ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2:9፣ ዘፀ. 19:5-6፣ ኤፌ. 2:19–22፣ 1ቆሮ. 3:16-17፣ 1ቆሮ. 12:12–26፣ ዮሐ. 10:1–11፣ መዝ. 23፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :--“አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል አንድ ነው፡፡ ክርስቶስም እንዲሁ ነው፡፡” (1ቆሮ. 12፡12)፡፡
መ
ጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ማንም ሰው መጽሐፉ በምስሎችና ምልክቶች
የተሞላ መሆኑን እና እነዚህ ትዕይንቶች ደግሞ ከራሳቸው ይልቅ ወደ
ገዘፉ ተጨባጭ ሐቆች እንደሚያመለክቱ ይረዳል፡፡ ለአብነት ያህል
መላው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመሥዋዕት ሥርዓቶች የሱስን እና አጠቃላይ የደኅንነት
እቅድ የሆነውን እውነት አመላካች ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
ሌሎች አያሌ ምስሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን እንደውም አንዳንዴ
በጣም መሰረታዊ የሆኑት እንደ ውሃ፣ እሳት እና ነፋስ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች እንደየ
ጽሑፉ ዐውድ የመንፈሳዊው እና ሥነ መለኮታዊው እውነት ገጽታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ
የሱስ በሚከተለው ንግግሩ “ነፋስ ወደሚወስደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤
ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ
ሁሉ እንዲህ ነው” (ዮሐ. 3፡8) በማለት ነፋስን በመንፈስ ቅዱስ ተምሳሌትነት
ሲያቀርብ ይታያል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በዓለም ፊት ተገልጦ እንዲታይ ጥሪ የሚያቀርበውን
ቤተ ክርስቲያናዊ ኅብረት ይፋ ለማድረግ ብዛት ያላቸውን ምስሎች ይጠቀማል፡፡
ምንም እንኳ እያንዳዱ ግለሰባዊ ምልከታ በራሱ የተሟላ ሊሆን ባይችልም፤ ይልቁንም
እነዚህ ምስሎች ጠቅለል አድርገው ስለ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ብዙ ነገሮችን
ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል፡--ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ስላላት ግንኙነት፣
አባላት እርስ በርሳቸው ስለሚኖራቸው ግንኙነቶችና በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን
ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖራት ግንኙነቶች አንኳር የሚባሉት ናቸው፡፡
የዚህ ሣምንት ትምህርታችን በአንዳንድ ገጽታዎች ላይ ምልከታ በማድረግ በክርስቶስ
ያለንን ኅብረት እንዴት እንደሚገልጹልን እናያለን፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2፡9፣ ዘፀ. 19፡5-6፣ ዘዳ. 4፡20፣ 7፡6፡፡ ጥቅሶቹ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በተለየ ስላላቸው ክብር ምን ይላሉ?
ቤተ ክርስቲያን ስንል ጉዳዩ በቀጥታ የሚያያዘው ከሕንፃው ሳይሆን ከሕዝብ
(ከምዕመን) ጋር ቢሆንም፤ አሁንም ሕዝብ ስንል ማንኛውንም ሕዝብ ማለታችን
አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን እንደ አባታቸውና አዳኛቸው የተቀበሉ፣
በክርስቶስ የተዋጁና እርሱን የሚታዘዙ የእግዚአብሔር ንብረት ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይህ
ገጽታ የደኅንነት እቅድ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሕዝቦች
እንዳሉት እና በብሉይ ኪዳኗ እስራኤል ብሎም በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን መካከል
የተሳሰረ ቀጣይነት ለመኖሩ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ጊዜ አንስቶ
ከውሃ ጥፋት በፊትና በኋላ ከነበሩ አባቶች እንዲሁም ከአብርሃም ጋር ኪዳን ገባ፡
፡ ይኸውም ሕዝቡ በዚህ ዓለም የአምላካዊው ፍቅር፣ ምህረትና ፍትሕ ተወካይ
እንዲሆን ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝቦች “የተመረጠ ትውልድ”፣ “የንጉሥ ካህናት”፣ “ቅዱስ
ሕዝብ” ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ መጠሪያዎች የሕዝቡን ለተለየ ዓላማ መጠራት
ይጠቁማሉ፡ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን
ታላቅ ሥራ እንድታውጁ” ነው (1ጴጥ. 2፡9)፡፡ በተጨማሪ አባባሉ በዘፀ. 34፡6-7
የቀረበውን የእግዚአብሔርን በምሕረት የተሞላ ባህሪ ያስተጋባል፡ “ቤተ ክርስቲያን
አባሎቿ በሕይወታቸው የከበረውን አምላካዊ ባህሪ እንዲያንጸባርቁና መልካምነቱንና
ምኅረቱን ለሰዎች ሁሉ ያውጁ ዘንድ እግዚአብሔር የገዛ ርስቱ አድርጎ ገዛት”—The
SDA Bible Commentary, vol. 7, p. 562.
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 7፡6-8፡፡ እግዚአብሔር የአብርሃምን ትውልድ የገዛ ሕዝቡ
አድርጎ እንዲመርጥ የገፋፋው ነገር ምንድን ነው? ይህ ዛሬም ሊሠራ የሚችለው
እንዴት ነው?
ዛሬ “ቅዱስ ሕዝብ” (ሌላው የቤተ ክርስቲያን ገጽታ?) የሚለው መጠሪያ የሚውለው
ለየትኛው አገር ሕዝብ ነው ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ብንችልም መልሱ--የለም ነው፡፡
ሁሉም ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የእግዚአብሔር ፍቅር እና ጸጋ የማይገባቸው ናቸው፡
፡ ምንም እንኳ ቅዱስ ሕዝቦቹ እንድንሆን አምላካዊው ቃል ጥሪ ቢያደርግልንም
የእስራኤል መመረጥና መመስረት እውን የሆነው ከገዛ ፍቅሩ የተነሳ እንጂ ከሰብዓዊው
ፍጡር በመልካም ሥራ አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ የእግዚአብሔር
ሕዝቦች መመስረት እርሱ ለፍጡሮቹ ያለውን ፍቅር ያመላክታል፡፡ ሕዝቦቹ ኃጢአት
ሠርተው በአገር ደረጃ ክህደት ቢፈጽሙም፤ እግዚአብሔር ግን ለአብርሃምና ሕዝቡን
ለሚያድነው ለዘሩ ፍሬ ለክርስቶስ የገባውን ኪዳን ጠበቀ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች
የተመረጡት ከጸጋው የተነሳ እንደመሆኑ የመዳናቸውም መንስኤ ይሄው ነው፡፡ ይህ
ጭብጥ ተራ የሆነው ትውልዳችን ከማይገባው አምላካዊ ጸጋ ጋር የፈጠረውን ትስስር
ያስታውሰናል፡፡
“የእግዚአብሔር ሕዝቦች” ብንሆንም እንኳ ደኅንነታችን ክርስቶስ ለእኛ
ያደረገው ነገር ውጤት እንጂ እኛ ለራሳችን ማድረግ የምንችለው ነገር ያለመሆኑን
የተቀደሰ እውነታ ሁልጊዜ ከፊታችን እንደጠበቀን መጓዝ ያለብን ለምንድን ነው?
በአዲስ ኪዳን የተገለጸው ሌላው የእግዚአብሔር ሕዝቦች ገጽታ አምላካዊው ቤት ወይም ቤተሰብ ነው፡፡ በዐለቶች እና ግንቦች የተመሰለው ዘይቤአዊ አነጋገር በቤተክርስቲያን ለሚስተዋል የረቀቀ እና እርስ በርስ የመረዳዳት ሰብዓዊ ተፈጥሮ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “ሕያዋን ድንጋዮች” (1ጴጥ. 2፡5) በማለት ይጠቅሳል፡፡ ይህ ዘይቤአዊ አነጋገር ጽናትንና ጥብቅነትን ይገልጻል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡19-22፡፡ ጳውሎስ በመልእክቱ ጎላ አድርጎ የገለጻቸው ሃሳቦች ምንድን ናቸው? ይህ ምስል በቤተክርስቲያን ውስጥ ስላለው አንድነት ምን ይነግረናል?
በዚህ ጥቅስ ጳውሎስ ሁለቱን የቤተ ክርስቲያን ገጽታዎች በአንድ ያጣምራል፡
አንደኛው ግዑዙ ቤት ወይም ህንፃ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ሰብዓዊው ቤተሰብ ነው፡፡
አንድ ድንጋይ በራሱ በጣም የከበረ ባይሆንም ከሌሎች ድንጋዮች ጋር ሲተሳሰር
ግን ብርቱ ውሽንፍር መቋቋም የሚችል ግንብ ይሆናል፡፡ ማንም ክርስቲያን ብቻውን
ብርቱ ሊሆን አይችልም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር ሊዛመድና ኅብረት
ሊፈጥር ይገባል፡፡ አንድ ሕንፃ ጽኑ ሆኖ እንዲቆም ከተፈለገ በጠንካራ መሰረት ላይ
ማረፉ የግድ ይሆናል፡፡ መሰረቱ የሱስ ክርስቶስ ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር
ቤት “የማዕዘን ድንጋይ” ነው (1ቆሮ. 3፡11)፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን
የአገልግሎቷ የማዕዘን ድንጋይ ከማድረግ የምትገታ ከሆነ ሕልውናዋን ታጣለች፡፡
ቤተ ክርስቲያን--የየሱስ ሕይወት፣ ሞት፣ ትንሳዔ፣ እርገት እና ዳግም ምጽአት ናት፡፡
ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ፈጥረው መልካሙን የየሱስ የምሥራች ለዓለም የሚያካፍሉ
አማኝ ማኅበረሰቦችን ቅርጽ ትፈጥራለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን አጀንዳ የሱስ እና የሱስ
ብቻ ነው፡--ማንነቱ፣ ለእኛ ያደረገልንና እያደረገልን ያለው ነገር፣ እርሱን እንደ ጌታ
እና እንደ አዳኝ የሚቀበል ማንኛውም ሰው የሚሰጠው ስጦታ…፡፡ የቤተሰብ ገጽታም
እንዲሁ ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ ይህኛው የሚያርፈው በራሳቸው በሰዎች የእርስ በርስ
ግንኙነት ላይ ነው፡፡ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህት የተለመደው የቤተሰብ ገጽታ
ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለ ትስስር ጠንካራ እንደ መሆኑ
አንዱ ለሌላው ያለው ታማኝነት ውጪያዊውን ግንኙነት ያስንቃል፡፡ ታማኝነት ትልቁ
የኅብረት ክፍል እንደመሆኑ--ለመሆኑ ታማኝነት የጎደለው የቱንም ዓይነት ኅብረት
ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው?
ይህ ገጽታ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንዴት ይዛመዳል? የቤተ ክርስቲያን አባላትም
እንዲሁ የአንዱ ትልቅ ቤተሰብ አካል ናቸው፡፡ እኛ እርስ በርስ የተሳሰርነው እንደ
ሰብዓዊ ፍጡርነታችን የሁላችንም አባት በሆነው አዳም ብቻ ሳይሆን ሁለተኛው
አዳም ከሆነው ከየሱስ ጋር “በአዲስ ልደት” ተሞክሮ በመዛመዳችን ነው፡፡ በዚህ
የተነሳ የእርስ በርስ ኅብረት የፈጠርነው በኃይማኖታዊ እውነቶች ብቻ ሳይሆን ከየሱስ
ባገኘነው አዲስ ሕይወት የተለወጥን በመሆናችን ጭምር ነው፡፡
የሚያሳዝነው ሁሉም ሰው ከገዛ ቤተሰቡ ጋር ድንቅ የሚባል ዓይነት ተሞክሮ
የለውም፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ ገጽታ ለእነርሱ እምብዛም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡
ታዲያ እንደ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ወገኖች ኖሯቸው የማያውቀው ዓይነት ቤተሰብ
መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
ሌላው ጳውሎስ ከህንፃ ጋር በተቆራኘ ጥቅም ላይ ያዋለው ዘይቤአዊ አነጋገር
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ ውድ እና የከበረ
ዋጋ ያለው ሕንፃ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ጳውሎስ በ1ቆሮ. 6፡19 ሰብዓዊውን አካል
ከመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ጋር ሲያመሳክር በ1ቆሮ. 3፡16-17 ደግሞ ይህንኑ ምስል
ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጋር በማገናዘብ ያቀርባል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 3፡16-17፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ
ናት ሲል ምን ማለቱ ነው? በቁ. 17 ስለ ምን እያስጠነቀቀ ነው?
ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ባወሳበት በዚህ ጽሑፍ ስለ ግዑዙ ሕንፃ ወይም
የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ እየተናገረ እንዳልነበር ግልጽ ነው፡፡ ይህ
ዘይቤአዊ አነጋገር ለአንድ ዓላማ የተስማማ ኅብረት ስላለው አካል--ይኸውም
የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ኅብረት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑንና እርሱ
በመንፈስ በመካከላቸው እንደሚያድር ይናገራል፡፡
እንደ ጳውሎስ ከሆነ እግዚአብሔር በክርስትና ኅብረት መሃል ያድራል፡፡ ሆኖም
ይህን ኅብረት ለማጥፋት የሚሞክር ማንም ሰው አምላካዊውን ፍርድ ተከትሎ
የሚመጣውን ውጤት ይቀበላል፡፡ የአማኞች አንድነት--የዚህ ኅብረት እና
የእግዚአብሔር በዚህ መቅደስ መገኘት አስኳል ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ ጥቅስ የአንድን
ሰው አካላዊ ሁኔታ ከመንከባከብና ከመጠበቅ አኳያ አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ ሲውል
ቢስተዋልም (ክርስቲያኖች ይህን ማድረግ ቢጠበቅባቸውም) ጳውሎስ በተለይ እያነሳ
የነበረው ነጥብ ግን ይህ አልነበረም፡፡ ይልቁንም መልእክቱ የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት
የሚያፈርሱትን ያስጠነቅቃል፡፡
ከዚህ ቀደም ባለው ምዕራፍ ጳውሎስ ለአንድነት ፈታኝ ያላቸውን ነጥቦች በማንሳት
ይሞግታል፡ “በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር” መከፋፈል አለ (1ቆሮ. 3፡3)፡፡ እነዚህ
አመልና ባህሪዎች የእግዚአብሔርን በቤተ መቅደሱ መገኘት የሚያገልሉ ደንበኛ
የክርስትና አንድነት ስጋቶች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር በቤተ ክርስቲያን የሚነሱ ግጭቶች
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ማፍረስ ይችላሉ፡፡
ግጭቶች በቤተ ክርስቲያን ሲቀሰቀሱ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የሰጠው
ምክረ ሃሳብ ዛሬም በሥራ ላይ መዋል የሚችል ነው፡፡ “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ
መለያት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም
እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” (1ቆሮ. 1፡10)፡፡
በጳውሎስ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን የገጠሟት ችግሮች--ቅናት፣
ክርክርና መከፋፈል ብቻ አልነበሩም፡፡ እነዚህን ችግሮች እኛም ብንሆን ዛሬ
እንጋራቸዋለን፡፡ አንድነታችን ሥጋት ላይ እንዳይወድቅ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ
ለመሥራት በመሻቱ ረገድ የእያንዳንዳችን ሚና ምንድን ነው?
ምናልባት ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ስለ ተለያዩ ብልቶች ጠንከር ባለ መንገድ
የሚናገረው በጣም ታዋቂው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስል ወይም ገጽታ የክርስቶስ አካል
ነው፡፡ “አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ
ቢሆኑም አካል አንድ ነው፡፡ ክርስቶስም እንዲሁ ነው… እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ
አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ” (1ቆሮ. 12፡12፣ 27)፡፡
አንዱ አካል የተገነባው ከብዙ ልዩ ልዩ ብልቶች እንደ መሆኑ እያንዳንዱ ብልት የራሱ
የሆነ የተለያየ ተግባርና ኃላፊነት አለው፡፡ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን
ሁኔታም ከዚህ ተመሳሳይ ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 12፡12-26፡፡ ለመሆኑ ይህ ብዙ ብልቶች ያሉት አንድ
አካላዊ ገጽታ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ መተግበር የሚችለው እንዴት ነው?
ዓለማቀፍ አደረጃጀት ላላቸው እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ባሉ
ተቋሞች መተግበር የሚችለውስ እንዴት ነው?
እውነተኛ የክርስቲያን አንድነት የሚመጣው በጥላቻና በንቀት ውስጥ ሳይሆን
ከዚያ በጸዳ ብዝሐነት ነው የሚል ሀሳብ የያዘው በ1ቆሮ. ምዕ. 2 የምናገኘው የጳውሎስ
አስተምህሮ ጥልቀት ያለው ተጨባጭ እውነታ ይዞአል፡፡ የዚህ የተለያየ ማንነት
መገለጫ የሆነው ብዝሐነት ምንጩ መንፈስ ቅዱስ በመሆኑ መደነቅ የለብንም፡፡
ሰብዓዊው ብልቶች አስገራሚ አንድነት ብቻ ሳይሆን አስገራሚ ልዩነትም እንዳላቸው
ሁሉ በዚህ ብዝሐነት ውስጥ የክርስቶስን ምሉዕነትና ባለጸግነት የሚገልጸው የክርስቶስ
አካል ነው፡፡
ይህ ገጽታ እንደ ቤተ ክርስቲያን እኛን በቀጥታ ይናገራል፡፡ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት
ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ተስፈንጣሪ የሚባሉ ዕድገቶችን
አስመዝግባለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከተለያዩ ታሪካዊ ዳራዎች፣ ባሕሎችና አካባቢዎች
የተውጣጡ አማኞችን ማቀፏ እሙን ቢሆንም፤ የብሔር፣ የዘር፣ የባህል፣ የትምህርት
እና የዕድሜ ልዩነቶች በክርስቶስ ያለንን አንድነት እንዲከፋፍሉ መፍቀድ የለብንም፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ይህን ብዝሐነት የአንድነት ምንጭ አድርጎ ካረቀው በልዩነቶቹ
ውስጥ ሁላችንም የክርስቶስ መሆናችን ተገልጦ የሚታይ ይሆናል፡፡
ከላይ እንደ ተመከትነው እያንዳንዳችን ማንም ብንሆን ወይም ከየትም ብንመጣ
ሁላችንም ከመስቀሉ ግርጌ እኩል ነን፡፡ በዙሪያችን ያለው ዓለም አብልጦ በተበጣጠሰ
ቁጥር ቤተ ክርስቲያን በብዝሐነት ውስጥ ወዳለው አንድነት መድረስ እንደሚቻል
ማሳየቷ የግድ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የወንጌልን ፈዋሽና አስታራቂ ኃይል
ገልጦ የማሳየት ክህሎት አላቸው፡፡
ጳውሎስ እንዴት ወደዚህ አንድነት መድረስ እንደሚቻል ይነግረናል፡፡
ክርስቶስ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ… ነውና” (ኤፌ. 5፡
23)፡፡ “እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው” (ቆለ. 1፡18)፡፡ እያንዳንዱ
አማኝ ከክርስቶስ ጋር በመንፈስ በመገናኘቱ መላው አካል ከአንድ ማዕድ ይቆርሳል፡፡
እንዲህ ከሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት፣ ያወቅነውን እውነት መታዘዝ እንዲሁም
በክርስቶስ አካል አንድነት የምንጋራውን የአምልኮና የጸሎት ተሞክሮ አስፈላጊነት
እንደ ተጋነነ ነገር መቁጠር አንችልም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 10፡1-11፡፡ ከዚህ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከቀረበ ምሳሌያዊ አነጋገር ስለ አንድነት የሚናገሩት የትኞቹ ናቸው? በተጨማሪ መዝ. 23 ያንብቡ፡፡
በዘመናዊዎቹ ትላልቅ ከተሞች የትኛውንም ዓይነት የከብት እርባታ ሥራ መመልከት
አይቻልም፡፡ ዛሬ በበግ እና በእረኛ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያውቁ ጥቂት
ቢሆኑም ነገር ግን የሱስ ይህን ምሳሌያዊ አነጋገር ሲጠቀም ሰዎች ምን ለማለት
እንደፈለገ ያስተውላሉ፡፡ የሱስ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ” ብሎ እንደተናገረ ይህን
አባባል ተቀብለውና አድንቀው ወዲያውኑ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” ከሚለው
መዝ. 23፡1 ጋር ያመሳክራሉ፡፡ እዚህ ላይ የምናገኘው ምስል ወይም ገጽታ ግልጽ ብቻ
ሳይሆን ጉልህና ደማቅ ነው፡፡ በጥንታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ባህል እረኞች ስለ
በጎቻቸው ማንኛውንም ፈታኝ ሁኔታ በመጋፈጥ ረገድ የታወቁ ነበሩ፡፡ እረኝነት ስለ
አምላካዊው ባህሪና ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመግለጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም
ላይ ከዋሉ እጅግ ከበሬታ ካላቸው ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
በበጎች መልክ የቀረቡት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ገጽታ አስደናቂ ነው፡፡ የበጎች
ገራምነትና ራሳቸውን ከክፉ መከላከል አለመቻል አንዱ መሳጭ ተፈጥሮአቸው
መሆኑን ተከትሎ ከክፉ ከለላና ምሪት ለማግኘት በመልካም እረኛ ላይ መተማመን
ያደርጋሉ፡፡ በጎች ብልጠት የጎደላቸው ሆነው ይታያሉ፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚ በጎች
የሚጠፉበት ሁናቴ ሲከሰት እረኛው የገቡበት ገብቶ መልሶ ወደ በረቱ ያመጣቸዋል፡፡
ግልገል በጎች በእቅፍ መያዝን ጨምሮ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለበጎች ተገቢውን
ጥንቃቄ ለማድረግ ትዕግሥትና የሚፈልጉትን መረዳት ያሻል፡፡ ይህ በብዙ መንገድ ቤተ
ክርስቲያንን የሚወክል ፍጹም ምስል ይሰጠናል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባል ከመንጋው
እረኛ ጋር በሚኖረው ግንኙነት የተትረፈረፈ ጥቅም ከማግኘት ውጪ ሊያስፈራው
የሚገባ አንዳች ነገር አይኖርም፡፡
በግ የእረኛውን ድምፅ የመስማቱን አስፈላጊነት አስመልክቶ የሱስ በዚህ ምሳሌያዊ
አነጋገሩ አጽንኦት ሰጥቶአል፡፡ እንደ ሁናቴው ጥቂት መንጎችን በአንድ ጉረኖ ወይም
አጥር ባለው የበጎች መዋያ በማኖር ከክፉ መጠበቅ ይቻላል፡፡ ታዲያ ኋላ ላይ መለየት
የሚችሉት እንዴት ነው? እረኛው ማድረግ የሚኖርበት በጉሮኖው በራፍ ቆሞ
መጣራት ነው፡፡ በጎቹ ድምፁን አውቀው ወደ እርሱ ይመጣሉ፡፡ “የራሱ የሆኑትንም
ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል”
(ዮሐ. 10፡4)፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የእረኛውን ድምፅ መስማት ወሳኝ ነው፡፡ በእርግጥ
የእግዚአብሔር ሕዝቦች አንድነትና ደኅንነት ከእርሱ ጋር ባላቸው ቅርበት ይወሰናል፡፡
ድምፁን ሰምተው ከመታዘዛቸውም ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው፡፡
ባጠቃላይ ሰዎች እንደ በግ መታየቱን አይፈልጉም፡፡ ሆኖም በግን ያማከለው
ምሳሌያዊ አነጋገር ለእኛ ተገቢና ገጣሚ የሆነው ለምንድን ነው? እዚህ ላይ
የምናገኘው ምስል እረኛ እንደሚያስፈልገንና ድምፁን መታዘዝ ተገቢ መሆኑን
የሚነግረን እንዴት ነው?
፡ Ellen G. White, “The Divine Shepherd,” pp. 476–484, in
The Desire of Ages; “The Church on Earth,” pp. 240–243, in Counsels
for the Church.
“ቤተ ክርስቲያንን በማነጽና በማሳደግ የእግዚአብሔር አብ፣ የክርስቶስና የመንፈስ
ቅዱስ ወሳኝ ተግባራትን ተከትሎ የአማኞች መተባበርና አንድነት ወሳኝ ሚና አላቸው::
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ቤተ መቅደስ የሚለውን ዘይቤአዊ አነጋገር ከየሩሳሌም ቤተ
መቅደስ እና ከዘመን አይሽሬው የግሪክና ሮማውያን ውሁድ ኪነ ሕንፃ ጥበብ ዐውድ
አማኞች የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና በዐይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ አድርገው አቅርበዋል፡
፡ በዘመናት የተስተዋለው የአብያተ ክርስቲያናቱ ኪነ ሕንፃ እምብዛም የማይለዋወጥ
ተጽእኖ ያሳረፈ ይመስላል፡፡ ዘይቤያዊው አነጋገር ከሥነ ሕይወታዊው ምሳሌ ጥምረት
እና ከሥነ ሕንፃ አኳያ ጥቅም ላይ መዋሉ ጉዳዩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ ከብዙ ድካምና
ትዕግሥት በኋላ ‘የተጠናቀቀውን ሕንፃ ከመመልከት ይልቅ የግንባታ ታሪኩን ሂደት
በዐይነ ህሊናችን ለመሳል እንገፋፋለን፡፡’ ቤተ ክርስቲያን ‘የሕያው እግዚአብሔርን
ቤተ መቅደስ’ (2ቆሮ. 6፡16) ሕይወትና ታሪክ በትህትና የምትገልጽበት በዓይነቱ ልዩ
የሆነ አስደናቂ መብትና ሥልጣን ተሰጥቶአታል፡፡ ”—John McVay, “Biblical Metaphors for the Church: Building Blocks for Ecclesiology,” in Ángel Manuel
Rodríguez, ed., Message, Mission, and Unity of the Church (Hagerstown,
Md.: Review and Herald®, 2013), p. 52.
1.
ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የቤተ ክርስቲያን ገጽታ ወይም ምስል አሰብ
ያድርጉ፡፡ በአብዛኛው የሚወዱት የትኛውን ዓይነት ነው? ለምን? ቤተ ክርስቲያን
የተገለጸችባቸው አንዳንድ ዘይቤአዊ አነጋገሮች በሚከተሉት ጥቅሶች ይገኛሉ፡
-1ጢሞቴ. 3:15፣ 2ጢሞቴ. 2:3–5፣ 1ጴጥ. 2:9፡፡ ዘይቤአዊ አነጋገሮቹ ስለ ቤተ
ክርስቲያን ሌላ ምን ያስተምራሉ?
2.
“እግዚአብሔር ህዝቦቹ በጠበቀ የክርስቲያን ኅብረት ቁርኝት ውስጥ
እንዲኖሩ ይፈልጋል፡፡ በወንድሞቻችን ላይ የሚኖረን መተማመን ለቤተ ክርስቲያን
ብልጽግና አስፈላጊ ነው፡፡ ኃይማኖታዊ ቀውስ ሲፈጠር በሕብረት መቆምና መወሰን
ጠቃሚ ነው፡፡ በግዴለሽነት የሚወሰድ አንድ እርምጃ እና አስተዋይነት የጎደለው
አንድ ድርጊት--ቤተ ክርስቲያን ለዓመታት እንዳታገግም የሚያደርግ አስቸጋሪ ሁናቴ
ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol.
3, p. 446. ለቤተ ክርስቲያን ኅብረት ምን ያህል በጥንቃቄ ዘብ መቆም እንዳለብን
አስመልክቶ ይህ ማስጠንቀቂያ ምን ሊያስተምረን ይገባል? እያንዳንዳችን ለዚህ
የተቀደሰ ዓላማ ያለን ሚና ምን ይመስላል?
3.
“የእግዚአብሔር ሕዝቦች” ብንሆንም የመዳናችን መመኪያ የእግዚአብሔር
ጸጋ ብቻ እንደሆነ በእሑዱ ጥናታችን በአጽንኦት ቀርቦአል፡፡ ለነገሩ “የእግዚአብሔር
ሕዝቦች” ተብለን እንድንጠራ ባለ ልዩ መብት ያደረገን በእርሱ መልካም ሥራና
የመስቀል ላይ መሥዋዕትነቱ ማመናችንና መመካታችን መሆኑ አከራካሪ ሊሆን
ይችላል? ለምን?
ማጠቃለያ፡--አዲስ ኪዳን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ተፈጥሮ እና ተልዕኮ
ለመግለጽ የተለያዩ ዘይቤዎችን ይጠቀማል፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ ዘይቤዎች
እግዚአብሔር ሕዝቦቹን በጥንቃቄ እንደሚያይና እንደሚጠብቅ ያስተምሩናል፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝቦች አንዱ ከሌላው ጋር በብዙ ኅብር የተገመዱ መሆናቸውንና
አንዳችን ለሌላው እንድንሠራ የተጠራንበትን ሥራ መሥራት እንዳለብን እነዚሁ
ምስሎች በተጨማሪ ያስተምሩናል፡፡