የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ኢያሱ 24፣ ዘፍ. 12:7፣ ዘዳ. 17:19፣ ዘዳ. 5:6፣ 1 ነገሥት 11:2፣ 4፣ 9፣ 2 ጢሞ. 4፡7፣8።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ
ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት
ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት
ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን
እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያሱ 24፡15)።
የመጽሐፈ ኢያሱ የመጨረሻ ምዕራፍ የተቀመጠው በቃል ኪዳን ማደሻ
ሥነ ሥርዓት አውድ ውስጥ ነው፣ ነገር ግን በዚህኛው የሚመራው
ሸምገል ባለው የእስራኤል መሪ ነበር። ምንም እንኳን ራሱ ቃል ኪዳን
ሳይሆን የቃል ኪዳን ማደስ ሥነ ሥርዓት ዘገባ ቢሆንም፣ ምዕራፉ የጥንት ሩቅ
ምስራቅ ስምምነቶች ገጽታዎች አሉት፡ (1) የስምምነቱ ጀማሪ የሚታወቅበት
መግቢያ፤ (፪) በአለቃው እና በዜጋው መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ
የታሪክ መቅድም፣ (3) የቃል ኪዳኑ ድንጋጌዎች ዜጋው ለአለቃው ሙሉ
ታማኝነትን እንዲያሳይ የሚጠይቀው በአመስጋኝነት በመነሳሳት ነው። (4)
የመታዘዝ በረከቶች እና ቃል ኪዳኑን የማፍረስ እርግማኖች፣ (5) የዜጋው ቃል
ኪዳን ምስክሮች፣ (6) ለወደፊት ንባብ ሰነዱ ማስቀመጥ፣ እና (7) ቃል ኪዳኑን
ማጽደቅ በመያዛቸው ይመሳሰላሉ።
ኢያሱ ወደ ህይወቱ መጨረሻ ተቃርቧል፤ በቦታው ስለሚተካው ሰው
ምንም አልተባለም። የቃል ኪዳኑ መታደስ ለእስራኤል ንጉሣቸው ያህዌ እንደሆነ
እና ለእርሱ ታማኝ ሆነው ከቆዩ፣ ጥበቃውን እንደሚያገኙ ማሳሰቢያ ነው።
እስራኤል የሰው ንጉሥ አያስፈልጋትም። በእግዚአብሔር ብቻ እንደሚመራ
ሕዝብ፣ ብቸኛው ንጉሣቸው ጌታ መሆኑን ማስታወስ ነበረባቸው።
ለታህሳስ 17 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
“ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም
ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ።
እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ።” (ኢያሱ 24:1)
ሴኬም አብርሃም በመጀመሪያ ወደ ምድሪቱ በደረሰ ጊዜ መሠዊያ
የሠራበት እና እግዚአብሔር በመጀመሪያ የምድሪቱን ተስፋ የሰጠበት (ዘፍ.
12፡7) ነው። እንግዲህ፣ ለአብርሃም የተሰጡት ተስፋዎች ሲፈጸሙ፣ እስራኤል
የመጀመሪያው የተስፋ ቃል በተሰጠበት ስፍራ ከእግዚአብሔር ጋር ያላትን
ቃል ኪዳን እያደሰች ነው። የኢያሱ ጥሪ የያዕቆብን ቃል ያስታውሳል “አሁን
እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ” (ኢያሱ 24፡
23፣ ከዘፍ. 35፡2-4 ጋር ያነፃፅሩ)። ቃል ኪዳኑ የተገባበት መልክዓ ምድራዊ
አቀማመጥ በራሱ እና ሌሎችን “አማልክት” በመቃወም ለጌታ ያለንን ታማኝነት
ለማሳየት ጥሪውን ያስተላልፋል።
ኢያሱ 24:2-13ን ያንብቡ። አምላክ ለእስራኤላውያን የላከው መልእክት ዋና
ዓላማ ምንድን ነው?
እየታወሰ ባለው ያለፈ ጊዜ እግዚአብሔር ዋና ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡
“ወስጃለሁ፣” “ሰጠሁ”፣ “ልኬ ነበር”፣ “በመቅሰፍት መታሁ” “አደረግሁ”
“አወጣሁህ” “አዳንኩህ” ወዘተ ...። እስራኤል የትረካው ዋና ተዋናይ
ሳይሆን ዋናው ተጠቃሚ ነው። እስራኤልን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው።
እግዚአብሔር በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ እነዚያን
ጣዖታት እያገለገሉ ይቀጥሉ ነበር። የእስራኤል እንደ ሀገር መኖር በቅድመ
አያቶቿ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቸኛ ስራ የተደረገ ነው። እስራኤላውያን
በምድሪቱ ላይ መገኘታቸው ለመኩራራት ሳይሆን አምላክን ለማገልገል
ምክንያት ሊሆናቸው ይገባል።
የጌታ ንግግር በ “እናንተ” እና “እነሱ” (አባቶች) መካከል አምስት
ጊዜ የሚከሰተውን የግስ ለውጥ ይዟል። በሴኬም ያለው ይህ ትውልድ እና
አባቶች እንደ አንድ ተቆጥረዋል። ኢያሱ በዘዳግም 5፡3 ላይ ሙሴ የተናገረውን
ማለትም እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያደረገው ከአባቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ኢያሱ
በተናገረበት ወቅት ከተገኙት ሁሉ ጋር መሆኑን እያረጋገጠ ነበር። በንግግሩ
ሰዓት የነበሩት አብዛኞቹ ከግብጽ ሲወጡ አልነበሩም። “አብዛኞቹ” በኮሬብ
አልነበሩም። ሆኖም ኢያሱ ሁሉም በዚያ እንደነበሩ ተናግሯል። ባጭሩ፣
ያለፉት ትምህርቶች በእያንዳንዱ አዲስ ትውልድ መስተካከል አለባቸው።
ጥንት ለቀደሙት አባቶች የሰራ አምላክ የአሁኑን ትውልድ ወክሎ ለመስራት
ዝግጁ ነው።
እንደ ቤተ ክርስቲያን የተሻለ የጋራ ኃላፊነት ስሜት እንዲኖረን ማድረግ
የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ማለትም፣ የምናደርገው ነገር
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ ይነካዋል የሚለውን ሐሳብ መረዳት
የምንችለው እንዴት ነው?
ኢያሱ እስራኤላውያን ምን እንዲያደርጉ እየጠየቃቸው ነው? (ኢያሱ. 24:14፣15) በቅንነትና በእውነት ጌታን ማገልገል ማለት ምን ማለት ነው?
የኢያሱ ጥሪ እስራኤላውያን ለፈጣሪያቸው ታማኝ በመሆን
ልዩነታቸውን ጠብቀው በምድሪቱ ላይ መኖርን ወይም ማንነታችውን፣
አላማቸውን እና ተልዕኳቸውን በመተው ከብዙ ጣዖት አምላኪዎች መካከል
አንዱ ለመሆን መወሰን እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያል። ምርጫው የነሱ ነው።
የኢያሱ ጥሪ ሁለት ገጽ ያለው ነው፤ እስራኤል እግዚአብሔርን
በመፍራት “በቅንነትና በእውነት” ማገልገል አለበት። እግዚአብሔርን መፍራት
ማለት ዘላለማዊ መንቀጥቀጥ እና ስሜታዊ ያለመተማመን ሕይወት መኖር
ማለት አይደለም። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ቅድስና እና ወሰን
የሌለውን ማንነት በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የእኛን ትንሽነት፣
ኃጢአተኝነት እና ውሱንነት ከማወቅ የመነጨ ክብር እና ፍርሃትን ያመለክታል።
እግዚአብሔርን መፍራት ሁልጊዜ እርሱ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማወቅ፣ እሱ
የሰማይ አባታችን ብቻ ሳይሆን መለኮታዊ ንጉሳችንም መሆኑን ማወቅ ነው።
እንዲህ ያለው ግንዛቤ ለእግዚአብሔር የመታዘዝ ሕይወትን ያመጣል (ዘሌ.
19፡14፣ ዘሌ. 25፡17፣ ዘዳ. 17፡19፣ 2 ነገ. 17፡34)። “ፍርሃት” አንድ እስራኤላዊ
ሊኖረው የሚገባን ማንነት የሚገልጸው ውስጣዊ ዝንባሌ ቢሆንም አምላክን
ማክበር የሚያስገኘው ተግባራዊ ውጤት ግን እርሱን ማገልገል ነው።
ከእስራኤል የሚጠበቀው አገልግሎት በሁለት የዕብራይስጥ ቃላት
ተገልጧል፡ “በቅንነት” እና “በእውነት”። የመጀመሪያው ቃል (ታሚም)
በአብዛኛው የመሥዋዕቱን እንስሳ ፍጹምነት ለመግለጽ እንደ ቅጽል ያገለግላል።
የእስራኤልን አገልግሎት የሚገልጸው ሁለተኛው ቃል “እውነት” ወይም
“ታማኝነት” ነው (ዕብራይስጥ እመት)። ቃሉ በአጠቃላይ ቋሚነት እና
መረጋጋትን ያመለክታል። ቃሉ ዘወትር የሚያመለክተው በእስራኤል ላይ
በተገለጸው በታማኝ ባህሪው ተለይቶ የሚታወቀውን እግዚአብሔርን ነው።
ታማኝ ሰው የሚታመን እና እምነት የሚጣልበት ዓይነት ሰው ነው።
በመሠረቱ፣ ኢያሱ እስራኤል በታሪካቸው እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያሳየውን
ተመሳሳይ ታማኝነት እንዲያሳዩ እየጠየቀ ነው። እሱ የሚፈልገውን ነገር
በውጫዊ መልኩ ማክበር ብቻ ሳይሆን ካልተከፋፈለ ልብ የሚመነጭ ወጥነትን
ነው። ሕይወታቸው እግዚአብሔር ላደረገላቸው ነገር አመስጋኝነታቸውን
የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት። በመሠረቱ፣ እኛም ዛሬ ከኢየሱስ ጋር ባለን
ግንኙነት መኖር ያለብን እንደዚሁ ነው።
“በቅንነት” እና “በእውነት” ጌታን ማገልገል ለእርስዎ ምን ማለት ነው?
ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ እንዳንሰጥ የሚከለክሉን አንዳንድ ትኩረት
የሚከፋፍሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?
እንደ እውነተኛ እና ታማኝ መሪ፣ ኢያሱ የህዝቡን ነፃ ፍቃድ ያከብራል
እና እስራኤል ከግዳጅ ይልቅ በነጻ ምርጫ ጌታን እንዲያገለግሉ ይመኛል።
“የተመረጡት” የሚለው ግስ ሆን ተብሎ ጥቅም ላይ የዋለበት ምክንያት ይህ
ነበር (ኢያሱ 24:22 ይመልከቱ)። በሌሎች ምንባቦች ባካር “መምረጥ” የሚል
ትርጉም ያለውን ኃሳብ የያዘ ሲሆን የእስራኤልን በእግዚአብሔር መመረጥ
ይገልጻል (ዘዳ. 7:6-7፤ ዘዳ. 10:15፤ ዘዳ. 14:2)። እስራኤል በመለኮት ከተመረጡ
በኋላ ለእግዚአብሔር “አይሆንም” የማለት ነፃነት ነበራቸው፣ ነገር ግን ያ ከንቱ
እና ትርጉም አልባ ይሆን ነበር። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር እሺ” ብለው
በሕይወት መቀጠል ይችላሉ፣ ወይም ጀርባቸውን ከእርሱ አዙረው መኖርን
ማቆም ይችላሉ።
እስራኤል ለኢያሱ ጥሪ(ተማፅንዖ) የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? (ኢያሱ. 24:16-
18) ኢያሱ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ እሱም በዚያ መልኩ የመለሰው ለምን
ይመስላችኋል? (ኢያሱ 24:19-21)
እስራኤላውያን በሰጡት አዎንታዊ መልስ የአባቶቻቸውን አምላክ በዚያ
ሰዓት ባልተከፋፈለ ልብ ሊያገለግሉ የሚመርጡት “አምላካቸው” መሆኑን
ተናግረዋል (ኢያሱ 24:17-18)። ከእንዲህ ዓይነቱ የማያጠራጥር የታማኝነት
ማረጋገጫ በኋላ፣ ከኢያሱ የማረጋገጫ እና የማበረታቻ ቃላት እንጠብቃለን።
ሆኖም ይህ አልሆነም። በኢያሱ እና በህዝቡ መካከል በተደረገው ውይይት
ባልተጠበቀ ሁኔታ ኢያሱ ከሕዝቡ በተቃራኒ ቆመ። ቀደም ሲል ስለ አምላክ
የጸጋ ስጦታዎች ከመናገር ወደ እስራኤላውያኑ ዘወር ብሎ እግዚአብሔርን
በቀላሉ ማገልገል እንደማይቻላቸው ማስፈራራት ጀመረ።
በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ቃል የገቡትን (ዘፀ. 19፡
8፣ ዘጸ. 24፡3፣ ዘዳ. 5፡27) ቃላቱ ገና በከንፈራቸው ሳለ (ዘጸ. 32) የገቡትን ቃል
የረሱትን የመጀመሪያውን ትውልድ ቃል አባይነት ኢያሱ ያውቃል። ስለዚህም
ኢያሱ እስራኤላውያን ብዙ ነገሮችን እንዲያውቁ ፈልጓል። በመጀመሪያ፣
አምላክን ለማገልገል መወሰኑ ከባድ ውሳኔ ነው። እንደ እግዚአብሔር መገለጥ
መላውን ሕዝብ መቅረጽ ይኖርበታል። ያንን ግብ መከተል በረከቶችን
እንደሚያስገኝ አለመታዘዝ ደግሞ የሚያስከትለውን መዘዝ ሙሉ በሙሉ
መረዳት ያስፈልጋል። የኃጢአት ይቅርታ የማይገሰስ የሰው ልጅ መብት ሳይሆን
ከእግዚአብሔር ጸጋ የተገኘ ተአምር ነው።
ሁለተኛ፣ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚወስኑት
ውሳኔ የራሳቸው ውሳኔ እንጂ መሪያቸው ኢያሱም እንኳ የጫነባቸው ሊሆን
አይገባም።
ሦስተኛ፣ እስራኤል ሰዎች በራሳቸው ኃይል እግዚአብሔርን ማገልገል
እንደማይችሉ መገንዘብ ነበረባቸው። እግዚአብሔርን ማገልገል የቃል ኪዳኑን
ድንጋጌ በራስ ጉልበት በመጠበቅ የሚገኝ ሳይሆን ከአዳኛችንና ጌታችን ጋር
በሚኖረን የግል ግንኙነት የሚገኝና የሚዳብር ነው (ከዘጸ. 20፡1-2፤ ዘዳ. 5፡6,
7 ጋር ያነፃፅሩ)።
ኢያሱ 24:22-24ን ያንብቡ። ኢያሱ እስራኤላውያን ጣዖቶቻቸውን እንዲያስወግዱ ያቀረበውን ተማፅንዖ በድጋሚ መናገር ያስፈለገው ለምንድን ነበር?
የጣዖት አምልኮ ስጋት በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የነበረ አይደለም። ቀደም
ሲል፣ በሞዓብ ሜዳ ላይ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ሙሴ ተማፅንዖን አቅርቧል
(ዘዳ. 30፡19፣ 20)። በዚህ ሰዓት የሚታዩት አማልክት የግብፅ ወይም ከወንዙ
ማዶ ያሉት ሳይሆኑ “በመካከላቸው” የሚገኙ ነበሩ። ስለዚህም ኢያሱ
ልባቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲያዘነብሉ ሕዝቡን ተማጸነ። እዚህ ጥቅም
ላይ የዋለው የዕብራይስጥ ቃል ናታህ “መለጠጥ” “መታጠፍ” ማለት ነው።
ጎንበስ ብሎ ጸሎትን መስማት የሚጠበቅበትን አምላክ የሚገልፅ (2ኛ ነገ. 19፡
16፣ መዝ. 31፡2-3፣ ዳን. 9፡18) እና በኋላም በነቢያት አማካኝነት ከእስራኤል
የሚጠበቀው አመለካከት እንደሆነ የተነገረ ነው (ኢሳ. 55፡3፣ ኤር. 7፡24)።
ይኸው ቃል ልቡ ወደ ባዕድ አማልክት ባዘነበለ ጊዜ የሰሎሞንን ክህደት
ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል (1 ነገሥት 11፡2፣ 4፣9)። ኃጢአተኛው የሰው
ልብ ጎንበስ ብሎ የእግዚአብሔርን ድምጽ የማዳመጥ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ
የለውም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወደ መፈጸም ለማዘንበል በእኛ በኩል
ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ ይጠይቃል።
እስራኤላውያን የሰጡት መልስ “ቃሉን እንሰማለን” የሚል ነበር። ይህ
አገላለጽ መታዘዝን በውስጡ የያዘ ነው። እስራኤል ሕይወት አልባ ሕጎችን
እንድትከተል አልተጠየቀችም። ቃል ኪዳኑ ከጌታ ጋር ስላለው ህያው ግንኙነት
ነው፣ ይህም በመመሪያዎች ሙሉ በሙሉ ሊገለጽ አይችልም። የእስራኤል
ሃይማኖት ሕግ አጥባቂ እንዲሆን ፈጽሞ አልታሰበም፤ ይልቁንም ከቅዱስ እና
መሐሪ አዳኝ ጋር በእምነት እና በፍቅር የማያቋርጥ ውይይት መሆን ነበረበት።
ኢያሱ ባዕድ አማልክትን ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ ሲያዛቸው
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሦስት ጊዜ ቃል ከገቡ በኋላም ቢሆን
በእርግጥ እንደተፈጸመ የሚገልጽ ምንም መረጃ የለም። በጠቅላላው መጽሐፉ
ውስጥ የመታዘዝ ምሳሌዎች እንዲሆኑ በማሰብ የኢያሱ ትእዛዛት (ወይም
የሙሴ) መፈፀማቸውን ሪፖርት ማድረግ የተለመደ ነው። አሁን በመጽሐፉ
መጨረሻ ላይ ይህ አለመገኘቱ የኢያሱ ተማፅንዖ ተግባር ላይ መዋሉ ላይ
እርግጠኛ እንዳንሆን ያደርገናል። ጌታን እንድናመልክና እንድናገለግለው
የሚጠራው የመጽሐፉ ዋና ተማፅንዖ ለኢያሱ ዘመን ትውልድ ብቻ ሳይሆን
ይህን መልእክት ለሚያነብ ወይም ለሚሰማ ለእያንዳንዱ አዲስ የእግዚአብሔር
ሕዝብ ትውልድ ጭምር ነው።
ለጌታ አንድ ነገር ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ ቃል ገብተው ሳያደርጉ ቀርተዋል?
ያላደረጉበት ምክንያት ምንድነው? መልስዎ ስለ ፀጋ ምን ይነግርዎታል?
በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፈ ኢያሱን መደምደሚያ ያንብቡ (ኢያሱ 24፡29-33)። እነዚህ ቃላት የኢያሱን ሕይወት ወደ ኋላ የሚመለከቱ ብቻ ሳይሆኑ የወደፊቱን ጊዜ የሚጠባበቁ የሆኑት እንዴት ነው?
መጽሐፈ ኢያሱ ስለ ሊቀ ካህኑ አልዓዛር እና ስለ ኢያሱ ሞት በሚናገረው
ዘገባ በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ፍጻሜው ይመጣል። ፀሐፊው የኢያሱን ቀብር፣
የአልዓዛርን ቀብር እና የዮሴፍን አጥንት መቀበር በአንድ ላይ በመዘርዘር፣
ከምድሪቱ ውጭ የነበረውን ህይወት እና በምድሪቱ እየጀመረ ያለውን ህይወት
ያነፃፅራል። ከእንግዲህ መንከራተት አያስፈልግም። የመሪዎቹ ምድራዊ ቅሪቶች
ከህዝቡ ጋር መዞራቸው ቀረ። አባቶች ዘመዶቻቸውን በሴኬም በተገዛው መሬት
(ዘፍ. 33:19) በዋሻ ውስጥ ይቀብሩ ነበር (ዘፍ. 23:13፣ 19፤ ዘፍ. 25:9-10)።
አሁን ህዝቡ በምድሪቱ መኖር ስለጀመሩ መሪዎቻቸውን በእራሳቸው ርስት
ክልል ውስጥ ይቀብራሉ። ለአባቶች የተሰጡት የተስፋ ቃላት ተፈጽመዋል።
የእግዚአብሔር ታማኝነት የአሁኑን እና የወደፊቱን የእስራኤል ትውልድ
የሚያገናኝ ታሪካዊ ክር ነው።
የመጽሐፉ ማጠቃለያ አንቀጾች አጠቃላይ ትረካውን ካለፈው ትልቅ
ታሪክ ጋር በማቆራኘት፣ ለወደፊቱም መንገድ ይከፍታሉ። የካንተርበሪ የቀድሞ
ሊቀ ጳጳስ ሎርድ ጆርጅ ኬሪ በሽሬውስበሪ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተ
ክርስቲያን ባደረጉት ንግግር የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን “ለመጥፋት አንድ
ትውልድ የቀራት” እንደሆነች ተናግረዋል።
እንደውም ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ለመጥፋት አንድ ትውልድ
የቀራት ነች፣ በብሉይ ኪዳን የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎችም እንደዚሁ ነበሩ።
በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ እያበቃ ነበር። የወደፊት ዕጣ ፈንታው
የወደፊቱን ጊዜ ለሚመለከቱት ብዙ ጥያቄዎች በሚሰጡት መልሶች የተመሠረተ
ነው። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ታማኝ ይሆናሉን? መላውን መሬት
ለመውረስ ያላለቀውን ተግባር ማስቀጠል ይችሉ ይሆን? ከእግዚአብሔር
ጋር ተጣብቀው በጣዖት አምልኮ ውስጥ ሳይጠመዱ ይቆዩ ይሆን? በኢያሱ
ስር የነበረው ትውልድ ለጌታ ታማኝ ሆኖ ቆይቷል፣ ነገር ግን ቀጣዩ ትውልድ
ታላላቅ መሪዎቹን በመከተል መንፈሳዊ መመሪያ ይጠብቅ ይሆን? እያንዳንዱ
መጽሐፈ ኢያሱን የሚያነብ ተከታይ የእግዚአብሔር ሕዝብ ትውልድ፣
ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር ሊጋፈጥ ይገባል። ስኬታቸው የተመሠረተው በዕለት
ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ በሚሰጧቸው መልሶች እና ለወረሱት እውነት
በሚሰጡት ምላሽ ላይ ነው።
ኢያሱ እንደ ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድሏል” (2 ጢሞ. 4፡7)። የኢያሱ
ስኬት ቁልፍ ምንድን ነበር? እኛስ በተመሳሳይ የመዳን ዋስትና ለመጨረስ ዛሬ
ምን ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልገናል?
የኃይማኖት አባቶችና ነብያት ከሚለው መጽሐፍ
ላይ “የኢያሱ የመጨረሻ ቃላት” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።
“ከግብፅ ከወጡት ብዙ ሰዎች መካከል ጣዖትን ያመልኩ የነበሩ
ብዙዎች ነበሩ፤ በከነዓን ምድር ከሰፈሩ በኋላም ቢሆን ይህ አልተው ያለ
ልማድ በድብቅ ቀጥሎ ነበር። ኢያሱ በእስራኤላውያን መካከል ስላለው ክፋት
አስተውሎ ነበር፤ እናም የሚያስከትለውን አደጋ በግልጽ ተረድቶ ነበር። እጅግ
ከልቡ በዕብራውያኑ ሠራዊት መካከል እውነተኛ ተሃድሶ ይናፍቅ ነበር። ህዝቡ
በሙሉ ልባቸው ጌታን ለማገልገል ወስነው አቋም ካልወሰዱ፣ ቀስ በቀስ ከሱ
እየራቁ ራሳቸውን መለየታቸውን እንደሚቀጥሉ ያውቃል። . . . ከዕብራውያኑ
መካከል የተወሰኑት እውነተኛ መንፈሳዊ አምላኪዎች ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ
ቅንዓት የሌላቸው ወይም ቅንነት አገልግሎታቸውን የማይገልፅ ግብዞች ነበሩ።
አንዳንዶች ልባቸው ጣዖት አምላኪዎች ሆነው የራሳቸውን ስህተት አምነው
መቀበል የሚያፍሩ ነበሩ።”—Ellen G. White, Signs of the Times, May
19, 1881.
“ይህ የተቀደሰ ቃል ኪዳን ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ በሕግ መጽሐፍ
ተጽፎአል። ኢያሱም በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ካለችው ከአድባር ዛፍ
በታች ትልቅ ድንጋይ አቆመ። ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፦ እነሆ፥ ይህ ድንጋይ
ለእኛ ምስክር ይሆናል፤ “ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣
እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቶአል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም
በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል”
አላቸው” (ኢያሱ 24፥27)። እዚህ ላይ ኢያሱ ለህዝቡ የሰጠው መመሪያ
እና ማስጠንቀቂያ በራሱ ቃል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በግልፅ
ተናግሯል። ይህ ታላቅ ድንጋይ ለተከታዮቹ ትውልዶች ይመሰክራል፣ ይህም
ለመታሰቢያ ሆኖ ስለ ቃል ኪዳኑ መታደስ ክስተት ይመሰክራል፤ ደግሞም
እንደገና ወደ ጣዖት አምልኮ ከገቡ በሕዝብ ላይ ምስክር ይሆናል።”— Ellen
G. White, Signs of the Times, May 26, 1881
1. “እርሱ [እግዚአብሔር] ቅዱስ አምላክ ነው፤ ቀናተኛ አምላክ ነው” (ኢያሱ
“እርሱ [እግዚአብሔር] ቅዱስ አምላክ ነው፤ ቀናተኛ አምላክ ነው” (ኢያሱ
24:19) የሚለው አገላለጽ ትርጉም ላይ ተወያዩበት። እግዚአብሔር
ቀናተኛ አምላክ የሆነው በምን መልኩ ነው?
2. ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እሱ ከሚሰጠን የመምረጥ ነፃነት ጋር
ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እሱ ከሚሰጠን የመምረጥ ነፃነት ጋር
የተያያዘው እንዴት ነው? ማለትም፣ በእውነት ነፃነት ከሌለን በእውነት
ልንወድ እንችላለን? እውነተኛ ፍቅርን ማስገደድ ይቻል ይሆን? ካልሆነስ
ለምን?
3. ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ችቦውን ለቀጣዩ ትውልድ
ዛሬ
የቤተ
ክርስቲያን
መሪዎች
ችቦውን
ለቀጣዩ
ትውልድ
የሚያስተላልፉባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ምንድን ናቸው?
4. ስለ ኢያሱ ሕይወት እና በሕይወቱ ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን
ስለ ኢያሱ ሕይወት እና በሕይወቱ ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን
ያገለግሉ እንደነበረ ስለተቀመጠው መደምደሚያ ያሰላስሉ። ሰዎች ስለ
እናንተ ህይወት ምን መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ትፈልጋላችሁ?
ማሳሰቢያ
ድርጅቱ