የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
እርስዎ ስለ ሠሩት እጅግ ከባድ ስራ ያስቡ። ሥራውን በጣም ያከበደው ምን ነበር?
ሰዎች እርስዎ ከሚችሉት በላይ ጠብቀውብዎት ነበር? ሥራውን ለመስራት በቂ
ጊዜ ነበረዎት? ሥራውን አልወደዱትም ነበር? አብረዎት ከሚሠሩ ሰዎች ጋር
አልተግባቡም ነበር? ወይም ምናልባት አይሳካልኝም ብለው አስበው ነበር?
እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ለማዳን ያቀደውን ያስቡ። ይህ ዕቅድ በሰማይና
በምድር ያሉትን ሰዎች ሁሉ አንድ ያደርጋል። ይህ ይቻላል እንዴ? ሰዎች በመሆናችን
ይህንን ማድረግ አንችልም። እግዚአብሔር ግን ይችላል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ
ጥቂት ቀደም ብሎ ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል ከባድ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር:- “እንግዲህ
ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥
ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤
እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡19, 20)።
ኢየሱስ ማንም ይሆናል ብሎ ያላሰበውን ነገር እንዲያደርግ ጳውሎስን ወደ
አህዛብ ላከው። ኢየሱስ ጳውሎስን እንዲህ አለው:- “አይሁዳዊ ያልሆኑትን እውነትን
እንዲያስተውሉ ትረዳቸዋለህ። እነርሱ በጨለማ የሚኖሩ ሰዎችን ይመስላሉ። ስለ
እኔ እውነቱን አስተምራቸው። ያኔ በብርሃን (በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት) እንደሚኖሩ
ሰዎች ይሆናሉ። አሁን ሰይጣን በእነርሱ ላይ ሥልጣን አለው። ከጨለማ (ከኃጢአት)
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ምራቸው። ከዚያም እግዚአብሔር የሰሩትን ኃጢአት
ይቅር ይላቸዋል። በእኔ ስለሚያምኑ፣ እግዚአብሔር የራሱ ህዝብ እንደሆኑ አድርጎ
ይቀበላቸዋል” (ሐዋ. 26:18 ተብራርቶ)።
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሥራ መሥራት ቢኖርባቸው፣ ሥራውን
ወዲያውኑ ሊያቆሙት ይችላሉ። ነገር ግን ኢየሱስ የሰጠንን ተስፋዎች ማስታወስ
አለብን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸዋል፡- “እነሆ እኔ እስከ ዓለም
ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28:20)። ለጳውሎስም ኢየሱስ እንዲህ
አለው፡- “ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር፣ ለአንተም በምታይበት ነገር፣ አገልጋይና ምስክር
ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና” (ሐዋ. 26:16)።
ባጭሩ ኢየሱስ ማንም ሰው ሊሰራው የማይችለውን ሥራ ይሰጠናል። ምክንያቱ
ደግሞ ሥራውን ለማከናወን በእርሱ እንድንደገፍ ስለሚፈልግ ነው። ኢየሱስ ሥራውን
ለመስራት የሚያስፈልገንን ጥንካሬ እና ኃይል ሳያስታጥቀን፣ ሥራውን አይሰጠንም።
“ከእግዚአብሔር ጋር አብረን ስንሠራ፣ ኃይሉን ይሰጠናል። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ
ነው። እግዚአብሔር የሚያዘንን ሁሉ፣ በእርሱ ብርታት ልንፈፅመው እንችላለን። ሁሉም
የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የተስፋ ቃሎች ናቸውና።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የክርስቶስ
ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 333።
ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች መልዕክቱን በጻፈላቸው ጊዜ፣ በምድር ይኖር የነበረ
እያንዳንዱ ሰው መልካሙን የምሥራች ሰምቶ ነበር (ቆላ. 1:23)። በእርግጥ ሁሉም ሰው
አልተቀበለውም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ለተከታዮቹ (ማቴ. 28፡18-20) እና ለጳውሎስ
የሰጣቸውን ትእዛዛት በጥንቃቄ ይመልከቱ። ኢየሱስ ሁሉም ሰው የእሱ ተከታይ ይሆናል
ብሎ ቃል እንዳልገባ እንመለከታለን። በተጨማሪም ኢየሱስ ሁሉም ሰው ክርስቲያን
ይሆናል ብሎ ቃል አልገባም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር
እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው
ይመጣል” (ማቴዎስ 24:14)። የምሥራቹ ቃል “ምስክር” የሚሆነው እንዴት ነው? ይህስ
ሥራ በትክክል እንዴት ይከናወናል?
በዚህ ሩብ ዓመት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን። ጳውሎስ
ለፊልጵስዩስ ሰዎች እና ለቆላስይስ ሰዎች የጻፋቸውን መልእክቶች እናጠናለን። ሁለቱም
መልእክቶች በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱም መልእክቶች ኢየሱስን ያሳዩናል።
በሰማይና በምድር ያሉትን ሰዎች አንድ ማድረግ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው። ያዕቆብ
በሕልሙ ከምድር ወደ ሰማይ የተዘረጋ መሰላልን ተመልክቶ ነበር (ዘፍ. 28፡12፣ ከዮሐ.
1፡51 ጋር ያስተያዩ)። መሰላሉ የኢየሱስ ምሳሌ ነው። የሰው ልጅ የሆነው ኢየሱስ
ከኃጢአት ያድነናል። የእግዚአብሔርም ልጅ ስለሆነ፣ እኛ በኃጢአት ላይ ድል እናደርግ
ዘንድ ረድኤትን እንድናገኝ፣ ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል።
የጳውሎስን መልዕክቶች ስናጠና፣ ኢየሱስ አዳኛችንና ረዳታችን መሆኑን
እንመለከታለን። ጳውሎስ ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ የተናገረውን እናያለን።
ኢየሱስ እኛን ለማዳን ወደዚች ምድር ይመጣ ዘንድ ስለተወው ክብር እንማራለን።
ጳውሎስ በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ፣ እሱ በመሰረተው የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን
የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ሲሞክር እናያለን። ከዚያም በጭራሽ ያልጎበኘውን
የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ለመፍታት ሲጥር እንመለከታለን። ጳውሎስ
በጊዜው በነበረችው ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ግንኙነቶችን ፈጥሮ
ነበር። እነዚህ ግንኙነቶች ደግሞ፣ ምንም እንኳን ጳውሎስ በሮም እስር ቤት ቢሆንም፣
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ረድተውታል። ጳውሎስ የቀረው ጊዜ
አጭር መሆኑን አውቆ ነበር። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር እንድትቀርብ
እና እርስ በርሷም እንድትቀራረብ ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ጳውሎስ
ዛሬ ያለችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ከሰማይ ጋር እንዴት እንደምትዋሃድ
አሳይቶናል። ከዚያም ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን፣ እርሱ በራዕ. 14 ላይ የሰጠንን ሥራ
መሥራት እንችላለን — እርሱም የሦስቱን መላእክት መልእክቶች መስበክ ነው።
ክሊንተን ዌለን የፒ.ኤች.ዲ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሲሆን፣ በጀነራል
ኮንፈረንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር ኢንስቲትዩት ይሰራሉ። ዶ/ር ዌለን የአዲስ ኪዳን
ርዕሰ ጉዳዮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴና የአድቬንቲስት ታሪክ ምሁር ናቸው። ዶ/ር
ዌለን በጀርመን፣ ኒውዚላንድ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፊሊፒንስ ሠርተዋል።
እሳቸውና ባለቤታቸው ጂና ሁለት ልጆች፣ ምራትና ሁለት የልጅ ልጆች አሏቸው።