ለመጨረሻው ጊዜ መዘጋጀት
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከግንቦት 4- 10

ሰባተኛ ትምህርት

May 12 – 18


የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24-25



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 24:1–25፣ ራእ. 13:11–17፣ ማቴ. 7:24–27፣ ሉቃ. 21:20፣ ማቴ. 25:1–30፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ ‘ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ’ ” (ማቴ. 24፡24)

የሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ጊዜያቶችና እንዴት ለወደፊቱ መዘጋጀት እንዳለብን አስመልክቶ በማቴ. ምዕ. 24 እና 25 አስፈላጊ እውነቶችን ይገልጽልናል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች ክርስቶስ ስለ መጨረሻዎቹ ጊዜያቶች የተወልን ትምህርቶች ናቸው ቢባል ያስኬዳል፡፡ የሱስ ስለ እነዚያ የምድር መጨረሻ ክስተቶች እየተናገረ ወዲያው ደግሞ እርሱ ከነበረበት ዘመን ብዙም ሳይርቅ ሊሆን ያለውን የየሩሳሌምን ጥፋት እና በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን እልቂት እንዲሁ ተመልክቶ ነበር፡፡ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው መልእክት ከእነርሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶችም ሆነ በተለይ ደግሞ ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ባሉ የመጨረሻዎቹ ዘመናትና በምጽአቱ ወቅት ለሚኖሩ ሕዝቦች ገጣሚ ናቸው፡፡ የሱስ መጪውን ጊዜ ሲስል ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እና ምቹ ይሆናል አላለም፡፡ ይልቁንም የጦርነት ወሬ፣ መቅሰፍት፣ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች እና ስደት የዓለም ብሎም የቤተ ክርስቲያኑ ዕጣ ፈንታ ይሆናል ሲል ነው ያስጠነቀቀው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን በዘመናት የሆኑትን በመቃኘት የየሱስ ትንቢቶች ምን ያህል ትክክል እንደ ነበሩ በአግራሞት መመልከት እንችላለን፡፡ በዚህ የተነሳ በእኛ ዘመንም ሆነ ከእኛ በኋላ ፍጻሜ ለሚያገኙት ትንቢቶች ልናምነው እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ የሱስ ወደ ፊት ስለሚመጣው ነገር እንደው ማስጠንቀቂያ ብቻ አልተወም፡፡ በማቴ. 25 ከቀረቡት የየሱስ ምሳሌያዊ አባባሎች መመልከት እንደምንችለው--ምክሩን የሚሰሙና የሚያከብሩ “‘የሰው ልጅ’” በሚመጣ ጊዜ ዝግጁ ሆነው መጠበቅ ይችላሉ፡፡ አዎ--አስቸጋሪ ጊዜያቶች ይመጣሉ፤ ነገር ግን እርሱ ዳግም በሚገለጥበት ጊዜ የሚገናኙትን ሕዝቦች ያዘጋጃል፡፡

ግንቦት 5
May 13

ትንቢት ማረጋገጫ ብርቱ መንገድ


ከመስቀሉ አስቀድሞ በነበሩት የመጨረሻዎቹ ቀናት ደቀ መዛሙርቱ በደብረ ዘይት ተራራ ከየሱስ ጋር ተነጋግረው ነበር፡፡ የሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚወድም ሲናገር እርስዎ በዚያ ቦታ ቢኖሩ ሊሰማዎ የሚችለውን ስሜት በዓይነ ኅሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በትክክል በአእምሮአቸው የነበረውን ነገር ለማወቅ ባይቻልም ነገር ግን ይህን ተከትሎ የጠየቋቸው ጥያቄዎች የቤተ መቅደሱን መውደም ከ“ ‘ዓለም መጨረሻ’ ” (ማቴ. 24፡3) ጋር እንዳያያዙት የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ ማቴ. 24፡ 1-25፡፡ የሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት አስመልክቶ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ጠቅለል ያሉ መልእክቶች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ክርስቶስ ወደ ኋላ ከረጅም ዘመናት አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ ማታለያዎች እንዳሳሰቡት ማቴ. 24፡1-25 በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ ከእነዚህ ማታለያዎች መካከል ሐሰተኛ ነቢያትና ክርስቶሶች ይገኙበታል፡፡ አንዳንዶች ክርስቶስን እንወክላለን እስከ ማለት ሲደርሱ (ሐሰተኛ ነቢያት) ሌሎች ደግሞ ጭራሽ ክርስቶስ ነኝ ብለው ይመጣሉ፡፡ ታዲያ በእጅጉ የሚያሳዝነው ሰዎች እነርሱን ማመናቸውና መከተላቸው ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አሳዛኝ ክስተቶችን ብንመለከትም ነገር ግን ክስተቶቹ የእግዚአብሔርን ቃል በብርቱ የሚያረጋግጡልን ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በቀድሞዎቹ ዘመናት እንዲሁም ዛሬ በእኛ ዘመን አሳቾች “እኔ ክርስቶስ ነኝ” ብለው ተነስተዋል፡፡ እንዴት አስገራሚ ትንቢት ነው! እኛ በዚህ ዘመን መፈጠራችን ከብዙ ምዕተ ዓመታት አስቀድሞ የነበሩትን ታሪኮች በመቃኘት (በክርስቶስ ዘመን የነበሩት ያልታደሉትን) ትንቢቱ ምን ያህል ትክክል እንደ ሆነ መመልከት እንችላለን፡፡ ወደ መጨረሻው ቀውስ ስንቃረብ እንደነዚያ ዓይነቶቹ ማታለያዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ፈጽሞ መደነቅ የለብንም፡፡ እንዲሁም የሱስ ከአዎንታዊው የእምነት ዐውድ አኳያ የዓለምን ሁናቴ የገለጸበትን መንገድ ይመልከቱ፡፡ ከክርስቶስ አንስቶ ባለው የምድር የተለያዩ ዘመናት ታሪክ ሰዎች የሰብዓዊው ዘር ሥቃይና እንግልት እንዲጠፋ ወይም ቢያንስ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋሉ ብለው በሚያምኑባቸው ነገሮች ላይ ተስፋቸውን አኑረዋል፡፡ ሰዎች በአንድ ወቅት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፣ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ወይም የሳይንስ ግስጋሴ አልያም አመክንዮ--ፍጹም ወደ ሆነ ዉሁድና ስምሙ ዓለም ያገባናል የሚል ታላቅ ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተስፋዎች ሁሌም ቢሆን የተመሰረቱት ጤነኛ ባልሆነ መሰረት ላይ ለመሆኑ በሥቃይ የተሞሉት የታሪክ ተሞክሮዎች በተደጋጋሚ ምስክር በመሆን አሳይተዋል፡፡ ዛሬ ይህች ዓለም የሱስ ይሆናል ብሎ በተናገረበት ሁናቴ ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚያ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ከየሱስ አንደበት የወጡ ቃላት ሰብዓዊዎቹ ተስፋዎች ምን ያህል በስህተት የተመሩ እንደሆኑ ያሳያሉ፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡ 25፡፡ እምነታችን እንዲጠነክር ሊረዳ ከሚችለው ከዚህ አባባል ምን መውሰድ እንችላለን?

ግንቦት 6
May 14

እስከ መጨረሻው መታገስ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡9፣ ራእ. 13፡11-17፡፡ የሱስ በማቴዎስ ወንጌል በተናገረውና ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ እንዲጽፍ ካነሳሳው ሃሳብ ጋር ምን ዓይነት ትይዩነት ይስተዋላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ገቢራዊ ከሚሆኑትና የሱስን ከሚያሳስቡት ጉዳዮች አንዱ መንግሥታት እውነትን እንዲቃወሙና በዓለም ላይ የሐሰት አምልኮዎች እንዲተገብሩ የሚያደርጉ ዓለማቀፋዊ ማሳቻዎች ናቸው፡፡ ለእውነት ጸንተው የሚቆሙ ጥላቻ፣ መከራ--ባስ ሲልም ሞት ይደርስባቸዋል፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡13፡፡ በዓለማቀፍ ተቃውሞ መሃልም እንኳ ለመዳንም ሆነ ታማኝ ለመሆን ቁልፉ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“አእምሮአቸውን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ያጠነከሩ ወገኖች በታላቁ ውዝግብ መሃል እስከ መጨረሻው ጸንተው ይቆማሉ፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 593. አባባሉ--አእምሮአቸውን በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ምሽግ ውስጥ ያኖሩ ሁሉ በማንኛውም የመጨረሻው ጊዜ ማታለያ ተጠርገው አይወሰዱም የሚል አንደምታ አለው፡፡ ለዚህ ዘመን የተሰጠውን እውነት መሰረተ ሀሳብ አጥብቀው ካልያዙ በቀር ማታለያዎቹ ለያነሆልሏቸው ይችላሉ፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 7፡24-27፡፡ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል ሌላው ወሳኝ ነገር ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በአምላካዊው ቃል ዕውቀት ብልህ ሆኖ መሞላት አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን የሱስ እንደሚለው ወደ ፊት የምንጋፈጠውን መከራ ለመቋቋም ያ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የተማርነውን ነገር በተግባር ማዋል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ይህ ማለት የሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም እውነትን መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ ከላይ በቀረበው ምሳሌያዊ አነጋገር ሁለቱም ቤት ሠሪዎች የየሱስን ቃል ሰምተዋል፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረው ልዩነት የጽናት ጉዳይ ሲሆን ይኸውም የሱስ አስተምሮ የነበረውን መታዘዝ ነው፡፡ የሚታዘዝ ሰው ጸንቶ ሲቆም የማይታዘዘው ግን የሚወድቀው ለምንድን ነው? አንድ ሰው በእምነቱ ጸንቶ እንዲቆም በማድረጉ ረገድ መታዘዝ የሚያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?

ግንቦት 7
May 15

“የጥፋት ርኩሰት”


ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ጊዜ ባደረገው ታላቁ ንግግር ከዳንኤል መጽሐፍ (ዳን. 9፡27፣ 11፡31፣ 12፡11) በመውሰድ ወደ “የጥፋት ርኩሰት” (ማቴ. 24፡15) ያመላክታል፡፡ እግዚአብሔር “ርኩሰት” የሚለውን ቃል ጥቅም ላይ የሚያውለው በሕጉ ላይ ከፍተኛ ጥሰት ሲደርስ ይኸውም እንደ ጣዖት አምልኮ (ዘዳ. 27፡15) ወይም በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ አጸያፊ ግንኙነት ሲከሰት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ “የጥፋት ርኩሰት” አንድ የሆነ ኃይማኖታዊ ክህደትን ያካትታል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡15፣ ሉቃ. 21፡20፡፡ ጥቅሶቹ የሱስ ከ “ጥፋት ርኩሰት” ጋር በተያያዘ የተናገረውን በተሻለ እንድናስተውል የሚረዱን እንዴት ነው

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እነዚህ ሁለት ጥቅሶች በየሱስ ትንቢቶች መሰረት ብዙም ሳይቆይ 70 ዓ.ም. ላይ አረማዊው ሮም የሩሳሌም ከተማን ብቻ ሳይሆን ቅዱስ የነበረውንም ቤተ መቅደስ በማውደም ያደረሰውን አስከፊ ጥፋት በማካተት ያቀርባሉ፡፡ የሆነው ሆኖ እንደ የሩሳሌም ውድመት ዓይነት የወደፊቱና የመጨረሻው ጊዜ ክስተቶች ሆነው የሚቆዩና በቅርብ ገቢራዊ የሚሆኑ የዚህ ትንቢት ዳግመኛ ፍጻሜዎች አሉ፡፡ “ክርስቶስ በየሩሳሌም የተመለከተው ባለማመን ልቡ የደነደነው የዐመጸኛው ዓለም ተምሳሌት፤ አምላካዊውን ፍርድ በፍጥነት ለመቀበል ተጣድፎ ነበር”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 22. በዳን. 12፡11 እና 11፡31 የምናገኘው “የጥፋት ርኩሰት” የሚገለጠው በቀጣዩ የሮም ዕድገት ደረጃ ወይም ምዕራፍ በምናገኘው ጳጳሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት አማራጭ የአምልኮና የደኅንነት ህግ በመደንገግ ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ ለእኛ ያደረገልንንና አሁን እያደረገልን ያለውን--ከሥልጣኑ ውጪ የራሱ ለማድረግ ይሻል፡፡ ዳን. 8 በተለይም ከቁ. 9-12 ክስተቶቹን ከራሳቸው የታሪክ ዐውድ ማለትም ሁለት ምዕራፎች ወይም ደረጃ ካለው የሮም ሥልጣን አኳያ በመመደብ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ በትንሹ ቀንድ ፈጣን የአግድሞሽ መስፋፋት የተስተዋለበት (ዳን. 8፡9) ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ የአረማዊውን ሮም ፈጣን ግስጋሴ ያሳያል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ (ዳን. 8፡10-12) ትንሹ ቀንድ አንዳንድ ከዋክብትን ቁልቁል እየጣለና (የእግዚአብሔርን ሕዝቦች እያሳደደ) ራሱን “ከሰማይ ሰራዊት አለቃ” ይኸውም ከየሱስ እኩል ከፍ ከፍ እያደረገ በፍጥነት ሽቅብ ያድጋል፡፡ ይህ ሁኔታ አረማዊውን ሮም አሽመድምዶ ከእርሱ ላይ ብቅ ያለውንና ዛሬ ድረስ በሮም ጸንቶ ያለውን ጳጳሳዊ ሥርዓት የዕድገት ደረጃ ይወክላል፡፡ (ተመሳሳይ ኃይል የነበራቸው ሁለቱ የዕድገት ደረጃዎች ትንሹ ቀንድ በሚል አንድ ዓይነት ተምሳሌታዊ አገላለጽ የተወከሉበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡) በዳን. 7፡9-10 የምናገኘው ፍርድ፣ በዳን. 8፡14 የቀረበው የቤተ መቅደሱ መንጻት እንዲሁም በማቴ. 24፡29 የቀረቡት የሰማይ ኃይላት መናጋት ምልክቶች በመጨረሻዎቹ ቀናት እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ያሳያሉ፡፡

ግንቦት 8
May 16

አሥሩ ልጃገረዶች


የሱስ በማቴ. 24 ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሰፊ ንግግር ካደረገ በኋላ በማቴ. 25 ደግሞ ለዚያ ጊዜ እንዴት መዘጋጀት እንደሚገባ ይናገራል፡፡ ስለ አስሩ ልጃገረዶች በተምሳሌት የሚናገሩትን የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡1-13፡፡ የሱስ ለዳግም ምጽአቱ እንዴት መዘጋጀት እንዳለብን ሊረዳን የሚችል ምን ዓይነት ነገር እየነገረን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሱስ ስለ አሥሩ ልጃገረዶች በማውሳት የመጀመሪያ ንግግሩን ምዕራፍ ይከፍታል፡፡ “ ‘ልጃገረዶች’ ” በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል የጌታን አዳኝነት በግል ተቀብለው ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ወገኖችን ይወክላል፡፡ እነዚህ ሰዎች በታላቁ ውዝግብ ወቅት ከሰይጣን በኩል አልቆሙም፡፡ ይልቁንም ለሰማያዊው መንግሥት ገጣሚዎች ናቸው (ማቴ. 25፡1)፡፡ ነገር ግን በመጨረሻው ጊዜ ሁሉም አንቀላፉ (ማቴ. 25፡5)፡፡ ክርስቶስ ደግሞ ሳንዘጋጅ ዳግመኛ እንዳይገለጥ--ሁሌም ተግቶ ወይም ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ አስጠንቅቆአል (ማቴ. 24፡42)፡፡ መብራታቸውን የያዙት አሥሩም ልጃገረዶች ሙሽራውን ለመቀበል ወጡ፡፡ ይህም ሁሉም ዳግም ምጽአቱን አሻግረው እየተመለከቱ እንደሆን ያሳያል፡፡ ሆኖም ሙሽራው በመዘግየቱ በመምጣቱ ላይ እምነት የነበራቸው ወገኖች እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ፡፡ ሳይታሰብ እኩለ ሌሊት ላይ የሙሽራው መምጣት ስለ ተሰማ ሁሉም ከተኙበት ተቀሰቀሱ (ማቴ. 25፡1-6)፡፡ ያልተዘጋጁትና ዝንጉዎቹ ልጃገረዶች ግን በሆነው ነገር ተደነባበሩ፡፡ ለምን? “‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ’” (ማቴ. 25፡8) በሚል፡፡ ይህ አባባላቸው መብራታቸው እየደበዘዘ መሄዱን እንጂ መጥፋቱን አይገልጥም፡፡ ያላቸው ዘይት አነስተኛ በመሆኑ ክርስቶስን ለመገናኘት የሚያስችለውን ዝግጅት ለማድረግ አይበቃቸውም፡፡ ታዲያ ችግሩ ያለው ምኑ ላይ ነው? እነዚህ ልጃገረዶች ከክርስቶስ ጋር ጥልቅ የግንኙነት ተሞክሮ ሳይኖራቸው የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ይጠባበቁ የነበሩ ክርስቲያኖችን ይወክላሉ፡፡ ጥቂቱ ዘይት--በሕይወታቸው የሚስተዋለው ደብዛዛ የመንፈስ ሥራ በእጅጉ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሊጠፋ መቃረቡን ያሳያል፡፡ የሚያስፈልጋቸው መጠን ብዙ ሆኖ ሳለ እነርሱ ግን በጭላጯ ረክተው ነበር፡፡ “መንፈስ እንደ ራሱ መሻትና እንደፈቃዱ በሰብዓዊው ልብ ውስጥ በመሥራት አዲሱን ተፈጥሮ ያኖራል፡፡ በዝንጉዎቹ ልጃገረዶች የተወከሉት አማኞች ግን ጥልቀት በሌለው ተግባር ረክተው ነበር፡፡ እግዚአብሔርን አያውቁትም፡፡ የአምላካዊውን ባህሪ ምንነት ባለማጥናታቸው ከእርሱ ጋር አንድነት አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ እንዴት በእርሱ እንደሚታመኑ፣ አመለካከታቸውን በእርሱ ላይ እንደሚያደርጉም ሆነ እንደ ፈቃዱ እንደሚኖሩ አያውቁም፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሰጡት አገልግሎት መልክ ብቻ በመያዙ ቁልቁል አሽቆልቁሎአል፡፡”—Ellen G. White, Christ’s Object lessons, p. 411. ዝንጉዎቹ የሠሩት ዓይነት ስህተት እንዳንሠራ ወደ ራሳችን መመልከት የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ራስዎን ከእነርሱ በተመሳሳይ የሚያገኙ ከሆነ ከዚህ ሁናቴ ማምለጥ የሚችሉት እንዴት ነው?

ግንቦት 9
May 17

ስጦታዎችዎን ጥቅም ላይ ማዋል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡13-30፡፡ ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከመዘጋጀት አኳያ መክሊቶቻችንን ጥቅም ላይ ማዋላችን ምን ዓይነት ሚና አለው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳ የሱስ በዚህ ቦታ የሚጠቀመው ምሳሌያዊ አባባል ቀደም ካለው የተለየ ቢሆንም ነገር ግን ሁለቱም የሚናገሩት ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ስለመዘጋጀት ነው፡፡ የሁለቱም ሀሳብ የሚያጠነጥነው ስለተዘጋጁና ስላልተዘጋጁት ነው፡፡ እንዲሁም ከራሳቸው መንፈሳዊ ቸልተኝነት የተነሳ ከዘላለማዊ ጥፋት ጋር መጋፈጣቸውን ሁለቱም ምሳሌያዊ አባባሎች ያሳዩናል፡፡ ከአሥሩ ልጃገረዶች ጋር በተያያዘ የቀረበው ዘይት መንፈስ ቅዱስን ይወክላል፡፡ በማቴ. 25፡15 “ታላንት” በሚል የቀረበው ቃል ደግሞ የተወሰደው ከግሪክኛው ታላንታ ሲሆን “የወርቅ ቦርሳ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ “ታላንት ሁሉንም የተፈጥሮ ስጦታዎች ጨምሮ የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይወክላል፡፡”—The SDA Bible Commentary, vol. 5, p. 510. በተምሳሌታዊ አባባሎቹ የቀረቡት ሁሉም አገልጋዮች ከጌታቸው ንብረት ተቀብለዋል፡፡ እዚህ ላይ እነርሱም “‘ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል’ ” (ማቴ. 25፡15) ዐደራ የተቀበሉ የጌታቸው ንብረት መሆናቸውን ልብ ይሏል (ማቴ. 25፡14)፡፡ ንብረቱ የተሰጣቸው በዐደራ እንደመሆኑ፤ የራሳቸው ላልሆነው ንብረት ዐደራ ተቀባይ መጋቢዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጌታቸው ተመልሶ በመጣ ጊዜ “ ‘የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ’ ” (ማቴ. 25:19)፡፡ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ምንጩ መንፈስ ቅዱስ ነው (1ቆሮ. 12:1–11፣ 28–31፣ ኤፌ. 4:11)፡፡ አነስተኛ ስጦታ እንዳላቸው ለሚያስቡ ወገኖች መልካም የምስራች አለ፡፡ መቼም ያለ ሰጪ ስጦታ መቀበል አይቻልም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ታላቅ ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ በመቀበል ስጦታቸውን መውሰድ ይችላሉ፡፡ ስጦታዎች አንዴ በክርስቶስ የእኛ ሆነው የተሰጡን ቢሆንም ነገር ግን የልከኛው ንብረት ባለ ዐደራ መሆን መንፈስ ቅዱስን በመቀበልና ራስን ለእርሱ በማስገዛት ላይ መተማመን ያደርጋል፡፡ ትርፋማ ያልነበረው ባለ ዐደራ አገልጋይ ስህተት እዚህ ላይ ነበር፡፡ ግለሰቡ የሚያገላብጠው ዐደራ ቢሰጠውም እርሱ ግን ከመሰወር ውጪ ፈጽሞ አላንቀሳቀሰውም፡፡ በለጋስነት የተሰጠውን ዐደራ በሆነ መንገድ ለማበልጸግ ምንም ጥረት አላደረገም፡፡ በዚህ የተነሳ “‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ’ ” (ማቴ. 25፡26) በማለት የሱስ ሲኮንነው ይስተዋላል፡፡ የሱስ ይህን ተምሳሌታዊ አባባል የተጠቀመው ከመጨረሻው ጊዜ እና ከእርሱ መመለስ ዐውድ ነበር፡፡ ለመጨረሻዎቹ ቀናት ለመዘጋጀት ስጦታዎቻችንን ጥቅም ላይ ማዋላችን ወሳኝ መሆኑን አስመልክቶ ይህ ምን ያስተምረናል?

ግንቦት 10
May 18

ተጨማሪ ሀሳብ፡


“አንድ ታላንት የተቀበለው ሰው ‘መሬት ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ’፡፡ ግለሰቡ ከሁሉም አነስተኛውን ስጦታ ቢቀበልም ሊያበለጽገው ግን አልወደደም፡፡ አባባሉ የተሰጠኝ ስጦታ አነስተኛ ነው በሚል ሰበብ ራሳቸውን ከክርስቶስ አገልግሎት ለማግለል የሚሞክሩትን ያስጠነቅቃል፡፡ ጥቂት ላቅ ያሉ ነገሮችን ቢያደርጉ አብልጠው በደስታ መንቀሳቀስ በቻሉ ነበር፡፡ ጥቃቅን ነገሮችን ብቻ ማስተናገዳቸው አንዳችም ድርሻ እንደሌላቸው አድርገው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ መንስኤ ሆኗቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ስህተት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ጌታ ስጦታዎችን ሲሰጥ በባህሪ ላይ ፍተሻ ያደርጋል፡፡ የተሰጠውን ታላንት ለማበልጸግ ችላ ያለው ግለሰብ እርሱ ራሱ ታማኝ አገልጋይ አለመሆኑን አስመስክሯል፡፡ አምስት ታላንት ተሰጥቶት ቢሆን ኖሮ መሬቱን ምሶ አንዱን እንደቀበረ ከመሰወር ውጪ አያበለጽገውም ነበር፡፡ በአንዱ ታላንት ላይ ያሳየው አግባብ የጎደለው አጠቃቀም የሰማይን ስጦታ መናቁን አመላክቶአል፡፡ “‘ በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል’ ሉቃ. 16፡10፡፡ ብዙውን ጊዜ ትናንሾቹ ነገሮች ዝቅ ተደርገው ስለሚታዩ ተገቢው ዋጋ አይቸራቸውም፡፡ ነገር ግን ለአብዛኛው የሕይወት እውነተኛ ግብረገብ ስንቅ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው፡፡ በእርግጥ በክርስትና ሕይወት ፋይዳ ቢስ የሚባሉ ስጦታዎች የሉም፡፡ የትናንሾቹን ነገሮች አስፈላጊነት ዝቅ እያደረግን የምንመለከት ከሆነ ባህሪ የማነጽ ሥራችንን በአደጋ የተሞላ እናደርገዋለን፡፡”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 356.


የውይይት ጥያቄዎች፡



1.ሰዎች ማንኛውም ነገርም ሆነ ሰው ፍጹም በሆነ ሰላምና ውህደት የሚሠራበት ዓለም (utopia) በዚህ ምድር ገቢራዊ ይሆናል ብለው እንዲያምኑ ያደረጓቸው አንዳንዶቹ ርዕዮተ ዓለሞችና ጽንሰ ሃሳቦች ምንድን ናቸው? እነዚህ ጽንሰ ሃሰቦች ምን ነበሩ? ዋጋ ቢስ ሆነው የቀሩት ለምንድን ነው?
2.እግዚአብሔር አድርጉ ብሎ የነገረንን መታዘዛችን እምነታችንን ማጠንከር የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ማለት እምነት ያለ ሥራ “ሙት” (ያዕ. 2፡26) የሆነው ለምንድን ነው? “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁ” (ራእ. 14፡12) ሕዝቦችን ወደፊት የሚጠብቃቸውን አስቸጋሪ ሁናቴ ከግምት በማስገባት--ገና ነው ብለን ለምናስበው ግን በደጃፋችን ላለው ሁናቴ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3.ስለ አሥሩ ልጃገረዶች ጠለቅ አድርገው ለማሰብ ይሞክሩ፡፡ የእነርሱ ታሪክ በቀጥተኛም ሆኖ በሌሎች ፈርጀ ብዙ መንገዶች ለእኛ እንደ ማስጠንቀቂያ ሆኖ የቀረበው ለምንድን ነው? እንደ ዝንጉዎቹ ልጃገረዶች ራሳችንን እያታለልን ላለመሆኑ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
4.ቢቻል “የተመረጡትን” ለማሳት--ሲል ምን ማለቱ ነው? “የተመረጡ” ለሚለው ቃል ያለን ግንዛቤ ምን ይመስላል? (ማቴ. 24፡24፣ ሮሜ 33፣ ቆለ. 3፡21)፡፡ በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች የሚስተዋሉት የማሳቻ መንገዶች ምን ያህል ታላቅ መሆናቸውን ይህ ምን ይነግረናል?