“ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ…”
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከነሐሴ 11–17

8ኛ ትምህርት

Aug 17 - Aug 23




ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 5:2– 16፣ 38–48፣ ሮሜ 12:20-21፣ ሉቃ. 16:19–31፣ 12:13–21፣ ማቴ. 25:31–46።


መታሰቢያ ጥቅስ:-“ንጉሡም መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ አላቸው” (ማቴ. 25፡40)።

የ ሱስ ስለ ሌሎች የመቆርቆር ህይወት የመኖሩን እውነታ--በተለይ በእጦት ስለ ተንገላቱና ስለ ጠፉ ከተመለከትን በኋላ፤ ለሌሎች ጥንቃቄ ስለ ማድረግ ብዙ የሚናገረው ሊኖረው እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል። ተግባራዊው የየሱስ አስተምህሮ እንደ እግዚአብሔር ተከታይነታችን እንዴት መኖር እንዳለብን ትኩረት ያደርጋል። የሱስ በዚህ ምድር እንዳደረገው ሁሉ እኛም ፍትሕ እንድናደርግ፣ ደግነት እንድናሳይና ምህረት እንዳይለየን አጥብቆ ሲያስገነዝበን መመልከት እንችላለን። ምሳሌውን የምንከተል ከሆነ እርሱ እንዳደረገው ሌሎችን እናገለግላለን። በተጨማሪ የሱስ ስለ ሰማያዊው መንግሥት ተናግሮ ነበር። የሱስ በሰጠው መግለጫ መሰረት የሰማይ መንግሥት ዛሬም የምንወርሰው ተጨባጭ እውነታ ነው። ሰማያዊው ህይወት ለወትሮው በምድራዊው መንግሥት ቅድሚያ ከምንሰጥበት በተለየ ቅደም ተከተል እሴቶችንና የሥነ ምግባር ስብስቦችን የያዘ ነው። ከሰማያዊው መንግሥት ንድፍ ጋር የሚያስተዋውቁን የየሱስ አስተምህሮዎች--እግዚአብሔርን ስለ ማገልገል ብሎም ከሌሎች ጋር ዝምድና ስለ መፍጠር ያስተምሩናል። በተጨማሪ ሌሎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ጥንቃቄ እያደረጉ እነርሱን ማበረታታትና ማገልገል ለእግዚአብሔር ቀጥተኛ አገልግሎት ከምንሰጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው።

ነሐሴ 12
Aug 18

ከተራራው ስብከት ጋር መተዋወቅ


ከየሱስ ስብከቶች ረጅሙ ወይም ልዩ ልዩ አስተምህሮዎችን አሰባጥሮ የያዘ ቢኖር የተራራው ስብከት ነው። ይህ የሰማያዊውን መንግሥት ህይወት የቃኘበት ሦስት ምዕራፍ፤ ብፁዓን በሚል በሚታወቅ ቃል የሚጀምሩ እሴቶችን ይዞአል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5፡2-16። የሱስ “የተባረኩ ናቸው” እያለ የገለጻቸው የእነዚህ ዘጠኝ እሴቶች ወይም ሰዎች የጋራ ባህሪ ምንድን ነው?



ከእነዚህ ቃላት ጥልቅ መንፈሳዊ ትግበራ ጎን ለጎን በሥራ ላይ ሊውል የሚችለውንም ምንባብ እንዲሁ መሳት የለብንም። የሱስ በራሳችን እንዲሁም በዓለም ላይ ያለውን ድኽነት ለይተን መገንዘብ እንዳለብን ተናግሮአል። በተጨማሪም ስለ ጽድቅ፣ ትህትና፣ ምህረት፣ ሰላም ስለ መፍጠርና ስለ ልብ ንጽህና ተናግሮአል። እነዚህን ምርጥ እሴቶች ስንኖራቸው በሕይወታችን ብሎም በዓለም ላይ ሊመጣ የሚችለውን ተጨባጭ ልዩነት ልብ ልንል ይገባል። ይህ በየሱስ አጽንኦት የተሰጠው በሥራ ላይ ሊውል የሚችል ምንባብ ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ ዓለም ጨው እና ብርሃን ይሆኑ ዘንድ አጥብቆ ያስገነዝባል (ማቴ. 5፡13-16)።

ጨው እና ብርሃን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደረግ ጣል በተደረጉበት ዐውድ ሁሉ ልዩነት ያመጣሉ። ለምግብ ጣዕም ከመስጠቱ በተጨማሪ ምግብ ነክ ነገሮች ሳይበላሹ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚረዳው ጨው፤ በዙሪያችን ለሚገኙ ወገኖች መልካም የመሆናችን ተምሳሌት ነው። በተመሳሳይ ብርሃን ጨለማን ገልጦ መሰናክሉንና አደጋውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። መኖሪያ ቤት ወይም ከተማ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንዲሆን፣ አደጋን ከሩቅ ለይቶ ለመመልከት እንዲሁም እንደልብ ወዲህ ወዲያ ለመዘዋወር ብርሃን ወሳኝ ነው። በድቅድቅ ጨለማ ብርሃን ልንሆን እንደሚገባ የሱስ ይናገራል “ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” (ማቴ. 5፡16)። እነዚህ ሁለቱም ማለትም የጨው እና የብርሃን ተምሳሌቶች የየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሁሉ ዙሪያቸውን ባሉ ሰዎች ተጽእኖ እያሳደሩ ህይወታቸውን የማሻሻል ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳያሉ። ካዘኑ ጋር ስናዝን፣ የልብ ንጽህና ሲኖረን፣ ትህትናን ስንለማመድ፣ ምህረት ስናደርግ፣ ሰላም ስንፈጥርና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ ያኔ--ጨው እና ብርሃን ነን። የሱስ ስብከቱን የሚጀምረው የመንግሥቱ አካል ሆነው እያለ፤ ዝቅ ያለ ዋጋ የተሰጣቸውን እሴቶች አጥብቀን እንድንይዝ ጥሪ በማድረግ ነው።

የቤተ ክርስቲያንዎ ማኅበረሰብ ለአካባቢው ነዋሪ እንደ ጨውና ብርሃን ሆኖ እየሠራ የሚገኘው በምን መልኩ ነው? የቤተ ክርስቲያንዎን እንቅስቃሴ ተከትሎ የእርስዎ ማኅበረሰብ የተሻለ ስፍራ መሆን የቻለው እንዴት ነው? በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኒቱ በዚያ ስፍራ ባትኖር ማኅበረሰብዎ ላይ ምን ዓይነት ልዩነት ሊፈጠር ይችል ነበር?

ነሐሴ 13
Aug 19

ክፉውን በበጎ ማሸነፍ


የየሱስን አስተምህሮ ልብ ብለን ስናጤን፤ መልእክቱን እያቀረበላቸው የነበሩትን እነዚህ ሕዝቦች ይኖሩ የነበረበትን ሁናቴ ከግንዛቤ ማስገባት ፋይዳው የላቀ ነው። የሱስ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት አካባቢ ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ መሳብ ችሎ ነበር (ማቴ. 4፡25፣ 5፡1)። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በሮም ንጉሣዊ አስተዳደር ስር የሚኖሩ ተራ ሕዝቦች ሲሆኑ ከመካከላቸው ጥቂቶቹ ግን የአይሁድ ገዢዎችና የኃይማኖት መሪዎች ነበሩ። የተራው ሕዝብ የዕለት ከዕለት ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። በህይወታቸው እጅግ በጣም ውሱን አማራጮች ብቻ የነበሯቸው እነዚህ ሕዝቦች በከፍተኛ ግብር ጫና እና ኃይማኖታዊ ወግ ቀንበር ስር ወድቀው ነበር። እነዚህን ሕዝቦች ሲያስተምር፣ የአኗኗራቸው ሁኔታ ያሳሰበው የሱስ በየትኛውም ሁናቴ ቢገኙ፤ አሁን ከሚኖሩት በተሻለ ክብርና ወኔ የሚመላለሱበትን አቅጣጫ እያመላከታቸው ነበር። ለዚህ አንድ ምሳሌ በማቴ. 5፡39-48 ማግኘት እንችላለን፡ “ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ አዙርለት”፣ “ካባህን ጨምረህ ስጠው”፣ “ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ”--የተሰኙት በስፋት ከሚታወቁት መካከል ናቸው።

የሱስ በዚህ ስፍራ የገለጻቸው ትዕይንቶች የአብዛኞቹ አድማጮቹ የተለመዱ የዕለት ከዕለት ህይወት ነበሩ። እነዚህ ሕዝቦች በበላዮቻቸው ወይም በጌቶቻቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተደጋጋሚ ዕዳ ውስጥ በመግባታቸው ንብረቶቻቸውን ለመሬቱ ጌታ ወይም ለአራጣ አበዳሪው አስረክበዋል። ቅኝ ገዢዎቻቸው የሮም ወታደሮች ከባድ ሥራ እንዲሠሩ ጫና ያደርጉባቸው ነበር። ሕዝቡ ለሚደረግበት ጫና ሐቀኛ ምላሽ እንዲሰጥ፣ ለጨቋኞቻቸው የማይገባውንና የተሻለውን ክብር እንዲቸር የሱስ ሕዝቡን አስተምሮአል። እነዚህ ጨቋኞች ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ለመጠቀም በሞከሩ ቁጥር ሕዝቡ እንዴት መላሽ መስጠት እንዳለበት ሁልጊዜም ምርጫ ያለው ሲሆን፤ ይኸውም ውስጣቸውን ፈንቅሎ ለመውጣት የሚፈልገውን አመጸኝነት ገትተው በቸርነት በተሞላ ምላሽ የሚፈጸመውን ክፉ ድርጊት፣ ጭቆና እና ኢፍሐዊነት ገልጦ ማሳየት በመቻል ነው።

ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ማቴ. 5፡38-48 እና ሮሜ 12፡20-21። እነዚህን ሥር ነቀል የለውጥ መርኅዎች በህይወታችን መኖር ያለብን እንዴት ነው?



የሱስ ኦሪትንና ነቢያትን በአንድ በማጠቃለል የብሉይ ኪዳንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፍሬ ነገር ወርቃማ ሕግ በመባል በሚታወቀው ቀለል ያለ መርኅ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፡ “‘ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው’ ” (ማቴ. 7፡12)። ትእዛዙ የቱንም ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን ቢችል እንኳ በዚህ ስፍራ የተሰጠንን ትእዛዝ ለመተግበር ከአሁን ጀምሮ ጥረት ለማድረግ የሚንቀሳቀሱበት መንገድ ምን ሊሆን ይችላል?

ነሐሴ 14
Aug 20

ደጉ ሳምራዊ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 10፡25-27። ለየሱስ ጥያቄ ያቀረበው ሕግ ዐዋቂ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለውን ህይወት ለመኖር መሰረታዊ ያላቸውን የብሉይ ኪዳን ትእዛዛትን በአጭሩ አቅርቦለት ነበር። ለመሆኑ እነዚህ ሁለት ትእዛዛት እንዴት ይተሳሰራሉ?



የሱስ ጥያቄ ሲቀርብለት ይሰጥ የነበረው መልስ ድምዳሜ ጠያቂው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚጠብቀው የተለየ ውጤት ይዞ ይመጣ ነበር። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በሚል በዘሌዋ. 19፡18 ለተሰጠው መመሪያ ምላሽ ብዙዎች በእርሱ ዘመን የነበሩ ኃይማኖተኛ ሰዎች የዚህ የ “ባልንጀራ” መርኅ መጠንና ገደብ የት ድረስ ነው-በሚለው ዙሪያ ሰፊ ክርክር ያካሂዱ ነበር። ሰዎች መውደድ ያለባቸው ባልንጀሮቻቸውን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለሁሉም ሰው በጎ ማድረግ እንደሚገባ በመናገርና የስያሜውን ፍቺ ሰፋ አድርጎ በማቅረብ፤ የሱስ ተከታዮቹ እንዲያስተውሉት የነበረውን ብርቱ ፍላጎት አሳይቶአል፡ “‘እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ። እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሐዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኃጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል’” (ማቴ. 5፡44-45)።

ነገር ግን የኃይማኖት ሕግ ዐዋቂው የሱስን ሊፈትነው ስለፈለገ ሰፊ ክርክር ይካሄድበት ወደ ነበረው ጥያቄ በመውሰድ፡ “ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው (ሉቃ. 10፡29)። የሱስ በምላሹ የደጉን ሳምራዊ ታሪክ ቢነግረውም፤ “ባልንጀራ” ለተሰኘው ስያሜ ፍቺ መስጠት የመልሱ መጨረሻ አልነበረም። ይልቁንም በሥራ ላይ እንዲያውል የነገረው ይህን ነበር--“የአንተን እርዳታ ለሚሹ ሁሉ ፈጥነህ ባልንጀራችው ሁን!” (ሉቃ. 10፡36-37)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 10፡30-37። የሱስ በመንገድ ላይ ወድቆ እርዳታቸውን ይሻ የነበረውን ሰው በተመለከቱ ሦስት ገጸ ባህሪያት መካከል ያደረገው ንጽጽር አንደምታው ምንድን ነው?



ራሳቸውን ኃይማኖተኛ እያደረጉ ነገር ግን ስለ ሌሎች ሥቃይና እንግልት ግድ በማይሰጣቸው ላይ የሱስ የሰላ ትችት ሲሰነዝር መመልከት የተለመደ ነበር። “ክርስቶስ በደጉ ሳምራዊ ታሪክ የእውነተኛ ኃይማኖትን ተፈጥሮ ስሎልናል። እውነተኛ ኃይማኖት የሚገለጠው ሥርዓትና ወግ በመጠበቅ ሳይሆን በፍቅር የተሞሉ ተግባራትን በመፈጸም፣ ለሌሎች በጎ በማድረግና ከልብ በመነጨ መልካምነት ነው።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 497. እግዚአብሔር ጥሪ የሚያቀርበው የእርሱ ተከታዮች ለመሆን ለሚሹ ሁሉ እንደሆነ ለማሳየት የፈለገው የሱስ በአስተምህሮው--ለእግዚአብሔር ታማኝ እንዳልሆነ ተደርጎ ይቆጠር የነበረን የባዕድ አገር ሰው ተጠቀመ። እንደ መጀመሪያ አድማጮቹ ሁሉ፤ እኛም ወደ የሱስ ቀርበን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ምን ማድረግ እንዳለብን ብንጠይቀው፤ ሊሰጠን የሚችለው የመጨረሻ ትእዛዝ--የእናንተን እርዳታ ለሚሹ ሁሉ ፈጥናችሁ ባልንጀራችው ሁኑ፤ የሚል ይሆናል።

ነሐሴ 15
Aug 21

ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር


ስለ ሀብታሙ ሰው እና ስለ አልዓዛር በቀረበው ምሳሌያዊ ታሪክ (ሉቃ. 16፡1931) የሱስ የሁለት ሰዎችን ማለትም የአንድ ሀብታም እና ፍጹም ደኻ የነበረን ሰው ህይወት በንጽጽር ያቀርባል። እንደ ዛሬው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሕዝብ ጤና ተቋማት ባልነበሩበት በዚያ ዘመን በከፍተኛ እጦት ውስጥ የነበሩ ምስኪኖችና አካል ጉዳተኞች በሀብታሞች ደጃፍ ተኮልኩለው ይለምኑ ነበር። ሀብታሞች በጥቂቱም ቢሆን ለድኾች የችሮታ እጆቻቸውን ዘርግተው ሥቃያቸውን ያስታግሱላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ታሪክ የቀረበው ሀብታም ሰው ግን “በብርቱ ሥቃይ ለነበረው ወንድሙ ንፉግና ግዴለሽ ነበር”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 261. የምድራዊ ህይወታቸው ሁኔታ ሳይለወጥ ቢቀርም--ነገር ግን ሲሞቱና በእግዚአብሔር ሲዳኙ የነበራቸው ስፍራ በሚገርም ሁኔታ ተለዋወጠ። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ሉቃ. 16፡19-31 እና ሉቃ. 12፡13-21። በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች መሃል ያለው መመሳሰልና ልዩነት ምንድን ነው? በአንድነት ምን ያስተምሩናል?



ሰዎቹ ክፉ ተግባር ፈጽመው ወይም ግፍ ሠርተው ሀብት እንዳካበቱ የሚጠቁም ምንም ዓይነት ማስረጃ በሁለቱም ታሪኮች አናገኝም። ምናልባት ሁለቱም ሰዎች ጠንክረው ሠርተው፣ ንብረታቸውን በአግባቡ አስተዳድረውና በእግዚአብሔር ተባርከው ሊሆን ይችላል። ሆኖም በህይወት ላይ በነበራቸው አመለካከት ይሁን ወይም በእግዚአብሔር፣ በገንዘብ ወይም በሌሎች ነገሮች ብቻ አንድ የተፈጠረ የከፋ ስህተት ነበረ። ይህ ደግሞ እጅግ የላቀውን ዋጋ ማለትም የዘላለምን ህይወት አሳጥቶአቸዋል።

በየሱስ ዘመን ይንጸባረቅ ከነበረው ከህይወት በኋላ ዝነኛ ምናባዊ አመለካከት በመነሳት፤ በዚህ ህይወት የምናደርጋቸው ምርጫዎች ለቀጣዩ ተጽእኖ እንዳላቸው የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ታሪክ ያስተምረናል። እርዳታችንን አጥብቀው ለሚሹ የምንሰጠው ምላሽ ምርጫዎቻችንና ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ገልጸው ያሳያሉ። “አብርሃም” በሥቃይ ውስጥ ወዳለው ሀብታም ሰው እያመላከተና የተሻለውን ስለ መምረጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከበቂ በላይ አቅጣጫዎችን እንደሚሰጥ እየጠቆመ “ሙሴና ነቢያት አሏቸው፤ እነርሱን ይስሙ” (ሉቃ. 16፡29) ሲል መለሰለት።

የሱስ እንዳስተማረው ከሀብት ጋር የሚመጣን ፈተና መቋቋም ካልቻልን በቀር ከመንግሥቱ ሊያስቀረን፣ ከሌሎች ሊነጥለንና እኔነትን የሙጥኝ ብለን እንድንቀር ያደርገናል። በቅድሚያ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድንሻ በመቀጠል የተቀበልነውን በረከት በዙሪያችን ላሉ በተለይም በእጦት ለሚንገላቱ እንድናካፍል የሱስ ጥሪ ያቀርብልናል።

የእርስዎ የገቢ ሁኔታ የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችል፤ ገንዘብ ወይም የገንዘብ ፍቅር ክርስቲያኖች በህይወታቸው ትኩረት ሊያደርጉ የሚገባውን ነገር እንዳያዛባ እንዴት መጠንቀቅ ይችላሉ?

ነሐሴ 16
Aug 22

ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት


የሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ከተጠበቀው ፍጹም የተለየ መልስ ከሰጠባቸው ክስተቶች ሌላኛው በማቴ. 24 እና 25 ይገኛል። ደቀ መዛሙርቱ ወደ የሱስ ቀርበው በየሩሳሌም ስለሚገኘው ቤተ መቅደስ መፍረስና ስለ የሱስ ዳግም ምጽአት ጠይቀውት ነበር (ማቴ. 24፡1-3)። የሱስ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው ረዘም ያለ ምላሽ መደምደሚያው የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ እንግዶችን መቀበል፣ የታረዘውን ማልበስ፣ የታመመውን መንከባከብና የታሰሩትን መጠየቅ ነበር። “ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” (ማቴ. 25፡ 40፣45)።

ይህ ነጥብ የሱስ በመጨረሻው ፍርድ ጥያቄዎች ዙሪያ ትምህርቱን በመጀመር ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጣቸው ሥዕል ጋር ትስስር አለው። የሱስ በደቀ መዛሙርቱ በቀረቡለት ጥያቄዎች ስለ የሩሳሌም ጥፋት ምልክቶችና ማስጠንቀቂያዎች እንዲሁም ስለ መጨረሻው ዘመን በዛ ያሉ ቀጥተኛ መልሶችን በመላው ማቴ. 24 የሰጠ ቢሆንም፤ ተግቶ ስለ መጠበቅ አስፈላጊነትና በዳግም ምጽአቱ ተስፋ ብርሃን በተሻለ ህይወት ስለ መመላለስም እንዲሁ ተናግሮአል። ባልታሰበ ጊዜ ሊደርስ ወይም ሊዘገይ የሚችለውን ሙሽራ ለመቀበል ሁሌም ተዘጋጅተን መጠበቅ እንዳለብን አጥብቆ የሚያሳስበው የዝንጉዎቹና አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ምሳሌ ታሪክ በማቴ. 25 የመጀመሪያ ክፍል ቀርቦአል። የሦስቱ አገልጋዮች ታሪክ ደግሞ እርሱን እየተጠባበቅን-እንደሚፈለግብን መመላለስና ሥራችንን በትጋት መሥራት እንዳለብን ይነግረናል። እንዲሁም ስለ በጎችና ፍየሎች የቀረበው ምሳሌያዊ ታሪክ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በተለይ አጥብቀው ሊጠመዱ በሚገባቸው ኃላፊነቶች ዙሪያ ይናገራል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡31-46። የሱስ ስለ ምን እየነገረን ነው? ለምንድን ነው ይህ ደህንነት በሥራ ያልሆነው? እዚህ ላይ የሚያድን እምነት ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ አምላካዊው ቃል ምን ያስተምረናል?



ሌሎችን ስናገለግል እርሱን እንዳገለገልንና ለእርሱ እየሠራን ተደርጎ እንደሚቆጠር አስመልክቶ የሱስ የሰጠው ይህ መግለጫ በሁሉም ግንኙነቶቻችንና አመለካከቶቻችን ላይ ተሐድሶ ሊያመጣ ይገባል። የሱስን ምሳ ወይም እራት ሲጋብዙት ወይም ደግሞ በሆስፒታል ሲጠይቁት በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ። ይህን አገልግሎት ለማኅበረሰባችን አካል ለሆኑ ስናበረክት ለእርሱ እንዳደረግን እንደሚቆጠር የሱስ ነግሮናል። አቤቱ እንዴት ያለ አስደናቂ ዕድል ሰጥቶናል! የሱስ በእነዚህ ጥቅሶች የተናገራቸውን መልእክቶች በጸሎት መንፈስ ሆነው ያንብቧቸው። የሱስ ራሱን ከተራቡ፣ ከታረዙና ከታሰሩ ሰዎች ጋር ካዛመደበት ከዚህ ጽንሰ ሀሳብ ምን እንረዳለን? እንዴት መመላለስ እንዳለብን አስመልክቶ ይህ በእኛ ላይ ምን ዓይነት ብርቱ ግዴታዎች አስቀምጦአል?

ነሐሴ 17
Aug 23


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “The Good Samaritan,” pp. 497– 505, and “ ‘The Least of These My Brethren,’ ” pp. 637–641, in The Desire of Ages; “ ‘A Great Gulf Fixed,’ ” pp. 260–271, “ ‘Who Is My Neighbour?’ ” pp. 376–389, in Christ’s Object Lessons. “ክርስቶስ የመለያየትን፣ የራስ ወዳድነትንና ከፋፋዩን የጠባብ ብሔርተኝነት ግድግዳ በማፈራረስ ለሁሉም ሰብዓዊ ቤተሰብ ፍቅርን ያስተምራል። ሰዎችን ከራስ ወዳድነት ጠባብ ቀለበት ውሰጥ አውጥቶ ከፋፋይ የሆኑ የክልል ድንበሮችንና ሰው ሰራሽ ማኅበረሰባዊ ልዩነቶችን ያስወግዳል። እርሱ በጎረቤቶችና በመጻተኞች፣ በጓደኛሞችና በጠላቶች መካከል አንዳችም ልዩነት አያደርግም። እያንዳንዱን ችግርተኛ ነፍስ እንደ ባልንጀራችን፤ ዓለምን ደግሞ እንደ ሥራ መስካችን እንድንመለከት ያስተምረናል።”— Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 42. “ወርቃማው ሕግ እውተኛ የክርስቲያኖች ሕግ ነው። ከዚህ መደበኛ ሕግ ጋር ገጣሚ ያልሆነ ሁሉ አሳች ነው። ክርስቶስ ራሱን ስለ ሰብዓዊው ፍጡር በመስጠት ያከበረውን ስብዕና ዝቅ አድርጎ የሚመለከት፣ ስለ ሰብዓዊው እጦት፣ ሥቃይ ወይም መብት ግዴለሽ እንድንሆን የሚመራ ኃይማኖት ሐሰተኛ ነው። የደኻውንና በሥቃይ ውስጥ ያለውን የበደለኛውን ሰብዓዊ ወገን መብት ስንንቅና ስናቃልል ራሳችንን በክርስቶስ ላይ ክህደት ከሚፈጽሙ ተርታ እንፈርጃለን። ክርስትና በዓለም ላይ ያለው ኃይል እጅግ አነስተኛ የሆነበት ምክንያት ሰዎች የክርስቶስን ስም መጠሪያቸው እያደረጉ ባህሪውን ግን በሕይወታቸው በመካዳቸው ነው”—Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, pp. 136, 137.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.በዚህ ሣምንት ካጠናናቸው መሃል ይበልጥ ለእርስዎ ተወዳጅ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የትኛው ነው? ለምን?

2.ኤለን ጂ. ኋይት ለሰብዓዊው እጦት፣ ሥቃይ ወይም መብት ግዴለሽ ወደ መሆን ሊመራን ስለሚችል ኃይማኖት የጻፈቸውን መልእክት ይመልከቱ። እውነት ስላለን ምንም የሚመጣብን ነገር አይኖርም የሚለውን ወጥመድ በማስወገድ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

3.የ “እውነት” ባለቤት መሆን ስለሚጠይቀው ነገር በሐሙስ ጥናት የቀረቡት ጥቅሶች ምን ያሳዩናል?

ማጠቃለያ፡ የሰማይ ዜጎችና የእግዚአብሔር መንግሥት ወኪሎች በዚህ ምድር ሊኖራቸው ስለሚገባው የተለየ ዓይነት አኗኗር ጅማሮ የየሱስ አስተምህሮዎች በቂ ገለጻ ያደርጋሉ። ለድኾችና ለተጨቆኑ ጥንቃቄና ድጋፍ በማድረግ ዙሪያ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን መሰረት አድርጎ የገነባውን መልእክት ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚያስተጋባው ጌታ፤ ተከታዮቹ የእርሱን ዳግም ምጽአት እየተጠባበቁ በርኅራኄና በምኅረት የተሞላ ህይወት በመኖራቸው ዙሪያ አጽንኦት ይሰጣል።