በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከኅዳር 15-21

ዘጠነኛ ትምህርት

Nov 24 - Nov 30




እጅግ የላቀው አሳማኝ ማስረጃ

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 11:5152፣ ኤፌ. 2:13-16፣ 2ቆሮ. 5:17-21፣ ኤፌ. 4:25-5:2፣ ሮሜ 14:1-6፣ 1:14፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-- “ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካሕናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፡፡ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው” (ዮሐ. 11:51-52)፡፡

የ የሱስን አዳኝነት ማዕከል ባደረገና በመጨረሻው ዘመን ላይ አጽንኦት ሊሰጣቸው በሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የጋራ መልእክት አማካይነት አንድነት እንዴት መታየት እንደሚችል ባለፈው ሣምንት አጥንተናል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን መልእክት እና ለዓለም እንድናሰራጭ የቀረበልን ጥሪ የዛሬ ማንነታችንን ሰጥቶናል፡፡

በዚህ ሣምንት ከየዕለቱ የክርስቲያኖች ሕይወትና ከቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አኳያ በገሃድ በሚታየው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ የሱስ እንደ ተናገረው ቤተ ክርስቲያን አምላካዊውን የደኅንነትና የእርቅ መልእክት የማወጅ ሥራ ብቻ አትሠራም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ራሱ የዚያ እርቅ ወሳኝ መገለጫ ነው፡ ፡ በኃጢአትና በአመፃ በተከበበው በዚህ ዓለም፤ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ አዳኝ ኃይል ሕያው ምስክር ሆና ትቆማለች፡፡ አንድነት በጎደለውና ኅብረት ባልጎበኘው የቤተ ክርስቲያን ምስክርነት--የመስቀሉ አዳኝ ኃይል በዚህ ዓለም ሊታይ አይችልም፡ ፡ “ከየሱስ ጋር የሚኖር ኅብረት አንዱ አማኝ ከሌላው ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲፈጥር ያስችለዋል፡፡ ይህ አንድነት ኃጢአትን የማስወገድ ኃይል ላለው ለባለ ግርማውና በበጎነት ለተሞላው ክርስቶስ እጅግ አሳማኝ ማስረጃ ነው፡፡”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 5, p. 1148.

ሕዳር 16
Nov25

በየሱስ መስቀል ስር


እንደ ሌሎች አያሌ መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አንድነትም እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጠው ስጦታ ነው፡፡ አንድነት በሰብዓዊው ፍጡር ጥረት፣ መልካም ሥራና እቅድ የሚፈጠር ነገር አይደለም፡፡ በመሰረቱ የዚህ አንድነት ፈጣሪ የሱስ ክርስቶስ ሲሆን ይኸውም በሞቱና በትንሳዔው ነው፡፡ በጥምቀትና የኃጢአትን ይቅርታ በመቀበል ከሞቱና ከትንሳኤው ጋር በእምነት ገጣሚ ስንሆን፣ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር የጋራ ጉዳይ ሲኖረን እና የሦስቱን መላእክት መልእክት ለዓለም ስናሰራጭ--ያን ጊዜ ከክርስቲያን ወገኖችም ሆነ ከእርሱ ጋር ሕብረት ይኖረናል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 11፡51-52፣ ኤፌ. 1፡7-10፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን በየሱስ ሕይወት የአንድነት መሰረት የሆነው የትኛው ክስተት ነው?



“(ቀያፋ) ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካሕናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፡፡ ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔር ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው” (ዮሐ. 11:51-52)፡፡ ምንም እንኳ ቀያፋ የሱስ እንዲሞት ሲፈርድበት ምን እያደረገ እንደነበር ባያውቅም እግዚአብሔር እርሱን ተጠቅሞ አስገራሚውን የየሱስ ሞት ፍቺ እንዲብራራ ማድረጉ እንግዳና ያልተለመደ አቀራረብ ነው፡፡ ካኅናቱም ቢሆኑ ቀያፋ የተናገረው ነገር ምን ያህል ጥልቀት እንደነበረው የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ቀያፋ እንደሚያስበው ከፖለቲካ የዘለለ አባባል ከአንደበቱ አልወጣም፡፡ ዮሐንስ ስለ ሌሎች ምትክ እውን የሆነው የየሱስን ሞት አንድ ቀን “በአንድ ላይ ለሚሰበሰቡ” ታማኝ የእግዚአብሔር ልጆች ምን ማለት የመሆኑን መሰረታዊ እውነታ ለመግለጽ ይህን መልእክት እንደ ተጠቀመ ይታመናል፡፡

እንደ ሰባተኛ ቀን አደቬንቲስትነታችን የቱንም ዓይነት እምነት ወይም የምናውጀው መልእክት ቢኖረንም፤ የአንድነታችን መሰረት ስለ እኛ መሥዋእት የሆነውን የክርስቶስን ሞት መቀበላችን ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ--በጥምቀት ይህን በክርስቶስ ያለንን ኅብረት እንለማመዳለን “ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና፡፡” (ገላ. 3፡26-27)፡፡ ሌላው የእኛ የአድቬንቲስቶች በክርስቶስ ያለን እምነት ተምሳሌት እና በአንድ የሚያስተሳስረን ጥምቀት ነው፡፡ እኛ አንድ አባት ያለን እንደመሆኑ፤ ሁላችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ነን፡፡ ደግሞም በሞቱና በትንሣኤው የተጠመቅን አንድ አዳኝ አለን (ሮሜ 6፡3-4)፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን በባህል፣ በማኅበራዊ ሁኔታ፣ በብሔር ወይም በፖለቲካ አቋም ልንለያይ ብንችልም በየሱስ ያለን የጋራ እምነት ከእነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ባሻገር መጓዝ የሚኖርበት ለምንድን ነው?

ሕዳር 17
Nov26

የእርቅ አገልግሎት


ዓለማችን በስፋት ከምትታወቅባቸው ገጽታዎች መሃል--ቀውስ፣ ችግር፣ ጦርነት፣ ውዝግብ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች በግል፣ በማኅበረሰብ ብሎም በብሔራዊ ደረጃ ሕይወታችንን ያቃውሳሉ፡፡ ችግሮቹ ብቅ ባሉ ቁጥር መላው ሕይወት ውዝግብ ውስጥ መግባቱ እሙን ነው፡፡ ሆኖም ይህ የአንድነት ጸርም ሆነ ቀውስ ለዘላለም እንደተንሰራፋ አይኖርም፡፡ እግዚአብሔር ዩኒቨርስ አቀፍ ኅብረት ለማምጣት በሚያስችለው ተልዕኮ ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳ ኃጢአት መለያየት ቢያመጣም ነገር ግን ዘላለማዊው አምላካዊ የእርቅ ሂደት ሰላምና ፍጽምና ያመጣል፡፡ ጳውሎስ በኤፌ. 2፡13-16 መልእክቱ ክርስቶስ በአማኞች መካከል ሰላም ለማምጣት የሠራውን ሥራ የሚያሳዩ መርኅዎችን አስቀምጦአል፡ የሱስ በመስቀል ላይ ሞቱ አይሁዶችንም ሆነ አሕዛብን አንድ ሕዝብ በማድረግ ለያይቶአቸው የነበረውን የብሔርና የእምነት ግድግዳ አፈራርሶአል፡፡ ክርስቶስ ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ይህን ካደረገ፤ ዛሬ የቤተ ክርስቲያናችንን ምዕመናን የከፋፈለውን የዘር፣ የብሔርና የባህል ግድግዳ ምን ያህል ይንድ? እናም ከዚህ መነሻ ነጥብ ወደ ዓለም ሁሉ መድረስ እንችላለን፡፡

ጳውሎስ በ2ቆሮ. 5፡17-21 በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የፈጠርን አዲስ ፍጥረቶች መሆናችንን ይናገራል፡፡ ታዲያ በዚህ ዓለም ያለን አገልግሎት ምንድን ነው? እንደ አንድ ኅብረት ያለው የቤተ ክርስቲያን አካል በማኅበረሰባችን ምን ልዩነቶች ማምጣት እንችላለን?



አማኞች እንደ እግዚአብሔር አዲስ ፍጥረትነታቸው ወሳኝ የሆነውን የእርቅ አገልግሎት ሦስት እጥፍ ተቀብለዋል፡፡ (1) ቤተ ክርስቲያናችን በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር የተነጠሉ--አሁን ግን በክርስቶስ መሥዋዕትነትና አዳኝ ጸጋ--በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት የፈጠሩ አማኞችን ይዛለች፡፡ እኛ የመጨረሻውን ጊዜ መልእክት ለዓለም እንድናውጅ የተጠራን ትሩፋን ሕዝቦች ነን፡፡ አገልግሎታችን ዛሬም ከእግዚአብሔር የተነጠሉ ሕዝቦች ከእርሱ ጋር እርቅ ፈጥረው የተልዕኮአችን አካል እንዲሆኑ ነው፡፡ (2) ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ እርስ በርሳቸው እርቅ የፈጠሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከክርስቶስ ጋር አንድነት መፍጠር እርስ በርስ ስምሙ መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ በእርግጥ ሞቅ ያለ አቀራረብ የያዘና ሀሳባዊ ሳይሆን በግልጽ የሚታይና የሚጨበጥ ሐቅ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር እርቅ ሲፈጥርና በወንድምና እህቶች መሃል ሰላምና ኅብር ሲሰፍን--ያኔ ለአዳኛችንና ቤዛችን የሱስ ክርስቶስ--ለዓለም የታወቅን ምስክሮቹ እንሆናለን፡፡ “‘እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ’ ” (ዮሐ. 13፡35)፡ ፡ (3) ቤተ ክርስቲያን አምላካዊው የማዳን እቅድ አውነተኛና ብርቱ መሆኑን በዚህ የእርቅ አገልግሎት አማካይነት ለመላው ዓለም ትነግራለች፡፡ በብርሃንና በጨለማ መሃል ያለው ታላቁ ውዝግብ እግዚአብሔርን እና የእርሱን ባህሪ ያማከለ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአንድነትና በእርቅ ዙሪያ በሠራች ቁጥር ዩኒቨርስ ዘላለማዊውን አምላካዊ ጥበብ በተግባር መመልከት ይችላል (ኤፌ. 3፡8-11)፡፡

ሕዳር 18
Nov27

በተግባር የሚገለጥ አንድነት


ኤለን ኋይን በ1902 ላይ የሚከተለውን ጽፋ ነበር፡ “እያንዳንዱ ክርስቲያን ክርስቶስ በዚህ ምድር የኖረው ዓይነት ህይወት እንዲኖር ተጠርቶአል፡፡ እርሱ ለእኛ ምሳሌ የሆነው በእንከን ዐልባ ንጽህናው ብቻ ሳይሆን በትዕግሥቱ፣ በተረጋጋና ልብ በሚማርክ ባህሪው ነው፡፡”—Ellen G. White, in Signs of the Times, July 16, 1902. እነዚህ ቃላት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያቀረበውን ተማጽኖ የሚያስታውሱ ናቸው “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይሁን” (ፊልጵ. 2፡5)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡና የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ፡ ኤፌ. 4፡25-5፡2፡፡ ለክርስቶስ ታማኝነታችንን እንድናሳይ ግብዣ የቀረበልን በተለይ በየትኞቹ የሕይወታችን ክፍል ነው? በአደባባይ ሕይወታችን ለየሱስ ወንጌል ምስክር መሆን የምንችለው እንዴት ነው?



ክርስቲያኖች የየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉና የአምላካዊው ጸጋ ሕያው ምስክሮች እንዲሆኑ የሚጋብዙ አያሌ ጥቅሶች አሉ፡፡ በተመሳሳይ እኛም ስለ ሌሎች ደኅንነት እንድንጥር ግብዣ ቀርቦልናል (ማቴ. 7፡12)፣ አንዱ የሌላውን ሸክም እንዲሸከም (ገላ. 6፡2)፣ በታይታ ከተሞላ የተካበደ ሕይወት በተቃራኒ ቀለል ባለውና ውስጣዊው መንፈሳዊነት ላይ ትኩረት ማድረግ (ማቴ. 16፡24-26፣ 1ጴጥ. 3፡3-4)፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ናቸው (1ቆሮ. 10፡31)፡፡

“ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ፡፡ ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ” (1ጴጥ. 2፡11-12)፡፡ እኛን በሚመለከቱ ላይ የክርስትና ባህሪ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽእኖ ምን ያህል በተደጋጋሚ ዝቅ አድርገን እየተመለከትን ነው? በሚያውክና የሚያስቆጣ ሁናቴ ውስጥ የሚታይ ትዕግሥት፣ ውጥረትና ውዝግብ ባየለበት ድባብ የሚስተዋል ሥነ ሥርዓት መር ሕይወት፣ ለማይታገሥና ሻካራ ቃላት የሚቸር ገር ምላሽ--እነዚህ ሁሉ የበለጠ ለመሥራት እንድንሞክር የሚጋብዙን የየሱስ መንፈስ ምልክቶች ናቸው፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ለመልካም ነገርና ለእግዚአብሔር ክብር ኃይል በመሆን አምላካዊውን ባህሪ በተሳሳተ መንገድ በሚተረጉመው ዓለም ላይ በአንድነት ምስክር እንሆናለን፡፡ አማኞች እንደ ክርስቶስ ወኪልነታቸው የሚታወቁት ለግብረገብ ታማኝ በመሆናው ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎች ደኅንነት በሚያሳዩት ተጨባጭ ፍላጎት ጭምር ነው፡፡ ኃይማኖታዊ ተሞክሮአችን ከልብ የመነጨ እስከሆነ ድረስ ለሌሎች ተገልጦ የሚታይና በዓለም ላይ ተጽእኖ የሚኖረው ይሆናል፡፡ የክርስቶስን ጸባይ ለዓለም የሚገልጽ በፍቅር የተሳሰረ የአማኞች ጥምረት በእርግጥ ብርቱ ኃይል መሆን ይችላል፡፡

ምስክርነትዎ በሌሎች ዐይን ምን ይመስላል? አንድ ሰው የሱስን እንዲከተል ሊያደርገው የሚችል ምን ዓይነት ነገር በሕይወትዎ መመልከት ይችላል?

ሕዳር 19
Nov28

አንድነት በብዝሐነት ውስጥ


ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን በጥልቅ ይከፋፍሉ ስለነበሩ ጉዳዮች በሮሜ. 14፡ እና 15 ይናገራል፡፡ አንዱ ለሌላው መቻቻልና ትዕግሥት እንዲያሳይ እንጂ በእነዚህ ጉዳዮች ሳቢያ ቤተ ክርስቲያንን እንዳይከፋፍሉ ሮማውያንን በመምከር ሀሳቡን አቅርቦአል፡፡ ከጳውሎስ ምክረ ሃሳብ ምን መማር እንችላለን? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 14፡1-6፡፡ በሮም በነበሩት የቤተ ክርስቲያን አባላት ላይ ከመፍረድ ውጪ እርስ በርሳቸው ኅብረት እንዳይኖራቸው መንስዔ የሆኑ ምን ዓይነት ከኀሊና ጋር ቁርኝት የነበራቸው ጉዳዮች ነበሩ?



እነዚህ ጉዳዮች ከአይሁድ ሜዳዊ ሥርዓት ጋር የመበረዝ ሁኔታ ሳይገጥማቸው እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ ጳውሎስ እንደሚናገረው እነዚህ “አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች” (ሮሜ 14፡1) ደኅንነት የሚገኝባቸው ሳይሆኑ ለግለሰቡ የተተዉ የግል አመለካከቶችና ውሳኔዎች ናቸው (ሮሜ 14፡1)፡፡

በመጀመሪያ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች የተነሱት ከምግብ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 11 የቀረበው የእንስሳት ለምግብነት መዋል በዚህ በጳውሎስ መልእክት ግን ችግር ሆኖ አንመለከተውም፡፡ በጳውሎስ ዘመን የቀደሙት ክርስቲያኖች የዐሣማ ሥጋን ጨምሮ ሌሎች ንጹህ ያልሆኑ ምግቦችን መመገብ ስለ መጀመራቸው የምናገኘው መረጃ ባይኖርም ነገር ግን ጴጥሮስ እነዚህን ምግቦች አለመመገቡን እናውቃለን (ሐዋ. 10፡14)፡፡ ደግሞም በእምነቱ ያልጠነከረው አትክልት ብቻ መብላቱ (ሮሜ 14፡2) እና ውዝግቡ የአልኮል መጠጥንም ማካተቱ (ሮሜ 14፡17፣ 21) የጉዳዩ ትኩረት ከሜዳዊ ሥርዓቶች ጋር የተፈጠረውን መበረዝ ለማሳየት እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ንጹህ ያልሆነ በሚል በሮሜ 14፡4 የቀረቡት ቃላት ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥንታዊ የግሪክ ቃላት ትርጓሜ በብሉይ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋሉት ንጹህ ያልሆኑ እንስሳትን ለመጥቀስ እንጂ በዘሌዋውያን 11 የቀረቡትን ያልተፈቀዱ እንስሳት ለማመልከት አይደለም፡፡ የሮም ማኅረሰብ አካል የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በጉባዔ ኅብረት የሚመጡ ምግቦችን አይመገቡም ነበር፡፡ ለዚህ መንስኤው ምግቡ በአግባቡ የተዘጋጀ ወይም ለጣኦታት ያልቀረበ ላለመሆኑ የሚያሳምናቸው ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡

ጉዳዩ በተመሳሳይ ወደ ሣምንቱ ቀናትም ያመራል፡፡ ጳውሎስ ሰንበትን በመደበኛ መጠበቁን የምናውቅ እንደመሆኑ (ሐዋ. 13:14፣ 16:13፣ 17:2) ይህ አባባል የሣምንቱን ሰባተኛ ቀን አይጨምርም፡፡ ይልቁም ከተለያዩ የአይሁዳውያን የድግስ ወይም የጾም ቀናት ጋር ቁርኝት አለው፡፡ እነዚህን ሥርዓቶች በቅን ልቦና እና በታማኝነት የያዙ ሰዎች እንደ መዳኛ መንገድ እስካላሰቧቸው ድረስ እነርሱን በትዕግሥትና በመቻቻል ማለፍ የተገባ መሆኑን ለማመላከት ጳውሎስ መልእክቶቹን አስፍሮአል፡፡ አማኞች በተለይ ከመዳናችን ጋር ግንኙነት በሌላቸው ነጥቦች ሳንስማማ ስንቀር በክርስቲያኖች መካከል የሚኖር ኅብረት ራሱን በትዕግሥት፣ በገርነትና በርኅራኄ ሊገልጥ የተገባ ነው፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የምናምናቸውንና በተግባር የምንገልጣቸውን አስተምህሮዎች አድቬንቲስት ነን የሚሉ ሁሉ ሊያምኑና አጥብቀው ሊይዙ አይገባም? በክፍል ውስጥ ተወያዩበት፡፡

ሕዳር 2
Nov11

አንድነት በተልዕኮ ውስጥ


በሉቃ. 22፡24 በጌታ ራት ወቅት የተስተዋለውን የደቀ መዛሙርቱን ስሜት ከጴንጤቆስጤ ተሞክሮአቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ከነበረው ሁኔታ ጋር ለማስተያየት ይሞክሩ፡፡ እንዲህ ያለው ልዩነት በሕይወታቸው እንዲመጣ መንስዔው ምን ነበር?



አማኞች “በአንድ ልብ” እንደ ነበሩ በሐዋ. 1፡14 እና 2፡46 ተጠቅሶአል፡፡ ይህ ገቢራዊ መሆን የቻለው በአንድነትና በአንድ ቦታ ሆነው የሱስ አጽናኙን እንደሚልክላቸው የሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ በመሻት በጸሎት በመትጋታቸው ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች በአንድ ላይ ተሰባስበው የተሰጣቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ በነበረበት ወቅት አንዱ በሌላው ላይ ሒስ የሚሰነዝርበት ዕድል ነበር፡፡ እንደውም አንዳንዶች የጴጥሮስን ክህደትና (ዮሐ. 18፡15-18፣ 25-27) የቶማስን ጥርጣሬ (ዮሐ. 20፡25) እያነሱ መጠቋቆሚያ ሊያደርጓቸው በቻሉ ነበር፡፡ በየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ከፍ ያለውን ሥልጣንና ክብር ለማግኘት ዮሐንስ እና ያዕቆብ ያቀረቡትን ጥያቄ (ማር. 10፡ 35-41) ወይም የማቴዎስን የቀድሞ ቀረጥ ሰብሳቢነት እያስታወሱ አንዱ ሌላውን በተቸ ነበር (ማቴ. 9፡9)፡፡

ሆኖም ግን “እነዚህ የመዘጋጃ ቀናት ልቦቻቸውን በጥልቅ የሚፈልጉባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ መንፈስ ቅዱስ አጥብቆ እንደሚያሻቸው በጥልቅ የተገነዘቡት ደቀ መዛሙርት ነፍሳትን ለማዳን ሥራቸው ገጣሚ የሚሆን መንፈስ እንዲፈስላቸው ወደ ጌታ አለቀሱ፡ ፡ ልመናቸው እንደው ጌታ እነርሱን እንዲባርክ ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የነፍሳት መዳን ጫና ክፉኛ ይሰማቸው ነበር፡፡ ወንጌል ለዓለም መድረስ እንዳለበት አጥብቆ የተሰማቸው እነዚህ ወገኖች ክርስቶስ እንደሚልክላቸው ቃል የገባላቸው ኃይል እንደሚገባቸው ሆነው ተቀበሉ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 37. በደቀመዛሙርቱ መካከል የነበረው ኅብረትና ጽኑ ጸሎት በጣም አስፈላጊ ለሆነው ለዚህ የጴንጤቆስጤ ተሞክሮ አዘጋጃቸው፡፡ ወደ እግዚአብሔር በቀረቡና የግል ልዩነቶቻቸውን ባስወገዱ ቁጥር የየሱስን ትንሳኤ ለመመስከር ፍርሀት ዐልባና ደፋር አድርጎ መንፈስ ቅዱስ አዘጋጃቸው፡፡ የቀድሞ ጉድለቶቻቸውና ውድቀቶቻቸው ይቅር መባላቸውን ያወቁት ደቀ መዛሙርት ሁኔታው ወደ ፊት የሚቀጥሉበትን ወኔ ሰጣቸው፡፡ የሱስ በሕይወታቸው ያደረገላቸውን ነገር ጠንቅቀው ይገነዘቡ ነበር፡ ፡ የመዳን ተስፋ ያለው በእርሱ ውስጥ መሆኑን ያውቁ የነበሩት እነዚህ አማኞች የክርስቶስን ባህሪ ገልጦ የማሳየት ጽኑ ምኞት ነበራቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ጌታ በእነርሱ ውስጥ ብርቱ ነገሮችን ቢያደርግ ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡ ይህ በእርግጥ ለእኛ ታላቅ ትምህርት ነው፡፡

በሰዎች ሕይወት ውስጥ ስህተት ማግኘት ሁሌም ቀላል ነው፡፡ በውሁዷ ቤተ ክርስቲያን ለግዙፉ አምላካዊ ተልዕኮ ከመሥራት አኳያ የሌሎችን ስህተት ወደ ጎን ማለትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሕዳር 2
Nov11

ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Ellen G. White, “Unity in Diversity,” pp. 98-103, in Evangelism. ምንም እንኳ በአማኞች መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ራሷን ከክርስቶስ ጋር በማዋሃድ እንዴት ለዓለም ብርቱ ምስክር ለመሆን እንደበቃች-ይህ በትምህርተ ጥቅስ የቀረበው መልእክት እንድናስተውል ይረዳናል፡፡ “መንፈስ ቅዱስ ውሳኔ በመስጠቱ ሂደት የቀደመችውን ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደመራት አምላካዊው ቃል ይገልጽልናል፡፡ ይህ ደግሞ የቀረበ ትስስር ባላቸው ሦስት መንገዶች ገቢራዊ ለመሆን በቅቶአል፡ (1) ራእዮች፡ (ለምሳሌ፡ ሕዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት በመንፈስ ቅዱስ ተነገረው፣ ቆርኔሌዎስ፣ አናንያስ፣ ፊልጶስ፣ እንዲሁም / ምናልባት/ የተጣለው ዕጣ)፣ (2) አምላካዊው ቃል፡ (3)፡ የጋራ መግባባት (መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ኅብረት መካከል ይሠራ ነበር)፡፡ አማኞች የባህል፣ ኃይማኖታዊ አስተምህሮና ሌሎች ልዩነቶች ሲገጥሟቸው መንፈስ ቅዱስ በጋራ የሚያግቧቧቸውን ነጥቦች ተጠቅሞ ወደ ውሳኔ እንዲመጡ ይረዳቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የመሪዎቹን ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ማኅበረሰቡንም ንቁ ሚና እንመለከታለን፡፡ ነገሮችን ለመለየትና ለማስተዋል ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም እናያለን፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት--መላው ማኅበረሰብ በአምላካዊው ቃል ላይ በነበረው መረዳት፣ በማኅበረሰቡ ተሞክሮ እና ያሹዋቸው በነበሩ ነገሮች እንዲሁም አገልጋዮች ይሰጡ በነበረው አገልግሎት መታየት ችሎ ነበር፡፡ አምላካዊው ቃል፣ ጸሎትና ተሞክሮ የሥነ መለኮታዊው አስተምህሮ አላባ የሆኑባቸው አያሌ በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ የውሳኔ ሂደቶች ገቢራዊ ለመሆን በቅተው ነበር፡፡””—Denis Fortin, “The Holy Spirit and the Church,” in Ángel Manuel Rodríguez, ed., Message, Mission, and Unity of the Church, pp. 321, 322.


የመወያያ ጥያቄዎች





1. በረቡዕ ትምህርት መጨረሻ ላይ ለቀረበው ጥያቄ በተሰጡት መልሶች ላይ ተወያዩ፡፡

2. በየሱስ ሞትና ትንሣኤ ከሚያምኑ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያለን ተዛምዶ ምን ይመስላል?

ማጠቃለያ፡ ለቤተ ክርስቲያን ኅብረት መኖር እጅግ አሳማኙ ማስረጃ የሱስ እንደ ወደደን እኛም እርስ በርሳችን መዋደዳችን ነው፡፡ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘታችንና እንደ አድቬንቲስት የምንጋራው መዳናችን የኅብረታችን ምርጥ ማስተሳሰሪያዎች ናቸው፡፡ በክርስቶስ--አንድነታችንን ለዓለም ማሳየትና ሁላችንም በአንድ የምንጋራውን እምነት መመስከር እንችላለን፡፡ ከዚህ ውጪ እንድናደርግ አልተጠራንም፡፡