የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከታህሳስ 3 – 9

12ኛ ትምህርት

Dec 12 - Dec 18




ሰንበት፡ ፈጣሪ አምላክን የምንለማመድበት እና ፈቃዱን የምንኖርበት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ 1, 2; ዘጸ. 16:14–29; ኢሳ. 58:1–14; ማቴ. 12:1–13; ሉቃ 13:10–17.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“ደግሞም እንዲህ አላቸው ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው” (ማር. 2፡27)

ጁ ዲ ከሁለተኛ ዲግሪ መርኀ ግብር ተማሪዎች መሃል ብቸኛዋ አድቬንቲስት ናት። በሰንበት ዕለት በሚደረጉ አንዳንድ ማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ ላለመገኘት መምረጧ እምነቷ ጎልቶ እንዲታይ መንስኤ ሆኖአል።

አንድ ቀን ከጓደኞቿ አንዷ የሆነችው ጌይል ወደ ቤቷ ጠራቻት። ጌይል ባለቤቷ ለቀጣዮቹ ስድስት ሣምንታት በሥራ ምክንያት ስለማይኖር ቀጣዮቹን ስድስት አርብ ምሽቶች ከእርሷ ጋር እንድትሆን እንደምትፈልግ ነገረቻት። ምክንያቱም ጁዲ በእነዚህ ጊዜያቶች ምንም ነገር እንደማታደርግ ጌይል ታውቅ ነበር።

ለቀጣዮቹ አራት አርብ ምሽቶች አብረው ይበሉ፣ ሙዚቃ ያዳምጡ እንዲሁም የክርስትና ተሞክሮአቸውን ይጋሩ ነበር--ብቻ በአጠቃላይ በአብሮነት ጊዜያቸው ደስተኞች ነበሩ። አምስተኛው ሣምንት መጨረሻ ላይ ጌይል አንዳንድ ነገሮች እየገዛች መሆኑን ለጁዲ ነገረቻትና ሰዓቷን ተመለከተች። ውይ አምላኬ! ሰንበት ተቃርቦአል ብላ አሰበች። ባለፉት አራት አርብ ምሽቶች በክርስትና ተሞክሮዋ አንድ አዲስ ነገር እንደ ተለማመደች በድንገት ተገነዘበች። በእምነቷ በማደጓና ስለ አምላኳ ተጨማሪ ነገሮችን በመማሯ እምነቷ ላይ መተማመን አግኝታለች። ሰንበት ለትምህርት እና ለግል ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ሰንበትን እንደ እረፍት ቀን ብቻ ሳይሆን እንደ ትምህርት መቅሰሚያ ዕለት አድርገን እንዴት ማሰብ እንዳለብን የሚያስታውሰን ይህ ታሪክ በእርግጥም መሳጭ ነው።

ታህሳስ 4
Dec 13

የሚገረሙበት እና የሚደነቁበት ጊዜ


በዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ እግዚአብሔር ሁለት ተጓዳኝ የፍጥረት ታሪኮችን ሊሰጠን ለምን እንደ መረጠ አስበው ያውቃሉ? ምድር ቅርጽ ስለመያዟ እና በመቀጠል በአስደናቂ ለውጥ ሕይወት ማፍራቷ፤ በመጨረሻም በስድስተኛው ቀን ወንድ እና ሴት ሆነው በተፈጠሩ ሰዎች የፍጥረት ሥራ መደምደሙን አስመልክቶ ዘፍ. ምዕ. 1 ስለ ፍጥረት ሣምንት በዝርዝር ይነግረናል። ዘፍ. ምዕ. 2 ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ምልከታ ቢያደርግም፤ ይህ የሚስተናገደው ከተለየ አተያይ ነው--በሰባተኛው ቀን ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ። አሁን አዳም የትዕይንቱ ማዕከላዊ ክፍል እንደ መሆኑ ማንኛውም ነገር ለእርሱ እና ለሴቲቱ በዚያ ህልውና እንዳገኙ ተገልጾአል--አትክልቱ፣ ወንዞቹ፣ እንስሳቱ፣ ሴቲቱም ጭምር።

ፍጥረትን እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ በአንድ ቃል መግለጽ አይቻልም። በመጀመሪያ ፍጹም የሆነውን ውበት በጥልቅ የሚያዩ ዐይኖች ስላሉት ኃያል እና ጥበበኛ አምላክ እንማራለን። በመቀጠል ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩና አንዳቸው ለሌላቸው እንዲጠነቀቁ፤ ተመሳሳዩን ለሌሎች ፍጥረቶች እንዲያደርጉ ከሚፈልገውን የግንኙነት አምላክ ጋር እንገናኛለን።

ጥቅሶቹን፡ ዘፍ. 1 እና 2 ካነበቡ በኋላ የመጀመሪያው ሰንበት ቀን (ዘፍ፣. 2፡1-3) እንዴት ከመጀመሪያው የፍጥረት ታሪክ ጋር እንደሚተሳሰር ለማሰብ ይሞክሩ። እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን መባረኩ እና የተቀደሰ ማድረጉ ምን ማለት እንደሆነ እንዲያስተውሉ የሰጡት መደምደሚያ እንዴት ሊረዳዎ ይችላል?



በዚያ የመጀመሪያ ሰንበት ቀን ራስዎን እንደ አዳም ወይም ሔዋን አድርገው ይሳሉ። ከተፈጠሩ የመጀመሪያዎ ቀን፣ ከባለቤትዎ ጋር የመጀመሪያዎ ቀን እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የመጀመሪያዎ ቀን። እንዴት ያለ የትምህርት ቀን ነው! እንዲህ ያለውን እጹብ ድንቅ ውበት ከፈጠረው አምላክ መማር ጀምረዋል። በአንድ ወቅት ባዩት ዝሆን ተደንቀው ሳያባሩ ወዲያው ደግሞ እንቁራሪት ይመከታሉ--ሁሉም ልዩ እና ድንቅ። የሚቦርቅ ቀጭኔ ወይም ጎሽ ይመለከቱና ፈገግ ይላሉ። በሚመለቷቸው መጠነ ሰፊ ህብረ ቀለማትና ቅርጾች እንዲሁም በሚሰሟቸው ውብ ለዛና ቃና ያላቸው ሙዚቃዊ ድምጸቶች--ብቻ ምኑ ቅጡ፤ እንደው በጸጥታና በአድናቆት ይደመማሉ። የሚቀምሷቸውም ሆነ የሚያሸቷቸው ነገሮች የሚሰጦትን ልዩ የደስታና ፍስሐ ስሜት መገንዘብ ጀምረዋል። ሆኖም ከሁሉም በላይ ግን ስለ ግንኙነቶች፣ ኃላፊነት፣ ጥንቃቄና እንክብካቤ መማር ይጀምራሉ። እነዚህን ነገሮች ከፈጣሪዎ ከቀሰሙ በኋላ፤ ከተቀሩት ፍጥረታት ጋር መለማመድ ይጀምራሉ።

የመጀመሪያው ሰንበት በአዳምና ሔዋን ላይ የተለየ ፍላጎት የማያጭር ተሞክሮ እንዳልነበር ይገመታል። ትኩረታቸውን በፈጣሪያቸው እና በፍጥረት ሥራው ላይ እንዲያደርጉ የሚያስችል በእግዚአብሔር የተፈጠረላቸው ዕድል ነበር። ጊዜው አብልጠው የሚገረሙበትና የሚደነቁበት ነበር።

አዳምና ሔዋን በዚያ የመጀመሪያ ሰንበት ያገኟቸውን የተለያዩ ትምህርት ሰጭ ዕድሎች በዝርዝር ለማስቀመጥ ይሞክሩ። ለየት ባለ መልኩ ቢሆንም፤ ከእነዚህ ዕድሎች መሃል ዛሬም ሥራ ላይ መዋል የሚችሉት የትኞቹ ናቸው? የሰንበት ቀንዎን እንዴት ማበልጸግ ይችላሉ?

ታህሳስ 5
Dec 14

የተረሳው እንደገና የተገኘበት ጊዜ


ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲያወጣ በተጠየቀ ጊዜ አብዛኛው ሕዝብ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑን ግንዛቤም ሆነ አመለካከት ማጣቱ ግልጽ ነበር። አስደናቂ የወደፊት ተስፋ የሰጣቸውና ኪዳን የገባላቸው፣ አምልኮአቸውን የሚፈልግ ይህ አምላክ ማን እንደሆነ ዳግም ሊደርሱበት የግድ ነበር። በዚህ የግንዛቤ ጉዞአቸው ሰንበት ቁልፍ የመማሪያ ተሞክሮ መሆኑ እሙን ነው። እንዲሁም ከእግዚአብሔርና ከሕዝቡ ጋር የተለየ ግንኙነት ለነበራቸውም ሕዝቦች ግልጽ ምልክት መሆን ይችላል። የመናው ተሞክሮ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ያስተማረበትን መንገድ ያሳያል። በዘፀ. 16፡14-29 እስራኤላውያን ሊማሯቸው የሚገቡ ምን ዓይነት ትምህርቶች ቀርበዋል?



እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በተዓምር ከሰማይ መና እያወረደ ለየዕለቱ የሚሆን በቂ ምግብ ይሰጣቸው ነበር። ይሰበስቡ ከነበረው መጠን በላይ ሰጥቶአቸው ቢሆን ኖሮ የሚያሻቸውን እያሟላ የነበረውን አምላክ በዘነጉት ነበር። ስለዚህ በየቀኑ ተዓምራት ያደርግላቸው ስለነበር የእግዚአብሔርን ጥንቃቄ መመልከት ቻሉ። ሆኖም የመናው ተዓምራት ጉዳይ በሰንበት ዕለት የተለየ ነበር። ሁለት ተዓምራቶች ይፈጸሙ ነበር፡ አርብ ዕለት የሚወርደው መና እጥፍ መሆን እና ምግቡ በማደሩ ሳይበላሽ መቅረቱ። ይህ ሁኔታ አዳኛቸው የሆነውን ይህን አምላክ እንዲያደንቁና የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ዳግም እንዲያስተውሉ ረድቶአቸዋል።

እስራኤላውያን ይህን መና ለ40 ዓመት በሉ (ዘፀ. 16፡35)። እግዚአብሔር እንዴት እስራኤላውያንን በምድረ በዳ እንደ መራቸው ያስታውሱ ዘንድ ሙሴ አንድ ጎመር መና ወስዶ ለመታሰቢያ እንዲያቆም እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር (ዘፀ. 16፡ 32-33)። መታሰቢያው የሰንበትን ቀን አስመልክቶ የነበራቸውን ተሞክሮም እንዲሁ የሚያስታውሳቸው ነበር።

ሰንበት እስራኤላውያን የረሱትን ማንነታቸውን እና አምላካቸውን ዳግም እንዲያገኙ እግዚአብሔር እነርሱን የረዳበት አንዱ መንገድ ነበር። እንዲታዘዙና ሰንበትን ቅዱስ አድርገው እንዲጠብቁ ተጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የፈጣሪያቸውን ባህሪ በጥልቅ ከማስተዋል እና ከእርሱ ጋር ዘላቂ ኪዳን ከመገንባት ዐውድ ነበር።

ሰንበት “አሰልቺ” ከሆነበት በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ከሚገኝ ታዳጊ ወጣት ጋር እየተነጋገሩ ነው። ሰንበትን የሚጠብቀው መጽሐፍ ቅዱስ እና ወላጆቹ ያን ማድረግ እንዳለበት ስለነገሩት ብቻ ነው። ሰንበትን በአዎንታዊ የመማር ተሞክሮ ዳግም ማግኘት ይችል ዘንድ ምን ዓይነት ሀሳቦች ሊያካፍሉት ይችላሉ?

፡ ታህሳስ 6
Dec 15

አሳሳቢ ጉዳዮችን የምንማርበት ጊዜ


እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ውጣ ውረድ የበዛው ተሞክሮ ከሰንበት ጋር ከነበራቸው ሁኔታ ቁርኝት ነበረው። ሰንበትን ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆናቸው፤ እርሱ በህይወታቸው እንደማያስፈልጋቸው አምላክ የመውሰዳቸው ምልክት አድርጎ ተመልክቶት ነበር (ኤር. 17፡19-27)። ሰንበትን ለመጠበቅ የሚደረግ የታደሰ ቁርጠኝነት፤ ወደ ቀድሞው ንጽህና የመመለስ አካል ነበር--ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ትክክለኝነት የሚያሳይ ምልክት። ኢሳ. 58 አስገራሚ ንጽጽር ያቀርባል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 58፡1-14። እግዚአብሔር ለዚህ ዘመን ገጣሚ በሆነ መልእክቱ ለህዝቦቹ ምን እያለ ነው?



እስራኤላውያን በአምልኮአቸው እና በጾማቸው የእግዚአብሔር ተከታዮች ቢመስሉም ነገር ግን ከአምልኮ በኋላ ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ ለእግዚአብሔር ሕግ ከልብ የመነጨ ቁርጠኝነት አይታይበትም። እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚጠብቀውን እያመላከተ ኢሳ. ምዕ. 58 መልእክቱን ይቀጥላል።

ይህ ብቻ አይደለም። በተጨማሪ ኢሳ. 58፡13-14 ያንብቡ። እግዚአብሔር በጥቅሱ መጨረሻ ሰንበት ላይ ትኩረት ያደረገው ለምንድን ነው? እዚህ ላይ ነቢዩ ከተቀሩት ምዕራፎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ሀረጎች በመጠቀም ያስጠነቅቃል፡ “የልብህን ባታደርግ”፣ “በገዛ መንገድህ ከመሄድ…ብትቆጠብ”፣ “እንደ ፈቃድህ ከማድረግና ከከንቱ ንግግር ብትቆጠብ።” በሌላ አነጋገር ሰንበት በአምልኮ ወቅት ከሚኖረን ሁናቴ ተቃራኒ ህይወት የምንመራበት፣ የግል ጉዳዮቻችንን የምናሰላስልበት እና የልምድ አምልኮ ለማድረግ የምንመላለስበት ጊዜ አይደለም። ሰንበት “ደስታ” የሞላበት እና “የተከበረ” ቀን ሊሆን ይገባል። ሰንበት አምላካዊውን ባህሪ እና ዓላማ በመማራችን ደስ የምንሰኝበት እና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እነዚህን ባህሪዎችና ዓላማዎች በህይወታችን የምናሳይበት--ሆኖ በተቀረው የምዕራፉ ዐውድ ቀርቦአል። ሰንበትን እንዴት ማክበርና በዕለቱ አምልኮ ማድረግ እንደሚገባ ማወቅ ብቻውን በቂ አይደለም። ትምህርት በህይወት ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይገባል።

በሰንበት ደስ ይሎታል? ካልሆነ--ያንን ለመለወጥ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሰንበትን ስለ “ማክበር” ተምረዋል? ይህ ምን ማለት እንደሆነ ከተቀሩት የክፍል ተማሪዎች ጋር ተወያዩ።

ታህሳስ 7
Dec 16

ሚዛናዊ የሆነው ነገር የሚገኝበት ጊዜ


የሱስ አምላካዊውን ሕግ ያከብርና ይጠብቅ ነበር (ማቴ. 5፡17-18)። የሕጉን አተረጓጎም ተከትሎ የሱስ የኃይማኖት መሪዎችን ተጋጥሞአል። ሰንበትን ለመጠበቅ ከመምረጥ ውጪ አንደኛውም ትምህርቱ በዚህ ሕግ ላይ ተግዳሮት አልነበረውም። በሰንበት በየምኩራቡ ቶራ ተነብቦ ሲያበቃ ትርጉም ይቀርብ ነበር። ምኩራቦች በየሰንበቱ ይህን ዕድል ለሕዝቡ ከመስጠት ታቅበው አያውቁም። ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን የሕጉን ፊደል ቢያውቁም ነገር ግን የሱስ ተከታዮቹን አብልጦ በእርሱ ሰንበት ቀን ያስተምራቸው ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 12፡1-13፣ ሉቃ. 13፡10-17። የሱስ በእርሱ ዘመን ለነበሩ ሕዝቦች የሚያስተምረው ምን ነበር? ዛሬ እኛንስ?



የሱስ በሰንበት መፈወሱን ተከትሎ የተነሱ ውዝግቦች--ስለ ኃጢአት ተፈጥሮ፣ ሰንበት ስለ ተሰጠበት ምክንያት፣ በየሱስ እና በአባቱ መካከል ስላለው ግንኙነት እንዲሁም ስለ የሱስ ሥልጣን ተፈጥሮ--አስፈላጊ ነጥቦች የተዳሰሱበት መንፈሳዊ ሙግቶች እንዲደረጉ መንስኤ ሆኖ ነበር።

የሱስ ስለ ሰንበት ያለው አመለካከት በሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ አጠር ብሎ ቀርቦአል፡ “ደግሞም እንዲህ አላቸው ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም። ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው” (ማር. 2፡27)። ሰንበት እንደ ሸክም ሊታይ እንደማይገባ አጽንኦት ሊሰጥ ፈልጎአል። ሰንበት የተፈጠረው ሰዎች ለፍጥረቱ ዋጋ የሚሰጡበት ተሞክሮ ውስጥ እያለፉ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ የሚማሩበት ልዩ ዕድል እንዲያገኙ ነው።

የሱስ የፈጸመው የፈውስ ድርጊት ጥያቄ እንዲያስነሣ በማድረግ--ደቀ መዛሙርቱ፣ የአይሁድ መሪዎች እንዲሁም የተሰበሰበው ሕዝብ ስለ አምላካዊው ቃል፣ ስለ እምነታቸው ብሎም ስለ እግዚአብሔር አምላክ በጥልቀት እንዲያስቡ ገፋፋቸው። ማናችንም ብንሆን በራሳቸው መጥፎ ሊሆኑ በማይችሉ ሕግጋትና ደንቦች በቀላሉ ልንተበተብ እንችላለን። ሆኖም ስለምናገለግለው አምላክ ዕውቀት ሲኖረን፤ ይህ ዕውቀት ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን ፍጻሜ ይዞ ይመጣል። ይህም ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው የጽድቅ ሥራ ላይ ታምነን እርሱን በታማኝነት ወደ መታዘዝ ይመራናል። የእርስዎ ሰንበት አጠባበቅ ምን ይመስላል? በጌታ የሚያርፉበትና እርሱን በተሻለ የሚያውቁበት እውነተኛ ጊዜ ከማድረግ ይልቅ ይህን አታድርግ፣ ያን አታድርግ ወደሚለው ለውጠውት ይሆን? እንዲያ ከሆነ፤ እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ካቀደልዎ የበለጠውን ማግኘት ይችሉ ዘንድ እንዴት መቀየር ይችላሉ የሚችሉት እንዴት ነው?

ታህሳስ 8
Dec 17

ማኅበረሰቡ በአንድነት የሚሰበሰብበት


የሱስ በሣምንታዊው የምኩራብ አገልግሎት በመገኘት ለደቀ መዛሙርቱ ምሳሌ ነበር። ከትንሣኤው በኋላ ሌሎች የየሱስ ተከታዮች እንዳደረጉ ሁሉ እነርሱም ይህንኑ አካሄድ ተከተሉ። ሰንበት ማኅበረሰቡ በአንድ ላይ እንዲሰባሰብና እንዲማር ቁልፍ አጋጣሚ ከመሆኑ አኳያ ሐዋርያት ከትንሣኤው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ማንሣት ይችሉ ዘንድ ምኩራቡ ዋንኛ ከነበሩ መሰብሰቢያ ስፍራዎች አንዱ ሆነላቸው። ደግሞስ የሱስ በየሰንበቱ በምኩራብ የሚነበበውና በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ የተተነበየው ዕብራዊ መሲህ አይደል? ታዲያ አማኞች የሱስን ከፍ ከፍ ለማድረግ ከምኩራቡ የተሻለ ምን ዓይነት ቦታ ሊያገኙ ይችላሉ? በተለይ ለአይሁድና ለሌሎች “እግዚአብሔርን ለሚፈሩ” (ሐዋ. 13፡16፣26) ሲመሰክሩ?

የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ። የየሱስ ተከታዮች በየዐደባባዩ እንዴት እንደ መሰከሩ ምን ይነግሩናል? እነዚህን ጥቅሶች ሲያነቡ፡ የት ሆነው ይናገሩ እንደ ነበር፣ ለማን ይናገሩ እንደነበር፣ ምን እንደተባለና ውጤቱ ምን እንደ ሆነ ያስቡ። ሐዋ. 13:14–45፣ ሐዋ. 16:13-14፣ ሐዋ. 17:1–5፣ ሐዋ. 18:4።



የሐዋርያት ምስክርነት ግላዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነበር። “አባቶቻችን” (ሐዋ. 13፡17) በሚል ቃል የሚጀምረው ጳውሎስ ከግብፅ አንስቶ የእስራኤልን ታሪክ እያብራራ፣ የመሳፍንቱንና የነገሥታቱን ዘመን ጠቅሶ ዳዊት ላይ ሲደርስ ፍጹም በሆነ ሽግግር ወደ የሱስ ያመራል።

ጳውሎስ እና ሌሎች ሐዋርያት የግል ተሞክሮአቸውና መረዳታቸው ከአምላካዊው ቃል ዐውድ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ጭምር አሳይተዋል። መረጃ ያቀርቡ፣ ይመረምሩና ይወያዩ ነበር። በስብከት፣ በማስተማር እና በውይይት ይቀርብ የነበረው የግል ምስክርነትና የቅዱሳት መጻሕፍት ጥምረት በጣም ኃይለኛ ነበር። አንዳንድ የኃይማኖት መሪዎች ሐዋርያት በነበራቸው ሥልጣንና ይህን ተከትሎ በአይሁድ እና አይሁድ ባልሆኑ ሕዝቦች ባፈሩት ተሰሚነት ይመቀኙአቸው እንደ ነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያሳዩናል።

ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ በስብከትም ሆነ በማስተማር (በማካፈል) ትንቢትን እና መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ታበረታታለች። የሰንበት ትምህርት ጥናት እና የዋናው አገልግሎት (ስብከት) እንዲሁም የወጣቶች መርኀ ግብር ጥምረት ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አምልኮ ጠንካራ መደበኛ ትምህርታዊ መሰረት ይሰጣል። ምንም እንኳ ይህ በሌሎች የመማሪያ ተሞክሮዎች መጎልበት ቢያስፈልገውም፤ ለሰንበት ትምህርት ተሞክሮ መሰረታዊና አስፈላጊ ነው።

ታህሳስ 9
Dec 18


ተጨማሪ ሀሳብ


የዘመና ምኞት መጽሐፍ፡ “ሰንበት” በሚል የቀረበውን ምዕራፍ ከገጽ 276- 285 ያንብቡ።

“ለአይሁዶች ከተሰጡት መመሪያዎች ሁሉ እንደ ሰንበት በአካባቢያቸው ከነበሩት ሕዝቦች የተለየ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የለም። የእግዚአብሔር እቅድ ሰንበትን በማክበር አይሁዶች እርሱን አምላኪ መሆናቸው እንዲታወቅ ነበር። ዕቅዱ ሰንበት የእስራኤል ልጆች ከጣዖት አምልኮ ተላቅቀው ከእውነተኛው አምላክ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ምልክት እንዲሆን ነበር። ነገር ግን ሰንበትን በቅድስና ለማክበር ሰዎች የተቀደሱ መሆን አለባቸው። በኃይማኖት የክርስቶስ ጽድቅ ተካፋይ መሆን አለባቸው። “የሰንበትን ቀን አስብ ትቀድሰው ዘንድ” የሚለው ትእዛዝ ለእሥራኤላውያን በተሰጠ ጊዜ አምላክ በተጨማሪ “ቅዱስ ወገን ትሆኑኛላችሁ” አላቸው (ዘፀ. 20፡8፣ 22፡31)። በዚህ ሁኔታ ብቻ ነበር ሰንበት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አምላኪ መሆናቸውን ለይቶ የሚያሳውቃቸው” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 278-279።)

“ስለዚህ ሰንበት እኛን ለመቀደስ የሚቻለው የክርስቶስ ኃይል ምልክት ነው… ሰንበት የክርስቶስ የመቀደሱ ኃይል ምልክት እንደ መሆኑ መጠን በክርስቶስ አማካይነት የእግዚአብሔር የእስራኤላውያን ወገን ለሚሆኑ ሁሉ ተሰጥቶአል” (የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 285)


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ብዙውን ጊዜ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች በሰንበት ያልተፈቀደውን ነገር ምን እንደሆነ በማሰላሰል ጊዜ ያጠፋሉ። ሰንበት ጠባቂዎች በዚህ ትምህርት ውስጥ በተብራሩት እሳቤዎች ላይ እንዲያተኩሩ እና ሰንበትን እንደ ትምህርታዊ ልምምድ እንዲወስዱ የሚያደርጉ ጥያቄዎች ያዘጋጁ። ለምሳሌ “ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ይበልጥ እማር ዘንድ በሰንበት ምን ማድረግ እችላለሁ?”

2.ከላይ በኤለን ኋይት የቀረቡትን ሀሳቦች ልብ ይበሉ። ሰንበት ጠባቂዎች በማኅበረሰቡ ተለይተው እንዲታዩ የሚያደርጋቸው ሰንበትን የመጠበቃቸው ልምድ አይደለም። “የክርስቶስ ጽድቅ ተካፋዮች” እና “ቅዱሳን” ምን ዓይነት ስብዕና አላቸው? የሚለው ነው። ይህ ከሰንበት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት አለው?

3.የሰንበት ልምዳችሁን በየትኞቹ መንገዶች ማበልጸግ ትችላላችሁ? በቀጣዮቹ 12 ወራት በሰንበት ሊያተኩሩባቸው የሚፈልጓቸውን ሦስት ግቦች ይለዩ።