የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሰኔ 10 - 16

13ኛ ትምህርት

Jun 17 - 23




በእግዚአብሔር ክብር መብራት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ-:- 1ኛ ተሰ. 5:1–6፤ ዮሐ. 8:32፤ ራዕይ 18:1፤ ራይዕ 4:11፤ ዘጸ. 33:18፣ 19፤ ራዕይ 5:6፣ 12፤ ራዕይ 13:8።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ:- “ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች” (ራዕይ 18:1)።

ይፍጠንም ይዘግይም፣ የመጨረሻዎቹ ክስተቶች ይመጣሉ። በትክክል መቼና እንዴት እንደሚከሰቱ አልተነገረንም። አራተኛውን ትዕዛዝ ከመጠበቅ በተቃራኒ የእሁድን ጥበቃ የሚያስገድድ ሕግ ይወጣል። የራዕይ መጽሐፍ ሊከሰቱ ስላሉ ወሳኝ ጉዳዮች፣ በጉዳዩ ላይ ስለሚሳተፉ ወሳኝ ተዋኒያን እና አስፍተን ስንመለከት መቼና እንዴት እንደሚሆን በትክክል አልነገረንም። ነገር ግን የሚበቃን ያህል ተነግሮናል። ከአራተኛው ትዕዛዝ በተቃራኒ እሁድ እንዲጠበቅ የሚያስገድድ ሕግ ይተላለፋል። ሊከሰቱ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችንና በጉዳዩ ላይ የሚሳተፉ ወሳኝ ተዋኒያንን በሰፊው ስንመለከት ሕዝብ ሁሉ “ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው” (ራዕይ 14:7) ከመስገድ በተቃራኒ “ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ” (ራዕይ 13:8) ለአውሬውና ለምስሉ ሲሰግዱ ምን እንደሚሆን የራዕይ መጽሐፍ ነግሮናል። በሌላ አገላለጽ ጌታ ኢየሱስን ለመከተልና ትዕዛዛቱን ለመታዘዝ የመረጡ ሁሉ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ይቆያል። በሰው መዝገብ ላይ ከመመዝገብ ይልቅ በእግዚአብሔር መዝገብ ላይ ተመዝግቦ መገኘት ምንኛ የተሻለ ነው።

እግዚአብሔር የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያንን ያስነሳው ይህንን መልእክት እንድትሰብከ ነው። ስለዚህ እኛ ራሳችን እውነትን ልክ በኢየሱስ እንዳለ ማመንና ክርስቶስ ለእኛ በመሞቱ ላይና በእርሱ የመዳናችን ማረጋገጫ ላይ ማዕከል ባደረገው የራዕይ ምዕራፍ 14፡ 6 “ዘላለማዊ ወንጌል” መለወጥና አዲስ መሆን አለብን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሰኔ 17 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ሰኔ 11
Jun 18

ለመጨረሻው አስጨናቂ/የህውከት ጊዜ መዘጋጀት


1ኛ ተሰ. 5:1–6ን ያንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰው ታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚሆኑ ነገሮች የሚሰጠን ማስጠንቀቂያ ምንድር ነው?



ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ የነበሩ አማኞችን በክርስቶስ ዳግም ምጻት አውድ እንዲነቁና በመጠን እንዲኖሩ አደፋፈራቸው። ጳውሎስ ያኔ ለነበሩ አማኞች ይህንን ካለ ዛሬ ለእኛ ምን ይለን ይሆን?

የጌታ ቀን እንደ ሌባ ያገኛቸው ዘንድ በጨለማ ውስጥ እንዳልሆኑና “የብርሃን ልጆች” እንደሆኑ ተናግሮ ነበር (1ኛ ተሰ. 5:4፣ 5)። ኢየሱስ “ንቁ” የሚለውን ንግግር የተጠቀመው እውነተኛል ልባዊ ከሆነ ጸሎት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ነበር (ማቴ. 24፡42፤ 26፡40፣ 41)። መንቃት ማለት በመንፈሳዊ ሁኔታ ንቁ ሆኖ መገኘት ማለት ነው። በመጠን መኖር ማለት የምንኖርበት ዘመን ግድ የሚለንና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የምናደርግ መሆን አለብን ማለት ነው።

ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ትላለች፡- “እኛ እውነቱን የምናውቅ ሰዎች በዓለም ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ቶሎ ሊመጣ ስላለውና ከአቅም በላይ ስለሆነ ነገር መዘጋጀት አለብን። ”—Testimonies for the Church, vol. 8, p. 28.

ለዓለም ድንገት ቢሆንም ለእኛ ድንገት መሆን የለበትም። መቼ እንደሚሆን ባናውቅም እየመጣ መሆኑን ማወቅ የሚያስችለንን ያህል ማየት እንችላለን፤ የመዘጋጀት ቀንም አሁን፣ ዛሬ እንደሆነ ማየት እንችላለን። ዳንኤል ምዕራፍ 2ን ይከልሱና በትንቢቱ መሰረት የተነሱና የወደቁ መንግስታትን ቅደም ተከተል ልብ ይበሉ። እግዚአብሔር ያለው ነገር እንደሚፈጸም እንዴት መተማመን እንደምንችል ይህ ምን ሊያስተምረን ይገባል?



ክርስቶስ የመጨረሻውን ዘመን መልእክት የሰጠን እየመጣ ያለውን ነገር አውቀን ለዚያ ነገር መዘጋጀት እንድንችል ነው፡፤ የዳንኤልና ራዕይ ትንቢቶች ከዘመኑ የትንቢት ሥጦታ ጋር ተዋህደው በዚህ ዓለም ላይ እየመጣ ያለው ነገር ምን እንደሆነ መለኮታዊ መረዳት ይሰጡናል። የእግዚአብሔር ትንቢታዊ ቃል የድነት ታሪክን አስቀድሞ የዘረዘረልን ሲሆን ዳንኤል ምዕራፍ 2 በእግዚአብሔር መታመን የምንችልበትን ኃይለኛ የሆነ ምክንያታዊ ማረጋገጫ ይሰጣል። ጳውሎስ ሌሎች እንደሚያንቀላፉ አናንቀላፋ ይላል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? እያንቀላፋን ከሆነ ማንቀላፋታችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እያንቀላፋን ከሆንን ሊያነቃን የሚችለው ምንድር ነው?

ሰኔ 12
Jun 19

እውነትን ማወቅ


ዮሐ. 8:32፤ 7:17፤ 17:17ን ያንብቡ። እውነትን ስለማወቅና እውነት ስለሚገኝበት ቦታ ኢየሱስ የሚሰጣቸው ተስፋዎች ምንድር ናቸው?





እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው የመጨረሻ ተማጽኖ ከባቢሎን ስህተቶች እንዲያመልጡና በቃሉ ውስጥ ባለው ዘላለማዊ እውነት ብርሃን እንዲራመዱ ነው። የሁሉም ነገር ቁልፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጣበቁና የሚያስተምረውን ነገር ከተከተሉ በመጨረሻው አስጨናቂ ጊዜ፣ በተለይም ሰንበትን በተመለከተ አይታለሉም።

የሁለተኛው መልአክ መልእክት ከስህተት ይልቅ እውነትን፣ ከሰዎች ልማድ/ወግ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን፣ ከውሸት አስተምህሮ ስህተቶች ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል አስተምህሮዎች እንድንቀበል ተማጽኖ ያቀርባል።

የመጀመሪያዎቹን ሁለት መላእክት ተከትሎ የሚመጣው የሶስተኛ መልአክ መልእክት ስለ አውሬው ምልክት ያስጠነቅቀናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ አውሬ ፖለቲካዊ ወይንም ኃይማኖታዊ ኃይልን ይወክላል። በራዕይ 13 እና 14 ላይ ከባህር የወጣው አውሬ እንደ ዓለም አቀፋዊ የአምልኮ ሥርዓት የተነሳው ከሮም ነው። በመጨረሻም ይህ የሮም ኃይል ተጽእኖውን ወደ መላው ዓለም በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያንን እና መንግስትን አንድ ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይመራል። ግቡ የኢኮኖሚ ነውጥ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍቶች፣ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ቀውስ እና ዓለም አቀፋዊ ግጭት ባለበት ወቅት የዓለምን አንድነት ማምጣት ነው።

በመጨረሻም በዚህ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ላይ የተባበሩት የአሜሪካ መንግሥታት የመሪነት ቦታ ይወስዳሉ። “ነፍስ አትሞትም በሚለውና እሁድ በቅድስና እንዲጠበቅ በሚያስተምረው በሁለቱ ታላላቅ ስህተቶች አማካይነት ሰይጣን ሕዝብን በማታለያው ሥር ያደርጋል። የመጀመሪያው መናፍስትን ለመጥራት መሰረት ሲጥል የኋለኛው ደግሞ ከሮም ጋር ግንኙነት ይፈጥራል። የተባበሩት የአሜሪካ መንግሥታት ፕሮቴስታንቶች መናፍስትን ከመጥራት ጋር እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ እጆቻቸውን ከባህረ ሰላጤው ባሻገር ለመዘርጋት ግንባር ቀደም ይሆናሉ። ከሮም ኃይል ጋር እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ እጆቻቸውን ከጥልቁ ላይ ይዘረጋሉ። ከዚህ የሶስትዮሽ አንድነት ተጽእኖ የተነሣ ይህ አገር የሰዎችን መብት በመርገጥ ረገድ የሮምን ዱካ ይከተላል።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 588.

እነዚህ መልእክቶች በልባቸው ውስጥ ባለው ሕያው በሆነ የኢየሱስ እምነት አማካይነት ትዕዛዛቱን እንዲጠብቁ ለክርስቶስ ታማኞች ጥሪ በማስተላለፍ ይደመደማሉ። (ራዕይ 14:12)። “እውነት አርነት ያወጣችኋል” የሚሉትን የኢየሱስን ቃላት የሚረዱት እንዴት ነው? ይህ ማለት ምን ማለት ነው? እውነት ነጻ ያወጣዎት እንዴት ነው? በዚህ አውድ “ነጻ” መሆን ማለት ምን ማለት ነው?

ሰኔ 13
Jun 20

ተሃድሶው ይቀጥላል


እግዚአብሔር በፍጻሜ ዘመን ያለውን ሕዝብ ያስነሳው መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛው አስተምህሮአቸው ካደረጉ፣ የድነታቸው ብቸኛው ምንጭ ክርስቶስ ብቻ ከሆነላቸው፣ መንፈስ ቅዱስ የብርታታቸው ብቸኛው ምንጭ ከሆነላቸው እና የጌታችን ዳግም መምጣት የተስፋዎቻቸው ሁሉ መደምደሚያ ከሆነላቸው ባለፉት ዘመናት ከነበሩ ታላላቅ የተሃድሶ አራማጆች ልምድ ጥቅም እንዲያገኙ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበትን ጨምሮ የስህተት ጨለማና ልማድ (ወግ) ለረዥም ጊዜ ሰውሮአቸው የነበሩ እውነቶች ከጌታችን መመለስ ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ ለዓለም ይታወጃሉ።

ተሃድሶውን መፈጸምና በምድር ላይ ያለውን ሥራ መጨረስ እንዲቻል ከክርስቶስ ጋር ለመሳተፍ የሶስቱ መላእክት መልእክት ለዚህ ለመጨረሻው ዘመን እንቅስቃሴ መወለድ ምክንያት ሆኗል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ ታላላቅ ትንቢቶች የእግዚአብሔርን የመጨረሻውን ዘመን መልእክት ለማወጅ ከተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየተነሳ ያለውን መዳረሻን የሚወስን መለኮታዊ እንቅስቃሴ ያሳያል። ራዕይ ምዕራፍ 14 በዘላለም ወንጌል የምስራች ምድርን እየሸፈነች ያለችውን ዓለም አቀፋዊ ቤተ ክርስቲያን ይገልጻል።

በራዕይ ምዕራፍ 14 ላይ የተጠቀሱትን ሶስት መላእክት የራዕይ ምዕራፍ 18ቱ አራተኛው መልአክ ተቀላቅሎአቸዋል። ይህ መልአክ “ምድር ከክብሩ (ከእግዚአብሔር ክብር) የተነሣ እንድትበራ” ለሶስቱ መላእክት አዋጅ ኃይል ይሰጣል (ራዕይ 18፡1)። ምዕራፍ 18 የሚያተኩረው ወደ ሰብአዊ ዘር ታሪክ መደምደሚያ ወደሚመሩ አብይ ክስተቶችና ወደ የመጨረሻው የወንጌል ድል አድራጊነት ነው። ራዕይ 18:1ን ያንብቡ። ዮሐንስ ስለዚህ መልአክ የሚነግረን ሶስት ነገሮች ምንድር ናቸው? (ዕንባቆም 2:14ን ደግሞ ይመልከቱ)።



በቤተ መቅደስ ውስጥ ባለው ዙፋን ላይ ከተቀመጠውና በግርማ ከተሞላው ከእግዚአብሔር ፊት የሚወርደው ይህ መልአክ በምድር ላይ እየመጣ ስላለው ነገር የምድር ኗሪዎችን ለማስጠንቀቅ የመጨረሻውን የምህረት መልእክት እንዲያውጅ ተልኳል።

ጥቅሱ መልአኩ “ታላቅ ስልጣን” እንዳለው ይናገራል። ሥልጣን ለሚለው ቃል የአዲስ ኪዳኑ የግሪክ ቃል ኤግዞውሲያ የሚል ነው። ኢየሱስ ይህን ቃል በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀመው ደቀ መዛሙርቱን ከመላክ ጋር በተጣጣመ መልኩ ነበር። በማቴዎስ 10፡ 1 ላይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በክፉ ኃይላትና ሥልጣናት ላይ “ሥልጣን” ሰጣቸው። በክፉና በመልካም መካከል በሚደረግ ጦርነት አሸናፊዎች እንዲሆኑ መለኮታዊ ኃይል ሰጥቶ ላካቸው። በማቴዎስ 28፡ 18፣ 19 ላይ በድጋሚ ይልካቸዋል፣ ነገር ግን በዚህ ሰዓት ሄደው “ከሕዝብ ሁሉ ደቀ መዛሙርትን እንዲያደርጉ” በምድርና በሰማይ ባለው “ሥልጣን ሁሉ” ላካቸው። በመጨረሻ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት ያሉ ጉዳዮች ወደ ባለ ሥልጣናት የሚደርሱት እንዴት ነው? የማንን ሥልጣን ነው የምንከተለው? የእግዚአብሔርን ወይስ የራሳችንን፣ የአውሬውን ወይስ የሌላ? አሁን እርስዎ እየተከተሉ ያሉት የማንን ሥልጣን ነው?

ሰኔ 14
Jun 21

የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ይሞላል


ራዕይ 4:11፤ 5:12፤ 19:1 እና 21:26ን ያንብቡ። በራዕይ 18፡1 ላይ በተገለጸው መሰረት ምድርን ከሚሞላው ከእግዚአብሔር ክብር ጋር የተገናኙ ቃላቶች ምንድር ናቸው?



በዩኒቨርስ ውስጥ በክፉና በመልካም መካከል እየተካሄደ ያለው ተጋድሎ ስለ እግዚአብሔር ክብር ወይም ዝና ነው። አማጺው ሰይጣን እግዚአብሔርን እንዲመለክ የሚጠይቅ ግን በምላሹ ጥቂት ነገር ብቻ የሚሰጥ ኢ-ፍትሃዊ ነው በማለት ከሶታል። የእግዚአብሔር ሕግ ነጻነታችንን የሚገድብና ደስታችንን ውስን የሚያደርግ ነው በማለት ክፉው ያውጃል።

የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ይህንን አፈታሪክ አክሽፎታል። ፈጣሪያችን እኛን ለማዳን በዚህ ዓለም ወዳለው የእባብ ጉድጓድ ገባ። በመስቀል ላይ ለሰይጣን ክሶች መልስ በመስጠት እግዚአብሔር አፍቃሪና ፍትሃዊ እንደሆነ አሳየ።

የመጨረሻው ዘመን ሕዝቡ በፍቅሩ በመማረክ፣ የእርሱ ክብር ጉዳይ ግድ ብሎአቸው ክብሩን ይገልጣሉ፤ ራስ ወዳድ ለሆነ፣ አምላክ ለሌለው ዓለም የእርሱን አፍቃሪና ራስን መስዋዕት የሚያደርግ ባህርይ ስለሚገልጡ ምድር በእግዚአብሔር ባህርይ ትበራለች። ዘጸ. 33:18፣ 19ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለሙሴ ክብሩን ያሳየው እንዴት ነበር? የእግዚአብሔር ክብር ምንድር ነው?



የእግዚአብሔር ክብር ባህርዩ ነው። እኛ በእግዚአብሔር ፍቅር ስንሞላና ባህርያችን በሚያድነው በእርሱ ፍቅር ሲለወጥ ምድር በእግዚአብሔር ክብር ትሞላለች።

በግል ሕይወታችን የእርሱን ፍቅር ማሳየት የእርሱን ክብርና ባህርይ ለዓለም ያሳያል። በመንፈሳዊ ጨለማ ለተጀቦነው ዓለም ሊታወጅ ያለው ሶስቱ መላእክት የያዙት የመጨረሻው መልእክት “እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” ይላል (ራዕይ 14:7)።

በመልካም ሥራችን፣ ወይም በጽድቃችን ወይም በእኛ መልካምነት ለራሳችን የሚገኝ ክብር የለም። “የክርስቶስ ጽድቅ መልእክት ከምድር አንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ሊያስተጋባ ነው።…ይህ የሶስተኛውን መልአክ መልእክት ወደ ፍጻሜ የሚያመጣ የእግዚአብሔር ክብር ነው። ”—Ellen G. White, Testimo- nies for the Church, vol. 6, p. 19. ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ በማለት ጽፋለች፡ - “በእምነት መጽደቅ ምንድር ነው? የሰውን ክብር በአቧራ ውስጥ በማስቀመጥ ሰው በራሱ ኃይል ለራሱ ማድረግ የማይችለውን ነገር ማድረግ ነው።”—Testi- monies to Ministers and Gospel Workers, p. 456.

እኛ ክብር የለንም፣ ነገር ግን ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

ሰኔ 15
Jun 22

በጉ፣ የታረደው በግ


በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ጠቀሜታ ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምልክቶች አሉ። እነዚህ ምልክቶች በሰማይ የነበረው ዘንዶ (ራዕይ 12፡3፣ 4፣ 7)፣ በሰማይ መካከል ይበሩ የነበሩ መላእክት (ራዕይ 14፡ 6)፣ በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠችው ሴት (ራዕይ 17፡3)፣ ወዘተ ናቸው። እነዚህ በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ናቸው። እነርሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጽፋቸው ዮሐንስን ያነሳሳው መንፈስ ቅዱስ ነው። የዚህን መጽሐፍ ቃል ለሚያነቡና ለሚተገብሩ እውነትን በመግለጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ገልጾአል፡- “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው” (ራዕይ 1:3)።

ነገር ግን በመላው የራዕይ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታይ ምልክት አለ። ይህ ምልክት ምንድር ነው? ምንንስ ይወክላል? ራዕይ 5:6፣ 8፣ 12፤ 7:17፤ 14:1፤ 15:3፤ 19:7፤ 21:22፣ 23፤ እና 22:1፣ 3ን ያንብቡ። የበጉ ምልክት ትርጉም ምንድር ነው? በራዕይ መጽሐፍ ይህን ያህል ብዙ ጊዜ የተገለጸበት ምክንያት ምንድር ነው?



የመጽሐፉ የመክፈቻ ቃላት እንደሚሉት ይህ “የኢየሱስ ክርስቶስ” ራዕይ ነው። በጉ ብቻ ሳይሆን “የታረደው” በግ (ራዕይ 5:6፣ 12፤ ራዕይ 13:8)። ይህ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን የራዕይ መጽሐፍና የሶስቱ መላእክት መልእክት ልብና ነፍስ ነው። በጉ፣ የታረደው በግ፣የተሰቀለው ኢየሱስ፣ የኃጢአታችን መስዋዕት፣ የመልእክታችን የትኩረት ነጥብ እስካልሆነ ድረስ ለጥሪያችን ታማኝ መሆን አንችልም፣ እግዚአብሔር ይህቺ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰራ ያስነሳትን ሥራም መስራት አንችልም።

“አስበንበት (ሆነ ብለን) የታረደውን በግ የአስተምህሮዎቻችንና የተልዕኮአችን ማዕከል፣ የምንሰብከው የእያንዳንዱ ስብከት፣ የምንጽፈው የእያንዳንዱ መጣጥፍ፣ የምንጸልየው የእያንዳንዱ ጸሎት፣ የምንዘምረው የእያንደንዱ መዝሙር፣ የምናካሄደው የእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና የምናደርገው የእያንዳንዱ ነገር ልብ (እምብርት) ማድረግ አለብን። በጉ በመስቀል ላይ ያሳየው ፍቅር ሰዎችን የምንይዝበትን መንገድ በመለወጥ ለዓለም ደግሞ ጥንቃቄ ማድረግ እንድንችል ያንቀሳቅሰን።”—Ángel Manuel Rodriguez, “The Closing of the Cosmic Conflict: Role of the Three Angels’ Mes- sages,” p. 70.

ይህ ማለት አደገኛ በሆኑ አውሬዎች፣ ጦርነት በሚያደርግ ዘንዶ፣ መቅሰፍቶች፣ ስደትና በአውሬው ምልክት መካከል በጉ፣ የታረደው በግ ከፊት ለፊት እና የሁሉም ማዕከል ሆኖ ይቆያል ማለት ነው። እርሱ ብቻና እርሱ ያደረገልን ነገር፣ አሁን እያደረገልን ያለ ነገር እና ሁሉም ነገር ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ፊት የሚያደርግልን ነገር፣ በመጨረሻም የሶስቱ መላእክት መልእክቶች የሚናገሩት ስለ እርሱ ነው። የታረደውን በግ በመልእክታችን ማዕከል (እምብርት) ላይ ማድረግ ሌሎችን ወደ መልእክቱ ለመምራት ብቻ ሳይሆን ለራስዎ መንፈሳዊ ሕይወትም ወሳኝ የሚሆነው ለምንድር ነው?

ሰኔ 16
Jun 23

ተጨማሪ ሀሳብ


“የእግዚአብሔር ባሪያዎች ፊታቸው በርቶ በቅድስና እያበሩ ከሰማይ የመጣውን መልእክት ለማወጅ ከቦታ ቦታ ይጣደፋሉ። በመላው ምድር ላይ በሺሆች በሚቆጠሩ ድምፆች ማስጠንቀቂያው ይሰጣል። ተዓምራቶች ይፈጸማሉ፣ ሕሙማን ይፈወሳሉ፣ አማኞችን ድንቆችና ተዓምራቶች ይከተሉአቸዋል። ሰይጣን በውሸት ተዓምራቶች፣ በሰዎች ፊት ከሰማይ እሳት በማውረድ ጭምር ይሰራል። ራዕይ 13፡13። ከዚህ የተነሣ የምድር ኗሪዎች አቋማቸውን እንዲለዩ ይደረጋሉ።

“መልእክቱ የሚተላለፈው በክርክር ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ ማሳመን ነው። ክርክሮች ቀርበዋል። ዘሮቹ ተዘርተዋል፣ አሁን እነዚህ ዘሮች በቅለው ፍሬ ያፈራሉ። በሚስዮናውያን ሰራተኞች የተሰራጩ የሕትመት ውጤቶች ተጽእኖአቸውን አሳድረዋል፣ ነገር ግን መልእክቱ አእምሮዎቻቸውን የነካቸው ብዙዎች መልእክቱን ሙሉ በሙሉ እንዳይረዱ ወይም ለእውነት እንዳይታዘዙ ተከልክለው ነበር። አሁን የብርሃን ጮራዎች ወደ ሁሉም ቦታ ጥሰው ይገባሉ፣ እውነት ጥርት ብሎ ይታያል፣ ታማኝ የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አስረዋቸው የነበሩ ገመዶችን ከእጆቻቸው ይቆርጣሉ። አሁን የቤተሰብና የቤተ ክርስቲያን ግንኙነቶች ይዘዋቸው የሚያቆዩበት ኃይል አይኖራቸውም። እውነት ከሌሎች ነገሮች ሁሉ የበለጠ ከብሮ ይታያል። እውነትን በመቃወም ሕብረት የፈጠሩ ወኪሎች ቢኖሩም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከጌታ ወገን ለመቆም ይወስናሉ።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 612.


የመወያያ ጥያቄዎች



- 1.ኤለን ጂ ኋይት “የጽድቅ በእምነት መልእክት በእውነት የሶስተኛው መልአክ መልእክት ነው” ብላለች።—Evangelism, p. 190. ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ጽድቅ በእምነት ከሶስቱ መላእክት መልእክት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

2. ራዕይ 14፡12ን በድጋሚ ያንብቡ። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅና በሕጋዊነት መካከል ያለው ልዩነት ምንድር ነው? መታዘዝ ሕጋዊነት የሚሆነው የት ነው? ትዕዛዛቱን የማይጠብቅ ሰው ሕጋዊ ሊሆን የሚችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

3. በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ስላሉት ጨካኝ አራዊትና አስፈሪ ማስጠንቀቂያዎች ስንናገር ለሚተቹን ሰዎች ምን መልስ መስጠት እንችላለን? በመጽሐፉ ውስጥ ተጽፋው ስላሉት ከምንናገረው ግልጽ ከሆነ መልስ ባሻገር ሌላ ምን መልስ መስጠት ይችላሉ?

4. አሁን በዓለም ላይ ስላሉት ክስተቶች በክፍላችሁ ውስጥ ተወያዩ። ወደ መጨረሻዎቹ ክስተቶች ሊመሩ የሚችሉ ምን ነገሮች ሲከሰቱ ተመለከቱ? እየኖርንበት ስላለንበት ዘመን በማወቅ እና ስላልተገለጹልን ነገሮች ፍሬ ቢስ ግምት በመያዝ መካከል ሚዛን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?



የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተከርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎትድርጅቶች የተሠጠ

ማሳሰቢያ


የትንቢት መንፈስ(Spirit of Prophecy - SOP )መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡

እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተከርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ከፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ አንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል።

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገለግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ከርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፤ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡

ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕከት መልዕከት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL