የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


መስከረም 12 - 18

14ኛ ትምህርት

Sep 23 - 29




የኤፌሶን ሰዎች በልብ ውስጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ኤፌሶን 1-ኤፌሶን 6።


የመታሰቢያ ጥቅስ:- “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስ ቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።” (ኤፌ. 2:8-10)።

ሎንደንን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኚዎች ወደ ሎንዶን ዓይን፣ ተሸከርካሪ ጎማ የሚመስል መስህብ፣ ወጥተው ይሳፈራሉ። ቴምስ ከሚባለው ወንዝ 450 ጫማ ከፍታ ላይ ሁሉንም ነገር ማየት ትችላላችሁ፡- ትልቁን ቤን፣ የፓርላማውን ቤት፣ እና በርካታ ታሪካዊ ቤተ መንግሥቶችና ደብሮችን (ካቴድራሎችን) ማየት ይቻላል።

ኒኮላስ ቶማስ “ቶም” ራይት ለተባለው የአዲስ ኪዳን ምሁር ሲጽፍ “ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ ከሌሎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ጋር በተገናኘ ሁኔታ የሎንዶን ዓይን ተብሎ እንደሚጠራው ሀውልት ሆኖ ይታያል። ይህ ጽሁፍ ከጽሁፎቹ ሁሉ የበለጠ ረዥም ወይም የተሟለ አይደለም፣ ነገር ግን እጅግ ውብ (አስደሳች) የሆነ የመሬትን አጠቃላይ አቀማመጥ እይታ ይሰጣል። ከዚህ ቦታ ሆኖ ጎማው ሲሽከረከር ስለ ጭብጥ መልእክቶቹ በተከታታይ ጥሩ እይታ ማግኘት ትችላላችሁ” ብሏል።-Paul for Everyone: The Prison Let- ters (London: S.P.C.K. [Society for Promoting Christian Knowledge Publishing], 2004), p. 3.

በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የጳውሎስ ትኩረት አከባቢያዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አልነበረም። ደብዳቤው የሚነበበው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው በሁሉም ቦታ ላሉ አማኞችና በየትኛውም ቦታ ላሉ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያናት እንደሆነ ሆኖ ነው። የደብዳቤው ዘመን ተሻጋሪነት ጳውሎስ የራሳችንን ዓለምና ሀሳብ ጥሶ ለመግባት የሚሰጠውን “አስደሳች እይታ” ይፈቅዳል። እያንዳንዱን ምዕራፍ በምንከልስበት ጊዜ ይህንን ጥያቄ በአእምሮአችን እንያዝ፡- እንደ አማኝ ሕይወታችንን መልክ ማስያዛቸውን መቀጠል ያለባቸው በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የተቀመጡ ምን ወሳኝ እውነቶች አሉ? *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 19 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

መስከረም 13
Sep 24

በክርስቶስ ተባርከናል


አንዳንዶች የኤፌሶንን መጽሐፍ እንደ የአዲስ ኪዳን ተራራ አድርገው ገልጸውታል። ተራራውን እንድንወጣ የሚመራን ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ላይ በፍጥነት ይዞን ይወጣል። ተራራው ጫፍ ላይ ሆነን የምናየው ነገር ወዲያውኑ ትንፋሻችንን የሚያቋርጥና የሚያስደንቅ ነው።

ኤፌሶን ምዕራፍ አንድ ላይ ያሰላስሉ። በተለየ ሁኔታ መገለጥ የሰጠዎ ምን አለ? ምን የከፍታ ጫፎችን ነው የሚመለከቱት?



ጳውሎስ በሰፊው የድነት እቅድ የመሬት አቀማመጥ ላይ ከተባረከው ቦታችን ጋር እያስተዋወቀን ሳለ ኤፌሶን 1:3-14 በአድማስ ላይ ያሉ ከፍተኛ ቦታዎችን መለየት እንድንችል በተራራው ጫፍ ላይ እንዳለ ካርታ ያገለግላል። ትዕይንቱ (ዕይታው) በክርስቶስ ሆኖ ባደረጋቸው የእግዚአብሔር በፀጋ የተሞሉ ተግባሮች አማካይነት ካለፈው ዘላለም አንስቶ እስከ መጪው ዘላለም ያለውን የድነት ታሪክ ሙሉ ጊዜ ይሸፍናል። እግዚአብሔር አማኞችን መቤዠቱ “ዓለም ከመፈጠሩ በፊት” (ኤፌ. 1:4) ተነሳሽነቱን የወሰደው መለኮት እንደሆነ እና አሁን በእኛ ሕይወት እየተፈጸመ ያለ እንደሆነ (ኤፌ. 1፡7፣ 8፣ 13፣ 14) የሚያሳይ ነው። እነዚህ ከፍጥረት በፊት የተነደፉ ስልቶች በዘመን መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ይሆናሉ (ኤፌ. 1፡9፣ 10)። ከዚያ በኋላ “በሰማይ” እና “በምድር” ያሉ “ነገሮች ሁሉ” ይሰበሰባሉ ወይም በክርስቶስ አንድ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር “ለዘመን ፍጻሜ” ያለው ዕቅድ ተፈጻሚ ይሆናል(ኤፌ. 1:10)። ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔርን ምስጢራዊ ዕቅድ በሙላት እንለማመዳለን (ኤፌ. 1:9)። በአሁኑ ሰዓት እኛ ቆመንበት ያለው ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ድነት እግዚአብሔር “ነገሮችን ሁሉ” ለመቤዠት ያለው ሰፊ ዕቅድ ወሳኝ አካል እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በተራራ ጫፍ ላይ መሆን ምሥጋና የማቅረብን መንፈስ ይፈጥራል። ጳውሎስ በኤፌሶን 1፡15-19 ላይ አማኞች እግዚአብሔር ያቀደላቸውን ድነት እንዲለማመዱ እየጸለየ ሳለ ለእግዚአብሔር ምሥጋና ያቀርባል። በዘመናት ሁሉ ሰዎች ሊያስቡአቸው የሚችሉአቸውን ኃይላት ሁሉ ወደሚገዛው (ኤፌ. 1፡20-23)፣ ከሙታን ወደተነሣው፣ ወደ ሰማይ ወዳረገውና ከፍ ከፍ ወዳለው ክርስቶስ ወደ ላይ እያመላከተን ሳለ ራሳችንን የምናገኘው ሌላ ቀጥ ያለ ተራራ እየወጣን ነው።

በክርስቶስ ኢየሱስ በተገለጸው የእግዚአብሔር ፀጋ ዛሬ በተራራው ጫፍ ላይ መኖር እንችላለን! ኤፌ. 1:4 “ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” ይለናል። ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ። ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በእርሱ ተመረጥን! እርስዎ እንዲድኑ እግዚአብሔር ያለውን ፍላጎት በተመለከተ ይህ ምን ታላቅ ተስፋ ሊሰጥዎ ይገባል?

መስከረም 14
Sep 25

የዳንነው እርስ በርሳችን እየተጠቃቀምን እንድንኖር ነው


ኤፌሶን ምዕራፍ 2ን እያነበቡ ሳለ የሚከተለውን ጥያቄ ለመመለስ ይሞክሩ፡- እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ምን አደረገልን?



“ነገር ግን እግዚአብሔር. . . ።” እነዚህ ቃላት ሰብአዊ ዘር ካወቃቸው ቃላት ሁሉ በተስፋ የተሞሉ ቃላት ናቸው። በኤፌ. 2፡1-10 ላይ ጳውሎስ አድማጮቹ ባለፈው ጊዜ የነበሩበትን አሰቃቂ ሁኔታ ይገልጻል። ሰብአዊ ዘር በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ወደማመጽ ያዘነበሉ የመሆናቸውን እና ሕይወታቸው በኃጢአትና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የመሆኑን አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋራል (ኤፌ. 2፡1-3)። “ነገር ግን በምህረቱ ባለፀጋ የሆነ አምላክ. . . ።” እግዚአብሔር ለእነርሱና ለእኛ ያደረገው ነገር ምንድር ነው? 1. በክርስቶስ ህያዋን አደረገን--የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ነው። 2. ከክርስቶስ ጋር አስነሣን--የክርስቶስ እርገት የእኛ እርገት ነው። 3. በሰማይ ከክርስቶስ ጋር አስቀመጠን-የክርስቶስ መንገስ የእኛም መንገስ ነው (ኤፌ. 2:4-7)። ዓላማትን የሚለውጡ የክርስቶስ ሕይወት ክስተቶችን በተመለከተ ዝም ብለን ቆመን ተመልካቾች አይደለንም! ክርስቶስ እነዚህን አስደናቂ እርምጃዎች የሚወስደው ከእኛ መልካም ሥራ ሳይሆን ከጸጋው የተነሣ ሲሆን (ኤፌ. 2:8, 9) የእርሱ ዕቅድ አማኞች ከኢየሱስ ጋር በሕብረት በመቆም “መልከም ሥራዎችን” እንዲለማመዱ ነው(ኤፌ. 2:10)።

ኤፌሶን 2:1-10 ከክርስቶስ ጋር በሕብረት እንደምንኖር ካስተማረን በኋላ ኤፌሶን 2:11-22 ደግሞ እንደ እርሱ ቤተ ክርስቲያን አካል ከሌሎች ጋር በሕብረት እንደምንኖር ያስተምረናል። የኢየሱስ ሞት አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጽናት (ኤፌ. 2:1-10) ወደ ላይ የሚያመለክቱ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በማጽናት (ኤፌ. 2:11- 22) የአግድሞሽ ጥቅምም አለው። በመስቀሉ አማካይነት አይሁድንና አህዛብን ይለይ የነበረውን ግድግዳ እና ክፍተቱን ያሰፋ የነበረውን የተሳሳተ የሕግ አጠቃቀምን አፈረሰ (ኤፌ. 2:11-18)። ኢየሱስ ደግሞ የሆነ አስደናቂ ነገር፣ ከአማኞች የተሰራ አዲስ ቤተ መቅደስ ገነባ። ከዚህ በፊት በቤተ መቅደሱ ቅዱስ ቦታዎች ውስጥ ይካሄድ ከነበረው አምልኮ ተገልለው የነበሩ አህዛብ ከአይሁድ ጋር አንድ በመሆን አምልኮውን ተቀላቀሉ። እኛም የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አካል፣ “የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተ መቅደስ” እንሆናለን(ኤፌ. 2:19-22)።

ዛሬ በእግዚአብሔር ጸጋ ከኢየሱስና ከመሰል አማኞች ጋር አንድነት ፈጥራችሁ የመኖር ዕድል አላችሁ። ኤፌሶን 2:8-10 በብዙዎች መለወጥ ላይ ሚና ተጫውቷል። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ማርቲን ሉተር ልቡን ያሸነፈውን ጸጋ ያገኘ ሲሆን ለተሃድሶ ማዕከላዊ የሆኑ ማረጋገጫዎችንም አግኝቶበታል። ያውም ድነት የሚገኘው በእምነት ብቻ፣ በክርስቶስ ብቻ፣ እና ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ እንደሆነ ነበር። ጆን ዊስሊ በሎንደን አልደርስጌት ጎዳና ከተለወጠ ከአሥራ ስምንት ቀናት በኋላ፣ በ1738 ዓ.ም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ “ከልቡ የሆነውን ጩኸት” እና “የአዲስ እንቅስቃሴ መግለጫ (መመሪያ)” ሰበከ። የስብከቱ ጥቅስ ምን ነበር? ኤፌሶን 2:8። (See A. Skevington Wood, “Strangely Warmed: The Wes- leys and the Evangelical Awakening,” Chris- tian History [magazine], vol. 5, no. 1 [1984]).

መስከረም 15
Sep 26



እኛ የህያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነን


የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አካል መሆን ወሳኝና አስደሳች የሚሆነው ለምንድር ነው? ኤፌሶን ምዕራፍ 3።



የቤተ ክርስቲያን አባላት ስለ ቤተ ክርስቲያን አዎንታዊ ነገር ሲናገሩ ስንሰማ ተደፋፍረናል። ነገር ግን በመካከላችን ካሉት አባላት መካከል ከፍተኛ ግለት ያላቸው እንኳን ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ላይ ከገለጸው ከጳውሎስ በደስታ ከተሞላ ምስክርነት ያንሳሉ። ጳውሎስ በኤፌሶን ላሉ አማኞች ያደረገውን ፀሎት ዘገባ በማቅረብ ይጀምራል (ኤፌ. 3:1 ከኤፌ.. 1:15-23 ጋር ያነጻጽሩ)፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ስለመፍጠሩ ለመነጋገር ሀሳቡን ያቋርጥና (ኤፌ. 3:2-13) ከዚያ በኋላ የጸሎት ዘገባውን ይጨርሳል (ኤፌ. 3:14-21)። በመንገድ ላይ ስለ እግዚአብሔር “ዕቅድ” ወይም “ምስጢር” ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን ወደማወቅ እንመጣለን፡-
♦ እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ስለ ቤተ ክርስቲያን “ምስጢር” ወይም
♦ “ዕቅድ” ነበረው (ኤፌ. 3:3-5፣ 9፣ 11)።
♦ በኢየሱስ ሕይወትና ሞት ለረዥም ጊዜ ተደብቆ የነበረው የድነት ዕቅድ “ተፈጸመ” (ኤፌ. 3:11፤ ከኤፌ. 2:11-22 ጋር ያነጻጽሩ)።
♦ በራዕይ አማካይነት ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን “ምስጢር” እና አህዛብ በእርሱ ውስጥ ሙሉ ተካፋዮች የመሆናቸውን አስደናቂ ጭብጥ ተማረ (ኤፌ. 3:3-6)።
♦ ጳውሎስ እንደ አህዛብ ሰባኪ ይህንን መልካም ዜና፣ “የክርስቶስን የማይመረመር ባለጠግነት በማሰራጨት” ይሳተፋል (ኤፌ. 3:8፣ 9)።
♦ ብዙዎች ወደ ክርስቶስ ሲመለሱ አይሁድንና አህዛብን ያካተተችው ቤተ ክርስቲያን “ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ” “በሰማያዊ ሥፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት” እያሳየች(ኤፌ. 3:10)፣ ሊመጣ ያለውን ጥፋታቸውን አሳውቃለች (ከኤፌ. 6:10-20 ጋር ያነጻጽሩ)። ሁሉን ነገር በክርስቶስ አንድ የማድረግ ዕቅድ (ኤፌ. 1፡10) በሂደት ላይ ሲሆን ጊዜውም አጭር ነው።

ቤተ ክርስቲያንን በዚህ መልክ መረዳቱ ጳውሎስ ለአማኞች እንዲጸልይ አነሳሳው። በኤፌሶን 3፡14-21 ላይ ያለውን ልባዊ ጸሎት ለእርስዎ እንደሚጸልይልዎ አድርገው ለምን አያስቡም? “በእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ እንዲሞሉ” (ኤፌ. 3:19) እና አንድነት በፈጠረችው ቤተ ክርስቲያን አስደናቂና ሊገለጥ ባለው ምስጢር እንዲሳተፉ እንደሚጸልይልዎ ለምን አያስቡም? ጳውሎስ በጻፈው መልእክት ብርሃን ሲታዩ መኖር የሌለባቸው፣ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባሉ አማኞች መካከል ያሉ የመለያ ግድግዳ ዓይነቶች ምንድር ናቸው? እነርሱን ለማስወገድ እርስዎ ምን ማድረግ ይችላሉ?

መስከረም 16
Sep 27

የእምነት አንድነት


በኤፌሶን ምዕራፍ 4 አማኞች አንዳንድ ነገሮችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እና ሌሎች ነገሮችን ስለማድረጋቸው እርግጠኞች እንዲሆኑ ጳውሎስ ይጠይቃቸዋል። እነዚያ ነገሮች ምንድር ናቸው?



ኤፌሶን ምዕራፍ 4 የሚጀምረውና የሚያበቃው እንደ ቤተ ክርስቲያን አባላት ለእርስ በርስ እንድንጠነቀቅ ጥሪ በማድረግ ነው (ኤፌ. 4:1-3፣ 32)። በእነዚህ ግብዣዎች መካከል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ማሳደግ አለብን ለሚለው ሀሳብ ጠንካራ ድጋፍ ይሰጣል። ሰባት “አንዶችን” በመዘርዘር ይጀምራል:- አንድ አካል አለ፣ አንድ መንፈስ፣ አንድ ተስፋ፣ አንድ ጌታ (የሱስ ክርስቶስ)፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት፣ አንድ እግዚአብሔርና አባት (ኤፌ. 4:4-6)። እኛ የታሰርነው በእነዚህ መንፈሳዊ እውነታዎች ነው። በርግጥ አንድ ሆነናል።

አንድነት ሥነ-መለኮታዊ እውነታ ሆኖ ሳለ የእኛን ጠንካራ ሥራ ይሻል። ስለዚህ ሁልጊዜ “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ መትጋት” አለብን(ኤፌ. 4:3 )። እያንዳንዳችን ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ንቁ የሆንን የክርስቶስ አካል “ክፍል” ስንሆን ነው(ኤፌ. 4:7-16)። እያንዳንዱ አባል ተስጥዖ ያለው የአካል ክፍል ስለሆነ ለዚህ አካል ጤንነት አስተዋጽዖ ማድረግ አለበት (ኤፌ. 4:7፣ 16)። ሁሉም በሐዋርያት፣ በነቢያት፣ በወንጌላውያን፣ በቀሳውስትና በመምህራን ሥራ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው (ኤፌ. 4:11፣ 12)። እነዚህ ነገሮች የአካሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ አብረን እንድናድግ በመርዳት እንደ ጅማት የማያያዝ (አንድ የማድረግ) ሥራ ይሰራሉ (ኤፌ. 4:13፣ 15)።

በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ነግሮአቸው ነበር፡- “እንደ ስህተት ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ንፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕጻናት መሆን ወደፊት አይገባንም” (ኤፌ. 4:14)። እነዚህ ቃላት በግልጽ የሚያመለክቱት ነገር ቢኖር ቀደምት ቤተ ክርስቲያን “ከሰዎች ማታለል” የተነሣ ውስጣዊ ተጋድሎ እንደነበረባት ነው።

ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርህሩኆች ሁኑ” (ኤፌ. 4:32) በማለት የመጨረሻውን ተማጽኖ ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ ሳለ አማኞች የቀድሞውን ልበ ደንዳናነት እንዲተው (ኤፌ. 4፡14-24) እና ቁጣንና ክፉ ንግግርን እንዲያስወግዱ፣ በዚህ ፋንታ የሚያንጽና ጸጋን የሚሰጥ ቋንቋ እንዲናገሩ ጠየቃቸው (ኤፌ. 4፡25-31)።

ይህ ስለ አንድነት የሚናገረው ምዕራፍ ነገሮች ሰላማዊ በሆኑ ጊዜ ለማንበብ ቀላል ነው። በሆነ ግጭት ውስጥ በምንገባበት ጊዜ የበለጠ ከባድ ስለሚሆን ማንበቡ በጣም አስፈላጊ ነው።

ዛሬ የክርስቶስ አካልን አንድነት እና እርሱ የሞተለትን አንድነት ለመለማመድ እያስታወሱ ነውን?

በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት አስተዋጽዖ ማድረግ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድር ናቸው? ማድረግ የምንችለውን ነገር ማድረግ የሚጠቅመው ለምንድር ነው?

መስከረም 17
Sep 28

እኛ ፀጋ ተቀባዮችና ሰጪዎች ነን


ኤፌሶን ምዕራፍ 5ን እያነበቡ ሳለ ጳውሎስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ወንጌልን እንዴት መኖር እንዳለብን በሚጠይቀው ሀሳብ ላይ ያሰላስሉ። ለእርስዎ ከምክሮቹ በተለየ ሁኔታ ትርጉም የሚሰጥዎ የትኛው ነው?



ኤፌሶን ምዕራፍ 5ን ከጅምሩ ጀምረው ማንበብ ከጀመሩ በውስጡ ያለውን ወሳኝ ሀሳብ ሙሉ ኃይል ሊያጡ ይችላሉ። ስለዚህ ንባብዎን ጳውሎስ “ለእርስ በርሳችሁ ቸሮች፣ ርኅረኆችና እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ባዮች ሁኑ” ከሚለው ከኤፌሶን 4፡ 32 ይጀምሩ።

እንደ አማኞች እግዚአብሔር ለእኛ ይቅርታና ጸጋ እንደሰጠን እኛም ለሌሎች ተመሳሳይ ባህርይ እንድናሳይ ተጠርተናል። እግዚአብሔርን መቅዳት አለብን! (ማቴ. 5:43-48 ጋር ያነጻጽሩ)።

ጳውሎስ ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅር የመቅዳትን የአኗኗር ዘይቤ ከተለመደው ከአህዛብ አቀራረብ ጋር ያነጻጽረዋል። ሰዎች ሁሉ ሌሎችን በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ እንዳሉ ወንድሞችና እህቶች ከመመልከት ይልቅ ብዙ ጊዜ ለራሳቸው የወሲብ ደስታ ይጠቀሙባቸውና በድርጊታቸው ይኩራራሉ( ኤፌ. 5፡ 3፣4)። የዚህ ዓይነት አቀራረብ እግዚአብሔር እያቀደ ባለው አዲስ ዓለም የወደፊት ሕልውና የለውም (ኤፌ. 5፡5-7)።

ከዚህ ይልቅ አማኞች የአብን ፍቅር እየቀዱ ካለፈው ጨለማ በመመለስ “እንደ ብርሃን ልጆች” መመላለስ አላባቸው (ኤፌ. 5:8-10)።

ጳውሎስ በድጋሚ “በጨለማ” ከሚደረጉ “ከጨላማ ሥራዎች” እንዲመለሱ ያስጠነቅቃቸዋል (ኤፌ. 5:11፤ 12)። ከዚህ በተቃራኒ በክርስቶስ ብርሐን መኖር አለብን (ኤፌ. 5፡ 13፣ 14)። ሕይወታችንን በስካር ከማባከን ይልቅ ስለ ፍቅሩ እግዚአብሔርን እያመሰገንን “ዘመኑን እንዋጃለን” (ኤፌ. 5:15- 21ን ይመልከቱ)።

ጳውሎስ ክርስቲያን ባሎችንና ሚስቶችን ሲመክር የእግዚአብሔርን ፍቅር የመቅዳትን ዋና ሀሳብ ያቀርባል። ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያኑ ያለው ራስን መስዋዕት የማድረግ ፍቅር ለክርስቲያን ባሎች ምሳሌ ሲሆን (ኤፌ፣ 5፡25- 33)፣ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ያላት ታማኝነት ደግሞ ለክርስቲያን ሚስቶች ምሳሌ ይሆናል (ኤፌ. 5፡22-24)። ሰብአዊ የወሲብ ፍላጎትን መረን በለቀቀና ራስ ወዳድ በሆነ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ክርስቲያን ባልና ሚስት ትኩረት የሚሰጡት ለእርስ በርሳቸው ዋጋ በመስጠትና “አንድ ሥጋ” በመሆን ላይ ነው (ኤፌ. 5:28-33)።

“እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ (የምትመስሉ) ሁኑ” (ኤፌ. 5:1)። በእግዚአብሔር ፀጋ ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ይህንን ምክር እንድትተገብሩ ተጠርታችኋል።

“በፍቅር እንድንሄድ” የሚነግረን ኤፌሶን 5፡ 2 ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡1 ላይ “እግዚአብሔርን ምሰሉ” ያለውን ለማስተዋል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

መስከረም 18
Sep 29


ተጨማሪ ሀሳብ


እኛ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ የእግዚአብሔር ሰላም ጠባቂ ሰራዊት መሆናችንን በመረዳት በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ላይ በማሰላሰል እንደመድማለን።

በኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን የሳለው እንደ የክርስቶስ አካል (ኤፌ. 1:22፣ 23፤ ኤፌ. 4:11-16)፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ (ኤፌ. 2:19-22) እና የክርስቶስ ሙሽራ/ሚስት(ኤፌ. 5:21-33) ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን 6፡10-20 ላይ እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት ይገልጽና ኃይለኛ ለሆነ ትጥቅ ጥሪ ያቀርባል። ይህ ንባብ ብዙ ጥቅም የሚሰጥና በስህተት የመረዳት አደጋም ያለበት ነው። የጳውሎስን ቃላት የጦርነት መሣሪያዎችን አንስተን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ጦረኛ እንድንሆን እንደተደረገ ጥሪ አድርገን በስህተት ልናስተውል እንችላን። ነገር ግን ጳውሎስ አጽንዖት ይሰጥ የነበረው በአንድነት ላይ፣ በሚያንጽ ንግግርና በገርነት ላይ ነበር (በተለየ ሁኔታ ኤፌ. 4፡25-5፡2ን ይመልከቱ)።

የእግዚአብሔርን የምሥራች “የሰላም ወንጌል” በማለት ይገልጸዋል (ኤፌ. 6:15)። በዚህ ግልጽ ዘይቤያዊ አነጋገር አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ጦርነትን እንድትገጥም ምክር የተሰጣት በተለምዶአዊ መንገድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከክፉ ጋር በምናደርገው መንፈሳዊ ጦርነት ሰላምን መጠበቅ አለብን። ጳውሎስ ወደ ታላቁ ተጋድሎ የጦር መስክ ይገባና ከእግዚአብሔር የጦር ሰራዊት ጋር እንድንሆን ጥሪ ያደርጋል።

ሊወጉን የተሰለፉ ኃይሎችን በፍጹም መናቅ ስለሌለብን ከፊታችን ስላለው ጠላት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ምዘና ማድረግ አለብን። እየተጋፈጥን ያለነው ዝም ብሎ ተራ ሰብአዊ ጠላቶችን ሳይሆን ክፉ በሆነ የጦር መሪ፣ በሰይጣን የሚመሩ (ኤፌ. 6፡11) “በሰማያዊ ሥፍራ ያሉትን የክፋት መንፈሳዊ ሰራዊት” ነው (ኤፌ. 6:12)። ነገር ግን በጠላቶቻችን ልንስፈራራ (ልንሸበር) አይገባንም። በጦርነቱ ውስጥ እግዚአብሔር አብሮን አለ (ኤፌ. 6:10)፣ ለጦርነቱ አስፈላጊ የሆኑ ምርጥ የጦር መሣሪያዎችን፣ የራሱን የጦር ዕቃ፣ “የእግዚአብሔርን ጦር ዕቃ” ሰጥቶናል(ኤፌ. 6:11፤ ከኢሳ. 59:15-17 ጋር ያነጻጽሩ)። እውነትን፣ ጽድቅን፣ ሰላምን፣ እምነትን፣ ድነትን እና መንፈስን ልናገኝ በምንችልበት ቦታ አድርጎልናል (ኤፌ. 6:13-17)። እግዚአብሔር ከፊታችን እስከሄደ እና ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጣታችን ድረስ እርሱ የሰጠንን የጦር መሣሪያ እስከታጠቅን ድረስ ልንሸነፍ አንችልም። ድል ተረጋግጧል።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ምንም እንኳን በሥራችን ባንድንም ጳውሎስ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ. 2:10) ብሎ ሲጽፍ ምን ማለቱ ነው? ታዲያ የመልካሙ ሥራችን ዓላማ ምንድር ነው?

2. ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይጽፋል:- “እንግዲህ በእኛ እንደሚሰራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው…” (ኤፌ. 3:20)። በእኛ የሚሰራው ኃይል ምንድር ነው? ይህ ኃይል በሕይወታችን መገለጥ ያለበት እንዴት ነው?



የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተከርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎትድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ


የትንቢት መንፈስ(Spirit of Prophecy - SOP )መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡

እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተከርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ከፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ አንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል።

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገለግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ከርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፤ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡

ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕከት መልዕከት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL