ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 9:7–9፣ 13– 20፣ መዝ. 82፣ መዝ. 101፣ መዝ. 146፣ ምሳ. 10:4፣ ምሳ. 13:23፣ 25፣ 30:7–9።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “ለዐቅመ ቢሶችና ለድኻ አደጎች ፍረዱላቸው፤ የችግረኛውንና የምስኪኑን መብት አክብሩ። ወገን የሌለውንና ችግረኛውን ታደጉ፤ ከግፈኛውም እጅ አስጥሏቸው” (መዝ. 82፡3-4)።
መ
ዝሙረ ዳዊት እና መጽሐፈ ምሳሌ እንደው በአምልኮ ጊዜ ወይም በሌሎች
ኃይማኖታዊ መርኀ ግብሮች ሳይሆን በተለመደው የዕለት ከዕለት ህይወት
ከእግዚአብሔር ጋር የመኖርን ተሞክሮ ያካፍሉናል። መጽሐፈ ምሳሌ ከግንኙነት
እና ቤተሰብ እስከ ንግድ ብሎም የመንግሥት አሠራር ልዩ ልዩ ተጨባጭ የጥበብ
አማራጮችን ሲሰጠን--የመዝሙር መጽሐፍ ደግሞ ከሐዘን እንጉርጉሮ እስከ
የእልልታ ምስጋና ያካተቱ የተለያዩ ስሜቶች እና መንፈሳዊ ተሞክሮዎች ስብስብ
የሆኑ መዝሙሮችን ይዞአል። እግዚአብሔር ስለ እያንዳንዱ የህይወታችን ሁኔታ ግድ
የሚለው አምላክ ከመሆኑ አኳያ እምነታችን በእያንዳንዱ ገጽታና ተሞክሮ ልዩነት
ሲያመጣ መመልከት እምብዛም ላይከብድ ይችላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ በወደቀ ዓለም ማንኛውም የህይወት ነጸብራቅ የሰው
ልጅ ሁኔታ ላይ የተንሰራፋውን የፍትሕ መጓደል ችላ ብሎ ማለፍ አይችልም።
በእርግጥ ኢፍትሐዊነትን አስመልክቶ ጌታ ለወገኖቹ ጥንቃቄ እንደሚያደርግና
ችግሩን ለማስታገስ እንደሚመኝ በተደጋጋሚ ገተልጾአል። ተስፋ ለሌላቸው ተስፋ
የሆነው እነሆ እርሱ ነው።
ምንም እንኳ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በመጻሕፍቱ የቀረቡትን ሀሳቦች ገረፍ አድርገን
ብቻ የምናልፍ ቢሆንም፤ ምናልባት በዙሪያችን የሚገኙ ድኾችን፣ የተጨቆኑትንና
የተረሱትን ከማገልገል ብሎም ከመርዳት ግዴታ አኳያ የቀረበው ይህ ትምህርት
ይበልጥ ወደ ተግባር እንዲገቡ ያነሳሳዎ ይሆናል።
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው እግዚአብሔር በችግርና በሥቃይ ውስጥ ያሉ
ወገኖችን ይመለከታል፣ ይሰማልም። በእግዚአብሔር እየታመኑ ነገር ግን የፍትሕ
መጓደል የገጠማቸውን ወገኖች የልቅሶ ድምፅ በመዝሙረ ዳዊት በተደጋጋሚ
እንሰማለን። የአምላካዊው በጎነት፣ ፍትሕ እና ብርቱነት በተቃራኒው በተሰለፈ
ኢፍትሐዊነትና ጭቆና ስር የወደቀ መስሎ በመዝሙሮቹ ድምጽ ውስጥ ይሰማል።
አዎ፤ ዛሬም በመዘመር ላይ ያሉት እነዚሁ መዝሙሮች ናቸው። የወገኖች ህይወትም
ሆነ እምነት እነሆ ዛሬም አለ እንጂ አልጠፋም። አሁንም ተስፋ አለ። ክፉው ባለ ድል
ከመሆኑ በፊት፣ የተጨቆኑት ሊሸከሙ ከሚችሉት በላይ በሚጫንባቸው መከራ
ከመጥፋታቸው አስቀድሞ--ጉዳዩ ከቁጥጥር ሳይወጣ እግዚአብሔር ጣልቃ ይገባ
ዘንድ ነጋ ጠባ ይወተወታል። የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ በእነዚህ ወገኖች የእምነት
ማረጋገጫ እና በህይወት ፈተና መካከል ያለውን ክፍተት ለማገናኘት የሚሞክር
ይመስላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 9፡7-9፣ 13-20። ባለ መዝሙሩ ዳዊት እነዚህን ስንኞች
ሲጽፍ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደ ነበር ለመገመት ይችላሉ? በእግዚአብሔር
መልካምነት እና ዳዊት በወቅቱ በነበረው ተሞክሮ መካከል ያለው ውጥረት ሊሰማዎ
ይችላል? ጽኑ ፈተና በገጠሞት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያሎትን እምነት ጠብቀው
እንደያዙ ማለፍ የቻሉት እንዴ ነበር?
የእግዚአብሔር መልካምነትና ጻድቅ ፍርድ--ተስፋና ኪዳን ለዚህ ውጥረት ምላሽ
በመሆን በመዝሙረ ዳዊት በተደጋጋሚ ቀርቦአል። ክፋትና ኢፍትሐዊነት ለጊዜው
አሸናፊ ቢመስሉም፤ እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችንና አመጸኞችን ይዳኛል። ጉዳት
የደረሰባቸውና የተጨቆኑ ሲነጹና ወደ ቀደመው ንጽህና ሲመለሱ አመጸኞች ግን
ፍርዳቸውን ያገኛሉ።
ሲ. ኤስ. ልዊስ በመባል የሚታወቁ ጸሐፊ ሪፍሌክሽንስ ኦን ዚ ሳልምስ በሚለው
መጽሐፋቸው በመዝሙር መጽሐፍ በተደጋጋሚ በተገለጠው አምላካዊውን ፍርድ
መናፈቅ ዙሪያ በመጀመሪያ የተሰማቸውን አግራሞት ይገልጣሉ። ዛሬ አያሌ መጽሐፍ
ቅዱስ አንባቢዎች አምላካዊውን ፍርድ የሚያስፈራ ነገር አድርገው እንደሚመለከቱ
ማስተዋላቸውን የሚገልጹት እኚሁ ጸሐፊ፤ የቀደመውን የዕብራውያን አመለካከት
በማጤን እንደሚከተለው ጽፈዋል፡ “ያፈሩትን ሐብት ንብረት የተገፈፉ በሺህ
የሚቆጠሩ ባለመብቶች ድምፅ ቢያንስ በስተ መጨረሻ ይደመጣል። እርግጥ ነው
እነዚህ ወገኖች ፍርድ አይፈሩም። የእነርሱ ጉዳይ ሊሰማ ይችል እንደሆን እንጂ
ምላሽ እንዳጣ ያውቃሉ። በስተመጨረሻ--ጌታ ሊፈርድ ዳግም ሲገለጥ ግን ያኔ
መፍትሔውም ይመጣል።”—C. S. Lewis, Reflections on the Psalms (New
York: Harcourt, Brace and Company, 1958), p. 11.
በጭቆና፣ ምዝበራና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ላሉ ወገኖች እነሆ ዛሬም ተስፋ መኖሩን
በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ እንመለከታለን።
አምላካዊውን ፍርድ እንድንፈራው ሳይሆን በአዎንታዊ እንድናየው
የሚያደርጉ ምን ዓይነት ምክንያቶች አሉን?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 82። እዚህ ላይ የተሰጠን መልእክት ምን ይመስላል?
ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ማኅበረሰብ በታሪካቸው ብዛት
ያላቸው ሕግና ደንቦች በተለያዩ ጊዜያቶች ሰጥቶአቸው የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ ግን
በዚህ ዕቅድ መሰረት ከመኖር ተጨናገፈ። በቀላሉ በዙሪያቸው ከነበሩ ሕዝቦች ጋር
በመመሳሰል ኢፍትሐዊና ጨቋኝ የአኗኗር ዘይቤ ተጽእኖ ስር ወደቁ። መሪዎችና
ፈራጆች የግል ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ ሆኑ፤ ይሁንታቸው በጉቦ የሚገዛ ሆነ።
ተራውን ሕዝብ፣ በተለይም ምስኪኑን የሚከላከል የሕግ ከለላ ባለመኖሩ ለጭቆናና
ብዝበዛ ተጋላጭ ሆኑ።
መዝ. 82 ለእንዲህ ያለው ሁኔታ የተሰጠ ምላሽ ነው። እግዚአብሔር የፈራጆች
ሁሉ ፈራጅ ሚና እንዳለው በመግለጽ የሕዝቡን መሪዎች እና ፈራጅ ዳኞች ሳይቀር
እንደሚዳኝ ይሳያል። ይህ ክፍል አጽንኦት እንደሚሰጠው ከሆነ በማኅበረቡ ውስጥ
እንዲህ ዓይነት ሚና መኖሩ የሚሰማቸው ሰዎች “በእርሱ ስር ፈራጆች ሆነው
ይሾማሉ”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 198. የእግዚአብሔር
ተወካዮችና የበታቾቹ ሆነው ኃላፊነታቸውን በመረከብ ሥራቸውን ያካሂዳሉ። እንደ
ባለመዝሙሩ አመለካከት ከሆነ አምላካዊው ፍትሕ ምድራዊው ፍትሕ እንዴት
መሥራት እንዳለበት የሚያሳይ ተምሳሌት ነው። ፍትሐዊነት ወይም ኢፍትሐዊነት
የሚለካበት--ፈራጆቹም የሚዳኙበት ነው።
በዚያ አገር ተንሰራፍቶ በነበረው ኢፍትሐዊነት ላይ ጣልቃ ተገብቶ እንዲቆም
እንዲደረግ በመጠቆም የዚህ ጽሑፍ ክፍል መልእክት ይደመደማል (መዝ. 82፡8)።
እንደ አብዛኞቹ የባለ መዝሙሩ መልእክቶች ሁሉ ይህኛውም ድምጽ የሌላቸውና
የተጨቆኑ--በሚኖሩበትና በሚሠሩበት ስፍራ ኢፍትሐዊ በሆነ ሥርዓት ጸጥ እንዲሉ
የተደረጉ፤ ድምጻቸው እንዲሰማ ያደርጋል።
መዝ. 82--የሁሉ የበላይ ዳኛ ለሆነውና የዩኒቨርስ ብሎም የምድር መንግሥታት
ሉዓላዊ ገዢው እግዚአብሔር አምላክ ተማጽኖ ያቀርባል። እንዲህ ዓይነቱ ልመና
ሊቀርብለት የሚችል የላቀ ኃይል ባለቤት ፈራጅ ወይም ባለሥልጣን የለም። ምድራዊ
ፍርድ ሰጪዎች የደኻውንና የተጨቆነውን የልቅሶ ድምፅ በማይሰሙበት ጊዜ
(በመልእክቱ በተደጋጋሚ ሲከሰት እደተስተዋለው) እርዳታ የሚሻውንም ምስኪን
ድምጽ የሚሰማና ምላሽ የሚሰጥ አምላክ ለመኖሩ አጽንኦት ይሰጣል።
በህይወታችን፤ በተለያዩ ጊዜያቶች የፍትሕ መጓደል ሰለባዎች ልንሆን ብንችልም፤
በሌላ ጊዜ ደግሞ የፍትሕ መጓደል አድራሾቹ እኛው ራሳችን ሆነን ልንገኝ እንችላለን።
እኛ ጨቋኞች ወይም ተጨቋኞች ብንሆንም--እንደ መዝ. 82 ዓይነት መልእክቶች
ወደ ውስጣችን የመመልከት ዕውቀትና ጥበብ እንድናገኝ ያስችሉናል። እግዚአብሔር
ልጆቹ እንደሆኑና በተሻለ መመላለሳቸውን እንደሚፈልግ የሚገልጽላቸው
የኢፍትሐዊ ዳኞች ጉዳይም እንዲሁ እርሱን ያሳስበዋል (መዝ. 82፡6)። በተቃርኖ
አቅጣጫ የተሰለፉ--ራሳቸውን ለመለወጥ ዝግጁ ከሆኑና ይህ እንዲሆን ከፈቀዱ
ለእነርሱም ተስፋ እንዳለ መመልከት እንችላለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 101። ምንም እንኳ መልእክቱ የተጻፈው በአስተዳደር ኃላፊነት ለተቀመጡ ቢሆንም--እኛ በየትኛውም የሕይወት መስክ ብንሰለፍም ከምዕራፉ ምን ዓይነት ጠቃሚ ምክረ ሀሳብ መውሰድ እንችላለን?
ከላይ እንደተጠቀሰው መዝ. 101 የተጻፈው በተለይ በአስተዳደር ኃላፊነት ለተቀመጡ
ሰዎች ነው። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በነገሠባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት እነዚህን
ጥቅሶች እንደ ደረሳቸው ይታመናል። እንደውም በውስጣቸው የያዟቸው ሀሳቦች ዳዊት
በነገሠ ጊዜ ከገባው ቃል ኪዳን ጋር ተወራራሽነት እንዳላቸው መመልከት ይቻላል። ዳዊት
በመጀመሪያ የሳኦል ተዋጊ ወታደር፤ ቀጥሎ ደግሞ ከሳኦል ፊት የሚሸሽ ተቅበዝባዥ
የነበረባቸው ቀናት--መንገዱን የሳተ ንጉሥ በአገሩና በቤተሰቡ ላይ እንዴት ጉዳት
ማድረስ እንደሚችል ምስክር ሆነውታል። ዳዊት ከወትሮው የተለየ ንጉሥ ለመሆን
ቆርጦ ተነስቶ ነበር።
ምናልባት ጥቂቶቻችን የፖለቲካ ሥልጣን ሊኖረን ቢችልም፤ በሌሎች ላይ ተጽእኖ
የማድረግና የማበረታታት ኃላፊነት ያለብን ግን ሁላችንም ነን። እነዚህ ነገሮች-በህይወታችን፣ ማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን፣ በቤተሰብ
ወይም በቤተ ክርስቲያን ገቢራዊ መሆን ይችላሉ። “በመዝ. 101 የቀረቡት የዳዊት መሃላና
ቃል ኪዳኖች በቤት ላይ ሊደርስ ለሚችል ተጽእኖ ዘብ የመቆም ኃላፊነት ያለባቸው
ሁሉ መሃላና ቃል ኪዳን ሊሆን ይገባል።”—Counsels to Parents, Teachers, and
Students, p. 119.
ዕድሉን ባገኘን ቁጥር እነዚህን መርኅዎች በእኛ ላይ የመሪነት ሚና ባላቸው መሪዎቻችን
ላይ ለማስፋፋትና ለማስጠበቅ ዝግጁ ልንሆን ይገባል። ደግሞም እኛ ሁላችን እንደ
መሪነታችንና ተጽእኖ አሳዳሪነታችን ለሌሎች በረከት መሆን እንድንችል የሚረዱንን
የዳዊትን የመሪነት መርኅዎች ሥራ ላይ የማዋል ዕድሉ አለን።
የዳዊት መነሻ ነጥብ ለእርሱ የመሪነት ኃላፊነት የሁሉም ነገር መሠረት ለሆነለት
ለእግዚአብሔር አምላክ ምሕረትና ፍትሕ ክብር መስጠት ነው (መዝ. 101፡1)። እነዚህኑ
ልዩ ባህሪያት በህይወቱና በሥራው ለመማርና በተግባር ላይ ለማዋል ተመኝቶ ነበር።
ይህን ለማድረግ በተለይ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች ወጥመድ የሚሆኑባቸውን-መጥፎ ተግባራት፣ ሙስና እና ታማኝነትን የማጉደል ፈተናዎች ተቋቁሞ ማለፍ ነበረበት።
ዳዊት ቀናውን እንዲያደርግ ሊረዱት የሚችሉ መልካም አማካሪዎች ከጎኑ
እንደሚያስፈልጉት በማስተዋሉ፤ እምነት የሚጣልባቸውን አማካሪዎችና ሀቀኛ
አስተዳዳሪዎችን ለመሾም ቁርጥ ሀሳቡ አደረገ። ፍትሕና ምህረት አብረውት ለሚሠሩትም
ሳይቀር እንደ ግል የመሪነት መለያው መታወቅ ነበረባቸው።
ምናልባት የየራሳችን አማካሪዎችና የበታች ሹማምንት ሊኖሩን ባይችሉም
እንኳ በፍትሕና ምህረት እንድንኖርና እንድንመራ በሚያስችሉ ተጽእኖዎች
መሞላት የምንችለው እንዴት ነው?
ወደ መዝሙር መጽሐፍ መደምደሚያ እየተቃረብን ስንመጣ በለሆሳስ ይደመጥ የነበረው የምስጋና ድምጽ እያደገና እየገዘፈ ማስተጋባት ሲጀምር ይስተዋላል። የመጨረሻዎቹ አምስት ምዕራፎች “ጌታን አመስግኑት!” በሚል ቀላልና ቀጥተኛ ትእዛዝ ቢጀምሩም--ምዕ. 146 ግን ለዚህ ምስጋና ተቀዳሚ ምክንያት የሆነውን ይኸውም፤ እግዚአብሔር የድኾች እና የተጨቆኑ ወገኖች ሁኔታ የሚያሳስበው አምላክ በመሆኑ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ያደርጋሉ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 146። በዚህ ምዕራፍ የቀረበልን መልእክት ምንድን ነው? በተለይ በመዝ. 146፡5-9 እግዚአብሔር ምን እያለ ነው?
እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፈጣሪ እንደ መሆኑ መጠን (መዝ. 146፡6) ዳኝነቱ፣
ሰጪነቱ፣ አርነት አውጪ መሆኑ፣ ፈዋሽነቱ፣ ረዳትነቱና መከታነቱ በዚህ ዓለም
ያለማቋረጥ እየሠራ ያለውን ሥራ ገልጠው ያሳያሉ--በተለይ ዕርዳታዎቹ ለሚያሹዋቸው
ወገኖች። ይህ ትዕይንት እግዚአብሔር በሕይወታችን፣ በማኅበረሰባችን ብሎም
በዓለማችን የሚያደርገውንና ለማድረግ የሚመኘውን አብልጦ ያሳያል።
ለተቸገሩ እርዳታ ማድረግ ያለብን እግዚአብሔር አድርጉ ብሎ ስላዘዘን ነው ብለን
አንዳንዴ እናስባለን። ነገር ግን ይህ ጉዳይ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያደረገው ነገር
እንደመሆኑ እኛም እርሱን እንቀላቀል ዘንድ በመዝ. 146 ጥሪ ቀርቦልናል። ከድኽነት፣
ከጭቆና እና ከበሽታ በተቃራኒ ስንሠራ፤ ከእግዚአብሔርና ከእርሱ ዓላማ አኳያ
መሰለፋችን እርግጥ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ፈጥሮ እንደ መዝ. 146 ያሉ
መልእክቶችን ከግብ ለማድረስ ከመሥራት የላቀ ምን ዓይነት ልዩ መብትና ጥቅም
አለ?
ነገር ግን ለእኛ የሚበጁ ሌሎች ጠቀሜታዎችም አሏቸው። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች
እግዚአብሔርን ለማግኘት ስላደረጉት ጥረትና ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት
ለመመስረት ስላላቸው ምኞት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። ሆኖም
እግዚአብሔርን ከምናገኝባቸው መንገዶች አንዱ እርሱ ከሚሠራው ሥራ ጋር
ጥምረት መፍጠር መሆኑን እንደ መዝ. 146፡7-9 ያሉ እና ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ የምናገኛቸው አያሌ ጥቅሶች ያመላክቱናል። በመዝ. 146 እንደሚናገረው
እርሱ የደኻውን፣ የታመመውንና የተጨቆነውን ተስፋ ለማለምለም የሚሠራ
ከሆነ እኛም አብረነው ልንሠራ ይገባል። “ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ከፍ
ያለውን የእርሱን ትኩረት ድርሻ ለተቀበሉ ድኾችና በሥቃይ ውስጥ ላሉ አብሮነቱን
ለማሳየትና ለመሥራት ነው። እርሱ ዛሬም በልጆቹ ስብእና ውስጥ ሆኖ ወዮታንና
ሥቃይን ያስታግስ ዘንድ ድኾችንና በእጦት የሚገኙትን ይጎበኛል።
“ሥቃይንና እጦትን ለማስወገድ ካልሠራን የአምላካዊውን ምኅረትና ፍቅር
የምናስተውልበት ምንም መንገድ አይኖርም። በርኅራኄ የተሞላውንና የሌላውን
ችግር የሚካፈለውን ሰማያዊ አባት አዛኝነት የምንረዳበት አንዳችም መንገድ
አይኖርም። ወንጌል በብርቱ ዕጦትና ድኽነት ውስጥ ወዳሉ ማኅበረሰቦች ሲገባ
የሚያገኘውን ያህል ታላቅ ፍቅር በሌላ ስፍራ አያገኝም።”—Ellen White, Testimonies for the Church, vol. 7, p. 226.
ሌሎችን ለማገልገል እንዴት ከእግዚአብሔር ጋር ቀረቤታ መፍጠር እንዳለብን
አስመልክቶ የእርስዎ ተሞክሮ ምን ይመስላል?
መጽሐፈ ምሳሌ የጥበብ ቃላት ስብስብ እንደመሆኑ ስፋት ያላቸውን ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮችና የህይወት ተሞክሮዎች ይዳስሳል። ከእነዚህ መሃል የድኽነት፣ የሐብት፣ የደስታ፣ የፍትሕ እና ኢፍትሐዊነት ነጸብራቆች ቀርበዋል--አንዳንዴም ለየት ካለ አመለካከት አኳያ። ህይወት ሁሌም ቀላልና አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ሁሉ፤ መጽሐፈ ምሳሌ በህይወታችን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ሁኔታዎችና ምርጫዎች ያስጠነቅቀናል። ይህ ደግሞ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑትንም ያካትታል። ጥቅሶቹን እያነበቡ ያነጻጽሩ፡ ምሳ. 10:4፣ 13:23-25፣ 14፡31፣ 15፡15፣ 14:31፣ 15:1516፣ 19:15፣ 17፣ 30:7–9። ጥቅሶቹ ከሐብት፣ ከድኽነትና በዕጦት ያሉትን ከመርዳት ጋር በተጓዳኝ ምን ይላሉ?
እግዚአብሔር የድኾችና የጥቃት ተጋላጭ ደካሞች ጉዳይ እንደሚያሳስበው መጽሐፈ
ምሳሌ አጽንኦት ይሰጣል። አንዳንዴ ሰዎች ዙሪያቸውን ባሉ ልዩ ልዩ ሁናቴዎች፣
በተሳሳተ ምርጫ ወይም በደረሰባቸው ብዝበዛ መንስኤ ሊደኸዩ ቢችሉም፤ ጌታ ግን
ሁሌም ፈጣሪያቸው (ምሳ. 22፡2) እና መከታቸው ነው (ምሳ. 22፡22-23)። እነዚህ
ሰዎች የቱንም ዓይነት ስህተት ሊሠሩ ቢችሉም እንኳ የጭቆና ቀንበር ሊሸከሙ
ወይም የሌሎች መጠቀሚያ ሊሆኑ አይገባም።
መጽሐፈ ምሳሌ ጥበብን በመምረጥና እግዚአብሔርን በመታዘዝ የተሻለ ህይወት
ቢለግስም፤ ሐብት ሁሌም በእግዚአብሔር የመባረክ ውጤት መሆን አይችልም።
ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ከሁሉም በላይ አስፈላጊና ውሎ አድሮ ከቁሳዊው የሐብት
ክምችት በላቀ ተሸላሚ ማድረጉ እሙን ነው፡ “ከጽድቅ ጋር ጥቂት ነገር፣ በግፍ ከሚገኝ
ብዙ ትርፍ ይሻላል” (ምሳ. 16፡8)።
ሌላው መጽሐፈ ምሳሌን የሚያሳስበው ጉዳይ በንግድ ሥራ፣ በመንግሥት ኃላፊነትና
ፍትሕን በማስፈን ረገድ ሊኖር የሚገባ ሐቀኝነት ነው (ምሳ. 14:5፣ 25፣ 16:11–13፣ 17:15፣
20:23፣ 21:28፣ 28:14–16)። መጽሐፈ ምሳሌን የሚያሳስበው የግለሰቦች ህይወት ሁኔታ
ብቻ አይደለም። ይልቁንም ባጠቃላይ ማኅበረሰቡ ስለ ሁሉም ጥቅም ሲባል እንዴት
መሥራት እንዳለበት ብርሃን ይፈነጥቃል--በተለይ ከለላ ለሚያሻቸው ምስኪኖች።
ሹማምንትና ገዢዎች በእግዚአብሔር እርዳታ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ድጋሚ
ማስታወሻ (ምሳ. 8፡15-16) የተሰጠን ሲሆን፤ ለተቸገሩ ሁሉ የጸጋውና የርኅራኄው
ወኪሎች ሆነው ይሠሩ ዘንድ ተጠርተዋል።
በአጉል ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች የሐዘኔታ ስሜት ማሳየት ቀላል ሊሆን
ቢችልም፤ ይህን የሐዘኔታ ስሜት ወደ ድርጊት መለወጥ የምንችለው እንዴት
ነው?
Read Ellen G. White, “The Last Years of David,” pp.
746–755, in Patriarchs and Prophets; C. S. Lewis, “‘Judgment’ in the
Psalms,” pp. 15–22, in Reflections on the Psalms.
“የዳዊት መዝሙር ሰዎች እያወቁ ከሚፈጽሙት ጥልቅ በደል አንስቶ እራስን
እስከ መውቀስና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እስከሚያስችል ግዙፍ
እምነት ድረስ ያለውን አጠቃላይ የሕይወት ተሞክሮ ይዳስሳል። ኃጢአት ሐፍረትና
መከራ ብቻ እንደሚያመጣ የዳዊት ሕይወት ታሪክ ይነግረናል። እጅግ ጥልቅ
የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅርና ምህረት ግን የተጸጸተችውን ነፍስ ቀና በማድረግ
የእግዚአብሔር ልጅነትን ማእረግ ያጎናጽፋታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከቀረቡት
ጠንካራ አምላካዊ ማረጋገጫዎች አንዱ የሆነው ይህ ክፍል በታማኝነት፣ በፍትሕና
በአምላካዊው ምህረት ኪዳን ዙሪያ ምስክርነቶችን ይዞአል።” የኃይማኖት አባቶችና
ነቢያት፡ ቅጽ 2 ገጽ 436።
በመጽሐፈ ምሳሌ የምናገኛቸው “መርኅዎች በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ
አስተዳደራዊ ሥርዓት የማኅበረሰቡን ደኅንነት የሚያስጠብቁ ናቸው። የማኅበረሰቡን
ሐብት የማፍራትም ሆነ በሕይወት የመኖር ደህንነት የተጠበቀ የሚያደርጉት እነዚሁ
መርኅዎች ናቸው። መርኅዎቹ በሁሉም ዘንድ መተማመን እንዲፈጠርና ትብብር
እንዲኖር የሚያስችሉ ሲሆን፤ ዓለም ጌታ በቃሉ የሰጠውና በሰብዓዊው ልብ ሙሉ
ለሙሉ ወደ መሰወር ያዘነበለው የዚህ አምላካዊ ሕግ ባለ ዕዳ ነው።”—Ellen G.
White, Education, p. 137.
1.ራስዎን እንደ መሪ ወይም እንደ ተጽእኖ አሳዳሪ የሚያዩበት መንገድ ምን
ይመስላል? በዚያ የሕይወትዎ ገጽታ የፍትሕ ወኪል መሆን የሚችሉት እንዴ
ነው?
2.ስለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ባህልና ማኅበረሰባዊ አወቃቀር አሰብ ያድርጉ።
በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ዕጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ አሁን ያለውን
መዋቅር ተጠቅመው እንዴት መሥራት ይችላሉ?
3.የፍትሕና የቅንነት መርኅዎች ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመገንባት በጣም
አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
4.መጽሐፈ ምሳሌ ሕይወታችንን በአግባቡ በምንመራበት ጥበብ ዙሪያ ትኩረት
ከማድረጉ አኳያ እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ ስለመሆኑ ምን ይለናል?
ማጠቃለያ፡ መዝሙረ ዳዊትና መጽሐፈ ምሳሌ በተለይ በህይወት ዙሪያ
ሊገጥሙ በሚችሉ የጋራ ተሞክሮዎችና ፈተናዎች መሃል በታማኝነት ስለ
መኖር ይናገራሉ። ሁለቱም መጻሕፍት እግዚአብሔር ለማኅበረሰቡ ያለውን
ራእይ ከማጋራታቸው ባሻገር፤ በተለይ የድኾችና በጭቆና ቀንበር ሥር ያሉ
ምስኪኖች ሁኔታ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
የመዝሙረ ዳዊት የልቅሶ ድምፆች እና የመጽሐፈ ምሳሌ የጥበብ ቃላት-በተደጋጋሚ ችላ የተባሉትን ወይም ብዝበዛ የደረሰባቸውን ምንዱባን ሁኔታ
እግዚአብሔር እንደሚመለከትና መከታቸው ለመሆን ጣልቃ እንደሚገባ
ያሳያሉ። እግዚአብሔር እንደዚያ ዓይነት አምላክ ከሆነ እኛም አርአያነቱን
መከተላችን የግድ ይሆናል።