በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከኅዳር 22-28

አስረኛ ትምህርት

Dec 01 - Dec 07




ሕብረት እና የፈረሱ ግንኙነቶች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 4:11 ፊልሞ. 1–25፣ 2ቆሮ. 10:12–15፣ ሮሜ 5:8–11፣ ኤፌ. 4:26፣ ማቴ. 18:15–17፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-- “የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከእርሱ ጋር ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም!” (ሮሜ 5፡10)፡፡

ቀ ደም ብለን እንደ ተመለከትነው ከጴንጤቆስጤ በኋላም እንኳ በአማኞች መካከል የነበረው ግንኙነት አልፎ አልፎ በውጥረት የተሞላ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባላት ከእነዚህ ፈታኝ ጉዳዮች ጋር መጋፈጣቸውን የአዲስ ኪዳን ተደጋጋሚ ምሳሌዎች ይጠቁማሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መርኅዎች በመጠቀም ውዝግቦችን ለመፍታት ስንሞክርና ከክርስቶስ ጋር ያለንን አንድነት ስንጠብቅ አዎንታዊ ውጤቶች ተገልጠው መውጣት ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ መርኅዎች ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የከበረ ዋጋ አላቸው፡፡

በዚህ ሣምንት ጥናታችን ወደ ቀደመ ንጽህናቸው የተመለሱ ግንኙነቶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ደግሞም ሰብዓዊ ግንኙነቶቻችን ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት ላይ እንዴት ተጽእኖ እንደሚያሳድር እንመለከታለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም እርስ በርስ የማቀራረብ ሥራ ይሠራል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርስ ባለን ግንኙነት እንቅፋት የሆኑ የጥል ግድግዳዎችን ያፈራርሳል፡፡ በአጭሩ የወንጌል ኃይል ግዙፍ ማሳያ--ቤተ ክርስቲያን የምትለው ሳይሆን እየኖረችበት ያለው መንገድ ነው፡፡

“‘እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ’ ” (ዮሐ. 13:35)፡፡ ያለዚህ ፍቅር ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የምናወራው ሁሉ ከንቱ ይሆናል፡፡

ሕዳር 2
Nov11

ወደ ቀድሞ ንጽሕናው የተመለሰ ወዳጅነት


ጳውሎስ እና በርናባስ አብረው ለየሱስ የመመሥከር ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ ሆኖም ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ አብሮአቸው ይሂድ ወይም አይሂድ በሚለው ሃሳብ በመካከላቸው የከረረ አለመግባባት ተፈጠረ (ሐዋ. 15፡36-39)፡፡ ወንጌልን ከመስበክ ብርቱ አደጋዎችና ተግዳሮቶች አኳያ በአንድ ወቅት ዮሐንስ ጳውሎስንና በርናባስን ትቶ ወደ መኖሪያው የሩሳሌም ተመልሶ ነበር (ሐዋ. 13፡13)፡፡

“ይህ ውሳኔ ጳውሎስ ማርቆስን በተቃራኒ እንደውም ያለ ምኅረት እንዲመለከተው መንስዔ ሆነ፡፡ በሌላ በኩል በርናባስ ማርቆስ የነበረውን የልምድ ማነስና በአገልግሎት አለመብሰል በመመልከት ወደ ይቅርታው አመዘነ፡፡ ለክርስቶስ ጠቃሚ አገልጋይ የሚያደርገውን ብቃት በማርቆስ ውስጥ የተመለከተው በርናባስ አገልግሎቱን እንዳያቆም ውስጡን ሽብር ገባው፡፡””—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 170. ምንም እንኳ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ሰዎች ቢጠቀምም በመካከላቸው የነበሩ አለመግባባቶች መፍትሔ ይሹ ነበር፡፡ ጸጋን የሰበከ ሐዋርያ ቅር ላሰኘው ለጋ ሰባኪ ተጨማሪ ጸጋ መቸር አስፈልጎት ነበር፡፡ የይቅርታው ሐዋርያ ይቅር ማለት አስፈልጎት ነበር፡፡ ዮሐንስ ማርቆስ በበርናባስ ጽኑ መካሪነት እየጎለበተ በመሄዱ (ሐዋ. 15፡39) ውሎ አድሮ ጳውሎስ በተመለከተው ለውጥ ልቡ ተነካ፡፡

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና በቆለስያስ ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን የጻፈው ደብዳቤ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር የነበረውን ግንኙነት ማደሱንና በዚህ አዲስ ሰባኪ ላይ የነበረውን መተማመን የገለጠው እንዴት ነበር? ቆለ. 4:10-11፣ 2ጢሞቴ. 4:11፡፡





ምንም እንኳ ጳውሎስ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር የፈጠረው የእርቅ ዝርዝር ሃሳብ በግልጽ ባይሰፍርም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ሃሳብ ግን ግልጽ ነው፡፡ ዮሐንስ ማርቆስ ለሐዋርያው ከታመኑ ባልደረቦች አንዱ ለመሆን በቃ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ-ዮሐንስ ማርቆስ ወደ ቆለስያስ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ እንዲቀበሉት ስለ እርሱ ከፍ ያለ አስተያየት ሰጥቶአል፡፡ ጳውሎስ “በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ” (2ጢሞቴ. 4፡11) በማለት በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ጢሞቴዎስ ማርቆስን ወደ ሮም ይዞ እንዲመጣ አበክሮ ሲያደፋፍረው እናያለን፡፡ የጳውሎስ አገልግሎት ይቅር ባለው ወጣቱ ሰባኪ ዳብሮ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በሁለቱ መካከል የነበረው ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፤ ግንኙነታቸው ወደ ቀድሞ ንጽህናው ተመልሶ የወንጌልን ሥራ አብረው ለመሥራት ቻሉ፡፡

የጎዱንን ወይም ቅር ያሰኙንን ይቅር ማለት መማር የምንችለው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ይቅርታ የቀድሞውን ንጽና ፍጹም አድርጎ የማይመልሰው ለምንድን ነው? ይህ ሁሌም ላያስፈልግ የሚችለው ለምን ይሆን?

መስከረም 29
Oct 9


ከባርነት ወደ ልጅነት


ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ከቆላስያስ ወደ ሮም ይኮበልል ከነበረ አናሲሞስ ከተባለ ባርያ ጋር ተገናኝቶ ነበር፡፡ ጳውሎስ የአናሲሞስ አሳዳሪ የነበረውን ጌታ በግል ያውቀው እንደ ነበር ለመገንዘብ ቻለ፡፡ ጳውሎስ ወደ ፊልሞና የጻፈው መልእክት ይህ ወዳጁ ከኮብላይ ባሪያው ጋር የነበረውን ግንኙነት ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንዲመልስ የቀረበ የግል ተማጽኖ ነበር፡፡

ሰብዓዊ ግንኙነቶች ለጳውሎስ ትርጉም ነበራቸው፡፡ ነፋስ የገባቸው ግንኙነቶች ለመንፈሳዊው ዕድገትና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ጎጂ መሆኑን ሐዋርያው ያውቅ ነበር፡፡ ፊልሞና በቆላስያስ የቤተ ክርስቲያን መሪ ስለ ነበር በአናሲሞስ ላይ ቂም የሚይዝ ከሆነ በክርስትና ምስክርነቱ እና ገና ክርስቲያን ባልሆነው ማኅበረሰብ በሚኖረው አገልግሎት ላይ ጥላ ማጥላቱ አይቀሬ ነበር፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ፊልሞ. 1-25፡፡ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ስለ ተመለሰ ግንኙነት ከዚህ ምን ዓይነት ጠቃሚ መርኅዎች እናገኛለን? እዚህ ላይ ቁልፉ ቃል መርኅዎች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡





በቅድሚያ ጳውሎስ ስለ አስከፊው የባርነት ቀንበር አንዳች ነገር ሳይል መቅረቱ ሊያስገርም ቢችልም ነገር ግን ሐዋርያው የተከተለው ሥልት ከዚህ በላቀ ውጤታማ ነበር፡፡ ሁሉንም ዓይነት የመደብ ልዩነቶች በማፈራረሱ ረገድ ወንጌል ተስማሚና የሰጠ ነው (ገላ. 3፡28፣ ቆለ. 3፡10-11)፡፡ አሁን ሐዋርያው አናሲሞስን መልሶ ወደ ፊልሞና የላከው እንደ ባሪያ ሳይሆን በየሱስ እንደ ልጁና በጌታ እንደ “ተወዳጅ ወንድም” (ቁ. 15) ነበር፡፡

የኮብላይ ባሮች የወደፊት ዕጣ ደብዛዛ መሆኑን ጳውሎስ ያውቅ ነበር፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሊያዙ ከመቻላቸው በላይ በሰቆቃና በድኅነት የተሞላ ሕይወት እንዲገፉ የተፈረደባቸው ነበሩ፡፡ አሁን ግን አናሲሞስ በክርስቶስ የፊልሞን ወንድምና ፈቃደኛ ሠራተኛ እንደመሆኑ የተሻለ ተስፋ አለው፡፡ ምግቡ፣ መኖሪያውና ሥራው በፊልሞና አማካይነት አስተማማኝ ይደረግለታል፡፡ ተበላሽቶ የነበረው ግንኙነት ወደ ትክክለኛው ስፍራ እንዲመለስ መደረጉ በአናሲሞስ ሕይወት ላይ አስደናቂ ልዩነት ምጣቱ እሙን ነው፡፡ አናሲሞስ “ታማኙና ተወዳጁ ወንድም” በሚል የሚጠራ የጳውሎስ የወንጌል አጋር ሠራተኛ ለመሆን በቃ (ቆለ. 4፡9)፡፡ በሁለቱ የየሱስ አማኞች መካከል እርቅ እንዲወርድ እጅግ የጋለ ቅንአትና ልበ ቀናነት የነበረው ጳውሎስ በገንዘብ የሚካካስ ነገር እንኳ ቢኖር ማንኛውንም መጠን ከገዛ ኪሱ ለመክፈል ዝግጁ ነበር፡፡

በሰብዓዊ ግንኙነትዎ ሊከሰቱ ከሚችሉ ማናቸውም ዓይነት ጭንቀት፣ ውጥረት ብሎም ስብራት ከላይ ከተመለከቱት የወንጌል መርኅዎች ምን ዓይነት ጠቃሚ ነጥቦች መውሰድ ይችላሉ? እነዚህ መርኅዎች በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ሊከሰቱ የሚችሉ መሰነጣጠቆችን የሚገቱት እንዴት ነው?

ሕዳር 2
Nov11

መንፈሳዊ ስጦታዎች ለአንድነት


የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩባትን ጥልቅ ችግሮች ቀደም ባለው ትምህርታችን ተመልክተናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ወሳኝ የሆኑትን እንደ ፈውስና ወደ ቀደመው ሰላም መመለስ--የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት መርኅ ይሰጡናል? 1ቆሮ. 3:5–11፣ 12:1–11፣ 2ቆሮ. 10:12–15፡፡





ሐዋርያው በእነዚህ ምንባቦች ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ወሳኝ የሆኑ መርኅዎችን አብራርቶአል፡፡ ምንም እንኳ እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ጋር ተጣምሮ የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ቢገነባም፤ የሱስ ለቤተ ክርስቲያን የተለያዩ አገልግሎቶች ልዩ ልዩ ሠራተኞችን መመደቡን በመልእክቱ ያሳያል (1ቆሮ. 3፡9)፡፡

እግዚአብሔር እንድንፎካከር ሳይሆን እንድንተባበር ጥሪ ያቀርብልናል፡፡ እያንዳንዱ አማኝ ለክርስቶስ አካል ብሎም ለማኅበረሰቡ ተባብሮ አገልግሎት የሚሰጥበት ጸጋ ከእግዚአብሔር ተሰጥቶታል (1ቆሮ. 12፡11)፡፡ የላቁ ወይም ያነሱ የሚባሉ ስጦታዎች የሉም፡፡ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም አስፈላጊ ናቸው (1ቆሮ. 12፡18-23)፡ ፡ በእግዚብሔር የተሰጡን ስጦታዎች ለራስ ወዳዱ ስብዕና ታይታ ሳይሆን ወንጌልን እንድናሰራጭ በመንፈስ ቅዱስ የተበረከቱልን ስጦታዎች ናቸው፡፡

ተስፋ ወደ ማስቆረጥ ወይም ወደ ግብዝነት የሚመራው ያንዱን ስጦታ ከሌላው ጋር ማወዳደር--ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው፡፡ ሌሎች እጅግ ከእኛ “የላቁ” ሆኖ የሚሰማንና የምናስብ ከሆነ በየትኛውም አገልግሎት ላይ ብንገኝም ራሳችንን ከእነርሱ ጋር እያወዳደርን በቀላሉ ተስፋ ወደ መቁረጥ ልናመራ እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል እኛ ለክርስቶስ የምንሠራውን ሥራ ከሌሎች በላቀ ውጤታማ አድርገን የምንመለከት ከሆነ በኩራት ስሜት መኮፈስ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁለቱም አመለካከቶች የእርስ በርስ ግንኙነታችንንና ለክርስቶስ የሚኖረንን ውጤታማነት ያሽመደምዳሉ፡፡ ክርስቶስ በሰጠን ተጽእኖ ዙሪያ ስንሠራ በምስክርነታችን ደስታና ፍስሐ እናገኛለን፡፡ አገልግሎታችን የሌሎች አባላትን ጥረት የተሟላ በማድረግ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንድትራመድ ያስችላታል፡፡

በአገልግሎት ስጦታው ቅናት ስላሳደረቦት የሆነ ሰው ማሰብ ይችላሉ? በተመሳሳይ እርስዎ ያሎትን ስጦታዎች ከሌሎች ጋር ሲያነጻጽሩ ም ን ያህል የኩራት ስሜት ተሰምቶታል? ዋናው ነጥብ ጳውሎስን አሳስበው የነበሩ ነገሮች በኃጢአት በወደቀው ዓለም ውስጥ ሁሌም የሚኖሩ መሆናቸው ነው፡፡ በየትኛውም ወገን ልንወድቅ ብንችል፤ ከክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት ጠብቀን ለመጓዝ ወሳኝ የሆኑትን ራስ ወዳድ ያልሆኑ አመለካከቶች መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሕዳር 2
Nov11

ይቅር ማለት


ለመሆኑ ይቅርታ ማድረግ ወይም ይቅር ማለት ምንድን ነው? ይቅር ማለት አስከፊ በደል የፈጸመብንን ሰው ድርጊት ትክክለኛነት ማሳየት ይችላል? ይቅርታዬ በበደል ፈጻሚው ንስሐ ላይ የተመሰረተ ነው? ያዘንኩበት ሰው የእኔ ይቅርታ የማይገባው ቢሆንስ?

የሚከተሉት ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የይቅርታ ተፈጥሮ ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዱናል? ሮሜ 5:8–11፣ ሉቃ. 23:31–34፣ 2ቆሮ. 5:20-21፣ ኤፌ. 4:26፡፡





ክርስቶስ እኛን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ተነሳሽነቱን ወሰደ፡፡ “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ የሚመራ” ነው (ሮሜ 2፡4)፡፡ እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅን፡፡ የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንጂ ንሰሐ መግባታችንና ኃጢአታችንን መናዘዛችን እርቅ አይፈጥርም፡፡ የእኛ ድርሻ የተደረገልንን መቀበል ብቻ ነው፡፡

ኃጢአታችንን ሳንናዘዝ የይቅርታን በረከቶች መቀበል አለመቻላችን እሙን ነው፡ ፡ ይህ ማለት ኑዛዜአችን በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ይቅርታን ይፈጥራል ማለት አይደለም፡፡ ይቅርታ ሁሌም ቢሆን በእርሱ ልብ ውስጥ አለ፡፡ ይልቁንም የኃጢአት ኑዛዜ የለመንነውን መቀበል እንድንችል ያደርገናል (1ዮሐ. 1፡9)፡፡ ኑዛዜ እጅግ ወሳኝ የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን አመለካከት ሰለሚለውጥ ሳይሆን እኛ በእርሱ ላይ ያለንን አመለካከት ስለሚለውጥልን ነው፡፡ ንስሐ በመግባትና የኃጢአት ኑዛዜ በማድረግ በደለኝነታችንን እንድንቀበል ለሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ራሳችንን ስናስገዛ የተለወጥን እንሆናለን፡፡v ይቅር ማለትም እንዲሁ ለገዛ መንፈሳዊ ደኅንነታችን በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ በደል የፈጸመብን ግለሰብ ይቅርታ የማይገባው ሰው ቢሆን እንኳ ለይቅርታ ዳተኞች ስንሆን ከጎዳን ሰው ይበልጥ ተጎጂዎች እንሆናለን፡፡ አንድ ሰው ቢበድሎትና ይህን የበደሎትን ሰው ይቅር ባለማለትዎ ጉዳቱ በውስጥዎ እያመረቀዘ ቢሄድ፤ ግለሰቡ ከቀድሞው በበለጠ እንዲጎዳዎ እየፈቀዱለት ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ አጉል ስሜቶችና ጉዳቶች ለቤተ ክርስቲያን መከፋፈልና ውጥረት ተደጋጋሚ መንስዔዎች ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል መፍትሔ ማግኘት ያልቻለ ጉዳት የክርስቶስን አካል አንድነት ይጎዳል፡፡

ይቅርታ ክርስቶስ እኛን ከኩነኔ ይቅር እንዳለ በተመሳሳይ ከኩነኔአችን ነጻ ማድረግ ነው፡፡ ይቅር ማለት ለበደለን ሰው ባህሪ ትክክለኛነት ምክንያት መሆን አይችልም፡ ፡ እኛ በክርስቶስ ላይ በደል ፈጽመን ስናበቃ እርሱ ይቅር ብሎ እንደታረቀን ሁሉ በተመሳሳይ ከበደለን ሰው ጋር እርቅ መፍጠር እንችላለን፡፡ ይቅር የተባልን ሰዎች እንደመሆናችን እኛም ይቅር ማለት እንችላለን፡፡ የተወደድን እንደመሆናችን እኛም መውደድ እንችላለን፡፡ ይቅር ማለት ምርጫ ነው፡፡ የሌላው ሰው ድርጊት ወይም አመለካከት ምንም ሊሆን ቢችል እኛ ግን ይቅር ማለትን መምረጥ እንችላለን፡፡ ይህ እውነተኛው የየሱስ መንፈስ ነው፡፡

በክርስቶስ ያገኘነው ይቅርታ ላይ ትኩረት ማድረጋችን ሌሎችን ይቅር ማለት መማር እንድንችል እንዴት ይረዳናል? ይህ ይቅርታ የክርስትና ተሞክሮአችን ወሳኝ ገጽታ የሆነው ለምንድን ነው?

ሕዳር 2
Nov11

ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ እና አንድነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 18፡15-17፡፡ በቤተ ክርስቲያን አባል በደል ሲደርስብን ውዝግቦችን ለማርገብና መፍትሔ ለማምጣት የሱሰ የሰጠን ሦስቱ ቅደም ተከተሎች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን የመፍትሔ ሃሳቦች ለዛሬው ሁኔታች ጥቅም ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?





የሱስ በማቴ. 18 ለመስጠት የተመኘው ምክረ ሃሳብ በቤተ ክርስቲያን ሊነሱ የሚችሉ ግላዊ ግጭቶችን ለመፍታት ጉልህ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሁለቱ የተጋጩ ሰዎች ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ማድረግ የእርሱ እቅድ የሆነው የሱስ “‘ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተ እና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው’ ” (ማቴ. 18፡15) ሲል በይፋ ይናገራል፡፡ በሁለት ሰዎች ጥል መሃል ብዙዎች በገቡ ቁጥር ልዩነቶች ይበልጥ እየሰፉ ሊሄዱና የሌሎች ወገኖችም ኅብረት የዛኑ ያህል ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡ ፡ የገላጋዮችን ጎራ መለየት ተከትሎ ጉዳዩ ይበልጥ እየከረረ የሚሄድበት ዕድልም ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች ልዩነቶቻቸውን በግል ለማርገብ ሲሞክሩ፤ በክርስትና የፍቅር መንፈስና የጋራ መተሳሰብን ተከትሎ የእርቅ ድባብ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ወገኖች ልዩነቶቻቸውን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርጉ መንፈስ ቅዱስ አብሮአቸው ለመሥራት የሚያስችለው ሁናቴ ይፈጠርለታል፡፡

አንዳንዴ ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረግ የአንድ ወገን ልመናና ተማጽኖ ውጤት ላያመጣ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲፈጠር አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ይዞ የተጋጨነውን ሰው ማናገር ተገቢ እንደሆነ የሱስ ይነገረናል፡፡ ይህ ሁለተኛው ዓይነት የእርቅ ሂደት ሁሌም ቢሆን የመጀመሪያውን መከተሉ የግድ ይሆናል፡፡ ዓላማው ሰዎችን ማቀራረብ እንጂ ማራራቅ አለመሆኑ ላፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም፡ ፡ በቅራኔ ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች ለማግባባት የቀረበው አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ዓላማ የአንዱን ወገን ትክክለኛነት ለማሳየት ወይም ሌላኛውን ጥፋቱ ያንተ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ሁለት ባይተዋር ልቦች በክርስቲያን ፍቅር እና ርኅራኄ የተሞሉ ምክረ ሃሳቦችን በመለገስና በጸሎት አደራ ጭምር ለመሸምገል ሊመጡ ይገባል፡፡ በእርግጥ እነዚህን ሁሉ ቅራኔዎችን መፍቻ መንገዶች ውጤታማ የማይሆኑባቸው አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ጉዳዩን ወደ ቤተ ክርስቲያን መውሰድ ተገቢ አድርጎ የሱስ ያዘናል፡፡ በእርግጥ ይህን ሲል ሰንበት ማለዳ የሚደረገውን የአምልኮ አገልግሎት ለግል ጸብና ውዝግብ ሽምገላ አውሉ አለማለቱ ግልጽ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅደም ተከተሎች ሁለቱን ግለሰቦች ለማስታረቅ እገዛ ማድረግ ካልቻሉ ጉዳዩን ለመውሰድ ተገቢ የሚሆነው ስፍራ የቤተ ክርስቲያን ቦርድ ይሆናል፡፡ አሁንም ቢሆን የክርስቲያኖች ዓላማ በሻከሩ ልቦች መሃል እርቅ እንዲሰፍን ማድረግ እንጂ አንዱን አካል ጥፋተኛ አድርጎ ሌላውን በነፃ ለማሰናበት አለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

“ቅሬታዎ ሥር ሰድዶ ወደ ጥላቻ እንዲያመራ አይፍቀዱ፡፡ የወንድምዎን ቁስል በመርዛማ ቃላት አያመርቅዙ፡፡ ይህ የሰሚውን አእምሮም ይበክላልና፡፡ የእርስዎንም ሆነ ያልተግባቡት ሰው አስተሳሰብ በመራር ቃላት እየሞላ እንዲቀጥል አይፍቀዱ፡፡ ይልቁንም ወደ ወንድምዎ ሄደው በትህትናና በቅንነት ስለ ጉዳዩ ያናግሩት፡፡”—Ellen G. White, Gospel Workers, p. 499.

ሕዳር 2
Nov11


ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Read the article “Forgiveness,” pp. 825, 826, in The Ellen G. White Encyclopedia. “ሠራተኞች ከገዛ ነፍሳቸው የማይነጥሉት ክርስቶስ ሲኖራቸው፣ ሁሉም ዓይነት ራስ ወዳድነት ሲሞት፣ መፎካከር ሲከስም፣ በእኔ እበልጥ እሳቤ ጠብ ወይም ጥል ሲቀር፣ አንድነት ሲሰፍን፣ ራሳቸውን ሲቀድሱ፣ አንዱ ለሌላው ያለው ፍቅር ሲታይና በልብ ውስጥ ሲሰማ--ከተሰጠው አምላካዊው ተስፋ ቅንጣት ታክሏ ሳትጎድል የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእርግጠኝነት በላያቸው ይፈሳል፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 175. “በታላቁ የጌታ ቀን ማማችንና መጠጊያችን አድርገን ከክርስቶስ ጋር የምንቆም ከሆነ ሁሉንም ዓይነት ቅናት፣ ምቀኝነትና እኔ እበልጥ ባይነት ከእኛ ማስወገዳችን የግድ ይሆናል፡፡ ቅድስና የጎደላቸው እነዚህ ነገሮች ዳግም እንዳያለመልሙና እንዳያፈሩ ከሥረ መሠረታቸው መንቀልና ማስወገድ አለብን፡፡ ራሳችንን በጌታ በኩል ቅዱስ አድርገን እናኑር፡፡”—Ellen G. White, Last Day Events, p. 190.


የመወያያ ጥያቄዎች





1. ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ቆለ. 3፡12-17፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ የቆላስያስ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲኖራቸው በሚያበረታታቸው የክርስትና ብቃቶች ዙሪያ ተወያዩ፡፡ እነዚህ ብቃቶች ለግጭት አፈታቶች መሰረት የሆኑት ለምንድን ነው? የሱስ በማቴ. 18፡15-18 የሚሰጠንን መርኅዎች በማቀፍ ምሪት የሚሰጡን እንዴት ነው?

2. በቆለ. 3፡12-17 የቀረቡትን አስተምህሮዎች በድጋሚ ይመልከቱ፡፡ እነዚህ ነገሮች ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ፍጹም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

3. ጠቅለል አድርገን ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ማለትም ወደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ስንመለከት--ወደ ዓለም ለመድረስ የሚያስፈልገው ዓይነት ኅብረት እንዳይኖረን ወደ ኋላ የሚጎትተን የገዘፈ ነገር ምንድን ነው? ኃይማኖታዊ አስተምህሮአችን ነው? በእርግጥ አይደለም፡፡ እነርሱማ ለዓለም እንድናውጃቸው በእግዚአብሔር የተሰጡን መልእክቶች ናቸው፡፡ ምናልባት ችግሩ በብቸኝነት ያለው ራሳችን ላይ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያሉን ግላዊ ግንኙነቶች፣ ምቀኝነት፣ ንትርክ፣ ራስ ወዳድነት፣ እኔ እበልጥ--እኔ እሻል ምኞት እና ሌሎች እልፍ ነገሮች፡፡ በሁሉም ቤተ ክርስቲያኖቻችን አንድነትን ከማየታችን አስቀድሞ በቅድሚያ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለውጥ እንዲያመጣ ለምን አብልጠው አይማጸኑትም?

ማጠቃለያ፡ የየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ስለ ፈውስና ስለ መለወጥ ያወሳል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጋር መልካምና የቀረበ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ አስመልክቶ ብርቱ መርኅዎችንና ምሳሌዎችን ይሰጠናል፡፡