ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 8:1 –7፣ ማቴ. 13:3–7፣ 22፣ ዘፍ. 3:1–6፣ ኢሳ. 56:11፣ ማቴ. 26:14–16፣ 2ጴጥ. 1:5– 9፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ ‹‹“ ‘በእሾኽ መሃከል የተዘራው ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራውን ሰው ይመስላል’ ” ›› (ማቴ. 13:22)፡፡
አፍቅሮተ ንዋይና አፍቅሮተ ቁስ በብዙ አቅጣጫዎች ሊመጡብን ይችላሉ፡፡ ኤለን ኋይት በተንኮል የተሞሉትን ማራኪ የዲያብሎስ ማዘናጊያ ዘዴዎች እንዲህ ስትል ትገልጻቸዋለች፡፡ “ ‘በተትረፈረፈ ሀብትና ንብረት ወደ ተሞሉት እያመራችሁ ለምድራዊው ህይወት ብቻ እንዲጨነቁ፣ እንዲጠበቡ አድርጓቸው፡፡ የምድራዊው ርስት ባለሀብት ብቻ ሆነው ይቀሩ ዘንድ ዓለምን እጅግ ውብና ማራኪ አድርጋችሁ በፊታቸው አቅርቡላቸው፡፡ ፍቅራቸውም ሆነ መውደዳቸው በምድራዊ ነገሮች ላይ ብቻ ተተክለው እንዲቀሩ አድርጉ፡፡ ከእኛ በተቃራኒ ለአምላካዊው ጉዳይ የተሰለፉ አማኞች ዓላማቸውን የሚያሳኩበት የገንዘብ አቅም እንዳይኖራቸው በተቻለ አቅም መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ገንዘብ ሁሉ በመዋቅራችን ሥር ካልተዳደረና በአማኞች እጅ የሚገባ ከሆነ ምርኮዎቻችንን ከመዳፋችን እየፈለቀቁ በመንግሥታችን ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የክርስቶስን መንግሥት ስለ ማነጽና ስለ ምንጠላው እውነት መሰራጨት በመትጋት ፋንታ ስለ ንዋይ ብቻ አብልጠው እንዲጨነቁ የምናደርጋቸው እስከሆነ ድረስ ተጽእኖአቸውን መፍራት አያሻንም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ራስ ወዳድና አጉል ምኞት የተጸናወተው ሰው ከጉልበታችን ስር ውሎ በስተመጨረሻ ከእግዚአብሔር ሕዝብ የተነጠለ እንደሚሆን አበጥረን እናውቃለን’ ”— Counsels on Stewardship, pp.
154, 155.
እንዳለመታደል ሆኖ ከላይ የቀረበው ማዘናጊያ ዘዴ በሚገባ እየሠራ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህን መንፈሳዊ መሰናክል መገርሰስ እንችል ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል የሚለንን እየተመለከትን ከፊታችን የተጋረጡትን አደጋዎች ለማጤን እንሞክር፡፡
ታዋቂው የቴሌቪዥን ሰባኪ እንዲህ ሲሉ አንድ ቀለል ያለ መልእክት አቅርበው ነበር፡ እግዚአብሔር ሊባርክዎ ይፈልጋል፡፡ የመባረኩ ማረጋገጫ ደግሞ በእጅዎ የሰጠዎ የተትረፈረፈ ቁስ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለእግዚአብሔር ታማኝ እስከሆኑ ድረስ እግዚአብሔር ባለሀብት ያደርጎታል፡፡
ይህ ጽንሰ ሃሳብ ወይም የጽንሰ ሃሳቡ ልዩ ልዩ ፈርጅ የብልጽግና ወንጌል በመባል ይታወቃል እግዚአብሔርን ተከተል በዓለም ሀብትና ንብረት ይሞላሃል--የሚል፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ የተሳሳተ የነገረ መለኮት አስተምህሮ ከማለት ውጪ ሌላ ሊባል
አይችልም፡፡ በምድራዊ ቁስ የተሞሉና ደስተኛ መሆን ይሻሉ? እንግዲያውስ ለእርስዎ “ መልካም የምስራች” አለን፡፡
ወንጌልን ለምድራዊው ሀብት ዋስትና አድርጎ ማቅረብ የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ቋንቋ በግማሽ ከላዩ ጣል ከማድረግ በዘለለ መላወስ ያልቻለው እንዲህ ያለው እምነት፤ ከአምላካዊው ቃል ጋር መጣጣም ስለሚሳነው እኔነትን ማዕከል ያደረገ አስተምህሮ ያንጸባርቃል፡፡ በዚህ ሐሰት ውስጥ የኃጢአት ሁሉ መሰረት የሆነው እኔነትና ከማንኛውም ነገር በላይ እኔነትን የማርካት ምኞት ቁልጭ ብሎ ተቀምጦአል፡፡
የብልጽግና ወንጌል ነገረ መለኮት አስተምህሮ እንደሚለው ለእግዚአብሔር ስንሰጥ ቁሳዊውን ሀብትና ንብረት ለማፍራት ማስተማመኛ እናገኛለን፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው አስተምህሮ እግዚአብሔርን ሱቅ በደረቴ ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ደግሞ ገበያ ተኮር ውል ይሆንና፤ ይህን ሳደርግ በምላሹ ያንን እንደምታደርግ ቃል ግባልኝ-ዓይነት ቅርጽ ይይዛል፡፡ ስለዚህ የምንሰጠው በመስጠት አግባብ ሳይሆን ምላሹን ከመጠባበቅ አኳያ ይሆናል፡፡ የብልጽግና ወንጌል ማለት ይኸው ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ 2ቆሮ. 8፡1-7፡፡ የሐዋርያው መልእክት ምን ይመስላል? ከብልጽግና ወንጌል በተቃራኒ ምን ዓይነት መርኅዎች በጥቅሶቹ ሰፍረዋል? ሐዋርያው “የቸርነት ሥራ” (2ቆሮ. 8፡7) ሲል ምን ማለቱ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳ እነዚህ ሕዝቦች “ድኽነታቸው ብርቱ ቢሆንም” (2ቆሮ. 8፡2) አብልጠው ለጋሶች ስለነበሩ ከአቅማቸው በላይ ይሰጡ ነበር፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ብዛት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንድ ሰው የሚያፈራው የተትረፈረፈ ሀብት ከእግዚአብሔር ጋር በጽድቅ ለመመላለሱ በቂ ማስረጃ መሆን ይችላል የሚለውን የብልጽግናን ወንጌል የተሳሳተ አባባል እንድናስተውል ይረዱናል፡፡
ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው ነገር ግን ይህ ነው የማይባል ምድራዊ ሀብትና ንብረት ያልነበራቸው በምሳሌ የሚያቀርቧቸው ሰዎች ይኖራሉ? በተቃራኒው በምድራዊ ሀብት በልጽገው ለእግዚአብሔር ታማኝ ያልሆኑትስ? ሀብትን እንደ አምላካዊ በረከት ማሳያ መቁጠርን አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?
ክፉ ምኞት እንደ ማንኛውም ኃጢአት መጀመሪያ በልብ ውስጥ ይጠነሰሳል፡፡ በመቀጠል በውስጣችን ይጎለብትና በውጪ መታየት ይጀምራል፡፡ በኤደን የሆነው ይኸው ነበር፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡1-6፡፡ ሰይጣን ሔዋንን ለማጥመድ ምን ተጠቀመ? ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሰብዓዊውን ዘር ለማታለል ተመሳሳይነት ያላቸውን መርኅዎች ጥቅም ላይ እያዋለ ያለው እንዴት ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
“ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ፡፡” (ዘፍ. 3፡6)፡፡
አንድ ሰው ነገሮችን በጥልቅ መመልት ከቻለ፤ የማስታወቂያው ኢንደስትሪ ብልጭልጩን አጓጊ አድርጎ እያቀረበ የኤደንን ታሪክ በምሳሌነት እየደገመ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል፡፡ ሔዋን የማያስፈልጋትን ነገር ያስፈልገኛል ብላ እንድታስብ ያደረገው ዲያብሎስ፤ ቀድሞውኑ በእጇ ካለው ሁሉ በላቀ እንድትመኘውና ጉጉት እንዲያድርባት አድርጎ ያን የተከለከለ ዛፍ ፍሬ አቀረበላት፡፡ እንዴት ያለ ብልህ ዘዴ ነው! የእርሷ ውድቀት እያንዳንዳችን በክፉ ምኞት ስንወድቅ የሚከሰቱት ሦስት ቅደም ተከተሎች ማሳያ ነው--ማየት፣ መመኘት፣ ማድረግ፡፡
እንደ ምንዝር ሁሉ ከሥጋችን መጋረጃ ጀርባ ተሸሽጎ የሚገኘው ክፉ ምኞት ኃጢአት የመሆኑ ነገር እርግጥ ነው፡፡ ውሎ አድሮ ፍሬ እንዲያፈራ ከፈቀድንለት ውጤቱ አውዳሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በመጉዳት በምንወዳቸው ወገኖች ላይ ጠባሳ ሊተውና ነጋ ጠባ በጸጸት ሊጠብሰን ይችላል፡፡
ክፉ ምኞት በመላው ማንነታችን እንዲንሰራፋ ስንፈቅድ ማንኛውንም የህይወት መርኅ ገለባብጦ ዐናት ላይ ፊጥ ይላል፡፡ ነጉሥ አክዓብ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ ተመለከተ፣ ተመኘው፣ ንግሥቲቷ ሚስቱ እስክታስገድለው ድረስ እንደተበሳጨና እንደተቆጣ ሰነበተ (1ነገሥ. 21)፡፡ አካን የሚያምረውን ካባና ገንዘብ በተመለከተ ጊዜ እጅግ ከመጎምጀቱ የተነሳ ወሰደው (ኢያሱ 7፡20-22)፡፡ ክፉ ምኞት ውሎ አድሮ ለየት ያለ ራስ ወዳድ ቅርጽ የመያዝ ባህሪ አለው፡፡
“ራስ ወዳድነት በመላው ማንነት የሚሰራጨውን ኃጢአት ቅርጽ የሚይዝ ከሆነ፤ ክፉ ምኞት ደግሞ በመላው ማንነት የሚሰራጨውን ራስ ወዳድ ቅርጽ እንደሚይዝ ሆኖ መታየት ይችላል፡፡ ይህን አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” (2ጢሞቴ. 3፡1) በማለት በመጨረሻዎቹ ዘመኖች ላይ ገቢራዊ ስለሚሆነው ክህደት ሲገልጽ በዚያን ወቅት አብልጦ እያየለ የሚሄደውን ራስ ወዳድነት የሁሉም ክፉ ፍሬዎች ስር አድርጎ ያቀርብና፤ ክፉው ምኞት ግን የዚህ ኃጢአት ቀዳሚ ፍሬ ነው በማለት በሁለቱ መሃል ያለውን አስደናቂ ትስስር ያሳየናል፡፡ ‘ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ ይሆናሉ’ [2 ጢሞቴ. 3:2]”—John Harris, Mammon,(New York: Lane & Scott, 1849) p. 52.
ማንኛውም የዓለማዊ ክፉ ምኞት አዝማሚያ በእኛ ውስጥ መኖሩን መገንዘባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 56፡11፡፡ ስለ ምን ዓይነት ኃጢአት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በኃጢአት መውደቃችንን ተከትሎ ሁሌም ጠገብኩን የማናውቅ፣ የግል ጥቅማችንን ብቻ አሳዳጅ ፍጡራን ሆነናል፡፡ ስለዚህ ጸባያችን ከስስት ውጪ የክርስቶስን ባህሪ ያንጸባርቃል ብሎ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ” (2ቆሮ. 8፡9)፡፡
በምድር ታሪክ ስስት በዓለማችን ላይ ያስከተለውን ጉዳት የሚያውቀው አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስስት አያሌዎችን ለጦርነት አሰልፏል፡፡ ስስት ብዙዎችን ወደ ወንጀል በመምራት በራሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ሰቆቃና ውድመት አስከትሎአል፡፡ ስስት ማንኛውንም የአስተናጋጁን መልካም ስብዕና በዝብዞ ግለሰቡ አብልጦ ስስታም እስኪሆን እንደማይለይ ቫይረስ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ስስት ማንኛውንም ምኞት፣ ሥልጣንም ሆነ ንብረት አጥብቆ የሚሻ ደዌ ነው፡፡ አሁንም በድጋሚ--ያያል፣ ይመኛል ያደርጋል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ማቴ. 26፡14-16፡፡ ከዚህ አሳዛኝ ታሪክ ስለ ስስት ብርቱ ኃይል ምን መማር እንችላለን?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ይሁዳ “‘እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?’ ” (ማቴ. 26፡15) በማለት የተናገረውን ልብ ይሏል፡፡ ስስት ማንነታችንን እንዲቆጣጠር ስንፈቅድ ምን ሊከተል እንደሚችል ተነጋገሩ፡፡ በምድር ታሪክ በጣም ዕድለኞች ከሚባሉ ጥቂቶች አንዱ የነበረው ይሁዳ ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር ከመጣው የሱስ ጋር አብሮ ኖሮአል፣ ለሠራቸው ተአምራቶች ምስክር ሆኖአል፣ የህይወትን ቃላት ሲሰብክም ሰምቶአል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ስስትና አጉል ምኞት ወዴት እንደመሩት ይመልከቱ፡፡
“አዳኛችን ውሎ አድሮ ክህደት የሚፈጽምበትን ሰው እንዴት አድርጎ ተንከባከበው! የሱስ ስለ ቸርነትና መርኅ ሲያስተምር ስግብግብነትን ክፉኛ አወገዘ፡፡ የሱስ ለይሁዳ የአልጠግብ ባይነትን አስከፊነት አሳየው፡፡ ይሁዳም ይህ ጸባዩ በተደጋጋሚ ተገልጦ መታየቱንና ኃጢአቱም በግልጽ መስተዋሉን ቢገነዘብም፤ ለመናዘዝና ኃጢአቱን ለመተው ግን አልፈለገም ነበር፡፡” —Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 295.
አጥብቆ ካልተጠነቀቀ በቀር በህይወቱ ወይም በጸባዩ ንፉግነት ሊታይበት የማይችል ሰው ማን ነው? ይህን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ በእግዚአብሔር ጸጋ በቁጥጥራችን ስር ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ሰዎች ባለሀብት ቢሆኑ ወይም ቢደኸዩ ስስት፣ አጉል ምኞት፣ አፍቅሮተ ንዋይና አፍቅሮተ ቁስ--በክርስቲያን ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ እናስተውል ዘንድ ጥቅሶቹ ምን ይላሉ?
ሐዋ. 24:24–26_______________________________________________________________________
ገላ. 5:22–25__________________________________________________________________________
2ጴጥ. 1:5–9___________________________________________________________________________
እነዚህ ጥቅሶች እንዴት መኖር እንዳለብን አስመልክቶ በምክረ ሃሳብ የበለጸጉና በመለኮታዊ ትእዛዝ የተሞሉ ናቸው፡፡ ከመሀከላቸው የተለመደውን አላባ ይኸውም ራስን መግዛት ልብ ይበሉ፡፡ ጉዳዩን በተለይ ከስስት፣ ከአጉል ምኞትና ከአፍቅሮተ ቁስ ባህሪ አኳያ ከተመለከትነው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ሀሳባችንን፤ በቀጣይ ድርጊታችንን በመቆጣጠር ራሳችንን መግዛት ከቻልን ብቻ
እየተነጋገርንባቸው ያሉት ነገሮች ከሚያስከትሉት አደጋ መጠበቅ እንችላለን፡፡
ራሳችንን ለጌታ ኃይል ለማስገዛት ባቀረብነው መጠን ብቻ እንዲህ ያለውን ራስ መግዛት መለማመድ እንችላለን፡፡ በተለይ እነዚህን ኃጢአተኛ ባህሪያት ረዘም ላሉ ጊዜያት ከተለማመድንና አብረውን ከኖሩ፤ ማናችንም በራሳችን ልናሸንፋቸው አንችልም፡፡ በእነዚህ ብርቱ ማታለያዎች ላይ ባለድል መሆን የምንሻ እስከ ሆነ ድርስ የመለኮታዊው መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን መሥራት በእርግጠኝነት ያስፈልገናል፡፡ “በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” (1ቆሮ. 10፡13)፡፡
ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡--(2ጴጥ. 1፡5-9)፡፡ ጴጥሮስ እንድንራመድበት የሚያመላክተን መንገድ ምን ይመስላል? የአካሄዱ ቅደም ተከተሎችስ ምንድን ናቸው? በተለይ ከስስትና ከክፉ ምኞት ጋር ከምናደርገው ግብግብ አኳያ እንዴት መጓዝ እንዳለብን መማር የምንችለውስ በምን መልኩ ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ደስተኛ መሆንና እርካታ ማግኘት የሰብዓዊው ዘር የመጨረሻ ግቦች ቢሆኑም፤ ነገር ግን የሕንፃ፣ የመሬትና እንደ ውሃ የሚፈሰው መኪና ባለቤት መሆን የዚህ ግብ ባለቤት አያደርግም፡፡ ምንም እንኳ ሰዎች ይህ እውነት መሆኑን ውስጣቸው ቢያውቅም በሀብት መመሰጡን ግን እንደቀጠሉበት ነው፡፡ ከማየት፣ ከመመኘትና የተመኙትን የራስ ከማድረግ በላይ ምን የቀለለ ነገር አለ? ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች እንደ ማንኛውም ሰው በአፍቅሮተ ቁስ እሴቶች ይፈተናሉ፡፡ ይህም ሆኖ ባለማቋረጥ የሚሰበሰበው ቁስ ደስታ ወይም እርካታ አያስገኝም፡፡ በዚያ ፋንታ ችግሮች ይዞ ከተፍ ይላል፡፡ ብዙ ሀብት በነበረው በዚያ ጎልማሳ ሰው እንደታየው መስማት የተመኘውን ባለመስማቱ ወይም ልቡ የሻተውን ባለማግኘቱ እያዘነ ከየሱስ ፊት ሄደ፡፡ “ቁሳዊ እሴቶች… ዝቅ ካለው የሕይወት እርካታና ደስታ እስከ ጭንቀትና ስጋት፤ ብሎም ከአካላዊ ችግሮች እንደ ራስ ምታት፣ የማንነት ቀውስ፣ ራስን ማምለክና ጸረ-ማኅበረሰባዊነት ድረስ የሰዎችን የደህንነት ስሜት ከማመንመን ጋር የተቆራኘ ዝምድና አላቸው፡፡” —Tim Kasser,
The High Price of Materialism (Cambridge, Mass.: The MIT Press, 2002), p. 22.
አፍቃሪ ቁስ ክርስቲያኖች ከሀብት ዋንጫ በኩራት ቢጎነጩም መንፈሳዊ ህይወታቸው ግን በጥም የተቃጠለ ነው፡፡ ክርስቶስ ከሚሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ፈጽሞ አይጠማም (ዮሐ. 4፡14)፡፡