የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ሉቃስ 12:16–21፤ መክብብ 2:18–22፤ ምሳሌ 27:23–27፤ 2ኛ ቆሮ. 4:18፤ መክብብ 5:10፤ ቆላ. 1:15–17።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ” (ራዕይ14:13)።
ገ
ቢ ወደምናገኝባቸው አመታት መጨረሻ ስንቃረብ የሕይወት መጨረሻን
ማሰብ ስለምንጀምር ስለ ገንዘብ ያለን ትኩረት ያሉንን ሀብቶች ወደ
መጠበቅ ይመለሳል። ከሥራ ወደ ጡረታ የመተላለፊያ ጊዜ እጅግ አስጨናቂ
ልምምድ ነው። ገንዘባችንን በተመለከተ ወደ ፊት ለመቀጠል ከሁሉ የተሻለው
መንገድ ምንድር ነው?
ሰዎች በተፈጥሮ እያረጁ ሲሄዱ ስለ ወደፊቱ መጨነቅ ይጀምራሉ።
እጅግ የተለመዱ ፍርሃቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡- ቶሎ የመሞት ፍርሃት
(ለቤተሰብ የሚያስፈልጉ ነገሮች ከመደረጋቸው በፊት)፤ ከሚፈለገው በላይ ረዥም
ዕድሜ የመኖር ፍርሃት (ንብረታቸው ወይም የቆጠቡት ገንዘብ ሊያኖራቸው
ከሚችለው ዕድሜ በላይ)፤ አደገኛ ህመም (ንብረቴ በሙሉ በአንዴ ሊያልቅ ነው
የሚል ፍርሃት)፤ እና አእምሮአዊ እና/ወይም አካላዊ ድካም (ማን ይጠነቀቅልኛል?
የሚል ፍርሃት)።
በእነዚህ ፍርሃቶች ላይ አስተያየት ስትሰጥ ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ
በማለት ጽፋለች፡- “የእነዚህ ፍርሃቶች ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ነው።…እግዚአብሔር
እንዲይዙ የሚፈልግባቸውን ቦታ ቢይዙ ኖሮ የዕድሜያቸው የመጨረሻዎቹ ቀናት
ከሁሉ የተሻሉና በደስታ የተሞሉ ይሆኑ ነበር።…እስከሚቻላቸው ድረስ ስጋትንና
ሸክሞችን ወደ ጎን በመተው ጊዜያቸውን በደስታ መሙላትና ለሰማይ መብሰል
አለባቸው።”—Testimonies for the Church, vol. 1, p. 424.
በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር ስለ ዕድሜያችን የመጨረሻ ቀናት
የሰጠንን ምክር እንከልሳለን። ማድረግ ያለብንና ማድረግ የሌለብን
ነገሮች ምንድር ናቸው? መከተል ያለብን መርሆዎችስ ምንድር ናቸው?
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመጋቢት 2 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ሉቃስ 12:16–21ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ለእኛ የሚሆን ምን መልእክት አለ? ጌታ ለሞኙ ሰው ምን ዓይነት ጠንካራ ተግሳጽ ነበር የሰጠው? ለንብረታችን ስላለን አመለካከት ይህ ለእኛ ምን ይነግረናል?
መልእክቱ ከዚህ በላይ ሰፊ ቢሆንም በጡረታ ጊዜ ማድረግ ስለሌለብን ነገር ኢየሱስ
የነገረው ታሪክ ይህ ነበር ብሎ ሰው መከራከር ይችላል። በዚህ መሰረት አንድ ሰው
ያከማቸውን ንብረት ለራሱ ለመጠቀም ሥራ እያቆመ ከሆነ መጠንቀቅና ይህን
ታሪክ በልቡ ውሰጥ መያዝ ያስፈልገዋል። ችግሩ ያለው ጠንክሮ በመስራት ወይም
ሀብት በማግኘት ላይ አይደለም፣ በተለይም አንድ ሰው እያረጃ ሲሄድና ሀብታም
ሲሆን። ችግሩ ያለው ለሀብት ባለው አመለካከት ላይ ነው። ‹‹ነፍሴ ሆይ፣ ዕረፊ፥
ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ›› የሚሉ ቃላቶቹ እዚህ ላይ ያለውን እውነተኛውን
ጉዳይ ይገልጻሉ።
“የዚህ ሰው ዓላማ ከሚጠፉ እንስሳት ዓላማ የሚበልጥ አልነበረም። ይኖር
የነበረው እግዚአብሔር ወይም ሰማይ ወይም የወደፊት ሕይወት እንደሌለ አድርጎ
በመመልከት ነበር። ያለው ንብረት በሙሉ የራሱ እንደሆነና ለእግዚአብሔርም
ሆነ ለሰው ባለዕዳ እንዳልሆነ በማሰብ ይኖር ነበር።”—Ellen G. White,
Christ’s Object Lessons, pp. 257, 258.
በሕይወታችን በዚህ ደረጃ የሌሎችን ፍላጎትና የእግዚአብሔርን ሥራ ችላ
በማለት ለራሳችን ብቻ የምናስብ ከሆነ የሞኙን ሰው ምሳሌ እየተከተልን ነን።
በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ ሀብታሙ ሰውዬ ሰነፍ ወይም የማይታመን ስለመሆኑ
ምንም የሚያመለክት ነገር የለም። ችግሩ እግዚአብሔር በአደራ የሰጠውን ንብረት
የተጠቀመበት መንገድ ነው። የመሞቻ ቀናችንን ስለማናውቅ የራስ ወዳድነት
ሕይወትን ከመከተል ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በመኖር ሁልጊዜ
ዝግጁ መሆን አለብን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰው የሚሰራውና ውጤታማ መሆን የሚችለው
እስከቻለ ድረስ እንደሆነ አጠቃላይ ስዕል ተሰጥቷል። እንዲያውም ታላላቅ
ትንቢታዊ መጽሐፍት የሆኑትን ዳንኤልንና ራዕይን የጻፉ ሰዎች መጻሕፍቱን
ጽፈው ሲጨርሱ ሁለቱም በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንደነበሩ መገንዘብ ይቻላል።
ይህ ወቅት የሰው አማካይ ዕድሜ 50 ዓመት የነበረበት ወቅት ነበር። ኤለን ጂ
ኋይት እጅግ ታዋቂና እጅግ ተወዳጅ ከነበሩ መጻሕፍቶቿ መካከል እንደ ዘመናት
ምኞት ያሉ አንዳንድ መጻሕፍትን ያሳተመችው ዕድሜዋ ከ70 ዓመት ካለፈ
በኋላ ነበር። ስለዚህ ጤናማ እስከሆንን ድረስ ዕድሜ፣ በምንም መልኩ ቢሆን፣
ውጤታማና ጠቃሚ ሥራ መስራትን እንድናቆም ምክንያት መሆን የለበትም።
ኢየሱስ ዳግም ምጻቱን የሚጠባበቁ ሰዎችን ዝም ብለው እንዲጠብቁ ሳይሆን
መሥራታቸውንም እንዲቀጥሉ መከራቸው (ማቴ. 24:44–46)።
በየትኛውም ዕድሜና የገንዘብ መጠን በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ሰው
በወደቀበት ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ማምለጥ የምንችለው
እንዴት ነው? “ለምንድር ነው እየኖርኩ ያለሁት?” ብላችሁ ራሳችሁን
ጠይቁ።
ቢሊ ግራም የተባለ ታዋቂ ሰባኪ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት እና ዕድሜው እየገፋ ባለበት ወቅት አንድ ሰው ስለ ሕይወት እጅግ የሚያስደንቀው ነገር ምን እንደሆነ ጠየቀው። እርሱም ‹‹እጥረቱ›› ነው በማለት መለሰ። ሕይወት በቶሎ የሚያልፍ ነገር መሆኑ አያጠያይቅም። የሚከተሉት ጥቅሶች በዚህች ምድር ስላለው ስለ ሰው ሕይወት ምን ያስተምሩናል? መዝሙር 49:17፤ 1ኛ ጢሞ. 6:6፣ 7፤ መዝ. 39:11፤ ያዕቆብ 4:14፤ መክብብ 2:18–22።
ሕይወት በቶሎ የሚያልፍ ብቻ ሳይሆን ስትሞት ቢያንስ ካካበትከው ቁሳዊ ንብረት
እንኳን ምንም ነገር ይዘህ አትሄድም። ባህርይስ? ያ ሌላ ታሪክ ነው። “በሞተ ጊዜ
ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና” (መዝ.
49:17)፤ ይህ ማለት ማንም ቢሆን የለፋበትን ነገር ሌላ ሰው እንዲጠቀመው ትቶ
ያልፋል ማለት ነው። ማን ያገኘዋል የሚለው የሚደገፈው አስቀድሞ በተዘጋጀው
ዕቅድ ነው።
ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሰው ርስት (የግል መሬት) ባይኖረውም አብዛኛው
ሕዝብ፣ ለብዙ ዓመታት ከመስራታቸው የተነሣ የተወሰነ ሀብት አፍርተዋል
(አካብተዋል)። በመጨረሻ እርስዎ ሲያልፉ ያ ሀብት ምን ይሆናል የሚለው ጥያቄ
እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ነው።
በሕይወታቸው ፍጻሜ ላይ ሀብት ላካበቱ ሰዎች፣ ንብረታቸው ምንም ያህል
ትልቅ ወይም ትንሽ ቢሆን፣ ስለ ርስታችን ማቀድና ከእግዚአብሔር በመቀበል
የተባረክንበትን ነገር በአግባቡ መያዝ የመጨረሻው ተግባራችን መሆን አለበት።
በኑዛዜ ወይም በአደራ ያዘጋጀኸው የርስት ዕቅድ ከሌለህ የመንግስት ወይም
የአገር ሕጎች ተግባራዊ ይሆናሉ (ይህ ሁሉ የሚደገፈው በምትኖርበት ቦታ ነው)።
ሳትናዘዝ ከሞትክ የመንግስት ድንጋጌዎች ሀብትህን ወደ ዘመዶችህ ያስተላልፋሉ፤
እነርሱ ቢፈልጉም ባይፈልጉም፣ በአግባቡ ቢጠቀሙም ባይጠቀሙም፣ ለዚያ
ሰው ከሀብትህ የተወሰነውን ከፍለህ ለመስጠት ብትፈልግም ባትፈልግም ሕጉ
ተግባራዊ ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ምንም ነገር አታገኝም። አንተ የምትፈልገው
ያ ከሆነ መልካም፤ ካልሆነ ግን አስቀድመህ ዕቅድ ማዘጋጀት አለብህ።
በቀላል አገላለጽ እግዚአብሔር የሁሉም ነገር ባለቤት ስለሆነ (መዝሙር 24፡1ን
ይመልከቱ)፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ስንመለከት እግዚአብሔር በአደራ የሰጠንን
ነገር ከተጠቀምን በኋላ፣ የቤተሰቦቻችን ፍላጎቶችም ከተሟሉ በኋላ፣ የቀረውን
ነገር ባለመብት ለሆነው ባለቤት መመለስ አለብን ብሎ መደምደም ትክክለኛ
ሀሳብ ነው።
እንደምናውቀው ሞት በየትኛውም ሰዓት፣ ሳይጠበቅ በድንገት፣ ዛሬም
ቢሆን ሊመጣ ይችላል። እርስዎ ዛሬ የሚሞቱ ቢሆን የቤተሰብ አባላትዎ
ምን ይሆናሉ? ሀብትዎስ ምን ይሆናል? እርስዎ እንደሚፈልጉት
ይከፋፈላል?
በብሉይ ኪዳን ዘመን አብዛኞቹ የእሥራኤል ልጆች ገበሬዎችና የበጎች
እረኞች ነበሩ። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለመስጠት ከገባቸው ቃል ኪዳኖች
አንዳንዶቹ በግብርና ቋንቋ የተገለጹ ነበሩ። ለምሳሌ በምሳሌ 3፡ 9ና 10 ላይ እኛ
ገንዘብን በተመለከተ ለእግዚአብሔር ታማኝ ብንሆን ኖሮ ‹‹ጎተራዎቻችን በእህል
ሞልተው ይትረፈረፉ ነበር›› ይላል። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ጎተራ የላቸውም።
ስለዚህ እግዚአብሔርን ለመከተልና ለመታዘዝ ፈቃደኛ ብንሆን ኖሮ እርሱ
ሥራችንን ወይም ንግዳችንን እንደሚባርክ እንረዳለን።
ምሳሌ 27:23–27ን ያንብቡ። ዛሬ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች
“መንጎቻችሁ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ትጉ” የሚለውን ሀሳብ እንዴት
ትተረጉሙታላችሁ?
ነገር ግን ድሆችን የሚረግጡ ወይም ሀብታቸውን በተመለከተ ስስታም የሆኑ
ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃቸዋል። ታማኝነትን በማጉደል ወይም ሌሎችን
በመጨቆን የሚፈራ ሀብት ካልሆነ በቀር መጽሐፍ ቅዱስ ሀብትንም ሆነ ሀብት
ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት አይኮንንም። በመጽሐፈ ምሳሌ የተጠቀሰው
የዛሬው ጥቅስ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን በቂ የሆነ ነገር እንዲኖረን ገንዘብን
በተመለከተ መትጋት እንዳለብን ያመለክታል። “ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ
ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይኖርሃል” (ምሳሌ 27:27)።
ይህን ጥቅስ ለዛሬ በሚገጥም መልኩ እንዴት እንደገና መጻፍ እንችላለን?
ምናልባት “የገንዘብ መዝገቦቻችሁን ከልሱአቸውና ያላችሁበትን ሁኔታ ወስኑ”
ብለን ሀሳብ መስጠት እንችላለን፤ ወይም “ገቢና ወጪ መመዝገቢያ የሂሳብ
መዝገባችሁን ስሩና የእዳና የትርፍ መጠናችሁን ተረዱ” ማለት እንችላለን።
ገንዘብን ማፍራት በምትችሉባቸው ጊዜያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑዛዜአችሁን ወይም
ሌሎች መረጃዎችንና አሁን ያላችሁን ንብረት ከልሶ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከል
አግባብነት ያለው ነገር ነው። ያለ ጊዜ መሞትን ወይም ከጤና ምክንያቶች
የተነሣ ንብረቶቻችሁ የት መሄድ እንዳለባቸው መወሰን አለመቻልን ለመከላከል
እንደ ኑዛዜና የአደራ መረጃዎች የመሰሳሉ ዶኩሜንቶች አስቀድሞ ርስትን
በማቀድ ሂደት ውስት ቦታቸውን መያዝ አለባቸው። ሀሳቡ እየነገራችሁ ያለው
ንብረቶቻችሁ የእናንተ ንብረቶች መሆናቸውን በሚያቆሙበት ጊዜ ለሚሆነው
ነገር አስቀድማችሁ ማቀድ እንዳለባችሁ ነው።
በአጭሩ፣ እግዚአብሔር ለባረከን ነገር መልካም መጋቢዎች መሆን አለብን የሚለው
ሀሳብ የሚመለከተው በሕይወት እያለን ያለንን ነገር ብቻ ሳይሆን እኛ ከሞትን
በኋላ የሚሆነውንም ነገር ጭምር ነው። ለዚህ ምክንያቱ ጌታ እኛ በሕይወት
እያለን ባይመለስ፣ ይብዛም ይነስም ቁሳዊ ሀብታችንን ወደ ኋላ ትተን መሞታችን
አይቀርም። እኛ የተባረክንበት ነገር ለሌሎች በረከት እንዲሆንና የእግዚአብሔር
ሥራ እንዲስፋፋ አሁን የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ የእኛ ጉዳይ ነው።
“ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና” (ምሳሌ 27:24)። ይህን ሀሳብ
በአእምሮአችን መጠበቅ የሚያስፈልገው ለምንድር ነው?
ገንዘብን እንዴት መያዝ እንዳለብን በተመለከተ ከእነዚህ ጥቅሶች ምን መርሆዎችን መውሰድ እንችላለን? 1 ጢሞ. 6:17___________________________________________________________________
2 ቆሮ. 4:18____________________________________________________________________
ምሳሌ 30:8_____________________________________________________________________
መክብብ 5:10__________________________________________________________________
ገንዘብ በሰብአዊ ፍጡራን ላይ ኃይለኛና ብዙዎችን ወደ ጥፋት የመራ
የመቆጣጠር አቅም ሊኖረው ይችላል። እጅግ ብዙ ገንዘብ እያላቸው
ተጨማሪ ገንዘብ ለማጋበስ ሲሉ አስከፊ የሆኑ ነገሮችን ስለፈጸሙ ሰዎች
ያልሰማ ሰው ማን ነው?
ነገር ግን እንዲህ መሆን አይገባም ነበር። በረከት እንዲሆን የተሰጠውን
ቁሳዊ ሀብት ወደ እርግማን ለመለወጥ የሚሞክረውን የጠላትን ሙከራ
በእግዚአብሔር ኃይል ማሸነፍ እንችላለን።
መልካም መጋቢ በመሆን አውድ ውስጥ ለሞት ማቀድን በተመለከተ ብዙ
ሰዎች የሚገጥማቸው አደጋ ‹ስሞት ሁሉንም መስጠት እችላላሁ›› በማለት
አሁን ሀብትን የማከማቸት ፈተና ነው። ይህን ማድረግ አሁኑኑ ሁሉንም ነገር
ተጠቅሞ ከመጨረስ የተሻለ ቢሆንም (አንድ ቢሊየነር በትክክል እየኖረ መሆኑን
የሚያውቀው ለቀብሩ ገንዘብ ለማውጣት የተሰጠው ቼክ በባንክ በቂ ገንዘብ
የለም ተብሎ ተመላሽ ሲሆን እንደሆነ ተናግሮት ነበር) ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ
እንችላለን፣ ማድረግም አለብን።
“ብዙ ሰዎች ሲሞቱ የበጎ አድራጎት ሥራ እንደሚሰሩ ህሊናቸውን አሳምነው
ጸጥ በማድረግ በሕይወት እያሉ ለሥራው ገንዘብ ከመስጠት ይቆጠባሉ።
በሕይወት እያሉ ምንም ነገር ለመስጠት በእግዚአብሔር ማመንን እና መታመንን
ለመለማመድ አይደፍሩም። ነገር ግን ክርስቶስ ከተከታዮቹ የሚፈልገው በሞት
አልጋ ላይ ሆኖ የሚፈጸም በጎ አድራጎት አይደለም። ይህ በሕይወት እያሉ
ላሳዩት ራስ ወዳድነት መሻሪያ (ማካካሻ) ሊሆን አይችልም። ንብረታቸውን
እስከ መጨረሻዋ ቅጽበት ሞጭጨው የሚይዙ ሰዎች በመጨረሻ ለሥራው
ሳይሆን ለሞት አሳልፈው ይሰጣሉ። ያለማቋረጥ ክስረት እየተከሰተ ነው። ባንኮች
ግዴታቸውን መወጣት እያቃታቸው ንብረት በብዙ መንገዶች ይበላል። ብዙዎች
የሆነ ነገር ለማድረግ ያቅዱና ጉዳዩን ስለሚያዘገዩ ገንዘቡ ወደ ግምጃ ቤቱ በፍጹም
እንዳይመጣ ለመከልከል ሰይጣን ይሰራል። ገንዘቡ ለእግዚአብሔር ከመመለሱ
በፊት ስለሚጠፋ ሰይጣን ከፍ ከፍ ይላል።”—Ellen G. White, Testimonies
for the Church, vol. 5, p. 154.
ለቁሳዊ በረከቶቻችን አጠቃቀም ትክክለኛነት የምንሰጠውን ማረጋገጫ
በተመለከተ እጅግ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድር ነው?
ሰብአዊ ፍጡራን ኃጢአት ባይሰሩ ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት ምን
ይመስል እንደነበር ማወቅ ከባድ ቢሆንም በእርግጠኝነት አንድ ነገር እናውቃለን፡
- የሰው ልጅ ታሪክ መጻፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዓለማችንን እንደ በሽታ የወረሩ
ሀብት ማጋበስ፣ ስስትና ድህነት አይኖሩም ነበር። ሰርተን ለፍተን ላፈራነው ነገር
ያለን የባለቤትነት ስሜት፣ በታማኝነት ሰርተን ያፈራነው ከሆነ በትክክል የእኛ
ሲሆን፣ ይህ በወደቀው ዓለም ያለው ሕይወት መገለጫ ነው። ነገር ግን በመጨረሻ
ምንም ያህል ሀብት ቢኖረን ወይም ባይኖረን ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብን አንድ
አስፈላጊ ነጥብ አለ።
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። በሁሉም ጥቅሶች ውስጥ ማዕከላዊው
ነጥብ ምንድር ነው? ያ ነጥብ እግዚአብሔር የባረከንን ቁሳዊ ሀብት
በመጠቀም በምናደርገው ነገር ላይ ተጽእኖ መፍጠር ያለበት እንዴት
ነው? (መዝሙር 24:1፣ ዕብ. 3:4፣ መዝሙር 50:10፣ ዘፍ. 14:19፣ ቆላ.
1:15–17)።
እርሱ በአደራ ለሰጠን ነገር እኛ መጋቢዎችና አስተዳዳሪዎች ነን፤
ይህ ማለት እግዚአብሔር የሁሉም ባለቤት ሲሆን ሕይወትን፣ ሕልውናን እና
ማንኛውንም ነገር ሰርተን እንድናገኝ ብርታት የሚሰጠን እርሱ ነው። ስለዚህ
እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር መጠቀም ስናቆምና ለቤተሰባችን አስፈላጊውን ነገር
ካደረግን በኋላ ቀሪውን ለእርሱ መመለስ አለብን።
“ለእግዚአብሔር ሥራ ስትሰጡ ለራሳችሁ በሰማይ ሀብት እያከማቻችሁ ነው።
በሰማይ የምታከማቹት ነገር ሁሉ ከአደጋና ከጥፋት የተጠበቀ ሲሆን ዘለቄታ
ወዳለው ዘላለማዊ ሀብት እያደገ ይሄዳል።” “በሰማይ መንግስት ባለው የቁጠባ
ደብተራችሁ ይመዘገባል።”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship,
p. 342.
አሁን በሕይወት እያለን መስጠት ብዙ ጥቅሞች አሉት። ጥቂቶቹ የሚከተሉት
ናቸው፡-
1.ለጋሹ ስጦታው ያመጣውን ውጤቶች ማየት ይችላል። ለምሳሌ አዲስ የቤተ
ክርስቲያን ሕንፃ፣ በኮሌጅ የሚማር ወጣት፣ እየተካሄደ ያለ የወንጌል ጥረት
ወዘተ…።
2.ፍላጎቱ እጅግ ትልቅ ሲሆን አገልግሎቱ ወይም ግለሰቡ ተጠቃሚ መሆን
ይችላል።
3.እርስዎ ከሞቱ በኋላ በቤተሰብ ወይም በጓደኞች መካከል ጠብ አይኖርም።
4.የልግስናንና ሌሎችን የመውደድን ቤተሰባዊ እሴቶች ጥሩ ምሳሌ ያስቀመጣል።
5.የርስት ግብር መዘዞችን ይቀንሳል።
6.ስጦታችሁ ለምትፈልጉት አካል እንዲሰጥ ዋስትና ይሰጣል (ከፍርድ ቤቶች
ወይም የፈለጉትን ባለማግኘታቸው ከተበሳጩ ዘመዶች ጣልቃ ገብነት ነጻ
ያደርጋል)።
7.የለጋሹ ልብ ከራስ ወዳድነት ራስን ወደመካድ መለወጡን ያሳያል።
8.በሰማይ ሀብትን ያከማቻል።
:- ስለ ንብረት ክፍፍል በሚናገር በዚህ ወሳኝ ርዕስ ላይ ኤለን
ጂ ኋይት ሁለት ምዕራፎችን ጽፋለች። ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች በሚል መጽሐፍ
ሶስተኛው ቅጽ ገጽ 116-130 ላይ ‹‹(ላረጁ) እና ሀብታም ወላጆች›› የሚለውን
እና ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች በሚል መጽሐፍ ቅጽ አራት ገጽ 476-485 ላይ
‹‹ኑዛዜዎች እና ውርሶች›› የሚለውን ክፍል ይመልከቱ።
ምክረ መጋቢነት በሚል መጽሐፍ ገጽ 323-335 ላይ ስለ ርስት ማቀድ
የሚናገር ክፍል አለ። ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ጽፋለች፡- “ብዙዎች ለመሞት
እስከሚቃረቡበት ጊዜ ድረስ ለማስተላለፍ ሀሳብ የሚያቀርቡትን ነገር ክርስቲያኖች
ቢሆኑ ኖሮ ሕይወትን መቆጣጠር በሚችሉበት ጊዜ ያደርጉት ነበር። ራሳቸውንና
ንብረታቸውን ለእግዚአብሔር ቀድሰው ይሰጣሉ፤ እንደ እግዚአብሔር ንብረት
መጋቢ በመስራት ከድርጊታቸው እርካታ ያገኛሉ። የራሳቸው ዕቅድ ፈጻሚ
በመሆን ሀላፊነቱን ወደ ሌላሎች ከማስተላለፍ ይልቅ ራሳቸው የእግዚአብሔርን
ጥያቄዎች ይፈጽማሉ።”—Testimonies for the Church, vol. 4, p. 480.
“የራሳቸው ዕቅድ ፈጻሚዎች” ስትል ምን ማለቷ ነው? በኑዛዜ ላይ ተናዛዡ
ከሞቱ በኋላ በኑዛዜው መሰረት ንብረቱን የማከፋፈል ዕቅዱን የሚፈጽምለትን
ሰው ይበይናል። የራስህ ዕቅድ ፈጻሚ ስትሆን ንብረትህን ገና በሕይወት እያለህ
ራስህ ታከፋፍላለህ ማለት ነው። ይህን በማድረግህ ውጤቶቹን በመመልከትና
እግዚአብሔር የሰጠህን መክሊቶች በአግባቡ ሥራ ላይ እያዋልክ መሆንን በማወቅ
እርካታ ታገኛለህ።
ለክርስቲያን የክርስቶስ ዳግም ምጻት “የተባረከ ተስፋ” ነው። ክርስቶስ
በሰማይ ደመና ሲመጣ ማየት እንዴት ድንቅ እንደሆነ ሁላችንም አስበን
እናውቃለን። “ደግ አድርገሃል” የሚሉ ቃላቶችን ለመስማት ሁላችንም እንጓጓለን።
ነገር ግን ኢየሱስ ከመመለሱ በፊት ወደ እረፍታችን የምንሄድ ከሆነስ? የእርሱን
ፈቃድ በትክክል ተከትለን ከሆነ ለርስታችን ካዘጋጀነው ዕቅድ የተነሣ እኛ ከሞትን
በኋላ ሥራው እንደሚቀጥል ስለምናውቅ በእኛ ጥረት ሥራው ወደ ፊት እየቀጠለ
መሆኑን በማየት እርካታ እናገኛለን።
:1.ምንም እንኳን አሁን ሀብት በሰማይ ማስቀመጥ ብንችልም ይህ
ድነትን ለማግኘት ወይም ‹‹ለመግዛት›› ከመሞከር ጋር ተመሳሳይ
የማይሆነው ለምንድር ነው?
2.አሁን ያለንን ነገር በመስጠት ለጋስ መሆን የተገባ ቢሆንም
ጠቢብ መሆንም አለብን። ሰዎች፣ በተለይም ቀን ቀጣሪዎች፣
ይህን የመሰሉ ክስተቶች በዚህ ቀን ስለሚፈጸሙ፣ ያኔ ገንዘባችን
ዋጋ ቢስ ስለሚሆን ገንዘባችንን ወደ እነርሱ አገልግሎት እንድንልክ
ተማጽኖ የሚያቀርቡ ሰዎችን የሰማነው ስንት ጊዜ ነው?
በዚህ ማጭበርበርና ገንዘባችንን ለእግዚአብሔር ስራ መጠቀም
በምንችልባቸው ህጋዊ መንገዶች መካከል መለየት የምንችለው
እንዴት ነው?