ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1–3፣ ሐዋ. 17:28፣ መዝ. 148፣ መዝ. 24:1፣ ዘፍ. 4:1–9፣ ማቴ. 22:37–39፣ ራእ. 14:7።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “ድኾችን የሚያስጨንቅ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤ ለተቸገሩ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል” (ምሳ. 14፡31)።
ብ
ዙ ተጨንቀውና ተጠብበው ከእንጨት ወይም ከብረት አንድ የሆነ የሥነ
ጥበብ ወይም የዕደ ጥበብ የፈጠራ ሥራ ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ለአንድ ሰው
ሲያበረክቱ--ግለሰቡ ሰባብሮት ወይም የትም ጥሎት ተመልክተው ያውቃሉ? እንዲያ
ከሆነ--ይህን ዓለም ፈጥሮ ለሰብዓዊ ፍጡራን የሰጠው አምላክ በኃጢአት ስብራት
ሲያደርሱበት የተሰማውን ስሜት በጭላንጭልም ቢሆን ይረዳሉ እንደ ማለት ነው።
ይህች ዓለም በብዙ ጥንቃቄ መፈጠሯንና እያንዳንዱ የፍጥረት ሥራ “መልካም”
እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እግዚአብሔር ስለ ፍጥረቱ የተሰማውን ስሜት
አስመልክቶ ዘፍ. 1 እና 2 ጉልህ ምልከታ ይሰጠናል። እግዚአብሔር ከፈጠራቸው
ሰዎች ጋር በገጠመው ፍጥጫ፤ የሰውን ውድቀትና የአምላካዊውን ልብ ስብራት
ታሪክ ከዘፍ. 3 አንስቶ ከቀረበው ምንባብ ዐውድ እናገኛለን።
ምንም እንኳ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የዘለቀ ኃጢአት፣ ብጥብጥ፣
ኢፍትሐዊነትና ዐመጻ በምድር ላይ ቢሰፍንም፤ እግዚአብሔር ግን በሚያስደንቅ
መልኩ ይህችን ዓለም ከመውደድ ወደ ኋላ አላለም። ይበልጥ የሚያስደንቀው ደግሞ
ይህችን ዓለም ለመዋጀትና ዳግም ለመፍጠር የሚያስችለውን ዕቅድ ሲያወጣ፤ እንደ
አማኝ ግዙፎቹ ዕቅዶች ይሰምሩ ዘንድ የምንጫወተውን ሚና ሰጥቶናል። የእርሱ
ጸጋ ተቀባዮች መሆናችን እርግጥ እንደመሆኑ፤ በዚህ በተቀበልነው ጸጋ ከጌታ ጋር
ተባባሪዎች ሆነን የምንሠራው ሥራ ተሰጥቶናል።
ይህ ዓለምና በውስጡ የያዘው ህይወት፣ የገዛ ህይወታችንና በህይወታችን
የምናደርገው ነገር፣ በዙሪያችን ያለ የእያንዳንዱ ሰው ህይወትና ከሰዎች ጋር
የምንፈጥረው መስተጋብር፣ ራሷ ህይወትና ምርጥ ህይወት ልንኖር የምንችልበት
መንገድ--ሁሉ ጅማሬ እግዚአብሔር ነው “‘የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣
ያለነውም በእርሱ ነውና” (ሐዋ. 17፡28)።
የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አፈጣጠር ታሪክ በዘፍ. 1፡26-31 ይመልከቱ። ታሪኩ ስለ
እግዚአብሔር አምላክ ምን ዓይነት ጠቃሚ ማብራሪያዎችን ይዞአል? የሰዎችን ታሪክ
አስመልክቶስ ምን ዓይነት አስፈላጊ ነገሮችን ይነግረናል?
በተፈጥሮ ውስጥ በቂ ጊዜ በማሳለፍ፣ ወደ ፍጥረቱ በማማተርና በፍጥረቱ
ውስጥ የአምላካዊውን ባህሪ በጨረፍታ በመመልከት ስለ እግዚአብሔር ብዙ
መማር እንደምንችል በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። ደግሞም እኛ ራሳችን
እግዚአብሔርን ያስተዋልንበትን መንገድ በመመርመር እርሱ ዓለምን እንዴት
እንደ ፈጠረ በውልብታም ቢሆን መመልከት እንችላለን። ለምሳሌ እግዚአብሔር
የሥርዓት አምላክ ከሆነ፤ በፍጥረቱ ውስጥ ሕግና ሥርዓት እንደምናገኝ መጠበቅ
ይኖርብናል። ወይም እግዚአብሔር የፈጠራ ሥራ አምላክ እንደሆነ የምናምን ከሆነ
እርሱ በፈጠረው ዓለም ውስጥ አስደናቂ የፈጠራ ሥራዎችን በማግኘታችን ልንደነቅ
አይገባም።
በተመሳሳይ እግዚአብሔር የግንኙነት አምላክ እንደሆነ እናምናለን። አንዱ ከሌላው
ጋር ያለው ግንኙነት እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን በአንድ ያስተሳሰረበት ቁልፍ
መሣሪያ ሆኖ እናገኘዋለን። እርሱ እያንዳንዱ የዚህ ዓለም ፍጥረት ከተቀረው ጋር
ግንኙነት እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮአል። እንስሳትን የዝምድና ኅብር እንዲኖራቸው
አድርጎ ፈጥሮአል። ሰብዓዊ ፍጡሮችን ከራሱ ከፈጣሪ ጋር፣ እርስ በርሳቸው
እንዲሁም ከተቀሩት ፍጥረታት ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጠረ።
ስለ እግዚአብሔር ያለን እሳቤ በብዙ መልኩ ውሱንና የተገደበ ቢሆንም፤ ከእርሱ
ጸባይ መመልከት የምንችለው ነገር ዓለም እንዴት መሆን እንዳለባት ዳግም
እንድናጤን ሊገፋፋን ይገባል።
ምድር ግልጽ ሆኖ የሚታይ የኃጢአት ውድመት ቢደርስባትም፤ ይህች
ዓለም ዛሬም የአምላካዊው ባህሪ ነጸብራቅ መሆኗን እንዲያስተውሉ
እንዴት ትረዳዎታለች?
ማንም ቢሆን በጥንቱ የኤደን ትዝታ በቀላሉ ሊቆዝም ይችላል። እግዚአብሔር
ለአዳምና ሔዋን መኖሪያ አድርጎ በፈጠረላቸው የአትክልት ስፍራ በቀረቡ
መግለጫዎች ውስጥ በልባችን የናፍቆት ስሜት እንዲያጭር የሚያደርጉ ነገሮች አሉ።
ዓለም እንዴት እንደሚሠራ ለመረዳት ቢያዳግተንም እንኳ በተሞክሮው ውስጥ
ማለፍ እንዳለብን ግን ይሰማናል። ውስጣችን ሊኖር የሚችለው የእርካታ ስሜትና
ምሉዕነት “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ”
በሚል እርሱ የተሰማውን ስሜት የሚጋራ ይመስላል። እግዚአብሔር የሠራው ነገር
ውበትን ሊሠራ ከሚችል ብቃት ጋር በአንድ አጣምሮ የያዘ ነበር። በቅርጽም ሆነ
በግብር አስደናቂ ውበት የተላበሰ ንድፍ ነበር። በህይወትና ቀለማት የፈካ ብቻ ሳይሆን
ህይወት እንድታብብ የሚያስችለውን ማንኛውንም አስፈላጊ ግብዓት አሟልቶ የያዘ
ነበር። እግዚአብሔር በጥቂት ፋታ የመንፈስ መነሳሳት እንዲፈጠር እያደረገ መልካም
የሆነውን የዚህን ዓለም የፍጥረት ሥራ መሥራቱ ብዙም የሚደንቅ አይሆንም።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ እግዚአብሔርም “መልካም እንደሆነ አየ” በሚል በተደጋጋሚ
ስለ ቀረቡት መግለጫዎች ፍቺ ምን ያስባሉ? ዘፍ. 1:4፣ 10-12፣ 18፣ 25፣ 31።
ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሰው ሙሉ ለሙሉ በኃጢአት ከወደቀ
በኋላ ቢሆንም አምላካዊው ቃል እንደ ኢዮ. 38-41 እና መዝ. 148 ባሉ በፍጥረት
ሥራ ሐሴት በሚያደርጉ ምስጋናዎችና ውዳሴዎች የተሞላ ነው። እነዚህ ነገሮች
ምድር በመጀመሪያ እንደ ተፈጠረች ማለትም ኃጢአት ሳታውቅ ብቻ የነበረውን
ሁናቴ በጨረፍታ በመመልከት በኃላፊ ጊዜ አለመጻፋቸውን ማስታወስ የግድ
ይሆናል። ይልቁንም ዛሬም በዓለማችን በተጨባጭ በሚስተዋለው መልካምነት ላይ
ሐሴት እናደርግ ዘንድ በኃላፊ ሳይሆን በአሁን ጊዜ ተጽፈዋል።
ዙሪያችንን የከበቡንን ኢምንት የሚመስሉ አስገራሚ ነገሮች እያደነቅንና
በእግዚአብሔር እየተመካን ምስጋና እናቀርብለት ዘንድ የሱስ ከዓለም ስለሚጠብቀን
አምላካዊ ቸርነትና ጥንቃቄ በምሳሌ ነግሮናል (ማቴ. 6፡26፣ 28-30)። ዐይኖቻችንን
ከፍተን አስደናቂውን የፍጥረት ሥራ ብንመለከት፤ ከፈጣሪያችን የተበረከተልን
ገራሚ ስጦታ ተቀባዮች መሆናችንን በእውነት ማየት እንችላለን። በአስቸጋሪ ሁናቴ
ውስጥ ልንሆን ብንችል እንኳ ምላሻችን ለስጦታ ሰጪው ምስጋና ማቅረብና ራስን
በትህትና ማስገዛት ሊሆን ይገባል።
ይህ ዛሬ በጨረፍታ የምንመለከተውና የተሞክሮአችን አካል የሆነው የምድር
ውበት፣ ደስታና መልካምነት በአንድ ወቅት በሙላት የዓለም አካል እንደነበረ
ሁሉ፣ አንድ ቀን እንደገና ገቢራዊ እንደሚሆን በአምላካዊው የፍጥረት ሥራ ሐሴት
የምናደርግና ዳግም ምጽአቱን የምንጠባበቅ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ልንገነዘብ
ይገባል።
ከተፈጥሮ ጋር ካሎት ቁርኝትና ተሞክሮ አኳያ በተለይ ስለ
አስገራሚው የፍጥረት ሥራ የትኛውን ያደንቃሉ? በዕለት ከዕለት
ህይወትዎ በአስገራሚው ተፈጥሮ አማካኝነት ጌታን በተሻለ ማወቅ
የሚችሉት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የኤደን አትክልት ስፍራ እና አዲስ የተፈጠረችው ምድር ህይወት እንዲያብብባቸው--በተለይም ሰብዓዊ ፍጡራን ሐሴት ያደርጉባቸው ዘንድ በብዙ የተትረፈረፉ ነገሮች የተሞሉ ነበሩ። ደግሞም እግዚአብሔር ለመጀመሪያዎቹ ወንድ እና ሴት ፍጥረቶቹ እንዲሁም ከእነርሱ በኋላ የምንመጣው እኛ ጭምር በፍጥረቱ የምንጫወተውን ሚና ሰጠን። በፍጥነት ይፋ ሆኖ መታየት እንደ ቻለው--አዳምና ሔዋን በዚህ አዲስ ምድር ላይ የተለየ ማዕረግ ተሰጣቸው። አዳም በመጀመሪያ የተሰጠው ሥራ እንስሳትንና አዕዋፋትን መሰየም ነበር (ዘፍ. 2፡19)። በመቀጠል ከራሱ ከእግዚአብሔር በበረከት መልክ የቀረበለት ሌላ ሚና ተሰጠው “እግዚአብሔርም ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ሁሉ ግዟቸው’ ብሎ ባረካቸው” (ዘፍ. 1፡28)። የሚከተሉትን ሁለት ጥቅሶች ማለትም ዘፍ. 1፡28 እና 2፡15 ያስተያዩ። ሰብዓዊውን የሥራ ኃላፊነት በአንድ ወይም በሁለት ዓረፍተ ነገሮች እንዴት ማስቀመጥ ይችላሉ?
ዘፍ. 1፡28--በአብዛኛው የክርስትና ታሪክ ተፈጥሮን እስከ ማውደም የደረሰ
የመበዝበዣ ፈቃድ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሎአል። በእርግጥ ምድር የተፈጠረችው
ለሰው ህይወት፣ ጥቅምና ደስታ ሲባል ቢሆንም--ለሰው የተሰጠው ኃላፊነት
“እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት” ነው (ዘፍ. 2፡15)።
ስለ መጋቢነት ስንነጋገር በቅድሚያ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ገንዘብ
ቢሆንም፤ ነገር ግን በመጋቢነት ዙሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው የመጀመሪያ
ትእዛዝ እግዚአብሔር ፈጥሮ በአደራ የሰጠንን ምድር ስለ መጠበቅና ስለ መንከባከብ
ይናገራል። ለአዳምና ሔዋን የተሰጠው ትእዛዝ ምድር የልጆቻቸውና የቀጣዮቹ
ትውልዶች የጋራ መኖሪያ እንደምትሆን አስቀድሞ የተመለከተ ነበር። ለምድር
በነበረው የቀደመ ዕቅድ መሰረት ይህች አዲስ የተፈጠረች ዓለም ለመላው ሰብዓዊ
ፍጡራን--የህይወት፣ የመልካምነትና የውበት ምንጭ ሆና የምትቀጥል ሲሆን፤
አዳምና ሔዋን ምድርን በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ የላቀ ሚና ይኖራቸው ነበር።
ምድር ዛሬም የጌታ ናት (መዝ. 24፡1)፤ እኛም እግዚአብሔር በሰጠን ነገሮች ሁሉ
መጋቢ እንድንሆን ተጠርተናል። ምናልባት በዚህ በወደቀ ዓለም እንደ መጋቢ የእኛ
ኃላፊነት እንደውም የላቀ ነው ብለን መደምደም እንችላለን።
በዚህ በወደቀ ዓለም የምድር መጋቢ መሆን ለእርስዎ ምን ትርጉም
አለው? ይህን ኃላፊነት መገንዘብዎ በየዕለት ሕይወትዎ ላይ ምን ዓይነት
ተጽእኖ ይኖረዋል?
እግዚአብሔር በምድር ላይ ለማንም ሳይሰጥ ለአዳምና ሔዋን ብቻ የቸረው ነገር
ቢኖር የመምረጥ ነፃነት ነው። ከእጸዋት፣ ከዛፎችና ከእንስሳት በተቃራኒ እነርሱ
መምረጥ የሚችሉ ሰብዓዊ ፍጡራን ነበሩ። ለሰብዓዊው የመምረጥ ነፃነት ከፍተኛ
ዋጋ የሰጠው እግዚአብሔር እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ራሱኑ ላለመታዘዝ መምረጥ
እስኪችሉ የሚፈቅድ ነፃነት ሰጣቸው። ከሰብዓዊ ፍጡሮቹ ጋር ፍቅርንና የመምረጥ
ነፃነትን መሰረት ያደረገ ከፍ ያለ ግንኙነት እንዲኖረው ያቀደው አምላክ በዚህ ድርጊቱ
መላውን የፍጥረት ሥራውን አደጋ ላይ ጣለ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ልዩ ሰብዓዊ ፍጥረቶቹን ተጠቅሞ
መልካምና ፍጹም የሆነችውን ዓለም ምስቅልቅሏን ለማውጣት በጽኑ የሚሻ አውዳሚ
ነበር (እዚህ ላይ መላእክት የመምረጥ ነፃነት ባለቤት መሆናቸውን ልብ ይሏል)።
እባብን ተጠቅሞ የተናገረው ዲያብሎስ ፍጹምና ምሉዕ በሆነው የእግዚአብሔር
ስጦታ ላይ ጥያቄ አቀረበ። እግዚአብሔር ከሰጣቸው በላይ መመኘታቸው፣
አምላካዊውን በጎነት መጠራጠራቸውና በራሳቸው ላይ መታመናቸው ዋንኞቹ
ፈተናዎች ነበሩ።
በእግዚአብሔር የተነደፈውና ለፍጥረት ወሳኝ የነበረው ግንኙነት በዚያ ምርጫ
እና ድርጊት ተበጠሰ። ከፈጣሪያቸው ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ሆነው የተነደፉት
አዳምና ሔዋን ከእንግዲህ ከእርሱ ጋር ሐሴት ማድረጋቸው አከተመ (ዘፍ. 3፡
8-10)። እነዚህ ሁለት ሰብዓዊ ፍጡሮች እርቃናቸውን መሆናቸውንና ሐፍረት
እንደ ተሰማቸው በድንገት አስተዋሉ። በሁለቱ መካከል የነበረውም ግንኙነት
እንደማይጠገን ሆኖ ተለወጠ። ከተቀረው የምድር ፍጥረታት ጋር የነበራቸውም
ግንኙነት እንዲሁ ውጥረት የሰፈነበትና የተበላሸ ሆነ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡16-19። ጥቅሶቹ በሰብዓዊ ፍጡራንና በተፈጥሮ መካከል
ስለ ተለወጠው የግንኙነት ሁኔታ ምን ይነግሩናል?
በተጨባጭ በተከሰተው ኃጢአት መንስኤ ህይወት በድንገት ለአዳም፣ ለሔዋንና
ለተቀረው ፍጥረት በሙሉ አስቸጋሪ ሆነች። በተለይ ሰብዓዊውን ፍጡርና የእርስ
በርስ ግንኙነቱን የጎዳው የኃጢአት ውጤት በገሃድ የሚታይ ነው። ከፈጠረን አምላክ
ጋር በጣም እንድንራራቅ አደረገን። ቤተሰቦቻችን በብዙ መንገድ የዚህ ችግር ገፈት
ቀማሽ ናቸው፤ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነትም ባብዛኛው በተግዳሮት የተሞላ ነው።
ከምንኖርባት ዓለምና ከተፈጥሮ ጋር ያለን ግንኙነትም እንዲሁ ትግል የበዛበት
ነው። ፈርጀ ብዙዎቹ የህይወታችን ገጽታዎችም ሆኑ ዓለማችን በኃጢአት ምክንያት
የተከሰተውን ብልሽት ያሳያሉ።
ዓለም የዛሬውን ገጽታ እንድትይዝ ሆኖ በእግዚአብሔር አልተፈጠረችም። በዘፍ. 3
የምናነበው “እርግማን” ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ምድራችንን ዳግም ለመፍጠርና
በኃጢአት የተሰበረውን ግንኙነት ለመጠገን የሰጠውን ተስፋ ጭምር ነው።
ኃጢአት በህይወታችን ሊኖረው ከሚችል ውጤት ጋር መታገላችንን እየቀጠልን፤
የቀደመችውን ዓለም መልካምነት እንድንጠብቅና እግዚአብሔር ለዚህ ዓለም
ያለውን ዕቅድ በህይወታችን በተግባር እንድናሳይ ተጠርተናል።
ኃጢአት ከገባ በኋላ ምድርን ምስቅልቅሏን ለማውጣት ብዙ ጊዜ አለወሰደበትም። በቅናት መጦዝ፣ በስህተት ማስተዋልና በቁጣ መንደድ የመጀመሪያው ግድያ በወንድማማቾች መካከል እንዲፈጸም መንስኤ ሆነ። ቃየን ስለ ሠራው ኃጢአት እግዚአብሔር በጠየቀው ጊዜ የሰጠው ምላሽ ምጸታዊ ነበር “‘ አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?’ ” (ዘፍ. 4:9)። እግዚአብሔር በመጀመሪያ በጠየቀው ጥያቄ ውስጥ “አዎ፣ በትክክል የወንድምህ ጠባቂ ነህ የሚል ሃሳብ በተዘዋዋሪ ይዞአል። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ምሳ. 22፡2። በዚህ ቀላል በሚመስል ዐረፍተ ነገር ውስጥ በተዘዋዋሪ የምናገኘው ሀሳብ ምንድን ነው? ከባልንጀሮቻችን ሰብዓዊ ፍጡራን ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምን ይነግረናል?
እያንዳንዱ የምንገናኘው ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠሩ ፍጥረታት
መካከል አንዱ እንደ መሆኑ፤ የቱንም ያህል ደካማና የተፍረከረከ ቢሆንም ሁላችንንም
ከእግዚአብሔር ፍጥረት ጋር በአንድ የሚያስተሳስረን የእርስ በርስ መገናኛ
ዘዴ አካል ነው። “እኛ ሁላችን በሰብዓዊው ድርና ማግ በአንድነት ተሸምነናል።
በሰብዓዊ ፍጡራን መካከል የሚከሰት ማንኛውም ክፋት በሁሉም ላይ አስጊ አደጋ
ያስከትላል።”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, p. 345. ወደድንም
ጠላንም በዚህ በጋራ በሚያስተሳስረን ገመድ የተነሳ በፈጣሪም ሆነ በሰው ፊት
እግዚአብሔር የሰጠን ኃላፊነት አለብን (ማቴ. 22፡37-39)።
እግዚአብሔር ፈጣሪያችን መሆኑን የሚናገረው መልእክት በመላው የመጽሐፍ
ቅዱስ ገጾች ተደጋግሞ ሲቀርብ እንመለከታለን። ለምሳሌ ሰንበትን እንድናስታውስና
(ዘፀ. 20፡11) በመጨረሻው ዘመን ለእግዚአብሔር እንድንሰግድ (ራእ. 14፡7) ጥሪ
የቀረበበት አንዱ ምክንያት ይኸው ነው። እንዲሁም በዕጦት ላሉ ተገቢውን ድጋፍ
ማድረግና በችግራቸው መድረስ ተቀዳሚ አጽንኦት የተሰጠው ተግባር ነው።
እኛ ሁላችን በጋራ በሚያስተሳስረን የቀደመው ጅማሮአችን ይኸውም
በእግዚአብሔር ተሳሰረናል። “ደኾችን የሚያስጨንቅ እግዚአብረሔርን ይንቃል”
(ምሳ. 14፡31)።
እግዚአብሔር እንደ ፈጣሪነቱ አምልኮአችንን እና አገልግሎታችንን ጨምሮ
መላውን ህይወታችንን በባለቤትነት ለመጠየቅ ባለ መብት ነው። አንዳንዴ ፈታኝና
ምቾት የሚነሳ ሊሆን ቢችልም፤ በእርግጥም የወንድማችን “ጠባቂ” ነን።
እንደ ፈጣሪ፤ እግዚአብሔር ያለው ባለመብትነት በመላው የመጽሐፍ
ቅዱስ ገጾች ተደጋጋሚ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የቀረበው ለምን ይመስሎታል?
ይህ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ ሐቅ ከሌሎች ጋር
በሚኖረን አግባብ ላይ ተጽእኖ የሚኖረው ለምንድን ነው?
1.ከላይ የቀረበውን የኤለን ኋይት መግለጫ በጥንቃቄ ይመልከቱ። ለመሆኑ
ምን እያለች ነው? በዙሪያችን አብልጦ ተንሰራፍቶ ለምንመለከተው
ድኽነት ውሎ አድሮ ኃላፊነቱ የማን ነው ትላለች? አባባሉ ታማኝ
መጋቢነት በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆኑ ምን ይነግረናል?
2.በኃጢአት ምክንያት በደረሰ በሺ የሚቆጠሩ ዓመታት ብልሽት
በኋላ የፍጥረትን መልካምነት ለመመልከት ምን ያህል ይቻለናል?
በእግዚአብሔር ፈጣሪነት የምናምን ሕዝቦች እንደመሆናችን ሌሎች
የእርሱን የፍጥረት ሥራ መልካምነት መመልከት እንዲችሉ ምን
ማድረግ እንችላለን?
3.መጋቢነት የተሰኘውን ቃል እንዴት ያስተውሉታል? የዚህ ሣምንት
ትምህርታችን መጋቢ የተሰኘውን ቃል ፍቺ ሰፋ ባለ ሁኔታ እንዲመለከቱ
እረድቶታል? በተለይ በዚህ ማዕረግ በእግዚአብሔር ከመጠራታችን
አኳያ?
4.ይህ ሰው “በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረና በእርሱ የተወደደ
ነው” የሚል ጽሑፍ በእያንዳንዱ የምንገናኘው ሰው ላይ የምንመለከት
ቢሆን ኖሮ፤ ይህ አባባል በሌሎች ላይ ባለን አመለካከትና ቀረቤታ ላይ
ምን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ ይችል ነበር?
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር መልካምና የተሟላ ዓለም ከፈጠረ በኋላ
የፍጥረት ሥራውን “እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት” በአምሳሉ
የፈጠረውን ሰው ሾመ። ምንም እንኳ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለእኛ
ያቀደውን ነገር ኃጢአት ቢያበላሸውም ዛሬም እንደ መጋቢ መልካም ለሆነው
የፍጥረት ሥራ እና ለባልንጀራችን በጎነት የምንጫወተው ሚና አለን።