ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 28:1–14፣ ኤር. 3:14–18፣ መሳፍ. 17:6 ፣ 1ነገሥ. 12:1–16፣ 1ቆሮ. 1:10–17፣ ሐዋ. 20:25–31፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :--“ ‘የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው’ ” (ምሳ. 9:10)
የ እስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲታዘዝ የሚጠይቅ ተደጋጋሚ ጥሪ በብሉይ ኪዳን ነቢያት ይቀርብ ነበር፡፡ አለመታዘዝና ቸልተኝነት ወደ ክህደትና መከፋፈል መምራቱ ዕሙን ነው፡፡ ኃጢአት በተፈጥሮው ከሚያስከትለው ውጤት እነርሱን ለመታደግና በብዙ ባዕዳን ሕዝቦች መሃል ለመቀደስ ሲባል ለአምላካዊው ሕጎች መታዘዛቸው የግድ ነበር፡፡ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መከተሉ በአንድ ልብ እንዲሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ፤ ኅብረታቸው ዙሪያ ገባውን ሰንጎ የያዘውንና ጥሶ ሊገባ የሚዳዳውን የአረማውያን አምልኮ ልምድ እንዲቋቋሙ የሚያስችል መፍትሔ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ እስራኤል የተቀደሰና በዙሪያው ለነበሩ ሕዝቦች ምስክር እንዲሆን ነበር፡፡ ጌታ ዕብራውያንን ከምድረ ግብፅ ከታደገ በኋላ ሙሴ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡ “ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ፡፡ በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ ‘በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው’ ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና” (ዘዳ. 4፡5-6)፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ለእግዚአብሔር ታማኝ ቢሆኑ ኖሮ አብልጠው መባረካቸውና ለሌሎችም በረከት መሆናቸው እምብዛም አያጠያይቅም፡፡ በተቃራኒው ታማኝነትን ማጉደል ከብዙ በጥቂቱ ለመጠነ ሰፊ ችግርና መለያየት ይዳርጋል፡፡
በአለመታዘዝና ሥርዓተ አልበኝነት በተሞላው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ፤ አንዴ ታማኝ ሆነው ወደ እርሱ ሲመለሱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቀድሞው በባሰ ሲያምጹና ሲወዛገቡ በተደጋጋሚ ተስተውሎአል፡፡ ይህ ሁኔታ ሰርክ ሲታይ የኖረ ሐቅ ነው፡ ፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አምላካዊውን ፈቃድ ዘወትር በንቃት በተከተሉ ቁጥር የሰላምና ህይወት በረከት ይበዛላቸው ነበር፡፡ በተቃራኒው ሲያምጹና የገዛ ፈቃዳቸውን ሲከተሉ ህይወታቸው ከአምላካዊው ረድኤት የራቀና በጦርነት ብሎም በግጭት የተሞላ ይሆን ነበር፡፡ እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ አስቀድሞ ይህ ሊሆን እንደሚችል የተነበየው ጌታ ለህልውናቸው አደገኛ የሆነውን ውጤት እንዴት ማስቀረት እንደሚችሉ መፍትሔውን ሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 28፡1-14፡፡ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ቢጸና ኖሮ ምን ዓይነት በረከቶች መቀበል ይችል ነበር?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 3፡14-18፡፡ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ንስሐ እንዲገቡና
ወደ እርሱ እንዲመለሱ ካቀረበው ጥሪ ምን እንማራለን? ጌታ ለሕዝቡ ስላለው ፍቅር
እና ትዕግሥት ምን ይነግረናል?
ሕዝቡ አመጸኛ፣ ከኅብረት አፈንጋጭና ጣኦት አምላኪ ቢሆንም እግዚአብሔር
ግን አፍቃሪ፣ መሐሪና ቸር ሆኖ የቀረበበት የኤርምያስ መጽሐፍ እጅግ ያስገርማል፡፡
ሕዝቡ ንስሐ ገብቶ ከስህተት መንገዱ እንዲመለስ እግዚአብሔር ዘወትር ግብዣውን
ያቀርባል፡፡ አዲስ ንጽህናና ተስፋ እንደሚሰጠን በተደጋጋሚ ቃል ገብቶናልና፡፡
“ ‘ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፣ ‘እኔ መሐሪ ስለሆንሁ፣
ከእንግዲህ በቁጣ ዐይን አላይሽም’ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ‘ለዘላለም አልቆጣም፡
፡ በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመጽሽ፣ ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣
በየለምለሙ ዛፍ ስር አሳልፈሽ በመስጠት፣ ለእኔ ባለመታዘዝሽ በደለኛ መሆንሽን
ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ ’ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ኤር. 3፡ 12-13)፡፡
እነዚህ በኤርምያስ የተነገሩ ቃላት ለሕዝቡ የቀረቡት የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ለሙሉ
ችላ በተባለበት ወቅት ነበር፡፡ ምንም እንኳ በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን አንዳንድ የተሐድሶ
እንቅስቃሴዎች ቢጀመሩም፤ ብዙዎች እግዚአብሔርን በታማኝነት መታዘዛቸውን
እንዲቀጥሉ የሚያስችል መንፈሳዊ ግፊት አልተሰማቸውም ነበር፡፡ መተላለፋቸው፣
በጦኦት አምልኮ መውደቃቸውና ራስ ወዳድ ህይወታቸው ለመንፈሳዊና ፖለቲካዊ
ኪሳራ ዳርጎአቸው ነበር፡፡ እነዚህ ሕዝቦች አምላካዊውን ፈቃድ ከማድረግ ባፈገፈጉ
ቁጥር የወደፊቱ ነገር በእጅጉ አስጊ ገጽታ የተላበሰ ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር
በኤርምያስ አማካይነት እንዴት እንደተማጸናቸው በነቢዩ መልእክት እንመለከታለን፡
፡ የተሻለውን የወደፊት ማንነት ያቀደላቸው ይህ ጌታ ዳግመኛ ወደ ብልጽግና፣ ወደ
መንፈሳዊ ኅብረት እና የተሟላ ጤንነት ሊመልሳቸው ናፈቀ፡፡ ሆኖም ይህ እውን መሆን
የሚችለው እውነተኛውን እምነት ተከትሎ በሚመጣው እውነት ውስጥ በእምነት
መኖር እስከ ቻሉ ድረስ ብቻ ነበር፡፡
በመታዘዝ እና አለመታዘዝ መሃል ያለው ልዩነት በግል ሕይወትዎ ያለው
ትርጉም ምን ይመስላል?
የጌታን ፈቃድ ያልተከተሉ አያሌ እስራኤላውያን ድርጊታቸው ያስከፈላቸውን ብርቱ
ዋጋ የመጽሐፈ መሳፍንት ታሪኮች ያሳዩናል፡፡ እስራኤላውያን ከነዓን ገብተው ብዙም
ሳይቆዩ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ዙሪያቸውን ከከበቧቸው አጎራባች ሕዝቦች የሐሰት
አማልክት ጋር ማቆራኘት ጀመሩ--ይህ ደግሞ በትክክል እንዳታደርጉ የተባሉት ነገር
ነበር፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ሕዝቦች የገጠማቸው ችግር በዚህ ብቻ የሚያበቃ
አልነበረም፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መሳ. 17፡6፣ 21፡25፡፡ በእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል ይበልጥ
ይነሱ ስለነበሩ ችግሮች ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል? በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል
ይከሰቱ በነበሩ የመከፋፈል መንስዔዎች ዙሪያ ተነጋገሩ፡፡
የሕዝቡ አንድነት የተመሰረተው ለጌታ ታማኝ ለመሆን በነበራቸው ቁርጠኝነት
ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር በገቡት ኪዳን ነበር፡፡ እስራኤላውያን በተለይ
ማንነታቸው በአጎራባች ሕዝቦች ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ በፈቀዱና እያንዳንዱ ሰው
ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን ባደረገ ቁጥር ወደ ጥፋት ጎዳና ማዘንበሉ ሳይታለም
የተፈታ ነው፡፡ እኛ ሁላችን በኃጢአት የወደቅን ከመሆናችን አኳያ በየግላችን ይበጃል
ያልነውን አካሄድና የየልባችንን ዝንባሌ እንድንከተል ብንተው፤ እንድንራመድበት
እግዚአብሔር ከጠራን መንገድ ስተን መጥፋታችን ዕሙን ነው፡፡
እስራኤላውያን በመስፍኖች ይተዳደሩ በነበሩበት ወቅት ስለነበረው መንፈሳዊ እና
ማህበራዊ ሁኔታዎች የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ይነግሩናል?
መሳ. 2:11–13
መሳ. 3:5–7
“ያለመታዘዝን ውጤት ሙሴ ለሕዝቡ እንዲነግር ጌታ አስተምሮት ነበር፡፡
የእግዚአብሔርን ሕግ ለመታዘዝ ሲቃወሙ ራሳቸውን የሕይወት ባለቤት ከሆነው
ጌታ ስለሚነጥሉ፤ አምላካዊው በረከት ወደ እነርሱ ለመድረስ ይሳነዋል፡፡ አልፎ አልፎ
እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ሲከበሩና በጥንቃቄ ሲስተዋሉ በአይሁዳውያን ላይ ይፈሱ
የነበሩ በረከቶች ከእነርሱ አልፈው ለሌሎችም አጎራባች ሕዝቦች ይተርፉ ነበር፡፡ ሆኖም
የእነዚህ ሕዝቦች አብዛኛው ታሪክ እግዚአብሔርን የመርሳት እና በምድር የእርሱ
ተወካይ ሆነው ከፍ ባለ ማዕረግ ለመሰየም የተሰጣቸውን ልዩ መብትና ጥቅም የዘነጋ፣
ከማየትም የተጋረደ ነበር፡፡ በእርሱ የተጠየቁትን አገልግሎት በመንፈግ በአምላካቸው
ላይ ስርቆት ፈጸሙ፡፡ ለሌሎች መልካም ኃይማኖታዊ አመራር ከመስጠትና ምሳሌ
ከመሆን ተሰናከሉ፡፡ በባልንጀራዎቻቸውም ላይ ተመሳሳይ ስርቆት ፈጸሙ፡፡
መጋቢዎች ሆነው የተሾሙበትን የወይን ተክል ፍሬ ለራሳቸው ለመውሰድ ተመኙ፡
፡ ክፉ ምኞታቸውና ስግብግብነታቸው በአረማውያን ሳይቀር የተናቁ አደረጋቸው፡፡
በዚህም አረማዊው ዓለም የእግዚአብሔርን ባህሪ እና የመንግሥቱ መሰረት የሆነውን
ሕግ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጉምበትን ምክንያት አገኘ፡፡”—Ellen G. White,
Prophets and Kings, pp. 20, 21.
እንደ ቤተ ክርስቲያን የገዛ ድርጊቶቻችን ዙሪያችን ባሉ ባልንጀሮቻችን ላይ
ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉት እንዴት ነው? የእነዚህን ሰዎች ልብ በአዎንታዊ መንገድ
ለመንካት የሚያስችል ምን ዓይነት ቅመም በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ውስጥ
መመልከት ይችላሉ?
መሳ. 2: 11-13
መሳ. 3: 5-7
የክህደት መንገድ እና አስከፊ መዘዙ በአንድ ጀንበር እውን አልሆነም፡፡ ይልቁንም ለምዕተ ዓመታት የተከማቹ የተሳሳቱ ምርጫዎች በመጨረሻ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አስደንጋጭና አስፈሪ ጦስ ይዘው ከተፍ አሉ፡፡ የንጉሥ ሮብዓምን ታሪክ በ1ኛ ነገሥ. 12፡1-16 ይመልከቱ፡፡ በእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል እንዲህ ያለው አስፈሪ መከፋፈል እንዲከሰት ምክንያት የሆነው ነገር ምን ነበር?
“እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን በጎ ፈቃድ ሮብዓምም ሆነ እነዚያ ልምድ
የለሽ፣ አብሮ አደግ--ወጣት አማካሪዎቹ አስተውለው ቢሆን ኖሮ፤ በመንግሥታዊው
አስተዳደር ተሐድሶ እንዲመጣ ሕዝቡ ላቀረበው ጥያቄ ጆሮዎቻቸውን በሰጡ ነበር፡፡
ሆኖም ሴኬም ላይ በተደረገው ጉባዔ አግኝተውት በነበረው ዕድል መንስኤን ከውጤት
መለየት ስለተሳናቸው ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሕዝብ ላይ ሊኖራቸው ይገባ የነበረው
ተጽእኖ እስከ ወዲያኛው ደካማ ሆኖ ቀረ፡፡ በሰለሞን የንግሥና ዘመን የነበረው ጭቆና
ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግና በዚያ ላይ ሌላ ግፍ የማከል ቁርጠኝነት እግዚአብሔር
ለእስራኤል ከነበረው ዕቅድ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነበር፡፡ ሕዝቡም በእነርሱ ላይ
ጥርጣሬ እንዲያድርበት የሚያደርግ ከበቂ በላይ ምክንያት ማግኘት ቻለ፡፡ ንጉሡና
በእርሱ የተመረጡ አማካሪዎቹ ሥልጣንን እንዲህ ጥበብና ርኅራኄ በጎደለው መንገድ
ለመለማመድ መሞከራቸው፤ በሥልጣን መታበይንና በደረጃ ትምክህት ማድረግን
ገልጦ አሳየ፡፡”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 90.
ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን ጥበብ የሚያሻ ስለመሆኑ የሚከተሉት ሀሳቦች ምን
ይነግሩናል? የእውነተኛ ጥበብ ምንጩ ወዴት ነው?
ምሳ. 4:1–9
ምሳ. 9:10
ያዕ. 1:5
በሕዝቡ ላይ ተጭኖ የነበረውን ቀንበር ይበልጥ የማክበድ ውሳኔ ላይ የደረሰው
ችኩሉና ጥበብ የጎደለው የሮብዓም ታሪክ በእስራኤል መንግሥት ህልውና አሳዛኙ
ክስተት ነው፡፡ ንጉሡ ከሁለት የተለያዩ አማካሪ ቡድኖች ምክር ለማግኘት ሞክሮ
ነበር፡፡ ሆኖም ይህ የአብሮ አደጎቹንና ልምድ የሌላቸውን ወጣቶች እንጭጭ ሐሳብ
የመከተሉ የመጨረሻ ውሳኔው አባቱ ሰሎሞንም ሆነ አያቱ ዳዊት ላለፉት 80 ዓመታት
በገነቧት አገር ላይ ብርቱ ውድመት አስከተለ፡፡ ከአባቱ ይልቅ እርሱን የበረታ አድርጎ
በማቅረብ ሕዝቡን ለማስፈራራት የተቀበለው ይህ ምክር በእርግጥም የሞኝ ነበር፡፡
ሕዝቡ ተጭኖበት የነበረው ቀንበር እንዲነሳለት ለጠየቀው ተማጽኖ የድጋፍ ስሜት
አሳይቶ ሥራ ላይ ማዋል፤ ንጉሡ የሚከተለው የአመራር ዓይነት ሊሆን አይገባም
የሚለው የወጣት አማካሪዎቹ እምነት ነበር፡፡ በዚህ ፋንታ አምባ ገነን እና ጨካኝ
አድርጎ ራሱን ለሕዝቡ ማቅረብ ይኖርበታል ብለው ተናገሩ፡፡ በመጨረሻ ሮብዓም
ደካማን የሚያጠቃና የሕዝቡ አመኔታና ታማኝነት የማይገባው አድርጎ ራሱን አቀረበ፡
፡ ይህን ተከትሎ የእግዚአብሔር ዓላማ ያልነበረውና ሊሆን የማይገባው መከፋፈል
በእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል ተፈጠረ፡፡
በእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል ይደርስ የነበረው የመከፋፈልና ኅብረት
የማጣት ችግር በአዲስ ኪዳንም ሳያባራ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ቀጠለ፡፡ ለምሳሌ
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፋቸው የመጀመሪያዎቹ አራት ምዕራፎች በአማኞች
መሃል ሕብረት እንዲኖር ይማጸናሉ፡፡ በኤፌሶን እያለ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን
ስለ ተፈጠሩ የተለያዩ መከፋፈሎች የሰማው ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት
አስፈላጊነትና መለያየት መወገድ ብዕሩን ማንሳት ይጀምራል፡፡ የዚህ መጥፎ ሁኔታ
እየተስፋፋ መሄድ በእጅጉ ያሳሰበው ሐዋርያው፤ ለችግሩ የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ
ለመለገስ የተቻለውን ለማድረግ ሲጥር ይስተዋላል፡፡
በ 1ቆሮ. 1፡10-17 መሰረት በአማኞች መካከል መከፋፈልና ጠብ እንዲፈጠር
መንስኤ የሆነው ነገር ምን ሊባል ይችላል?
ከቀሎዔ ቤተሰቦች አንዱ በአማኞች መካከል ስለነበረው መከፋፈልና ክርክር
ለጳውሎስ ሲነግረው፤ በቆሮንቶስ የነበሩ ወንድምና እህቶች ጉዳይ ሐዋርያውን አብልጦ
ያሳስበው ጀመር፡፡ ሐዋርያው በመልእከቱ መግቢያ የተጠቀማቸው ቃላት ጉዳዩ ምን
ያህል እንዳሳሰበው ያሳያሉ፡፡ “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣
አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” (1ቆሮ. 1፡10) ይህ የመፍትሔ ሀሳብ እንደ
ክርስቲያን ዘወትር በአንድ ልብ መመላለስ እንደሚኖርባቸው የሚያስታውስ ነበር፡
፡ በመካከላቸው አለመግባባትና መከፋፈል እንዲፈጠር ያደረገው ነገር ምንም ይሁን
ምን ጳውሎስ እንዲቆም ፈልጎአል፡፡
ሰዎች የቱንም ያህል ችሎታና ስጦታ ሊኖራቸው ቢችልና ለአገልግሎት ቢጠሩ
እንኳ፤ ክርስቲያኖች የተጠሩት ክርስቶስን እንዲከተሉ መሆኑን ጳውሎስ የቆሮንቶስ
አማኞችን ሲያስታውስ እንመለከታለን፡፡ አማኞች ጎራ ከፍለው የፈጠሩት መለያየት
የክርስቶስ ፈቃድ አለመሆኑን ለነገ ሳይል ቁርጥ አድርጎ ነግሮአቸዋል፡፡ የክርስትና
ሕብረት አስኳል ክርስቶስ እና እርሱ በመስቀል ላይ የፈጸመው የመሥዋዕትነቱ እውነታ
መሆኑንም ጭምር ተናግሮአል (1ቆሮ. 1፡13)፡፡
አንድ ሰው የቱንም ያህል “የከበረ” መንፈሳዊ ነገር ባለቤት፣ መካሪና ተቆጪ፣
ሰባኪና መሪ ሊሆን ቢችል--የክርስትና ኅብረት ምንጭ እውነታው የሚገኘው በሌላ
በማንም ሳይሆን በየሱስ ክርስቶስና በእርሱ በተሰቀለው ብቻ ነው፡፡ እኛ ሁላችን
በመስቀሉ ግርጌ በተመሳሳይ ደረጃ እንገኛለን፡፡ ጥምቀታችን እርሱ ብቻ ከኃጢአታችን
ሊያነጻን በሚችለው በየሱስ ነው፡፡ ይህም ቢሆን በክርስቶስ የሚኖረንን ኅብረት
ለማምጣት በተጨባጭ የመሥራት ግዴታ ተጥሎብናል፡፡ በመሆኑም እንደ ሰባተኛ
ቀን አድቬንቲስትነታችን የእምነትና የተልዕኮ አንድነታችን ብቻውን ዋስትና ሊሆነን
እንደማይችል ይህ አበክሮ ይነግረናል፡፡ የክርስቶስ ፍቅርና ጌትነት አንድ ካላረገን
በቀር መከፋፈልና አለመግባባት የዛሬውን የቤተ ክርስቲያናችንን ኅብረት ሊያመነምን
ይችላል፡፡
ጳውሎስ በመልእክቱ ያስቀመጣቸውን አደጋዎች ማስወገድ የምንችለው
እንዴት ነው? ከክርስቶስ ውጪ ለማንኛውም ሰው ማሳየት በሚገባን ታማኝነት
ዙሪያ ዘወትር ጥንቁቅ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 20፡25-31፡፡ ጳውሎስ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች
ያስጠነቀቀበት ጉዳይ ምን ነበር? ይህ እንዳይሆን ለመግታት ምን ማድረግ ነበረባቸው?
በአገልግሎት ዘመኑ ተደጋጋሚ ተቃውሞ ይደርስበት የነበረው ጳውሎስ የየሱስ
ክርስቶስን ወንጌል ንጽህና ጠብቆ ማቆየት ቀላል ሊሆን እንደማይችል ያውቅ ነበር፡፡
ሐዋርያው ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር በነበረው የስንብት ቃል በሕዝቅኤል ከጕበኛው
ወይም ጠባቂው ምሳሌ (ሕዝ. 33፡1-6) በማንሳት የወንጌል ንጽህና የተጠበቀ እንዲሆን
የማድረግ ኃላፊነት እነርሱም እንዳለባቸው ሲነግራቸው ይስተዋላል፡፡ ታማኝ እረኝነት
በወቅቱ አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት አሥራ ስድስቱም ጉባዔዎች ይጠበቅ ነበር፡፡
ስለ ሐሰተኛ መምህራን “ነጣቂ ተኩላዎች” (ሐዋ. 20፡29) በሚል በጳውሎስ
የቀረበው አገላለጽ የሱስ የበግ ለምድ ለብሰው በመካከላችሁ ለመግባት ከሚያሸምቁ
ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ (ማቴ. 7፡15) ብሎ የተናገረውን ያስታውሰናል፡፡ ጳውሎስ
ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ብዙም ሳይቆይ ሐሰተኛ መምህራን ተከስተው ሐዋርያው
በእስያ ባቋቋማቸው አብያተ ክርስቲያናት አማኞች ላይ ነጠቃ መፈጸም ጀመሩ፡፡
ጳወሎስ ለእስያ አብያተ ክርስቲያናት ከሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች መሃል አንዳንዶቹ
በኤፌ. 5፡6-14 እና ቆላ. 2፡8 ላይ ተጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ጳውሎስ በሁለተኛው የጢሞቴዎስ መልእክቱ በቤተ ክርስቲያን ሊከሰቱ
በሚችሉ የስህተት ትምህርቶችና ክሕደቶች ዙሪያ በኤፌሶን ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን
ኃላፊነት የነበረውን ጢሞቴዎስ ሲያስጠነቅቅ ይስተዋላል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 2፡14-19፣ 3፡12-17፡፡ ጢሞቴዎስ የሐሰተኛ መምህራንን
ሴራ ተቃውሞና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አስጠብቆ ማቆየት በሚችልበት ዘዴ
ዙሪያ ሐዋርያው ምን አለው?
በመጀመሪያ ጢሞቴዎስ “የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ” (2ጢሞቴ. 2፡15)
አገልጋይ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ነበረበት፡፡ እነዚህን ከንቱ ውዝግቦችና መላ
ምቶች ማርከስ የሚቻለው በእግዚአብሔር የተሰጡትን አስተምህሮዎች በትክክል
በማስተዋልና በማስረዳት ነው፡፡ ማንም ሰው በተሳሳተ ትርጓሜ ተሰናክሎ በየሱስ ላይ
ሊኖረው የሚገባውን እምነት እንዳያጣ መከላከል ይቻል ዘንድ፤ ማንኛውም የመጽሐፍ
ቅዱስ ጥቅስ ከአጠቃላዩ ሥዕል ተቃርኖ እንዳይኖረው ለአምላካዊው እውነት
ትክክለኛውን ፍቺ መስጠት የግድ ይሆናል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው
አከራካሪ ነጥቦች በእግዚአብሔር ቃል መርኅ ሥር እንዲገዙ ሲደረጉ አማኞች
በክርስቶስ ድል አድራጊውን ሕይወት ለመምራት የተዘጋጁ ይሆናሉ፡፡ ጳውሎስ ለራሱ
ለጢሞቴዎስ የሰጠው ሁለተኛው ምክረ ሀሳብ “እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከንቱ
ልፍለፋ ራቅ” (2ጢሞቴ. 2፡16) የሚል ነበር፡፡ ጢሞቴዎስ የከበረና ታማኝ አገልጋይ
መሆን የሚሻ ከሆነ፤ ረብ የለሽና መላ ምት ርዕሰ ጉዳዮችን ከአስተምህሮው ማራቅ
ነበረበት፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ እሰጣ ገባዎች አብልጠው ከአምላካዊው ጽንሰ ሀሳብ
ከማራቅ ውጪ የአማኙን እምነት አያንጹም (2ጢሞቴ. 2፡16)፡፡ እግዚአብሔርን
ወደ መምሰልና ወደ ስምምነት ሊመራን የሚችል አንድ ነገር--እውነት ብቻ ነው፡፡
ጢሞቴዎስ እነዚህን ስህተቶች ማስወገድ የግድ የሆነበትና በምዕመኑም ላይ ብርቱ
ግፊት ያደረገበት ምክንያት ትምህርቱ እንደማይሽር ቁስል በቤተ ክርስቲያን ሰርጎ
በመግባቱ ነበር (2ጢሞቴ. 2፡17)፡፡ ወደ ድምዳሜ ስንመጣ--የቤተ ክርስቲያንን
ኅብረት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችለው የሐሰት ትምህርት ማርከሻ የእግዚአብሔርን ቃል
መታዘዝ ሆኖ እናገኘዋለን (2ጢሞቴ. 3፡14-17)፡፡
በተመሳሳይ የሐሰት ትምህርታቸውን ተጠቅመው በመካከላችን መለያየት ሊያመጡ
ከሚችሉ የበግ ለምድ የለበሱ ነጣቂ ተኩላዎች መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
፡ Ellen G. White, “The Rending of the Kingdom,” pp.
87–98, in Prophets and Kings; “A Message of Warning and Entreaty,”
pp. 298–308, in The Acts of the Apostles.
“ጌታ የመረጣቸው አገልጋዮቹ እንዴት ለዛ ያለው አንድነት ማምጣት እንዳለባቸው
ይማሩ ዘንድ ምኞቱ ነው፡፡ አንዳንዶች በእነርሱና በሌሎች አገልጋዮች ስጦታዎች
መሃል ያለውን ልዩነት እጅግ አግዝፈው በማሰብ ፋይዳ ያለውን ኅብረት ለመፍጠር
አዳጋች አድርገው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን አማኞች የእውነትን ብርሃን ሊያደርሷቸው
የሚገቡ በተለያየ የአዕምሮ ሁናቴ የሚገኙ--ማለትም መልእክቱ እንደተመሰከረላቸው
የሚቃወሙ መኖራቸውን ሲያስታውሱ፤ ከወትሮው ለየት ባለ አግባብና አቀራረብ
እነዚህን አፈንጋጭ ልቦች ለአምላካዊው እውነት ለመክፈት መሥራት እንደሚችሉ
ያስተውላሉ፡፡ በዚህም ከሌሎች ጋር በኅብረት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ጥረት
ለማድረግ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ መክሊቶቻቸው የቱንም ያህል ብዝሃነት ቢኖራቸውም
ነገር ግን በአንድ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዱ ከአንደበታቸው
የሚወጣ ቃልም ሆነ ድርጊት ደግነትንና ፍቅርን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ
ሠራተኛ ታማኝ ሆኖ የተመደበበትን ስፍራ ሲሞላ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ኅብረት
የጸለየው ጸሎት ምላሽ ያገኛል፡፡ እነዚህ ወገኖች የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውንም
ዓለም ይገነዘባል፡፡—Ellen G. White, Gospel Workers, p. 483.
፡
1.
በአንድ ሰው “ዐይን” ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግ ተገቢነት ጥያቄ
አዲስ የፍልስፍና ሀሳብ አይደለም፡፡ ማዕከላዊነትን፣ የዕውቀት መጀመሪያ ወይም
የግብረገብን ገዢነት ጽንሰ ሃሳብ አልቀበል የሚለው ድኅረ ሥልጣኔ፤ መጽሐፍ ቅዱስ
ወደሚያስጠነቅቀው ሕገ ጠል ግርግር የሚወስደውን መንገድ የመጥረግ ኃይል አለው፡
፡ እኛ እንደ ክርስቲያንነታችን ብሎም በአጠቃላይ እንደ ቤተ ክርስቲያን ከእንዲህ
ያለው ፈታኝ ሁኔታ ጋር መጋጠም የምንችለው እንዴት ነው?
2.
የንጉሥ ሮብዓምን እና የእስራኤልን መከፋፈል ታሪክ አሰላስሉ (1ነገሥ. 12)
ዛሬስ ለእኛ ምን ትምህርት እናገኛለን?
3.
በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁከት፣ ጥልና መከፋፈል እንዳይነሳ ለመከላከል
የቤተ ክርስቲያን አባላትና መሪዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? እነዚህ ጉዳዮች
በፍጥነት እያደጉ ከመሄዳቸው አስቀድሞ እንዲገቱ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
እኛም እንደ አንዳንዶቹ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በወጥመድ እንዳንወድቅ-እንደ ቤተ ክርስቲያን አባልነታችን እንዴት መጠንቀቅ ይኖርብናል?
4.
በምሳ. 6፡16-19 በአለመስማማት ዙሪያ የቀረበውን መልእክት ዐውድ ያጥኑ፡
፡ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ሊከሰት የሚችልን ጸብና መለያየት ለማስቀረት ከዚህ
ምን ዓይነት ትምህርት ያገኛሉ?
ማጠቃለያ፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ወደ መከፋፈል የሚመሩ ሁኔታዎች ተጠቅሰው
እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በታማኝ መታዘዝ ሲመላለሱ የመከፋፈል
አደጋዎች በእጅጉ ቀንሰው ነበር፡፡ በመሳፍንቶች ዘመን የተስተዋሉትም ሆኑ በሮብዓም
ንግሥና ወቅት የታየው መጥፎ ውሳኔ የመከፋፈልን በራፍ ወለል አርገው ከፈቱ፡፡
በአዲስ ኪዳን ዘመንም የመከፋፈል ዕድል ያለ እንደመሆኑ፤ በመካከላችን ሊከሰቱ
የሚችሉ መከፋፈሎችንና መለያየቶችን መከላከል የሚቻልበት ምርጥ መንገድ
የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ማስተዋልና ለመታዘዝ የሚደረግ ቅዱስ ቁርጠኝነት
ናቸው፡፡