“ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ…”
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሐምሌ 20-26

5ኛ ትምህርት

Jul 27 - Aug 02




የነቢያት ልቅሶ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ሳሙ. 8:10–18፣ አሞጽ 5:10–15፣ ሚክ. 6:8፣ ዘፍ. 19:1–13፣ ሕዝ. 16:49፣ ኢሳ. 1:15–23።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን? (ሚክ. 6፡8)።

ከ መጽሐፍ ቅዱስ መሳጭ ገጸ ባህሪያት መካከል የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይጠቀሳሉ። ነቢያቱ ሁሌም በህዝቡ መሃል መሆናቸው ምቾት ባይሰጣቸውም እንኳ፤ ጎርናና ድምፃቸው፣ በድፍረት የተሞሉ መልእክቶቻቸው፣ ሐዘናቸው፣ ንዴታቸውና ቁጣቸው--በጣም አልፎ አልፎ የሚሰጧቸው መልእክቶች አፈጻጸም ችላ ሊባሉ የማይችሉ ሰዎች አድርጓቸው ነበር።

በቅድሚያ ወደ እስራኤልና ይሁዳ የተላኩት ነቢያት የተመረጡት ሕዝቦች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ነበር። ሕዝቡና መሪዎቹ በአጎራባች አገሮች ጣኦት እና አጓጉል የአኗኗር ስልት በቀላሉ ተነድተው ይወሰዱ ነበር። አንዳንዴ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያስታወሷቸው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ ሕዝቡ ያደረጋቸውን አስደናቂ ተግባራት እየጠቀሱ፣ መረር ሲል--ሊከተሏቸው የሚችሉትን ውጤቶች በማሳየትና በማስጠንቀቅ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ማድረግ የውለታ ቢሶቹ ነቢያት ፈታኝ ኃላፊነት ነበር።

ነቢያት በኃጢአትና ክፉ ተግባራት ዙሪያ ለመሪዎችና ለሕዝቡ ከሚሰጧቸው ማስጠንቀቂያዎች ጎን ለጎን የድኾች ጭቆና እና አይዟችሁ ባይ ረዳት የሌላቸው ምስኪኖች ጉዳይ ከፍ ያለ አጽንኦት የሚሰጣቸው ነበሩ። ጣኦት ማምለክ ስህተተት ነው? አዎ! ሐሰተኛ ኃይማኖታዊ ልማዶችን መከተልስ? አዎ ስህተት ነው! በደካሞችና በድኾች ላብ ያላግባብ መበልጸግ ለኩነኔ ይዳርግ ይሆን? አዎ!

ሐምሌ 21
Jul 28

ስለ ፍትሕ ያለማሰለስ የሚቀርብ ጥሪ


የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በግልጽ ዘርዝሮ ካስቀመጣቸው ዕቅዶች አኳያ ማለትም እንደ መጠራታቸው አልተመላለሱም። እግዚአብሔር በሰጣቸው የተስፋ ምድር ተቋቁመው ገና ብዙ ዘመን እንኳ ሳይኖሩ “‘ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ’” (1ሳሙ. 8፡5) የሚመራቸው ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ነቢይ እና ፈራጅ የነበረውን ሳሙኤል ጠየቁት።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ሳሙ. 8፡10-18። ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለሳሙኤል ላቀረበው ጥያቄ የሳሙኤል ማስጠንቀቂያ ምን ነበር?



ሳሙኤል ይህን ድርጊት ሌሎች ሕዝቦችን ለመምሰል ከሚደረግ እንቅስቃሴ አኳያ ተመልክቶት ነበር። ሳሙኤል የመጀመሪያውን ንጉሥ ይኸውም ሳኦልን ለማማከር ተመኝቶ የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ትንቢቱ ሰምሮ ወደ ተግባር እስኪለወጥ ምንም ያህል ጊዜ አልወሰደም። የእስራኤል መንግሥት በአስገራሚ ከፍታ ላይ በነበረባቸው የዳዊትና የሰሎሞን ንግሥና ዘመናትም እንኳ ከንቅዘትና ሥልጣንንን ያላግባብ ከመጠቀም ፈተና አላመለጡም ነበር።

በመላው የእስራኤልና ይሁዳ ግዛት ነገሥታት ዘመን እግዚአብሔር አምላካዊውን ፈቃድ የሚናገሩ ነቢያትን እየላከ የእስራኤል መሪዎችና ሕዝቡ ስለ ተረሱትና ስለ ተዘነጉት የማኅበረሰብ አባላት የሰጣቸውን ኃላፊነቶች ያስታውሳቸው ነበር። እስራኤላውያን በጽድቅ እንዲመላለሱና በሕብረተሰቡ መሃል ፍትሕ እንዲያደርጉ የሚማጸን ያላሰለሰ ጥሪ በዕብራውያን ነቢያት መልእክቶች ውስጥ እናገኛለን። የእስራኤልንና የመሪዎቿን አመጽ ፊት ለፊት ይጋፈጡ የነበሩት ነቢያት ድምጻቸው ለማይሰማ ምስኪኖች ሁሌም ድምጽ ነበሩ--በተለይ እስራኤላውያን አምላካዊውን ፈቃድ ከመታዘዝ ሲያፈነግጡ በቀላሉ ለጉዳት ለሚጋለጡት።

እንደነ አብርሃምና ኢያሱ ያሉት ጥልቅ ስሜት የተንጸባረቀባቸው የብሉይ ኪዳን ነቢያት--ፍትሕ በአፋጣኝ እንዲሰፍን ያቀረቡት ጥሪ ከእኛ ዘመን ዳተኝነት በእጅጉ ይቃረናል፡ “በወቅቱ ነቢያቱን አሳቅቀው የነበሩ ጉዳዮች ዛሬ የዓለማችን የዕለት ከዕለት ክስተቶች ናቸው. . . ትንፋሻቸውን ቀጥ ያደረገውና ትዕግሥታቸውን ያሟጠጠው ኢፍትሐዊነት እኛን ብርክ ባስያዘ ነበር። ያለማቋረጥ ገቢራዊ እየሆኑ ላሉ የኢፍትሐዊነት መገለጫዎች ማለትም--ግብዝነት፣ ዋሾነት፣ ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባራት፣ ሥቃይና መከራ፣ አልፎ አልፎ ከመበሳጨት ውጪ ደስተኞች ለመሆናችን እኛ ራሳችን ምስክሮች ነን። ኢምንት የተባለው ኢፍትሐዊነት እንኳ ሳይቅር በነቢያቱ ዘንድ ግዙፍ ትኩረት ይቸረው ነበር።”—The Prophets (New York: Jewish Publication Society of America, 1962), pp. 3, 4. እነዚህ ነቢያት የእግዚአብሔርን ልብ እና አእምሮ ገልጠው ያሳዩናል። እግዚአብሔርን በመወከል እየተናገሩ ዕንባ ባቀረሩ አምላካዊ ዓይኖች የዓለማችንን ኢፍትሐዊነትና ሥቃይ መመልከት እንድንችል ይረዱናል። ደግሞም ይህ ጥልቅ ስሜት--ወደ ተግባር ገብተን ከጌታ ጋር እየሠራን በጭቆና እና በሐዘን ተቆራምደው በዙሪያችን ለሚገኙ ምስኪኖች እፎይታ እንድናስገኝና መፍትሔ እንድንሆነ የቀረበልን ጥሪ ነው። አንዳንዴ በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት በሚያስከትሉ ማለትም “‘ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት’” ለመሆን የመመኘታችን ነገር ምን ይመስላል?

ሐምሌ 22
Jul 29

አሞጽ


“አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘እኔ እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤’ እግዚአብሔር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ፣ “ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ” ’ ” (አሞጽ 7፡14-15)

አሞጽ የእግዚአብሔር ነቢይ ለመሆን ጉድለቶች እንዳሉት ከመናገር ወደ ኋላ ያላለ ግልጽ ሰው ነበር። ሆኖም መልእክቱን ለእስራኤላውያን ሲያቀርብ አድማጮቹን ለመሳብ የሚያስችል በግልጽ የሚታይ ችሎታ እንዳለው ማስመስከር ችሎ ነበር። አሞጽ ለእስራኤል አጎራባች የነበሩት--ሶርያ፣ ፍልስጥኤም፣ ፊንቄ፣ ኤዶም፣ አሞንና ሞዓብ አንድ በአንድ በሚጠቅስበትና ስለ ወንጀላቸው፣ ጭካኔ የተሞላ ድርጊታቸውና ግፋቸው እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው በሚያወሳበት ዝናን ያተረፈ መልእክቱ ጽሑፉን ይጀምራል (አሞጽ 1፡3-2፡3)። እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ በቀረበው የክስ ማስረጃ ማጨብጨባቸውን ለመገመት ብዙም አይከብድም-በተለይ አብዛኞቹ ወንጀሎች በቀጥታ ያነጣጥሩ የነበረው በራሳቸው በእስራኤላውያን ላይ ከመሆኑ አኳያ።

በመቀጠል አሞጽ ቀስ በቀስ ፊቱን ወደ አገር ውስጥ ጉዳይ ይመልስና የእስራኤል ደቡባዊ አጎራባች በሆነውና ከእስራኤል ተነጥሎ በነበረው በይሁዳ ግዛት ላይ አምላካዊው ፍርድ እንደሚሰጥ ያውጃል። እግዚአብሔርን በመወከል የሚናገረው አሞጽ ይህን አምላክ መቃወማቸውን በመጥቀስ፤ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ አሻፈረኝ ማለታቸውንና ያንን ተከትሎ ስለሚመጡት ቅጣቶች ያወሳል (አሞጽ 2፡4-5)። አሞጽ በዙሪያቸው የነበሩ ሕዝቦች ያደርጉ የነበረውን ስህተት መጠቆሙን ተከትሎ የሰሜናዊ ግዛት ሕዝቦች አሁንም ደስ መሰኘታቸውን መገመት እንችላለን። የተቀረው የመጽሐፉ ክፍል በእስራኤል ይተገበሩ በነበሩ ክፉ ተግባራት፣ ጣኦት አምልኮ፣ ኢፍትሐዊነትና ተደጋጋሚ ውድቀቶች ዙሪያ ትኩረት ያደርጋል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ አሞጽ 3:9–11፣ 4:1-2፣ 5:10–15፣ 8:4–6። ስለ የትኛው ኃጢአት ነው ማስጠንቀቂያ የተሰጠው?



አሞጽ በመልእክቱ የተጠቀማቸው ቃላት ዲፕሎማሲያዊ አለመሆንና የማስጠንቀቂያዎቹ ክብደት--አምላካዊውን ጥሪ እጅግ ጽኑ ያደርጉታል። ይህ ደግሞ ወደ ልቦና መመለስና በመካከላቸው ላሉ ድኾች ጥንቃቄ ማድረግን ያካትታል፡ “ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ” (አሞጽ 5፡24)። የትንቢተ አሞጽ የመጨረሻዎቹ ጥቂት ቁጥሮች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደፊት ወደሚያገኙት ደኅንነት ያመላክታሉ (አሞጽ 9፡11-15)። “ሕዝቡ ጥልቅ በሆነ ክህደትና ታላቅ እጦት ላይ በነበረበት ሰዓት--እግዚአብሔር አምላክ የይቅርታና የተስፋ መልእክት ሰጣቸው።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 283. የተሳሳተውን ለማረም ጥብቅ ቃላት ለመጠቀም የተዘጋጀንባቸው አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆን? እነዚህ ቋንቋዎች ተገቢ የሚሆኑባቸውን ጊዜያቶች ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 23
Jul 30

ሚክያስ


“ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን? (ሚክ.6፡8)።



ይህ ጥቅስ ምናልባት በመጽሐፍ ቅዱስ አብልጠው ከሚታወቁ ጥቅሶች መሃል አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሆኖም ሌሎች ጥቅሶችን አዘውትረን እንደ ማስታወቂያ ወይም ፖስተር የምንጠቀመውን ያህል ይህንንም በተመሳሳይ ጥቅም ላይ አለማዋላችን ምናልባት ከጥቅሱ ዐውድ ጋር ያለን ቁርኝት እናስተውለዋለን ብለን ከምንገምተው በታች ሊሆን ይችላል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሚክ. 2:8–11፣ 3:8–12። ሕዝቡ ያደርግ የነበረውና ሚክያስ ያወገዘው ነገር ምን ነበር?



የእግዚአብሔር ሕዝቦች በታሪካቸውም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ወደ አዲስ ዝቅታ ሲወርዱ የታየበት ክስተት ቢኖር የአካዝ በይሁዳ መንገሥ ነበር። የጣኦት አምልኮና ያንን ተከትለው የመጡ ልዩ ልዩ የእርክስና ተግባራት እየተስፋፉ መሄድ ጀመሩ። በተመሳሳይ በወቅቱ የነበሩ ሌሎች ነቢያት ጭምር እንደ ተገነዘቡት ከሆነ ድኾች አስከፊ የጭቆና ቀንበር መሸከማቸውና የሌሎች መጠቀሚያ መሆናቸው ቀጥሎ ነበር።

ሚኪያስ በዘመኑ ከነበሩ የአምላካዊውን ቁጣ ነጋሪ ነቢያት ያነሰ መልእክተኛ አልነበረም። ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች መካከል አብዛኞቹ--ሕዝቡ የፈጸመውን የእርክስና ተግባርና ይህን ተከትሎ የመጣውን አምላካዊ ቁጣ እና ሐዘን እንዲሁም በመንገዳቸው እየመጣ የነበረውን ጥፋት የሚገልጹ ናቸው። ይህም ሆኖ እግዚአብሔር ግን በሕዝቡ ተስፋ አልቆረጠም ነበር። የነቢያቱ ጎርናና ድምጾችና ጥብቅ መልእክቶች እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍላጎት ያልተገታ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው። ስለዚህ ጌታ ለእነርሱ ካለው ፍቅርና ጥንቃቄ የተነሳ ማስጠንቀቂያዎቹን ሰጣቸው። እግዚአብሔር ይቅር ሊላቸውና ወደ ቀደመው ንጽህና ሊመልሳቸው ናፈቀ። እነሆ እርሱ ከዚህ በኋላ ለዘላም አይቆጣም (ሚክ. 7፡18-20)። ይህ በብዙዎች የሚታወቀው--በጽድቅ የመመላለስ፣ ምኅረትን የመውደድ፣ በትህትና የመራመድ “ቀመር” ዐውድ ነው። ላይ ላዩን ሲያዩት ቀላል ሊመስል ቢችልም፤ ነገር ግን በተጨባጭ እንዲህ ያለውን የእምነት ህይወት መኖር ብርቱ ተግዳሮት የበዛበት ነው--በተለይ ይህን ማድረግ ከማኅበረሰቡ የሚያገልል ሆኖ ሲሰማ። ሌሎች በምኅረት እየተሳለቁና በትዕቢት እየተራመዱ ከኢፍትሐዊነት አትራፊ በሚመስሉበት ድባብ በጽድቅ መመላለስ፣ ምኅረትን መውደድና በትህትና መራመድ ወኔ እና ጽናት ይጠይቃል። አንድ በእርግጠኝነት መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ይህን መንገድ ስንመርጥ ብቻችንን አንጓዝም። አምላካችን እግዚአብሔር አብሮን አለ።

በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ በመመላለስ፣ ምኅረትን በመውደድና በትህትና በመራመድ መሀል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

ሐምሌ 24
Jul 31

ሕዝቅኤል


ስለ “ሰዶም ኃጢአት” ምንነት ለተወሰኑ ክርስቲያኖች ጥያቄ ብናቀርብ ከጥፋቱ አስቀድሞ የተፈጸሙትን ልዩ ልዩ የዝሙት እና የርኩሰት ተግባራት ጠቅሰው የሚያስረዱ ብዙዎች ናቸው። ለነገሩ ዘፍ. 19፡1-13 ከሚሰጠን ሥዕላዊ ዘገባ አኳያ ማኅበረሰቡ ይገኝበት የነበረው የርኩሰት ደረጃ አፋጣኝ ውሳኔ የሚሻ እንጂ እሹሩሩ የሚባልበት አልነበረም።

የሚገርመው ነገር መልሱ ከታሰበው ይልቅ በጣም ውስብስብ ነው። “ ‘ “እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር” ’ ” (ሕዝ. 16፡49)። ጌታ በከተማዋ ውስጥ ይስተዋል የነበረውን ሌላውን ዓይነት የዐመጻ ተግባር ችላ አለማለቱ በግልጽ የሚታይ ነበር። እዚህ ላይ የሕዝቅኤል ትኩረት በኤኮኖሚ ኢፍትሐዊነትና በድኽነት የሚማቅቁ ምስኪኖች ዙሪያ ማነጣጠሩን ልብ ይሏል። በእግዚአብሔር ዐይን፤ እነዚህ ከኤኮኖሚ ጋር ቁርኝት ያላቸው ኃጢአቶች እንደ ዝሙቶቹ ሁሉ የከፉ ነበሩ?

ሕዝቅኤል ከአሞጽ፣ ከሚክያስና ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ የመጣ ነቢይ እንደመሆኑ የእርሱ የቀደሙ ትንቢቶች እየመጣ ስለነበረው ጥፋት የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። ሆኖም የሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ ከወደቀችና ሕዝቦቿ በግዞት ከተወሰዱ በኋላ የሕዝቅኤል ትኩረት እግዚአብሔር እነርሱን ነፃ ሕዝብ አድርጎ መልሶ በሚያቋቁምበት ተስፋ ዙሪያ ያነጣጠረ ሆነ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሕዝ. 34፡2-4፣ 7-16። እግዚአብሔር ብልሹ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን የእስራኤል መሪዎች ከመንጋው አኳያ የገመገመበትን መንገድ ያስተያዩ። “ደካማ” የሆነውን በግ ያስተናገዱበት መንገድ ከእርሱ ዘዴ ጋር እንዴት ይነጻጸራል?



ከሰዶም ጋር ተነጻጽረው መቅረባቸው ምን ያህል የከፋ ሁናቴ ላይ ይገኙ እንደነበር ቢያመላክትም፤ ጌታ ግን ከእርክስና መንገዳቸው ይመለሳሉ ብሎ ተስፋ በማድረግ እነርሱን ከመቅረብ አልተገታም ነበር። እግዚአብሔር የሩሳሌምን ወደ ቀድሞው ሁኔታዋ ለመመለስና ቤተ መቅደሱንም እንደገና ለመገንባት የሚያስችል ዕቅድ ዳግመኛ አውጥቶ ነበር። በእግዚአብሔር የተሰጧቸው ክብረ በዓላት ዳግመኛ መከበር ይጀምራሉ፤ ምድሪቱም እንደየ ትውልዳቸው ለሁሉም እኩል፣ እኩል ትከፋፈላለች (ሕዝ. 47፡13-48፡29)። ቀደም ሲል እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲወጡ በመጀመሪያ ለሙሴና ለእስራኤል ሕዝብ ግልጽ የተደረገው ዕቅድ አሁንም ሕዝቡ ከግዞት ሲመለስ ይተገበር ዘንድ አምላካዊው ፍላጎት መሆኑ ግልጽ ይመስላል። ይህ ደግሞ ለደካማው የሕብረተሰብ ክፍል እና ለመጻተኛው መቆርቆርን ያካትታል። እግዚአብሔር የተሻለ ምርጫ ማድረግ እየቻሉ በተሳሳተ መንገድ ለሄዱ ሕዝቦች ሳይቀር ሁለተኛ ዕድል የሚሰጥ አምላክ መሆኑ ለእርስዎ ምን ትርጉም አለው?

ሐምሌ 25
Aug 01

ኢሳይያስ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1:15–23፣ 3:13–15፣ 5:7-8። ነቢዩ ዙሪያውን ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ ለተመለከተው ነገር የሰጠውን ምላሽ እንዴት ይገልጹታል?



የኢሳይያስ መልእክት መክፈቻ የሆኑት የመጀመሪያዎቹ አምስት ምዕራፎች መረር ያለ ሒስ ቀላቅለው ይዘዋል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምላካቸውን ፈቃድ እንደተቃወሙና የክፋት ድርጊታቸውን የሙጥኝ ብለው እንደያዙ፤ መሆን የማይገባቸው ዓይነት ሕዝቦች መሆናቸውን ከገፉበት አይቀሬው ፍርድ እንደሚከተል--ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በህይወታቸውና በማኅበረሰባቸው ላይ ተሐድሶ ካመጡ ግን ተስፋ ተሰጥቶአቸው ነበር። ምናልባት ጥልቅ የሐዘን ስሜት የሚፈጥሩ ቃላት በኢሳይያስ መልእክቶች ይደመጡ ይሆናል። ኢሳይያስ እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነና ለሕዝቡ የሚሻው ምን እንደሆነ ካለው አረዳድ አኳያ--ስለ ጠፋው ነገር፣ በጉዳት ላይ ላሉና ለተረሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች፣ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ ሊመጣ ስላለው ፍርድ እያሰበ በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ነበረ።

ትንቢታዊ አገልግሎቱን በዚሁ መንገድ የገፋው ኢሳይያስ፤ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገር መለስ ብለው ያስታውሱ ዘንድ ሕዝቡን አጥብቆ ያበረታታል። በተጨማሪ እግዚአብሔር ወደ ፊት ሊያደርግላቸው ስላቀደው ነገር ተስፋ ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ጌታን አሁኑኑ አጥብቀው መሻታቸው ወሳኝ ነበር። ይህ ከእርሱ ጋር የሚመሰርቱት የታደሰ ግንኙነት እየፈጸሙ የነበረውን የተሳሳተ ድርጊት ጨምሮ በሌሎች ላይ የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲለውጡ ጭምር የሚያደፋፍር ነበር።

ኢሳይያስ በምዕ. 58 እና 59 መልእክቱ ፊቱን በተለይ ወደ ፍትሕ ጉዳይ ይመልሳል። “ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቆአል፤ ጽድቅም በሩቁ ቆሞአል፤ እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሎአል፤ ቅንነትም መግባት አልቻለም” (ኢሳ. 59፡14)። እግዚአብሔር በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዳለው አጽንኦት የሚሰጠው ኢሳይያስ፤ ሕዝቡን ሊታደግ “አዳኝ… ይመጣል” (ኢሳ. 59፡20) ሲል ይናገራል። የመሲህን መምጣት ማወጅ--በመላው ትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ አበይት ትኩረት የተቸረው ክፍል ነው። እርሱ ፍትሕ የማስፈን፣ ምሕረት የማድረግ፣ የፈውስ እና ወደ ቀድሞ ንጽህና የመመለስ ተግባራትን በማከናወን አምላካዊውን የበላይነት ዳግመኛ ያረጋግጣል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 9:6-7፣ 11:1–5፣ 42:1–7፣ 53:4–6። እነዚህ ትንቢቶች ስለ የሱስ ህይወት፣ አገልግሎትና ሞት ካሎት አረዳድ ጋር እንዴት ይዛመዳሉ? ትንቢቶቹ ወደዚህ ዓለም ስለ መምጣቱ ዓላማ ምን ይጠቁማሉ?

ሐምሌ 26
Aug 02


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “The Assyrian Captivity,” pp. 279–292; “The Call of Isaiah,” pp. 303–310, in Prophets and Kings. “በግልጽ የተመለከተውን ጭቆና፣ በከፋ ሁኔታ ላይ የነበረውን ኢፍትሐዊነት፣ ያልተለመደውን ቅንጦትና ብኩንነት በማውገዝ ከቀረበው መልእክት ባሻገር--ነቢያት በዘመናቸው ስለተስተዋለው ሐፍረተ-ቢስ ጾምና ሰካራምነት፣ አጸያፊ ዘማዊነትና ሴሰኝነት ድምጾቻቸውን ከፍ አድርገው ቢጮኹም፣ ተቃውሞአቸውም ሆነ ኃጢአትን ማውገዛቸው እንዲያው በከንቱ ነበር።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 282.

“በወቅቱ ሕዝቡ ይገኝበት የነበረው ማኅበራዊ ሁኔታ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ እንደ ነበር ኢሳይያስ ተመልክቶአል። ሰዎች የግል ሐብት ለማካበት ከነበራቸው ጥልቅ ምኞት የተነሳ በቤት ላይ ቤት፣ በመሬት ላይ መሬት ለመደራረብ ቀን ከሌት እንቅልፍ አልነበራቸውም. . . ፍትሕ ተጣመመ፣ ለድኾች ማዘንና ርኅራኄ ማድረግ አከተመ. . . ሌላው ቀርቶ ለረዳት ዐልባው ዘብ የመቆምና አለኝታ የመሆን ኃላፊነት የነበራቸው ገዢዎች ሳይቀሩ በድኾች፣ በመበለቶችና አባት በሌላቸው ህፃናት ላይ ለደረሰው ቀውስ ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ. . . “በዖዝያን ንግሥና የመጨረሻዎቹ ዓመታት ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን የማስጠንቀቂያና ግሳጼ መልእክቶች ይዞ ወደ ይሁዳ እንዲሄድ ጥሪ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን ኃላፊነቱን ሳይወጣ ቀረ።”—Pages 306, 307. “እነዚህ በነቢያት የቀረቡ ግልጽ ተማጽኖዎች. . . እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነፍስ የሚያቀርበው የጥሪ ድምፅ ሆነው በእኛም ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ ይገባል። የቀደመውን ቅን የክርስትና አካሄድ እየተጠቀምን፤ ሸክም ለበዛባቸውና ለተጨቆኑ ምኅረት ለማድረግ የሚያስችለንን ማንኛውንም መልካም አጋጣሚ በከንቱ ማሳለፍ የለብንም።”—Page 327.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.የትንቢት ተግባር የወደፊቱን መተንበይ እንደሆነ አብልጠን እናስተውላለን። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ለኖሩበት ዓለም የሰጡት ትኩረት--በነቢያቱ ሚና ዙሪያ ያሎትን ግንዛቤ የሚለውጠው እንዴት ነው?

2.ለእውነት መቆም ምን የህል አስቸጋሪና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የነቢያቱ ህይወትና መልእክት በጉልህ ያሳያል። ነቢያቱ የተናገሯቸውም ሆኑ ያደረጓቸው ነገሮች እነዚያው የተገለጹት መሆናቸውን ለምን ያምናሉ?

3.እግዚአብሔር አንዴ ሲቆጣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሕዝቡ ሲጨነቅ የሚያሳዩ ተፈራራቂ ጽሑፎች በነቢያቱ ቀርበዋል። እነዚህን ሁለት ገጽታ ያላቸውን አምላካዊ ጸባዮች እንዴት በአንድ ማቅረብ ይችላሉ?

ማጠቃለያ፡ በተደጋጋሚ ሲቆጡና ሲበሳጩ የሚታዩት የብሉይ ኪዳን ነቢያት ለእግዚአብሔር ፈቃድ ጠበቆችና ቀናኢ ተቆርቋሪዎች ነበሩ። ይህ ለድኾችና ለተጨቆኑ ፍትሐዊ ትኩረት እንዲቸር የሚጠይቅ ጥልቅ ስሜት የራሱን የእግዚአብሔር ሥጋት የሚያንጸባርቅ ነበር። ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ በነቢዩ የቀረበው ጥሪ ኢፍትሐዊነት እንዲያከትም የሚጠይቅም ነበር። ይህ ደግሞ ስለ ሕዝቡ የተሻለ የወደፊት ሕይወት ሲል እግዚአብሔር እንደሚተገብረው በራእይ ቃል የገባው ነገር ነበር።