የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከጥር 11-17

4ኛ ትምህርት

Jan 19 – Jan 25




የበጉ በዙፋኑ ላይ መቀመጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 4፣ ሕዝ. 1:5– 14፣ ራእ. 5፣ ኤፌ. 1:20–23፣ ዕብ. 10:12፣ ሐዋ. 2:32–36፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :- “ ‘እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ፡፡’ ” (ራእ. 3፡21)፡፡

እ ስካሁን የተመለከትናቸው ቀደም ያሉ ራእዮች ክርስቶስ ለምድር ሕዝቦቹ የላከውን መልእክት ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ አሁን ግን ራእዩ ከምድር ወደ ሰማይ በማቅናት ትኩረቱን “ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚገባው ነገር” ላይ ያደርጋል”(ራእ. 4፡1)፡፡ በራእ. ምዕ. 4-5 የቀረበው ራእይ የታላቁን ተቃርኖ አጠቃላይ ገጽታ ያስቃኘናል፡፡

በራእ. 12 እንደ ቀረበው ትዕይንት ሁሉ--በራእ. 4-5 የምናገኘው ተምሳሌታዊ አነጋገር ከየሱስ ምድራዊ አገልግሎት አንስቶ ያለውን የደኅንነትን እቅድ ታሪክ ያስቃኘናል፡፡ ሆኖም የወደፊቱ ወለል ብሎ ከመገለጡ አስቀድሞ፤ ክርስቶስ በድኅረ ቀራንዮ በሰማይ የከበረበትን ሁኔታ በጨረፍታ የምንመለከትበት ዕድል ተሰጥቶናል፡፡

በዚህም ምዕ. 4 እና 5 በወደፊቱ ክስተት ዙሪያ--በቀሪው የመጽሐፉ ክፍሎች በሰፈሩት የመልእክቶች ፍቺ ላይ ሰማያዊውን ምልከታ ይሰጠናል፡፡ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተጻፈው መልእክት ቀጥተኛ በሚባል ዓይነት ቋንቋ የቀረበ ቢሆንም ነገር ግን ከአሁን በኋላ በመጽሐፉ የምናገኛቸው መልእክቶች እንደ ወትሮው ለመፍታት ቀላል ሊሆኑ የማይችሉ ተምሳሌታዊና ውስጠ ወይራ ዘይቤዎችን የተላበሱ ይሆናሉ፡፡

ይህ ጥቅም ላይ የዋለ ቋንቋ ከብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ታሪክ የተወሰደ ነው፡፡ የራእይ መጽሐፍን ትክክለኛ ፍቺ ለማግኘት፤ ተምሳሌታዊውን ቋንቋ ከብሉይ ኪዳን ብርሃን አኳያ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡

ጥር 12
Jan 09

በሰማያዊው ዙፋን ቅጥር


ዮሐንስ ከእርሱ ዘመን እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ያለውን ጊዜ ያካተተውን የታሪክ ቅኝት አጠቃላይ ገጽታ ለመመልከት ወደ ሰማይ እንዲወጣ በየሱስ ግብዣ እንደቀረበለት እንመለከታለን፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 4፡1-8፣ ሕዝ. 1፡26-28፡፡ ራእ. 5፡11-14 ከሚሰጠን ብርሃን አኳያ ስለ ሰማያዊው ዙፋን ዕጹብነት ምን መማር እንችላለን?



ሐዋርያው በተከፈተው በር ወደ ሰማያዊው መቅደስና የእግዚአብሔር ዙፋን ተመለከተ፡፡ ዙፋኑ የእግዚአብሔርን ሥልጣንና በፍጡራኑ ላይ ያለውን ገዢነት ሲወክል፤ በዙፋኑ ዙሪያ ያለው ቀስተ ደመና ደግሞ ለሕዝቦቹ ያለውን ታማኝነት ያሳያል፡፡ሆኖም ባላንጣው ሰይጣን ይህን አምላካዊ ሥልጣን ተቀናቀነ። በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል ላለው ቅራኔ ዋንኛ መንስዔ የገዢነት ባለመብቱ--ማን ነው? የሚለው ነው፡፡

በሰማያዊው ዙፋን ዙሪያ የተደረገው ሰማያዊ ጉባዔ ዓላማ በእግዚአብሔር የዩኒቨርስ ገዢነት ባለመብትነት ዙሪያ ለሚነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት ነበር፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 4፡8-11፣ 5፡9-14፡፡ ከጥቅሶቹ ስለ እውነተኛ አምልኮ ምን መማር ይችላሉ? በምዕ. 4 ጌታ እግዚአብሔር መመለክ ያለበት እንዲሁም በራእ. 5፡ 9-14 በጉ የከበረ የሆነው ለምንድን ነው?



ስለ ሰማያዊው ዙፋን እና በዚያ ስፍራ ያለማቋረጥ ስለሚደረገው አምልኮ ራእ. ምዕ. 4 አጠቃላይ መግለጫ ይሰጣል፡፡

በምዕ. 4 የቀረበው አምልኮ የእግዚአብሔርን የመፍጠር ኃይል ሲያወድስ ምዕ. 5 ደግሞ በታረደው በግ ለተገኘው ቤዛነት ውዳሴ ያቀርባል፡፡ ይህ ደግሞ እውነተኛ አምልኮ አምላካዊውን የመፍጠር ሥራና ቤዛነት የሚቆጥር፣ ብሎም በዚያ ሐሴት የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመጀመሪያ ዓለምን የፈጠረው እግዚአብሔር አምላክ፤ በሰጠው የተስፋ ቃል መሰረት ይህቺኑ ምድር ዘላለማዊ የሕዝቦቹ መኖሪያ አድርጎ ወደ ቀደመ ንጽሕናዋ የመመለስ ኃይልና ችሎታ አለው፡፡ በወንጌል አስተምህሮ ዙሪያ አሰብ ያድርጉ፡ ስለ እኛ “የታረደው በግ” (ራእ. 5፡12) እኛን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መላውን ዩኒቨርስ የፈጠረው አምላክ ነው፡፡ በዚህ ህመም፣ ብጥብጥና ዐመጽ በበዛበት ዓለም እንዴት ያለ ተስፋ ተሰጥቶናል?

ጥር 13
Jan 09

በአምላካዊው ዙፋን የተሰየመው ሰማያዊ ጉባዔ


በራእ. 4፡4 የምናገኛቸው ሽማግሌዎች የተገለጹበት መንገድ መላእክት አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “ሽማግሌዎች” የተሰኘው መጠሪያ ማዕረግ ሁሌም ጥቅም ላይ የሚውለው ለሰብዓዊ ፍጡራን ነው፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች ዘወትር በእግዚአብሔር ሕልዎት ዙሪያ ከሚቆሙት መላእክት በተቃራኒ በዙፋኖች ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ነጫጭ ልብሶቻቸው የታማኞቹ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ልብሶች ናቸው (ራእ. 3፡4-5)፡፡ በራሳቸው ላይ የደፉት የድል አክሊል (በግሪክኛው ስቴፋኖል) በተለይ ድል ለነሱ ቅዱሳን የተዘጋጀ ነው (ያዕ. 1፡12)፡፡ በዚህም እነዚህ 24 ሽማግሌዎች አምላካዊው ክብር የተቸራቸው ቅዱሳን መሆናቸውን መመልከት ይቻላል፡፡

24 ቁጥር ተምሳሌታዊ ነው፡፡ በውስጡ ሁለት የ12 ስብስቦችን የያዘው ይህ ቁጥር በእግዚአብሔር ሕዝቦች ተምሳሌትነት መቅረቡን በመጽሐፍ ቅዱስ እንመለከታለን፡፡ እነዚህ 24 ሽማግሌዎች በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ዘመን ያሉትን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በድምሩ መወከል ይችላሉ፡፡ በተጨማሪ 24 ቁጥር በቀደመው ምድራዊ የቤተ መቅደስ አገልግሎት አካል የነበሩት የ24ቱ አለቆች ካህናት አመዳደብ ነጸብራቅ መሆን ይችላል (1ዜና 24፡1-19)፡፡

24ቱ ሽማግሌዎች ከዮሐንስ ራእይ አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሰው አለመታወቃቸው በሰማያዊው ዙፋን የተሰየሙ አዲስ ቡድኖች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ምናልባትም ትዕይንቱ ገቢራዊ ከመሆኑ ጥቂት ቀደም ብሎ የተሰየሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አነዚህ ሰዎች በየሱስ የመስቀል ላይ መሥዋዕትነት ወቅት ከሞት የተነሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል (ማቴ. 27፡51-53)፡፡ የሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ምርኮን ይዞ እንደወጣ ኤፌ. 4፡8 ይነግረናል፡፡

በዘላለማዊው የደኅንነት ዕቅድ የእግዚአብሔርን ፍትሐዊነት ይመሰክሩ ዘንድ እነዚህ 24 ሽማግሌዎች ሰብዓዊውን ዘር ወክለው ከየሱስ ጋር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ በራእ. 4 እንደ ተመለከተው ሽማግሌዎቹ ከተቀረው ጉባዔ ጋር ወደ ሰማያዊው ዙፋን የተወሰዱት የሱስ በመስቀል ላይ የአሸናፊነት ሞት ከሞተ በኋላ ለዕርገቱና በሰማያዊው ሥልጣን ለመክበሩ እማኝ ለመሆን ብሎም እርሱን ለመቀበል ነው፡፡ በተጨማሪ በራእ. 4፡6-8 ስለ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን ተጠቅሶአል፡፡ ይህን አገላለጽ በሚከተሉት ጥቅሶች ከቀረቡት ጋር ያስተያዩ፡ ሕዝ. 1፡5-14፣ 10፡20-22፣ ኢሳ. 6፡ 2-3፡፡



አራቱ ሕያዋን ፍጡራን የእግዚአብሔር የዙፋኑ ጠባቂዎችና ወኪል መላእክቶች ናቸው (መዝ. 99፡1)፡፡ ክንፎቻቸው አምላካዊውን ትእዛዝ ለማስፈጸም ያላቸውን ፍጥነት ሲያመላክት ዐይኖቻቸው ደግሞ የጥልቅ አስተሳሰብ ባለቤት መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ የአንበሳ፣ የጥጃ፣ የሰው እና የንስር ገጽታ መላበሳቸው መላውን የፍጥረት ሥርዓት መወከላቸውን ያሳያል፡፡ የእነርሱ መገኘት መላውን የእግዚአብሔር ፍጥረታት በዙፋኑ ፊት ይወከላል፡፡



ጥር 14
Jan 09

በማኅተም የታሸገው ጥቅል መጽሐፍ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 5፡1፣ ኢሳ. 29፡11-12፡፡ በማኅተም የታሸገው የጥቅል ፍቺ ምንድን ነው?



ይህ የታሸገ ጥቅል በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው አብ ቀኝ እጅ እንደ ነበር ይኸው በግሪክ የተጻፈ አምላካዊ ቃል ያመለክታል፡፡ ጥቅሉን የሚወስደውና በዙፋኑ ላይ ለመቀመጥ የተገባው መጠበቅ ነበረበት፡፡ እንደ ኤለን ጂ. ኋይት ገለጻ ጥቅሉ “የአምላካዊውን ጥበቃና ቸርነት እንዲሁም ትንቢታዊውን የሕዝቦችና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ልቅም አድርጎ ይዞአል፡፡

መለኮት የተናገራቸውን ቃላት፣ ሥልጣኑን፣ ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱን፣ በተምሳሌታዊ መንገድ የተናገራቸውን ሁሉንም ዘላለማዊ ምክሮች፣ እንዲሁም የመላውን ኃያላን የምድር ነገሥታት ታሪክ ይዞ ነበር፡፡ በዚያ ጥቅል ከምድር ታሪክ መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው እያንዳንዱ መንግሥት፣ ሕዝብና ቋንቋ በተምሳሌታዊ መንገድ ተገልጾ ነበር፡፡”—Ellen G. White, Manuscript Releases,vol. 9, p. 7. ባጭሩ የታሸገው ጥቅል ለኃጢአት ችግር መፍትሔ የማምጣትና የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር የመታደግ አምላካዊ ምስጢር ይዞ ነበር፡፡ ያ ምስጢር በሙላት መስተዋል የሚቻለው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት ይሆናል (ራእ. 10፡7)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 5፡2-7፡፡ ክርስቶስ የታሸገውን ጥቅል ለመውሰድና ማኅተሙን ለመፍታት ከመላው ዩኒቨርስ ብቸኛው የሆነው ለምንድን ነው?



ዙፋኑ ባለበት ስፍራ ተከስቶ የነበረው ቀውስ ከሰይጣን ዐመጻ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ ምንም እንኳ ይህች ምድር በእግዚአብሔር ብትፈጠርም ነገር ግን የሥልጣን ነጠቃ ባደረገው ሰይጣን ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡

የዮሐንስ ልቅሶ ከአዳም አንስቶ ከኃጢአት ባርነት አርነት ለመውጣት የተደረገውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች እምባ ያሳያል፡፡ ጥቅልሉ መጽሐፍ ለኃጢአት ችግር የሚበጀውን አምላካዊ መፍትሔ ይዞ ነበር፡፡ ያን ዕቅድ መገንዘብ የሚችለው በየትኛውም መስፈርት የማይለካው ራሱ አምላካዊው ኃይል ብቻ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ሆኖም የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር ለመቤዝት ከተለመደው ፍጹም የተለየ ክስተት አስፈልጎ የነበረ ሲሆን ይኸውም ድል የነሳውና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው በምድር ጌታና የሰማያዊው መቅደስ አማላጃችን የሆነው የሱስ ነበር፡፡ በክርስትና ተሞክሮአችን የሱስን ከሁሉም ማስቀደም የምንማረው እንዴት ነው?

ጥር 15
Jan 09

የበጉ በዙፋኑ መንገሥ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 5፡8-14፣ ኤፌ. 1፡20-23፣ ዕብ. 10፡12፡፡ ጥቅሶቹ በአንድነት ምን ዓይነት የላቀ ተስፋና መጽናኛ ይሰጡናል?



ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ ወደ ዙፋኑ ቀርቦ ጥቅልሉን ወሰደ፡፡ እንዴት ያለ ትዕይንት ነበር! ሥልጣናትና ኃይላት ሁሉ ራሳቸውን በፊቱ አስገዙ (ኤፌ. 1፡20-22)፡ ፡ በዚያን ወቅት መላው ዩኒቨርስ ለክርስቶስ ሕጋዊ የምድር ገዢነት እውቅና ሰጠ፡፡ በአዳም ጠፍቶ የነበረውም እነሆ ዳግም በክርስቶስ ተገኘ፡፡

ክርስቶስ በማኅተም የታሸገውን ጥቅል መጽሐፍ በመውሰዱ የመላው ሰብዓዊው ዘር ዕጣ ፈንታ በእጆቹ ላይ ዋለ፡፡ አራቱ ሕያዋን ፍጡራንና 24ቱ ሽማግሌዎች በራእ. 5፡9 እንዳደረጉት “ ‘መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኀተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል’ ”በማለት በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱለት፡፡ በዚህም ከፍ ያሉት መላእክትና የተዋጀው ሰብዓዊ ዘር ተወካዮች ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን መሥዋዕት ተቀበሉ፡፡ በኃጢአት የወደቀው ሰብዓዊው ፍጡር በመተላለፉ ይጠየቅ ለነበረው የሞት ዕዳ ክርስቶስ በደሙ ቤዛ ሆኖ ፍጹም ልናስብ የማንችለውን የመዳን ተስፋ አሟልቶ ሰጠን፡፡

አሁን አራቱ ሕያዋን ፍጡራን እና ሽማግሌዎቹ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ከነበራቸው የመላእክት ሰራዊት ጋር በአንድነት ዙፋኑን ከብበው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አዲሱ ንጉሥ በታላቅ ድምፅ ምስጋናና ውዳሴ አቀረቡ፡ “‘የታረደው በግ ኀይልና ባለ ጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል’” (ራእ. 5፡ 12)፡፡

በዚህ ወቅት የሰማይና የምድር ፍጥረታት ባንድነት ሆነው “‘ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኃይል፣ ለዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን” (ራእ. 5፡13) ሲሉ ለእግዚአብሔር አብ እና ለእግዚአብሔር ወልድ ንጉሣዊውን አክብሮት አቀረቡ፡፡ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን “ ‘አሜን’ ” ሲሉ፤ 24ቱ ሽማግሌዎች ደግሞ በግምባራቸው ተደፍተው ውዳሴያቸውን በማቅረብ ይህ በብርቱ ድምፆች ታጅቦ በሰማያዊው ዙፋን የተደረገ ታላቅ ሥነ ስርዓት ፍጻሜ ሆነ፡፡

ዩኒቨርስ አንድ ቀን በብርቱ ንዳድ ወይም በራሱ ምክንያት ብትንትኑ ይወጣል ሲሉ የፊዚክስ ምሑራን መላምታቸውን ይደረድራሉ፡፡ አስተሳሰቡ የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረው ፍጹም ተጻራሪ ነው፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀንን አሻግረን እያየን ሐሴት ማድረግን ዛሬ መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?

ጥር 16
Jan 09

የጴንጤቆስጤው አንደምታ


በሰው ልጆች የመዳን ታሪክ እጅግ ወሳኝ ከሆኑ ክስተቶች መሃል አንዱ በራእ. ምዕ. 5 የቀረበው፡ ክርስቶስ በድኅረ ቀራኒዮ እንደ ንጉሥና ሊቀ ካህናት ለሚሰጠው ሰማያዊ አገልግሎት መክበሩ ነው፡፡ የደኅንነትን እቅድ በአስገራሚ አኳኋን እውን ማድረግ የቻለው ክርስቶስ በሰማያዊው የእግዚአብሔር ቀኝ ዙፋኑን ወሰደ (ዕብ. 12፡2፣ ራእ. 3፡21)፡፡ ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ አማላጃችን መሆኑን ተከትሎ የወደቀው ሰብዓዊ ዘር በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር መድረስና የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ቻለ፡፡

ጥቅሶቹን ያነጻጽሩ፡ ሐዋ. 2፡32-36፣ ዮሐ. 7፡39፡፡ የክርስቶስ በሰማይ መክበር ለመንፈስ ቅዱስ መውረድ ያለው አስፈላጊነት ምንድን ነው? ክርስቶስ በሰማይ ከመክበሩ አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ለደቀ መዛሙርቱ መውረድ ያልቻለበት ምክንያቱ ምን ነበር?



ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ መክበሩን ተከትሎ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ወረደ፡፡ ራእ. 5፡6 ወደ ምድር ሁሉ ስለ “ተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት” ይጠቅሳል፡፡ ሰባቱ መናፍስት--መንፈስ ቅዱስ በዓለም የሚፈጽመውን ተግባር ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዘወትር በዙፋኑ ፊት እንደ ነበር የተገለጸ ቢሆንም (ራእ. 1፡4፣ 4፡5) ክርስቶስ በሰማያዊው ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ወደ ምድር ተላከ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር መላክ ከክርስቶስ ድኅረ ቀራኒዮ አገልግሎት መክበር ጋር ይተሳሰራል፡፡ ይህ ደግሞ የሱስ በአባቱ ፊት መቅረቡንና ስለ ሰብዓዊው ፍጡር የከፈለው መስዋዕትነት ተቀባይነት ማግኘቱን ያሳያል፡፡

“የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ ተከታዮቹ ቃል የተገባላቸውን በረከት የማግኘታቸው ምልክት ነበር. . . በሰማያዊው ደጃፎች ያለፈው ክርስቶስ በመላእክት ክብርና ውዳሴ በዙፋኑ ተቀመጠ፡፡ ይህ ሥነ ስርዓት እንዳበቃ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በሙላት ወረደ፤ በዚህም በአባቱ ዘንድ ዘላለማዊ ክብር የነበረው ክርስቶስ እነሆ አሁን ከበረ፡፡ ለሰብዓዊው ዘር ቤዛ የሆነው ጌታ መክበርና የጴንጤቆስጤው የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የእጅና ጓንት ግንኙነት ነው፡፡ ክርስቶስ አስቀድሞ በተናገረው መሰረት መንፈስ ቅዱስን ለተከታዮቹ ላከ፤ በሕዝቡ ላይ የተቀባው እርሱ--እንደ ካህንና እንደ ንጉሥ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ወሰደ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 38, 39.

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 4፡16፣ 8፡1፡፡ የሱስ እንደ ንጉሣችንና እንደ ካኅናችን በሰማያዊው ዙፋን የመቀመጡ እውነታ ምን ዓይነት ተስፋና መጽናናት ይሰጥዎታል? ከወደፊቱ የማያስተማምን ሁናቴና ከየቀኑ የህይወት መስተጋብር አኳያ በእርስዎ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምንድን ነው?

ጥር 17
Jan 09


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “ ‘To My Father, and Your Father,’ ” pp. 829–835, in The Desire of Ages; “The Gift of the Spirit,” pp. 47–56, in The Acts of the Apostles. በራእ. ምዕ. 4-5 የቀረበው መልእክት በተለይ በምድር ታሪክ መደምደሚያ ለሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አስፈላጊ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በጴንጤቆስጤ ወቅት በመውረድ የወንጌልን መሰበክ ጅማሮ አበሰረ፡፡

የወንጌል መልእክት አስኳል--እንደ ካኅንና ንጉሥ በሰማያዊው ዙፋን የተቀመጠው የሱስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የቀደመው የክርስትና እምነት እምብርትና (ዕብ. 8፡1) የስብከታቸው የማዕዘን ድንጋይ ነበር (ሐዋ. 2፡32-36፣ 5፡30-31)፡፡ አማኞች ስደት ሲደርስባቸውና አስቸጋሪ ሁናቴ ሲገጥማቸው ይህ እውነት የመነቃቂያ ሰበባቸውና የእምነታቸው መበረታቻ ምንጭ ነበር፡፡ (ሐዋ. 7፡55-56፣ ሮሜ 8፡34)፡፡

በውጤቱም አያሌዎች ለዚህ ስብከት ምላሽ ሰጡ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የየሱስ መገኘት ገቢራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ የእግዚአብሔር መንግሥት ራሱን ገለጠ፤ ይህን ማድረጉንም ቀጠለ፡፡ ሰብዓዊውን ልብ በመለወጥ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩ፣ ለእርሱ ክብር እንዲሰጡና እርሱን ብቻ በማምለክ ለዘላለማዊው ወንጌል (ራእ. 14፡7) ምላሽ እንዲሰጡ መምራት የሚችለው የክርስቶስ መልካም የምስራች ብቻ መሆኑ ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለበትም፡፡ ብቸኛው ተስፋችን በንጉሥነትና በካኅንነት በሰማያዊው መቅደስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው አዳኛችን ነው፡፡ እርሱ ዛሬ ከሕዝቡ ጋር እንደሆነ፤ እስከ ምድር መጨረሻ አብሮአቸው ይሆናል (ማቴ. 28፡20)፡፡ እነሆ አንድም ሳይቀር የወደፊቱ ሁሉ በእጁ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻውን መልእክት ለጠፉና በሥቃይ ላሉ ሰብዓዊ ወገኖች ስናደርስ፤ የወንጌልን መሰረታዊ ባህሪ ሁሌም በአእምሮችን ጠብቀን ማኖራችን ሙሉ ስኬት ሊያስገኝልን እንደሚችል መርሳት የለብንም፡፡ ማንኛውም ስብከታችን ከመስቀሉና መስቀሉ ስለ እግዚአብሔር ከሚያስተምረው እውነት ውጪ አጽንኦት ሊሰጥ አይገባም፡፡




የመወያያ ጥያቄዎች




1.ስለ ጌታ መልካምነት፣ ስለ ኀያልነቱ በተለይ ደግሞ ስለ ጸጋው እያወደስነውና እያመለክነው በሰማይ የምንሆንበት ቀን ይመጣል፡፡ ለዚያ ታላቅ ቀን ዛሬ የምንለማመዳቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ጌታ ላደረገልንና ለሚያደርግልን ሁሉ ከወዲሁ ባመስጋኝ ልብ ልናመልከውና ልናወድሰው የምንችለው እንዴት ነው?

2.ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 4፡11፣ 5፡9፡፡ የሱስ እያደረጋቸው ያሉ ምን ዓይነት ሁለት ሚናዎች እንመለከታለን? ሁለቱ ሚናዎች ከደኅንነት እቅድ አኳያ ሳይሆን ነገር ግን ጌታ አምልኮአችንን ለመቀበል እጅግ የተገባው የትኩረት ነጥብ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? ሰንበት እና ከሰንበት የምንማራቸው ነገሮች--እግዚአብሔርን አስመልክቶ የእነዚህ ሁለት አስደናቂ እውነቶች መግለጫ የሆኑት እንዴት ነው?