በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከኅዳር 1-7

ሰባተኛ ትምህርት

Nov 10 - Nov 16




ግጭቶች ሲከሰቱ

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሐዋ. 6:1– 6፣ ሐዋ. 10:1–23፣ ማቴ. 5:17–20፣ ሐዋ. 11:3–24፣ ሐዋ. 15:1–22፣ አሞጽ 9:11-12፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :--“ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና፡፡ በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ አንድ ናችሁ፡ ፡” (ገላ. 3፡27-28)፡፡

በ ማናቸውም ክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ አስቸጋሪ ከሚባሉ ተግባራት መካከል አንዱ የአመለካከት ልዩነት ሲፈጠር ከቤተ ክርስቲያን ማንነትና ተልዕኮ አኳያ አንድነትን ጠብቆ ማቆየት ነው፡፡ ልዩነቶች በከረሩ ቁጥር አስከፊ መዘዞች ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ የዛሬዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች በአዲስ ኪዳን ከምንመለከታቸው የተለዩ አይደሉም፡፡ ሰዎች ያው ሰዎች እንደመሆናቸው አንኳር በሚባሉ ነጥቦች ዙሪያ ልዩነቶች ይከሰታሉ፡፡ በዕውቀት ላይ ባልተመሰረቱ የሀሳብ ልዩነቶች እንዲሁም ቁልፍ በሚባሉ የብሉይ ኪዳን ታሪኮችና ልምዶች አተረጓጎም መንስኤ በቀደሙት ክርስቲያኖች መካከል ሙግት ነበር፡፡ ደግ አሳቢዎቹና አስተዋይ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና በአምላካዊው ቃል ኃይል ለውጥረቶቹ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ባያደረጉ ኖሮ ግጭቶቹ ቤተ ክርስቲያንን ገና በእንጭጩ ሊያጠፏት በቻሉ ነበር፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን የጉባዔን ኅብረት የተለማመደችበትን መንገድ አጥንተናል፡፡ በዚህ ሳምንት ይህችው ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን በማመንመን ሕልውናዋን አደጋ ላይ ሊጥሉ የነበሩ ወስጣዊ ግጭቶችን እንዴት እንደፈታች እንመለከታለን፡፡ ግጭቶቹ ምን ነበሩ? እንዴት መፈታት ቻሉ? ከእነዚህ ተሞክሮዎች ዛሬ ምን መማር እንችላለን?

ሕዳር 2
Nov11

ጎሳን ያማከለ ጭፍን ጥላቻ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሐዋ. 6፡1፡፡ በየዕለቱ ለመበለቶች ይደረግ በነበረው ምግብ የማደል ሥራ በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን የተነሳው ማጉረምረም ምክንያቱ ምን ነበር?



አንዳንድ የቀደሙ ክርስቲያኖች ከግሪክ በመጡ አይሁድ መበለቶች ላይ በነበራቸው ጭፍን ጥላቻ የተነሳ ከዕብራውያን ወገኖቻቸው ያነሰ ምግብ ያድሏቸው ነበር፡፡ ይህ በገሃድ የታየ አድልዎ በቀደሙት አማኝ ማኅበረሰብ መካከል መሰነጣጠቅ ፈጠረ፡፡ በወቅቱ በተጨባጭ አድልዎ ስለመኖሩ ወይም ስለ አለመኖሩ ጥቅሱ የሚለው ነገር ባይኖርም ነገር ግን አንዳንዶች ችግሩ አለ ብለው እንደሚያምኑ ብቻ ይገልጻል፡፡ ይህ ውዝግብ የቀደመችውን ቤተ ክርስቲያን አንድነት ሥጋት ላይ ጥሎ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን የጎሳ ልዩነት ፈጥኖ መታየቱ አብልጦ ትኩረትን ይስባል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 6፡2-6፡፡ ይህን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍታት በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን የተወሰዱ ቀለል ያሉ እርምጃዎች ምን ነበሩ?



የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ማደግ በሐዋርያት ላይ የማያባራ ከባድ ሸክም አስከትሎ ነበር፡፡ በተለምዶ “ዲያቆናት” በሚል የሚታወቁት (ምንም እንኳ አዲስ ኪዳን እንዲህ ብሎ ባይጠራም) የእነዚህ ሰባት ሰዎች መሾም በየሩሳሌም የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ውጥረት በመቀየር ብዙዎች በአገልግሎት የሚሳተፉበትን በር ከፈተ፡፡ ሐዋርያት ግሪክኛ ተናጋሪ አማኞች ያቀረቡትን ቅሬታ በጥንቃቄ ካዳመጡ በኋላ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጠየቋቸው፡፡ ለሐዋርያት ረዳት የሚሆኑ ሰባት ሰዎችን የመምረጡን ኃላፊነት ለዚሁ ቡድን መተዋቸውን ተከትሎ ግሪክ ተናጋሪ ሰባት ደቀ መዝሙሮችን በዕጩነት አቀረቡ፡፡ ተመራጮች “በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸው” (ሐዋ. 6፡3) መሆን ነበረባቸው፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ወንጌልን የመስበክና ለመበለቶች ምግብ የማደል ኃላፊነትን አካትቶ የነበረው የሐዋርያት አገልግሎት ለሁለት ቡድን ተከፍሎ የነበረ ሲሆን፤ እያንዳንዱ አገልግሎት ወንጌልን ለማወጅ እኩል ዋጋ ነበረው፡፡ ሉቃስ ቃሉን የሚሰብኩትን ሐዋርያትና ምግብ የሚያድሉ (ሐዋ. 6፡1) ዲያቆኖችን ለመጥቀስ የሚጠቀመው “አገልግሎት” /ዲያኮኒያ/ (ሐዋ. 6፡4) የተሰኘውን ተመሳሳይ ቃል ነው፡፡ መሪዎች ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ከአማኞች ብዙዎቹን በአንድ ላይ ከመሰብሰባቸው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ዓይነት ቁም ነገር ይመለከታሉ? (ሐዋ. 6፡2)

ሕዳር 3
Nov12

የአሕዛብ መለወጥ


በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ራሱን የቻለ ታላቅ ክስተት የሆነው የአሕዛብ ወደ የሱስ ክርስቶስ ወንጌል መለወጥ፤ በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ህይወት፣ ሕልውናና ተልዕኮ የውዝግብ መንስዔና ሥጋት መሆን የሚችል ነበር፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 10፡1-23፡፡ አሕዛብ ወንጌልን እንዲቀበሉ በማዘጋጀቱ ረገድ መንፈስ ቅዱስ በብዙዎች ልብ እየሠራ እንደ ነበር በምንባቡ የሚጠቁሙን ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?



ጴጥሮስ በዚህ በተመለከተው ራእይ በጣም ግራ ተጋብቶ እንደነበር እሙን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ እንደ ታማኝ አይሁድነቱ በሕጉ መሰረት ንጹህ ያልሆነ ወይም ርኩስ ምግብ ፈጽሞ ተመግቦ ባለማወቁ ነው (ዘሌዋ. 11፣ ሕዝ. 4፡14፣ ዳን. 1፡18)፡፡ ሆኖም የዚህ ራእይ ዓላማ ከምግብ ጋር የተያያዘ ሳይሆን፤ ለወንጌል ስርጭት ጋሬጣ በነበረው በአይሁዳውያንና አሕዛብ መካከል ስለ ተገነባው ግድግዳ ነበር፡፡ እነዚህ ግድግዳዎች እንደ ዛሬው ሁሉ በጥንቱም ዓለም ተስፋፍተው ነበር፡፡ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት የመጨረሻዎቹ አሥርተ ዓመታት የነበረው ክርስትና በተጨባጭ የተገነባው በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተተነበየውን መሲህ የግል አዳኛቸው አድርገው በተቀበሉ አይሁዳውያን ነበር፡፡ እነዚህ የቀደሙ የየሱስ ተከታዮች በተማሩት መሰረት ሕጉን የሚታዘዙ ታማኝ አይሁዳውያን ነበሩ፡፡ የየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የብሉይ ኪዳኖቹ ትእዛዛት እንደፋቁ ወይም እንደሻሩ አድርጎ አልተመለከተም (ማቴ. 5፡ 17-20)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 10፡28-29፣ 34-35፡፡ ጴጥሮስ በኢዮጴ የተቀበለውን ራእይ ፍቺ እንዴት ነበር ያስተዋለው? እንዲህ ዓይነቱን ትርጓሜ እንዲሰጥ ምን ገፋፋው?



አሕዛብ የክርስትናን ኅብረት የሚቀበሉበትን መንገድ መንፈስ ቅዱስ አዘጋጅቶ እንደ ነበር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንመለከታለን፡፡ ደግሞም አሕዛብ በቅድሚያ መገረዝ ወይም ወደ ይሁዲነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ይህን ማድረግ የሚችሉ ሆኑ፡፡

በጴንጤቆስጤ ቀን በየሱስ ተከታዮች ላይ የፈሰሰው ተመሳሳይ መንፈስ በቆርኔሌዎስና በቤተሰቦቹ ላይ መፍሰሱ ይህ በእርግጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ጴጥሮስና ባልደረቦቹን አሳምኖ ነበር (ሐዋ. 10፡44-47)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአይሁዳውያን እንደ ተሰጠ ሁሉ ለአሕዛብም መፍሰስ የሚችል ከሆነ፤ የሱስን እንደ መሲህ ለመቀበል መገረዝ እንደ ቅደመ ሁኔታ አለመጠየቁ ግልጽ ሆነ፡፡ ይህ ድምዳሜ በቀደምት ክርስቲያኖች መሃል ለተከሰተው ብርቱ ሥነ መለኮታዊ ውዝግብ መንስኤ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡

ሕዳር 4
Nov13

በመንፈስ መመራት


በቄሳርያ በነበረው ቆርኔሌዎስ ላይ የሆነው ነገር ብዙም ሳይቆይ ዜናው በየሩሳሌም ይኖሩ ወደ ነበሩ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጆሮ በመድረሱ ጴጥሮስ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡ በወቅቱ ጴጥሮስ ባደረገው ነገር አማኞች ተበሳጭተዋል፡ ፡ ምክንያቱም አይሁዳውያን የሙሴን ሕግ በሚረዱት መሰረት ታማኝ አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር እንዲመገቡ አይፈቀድላቸውም ነበር (ሐዋ. 11፡3)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 11፡4-18፡፡ ጴጥሮስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራና በዚህ ክስተት ስለነበረው የመሪነት ሚና ምን ዓይነት ማብራሪያ ሰጠ? የሆነውን በመግለጹ ረገድ የነጥቡ ዋንኛ ሃሳብ ምን ነበር?



ምንም እንኳ አንዳንዶች በጴጥሮስ ድርጊት ሕጋዊነት ዙሪያና አሕዛብን ለማጥመቅ እንዴት ውሳኔ ላይ እንደ ደረሰ ጥያቄ አንስተው የነበረ ቢሆንም ጴጥሮስ ግን ለዚህ ሁሉ በቂ ምስክር ነበረው፡፡ በጴንጤቆስጤ የተገለጠላቸው ያው መንፈስ ቅዱስ በተመሳሳይ መንገድ ተገልጦ ስላረጋገጠለት (ሐዋ. 11፡12) በዚህ ጉዳይ የተስተዋለው የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም፡፡ “ይህን በሰሙ ጊዜም የሚሉትን አጥተው እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ‘ይህማ ከሆነ፣ አሕዛብም ወደ ሕይወት ይመጡ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሐን ሰጥቷዋል ማለት ነዋ’” (ሐዋ. 11፡ 18)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 11፡19-24፡፡ በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ሕይወት በመቀጠል ምን ተስተዋለ?



በቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የተፈጸመው ይህ ያልተለመደ ድርጊት በተለይ ለእነርሱ ብቻ የሆነ እንጂ ለሌላው አሕዛብ ሊደገም እንደማይችል አድርገው በየሩሳሌም የነበሩ አንዳንዶች ያስቡ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ አስተሳሰብ የመንፈስ ቅዱስ እቅድ አልነበረም፡ ፡ ከእስጢፋኖስ ሞት (ሐዋ. 8፡1) በኋላ በየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የደረሰውን ስደት ተከትሎ ከየሩሳሌምና ይሁዳ አልፈው ወደ ሰማርያ፣ ፊንቄ፣ ቆጵሮስና አንጾኪያ ተበተኑ፡፡ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሱስን የግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ፡፡ የሱስ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተንብዮአል (ሐዋ. 1፡8)፡፡ አሕዛብ በአስደናቂና በከፍተኛ መጠን ወደ ክርስትና ከመግባታቸው አኳያ ራሳችንን በቀደምት አማኝ አይሁዳውያን ቦታ ብናስቀምጥ፤ ለነበሩ ተግዳሮቶች ምላሽ መስጠት ቀላል እንዳልነበር ለመረዳት አንቸገርም፡፡

በቤተ ክርስቲያንና በመልዕክታችን ዙሪያ ጠባብ አመለካከት በማስተናገድ ምስክርነታችንን ሊያሰናክል ከሚችል ሁኔታ መገታት የምንችለው እንዴት ነው?

ሕዳር 5
Nov14

የየሩሳሌም ጉባዔ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 15:1-2፣ ገላ. 2:11–14፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጽኑ ውዝግብ የፈጠሩ ሁለት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?



የቀደሙት ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን አንድነት ዙሪያ የተጋፈጡት አደገኛ ሁኔታ በተጨባጭ የደረሰ ክስተት ነበር፡፡ አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች ደኅንነት ለእግዚአብሔር የኪዳኑ ሕዝቦች ብቻ እንደተወሰነ በማሰብ መገረዝን እንደ አንድ የኃይማኖቱ መስፈርት ይመለከቱ ነበር፡፡ ከታማኝ የአይሁድ ዘይቤዎች አንዱ ከአሕዛብ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አለማድረግ--ከተደረገ ግን ደኅንነታቸው እንደሚረክስ ያስቡ ነበር፡፡

አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር ባላቸው ግንኙነት ጥብቅ ወግና ልማድ ነበራቸው፡፡ ሐዋርያት የየሱስ ተከታይ ለመሆን ምኞት ወዳደረባቸው አሕዛብ መድረስ ሲጀምሩ እነዚህ ወጎች ለአዲሱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንቅፋት ሆኑ፡፡ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን እንደ ተተነበየው መሲህ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ሕዝቦች አዳኝ በመሆኑ አሕዛብ መዳን የሚፈልጉ ከሆነ በመጀመሪያ የአይሁድን እምነት ተቀብለው ሲያበቁ፤ በመቀጠል ከአይሁዳውያን ጋር የኪዳኑን ሕግ መከተል አልነበረባቸውምን? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 15፡3-22፡፡ በየሩሳሌም ጉባዔ የቀረቡት አንዳንድ ጠንከር ያሉ ጉዳዮች ምን ነበሩ?



ይህ ከግርዘት እና ከአሕዛብ ጋር በሚኖር ግንኙነት ዙሪያ በቀጥታ ከብሉይን ኪዳን ታሪክ አተረጓጎም የተወሰደ ጠንከር ያለ ጉዳይ ስር የሰደደ ውዝግብ አስነስቶ ነበር፡ ፡ ሐዋርያት፣ ሽማግሌዎችና ከአንጾኪያ የመጡ ልዑካን በአንድ ላይ ለውይይት ቢቀመጡም ንግግራቸው ያለምንም መፍትሔ ረጅም ጊዜ የወሰደ ይመስላል፡፡ ከዚያም ጴጥሮስ፣ በርናባስና ጳውሎስ ንግግር አደረጉ፡፡ ጴጥሮስ በንግግሩ እግዚአብሔር ወደ አሕዛብ የሚደርሱበት መንገድ የቀየሰበትን ራእይ እንደ ሰጠው በማውሳት ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘውንም ስጦታ ጠቀሰ፡፡ ጳውሎስና በርናባስም እንዲሁ እግዚአብሔር በእነርሱ በኩል ለአሕዛብ ያደረገውን ታሪክ አካፈሉ፡፡ በውጤቱም የብዙዎች ዐይኖች ለዚህ አዲስ እውነት ተከፈቱ፡፡ “‘እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን’ ” (ሐዋ. 15፡11) ሲል ጴጥሮስ ተናገረ፡፡ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ተጠብቆ የቆየ ወግና ልማድ እነሆ ወንጌል በፈነጠቀው ብርሃን ተገፈፈ፡፡

ለረጅም ጊዜ ውስጥዎ ተጠብቆ የቆየ ኃይማኖታዊ አስተምህሮን የተረዱበትን መንገድ የቀየሩበት አጋጣሚ አለ? በኃይማኖታዊ አስተምህሮው በነበሮት አረዳድ ዳግመኛ ጥያቄ ሊኖርዎ ቢችል ከበፊቱ ልምድዎ ምን ተምረዋል?

ሕዳር 6
Nov15

አስቸጋሪ የመፍትሔ ሀሳብ


በአንጾኪያ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን ወደ የሩሳሌም ለመላክና ለግጭታቸው የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት የተወሰነ መተማመን ደረጃ ላይ መድረስ ነበረባት፡፡ ሆኖም በሐዋርያትና በሽማግሌዎች መካከል ሰዓታት የፈጀ ውይይት ከተደረገ በኋላ ጉባዔውን እንደ መራ የሚታመነው የየሱስ ወንድም ያዕቆብ መደረግ በሚኖርበት ጉዳይ ላይ ውሳኔ አሳለፈ (ሐዋ. 15፡13-20)፡፡ አሕዛብ ክርስቲያን ለመሆን መገረዝን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ወግና ልማዶች በመታዘዝ ወደ ይሁዲነት መለወጥ እንደማያስፈልጋቸው ጉባዔው ግልጽ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ አሞጽ. 9፡11-12፣ ኤር. 12፡14-16፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ እስራኤላውያን አጎራባች አገሮች ምን ዓይነት ትንቢት ተናግረው ነበር?



ያዕቆብ ከአሞጽ 9 በመጥቀስ በሚያቀርበው መረጃ ስለ ሕዝቦች መዳን በሌሎች የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የቀረቡ ማመሳከሪያዎችን እንመለከታለን፡፡ በእስራኤል ምስክርነትና ተሞክሮ መላውን ዓለም ማዳን አምላካዊው እቅድ ነበር፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ያቀረበው ጥሪ እርሱንና የእርሱን ትውልድ ተጠቅሞ ሁሉንም ሕዝብ መባረኩን ያካትታል (ዘፍ. 12፡1-3)፡፡ አሕዛብን አስመልክቶ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ምሪት--የጴጥሮስ፣ የበርናባስና የጳውሎስ አገልግሎት እንዲሁም የአያሌ አሕዛብ ወደ ክርስትና መለወጥ በዋዛ ሊታለፍ የማይችል ሐቅ ነው፡፡ እነዚህ ምስክርነቶች አብዛኞቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ እያገኙ መምጣታቸውን በየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያን ማኅበረሰብ መሪዎች መገንዘብ እንዲችሉ ረድተዋቸው ነበር፡፡ በእርግጥ እስራኤላውያን ከአሕዛብ ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር የሚመሩባቸውን ሕጎችና መመሪያዎች ራሱ እግዚአብሔር አስቀድሞ ሰጥቶአቸው ነበር (ዘሌዋ. 17፡ 18)፡፡ ያዕቆብም ቢሆን ወደ ውሳኔ ሲደርስ እነዚሁኑ ሕጎች ጠቅሷል (ሐዋ. 15፡29)፡፡ አሕዛብ አምላካዊውን ሕዝቦች ተቀላቅለው በየሱስ ደኅንነት እንዲያገኙ እግዚአብሔር ጥሪ እያቀረበ እንደ ነበር ለእያንዳንዳቸው ግልጽ ሆነላቸው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከዚያ በፊት ያልተመለከቷቸውን ወሳኝ እውነቶች በመግለጥ በአምላካዊ ቃል ላይ ጥልቅ ማስተዋል ሰጣቸው፡፡

በየሩሳሌም ለተደረሰው ውሳኔ የአንጾኪያ አማኞች የሰጡትን ምላሽ ሐዋ. 15፡30-35 እንደሚከተለው ይነግረናል፡ “ሕዝቡም ካነበቡት በኋላ አበረታች በሆነው ቃሉ ደስ ተሰኙ” (ሐዋ. 15፡31)፡፡

የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ራሷን ለአምላካዊ ቃል በማስገዛት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንዴት በፍቅር፣ በአንድነትና በመታመን በአንድነቷ ላይ ያንዣበበውን ቀውስ እንደ ቀለበሰች በዚህ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በቀረበው ብርቱ ምሳሌ እንመለከታለን፡፡ ሌሎች እያሉ ያሉትን ነገር ልንሰማ የማንፈልግ ቢሆንም እንኳ ነገር ግን የሚባለውን መስማትና ልክ ሊሆኑ እንደሚችሉም ከግምት ማስገባት ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ ምን እንማራለን?

ሕዳር 7
Nov16


ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Ellen G. White, “A Seeker for Truth,” pp. 131–142; “Jew and Gentile,” pp. 188–200, in The Acts of the Apostles. “ከተለያዩ ስፍራዎች የተመረጠውና በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የሰጠው ጉባዔ የአይሁድና የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናትን በማዋቀር ግንባር ቀደም ከሆኑ ሐዋርያትና መምህራን የተውጣጣ ልዑክ ነበር፡፡ የየሩሳሌም ሽማግሌዎች፣ ከአንጾኪያ የመጡ ረዳት ኃላፊዎችና ብርቱ ተጽእኖ የነበራቸው ቤተ ክርስቲያኖች የጉባዔው አካል ነበሩ፡ ፡ ጉባዔው ብሩህ በሆነ የውሳኔ ዐውድ እና በመለኮታዊው ፈቃድ ላይ በተመሰረተ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና የተመራ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ራሱ መንፈስ ቅዱስን ለአሕዛብ በመስጠት በዚህ ዙሪያ ላነሱት ጥያቄ መልስ መስጠቱን በውይይታቸው መጨረሻ መመልከት ቻሉ፡፡ የእነርሱ ድርሻ የመንፈስን ምሪት መከተል እንደሆነ አስተዋሉ፡፡ “ሁሉም የክርስትና አካል በዚህ ጥያቄ ላይ ድምፅ እንዲሰጥ አልተጠራም፡፡

ሐዋርያትና ሽማግሌዎች፣ ተጽእኖ አሳዳሪዎች እንዲሁም ፍትሕና ርትዕ አዋቂዎች በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ያገኘውን ይህን ሕገ ደንብ አረቀቁ፡፡ ይሁን እንጂ በውሳኔው ሁሉም ደስተኞች አልነበሩም፡፡ በራሳቸው አስተሳሰብ ይመሩ የነበሩ ግትር አስተሳሰብ አራማጅ አንጃዎች በሀሳቡ አልተስማሙም ነበር፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሃሳብ በራሳቸው ኃላፊነት በሥራው መሳተፍ ነበር፡፡ ማጉረምረም የበዛበት፣ ስህተት ፈላጊና ልል ባህሪ ይስተዋልባቸው የነበሩ እነዚህ ሰዎች አዳዲስ እቅዶችን እየነደፉ እግዚአብሔር የወንጌልን መልእክት እንዲያስተምሩ የሾማቸውን ወገኖች አገልግሎት ወደ ኋላ ለመጎተት ይጥሩ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዚያ ጊዜ ከገጠሟት እንቅፋቶች አንስቶ እስከ ዘመን መጨረሻ ተመሳሳይ ሳንካዎች አይለዩአትም፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 196, 197.


የመወያያ ጥያቄዎች





1. ግጭቶች በሚነሱ ጊዜ በዚህ ሣምንት ከተመለከትናቸው ግጭቶችን የመፍቻ ዘዴዎች የትኞቹን ቅደም ተከተሎች ለቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብዎ መተግበር ይቻላል? ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያን ካስተናገደቻቸው ጉዳዮች አንዱ ሥነ መለኮታዊ እንደመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ከባሕል፣ ከፖለቲካ ወይም ከጎሳ ጋር በተያያዘ ሥጋት ሲገጥመው ከእነዚህ ተሞክሮዎች ምን እንማራለን? ከላይ ከተመለከትናቸው መሃል የትኞቹን መርኅዎች ልናወጣ እንችላለን?

2. ከላይ የቀረበውን የኤለን ኋይት ጽሑፍ ደግመው ይመልከቱ፡፡ ምንም እንኳ ውሳኔውን ተከትሎ የተገኘው ውጤት አመርቂ ቢሆንም አንዳንዶች ግን አልረኩም ነበር፡፡ ከዚህ አሳዛኝ እውነታ ምን ዓይነት ትምህርት እናገኛለን?

ማጠቃለያ፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን አውዳሚ ውጤት ሊያስከትሉባት በሚችሉ ብዛት ያላቸው ውስጣዊ ውዝግቦች ተወጥራ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ስትመራና ራስዋን ለእግዚአብሔር ቃል ስታስገዛ እነዚህን ውዝግቦች ማስወገድና ከመከፋፈል መመለስ እንደምትችል ተመልክተናል፡፡