መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከጥር 12 – 18

አራተኛ ትምህርት

January 20–January 26
 

ከዓለማዊ አካሄዶች ማምለጥ

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 119:11፣ ኤፌ.6:18፣ ሮሜ 8:5-6፣ ዕብ. 11:1–6፣ 1ነገሥ. 3:14፣ ሕዝ. 36:26-27፡፡

 

የሳምንቱ መሪ ጥቅስ፦ “ በቁጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች፡፡... በሀብቱ የሚታመን ሁሉ ይወድቃል፤ ጻድቃን ግን እንደ አረንጓዴ ቅጠል ይለመልማሉ፡፡” ” (ምሳ. 11፡4፣ 28)

ምንም እንኳ ሰይጣን በየሱስ ባይሳካለትም እያንዳንዱን ሰብዓዊ ፍጡር መጣል ችሎአል፡፡ እርሱ ብቻ ነጻነት ሊሰጠን በሚችለው አምላክ ታምነንና በመንፈሳዊው የጦር ትጥቅ በእግዚአብሔር ኃይል ካልተዋጋን፤ ዓለም እኛን አባብሎ ከመውሰድ አይቦዝንም፡፡

ስለዚህ ትኩረታችንን በሰማያዊው ቸርነት ላይ ልናደርግ የግድ ነው፡፡ ዳዊት የሚከተለውን ሲጽፍ ይህ ህይወት ያለውን እውነተኛ ዋጋ ተገንዝቧል፡፡ “አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጎድልባቸውም፡፡” (መዝ. 34፡10)፡፡ ሰለሞን ጥበብና ማስተዋል ከብርና ወርቅ የላቀ ዋጋ እንዳለው ተረድቷል (ምሳ. 3፡13-14)፡፡ ዐይኖቻችንን ከንብረቶቻችን ላይ አንስተን የሁሉም ባለቤት በሆነው ክርስቶስ ላይ ስናሳርፍ፤ ያን ጊዜ የእውነተኛ ደስታና ቀና ህይወት ባለቤት እንሆናለን፡፡

ስሜታችንን በቀላሉ መግዛት ከሚችለው ከአማላዩ ዓለም ማምለጥ የምንችለው ከየሱስ ጋር በምንፈጥረው ስኬታማ ብሎም ወሳኝ ግንኙነት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የዚህን ግንኙነት አላባዎች እናጠናለን፡፡ ከጭምብሉ ዓለም በስተጀርባ የሚገኘውን ኃይል ለይተን ማወቃችን ለገዛ ራሳችን መንፈሳዊ ህይወት ስኬት ምን ያህል ፋይዳ እንዳለውና፤ ክርስቶስ በዚህ ምድር ለመመላለሳችን ምን ያህል ተጨባጭ ምክንያት እንደሆነ እናያለን፡፡
 

ጥር 13
January 21
 

ከክርስቶስ ጋር የተመሰረተ ግንኙነት

 

እምብዛም የተትረፈተፈ ነገር የሌላቸውን ጨምሮ የዚህን ዓለም ንብረት የሚወዱ ሰዎች ነፍስ--ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራት ሲገባ፤ ከዚህ ዓለም ጋር በብርቱ ሰንሰለት ተቆራኝታለች፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ምድራዊ ሀብት ንብረት ሊኖረን ባይችልም ነገር ግን አንቅልፍ አጥተን ቁሳዊውን ነገር የምንመኝ ከሆነና፤ ይኸው አጉል ምኞት በጌታ ቁጥጥር ስር መዋል ካልቻለ፤ ነፍስን ከደኅንነት መስመር አውጥቶ ለአስከፊ ችግር ሊዳርግ ይችላል፡፡ ሰይጣን ይህን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሰዎችን በቁሳዊው ነገር ፍቅር ለማጥመድ የተቻለውን ያህል ይሠራል፡፡

ታዲያ ለዚህ ብቸኛው መከላከያችን ምንድን ነው?

“አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊው ነገር ላይ አይሁን” (ቆለ. 3፡2)፡፡ ጳውሎስ አድርጉ ያለንን የምናደርገው እንዴት ነው? (በተጨማሪ እነዚህን ጥቅሶች ይመልከቱ፡ መዝ. 119፡11፣ ኤፌ. 6፡18)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አስተሳሰባችን በምን ላይ ሊያርፍ እንደሚገባ የሚናገር ሌላ ጥቅስ ማግኘት ይችላሉ? (ፊልጵ. 4፡8)

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ የማያቋርጥ አምልኮ (መዝ. 34፡1) የህይወትን ውጣ ውረድ ተከትሎ በየትኛውም አቅጣጫ ሊመጣ ከሚችል ዓለማዊነት ብቸኛው ፈውስ ነው፡፡ ሙሴ “ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ” (ዕብ. 11፡26)፡፡ ከማንኛውም ግንኙነት በፊት ቅድሚያ ልንሰጥ የሚገባው ለክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ በጽኑ እምነት ላይ የተመሰረተ መተማመን ከእኛ ይፈልጋል፡፡ ይህ ማለት እርሱ--እርሱ በመሆኑና ስላደረገልን ነገር ልናመልከው ይገባል እንጂ እምነታችንና ቁርጠኝነታችን ሊያስገኝልን የሚችለውን ጥቅም ተከትሎ መሆን የለበትም፡፡

ህይወታችን በየሱስ ሊሸሸግ፣ አምላካዊው ዕቅድም እቅዳችን ሊሆን የተገባ ነው፡፡ እውነተኛ ቁርጠኝነት እርፍ ጨብጦ “ወደ ኋላ” አለመመልከት ነው (ሉቃ. 9፡62)፡፡ እንደዚያ ያለውን ኪዳን ስንጠብቅ የሱስ በሙላት የምንንቀሳቀስበትን ኃይል ይሰጠናል፡፡ ራሳችንን ለእርሱ ስናስገዛ ይህ ዓለም በነፍሳችን ላይ ያለውን ይዞታ ይሰባብርልናል፡፡ ህይወታችን ተብለጭላጩን ግዑዝ ሳይሆን በነፍሳችን ውስጥ ያለውን ክፍተት ሊሞላ የሚችለውን ክርስቶስ ያማከለ ሊሆን የግድ ነው፡፡

እጅግ አጥብቀው ሽተውት ስለነበር ቁሳዊ ንብረት አሰብ ያድርጉ፡፡ የፈለጉትን እጅዎ ካስገቡ በኋላ በውስጥዎ የነበረው ደስታ ሳይደበዝዝ ለምን ያህል ጊዜ አብሮት መቆየት ቻለ?
 

ጥር 14
January 22
 

በዓለም ውስጥ

 

በዓለም ዙሪያ ከስድስት ቢልዮን የሚበልጡ መጽሐፍ ቅዱሶች ተሰራጭተዋል፡፡ ታዲያ ከእነዚህ ውስጥ እንደ ሕያው አምላክ ቃል የተስተዋሉት ስንቶቹ ናቸው? እውነትን ለማወቅ በቅን ልቦና የተነበቡትስ ምን ያህል ይሆኑ?

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ--ዮሐ. 5፡39፣ 14፡6፣ 20፡31፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ወንጌል ስለ የሱስ እጅግ ጠቃሚ መረጃ ይሰጠናል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሱት እነዚህ ጥቅሶች በተለይ ስለ እርሱ ምን ይላሉ? እርሱ ለእኛም ሆነ ለእምነታችን ያን ያህል አስፈላጊ የሆነበት ምክንያቱ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናው የእውነት ዋንኛው ምንጭ ስለሆነ ነው፡፡ የሱስ እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ መገለጡን ተከትሎ እርሱን ወደ ማወቅ እንመጣለን፡፡ ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ስለ የሱስ ማንነትና እርሱ ለእኛ ስላደረገልን ነገር በቂ ዕውቀት ይሰጡናል፡፡ ይህ ዕውቀት ከእርሱ ጋር በፍቅር ይጥለንና ህይወታችንንም ሆነ ነፍሳችንን በዘላለማዊ ጥበቃው ስር እናስገዛለን፡፡ የሱስን በመከተልና በአምላካዊው ቃል የተገለጸውን ቃሉን በመታዘዝ ከዓለምና ከኃጢአት ግዞት ነጻ መውጣት እንችላለን፡፡ “እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ” (ዮሐ. 8፡36)፡፡

በሮሜ 8፡5-6 የተሰጡን ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው? የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት በአእምሮአችን ለሚካሄደው ትግል እንዴት ሊረዳን ይችላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ዓለምን መውደድ በተለይም ለምድራዊው ቁስ የሚኖር ፍቅር ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረግን በቀር በቀላሉ ከእግዚአብሔር ሊያርቀን ይችላል፡፡ ለክርስትና ህይወት እጅግ ወሳኝ የሆነውን ዘላለማዊና ተጨባጭ መንፈሳዊ እውነታዎችን በሚያመላክተን በቃሉ ውስጥ ተጠብቀን መኖር አለብን፡፡

ለዓለማዊ ነገሮች የሚኖር ፍቅር አእምሮን ላቅ ወዳለ መንፈሳዊ ምግባር ማሳደግ አይችልም፡፡ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎችን በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነትና በክፉ ምኞት ይተካቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተገለጠው--ፍቅር ራሳችንን ለሌሎች የመስጠትን አስፈላጊነት በማስተማር ግንኙነትን ያጠናክራል፡፡ ዓለማዊነት ግን የሱስ ከሚወክለው ማንኛውም እውነት በተቃራኒ ሁሉንም ነገር ለራስ ብቻ ያግበሰብሳል፡፡
 

ጥር 15
January 23
 

የጸሎት ህይወት

 

“ ‘አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት’ ” (ዮሐ. 17:3)፡፡ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እምነታቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት መሆኑን ሲናገሩ መደመጣቸው እምብዛም አይገርምም፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ “ ‘የዘላለም ሕይወት’ ” ከሆነ፤ ይህን ሕይወት ከእርሱ ጋር በሚኖር ግንኙነት እናገኘዋለን እንደ ማለት፡፡ ደግሞም የዚህ ትስስር ማዕከል ግንኙነት መሆኑ አይታበልም፡፡ በትናንቱ ጥናታችን እግዚአብሔር በመለኮታዊ ቃሉ አማካኝት እንደሚገናኝን መመልከታችንን ልብ ይሏል፡፡ እኛም በበኩላችን በጸሎት አማኝነት ከእርሱ ጋር መገናኘት እንችላለን፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው አዕምሮአችንንና ልባችንን ከዚህ ዓለም ነገሮች በተቃራኒ በሰማያዊ ነገሮች ላይ የምናኖር እስከሆነ ድረስ ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ጸሎት ከራሱ ከዓለም ይልቅ እኛን ከፍ ወዳለው ግዛት የማመላከት ተፈጥሮ ስላለው ነው፡፡

ጸሎታችንም ቢሆን አንዳንዴ ራስ ወዳድነታችንን ብቻ የማንጸባረቅ ባህሪ ሊኖረው ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ጸሎታችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን የተገባ ነው፡፡

ይህን የተሳሳተ ጽንሰ ሃሳብ በመዝሙር ለማሳየት የፈለገች አንዲት ሴት “ኦ ጌታ ሆይ፤ አንዲት ማርቼዲስ አትገዛልኝም ወይ?” ብላ ነበር፡፡ እኛም ብንሆን ለዓለም መሞታችንን በምናሳይበትና ራሳችንን ለእግዚብሔር አሳልፈን በምንሰጥበት በጸሎት ወደ ጌታ ስንቀርብ፤ የእርሱን ፈቃድ እንጂ የራሳችን ላለመሻታችን እርግጠኞች ልንሆን የተገባ ነው፡፡

የጸሎታችን አካል ሊሆን የተገባው ዕብ. 11፡1-6 ላይ የምናገኘው እጅግ አስፈላጊ ክፍል ምንድን ነው? በተጨማሪ በእምነት ወደ ጌታ መምጣትና መጸለይ ምን ማለት ነው?

ከጸሎታችን ጋር የተሳሰረ እምነት ከሌለን ከንቱ ድፍረትና የሰይጣን ከአንገት በላይ እምነት በውስጣችን ሊገለጥ ይችላል፡፡ “ጸሎትና እምነት በቅርብ የተሳሰረ ህብረት ስላላቸው በአንድነት ሊጠኑ የተገባ ነው፡፡ በእምነት የሚጸለይ ጸሎት ውስጥ መለኮታዊ ሳይንስ አለ፡፡ ህይወቱን በተሳካ ሁኔታ የሚያከናውን እያንዳንዱ ሰው ይህን ሳይንስ መረዳት አለበት፡፡ ክርስቶስ እንዲህ ይላል ‘ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል፡፡’ (ማር. 11፡24)፡፡ ልመናችን እንደ እግዚአበሔር ፈቃድ ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ አስቀምጦልናል፡፡ በመሆኑም እንደሚሰጠን ቃል የገባልንን ነገሮች መጠየቅና የምንቀበለውን ነገር የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ማዋል ይኖርብናል፡፡ የተጠየቀው ከተሟላ ተስፋው ቁርጥ ያለና የማያጠራጥር ነው፡፡” — Ellen G. White, Prayer, p. 57.

ወደ ራስዎ የጸሎት ህይወት ይመልከቱ፡፡ ስለ ምን ይጸልያሉ? ቅድሚያ ስለሚሰጧቸው ነገሮች ጸሎትዎ የሚናገረው ነገር አለ? ሊጸልዩባቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
 

ጥር 16
January 24
 

የጥበብ ሕይወት

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው እጅግ ውብ ታሪኮች አንዱ እግዚአብሔር ከሁሉ አስበልጦ እንዲሰጠው ሰሎሞን ያቀረበው ልመና ነው፡፡ “መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?’ ” (1ነገሥ. 3:9)፡፡

ሰለሞን የእግዚአብሔርን ሀሳብ ሰምቶ የሚከተል ከሆነ ምድራዊ ሀብትና ብልጽግና ሊያደርስበት ከሚችለው ውድመት እንደሚታደገው ለሰሎሞን የነገረው ጠቃሚ ነገር ምን ነበር? 1ነገሥ. 3:14፣ 1ዮሐ. 5:3፣ 1ጴጥ. 4:17፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሰሎሞን የታላቅ ጥበብ ባለቤት ነበር፡፡ ሆኖም ጥበብ እንደሚገባው ካልተመላለሱባት ከመልካም መረጃ ያለፈ ዋጋ አይኖራትም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ጥበብ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አባባል መሰረት ገቢራዊ መሆን ካልቻለ እውነተኛ ጥበብ አይደለም፡፡ ስለ እግዚአብሔር አምላክና እርሱ ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር መጠነ ሰፊ ትክክለኛ መረጃ የነበሯቸው ብዙዎች በዓለም ተውጠው ጠፍተዋል፡፡ የሰሎሞን እግዚአብሔርን ሳይታዘዝ መቅረትም ጌታ በጠራው መንገድ ከመራመድ ባክኖ እንዲቀር መንስኤ ሆኖት ነበር፡፡ ሆኖም የዕድሜው አመሻሽ ላይ በእውነት ወደ ህሊናው ተመልሶ እንዲህ ሲል በትህትና ጻፈ “ጥበብ ከቀይ ዕንቁ ይበልጥ ውድ ናትና፤ ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም” (ምሳ. 8፡11)፡፡

ጥበብ የዕውቀትና ማስተዋል ትግበራ ነው፡፡ ዕውቀት በማስረጃ የተደገፈውን እውነት ግንዛቤ ደግሞ ማስተዋልን ይወክላል፡፡ ዕውቀታችንንና ማስተዋላችንን በሕይወታችን ላይ ማዋል ስንችል በሂደት ጥበብ ይመጣል፡፡ ብልህ መጋቢ የሚሻው ዕውቀትንና ማስተዋልን ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና ማስተዋል በመመላለስ የሚያካብተውን ተሞክሮ ነው፡፡

አንድ ሰው በተሰጠው ጥበብ ካልተመላለሰ፤ እጅግ አስተዋይና ብልህ የተባሉ ሰዎች ሳይቀር ባዶ በሆነው ቁስ የተከበበ አኗኗር ዘይቤ በቀላሉ ተጠልፈው ሊጠፉ እንደሚችሉ የሰሎሞን ምሳሌ ያሳየናል፡፡

ሁለቱን ጥቅሶች ያመሳክሩ፡ 1ቆሮ. 3፡19፣ ምሳ. 24፡13-14፡፡ በሁለቱ የጥበብ ዓይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? መልስዎን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ለማካፈል ይሞክሩ፡፡

ጥቅምት 16
January 25

መንፈስ ቅዱስ

 

በበጎና በክፉ መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ እሙን ነው፡፡ አንደኛው ወገን ወደ ክርስቶስ (ዮሐ. 6፡44) ሌላኛው ደግሞ ወደ ዓለም ይስበናል (1ዮሐ. 2፡16)፡፡ እኛ ራሳችንን ለማስገዛት ፈቃደኞች ከሆንን፤ በሕይወታችን ውስጥ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ሊመራን ይችላል--ፈቃደኛም ነው፡፡

“ ‘የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል’ ” (ዮሐ. 16:13፣ ዮሐ. 14፡16)፡፡ መንፈስ ቅዱስ የራሱን መንገድ በሚሻና በስሜታዊነት ሳይሆን በመርኅና በእውነት ላይ የተመሰረተ ህይወት እንድንኖር ኃይል ይሰጠናል፡፡ ለሰማያዊው ሕይወት ገጣሚ ዝግጅት ማድረግ ማለት በዚሁ ምድር በመንፈስ ቅዱስ አመራር የሚመላለስ ታማኝ ህይወት መኖር መጀመር ነው፡፡

ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመክራል “ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሰረት ነው” (1ቆሮ. 2፡5)፡፡ ብዙውን ጊዜ ዓለም በማባበያ ቁስ እየተጠቀመ ከጌታ ወደ ራሱ ቢስበንም፤ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ደግሞ መልሶ ወደ ጌታ ሲያመጣን ይስተዋላል፡፡

ከዓለምና ከማባበያዋ ጋር በሚደረግ ውጊያ የሚገኘው ስኬት የሚመጣው ከእኛ በላይ በሆነ ኃይል ነው--ሕዝ. 36:26-27፣ ዮሐ. 14:26፣ ኤፌ. 3:16-17፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንዲገዛን ስንፈቅድ የመንፈሳዊ ድል ባለቤቶች መሆናችንን ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ነገሮችን ያደርጋል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ሰይጣን በሰብዓዊው አእምሮ ላይ ኃይልና ብርታት እንዲኖረው የሚያስችሉት፤ ሐሰተኛ ንድፈ ሃሳቦችና ባህሎች ናቸው፡፡ የሰዎችን ትኩረት ሐሰተኛ መሰረት ወዳላቸው ነገሮች እየመራ የተሳሳተውን ባህሪ በውስጣቸው ይቀርጻል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአምላካዊው ቃል አማካይነት ለአእምሮ እየተናገረ እውነትን በልብ ውስጥ ያነቃቃል፡፡ በዚህም ስህተትን እያጋለጠ ከነፍስ ውስጥ ያባርራል፡፡ ክርስቶስ ምርጦቹን ሕዝቦቹን በስሩ የሚያስገዛው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በሚሠራው የእውነት መንፈስ አማካኝነት ነው፡፡” —Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 671.

የሱስ ከእርገቱ በኋላ እግዚአብሔርን በምድር እንዲወክል ሊሰጠን የሚችለው የመጨረሻው ስጦታ የእውነት ዘጋቢ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዓለምንና ዓለማዊውን “አዚም” የምናሸንፍበትን ኃይል ለእኛ ለመስጠት ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋል፡፡

ዓለም ሁላችንንም የመሳብ ኃይል አላት--አይደል? የዓለምን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ሊሰጥዎ ለሚችለው ለመንፈስ ቅዱስ ራስዎን አሳልፈው ለመስጠት የሚረዳዎ--ምን ዓይነት ምርጫ ባሁኗ ደቂቃ ማድረግ ይችላሉ?
 

ጥር 18
January 26
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

መጋቢነት በሁለት መንታ መርኅዎች ይዘወራል-በውዴታ ግዴታ እና በፍቅር፡፡ “የውዴታ ግዴታ ፍቅር የምትባል መንትያ እህት እንዳለችው አንዘንጋ፡፡ ታዲያ ሁለቱ ኅብረት ከፈጠሩ የሚሳናቸው ነገር የለም፡፡ ከተነጣጠሉ ግን--አንዳቸውም በተናጥል መልካም የማድረግ ችሎታ የላቸውም፡፡” —Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 62. ፍቅርን በተግባር ገልጦ ማሳየት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ፍቅር በውስጣችን መነሳሳት ይፈጥር ዘንድ ሁሌም በክርስቶስ መሥዋዕትነት ውስጥ ብቻ ውለን ልናድር ይገባል፡፡

መንትዮቹ ጥላቻና ዐመፅ ከላይ ከቀረቡት ተቃራኒ የዓለም መርኅዎች ናቸው፡፡ ዐመፅ ጥላቻ በተግባር የሚገለጥበት መንገድ መሆን ይችላል፡፡ ሉሲፈር በእግዚአብሔር ላይ ዐመፀ (ሕዝ. 28፡16-17)፡፡ እርሱ እስከ መጨረሻ እስከሚወገድ ይህን የዐመፃ ተግባር ከማድረግ አይገታም፡፡ እርሱ የፍቅርን ሥልጣን ወደ የሥልጣን ፍቅር ገለበጠው፡፡ የሱስ የነበረውን ሥልጣንና ኃይል አብልጠው ይጠሉ የነበሩት የእስራኤል ኃይማኖት መሪዎች መንገዳቸውን አልለወጡም ነበር (ማቴ. 22፡29)፡፡


 

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. በፍቅርና በውዴታ ግዴታ ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ጠለቅ ያለ ምልከታ አድርጉ፡፡ ኤለን ኋይት ፍቅርንና የውዴታ ግዴታን--መንትዮች ብላ በመጥራት “አንዳቸውም በተናጥል መልካም የማድረግ ችሎታ የላቸውም” ስትል ምን ማለቷ ነው? ፍቅር ያለ ውዴታ ግዴታ ምን ሊመስል ይችላል? የውዴታ ግዴታስ ያለ ፍቅር ምን ዓይነት ገጽታ አለው? ሁለቱ መነጣጠል የሌለባቸው ለምንድን ነው?

  2. የዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን መሪ ጥቅስ እንዲህ ይላል፡ “በቁጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች፡፡... በሀብቱ የሚታመን ሁሉ ይወድቃል፤ ጻድቃን ግን እንደ አረንጓዴ ቅጠል ይለመልማሉ፡፡” (ምሳ. 11፡4፣ 28)፡፡ የዚህ ጥቅስ ፍቺ ምንድን ነው? ስለ ሀብት ምን እያለ ነው? የማይለውስ ምንድን ነው?

  3. በሰሎሞን ህይወት ዙሪያ ተወያዩ፡፡ ከአምላካዊው መንገድ ምን ያህል ጭልጥ ብሎ መሄድ ይችል እንደ ነበር ተጠያየቁ፡፡ በምድራዊው የተትረፈረፈ ሀብት ከንቱነትና ባዶነት ዙሪያ በመጽሐፈ መክብብ የተጻፉ ጥቅሶችን ተመልከቱ፡፡ ትክክለኛውን መንፈሳዊ አካሄድ ጠብቀን ለመጓዝ ስለሚያስችለን ማለትም--ስለ ጸሎት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከክርስቶስ ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት በዚህ ሳምንት ያገኘነው ትምህርት ምንድን ነው?

  4. ሰዎች እዚህ ግባ የማይባል ሀብት ወይም ንብረት ሳይኖራቸውም ሰይጣን በሚያዘጋጅላቸው ወጥመድ የሚወድቁት ለምንድን ነው?

  5. በረቡዕ ትምህርት መጨረሻ ለየት ስላለው ጥበብ ለቀረበው ጥያቄ መልስዎ ምንድን ነው?