝቅያስ በሙሉ እምነት ለጸለየው ጸሎት ጌታ ይሁዳን ለመታደጉ ሙሉ ምላሽ የሚሆነውን ማረጋገጫ የሚሰጠው መልእክተኛ ላከበት (2ነገሥ. 19፡35-37፣ 2ዜና 32፡21-22፣ ኢሳ. 37፡36-38። ታላቅ ቀውስ ታላቅ ታምራት ይጠይቃል። የተረፈረፈው ሬሳ ብዛት 185,000 ነበር። ስለዚህ ሰናክሬም የገዛ ሞቱን ወደ ደገሰለት ወደ ቤቱ ከመመለስ በቀር ሌላ ምርጫ አልነበረውም (ኢሳ. 37፡7-38)

“የዕብራውያን አምላክ በትዕቢት ተወጥሮ በነበረው አሦር ላይ ድል ተቀዳጀ። የእግዚአብሔር ክብር ዙሪያቸውን ባሉ ሕዝቦች ፊት ታየ። በየሩሳሌም፤ የሕዝቡ ልብ በቅዱስ ደስታ ተሞላ”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 361. ሰናክሬም የሩሳሌምን ድል አድርጎ ቢሆን ኖሮ፤ በሰሜናዊ እስራኤል እንዳደረገው ሕዝቡን በግዞት በትኖ ማንነታቸውን እንዲያጡ በሆኑ ነበር። ከዚህ አኳያ መሲህ የሚወለድበት የአይሁድ ሕዝብ ስለማይኖር ታሪካቸው በዚሁ ተደምድሞ ይቀር ነበር። እግዚአብሔር ግን ተስፋውን ሕያው አድርጎ ጠበቀ።

በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አምላክ ገና ለማያምን ሰው የሚከተለውን ጥያቄ ቢጠይቅዎ ምን ይመልሱለታል፡ በዚያ ስፍራ እንዲወለዱ የሆኑ እነዚህ የአሦር ወታደሮች በዚህ መልኩ መሞታቸው ተገቢ ነው? ጌታ በዚህ ስፍራ የወሰደውን እርምጃ በግልዎ እንዴት ያዩታል?

የካቲት 4
Feb 11

በህመም እና በብልጽግና (ኢሳ. ምዕ. 38፣39)


ምንም እንኳ በኢሳ. 37 (2ነገሥ. 19) የተጠቀሰው ዐርነት ተፈጻሚነቱ ገና ቢሆንም፤ የኢሳ. ምዕ. 38 እና 39 (2ነገሥ. 20) ገቢራዊነት እግዚአብሔር ሕዝቅያስን ከሰናክሬም እጅ ካዳነበት ጊዜ ጋር በጣም የተቀራረበ ነው። በእርግጥ--ኢሳ. 38: 5-6 እና 2ነገሥት. 20:6 እንደሚያመለክቱት የአሦራውያን ስጋት አሁንም እንደ ተጋረጠ ነው። “የሕዝቅያስን ሞት እና የየሩሳሌምን ውድቀት ለማምጣት ቆርጦ ተነስቶ የነበረው ሰይጣን፤ ሕዝቅያስ ከጨዋታው ውጪ ከሆነ ተሐድሶ ለማድረግ የነበረው ጥረት ይቋረጣል፤ በዚህም የየሩሳሌም ውድቀት በፍጥነት እውን መሆን ይችላል የሚል እሳቤ ነበረው።”—The SDA Bible Commentary, vol. 4, p. 240. መልካም አመራር ለእግዚአብሔር ሕዝብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከላይ የቀረበው መልእክት ምን ይነግረናል? ጌታ ለሕዝቅያስ እምነት ማረጋገጫ ምን ምልክት ሰጠው? 2ነገሥ. 20:8–10፣ ኢሳ. 38:6–8።



አካዝ በእግዚአብሔር የቀረቡለትን ምልክቶች ባለመቀበል (ኢሳ. 7) ከአሦር ጋር ችግር ውስጥ የከተቱትን አካሄዶች ሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁን ምልክት ጠየቀ (2ነገሥ. 20፡8)። ስለዚህ አባቱ በይሁዳ ላይ ያመጣውን ችግር እንዲቋቋም እግዚአብሔር አበረታታው። በእርግጥም በአካዝ የሰዓት መቁጠሪያ ደረጃ ላይ የወረደውን የፀሐይ ጥላ መመለስ የሚቻለው በታምር ብቻ ነበር። ባቢሎናውያን የሰማያዊ አካላት እንቅስቃሴዎችን ያጠኑ፣ በትክክልም ይመዘግቡ ነበር። በመሆኑም በወቅቱ የተከሰተውን የፀሐይ እንግዳ ባህሪ በማስተዋል ምን ማለት እንደሆነ ተገርመዋል። ይህን ተከትሎ ንጉሥ መሮዳክ ባልዳን መልእክተኞች መላኩ ድንገተኛ ነገር አልነበረም። ባቢሎናውያን በሕዝቅያስ ማገገምና በተአምራዊ ምልክት መካከል ስላለው ግንኙነት ያውቁ ነበር።

እግዚአብሔር ለምን ይህን የተለየ ምልክት እንደመረጠ ዛሬ እኛ እናውቃለን። እርሱ ከምሥራቅ ጠቢባንን ወደ ቤተልሔም ለማምጣት ኮከብ እንደ ተጠቀመ ሁሉ፤ የፀሐይን ጥላ በመመለስ መልእክተኞች ከባቢሎን እንዲመጡ አደረገ። ይህ ስለ እውነተኛው አምላክ መማር የሚችሉበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ አጋጣሚ ነበር። መሮዳክ ባልዳን ከአሦር ነፃነቱን ለመቀዳጀት ሙከራ በማድረግ ሙሉ የሙያ ዘመኑን አሳልፏል። ይህ ንጉሥ ሕዝቅያስን ለመገናኘት ያነሳሳውን ምክንያት የሚያብራራ ብርቱ አጋር አስፈልጎት ነበር። ፀሐይ በሕዝቅያስ ጥያቄ የምትንቀሳቀስ ከሆነ እንግዲህ በአሦር ላይ ምን ማድረግ ይሳነዋል?

ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ለማክበር እና ባቢሎናውያንን ወደ እርሱ ለማመላከት የተፈጠረለትን አስደናቂ ዕድል ያጣው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? ኢሳ. 39። ሕዝቅያስ ስለ ጌታ ሊመሰክርላቸው ሲገባ ወደ ገዛ “ክብሩ” አመላከታቸው። ከዚህ ምን እንማራለን?

የካቲት 5
Feb 12


ተጨማሪ ጥናት


“የወረደውን የፀሐይ ጥላ በአስር ደረጃ ወደ ኋላ መመለስ የሚቻለው በእግዚአብሔር ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው። ይህ እግዚአብሔር የሕዝቅያስን ጸሎት መስማቱን ለማሳየት የተሰጠው ምልክት ነበር። ነቢዩ ወደ ጌታ አለቀሰ፡ እርሱም በአካዝ የፀሐይ መቁጠሪያ ደረጃ ወርዶ የነበረውን ጥላ በአስር ደረጃ ወደ ኋላ መለስ’ ቁ. 8–11።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 342. “ከሩቅ አገር ገዢ የተላኩት የእነዚህ መልእክተኞች ጉብኝት፤ ሕዝቅያስ ሕያው አምላክን ከፍ ከፍ የሚያደርግበትን ዕድል ሰጥቶት ነበር። ሌሎቹ ሁሉ ተስፋዎች በሸሹት ጊዜ የራሱን ሕይወት በመታደግ ውለታ ላደረገለት የፍጥረታት ሁሉ ደጋፊ ስለሆነው ስለ እግዚአብሔር አምላክ ቢናገራቸው ለእርሱ ምንኛ ቀላል ነበር! . . .

“ነገር ግን ትዕቢት እና ከንቱነት የሕዝቅያስን ልብ ተረከበ። እናም ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እግዚአብሔር ህዝቡን ያበለጸገበትን ውድ ሀብት በምቀኝነት ለተሞሉ ዐይኖች ለማሳየት ከፈተ። ንጉሡም ‘በግምጃ ቤቱ ውስጥ ያለውን ብሩን፣ ወርቁን፣ ቅመማ ቅመሙን፣ ምርጡን ዘይት እንዲሁም የጦር መሣሪያውን በሙሉ፣ ያለውንም ንብረት አንዳች ሳያስቀር አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በግዛቱ ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው ነገር አልነበረም።’ (ኢሳ. 39፡2)። ይህን ያደረገው እግዚአብሔርን ለማክበር ሳይሆን በባዕዳን መሳፍንት ፊት ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ነበር። ”- ገጽ 344-345።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሰይጣን ከአሦር የጦር አዛዠ የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ኃጢአት ሠርተዋል ብሎ እርስዎን ሲከስ የሚናገረው እውነት ነው (ዘካ. 3፡1)? እግዚአብሔር ምን ምላሽ ይሰጣል? ዘካ. 3፡2-5። በእነዚህ ክሶች ላይ ብቸኛ ተስፋችን ምንድን ነው? ሮሜ. 8፡1

2.ይቅር ከተባሉ በኋላ ሰይጣን ክሱን ያቆማል? ራእ. 12፡10። ይቅር ከተባሉም በኋላ፤ በኃጢአትዎ ምክንያት የእርሱ እንደሆኑ አድርጎ ክስ ሲያቀርብብዎ፤ የክሱ ተፈጥሮ ምንድን ነው? ዘዳ. 19፡16-21።

ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር ለታማኙ ንጉሥ ጩኸት ምላሽ በመስጠት ህዝቡን አዳነ፤ ማን እንደሆነም አሳየ። የምድርን መጨረሻ የሚቆጣጠር የእስራኤል ኃያል ንጉሥ፤ ሕዝቦቹን ለማጥፋት የሚሞክሩትን የሚያጠፋ ብቻ ሳይሆን የቱንም ያህል “ባቢሎናውያን” ቢሆኑም እንኳን--ሌሎችም ሕዝቦቹ ይሆኑ ዘንድ ዕድል ይሰጣል።