የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከጥር 18-24

5ኛ ትምህርት

Jan 26 – Feb 01




ሰባቱ ማኅተሞች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 6:1–14፣ ዘሌዋ. 26:21–26፣ ሕዝ. 4:16፣ ዘዳ. 32:43፣ 2ተሰ. 1:7–10.


መታሰቢያ ጥቅስ :- “ ‘ማኀተሞቹን ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል፡ ፡ ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤ እነርሱም በምድር ላይ ይግሣሉ’ ” ራእ. 5፡9-10፡፡

ክ ርስቶስ በማኅተም የታሸገውን ጥቅልል ስለ መውሰዱና በአዳም ታጥቶ የነበረው ዳግመኛ በእርሱ መገኘቱን የሚገልጸውና በራእ. 4-5 ቀርቦ የነበረው ይኸው ትዕይንት በምዕ. 6 ይቀጥላል፡፡ አሁን በጥቅሉ ያሉትን ማኅተሞች ለመክፈትና የደኅንነትን ዕቅድ ወደ መጨረሻው ግብ ለማድረስ ዝግጁ ነው፡፡ ጴንጤቆስጤ ክርስቶስ ወንጌልን ለዓለም በማዳረስ መንግሥቱን የሚያስፋፋበት ጅማሮ ሆኖ በገሃድ ታየ፡፡ የማኅተሞቹ መከፈት በጴንጤቆስጤ የተጀመረው የወንጌል መሰበክ መጀመርንና ይህን መልእክት መቃወም ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ያመላክታል፡፡ የሰባተኛውና የመጨረሻው ማኅተም መከፈት ወደዚህ ዓለም ታሪክ መደምደሚያ ያመጣናል፡፡

ራእ. 3፡21 የሰባቱን ማኅተሞች ፍቺ ቁልፍ ይሰጠናል፡ “ ‘እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ’ ”፡፡ ምዕ. 4 እና 5 ስለ ክርስቶስ አሸናፊነትና በአባቱ ዙፋን ሀሴት ማድረግ ሲነግረን፤ ምዕ. 7 ደግሞ አሸናፊዎች በክርስቶስ ዙፋን መቀመጣቸውን ይፋ ያደርግልናል፡፡ እንዲሁም ምዕ. 6 የየሱስን ዙፋን መጋራት ይችሉ ዘንድ በማሸነፍ ሂደት ስላሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይናገራል፡፡

ጥር 19
Jan 09

የመጀመሪያው ማኅተም መከፈት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡1-8፣ ዘሌዋ. 26፡21-26፣ ማቴ. 24፡1-14፡፡

በእነዚህ ጥቅሶች በጋራ የቀረቡትን ቁልፍ ቃላት ልብ ይበሉ፡፡ ትይዩ ሆነው በቀረቡት ጥቅሶች መሰረት ስለ መጀመሪያዎቹ አራት ማኅተሞች ፍቺ ምን ይማራሉ?



ሰባቱን ማኅተሞች ተከትለው የሚመጡት እንደ ሠይፍ፣ ረሐብ፣ ቸነፈርና የምድር አራዊት (ዘሌዋ. 26፡21-26) ዓይነት መርገሞች ከብሉይ ኪዳን ዐውድ ሊስተዋሉ የግድ ይሆናል፡፡ እነዚህን ሕዝቅኤል--የእግዚአብሔር “አራቱ አስፈሪ ፍርዶች” (ሕዝ. 14፡21) ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊነት ሲደበዝዝና ከእርሱ ጋር የገቡትን የታማኝነት ኪዳን ሲያፈርሱ፤ ከተኙበት ለመቀስቀስ ቁጣውን የሚገልጽባቸው የቅጣት ፍርዶች ነበሩ፡፡ በተመሳሳይ አራቱ ፈረሰኞች የእርሱን ዳግም ምጽአት የሚጠባበቁ ወገኖች ነቅተው እንዲገኙ እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ናቸው፡፡

በተጨማሪ በመጀሪያዎቹ አራት ማኅተሞች እና የሱስ በማቴ. 24፡4-14 በዓለም ላይ ምን እንደሚደርስ የሱስ ከሰጠው ገለጻ ጋር ግልጽ መስተጋብር አለ፡፡ አራቱ ፈረሰኞች ይህ ዓለም ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ፍጹም ቤታቸው አለመሆኑን ተገንዝበው በትክክለኛው አቅጣጫ ይራመዱ ዘንድ እነርሱን የሚጠብቅበት ዘዴ ነው፡፡

ምንም እንኳ ራእ. 6፡1-2 ተምሳሌታዊ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ስለ ድል አድራጊነት ይናገራል፡፡ ጥቅሶቹ ክርስቶስ በሰማይ ሰራዊት መሪነት በነጭ ፈረስ እየጋለበ ወደ ምድር ታሪክ መደምደሚያ ዐውደ ውጊያ የሚገሰግስበትን የራእ. 19፡11-16 ትዕይንት አእምሮ ላይ ያጭራሉ፡፡ የንጽሕና ተምሳሌት የሆነው ነጭ ቀለም ሁሌም የሚወክለው ክርስቶስንና ተከታዮቹን ነው፡፡

በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ ቀስት የያዘ ሲሆን፤ አክሊል ሲሰጠው ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ቀስት ይዞ እየጋለበ የሕዝቡን ጠላቶች ድል የነሳውን የብሉይ ኪዳኑን አምላካዊ አምሳል ገልጦ ያሳያል (ዕንባቆ. 3፡8-13፣ መዝ. 45፡4-5)፡፡ የፈረሱ ጋላቢ በዐናቱ የደፋው አክሊል በግሪክኛው እስጢፋኖስ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፤ ይኸውም የድል አክሊል እንደ ማለት ነው (ራእ. 2፡10፣ 3፡11)፡፡ ይህ ጋላቢ ድል እያደረገ ወደ ፊት የሚገሰግስ አሸናፊ ነው፡፡ በመጀመሪያው ማኅተም የተስተዋለው ትዕይንት ክርስቶስ መንግሥቱን ማስፋፋት የጀመረበትንና በጴንጤቆስጤ በብርቱ ኃይል ገቢራዊ የሆነውን የወንጌል ስርጭት ይገልጻል፡፡ ክርስቶስ በክብር ዳግም ሲገለጥ ገቢራዊ እስከሚሆነው የመጨረሻው ድል--እንደ ያኔ ሁሉ ዛሬም ለእርሱ አሸንፈን የየሱስ ተከታይ የምናደርጋቸው ሕዝቦች አሉ፡፡

በኤፌሶን ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጋር ትስስር ያለው የመጀመሪያው ማኅተም ትንቢታዊ ትዕይንት፤ ወንጌል በዓለም ዙሪያ በፍጥነት የተሰራጨበትን የሐዋርያት ዘመን ይገልጻል (ቆለ. 1፡23)፡፡ በኃጢአት ብንወድቅም ነገር ግን በክርስቶስ ሁሌም በአሸናፊው በኩል መሆናችንን ዘወትር ማስታወስ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ጥር 20
Jan 10

ሁለተኛውና ሦስተኛው ማኅተም


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡3-4፡፡ ስለ ቀዩ ፈረስና ጋላቢው በተሰጠው መግለጫ ወንጌልን ከመጥቀስ አኳያ እየተነገረ ያለው ነገር ምንድን ነው?



ቀይ ቀለም ደምን ይወክላል፡፡ ትልቅ ሰይፍ የነበረው የፈረሱ ጋላቢ በምድር የነበረውን ሰላም እንዲወስድ ተፈቅዶለት የነበረ ሲሆን፤ ይህም ሰዎች እርስ በርስ የሚጋደሉበትን መንገድ የከፈተ ነበር፡፡

ሁለተኛው ማኅተም ወንጌልን መቃወም ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ይገልጻል። ክርስቶስ በወንጌል ስርጭት መንፈሳዊ ጦርነት ሲያካሄድ፤ የክፉው ኃይል በምላሹ ጠንካራ መቋቋም ያሳያል፡፡ ይህን ተከትሎ ስደት የማያጠራጥርና አይቀሬ ይሆናል። የፈረሱ ጋላቢ ግድያ አይፈጽምም፡፡ በዚህ ፋንታ ሰላምን ከምድር ይወስዳል፡፡ በውጤቱም ስደት ይከተላል (ማቴ. 10፡34)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡5-6፣ ዘሌዋ. 26፡26፣ ሕዝ. 4፡16፡፡ ስለ ጥቁሩ ፈረስና ጋላቢው የተሰጠው መግለጫ ወንጌልን ስለ መስበክ ከተጠቀሰው ጋር በተጨባጭ የሚያዛምደው ምንድን ነው?



በጥቁሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ ምግብ የሚመዝንበት ሚዛን ይዞአል፡፡ ከዚያም እንዲህ ተባለ “‘አንድ እርቦ ስንዴ ለአንድ ቀን ደመወዝ፤ ሦስት እርቦ ገብስም ለአንድ ቀን ደመወዝ’ ” (ራእ. 6፡6)፡፡ በዚያ ዘመን እህል፣ ዘይት እና የወይን ጠጅ መሰረታዊ ፍጆታዎች ነበሩ (ዘዳ. 11፡14)፡፡ በጥንቃቄ ከተመዘነው እህል የሚጋገረውን ዳቦ መብላት ታላቅ እጦት ወይም ረሃብ መኖሩን ያመላክታል (ዘሌዋ. 26፡26፣ ሕዝ. 4፡ 16)፡፡

ዮሐንስ በኖረበት ዘመን እርቦ የአንድ ቀን ደመወዝ ነበር (ማቴ. 20፡2)፡፡ ረሃብ በሌለበት መደበኛው ጊዜ፤ የአንድ ቀን ደመወዝ ለአንድ ቤተሰብ የሚያስፈልገውን የዕለት ወጪ የመሸፈን አቅም ነበረው፡፡ ሆኖም ረሃብ መደበኛው የመገበያያ ዋጋ በብርቱ እንዲዋዥቅ የማድረግ ተጽእኖ አለው፡፡ በሦስተኛው ማኅተም ትዕይንት እንደ ተመለከተው ለአንድ ሰው ብቻ የሚበቃ ምግብ ለመግዛት ሙሉ ቀን መሥራት የግድ ነበር፡፡ የቀን ደመወዝ--አነስተኛ መጠን ያለውን የቤተሰብ አባላት ለመመገብ የሚያስችለውን፣ ርካሹንና የድኾች ምግብ የሆነውን ሦስት እርቦ ገብስ ለመግዛት ይውል

የሦስተኛው ማኅተም ሁኔታ ወንጌልን አበክሮ መቃወም ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ያመላክታል፡፡ ነጩ ፈረስ የወንጌልን መሰበክ የሚወክል ከሆነ፤ ጥቁሩ ፈረስ ደግሞ የወንጌልን አለመኖር ያሳያል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እህል የእግዚአብሔር ቃል ተምሳሌት ነው (ሉቃ. 8፡11)፡፡ ወንጌልን መቃወም በአሞጽ ትንቢት ከተነገረው በተመሳሳይ የእግዚአብሔር ቃል ረሃብ እንዲከሰት መንስዔ መሆኑ አያጠራጥርም (አሞጽ 8፡11-13)፡፡

ጥር 21
Jan 10

የአራተኛው ማኅተም ሁኔታ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡7-8፡፡ እዚህ ላይ የምናገኘው ትዕይንት ምን ይመስላል? ይህ ሁኔታ ከዚህ አስቀድሞ ከነበረው ጋር እንዴት ይነጻጸራል?



በአራተኛው ማኅተም ላይ የምናገኘው ፈረስ ቀለም በግሪክኛው እንደ ቀረበው አመድማ ወይም ግራጫ ነው፡፡ የጋላቢው ስም ሞት ሲሆን፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙታን ስፍራ የሆነው ሲኦል ደግሞ አጅቦ ይከተለው ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ የምድርን አንድ አራተኛ ሕዝቦች በሰይፍ፣ በረሃብ፣ በመቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲያጠፉ ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡

አራተኛው ማኅተም ለቸነፈርና መቅሰፍት ጥሪ ያደርግ ነበር፡፡ ትዕይንቱ ከያዘው እውነት መረዳት እንደሚቻለው ሰዎች ወንጌልን በመቃወማቸው ምክንያት የሚደርስባቸው መንፈሳዊ ረሃብ በማያጠራጥር መልኩ ወደ መንፈሳዊ ሞት ይመራቸዋል፡፡

የሞትና የሲኦል ኃይል ውሱን መሆኑ በእርግጥም መልካም የምስራች ነው፡፡ ደግሞም ሥልጣን የተሰጣቸው ከምድር በአንድ አራተኛው ክፍል ላይ ብቻ ነው፡፡ የሱስ የሲኦልና የሞት ቁልፍ እንዳለው ማረጋገጫ ይሰጠናል (ራእ. 1፡18)፡፡ በራእ. 2 ለቀረቡት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ለኤፌሶን፣ ሰምርኔስ፣ ጴርጋሞን፣ ትያጥሮን፣ የተሰጡትን መልእክቶች ይዘት አንዴ መለስ ብለው ለመቃኘት ይሞክሩ፡ ፡ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የነበረውን ሁናቴ ከመጀመሪያዎቹ አራት ማኅተሞች መከፈት ትዕይንት ጋር ያስተያዩ፡፡ በመሃላቸው ምን ዓይነት መመሳሰል አለ?



የሰባቱ ማኅተሞች ትዕይንት የወደፊቷን ቤተ ክርስቲያን ሁናቴ ያሳያል፡፡ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት እንደተስተዋለው ሁሉ፤ ማኅተሞቹ ከተለያዩ የክርስትና ታሪክ ዘመኖች ጋር ይዛመዳሉ፡፡ በሐዋርያት ዘመን ወንጌል በዓለም ዙሪያ በፍጥነት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ በሁለተኛው ማኅተም እንደታየው፤ በሮም ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ክርስቲያኖች ላይ ብርቱ ስደት ደረሰ፡፡ ሦስተኛው ማኅተም በአራተኛውና አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተስተዋለውን አስታራቂ ሃሳብ የመከተል አካሄድ የሚያመለክት ሲሆን፤ ይህ ዘመን በታሪክ “የጨለማው ዘመን” ተብሎ ወደሚታወቀው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እጦትና መንፈሳዊ ረሃብ የሰፈነበት ጊዜ ያመራ ነበር፡፡ አራተኛው ማኅተም በጨለማው ዘመን በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን መንፈሳዊ ሞት በተገቢ መንገድ ይገልጽልናል፡፡

“ዘይቱና የወይን ጠጁ” በሦስተኛው ማኅተም መቅሰፍት እንደማይጎዳ ራእ. 6፡6 ይነግረናል፡፡ ዘይት መንፈስ ቅዱስን፣ ወይን ደግሞ የየሱስ ክርስቶስን ማዳን ይወክላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እጦት በሚከሰትበት ጊዜ እንኳ እውነትን ለሚሹ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በሥራ ላይ ስለ መሆኑ ይህ በተጨባጭ ምን ይነግረናል?

ጥር 22
Jan 10

የአምስተኛው ማኅተም መከፈት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6:9-10፡፡ ምንድን ነው--እየተከሰተ ያለው ነገር?



በመጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ የተሰኘው ቃል መላውን ሰብዓዊ ማንነት ይወክላል (ዘፍ. 2፡7)፡፡ የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች ላይ የደረሰው ሞትና ስደት በዚህ ስፍራ የቀረበበት መንገድ--በምድራዊው የመስዋዕት ሥርዓት ይቀርብ ከነበረው በተመሳሳይ ደማቸው ከመሠዊያው በታች ፈስሶ ነው (ዘፀ. 29፡12፣ ዘሌዋ. 4፡7)፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለወንጌል ታማኝ መሆናቸው ኢፍትሐዊ ፍርድና ሞት አስከትሎባቸዋል፡፡ በዚህም አምላካቸው ጣልቃ ገብቶ አሳዳጆቻቸውን እንዲበቀል ወደ እግዚአብሔር አልቅሰዋል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች በምድር ስለተፈጸመው ግፍ ከመናገር ውጪ ስለ ሙታን ሁኔታ የሚሉት አንዳችም ነገር የለም፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡11፣ ዘዳ. 32፡43፣ መዝ. 79፡10፡፡ እግዚአብሔርን አጥብው ይዘው ለነበሩ ሰማዕታት የሰማይ ምላሽ ምን ነበር?



ሰማዕት ቅዱሳን የክርስቶስን ጽድቅ የሚያመለክተው ነጭ ልብስ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ንጽህናቸውን የሚያመላክተው ይህ ገጸበረከት የጸጋ ስጦታውን ለሚቀበሉ የተዘጋጀ ነው (ራእ. 3፡5፣ 19፡8)፡፡ ከዚያም እነርሱ ባለፉበት ተመሳሳይ ጎዳና ወንድሞቻቸው አልፈው ፍጹም እስኪሆኑ እንዲታገሱ ተነገራቸው፡፡ እዚህ ላይ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈው ራእ. 6፡11 ቁጥር የሚል ቃል እንደሌለው ልብ ይሏል፡፡ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የሰማዕት ቁጥር የተፈለገ አኻዝ ላይ መድረስ ይኖርበታል የሚል መልእክት የራእይ መጽሐፍ የለውም፡፡ ይልቁንም በባህሪያቸው ፍጽምና ዙሪያ ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመልካም ሥራቸው ሳይሆን፤ ነገር ግን የክርስቶስ ጽድቅ የሆነውን ነጭ መጎናጸፊያ በመልበስ ፍጹማን ሆኑ (ራእ. 7፡9-10)፡፡ ሰማዕት የሆኑት ቅዱሳን እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና የሺ ዓመቱ መጀመሪያ በመቃብር ይቆያሉ (ራእ. 20፡10)፡፡

ምንም እንኳ የሰባተኛው ማኅተም ሁኔታ በታማኝነታቸው የተነሳ ሚሊዮኖች ሰማዕት የሆኑበትንና በታሪክ መካከለኛው ዘመን ተብሎ የሚጠራውን ጊዜ ቢሸፍንም፤ ከዚህ በተጨማሪ ከአቤል ደም አንስቶ (ዘፍ. 4፡10) እግዚአብሔር በመጨረሻ “ ‘ስለ አገልጋዮቹ ደም’ ” (ራእ. 19፡2) እስከሚበቀል ያለውን የእርሱን ሕዝቦች ሥቃይና መከራ ወደ አእምሮ ያመጣል፡፡

“ጌታ ሆይ እስከ መቼ?” የተሰኙት ቃላት በዘመናት በሥቃይ ያለፉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ልቅሶ ነው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ሕይወት ስለ ፍትሕ መጓደል ያልጮኸ ማን አለ? አንድ ቀን ኢፍትሐዊነት በእርግጠኝነት ፍጻሜ ያገኛል ከሚል እምነት-ከአምስተኛው ማኅተም ትዕይንት ምን ዓይነት መጽናናት ያገኛሉ?

ጥር 23
Jan 10

የስድስተኛው ማኅተም መከፈት


በዚህ ጥላቻ በነገሠበት ዓለም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሐዊነትና አምላካቸው ጣልቃ እንዲገባላቸው የሚያሰሙትን ልቅሶ በአምስተኛው ማኅተም እንመለከታለን፡፡ እነሆ እግዚአብሔር የሕዝቡን ጸሎት ሰምቶ ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ ደርሶአል! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡12-14፣ ማቴ. 24፡29-30፣ 2ተሰ. 1፡7-10፡፡ በመልእክቶቹ የምናገኘው የተገለጠ ነገር ምንድን ነው?



እነዚያ አስቀድሞ በየሱስ የተነገሩ (ማቴ. 24፡29-30) እና በመካከለኛው ዘመን “ታላቁ መከራ” (ራእ. 7፡14) ማብቂያ ወቅት ገቢራዊ የሆኑ የዳግም ምጽአቱ ጠቋሚዎች--የስድስተኛው ማኅተም ፈለካዊ ምልክቶች ናቸው፡፡ በዚህ ስፍራ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት በተምሳሌታዊ አባባል ሳይሆን በግልጽ ቀርበዋል፡፡ እንደ እና የመሰለ ዓይነት ቃላት ጥቅም ላይ ሲውሉ፤ ከተምሳሌታዊ አባባል ጋር የማመሳሰል ሁናቴ ይስተዋላል፡፡

ፀሐይዋ እንደ ማቅ ጠቆረች፣ ጨረቃዋም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፣ የበለስ ዛፍ በብርቱ ነፋስ ስትወዛወዝ ያልበሰለው ፍሬ ከእርሷ እንደሚረግፍ ከዋክብት ረገፉ፣ ሰማይም እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፡ ፡ የምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖች በ1755 ለደረሰው ርዕደ መሬት ዕውቅና ይሰጣሉ፡ ፡ በምስራቃዊው ኒው ዮርክ እና ደቡብባዊው ኒው ኢንግላንድ ግንቦት 19/ 1780-እንደ ወትሮው ሳይሆን በጽልመት የተዋጠ ዕለት ማለፉ ተዘግቦአል፡፡ በተጨማሪ አስገራሚ የተባለ የተወርዋሪ ከዋክብት ዝናብ--ሕዳር 13/ 1833 በአትላንቲክ ውቂያኖስ ዘንቦአል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ከየሱስ ዳግም ምጽአት ጋር ተያይዞ የተነገሩ ትንቢቶች ፍጻሜ ማመሳከሪያ ናቸው፡፡ ሁናቴዎቹ--ታላቁ ዳግም መነቃቃት በመባል ለሚታወቀው በብዙ ምዕራፎች የተከፋፈለ የመነቃቂያ መርኅ ግብር መጀመር መንስኤ ሆኖአል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡15-17፣ 19፡11-21፣ ኢሳ. 2፡19፣ ሆሴ 10፡8፣ ሉቃ. 23፡30፡፡ ክርስቶስ ዳግም ሲገለጥ በተለያየ የኑሮ ዘይቤ ያለፉ ሕዝቦች ከሚከሰተው ነውጥ ራሳቸውን ለመደበቅ የሚያደርጉትን ጭንቀትና ጥበት በጥቅሶቹ የቀረቡት ትዕይንቶች ያስቃኙናል፡፡ “ ‘ተራሮቹንና ዐለቶቹንም፣ በላያችን ውደቁ፤ በዙፋኑ ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቁጣ ሰውሩን’ ” (ራእ. 6፡16)፡፡ ፍትሕ ሊሰፍንና ክርስቶስ “በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብር” (2ተሰ. 1፡10) እነሆ ጊዜው ደርሶአል፡፡ የዐመጸኞች መጨረሻ በራእ. 19፡17-21 ቀርቦአል፡፡

በሽብር ሥቃይ የወደቁት ዐመጸኞች “‘ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?’ ” ሲሉ በሚያቀርቡት የሽንገላ ጥያቄ ትዕይንቱ ይደመደማል፡፡ “‘ እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል?’ ” (ሚልክ. 3፡2)፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ምን ይመስላል? ለመልስዎ የሚያቀርቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያትስ ምንድን ነው? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ላይ ይዘው ለመቅረብ ይሞክሩ፡፡

ጥር 24
Jan 10


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “The World’s Need,” pp. 457– 460, in Testimonies to Ministers and Gospel Workers. የሰባቱን ማኅተሞች መከፈት የሚያሳየው ራእይ እግዚአብሔር በምድር ላሉ ሕዝቦቹ የሚጠነቀቅ አምላክ መሆኑን የሚያመላክት ተምሳሌት ነው፡፡ ኬኔት ኤ. ስትራንድ በመባል የሚታወቁት ጸሐፊ የሚከተለውን ሃሳብ አስፍረዋል፡ “እግዚአብሔር ሁሌም ለሕዝቡ የሚጠነቀቅ አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል፡፡

እግዚአብሔር ሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ዘወትር ከጎናቸው እንደ ነበር ታሪክ ራሱ እማኝ ይሆነናል፡፡ እንዲሁም ስለ ምድር መጨረሻ የተሟላ መረጃ በመስጠት በልግስና የተሞላና የተትረፈረፈ ዘላለማዊ ህይወት ባለቤት ያደርጋል፡፡ የራእይ መጽሐፍ ይህን ርዕሰ ጉዳይ አንስቶ ሰፋ ባለ ውብ አቀራረብ ይተነትነዋል፡፡ ስለዚህ የራእይ መጽሐፍ በምንም ዓይነት ከተለመደው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ጽሑፋዊ ቅኝት ያፈነገጠ፣ በውድቀትና ጥፋት የተሞላ ሥራ አይደለም፡፡

ይልቁንም የመጽሐፍ ቅዱስን መሰረተ ሃሳብ የያዘና የመልእክቱ የልብ ትርታ ነው፡፡ የራእይ መጽሐፍ አጥብቆ እንደሚያመለክተው ሞትና ሲኦልን ድል ያደረገው ‘ሕያው’ የሆነው እርሱ (ራእ. 1፡15) በእርግጥ ታማኝ ተከታዮቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም፡፡ ደግሞም በሥቃይ የተሞላ የሰማዕት ሞት ቢሞቱም እንኳ ‘የሕይወት አክሊል’ የሚጠብቃቸው ባለ ድል ናቸው (ራእ. 2፡10፣ 21፡1-4፣ 22፡4)፡፡ ”—Kenneth A. Strand, “The Seven Heads: Do They Represent Roman Emperors?” in Symposium on Revelation—Book 2, Daniel and Revelation Committee Series (Silver Spring, Md.: Biblical Research Institute, 1992), vol. 7, p. 206.




የመወያያ ጥያቄዎች




1.ሰባቱ ማኅተሞች ከተከፈቱበት ትዕይንት ምን ዓይነት ጠቃሚ ትምህርቶች አገኙ? ነገሮች የቱንም ያህል በምድር የከፉ ሊሆኑ ቢችሉ-እግዚአብሔር ግን ዛሬም ኃያል ገዢ በመሆኑ ውሎ አድሮ በክርስቶስ ያለን የተስፋ ቃል ሙሉ ለሙሉ ፍጻሜ ያገኛል ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው? 2.“ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ይድኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የተሰየመች ተቋም ናት፡፡ ይህች ተቋም አገልግሎት እንድትሰጥ ሆና የተደራጀች ሲሆን ተልዕኮዋ ወንጌልን ለዓለም ማዳረስ ነው፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 9. ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ አሰብ ያድርጉ፡፡

የወንጌልን መልእክት ይዞ ወደ ሕዝብ ለመድረስ ይበልጥ ታማኝ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? 3.በሐሙስ ትምህርት መጨረሻ ለቀረበው ጥያቄ ያዘጋጁትን መልስ በሰንበት ትምህርት ላይ ይዘው ይቅረቡ፡፡ በዚያ ቀን (በዳግም ምጽአቱ) ታማኝ ሆኖ መገኘት የሚችል ማን ነው? ለዳግም ምጽአቱ ዝግጁ ሆነን ለመገኘት ዛሬን እንዴት እንኑር--ከሚል ሃሳብ አኳያ በመልስዎ አንደምታዎች ላይ ተወያዩ፡፡