በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከመስከረም 19 - 25

አንደኛ ትምህርት

Sep 29 - Oct 05


ፍጥረት እና ውድቀት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1:26, 27፣ 1ዮሐ. 4:7-8፣ 16፣ ዘፍ. 3:16–19፣ ዘፍ. 11:1–9፣ ገላ. 3:29፣ ዘዳ. 7:6–11፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-- “ወደ ውጪም አውጥቶ፣ ‘ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቁጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቁጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል’ አለው፡፡ አብራም እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽቅ አድርጎ ቆጠረለት” (ዘፍ. 15፡5-6)፡፡

የ እግዚአብሔር ሕዝቦች ታሪክ በሰብዓዊው ፍጥረትና በአሳዛኙ የኃጢአት ውድቀት ይጀምራል፡፡ የቤተ ክርስቲያናዊውን ኅብረት ተፈጥሮ ለማስተዋል የሚደረግ ማንኘውም ዓይነት ሙከራ ከቀደመው አምላካዊ የፍጥረት ዕቅድ እና ከውድቀት በኋላ ባስፈለገው ወደ መጀመሪያው ንጽህና የመመለስ ተግባር ሊጀምር የግድ ይሆናል፡፡

ሰብዓዊው ፍጡር በአንድ ቤተሰብነት እንዲጸና የእግዚአብሔር ሀሳብ መሆኑን የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ይፋ ያደርጉልናል፡፡ የመለያየትና የመከፋፈል ሥር እንዲሰድና ያለመታዘዝ ውጤት አብልጦ እንዲንሰራፋ መንስዔው ኃጢአት ብቻ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ ከበሉ በኋላ (ዘፍ. 3፡ 11) እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኛቸው የተስተዋለው መስተጋብር ለዚህ መለያየት ፍንጭ ይሆነናል (ዘፍ. 3፡11)፡፡ በመሆኑም ይህን ኅብረት ወደ ቀደመው ሁኔታ መመለስ የደኅንነት እቅድ ከሚፈጽማቸው ተግባራት መካከል አንዱና ወሳኙ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ሕዝቦች አባት ተብሎ የሚጠራው አብርሃም በአምላካዊው የደኅንነት እቅድ ቁልፍ ሚና መጫወት የቻለ ሰው ነበር፡፡ አብርሃም የ “ጽድቅ በእምነት” (ሮሜ 4፡1-5) ታላቅ ምሳሌ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ የቀረበ ሲሆን፤ ይህ እምነት የእግዚአብሔር ሕዝቦችን እርስ በርስ ብሎም ከራሱ ከጌታ ጋር በአንድ ያስተሳስራል፡፡ እግዚአብሔር የቀደመውን ኅብረት ለመመለስና ለጠፋው ሰብዓዊ ዘር ያለውን አምላካዊ ፈቃድ ለማሳወቅ በሕዝቡ አማካይነት ይሠራል፡፡

መስከረም 20
Sep30


ፍቅር፡ እንደ ኅብረት መሰረት


በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕ. 1 እና 2 የፍጥረትን ታሪክ አማክሎ የሚፈሰው ግልጽ መልእክት በፍጥረት ሣምንት መጨረሻ ገቢራዊ ከሆነው አጠቃላይ ትዕይንት ጋር ስምምነትና ውህደት አለው፡፡ እግዚአብሔር በመጨረሻ ላይ የተናገራቸው ቃላት “እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍ. 1፡31) የሚሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ አባባሉ እግዚአብሔር ይህን ዓለም እና የሚኖሩባትን ሰዎች ፈጥሮ ሲጨርስ የተስተዋለውን ሥነ ውበት የሚያንጸባርቅ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ዓይነት ክፉ ወይም ተቃርኖ በስፍራው አለመኖሩን ጭምር አመላካች ነበር፡፡ የቀደመው የእግዚአብሔር የፍጥረት ዓላማ እያንዳንዱ የእጁ ሥራ እርስ በርስ ተስማምቶና ተደጋግፎ አብሮ የሚኖርበትን ብልሃት ያካተተ ነበር፡፡ ምድር ለሰብዓዊው ቤተሰብ ውብ ሆና ተፈጥራ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ፍጹምና የከበረውን የፈጣሪ ማንነት የሚያሳይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለዓለም የነበረው የቀደመ ሀሳብ እና ዓላማ ለዛ ያለውን ስምምነት፣ አንድነትና ፍቅር የተላበሰ ነበር፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1፡26-27፡፡ ሰብዓዊው ፍጡር በዘፍ. ምዕ. 1 እና 2 ከቀረቡት ሌሎች ፍጥረታት ይልቅ ተወዳዳሪ የማይገኝለትና ድንቅ ስለመሆኑ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?



የዘፍጥረት መጽሐፍ እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ይነግረናል፡፡ ስለ ሌሎች ፍጥረታት ያልተባለውን ያህል ስለ ሰው አፈጣጠር መነገሩን እንመለከታለን፡ ፡ “እግዚአብሔር ‘ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ ... አለ፡፡’ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡” (ዘፍ. 1፡26-27)፡፡ ምንም እንኳ የነገረ መለኮት ምሑራን በዚህ መልክ ትክክለኛ ተፈጥሮ እና በራሱ በእግዚአብሔር ባህሪ ዙሪያ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ቢሞግቱም፤ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የእግዚአብሔርን ባህሪ የሚያቀርቡት ፍቅር መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 4፡7-8፣ 16፡፡ እኛ መጀመሪያ እንዴት እንደተፈጠርን ማስተዋል እንድንችል ጥቅሶቹ በምን መልኩ ይረዱናል? ሁናቴው በፍጥረት ወቅት የምናገኘውን የቀደመ ኅብረት እንዴት ሊነካ ይችላል?



እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ እንዲሁም የሰው ልጆች ማፍቀር የሚችሉ ፍጥረቶች እንደ መሆናቸው (የተቀሩት የምድር ፍጥረታት የዚህ ጸጋ ተቋዳሽ አይደሉም) በአምላካዊው አምሳል መፈጠር ማለት ማፍቀር መቻልን ማካተቱ የግድ ይሆናል፡ ፡ ይሁንና ፍቅር ከሌሎች ጋር ባለ ግንኙነት ብቻ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ማንኛውም ፍጡር ይህን ባህሪ--ማለትም ማፍቀር የመቻልንና በጥልቅ የመውደድ ችሎታን ማካተቱ የግድ ይሆናል፡፡

መስከረም 21
Oct1


የውድቀት መዘዝ


ውድቀትን ተከትሎ የመጣው ጦስ እንዲህ በዋዛ ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የአዳምና ሔዋን አለመታዘዝ በሁሉም ሕይወት ባላቸው ፍጥረታት መካከል በነበረው ስምምነት ላይ መቃቃር ፈጠረ፡፡ እንደውም ይባስ ብሎ ዛሬ ድረስ በሰው ልጆች መሃል አለመስማማት፣ ብጥብጥ፣ አለመግባባትና ክፍፍል እንዲጠነሰስ መንስዔ ለመሆን በቃ፡ ፡ አዳምና ሔዋን ለደረሰባቸው ውድቀት አንዱ በሌላው ላይ በማመካኘት ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ፣ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌላው ጋር የነበራቸውን ውህደት አጡ (ዘፍ. 3፡12-13)፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነገሮች እየከፉ ሄዱ፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡16-19፣ 4፡1-15፡፡ እግዚአብሔር በፈጠረው ለዛ እና ስምምነት በነበረው ዓለም ኃጢአት ስላስከተለው ውጤትና ተጽእኖ ምን ይነግሩናል?



የአዳም አለመታዘዝ በሂደት መላውን የእግዚአብሔር ፍጥረታት በማወክ ለአያሌ ያልተጠበቁ ከስተቶች መዘዝ ለመሆን በቃ፡፡ ራሱ ተፈጥሮአዊው ዓለም ሳይቀር ኃጢአት ያስከተለውን የሥቃይ መዘዝ መቅመሱን ተያያዘው፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች እርስ በርሳቸው ሊዋደዱና አንዱ ለሌላው አለኝታ ሊሆን ሲገባ፤ ነገር ግን አንደኛው የእግዚአብሔርን ሌላው ደግሞ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን የአምልኮ መንገድ ሳይሆን የግሉን ራስ ወዳድ አምልኮ በመከተሉ ባይተዋር ሆኑ፡፡ ይህ ባይተዋርነት ጸብ ብሎም ሞት አስከተለ፡፡ ይሁን እንጂ በቃየን የተስተዋለው ድርጊት ባብዛኛው ያነጣጠረው በወንድሙ አቤል ላይ ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሔር ላይ ነበረ፡፡ ቃየን በእግዚአብሔር ላይ ብርቱ የቁጣ ስሜት ተሰማው (ዘፍ. 4፡5)፡፡ ይህ ቁጣው ደግሞ በአቤል ላይ የበቀል በትር እንዲሰነዝር መራው፡፡ በዚህም አለመታዘዝ በሰብዓዊው የእርስ በርስ ግንኙነት ላይ መቃቃር ፈጠረ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ፡፡” (ዘፍ. 6፡5)፡፡ ውሎ አድሮ ይህ የክፋት ተግባር ለጥፋት ውሃ እና ለቀደመው የእግዚአብሔር ፍጥረት ውድመት መንስኤ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ጀመረ፡፡ ሆኖም ግን በሰብዓዊው ፍጡር ተስፋ ያልቆረጠው እግዚአብሔር በኖኅ እና ቤተሰቡ አማካይነት የሰብዓዊውን ዘር ቅሪት በምድር ከማትረፍ ወደ ኋላ አላለም፡፡ ከጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ቤተሰቡ ቃል ገባ፡፡ በዝናብ ወቅት በሰማይ የሚወጣው ቀስተ ደመና ሰብዓዊውን ፍጡር ስለ አምላካዊው ጥበቃና እንክብካቤ፣ ደግነትና ምኅረት ዘወትር የሚያስታውስ ምልክት ሆነ (ዘፍ. 9፡12-21)፡፡ እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ ለእርሱና ለቃሉ ሙሉ ለሙሉ ታማኝ የሆነ አንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ የመመስረት ቅድመ እቅዱን ዳግም አዋቀረ፡፡ ኃጢአት መለያየት የሚያመጣባቸው መንገዶች ም ንድን ናቸው? ምርጫዎችዎ በሰዎች መሃል ስምምነትና አንድነት ለማምጣት እገዛ ያደርጉ ዘንድ አሁን የሚመርጧቸው ምርጫዎች ምን ሊሆኑ ይገባል?

መስከረም 22
Oct2


ከፍ ያለው ኅብረት ማጣትና መለያየት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 11፡1-9፡፡ ኅብረት የማጣቱና የመለያየቱ ችግር ይበልጥ እንዲከፋ ያደረገ ምን ዓይነት ነገር ተከሰተ?



ከጥፋት ውሃ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት ቀጣይ ክስተቶች የባቤል ግንብ ግንባታ፣ የቋንቋዎች መደበላለቅ እና እስከዚያ ጊዜ ድረስ አንድ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ ሰዎች በምድር መበተን ነበር፡፡ ምናልባት አንዳንዶቹ የኖኅ ዝርያዎች በጤግሮስ እና ኤፍራጥስ ወንዞች መካከል በነበረው መልክአ ምድር ውበትና በዐፈሩ ለምነት በመሳብ በያኔዋ ሰናዖር (በዛሬው ደቡባዊ ኢራቅ) ዘፍ. 11፡2--ለመክተም እና ግዙፉን የባቤል ግንብ ለመገንባት ወሰኑ፡፡

የአርኪዎሎጂ ጥናት እንደሚያሳየው ሜሶፖታሚያ በቀደመው ዘመን ከፍተኛውን የሕዝብ ብዛት የያዘ ክልል ነበር፡፡ ከነዋሪዎች መካከል ሱመራውያን አንዱ ሲሆኑ እነዚህ ሕዝቦች በሸክላ ገበታ ላይ የጽሑፍ ጥበብን በመፍጠር ተመስክሮላቸዋል፡፡ በጥሩ ሁኔታ የታነጹ ቤቶችን ይገነቡ የነበሩት ሱመራውያን ጌጣጌጦችን፣ የእጅ መሣሪያዎችን እና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በመሥራትም እንዲሁ የተካኑ ነበሩ፡፡ ለተለያዩ አማልክት የተሠሩ ልቀው ይታዩ የነበሩ ብዛት ያላቸው ቤተ አምልኮዎች በቁፋሮ ተገኝተዋል፡፡ በሰናዖር ምድር ሰፍረው የነበሩት የኖኅ ዝርያዎች ብዙም ሳይቆዩ እግዚአብሔር ዓለምን ዳግመኛ በውሃ እንደማያጠፋ ለኖኅ የገባለትን ቃል ዘነጉ፡፡ የባቤልን ግንብ መገንባት ወጣ ላለው ዕውቀትና ችሎታቸው መታሰቢያ ቅርሳቸው ነበር፡፡ ይህን ፕሮጀክት እንዲጀምሩ የገፋፋቸው ምክንያትና ምኞት ለምድራዊው ዝና እና ለስማቸው መጠሪያ የሚሆን ሀውልት ማቆም ነበር (ዘፍ. 11፡4)፡፡ “በመለኮታዊ ዓላማው መሠረት ሰዎች በእውነተኛ ኃይማኖት ትስስር አንድነታቸውን መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ጣዖት አምልኮና ከአንድ በላይ አምላክ የማምለክ አባዜ ይህን ውስጣዊ መንፈሳዊ ትስስር ሲበጥስ፤ የኃይማኖት አንድነትን ብቻ ሳይሆን የወንድማማችነትንም መንፈስ አጡ፡ ፡ በእንደ ባቤል ግንብ ፕሮጀክት ዓይነት ውጪያዊ ኅብረት በመመስረት የጠፋውን ውስጣዊ አንድነት ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ፈጽሞ የስኬት ባለቤት ሊያደርግ አይችልም፡፡”—The SDA Bible Commentary, vol.1, pp. 284, 285. የአዳምና ሔዋን ውድቀት የሰብዓዊውን ዘር ኅብረት እና የቀደመውን አምላካዊ ዕቅድ እንዳይሆን በማድረጉ፤ በአምልኮ ዙሪያ ውዥንብርና ግራ መጋባት ተፈጠረ፣ ክፋትና ምግባረ ብልሹነትም በምድር ዙሪያ ተሰራጨ፡፡ የሰብዓዊው መለያየት ወደ ብዙ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ዝርያዎች በመስረጹ እነሆ ዛሬ ድረስ በሕዝቦች መሃል ያለ ግንኙነት ከልብ ሳይሆን ከአንገት በላይ ሆነ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር በመለያየት እየጎዱን ያሉ የብሔር፣ የባህልና የቋንቋ ደዌዎችን በተጨባጭ ለመፈወስ የሚያስችሉን ቅደም ተከተሎች ምንድን ናቸው?

መስከረም 23
Oct3


አብርሃም፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አባት


ሦስቱ የዓለም ታላላቅ ኃይማኖት የሆኑት ይሁዲ፣ ክርስትና እና እስልምና አብርሃምን እንደ አባት ይመለከቱታል፡፡ ለክርስቲያኖች ይህ አንድነት ከመንፈሳዊ ግንኙነት ጋር በአንድ የተሳሰረ ነው፡፡ አብርሃም የትውልድ አገሩን ሜሶፖታሚያን ለቅቆ እንዲወጣ ጥሪ ሲቀርብለት “በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች በአንተ አማካይነት ይባረካሉ” (ዘፍ. 12፡ 3፣ ዘፍ. 18፡18፣ 22፡18)) የሚል ተስፋ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይህ በረከት የመጣው በየሱስ አማካይነት ነበር፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 11፡8-19፣ ሮሜ 4፡1-3፣ ገላ. 3፡29፡፡ ጥቅሶቹ የትኞቹን የአብርሃም ኃይማኖታዊ አላባዎች ይጠቅሳሉ? ደግሞም ከዛሬው የክርስትና ኅብረት ጽንሰ ሃሳብ ጋር እንዴት ይዛመዳሉ? የክርስትና አንድነት ዋነኛ አካል ምን መሆን እንዳለበት መገንዘብ እንችል ዘንድ ከመልእክቶቹ ምን እናገኛለን?



አብርሃም እንደ የኃይማኖት አባትነቱ ለክርስቲያናዊ ኅብረት አስኳል የሆኑ መሰረታዊ አላባዎችን ይሰጠናል፡፡ በመጀመሪያ--አብርሃም መታዘዝን ተለማመደ “አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ እሺ ብሎ ሄደ” (ዕብ. 11፡8)፡፡ በሁለተኛ ደረጃ--በአምላካዊው ኪዳን ላይ ተስፋ አደረገ፡፡ “በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋይቱ ምድር በእምነት ተቀመጠ፤ የተስፋውን ቃል አብረውት እንደሚወርሱት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር” (ዕብ. 11፡9-10)፡፡ ሦስተኛ--እግዚአብሔር አንድ ቀን ልጅ እንደሚሰጠውና የአብራኩ ፍሬዎች እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዙ አመነ፡፡ ለዚህ በሰጠው ምላሽ መሰረት እግዚአብሔር በእምነት አጸደቀው (ሮሜ 4፡1-3)፡፡ አራተኛ-በአምላካዊው የደኅንነት እቅድ የሚታመን ሰው ሆነ፡፡ አብርሃም ልጁን ይስሐቅ በሞሪያ ተራራ እንዲሰዋለት እግዚአብሔር ሲጠይቀው እጅግ ከፍ ያለውን የእምነት ፈተና ተፈተነ (ዘፍ. 22:1–19፣ ዕብ. 11:17–19)፡፡ ብሉይ ኪዳን አብርሃምን የእግዚአብሔር ወዳጅ አድርጎ ይገልጸዋል (2ዜና 20፡7፣ ኢሳ. 41፡8)፡፡ የእምነት ሕይወቱ፣ ጽኑ መታዘዙና በእግዚአብሔር ኪዳን ላይ የነበረው ልበ ሙሉነት እነሆ ለዛሬው የክርስትና ሕይወታችን ምሳሌ አድርጎታል፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ስለሚወስዷቸው እርምጃዎችና ከአንደበትዎ ስለሚወጡ ቃላት አሰብ ያድርጉ፡፡ ማንኛውም የሚናገሩትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር እምነትዎን በተጨባጭ ማንጸባረቅ የሚችለው እንዴት ነው?

መስከረም 24
Oct4


የእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች


እግዚአብሔር አብርሃም አገልጋዩ እንዲሆን በመጥራት እርሱን በዚህ ዓለም የሚወክለውን ሕዝብ ለራሱ መረጠ፡፡ ይህ ጥሪ እና ምርጫ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ጸጋ ነበር፡፡ ሰብዓዊው ውድቀት አስከፊ ውድመትና መለያየት ካስከተለ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያቀረበው ጥሪ መላው ሰብዓዊ ዘር ወደ ቀደመው ንጽህና የሚመለስበት የአምላካዊው እቅድ ማዕከል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደዚህ ንጽህና ለመምራት የሠራውን ሥራ ማጥናት ቅዱስ ታሪክ ሲሆን፤ የዚያ ዕቅድ ዐቢይ አካል ደግሞ ባለ ኪዳኑ የእስራኤል ሕዝብ ነበር፡፡ በዘዳግም ምዕራፍ 7 ቁጥር 6 እና 11 መሠረት እግዚአብሔር እስራኤልን ሕዝቤ ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? ይህን ከአብርሃም ዘር የሆነ ሕዝብ የራሱ አድርጎ የመረጠው ለምንድን ነው?



እግዚአብሔር ለሰብዓዊው ዘር ያለው ፍቅር እስራኤልን እንደ ራሱ ሕዝብ የመምረጡ ማዕከል ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካዊውን ዕውቀት በሕዝቦቹ ውስጥ ለማኖርና የሰብዓዊውን ዘር መቤዠት እውን ለማድረግ ሲል ከአብርሃም እና ከእርሱ ትውልድ ጋር ኪዳን ገባ (መዝ. 67፡2)፡፡ ይህም ሆኖ እግዚአብሔር እስራኤልን እንዲመርጥ ያደረገው እጅግ የላቀ ፍቅሩ ነው፡፡ የአብርሃም ትውልድ የማይገባው የነበረውን አምላካዊ ፍቅር የራሱ ለማድረግ የሚያስችል አንድም የሚመካበት ነገር አልነበረውም፡ ፡ “እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቁጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቁጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር” ዘዳ. 7፡7)፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመምረጥ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው እሴቶች ለሰብዓዊው መስፈርት እንግዳና የተገላቢጦሽ ናቸው፡፡ ሰዎች መሪዎችን ለመምረጥ ኃያልነትን፣ ችሎታንና በራስ መተማመንን ሲመለከቱ እግዚአብሔር ግን ጠንካራውና ብርቱው እንዲያገለግለው አይመርጥም፡፡ ይልቁንም ደካማነቱንና ከንቱነቱን የተረዳውን ይመርጣል፤ ይኸውም ማንም በራሱ እንዳይመካ ነው (1ቆሮ. 1፡26-31)፡፡ ሆኖም በእርሱ የተመረጡ ወገኖች ተሰጥቶአቸው የነበረውን ልዩ መብትና ጥቅም እንመልከት፡፡ “እስራኤል ሕዝቡ የተመሰገነና የተከበረ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ምኞት ነበር፡፡ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ጥቅም ለእነርሱ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ለራሱ ተወካይ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ስምሙ የባሕሪ ቅርጽ እንዲይዙ ከማድረግ ውጪ አንዳች የከለከላቸው ነገር አልነበረም፡፡

“ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዛቸው በዓለም ሕዝቦች ፊት አስደናቂ ብልጽግና ያጎናጽፋቸው ነበር፡፡ በእያንዳንዱ የሙያ ዘርፍ ጥበብና ችሎታ ሊሰጣቸው የሚችል እርሱ የዘወትር መምህራቸው እንደመሆኑ ለሕጉ በመታዘዛቸው ሞገስ ይሆናቸውና ከፍ ከፍ ያደርጋቸው ነበር፡፡ እርሱን ከታዘዙ ሌሎች ሕዝቦችን ያጠቁ ከነበሩ በሽታዎች ይጠበቁ ነበር፡፡ በጥልቅ የማሰብ ችሎታም ይባረኩ ነበር፡፡

“የእግዚአብሔር ክብር፣ ግርማ እና ኃይል በብልጽግናቸው ሁሉ ይገለጥ ነበር፡ ፡ የካኅናት መንግሥትና መኳንንት እንዲሆኑ ተጠሩ፡፡ እስራኤላውያን በምድር ታላቅ ሕዝብ ሊያደርጋቸው የሚችል እያንዳንዱ ስጦታ ተበርክቶላቸው ነበር፡፡”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 288. እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች--እግዚአብሔር ለጥንቶቹ እስራኤላውያን እና ለእኛ ባደረገው ነገርና ባቀረበው ጥሪ መሀል ምን ዓይነት መመሳሰሎችን ማግኘት እንችላለን? መልስዎን በሰንበት ጥናት ክፍለ ጊዜ ይዘው ይቅረቡ፡፡

መስከረም 25
Oct5



ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Ellen G. White, “The Creation,” pp. 44–51, and “The Call of Abraham,” pp. 125–131, in Patriarchs and Prophets. እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር የነበረው የቀደመ ዓላማ በተመሳሳይ በቤተሰብ እና በሰንበት ተቋማት ምስረታም ተንጸባርቆአል፡፡ የሱስ በማር. 2፡27-28 በግልጽ እንዳመለከተው የሰንበት እረፍት የተዘጋጀበት የቀደመ ዓላማ ለመላው ሰብዓዊ ዘር ጥቅም ሲባል ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የሰንበት ዩኒቨርስ አቀፍ ተፈጥሮ በራሱ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ከሌሎቹ የሣምንቱ ቀናት የለየው እስራኤልን እንደ ኪዳን ሕዝቡ ከመጥራቱ በፊት ብቻ ሳይሆን ኃጢአት በምድር ከመታወቁ አስቀድሞም ጭምር ነበር፡፡ ሰው ሁሉ ሰባተኛውን ቀን ቢጠብቅ፤ ዕለቱ ኅብረት የሚያመጣ ብርቱ ኃይል በሆነ ነበር፡፡ የአዳምና ሔዋን ትውልድ ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር እንዲሁም እርሰ በርስ ያላቸውን ኅብረት እንዲያስታውሱ ታቅዶ የተሰጠ የእረፍት ቀን ነበር፡፡ “በኤደን ገነት የተቋቋሙት ሰንበት እና ቤተሰብ በአምላካዊው ዓላማ እንዳይፈቱ ሆነው በአንድ ተገምደዋል፡፡ ከሌሎቹ የሣምንቱ ቀናት ይልቅ በዚህ ዕለት በበለጠ የኤደንን ሕይወት መኖር ይቻለናል፡ ፡ አባወራው እንደ ቤቱ ካኅን እንዲሁም እናትና አባት እንደ ልጆቻቸው መምህርና ጓደኛ ሆነው የቤተሰብ አባላት በሥራ፣ በጥናት፣ በአምልኮና በመዝናናት ጊዜአቸውን አንድ ላይ ያሳልፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እቅድ ነበር፡፡”—Ellen G. White, Child Guidance, p. 535.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1. በዘፍጥረት መጽሐፍ የሔዋን ከአዳም የጎን አካል መሠራት በባልና ሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው የጠበቀ ትስስር ምን ይገልጽልናል? በሁለት የትዳር ተጓዳኞች መካከል ሊኖር የሚገባው የጠበቀ ትስስር በተመሳሳይ በሕዝቡ መሃል እንዲኖር የሚመኘው አምላክ፤ ይህን ጥምረት በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች በምሳሌ የሚያቀርበው ለምንድን ነው?

2. ምንም እንኳ የሰብዓዊው ዘር በቋንቋና በብሔር መከፋፈል የቀደመው አምላካዊ ዕቅድ አካል አለመሆኑን የባቤል ግንብ ታሪክ ቢነግረንም፤ እነዚህን ተፈጥሮአዊ መለያየቶች አስንቀን መገኘት የምንችለው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ስብጥር ብትሆንም፤ ዛሬም ኅብረትና ስምምነትን መለማመድ የምትችለው እንዴት ነው?

3. በጥንቷ እስራኤል እና እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን በእኛ መጠራት መካከል ያሉ አንዳንድ መመሳሰሎች ምንድን ናቸው? ከሁሉ በላይ ለክርስቶስ መለኮታዊ ጥሪ ታማኝ እንድንሆን ከሚረዱን ነገሮች ምን እንማራለን?

ማጠቃለያ፡ የሰዎች ተስማምቶና እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ መኖር በፍጥረት ወቅት የነበረ የቀደመ አምላካዊ እቅድ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አለመታዘዝ የእግዚአብሔርን እቅድ አፋለሰ፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር በክርስቶስ ብቻ የሚገኘውን ወደ ቀደመው ንጽህና የመመለስ ኪዳን መጠበቅ የሚችልበትን ሕዝብ ለማቋቋም አብርሃምን ጠራ፡፡