ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ. 1:46–55፣ 4:16–21፣ 7:18–23፣ ማቴ. 12:15–21፣ ማቴ. 21:12–16 ማር. 11:15–19፣ ኢሳ. 53:3–6።
መታሰቢያ ጥቅስ:-“ ‘የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀበቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቆኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል” (ሉቃ. 4፡18-19)።
የ
ሱስ ሥጋ እንዲለብስ ከሆነባቸው ሌሎች ምክንያቶች በተጨማሪ አብ ምን
እንደሚመስል ሊያሳየን ወደዚህ ምድር መጣ። ይህንንም በትምህርቱ፣
መሥዋዕትነቱና በሕይወቱ፤ ይኸውም ከተራ ሰዎች ጋር መስተጋብር በመፍጠር
እውን አደረገ። አብዛኞቹ ድርጊቶቹ በሌሎች ህይወት ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ
ማምጣት ችለዋል። ይህ የመሲህ አገልግሎት ገጽታ ብብሉይ ኪዳን ነቢያት፣ በየሱስ
እናት ማርያም እንዲሁም ተልዕኮውን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባደረገበት በመጀመሪያ
ስብከቱ (ሉቃ. 4) በራሱ በየሱስ አስቀድሞ ተተንብዮ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ
የወንጌል ጸሐፊዎች የየሱስን ታሪክ ሲጽፉ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ቋንቋ በተደጋጋሚ
ተጠቅመዋል። በዚህ መልኩ የየሱስ ሕይወት በነቢያቱ ትውፊት ውስጥ በጉልህ
ታይቶአል--ለድኾችና ለተጨቆኑ የነበራቸውን ርኅራኄ ጨምሮ።
የሆነው ሆኖ የኃይማኖት መሪዎች የሱስን በጥርጣሬ ዐይን ይመለከቱት ነበር።
በዘግናኙ ኢፍትሐዊ ተምሳሌነታቸውና ጨካኝነታቸው የሱስ እንዲታሰር አደረጉ፣
ፍትሕ የጎደለው ዳኝነት ሰጡ፣ በመጨረሻም ሰቀሉት። ኢፍትሐዊ ፍርድ ምንኛ ልብ
እንደሚሰብር በገዛ ልጁ ሞት የደረሰበት እግዚአብሔር አብ ጠንቅቆ ያውቀዋል።
እርሱ በሞቱ የክፉውን አሰቃቂ ማንነት ገልጦ አሳየ። በትንሳኤው ደግሞ የህይወት፣
የበጎነትና የደኅንነት ድል አድራጊነቱን አስመሰከረ።
ማርያም ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ መልእክት ከገብርኤል ተቀበለች። መልእክቱ
የልዑል አምላክ ልጅ፣ ይኸውም የየሱስ እናት እንደምትሆን የሚያበስር ነበር።
ማርያም እነዚህን የሰማቻቸውን ቃላት ለማንም ከመንገሯ በፊት በዚያው ሰሞን
በእርጅና ዘመን የነበረችውን ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ወደ ደጋማው አገር
ሄደች። የሚገርመው ኤልሳቤጥም እንዲሁ እግዚአብሔር በታምር የሰጣትን ጽንስ
ለመውለድ ተቃርባ ነበር። ማርያም ገና ምንም ሳትናገር ኤልሳቤጥ በመንፈስ
ቅዱስ ተሞልታ ማርያም ይዛ የመጣችውን የምስራች አስቀድማ አወቀች። ሁለቱም
በአንድነት ሆነው በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እና መልካምነት ሐሴት አደረጉ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 1፡46-55። “ ‘ኃያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና’
” (ሉቃ. 1፡49) በሚል ለእርሷ ብቻ በግሏ ለሆነውና በአጠቃላይ ለሁሉም
የሚተርፈውን ምስጋና ልብ ይበሉ። ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ምስጋና እና
አምልኮ ግላዊና ሁሉን አቀፍ አጽንኦት ሊያካትት የሚገባው ለምንድን ነው?
ይህ ከመዝሙረ ዳዊት ወይም ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ነቢያት ጽሑፎች ጋር አቻ
ሊሆን የሚችል አስደናቂ የመዝሙር ስንኝ ነው። ማርያም ስለ እግዚአብሔር አምላክ
ገደብ ባለፈ አድናቆትና ምስጋና ተሞልታ ነበር። ማርያም እግዚአብሔር በገሃድ
በህይወቷ እየሠራ መሆኑን ብትመለከትም ነገር ግን ከዚያ ባለፈ እርሱ ለሕዝቧና
ለመላው ሰብዓዊ ዘር ያለውን የገዘፈ አንደምታም እንዲሁ በሚገባ ታስተውል ነበር።
ማርያም እንደ ነበራት ግንዛቤ ከሆነ እግዚአብሔር ኃያልና ምስጋና የሚገባው ብቻ
አልነበረም፤ ይልቁንም መሐሪና ይቅር ባይ፣ ትሑት የሆነውን፣ መንፈሱ የተሰበረውንና
ደኻውን በተለየ ዐይን የሚመለከት አምላክ ነው። መልአኩ መልካሙን የምስራች
ለማርያም አብስሮ ከሄደ በኋላ እንዲህ ስትል ዘመረች “ ‘ገዢዎችን ከዙፋናቸው
አውርዶአቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር
አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል’ ” (ሉቃ. 1፡52-23)።
የየሱስ ምድራዊ ህይወት ጅማሬ ላይ እርሱ እንደ ገዢ--ማለትም ከወትሮው የተለየ
መንግሥት ገዢ ሆኖ ሲተዋወቅ እንመለከታለን (ሉቃ. 1፡43)። አያሌ የመጽሐፍ
ቅዱስ ሐተታ አቅራቢዎች እንዳሉት ከሆነ የሱስ ሊያቋቁምና ሊመሰርት የመጣው
የእግዚአብሔር መንግሥት እዚህ ከተለመደው ጋር ሲተያይ የምድራዊውን መንግሥት
ሥርዓተ አወቃቀር የሚገለባብጥ ነበር። የየሱስ መንግሥት ከተገለጸባቸው መንገዶች
አኳያ የዚህ ምድር ገዢዎችና ባለጸጎች የተሰጣቸው ስፍራ ከሁሉ ዝቅ ያለ ሲሆን፤
ድኾች እና የተጨቆኑ ነጻ ወጥተዋል “በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል”።
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት የሚገለጥባት መሣሪያ መሆን
ካለባት፤ ማርያም እንዳስቀመጠችው የዚህ ዓለም ኃያላን ዝቅ--ትሑታን
ደግሞ ከፍ ከፍ የሚሉበት ምሳሌ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ገናና
ምድራዊ ስም ያላቸውንና ሀብታሞችን ሳናገልና እነርሱም የክርስቶስ ፍቅር
ተቀባይ መሆናቸውን ሳንዘነጋ የእንዲህ ዓይነቱ ነገር ምሳሌ መሆን የምንችለው
እንዴት ነው?
የሱስ ከኢሳይያስ መጽሐፍ ጥቅል አውጥቶ ያነበበው ጥቅስ የዕለቱ የጥቅስ
ንባብ እንዲሆን አስቀድሞ የተመደበ ይሁን ወይም የሱስ ሆን ብሎ ያወጣው (ኢሳ.
6፡1-2) ለመጀመሪያው ይፋዊ የስብከት አገልግሎቱ መዋሉ አጋጣሚ አልነበረም።
ወይም ደግሞ ሉቃስ “‘ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ’ ”
(ሉቃ. 4፡21) ሲል የዘገበው የየሱስ አጭር ስብከት ታሪክም እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ
አልነበረም።
የሱስ “ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል” የሚለውን የማርያም ድምጸት
የአገልግሎቱ አካል ማድረግ ጀመረ። የሱስ ያደርግ የነበረውንና ለማድረግ
የተዘጋጀበትን ተልዕኮ አስመልክቶ ሉቃስ የኢሳይያስን ትንቢት ተጠቅሞ ስለ
እርሱ ታሪክ ቢተርክልንም፤ ነገሩ ማርያም ከ30 ዓመታት በፊት የገለጸችውና
በሌላ መንገድ የቀረበበትም ነበር። ድኾች፣ በጉዳት ላይ የነበሩና የተጨቆኑ የተለየ
ትኩረት የተቸራቸውና የሱስ ይዞት እየቀረበ የነበረው መልካም የምሥራች ተቀባዮች
ነበሩ። የሱስ በኢሳ. ምዕ. 61 የሚገኙትን እነዚህን ጥቅሶች እንደ ተልዕኮው መገለጫ
አድርጎ ወስዷቸዋል። አገልግሎቱና ተልዕኮው ሁለቱም ማለትም መንፈሳዊና
ተግባራዊ መሆን ነበረባቸው። እኛ አንዳንዴ ከምናስበው በተቃራኒ እነዚህ ሁለቱ
እንደማይራራቁ ማሳየት ነበረበት። ለሰዎች አካላዊና ተግባራዊ ድጋፍ ማድረግ-የሱስና ደቀ መዛሙርቱ ቢያንስ በመንፈሳዊ ረገድ አገልግሎት የሚሰጡበት ክፍል
ነበር።
ጥቅሶቹን ካነበቡ በኋላ ያነጻጽሩአቸው፡ ሉቃ. 4፡16-21 እና 7፡18-23። የሱስ በዚህ
መልኩ መልስ የሰጠው ለምን ይመስሎታል? በመለኮትና በየሱስ መሲህነት ዙሪያ
ሊነሱ ለሚችሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እርስዎ እንዴት ምላሽ መስጠት ይችላሉ?
የሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲልክ የሰጣቸው ተልዕኮ ከዚህ ተልዕኮ ጋር መሳ ለመሳ
የሚሄድ ነበር። “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” (ማቴ. 10፡7) ብለው ማስታወቃቸው
እንዳለ ሆኖ “‘በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሱ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን
አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ’ ” (ማቴ. 10፡8) ሲል ተጨማሪ ትእዛዝ
ሰጥቶአቸው ነበር። የየሱስን አገልግሎት እሴቶችና መርኅዎች በስሙ እያንጸባረቁ
ለመንግሥቱ ላደማቸው ሕዝቦች መተግበር የአገልግሎታቸው አካል ነበር። ደቀ
መዛሙርቱም ቢሆኑ የተረሱትን፣ እንደ ሰው የማይቆጠሩትንና የጠፉት መቀላቀል
ነበረባቸው።
ይህን ሥራ ወሳኝ ከሆነው የሦስቱን መላእክት መልእክት ለጠፋው ዓለም
ከመስበክ ኃላፊነት ጋር ሚዛናዊ አድርገን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው?
የምናደርጋቸው ነገሮች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ “ወቅታዊውን እውነት”
ከመስበክ ጋር ዝምድና ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
ወንጌል በየሱስ የታምራት ሥራ ታሪኮች የተሞላ ነው--በተለይ በፈውስ ሥራዎቹ።
ኢሳይያስ በትንቢት እንደ ተናገረው ዐይነ ሥውሮችን ፈውሶአል አልፎ አልፎም ለብዙ
ዘመናት የአልጋ ቁራኛ የነበሩትን ሳይቀር ከደዌ እስራት ፈትቶአል (ማር. 5፡24-34፣
ዮሐ. 5፡1-15)። ከዚህ በላቀ አንካሳው ዳግመኛ እንዲራመድ፣ እንደ እርኩስ ይቆጠር
የነበረውንም ለምጻም በእጁ ዳስሶ እንዲነጻ አድርጎአል። በሰዎች አእምሮና አካል
ውስጥ የተንሰራፉ አጋንንትን ገስጾ አስወጥቶአል፣ የሞተውንም ሳይቀር አስነስቶአል።
ምናልባት እነዚህ የሠራቸው ታምራቶች ሕዝቡን ወደ እርሱ የሚስቡ፣ ለብዙዎቹ
ተጠራጣሪዎችና ነቃፊዎቹ ኃያልነቱን ያስመሰከሩ አድርገን እንወስድ ይሆናል። ይሁን
እንጂ ነገሮች ሁሌም የዚህ ዓይነት ገጽታ አልነበራቸውም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ
የሱስ ከፈወሰ በኋላ የተደረገውን ለማንም እንዳይነግሩ ያዝ ስለ ነበር ነው። ሆኖም
ፈውስ ያገኙ ሰዎች ድንቅ የሆነውን የምሥራች ለማንም ሳይተነፍሱ ለራሳቸው ብቻ
እንዳመቁ መቅረታቸው የማይሆን ነገር ይመስላል። የሱስ እነዚህ ታምራቶች በዐይን
ከመታየት የላቀ አንደምታ እንዳላቸው ለማሳየት እየሞከረ ነበር። በእርግጥ የታምራቱ
የመጨረሻ ግብ ፈውስ ያገኙት ሰብዓዊ ወገኖች እርሱን ተቀብለው የዘላለም ህይወት
ባለቤት መሆናቸው አይደል? ደግሞም የሱስ የፈጸማቸው የፈውስ ታምራቶች
የርኅራኄው መገለጫዎችም ነበሩ። ለአብነት ያህል የሱስ 5000 ሰዎችን እንዲመግብ
መንስኤ የሆነውን ማቴዎስ ሲጽፍ “ኢየሱስም ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ አይቶ
ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው” (ማቴ. 14፡14)። በጉዳት የነበሩ
ሰዎች ህመም ይሰማው የነበረው የሱስ አጠገቡ የነበሩትን ይረዳና መንፈሳቸውንም
ያለመልም ነበር።
በማቴዎስ ወንጌል የቀረበውን ይህን የኢሳይያስ ትንቢት ያንብቡ፡ ማቴ. 12፡15-21።
የሱስ ለጥቂቶች ወይም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ስላደረገው የፈውስ አገልግሎት
ኢሳይያስና ማቴዎስ በተለየ ያሳዩት መንገድ ምን ይመስላል?
“ክርስቶስ የፈጸመው እያንዳንዱ ታምራት የመለኮትነቱ ምልክት ነበር። እርሱ
ይፈጽማቸው የነበሩ ተግባራት አስቀድመው ስለ መሲህ የተነገሩ ቢሆንም፤ እነዚህ
የምህረት ሥራዎች ፈሪሳውያኑን በተጨባጭ ያስቀይሙ ነበር። በሰው ቁስል እንጨት
ስደድበት እንዲሉ የአይሁድ መሪዎች ለሰብዓዊው ሥቃይ ምላሸ ቢስ ልበ ደንዳኖች
ነበሩ። ስግብግብነታቸውና ጨቋኝነታቸው ክርስቶስ ያስገኘውን እፎይታ በብዙ
መልኩ ሥቃይና እንግልት ውስጥ የሚከት ነበር። በመሆኑም የእርሱ ታምራቶች
ለእነርሱ ግሳጼ ነበሩ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 406.
የየሱስ የፈውስ ታምራቶች የርኅራኄና የፍትሕ መገለጫዎች ነበሩ። ሆኖም
በራሳቸው የሁሉም ነገር መደምደሚያ አልነበሩም። ክርስቶስ ያደረጋቸው ነገሮች
ሁሉ አጠቃላይ ዓላማ ሰዎችን ወደ ዘላለማዊ ህይወት መምራት ነበር።
በወንጌል የተጻፉትን የየሱስ ታሪኮች ስናነብ--ለበሽተኞችና ለህጻናት የነበረው ጥንቃቄ፣ የጠፋውን ስለ መፈለግ የተናገራቸው ታሪኮች እንዲሁም ስለ መንግሥተ ሰማይ የተናገራቸው ልብ የሚያሞቁ መልእክቶች አብልጠው ወደ ደርባባ ማንነቱ ይስቡናል። እርሱን በምንመለከታቸው ሌሎች ታሪኮች ውስጥ ደግሞ ኃይለኝነቱንና እውነትን አፍረጥርጦ መናገሩን--በተለይ በዘመኑ የነበሩትን የኃይማኖት መሪዎችና እኩይ ተግባሮቻቸውን በመቃወም ያደረጋቸው ሊያስደምሙን ይችላሉ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 21:12–16፣ ማር. 11:15–19፣ ሉቃ. 19:45–48፣ ዮሐ. 2:13– 17። እነዚህ ተመሳሳይ የወንጌል ዘገባዎች በእያንዳንዱ የወንጌል ክፍል የቀረቡበት ተጨባጭ አንደምታ ምንድን ነው?
ይህ ክስተት በእያንዳንዱ ወንጌል ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ምክንያት ብዙም
አያስገርምም። ታሪኩ ተውኔታዊ፣ በድርጊት የተሞላና ጥልቅ ስሜት የሚታይበት
ነው። በገሀድ እንደቀረበው ቤተ መቅደሱ በዚህ መልክ አገልግሎት እንዲሰጥ
መደረጉ፤ ማለትም እውነተኛው አምልኮ ለመሥዋዕት በሚቀርቡ እንስሳት ግዢና
ሽያጭ መተካቱ የሱስን ክፉኛ አሳስቦት ነበር። እነዚህ መሥዋዕቶች ስለ ዓለም
ኃጢአት የሚሞተውን እርሱን እንዴት ባለ የእርክስና ተግባር እየወከሉ ነበር!
እንዲህ ያለው ቀጥተኛ ድርጊት ከዕብራውያን ነቢያት የቀደመ ተግባር ጋር ጥሩ
አድርጎ ይዛመዳል። ይህን ድርጊት አስመልክቶ በራሱ በየሱስ ወይም የወንጌል
ጸሐፊዎች ከኢሳይያስ፣ ከኤርምያስ ወይም ከመዝሙረ ዳዊት እየጠቀሱ በእያንዳንዱ
የወንጌል መጽሐፍ አስተያየት ሰጥተውበታል። የሱስ ነጋዴዎችንና ገንዘብ ለዋጮችን
ካበረረ በኋላ (ማቴ. 21፡11) ሕዝቡ የሱስን እንደ ነቢይ ስለ ተቀበለው ወደ እርሱ
መጥተው በዚያው በቤተ መቅደሱ ቅጥር በመፈወስና በማስተማር አገለገላቸው።
እነዚህ ሕዝቦች ትምህርቱን ሲሰሙና በእጆቹ ፈውስ ሲያገኙ ተስፋ በልባቸው
ማንሰራራት ጀመረ።
የኃይማኖት መሪዎች የሱስን እንደ ነቢይ ቢቀበሉትም--ለሥልጣናቸውና
ለማኅበራዊው አወቃቀር አደገኛ አድርገው ስለተመለከቱት በአለፉት ምዕተ ዓመታት
አባቶቻቸው ነቢያትን ለመግደል እንዳሴሩት፤ እነርሱም እርሱን ለመግደል ሴራ
መጎንጎን ጀመሩ (ሉቃ. 19፡47-48)።
ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ዘመን በቤተ መቅደሱ ላይ የደረሰው ችግር በአጥቢያ
ቤተ ክርስቲያኖቻችን እንዳይደርስ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባልነታችን የድርሻችንን
ለመወጣት ምን ማድረግ እንችላለን? በመንፈሳዊነት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ
ነገሮችን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ምን
ሊሆኑ ይችላሉ?
እግዚአብሔር የደኻውንና የተጨቆነውን ልቅሶ የሚያይ፣ የሚሰማና የሚያጽናና አምላክ ነው። እርሱ በየሱስ ውስጥ ሆኖ የምድራችንን የመጨረሻ ውርደት፣ ሥቃይና ኢፍትሐዊነት በሚያስገርም ሁኔታ የተቀበለ አምላክ ነው። ምንም እንኳ የየሱስ ርኅራኄና መልካምነት አንድም ሳይቀር በህይወቱና በአገልግሎቱ ተገልጦ ቢታይም፤ ከመጠን ያለፈ ጥላቻ፣ ምቀኝነትና ኢፍትሐዊነት ለሞት አበቃው። የሱስ በጌተሰማኒ የአትክልት ስፍራ ከጸለየው የጭንቀት ጸሎት አንስቶ ሲታሰር፣ ሲፈረድበት፣ ሲገረፍ፣ ሲፌዝበት፣ ሲሠቀልና ሲሞት በነበረው ቅደም ተከተል እጅግ ዘግናኝ የመከራና የጭካኔ ሂደት ውስጥ አለፈ። ይህ ሁሉ የከፋ ሥቃይ የተፈጸመው ጥፋት ባልተገኘበት፣ ንጹህና መልካም በሆነው በእርሱ ላይ ነበር፡ “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” (ፊልጵ. 2፡7-8)። ምንም እንኳ በደኅንነት መነጽር አማካይነት የሱስ ስለ እኛ የከፈለውን አስደናቂ መሥዋዕትነት በመመልከት ሐሴት ብናደርግም፤ ነገር ግን የደረሰበትን ጨካኝ ተግባርና ሥቃይ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 53፡3-6። ጥቅሶቹ ስለ በደለኞች ሲል ንጹሁ የሱስ ስለ ደረሰበት ሥቃይ ምን ይነግሩናል? ለእኛ ሲል ያለፈበትን አሰቃቂ መንገድ ማስተዋል እንድንችል ይህ እንዴት ይረዳናል?
የክፉውና የኢፍትሐዊ ፍርድ ሰለባ በመሆን ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው
እግዚአብሔር አምላክ በየሱስ ያውቀዋል። ንጹህ የሆነውን ሰው መግደል ፍጹም
የጭካኔ ተግባር ቢሆንም--እግዚአብሔርን መግደል ግን እጅግ የከፋ ነው። ምንም
እንኳ እኛ በተበጠሰና በወደቀ ሁናቴ ውስጥ ብንገኝም እግዚአብሔር ግን የእርሱን
በጎ አሳቢነት፣ ርኅራኄና ታማኝነት እንዳንጠራጠር አድርጎ ራሱን ገለጠልን፡
“በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም
ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኃጢአት አልሠራም” (ዕብ. 4፡
15)። የአምላካችን ጸባይ እንዴት ፍጹም ሆኖ ተገልጦአል! አእምሮአችን መስቀሉ
በሚወክለው መልካም የምሥራች ዙሪያ ይኸውም ስለ እግዚአብሔር እንዲያሰላስል
ማድረግ የምንጀምረው እንዴት ነው?
ለጌታ በምናደርጋቸው ነገሮች በተለይ በዕጦት ለሚገኙ ስንደርስ የሱስ ስለ
እኛ መሞቱን ያውም እገዛችን ለሚያሻቸው ምስኪኖች ጭምር መሥዋዕት
የመሆኑን እውነታ የተልዕኮአችንና የዓላማችን ማዕከል አድርገን መያዝ
የለብንም?
Read Ellen G. White, “In the Footsteps of the Master,”
pp. 117–124, in Welfare Ministry; “Days of Ministry,” pp. 29–50,
in The Ministry of Healing; “The Temple Cleansed Again,” pp. 589–
600; “In Pilate’s Judgment Hall,” pp. 723–740, in The Desire of Ages.
“እግዚአብሔር ሕጉን የሚተላለፉትን እንደሚቀጣ የሚያመላክት ወሳኝ ቃል
በማስረጃነት ሰጥቶአል። እርሱን በኃጢአተኞች ላይ ፍርድ እንደማይሰጥ እጅግ መሐሪ
አድርገው ራሳቸውን የሚሸነግሉ ቀራኒዮ መስቀል ላይ የሆነውን መመልከት ብቻ
ይበቃቸዋል። ኃጢአት ያልተገኘበት የእግዚአብሔር ልጅ ሞት ‘የኃጢአት ደመወዝ
ሞት’ መሆኑን ይመሰክራል። እያንዳንዱ በአምላካዊው ሕግ ላይ የሚፈጸም ጥሰት
ጻድቅ ፍርድ መቀበሉ የግድ ይሆናል። ኃጢአት የማያውቀው ክርስቶስ ስለ ሰዎች
ኃጢአት ሆነ። ሐዘን ልቡ እስኪሰበርና ህይወቱ እስኪቀጭ የበደለኛውን መተላለፍ
ተሸከመ፣ የአባቱም ፊት ከእርሱ ተሰወረ። ኃጢአተኞች ይቤዡ ዘንድ እነሆ ይህ ሁሉ
መሥዋዕትነት ተከፈለ። ከዚህ ውጪ በምንም መንገድ ሰብዓዊው ፍጡር ከኃጢአት
መቀጮ ነፃ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ያለ ዋጋ ተከፍሎ የቀረበውን ሥርየት ተካፋይ
ለመሆን እንቢ የሚል ማንኛውም ነፍስ የበደለኝነቱንና የመተላለፉን ቅጣት በራሱ
መቀበሉ የግድ ይሆናል።”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp.
539, 540.
1.ከላይ የቀረበውን የኤለን ኋይት መግለጫ ያንብቡ። በተጨባጩ ኢፍትሐዊነት
ዙሪያ ማለትም አንዳችም ኃጢአት ያልተገኘበት ክርስቶስ እንደ በደለኛ
ተቆጥሮ ስለ ተቀበለው ቅጣት ተነጋገሩ። ይህን ወሳኝ እውነት ሁሌም
ከፊታችን ማስቀደማችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2.የሱስ በተደጋጋሚ ይጠቅስ የነበረውን “መንግሥት” ለማምጣት የፖለቲካ
ተሐድሶ እንዲደረግ የተከራከረበት አጋጣሚ ፈጽሞ አልነበረም። ለነገሩ ዓለም
ለተጨቆኑና ለተበዘበዙ ፍትሕ እናሰፍናለን፣ እኩልነት እናመጣለን በሚል
መፈክር ባነሷቸው ብጥብጦችና ሁከቶች መልሰው ጨቋኝና አምባ ገነን
በሆኑባቸው አሳዛኝ ታሪኮች የተሞላች ናት። አንደኛው ጨቋኝ ሌላውን ጨቋኝ
ገልብጦ ሥልጣን ላይ ሲወጣ መመልከት የተለመደ ክስተት ነው። ምንም
እንኳ ክርስቲያኖች የተጨቆኑትን ለመርዳት በሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር
በአንድ ላይ መሥራት የሚችሉና የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፤ ሁሌም ቢሆን
ፖለቲካን ተጠቅመው እነዚህን ነገሮች ለማሳካት ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው
ለምንድን ነው?
3.የደኅንነት እቅድ የሱስን ስለ ጠየቀው ነገር ያስቡ። ጻድቁ የሱስ ጻድቅ
ላልሆንነው ስለ እያንዳንዳችን ሲል ሥቃይ ተቀበለ። ይህ ስለ እኛ የተከፈለ
ታላቅ መሥዋዕትነት በክርስቶስ አዲስ ሕዝቦች የሚያደርገን እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡ በወንጌል ላይ የተዋወቅነው የየሱስ አገልግሎት ከብሉይ ኪዳን
ነቢያት ሥራ ጋር ተጣቅሶ ተብራርቶአል። የወንጌል ለድኾች መሰበክ፣ የተጨቆኑ
አርነት መውጣትና መንፈሳቸው ለተሰበረ የቀረበው ፈውስ የመሲህ አመላካች
ሆነው በይፋ ተነግረዋል። ይህ ደግሞ የሱስ በመላው አገልግሎቱ ያሳየው
እውነታ ነው። ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት ለሆነው ለየሱስ ኢፍትሐዊ ሞት
ምስጋና ይግባውና በደላችን ይቅር መባል የሚችል ሆነ፤ የዘላለማዊ ህይወት
ተስፋ ባለቤቶች ለመሆንም በቃን።