ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው
በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል
ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው
ቢሮ ነው፡፡ መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ
ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት
ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው፡፡ የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ
የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ
ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም፡፡
በተለየ ካልተጠቀሰ በቀር በዚህ ሰንበት ትምህርት ጥቅም ላይ የዋሉት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ የተወሰዱት ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
አዘጋጅ፡ ጆናታን ዱፊ
ዘላለም አስረስ እንደተረጎመው
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች “የዘላለም ወንጌል” (ራእ. 14፡6) የሆነውን
የምሥራች ቃል ለዓለም ሁሉ እንድንሰብክ ተጠርተናል። ይህን በማድረግ የሱስ ደቀ
መዛሙርትን ስለ ማፍራትና ስለ ማጥመቅ የተናገረውን ቃል መታዘዛችንን እናሳያለን
“ ‘ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ
ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ” (ማቴ. 28:20)። የተጎዱን፣ የተጨቆኑን፣ ድኾችን፣
የተራቡንና፣ የታሰሩን ማገልገል ጌታ እንድናደርግ ካዘዘን መሃል ይወሳሉ።
ለነገሩ የሱስ የደጉን ሳምራዊ ተምሳሌታዊ ታሪክ (ሉቃ. 10፡30-36) ከተናገረ በኋላ
“ ‘አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ’ ” (ሉቃ. 10:37) አልነበር ያለው? ደግሞም “እረኛ
በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ፣ ሕዝቡን አንዱን ከሌላው ይለያል” (ማቴ. 25፡32)
ብሎ የወደፊቱን ያሳየው የሱስ ራሱ--የተራቡትን፣ የታመሙትን፣ የታረዙትንና
የታሰሩትን መርዳት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሮአል። “ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ
አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ”
(ማቴ. 25፡40)።
በሌላ አነጋገር ስለ ደኅንነት ታላላቅ እውነቶች ማለትም--ስለ ቤተ መቅደሱ፣
ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እና ስለ ሕጉ ዘላለማዊነት በይፋ ከማወጅ ጎን ለጎን
ሌሎችን በሚያስፈልጓቸው ሁሉ ልናገለግል የተገባ ነው። ወደ ሰዎች ለመድረስ፤
ስለ ሰዎች ከመሥራት የላቀ ምን የተሻለ መንገድ አለ? “የሱስ የተጠቀመበትን ዘዴ
መተግበር ብቻውን ወደ ሰዎች ለመድረስ የሚያስችል እውነተኛ ስኬት ያጎናጽፋል።
አዳኙ ለሰብዓዊው ፍጡር በጎ መመኘቱን በሚገልጥ ሁናቴ ከሰዎች ተቀላቀለ።
ለእነርሱ ያለውን ርኅራኄ ካሳያቸውና በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ካገለገላቸው በኋላ
መተማመናውን አገኘ። በመጨረሻም ‘ተከተሉኝ’ ሲል ጥሪ አቀረበላቸው”—The
Ministry of Healing, p. 143.
እግዚአብሔር ለድኾችና ለተጨቆኑ ያለውን የተለየ መቆርቆር የሚገልጹ 2,103
ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገኙ አንድ አኃዝ ያመለክታል። ስለ ተለያዩ
የእምነት መገለጫዎች፣ ስለ ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎችና በአጠቃላይ ስለ ክርስትና
አኗኗር ዘይቤ ከቀረቡ ማጣቀሻዎች ይልቅ በእጦት የሚገኙ ወገኖችን ስለ ማገልገል
የተሰጠው መልእክት በእጅጉ ይገዝፋል። በዙሪያችን ያለውን ህመምና ሥቃይ
ለማስታገስ የተለየ ትኩረት ሰጥተን ልንቀሳቀስ ይገባል። ይህን ማድረጋችን በወንጌል
ሥራችን ላይ እክል አይፈጥርም። እንደውም በተቃራኒው ወንጌልን በብርቱ ኃይል
ለማሰራጨት ያስችለናል።
እርግጥ ነው ስለ ሌሎች በጎ በማሰብ እነርሱን ለመርዳት መንሳቀስ መልካም
ነገር ነው። “ፍትሕን” ማድረግ (ሚክ.6፡8) ትክክልና መልካም በመሆኑ ብቻ
እናደርገዋለን። ፍትሕ እያደረግን፣ ሌሎች ለገጠሟቸው አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹና
ጊዜያዊ እጦቶች እርዳታ እያደረግን “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን” (1ጴጥ. 3፡
15) ይኸውም ወደ ክርስቶስ ዘላለማዊ ህይወት ተስፋ ማመላከት የተሻለ አይሆንም?
የሱስ ደዌን ፈወሰ፣ ዐይነ ሥውሩን አበራ፣ ለምጻሙን አነጻ ከዚያም አልፎ የሞተውን
አስነሳ። ሆኖም እነዚህ ታምራት ያደረገላቸው ወገኖች በሙሉ በጎልማሳነታቸው
ወይም በእርጅና ዘመናቸው ሞተው የለ? የሱስም ለአፋጣኙም ሆነ ለዘላቂው
ችግራቸው የቱንም ያህል ቢያገለግላቸውም--ከዚያ የላቀውን ግን አድርጎአል።
እርግጥ ነው በጉዳት ይገኙ የነበሩ ወገኖችን ካገለገለ በኋላ ተከተሉኝ ይላቸው ነበር።
በተመሳሳይ እኛም በጉስቁልና የሚኙ ወንድም እህቶችን እያገለገልን ተከተሉት
የምንልበት ትክክለኛ ምክንያት ይኸው ነው።
በዚህ ዓለም ላይ ፍትሕና ርኅራኄ እንዲሰፍን ካለን መሻት አኳያ አምላካዊውን
መንግሥት (ሉቃ. 4፡18-19) እየተለማመድን መሆናችን አያጠያይቅም። ቢያንስ
ታማኝ በመሆንና የቀናውን አካሄድ በመከተል እየሰበክነው እንገኛለን። ድኾችንና
የተጨቆኑትን ስንንከባከብ እግዚአብሔርን እያከበርንና እርሱን እያመለክን መሆኑ
እሙን ነው (ኢሳ. 58፡6-10)። ነገር ግን የተጎዱትን፣ በሥቃይ ያሉትንና ልባቸው
የተሰበረውን ከማገልገል ስንሰናከል እርሱን በተሳሳተ መንገድ እንወክላለን (ምሳ. 14፡
31)።
በዙሪያችን የሚገኙትን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖች ለማገልገል ስላለብን ኃላፊነት
የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል በዚህ ሩብ ዓመት የሰንበት ትምህርት ጥናታችን
እንመለከታለን።
“‘በነፃ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ’” (ማቴ. 10፡8)።
የዚህን ሩብ ዓመት የሰንበት ትምህርት ጥናት ያዘጋጁልን ጆናታን ዱፊ
ከጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ከ2012 ዓ.ም. አንስቶ የአለማቀፉ አድቬንቲስት ልማትና
ተራድኦ ተቋም (ADRA) ፕሬዚደንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ተቋሙን በ2008
አውስትራሊያ ላይ ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ ሰፊ ተሞክሮ ባካበቱበት በጤና
ማጎልበቻና ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና አጠባበቅ እድገት ዘርፍ በደቡብ ፓሲፊክ
ዲቪዥን የአድቬንቲስት ጤና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
3ኛ ሩብ ዓመት
ከሰኔ 22 2011 እስከ ከመስከረም 16 2012 ዓ.ም.