የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1 ቆሮ. 15፡12-19፣ ዮሐንስ 14፡1-3፣ ዮሐንስ 6፡26-51፣ 1 ተሰ. 4፡13-18፣ 1 ቆሮ. 15፡ 51-55።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ህይወት ሰጠን፤ ይህም ህይወት ያለው በልጁ ነው፡፡” 1 ዮሐንስ 5፡11-12
በ
ግሪክ ቋንቋ ቢጽፉም ሁሉም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች (ከሉቃስ በቀር)
አይሁዶች ነበሩ፣ እናም ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲናገሩ ከግሪክ አረማዊ
እይታ አንፃር ሳይሆን ከዕብራይስጥ ሙሉ የሆነ እይታ አንፃር ይናገሩ
ነበር።
ስለዚህ፣ ለክርስቶስና ለሐዋርያቱ፣ የክርስቲያኖች ተስፋ አዲስ ተስፋ ሳይሆን፣
በአባቶችና በነቢያት የተነገረው የጥንት ተስፋ መገለጥ ነው። ለምሳሌ፣ ክርስቶስ
አብርሃም አስቀድሞ እንዳየና ቀኑን በማየት እንደተደሰተ ተናግሯል (ዮሐ. 8፡
56)። ሄኖክ ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት መናገሩን ይሁዳ ተናግሯል (ይሁዳ
14-15)። በተጨማሪም የዕብራውያን መፅሐፍ ስለ እምነት ጀግኖች ሲናገር
እኛ የኛን እስክንቀበል ድረስ የማያገኙትን ሰማያዊ ሽልማት እንደሚጠብቁ
ይናገራል (ዕብ. 11፡39-40)። ነፍሳቸው በሰማይ ከጌታ ጋር ብትሆን ይህ
አባባል ትርጉም የለሽ በሆነ ነበር።
በክርስቶስ ያሉት ብቻ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው አጽንኦት በመስጠት
(1 ዮሐንስ 5፡11-12) ዮሐንስ ነፍስ በተፈጥሮዋ ሟች አይደለችም የሚለውን
ፅንሰ ሐሳብ ውድቅ አድርጎታል። በእርግጥም ከክርስቶስ ጋር ከሚኖር የማዳን
ግንኙነት በቀር የዘላለም ሕይወት የለም። እንግዲህ የአዲስ ኪዳን ተስፋ
ክርስቶስን ያማከለ ተስፋ ነው፣ እናም ይህ ሟች ህልውና አንድ ቀን የማይሞት
እንደሚሆን ተስፋን የሚሰጥ ነው።
*ለህዳር 10 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
የጥንት ግሪክ ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ (5ኛው ክፍለ ዘመን) ስለ
አንድ ነገድ ጽፏል፣ የዚያ ነገድ ሰዎች ሕፃን ሲወለድ ለአቅመ አዳም ከደረሰ
ሊደርስበት የሚችለውን መከራ አስቀድሞ በመገመት የሐዘን ጊዜ ይጀምራሉ።
ምንም እንኳን ይህ ልማድ ለእኛ እንግዳ ቢመስልም አሳማኝ የሚመስል ነገር
አለ።
ከሺህ ዓመታት በኋላ፣ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ
በአሜሪካ የወጣ ማስታወቂያ፣ “በአስር ዶላር ሊቀበሩ እየቻሉ ለምን በህይወት
ይኖራሉ?” ይላል።
በእግዚአብሔር እና በዘለአለም ተስፋ ብናምን እንኳን ህይወት ከባድ
ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን። ነገር ግን እዚህ ካለው አጭር እና ብዙ ጊዜ
በችግር የተሞላ ከሆነ ህይወት ባለፈ ምንም ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች ምን
ያህል ከባድ እንደሆነ ያስቡ። ሁላችንም የምንሞት መሆናችን ብቻ ሳይሆን
ሁላችንም እንደምንሞት እያወቅን መኖራችን በህይወት መኖርን ትርጉም
የለሽ እንደሚያደርገው ከአንድ በላይ ዓለማዊ ጸሐፊዎች ተናግረዋል። ይህ
ግንዛቤ ደግሞ ብዙውን ጊዜ በራሱ ከባድ እና በሀዘን የተሞላውን የሰው ልጅ
ህይወት በአጠቃላይ ቆይታ ባዶ እንዲሆን የሚያደርገው ነው። አንድ ፈላስፋ
ሰውን “እየተላቀቁ በሚሄዱ አጥንቶች ላይ የተንጠለጠለ በስባሽ ሥጋ” ብሎ
ገልፆታል።። የባሰ አሰቃቂ አገላለፅ ቢሆንም በድጋሚ ከአመክንዮው ጋር
መሟገት አስቸጋሪ ነው።
እርግጥ ነው፣ ከዚህ ሁሉ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን
በኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን። ቁልፉም ያ ነው፤ በኢየሱስ በሞቱና
በትንሳኤው ባገኘነው ተስፋ ምክንያት ይህ ተስፋ አለን። ያለበለዚያ ምን ተስፋ
አለን?
1 ቆሮንቶስ 15:12-19ን ያንብቡ። ጳውሎስ እዚህ ላይ የክርስቶስ
ትንሣኤ ከራሳችን ትንሣኤ ተስፋ ጋር ምን ያህል ዝምድና እንዳለው
ሲናገር ምን እያለ ነው?
ጳውሎስ ግልጽ ነው፡- ትንሳኤያችን ከክርስቶስ ትንሳኤ ጋር የማይነጣጠልና
የተሳሰረ ነው። የማንነሳ ከሆነ ደግሞ ክርስቶስ አልተነሳም ማለት ነው፤
ታድያ ክርስቶስ ካልተነሳ- ምን? “እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከአሁን
ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ” በሌላ አነጋገር ስንሞት እንደሞትን ለዘላለም
እንቆያለን፤ ሁሉም ትርጉም የለሽ ይሆናል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15:32
“ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ‘ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ!” ይላል።
አሁን ያለንበት አካል ካርቦን ላይ እንደተመሠረተ ፕሮቶፕላዝም ብቻ ከሆነና
የምንኖረው “ሠባ ዓመታት” ብቻ (እሱንም እድለኛ ከሆንን፣ ምናልባት ብዙ
ካላጨስን ወይም ብዙ ሀምበርገር ካልበላን) ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ
ነን። ኤለን ጂ ኋይት ጨምራ እንዲህ ማለቷ ምንም አያስደንቅም፤ “መንግሥተ
ሰማያት ሁሉ ነገራችንን ብንሰጠው የሚገባው ነው፤ እናም መንግሥተሰማያትን ካጣን ሁሉንም አጥተናል።” Sons and Daughters of God, p.
349.
ተስፋችን እና እምነታችን ምን ያህል ውድ እንደሆነ ያስቡ።
በያዝነው ለመጽናት እግዚአብሔር በረዳን መጠን የምንችለውን
ሁሉ ማድረግ ያለብን ለምንድነው?
ዮሐንስ 14:1-3ን ያንብቡ። ኢየሱስ እንደገና እንደሚመጣ ቃል
ከገባ 2,000 ዓመታት አልፈዋል። ይህ የተስፋ ቃል ኢየሱስ
ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ረዥም ጊዜያት ቢያልፉም ተስፋው
ለእኛ ትውልድ እንኳን ወሳኝ መሆኑን ሌሎች እንዲገነዘቡ መርዳት
የምንችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ አራት ጊዜ “በቶሎ እመጣለሁ!” ብሏል(ራእ.
3:11፣ ራእ. 22:7፣12፣20)። በቅርቡ ይመጣል ተብሎ መጠበቁ የሐዋርያት ዘመን
ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ አንቀሳቅሶታል፤ ለዘመናትም ከቁጥር በላይ የሆኑ
ክርስቲያኖችን ሕይወት በተስፋ ሞልቷል። ነገር ግን ብዙ ትውልዶች ሞተው
ካለፉ በኋላም ይህ ተስፋ ገና አልተፈጸመም። እናም ብዙዎች “ኢየሱስ በቅርቡ
ይመጣል” ብለን የምንሰብከው እስከ መቼ ነው? እነዚህ ቃላት የማይጨበጥ
ተስፋ ፈጥረው ይሆንን? (2 ጴጥ. 3:4) ብለው እየጠየቁ ናቸው።
ብዙ ክርስቲያኖች ረዥም ጊዜ ስለፈጀው ጥበቃ ቅሬታ አቅርበዋል (ከማቴ.
25፡5 ጋር ያነፃፅሩ)። ነገር ግን እኛ በእርግጥ “መዘግየት” መሆኑን እንዴት
እናውቃለን? ክርስቶስ የሚመለስበት ትክክለኛው ጊዜ የትኛው ይሆን ነበር?
ከ50 ዓመታት በፊት፣ ከ150፣ ከ500 ይሆን? ዋናው ነገር “ለአንዳንዶች
የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ
ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”
(2 ጴጥ. 3፡9)
ኢየሱስ ካረገ ብዙ መቶ ዓመታት ቢያልፉም የመምጣቱ ተስፋ ዛሬም ቢሆን
ጠቃሚ ነው። ለምን? ምክንያቱም እኛ ያለን አጭር ሕይወት ነው (መዝ.
90፡10)፣ ከዚያ በኋላ ምንም ሳናውቅ በመቃብር እናርፋለን (መክ. 9፡5-10)
ከዚያም እጣ ፈንታችንን ለመለወጥ ምንም ዕድል ሳናገኝ የመጨረሻው
ትንሣኤ ይሆናል (ዕብ. 9:27)። ስለ እያንዳንዱ ሙታን በተመለከተ (በክፍል
ሦስት ላይ እንደተገለጸው) ሁሉም ሙታን ተኝተው ምንም ስለማያውቁ ከሞቱ
በኋላ ከአንድ ወይም ከሁለት አፍታ በኋላ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይሆናል።
በግላችንም ቢሆን (በዘመናት እንደነበሩት እንደ ሁሉም የእግዚአብሔር
ሰዎች)፣ የክርስቶስ ምጽአት ከሞትን በኋላ ከአፍታ አይበልጥም። ያ በጣም
በቅርቡ ነው፤ አይደል?
እያንዳንዱ ቀን ሲያልፍ አንድ ቀን ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ
ደመና ወደ ክብሩ መገለጥ ያቀርበናል። መቼ እንደሚመጣ ባናውቅም እሱ
እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ዋናው ነገር ያ ነው።
አንድ ቄስ ስለክርስቶስ የመመለሻ ጊዜ ግድ እንደሌለው በመግለጽ
ሰበከ። እርሱ የሚያሳስበው የክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ብቻ
ነው። ይህ አመክንዮ የሚጠቅመን እንዴት ነው? ክርስቶስ ገና
ስላልተመለሰ ተስፋ ለቆረጠ ሰው እንዴት ሊጠቅም ይችላል?
በአንዱ ተአምራቱ፣ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን በትንሽ ዳቦና አሳ መግቧል (ዮሐንስ 6፡1-14)። (ዮሐ. 6፡15) ሕዝቡ እርሱን ሊያነግሱት እንዳሰቡ ስላወቀ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ሄደ። ነገር ግን በማግስቱ ህዝቡ እዚያ ተከተሉት፤ በዚያም ስለ ህይወት እንጀራ የሰጠውን ሀይለኛ ስብከቱን፣ የዘላለም ህይወት ስጦታ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስተማረ (ዮሐ. 6፡22-59)። ዮሐንስ 6:26–51ን ያንብቡ። ኢየሱስ የዘላለም ሕይወትን ስጦታ ከጻድቃን የመጨረሻ ትንሣኤ ጋር ያገናኘው እንዴት ነው?
ኢየሱስ በስብከቱ ውስጥ የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ ሦስት መሠረታዊ
ሐሳቦችን ጎላ አድርጎ ገልጿል። በመጀመሪያ፣ ራሱን “ከሰማይ የወረደ እንጀራ
ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ” (ዮሐንስ 6፡33፣58) በማለት ተናግሯል። “‘እኔ
(በግሪኩ ኤጎ ኤይሚ) የሕይወት እንጀራ ነኝ” (ዮሐንስ 6፡35፣ 48) በማለት
ኢየሱስ ራሱን የብሉይ ኪዳኑ ታላቁ “እኔ ነኝ” በማለት ራሱን አቅርቧል (ዘፀ.
3፡14)። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንደሚረጋገጥ
ገልጿል፡- “‘ወደ እኔ የሚመጣ’” እና “‘በእኔ የሚያምን’” ይህን በረከት ያገኛል
(ዮሐንስ 6፡35)። በመጨረሻም፣ ኢየሱስ ያለመሞትን ስጦታ ከመጨረሻው
ትንሳኤ ጋር አያይዞ፣ ለታዳሚዎቹ ሶስት ጊዜ ሲያረጋግጥ፣ “‘በመጨረሻውም
ቀን አስነሳዋለሁ’” (ዮሐንስ 6፡40፣ 44፣ 54) ብሎ ተናግሯል።
ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ የዘላለም
ሕይወት አለው” (ዮሐንስ 6፡47) በማለት ይህን አስደናቂ ተስፋ ሰጠ።
ስለዚህ፣ የዘላለም ሕይወት ስጦታ አሁን ያለ እውነታ ነው። ይህ ማለት ግን
አማኙ አይሞትም ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም “አስነሳዋለሁ” (ዮሐ. 6፡
40) የሚለው አገላለፅ ራሱ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ወደ ህይወት መመለስን
ስለሚናገር ነው።
ምስሉ ግልጽ ነው። ያለ ክርስቶስ ሰው የዘላለም ሕይወት የለውም። ነገር ግን፣
ክርስቶስን ከተቀበልን እና የዘላለም ህይወት ማረጋገጫ ካገኘን በኋላ፣ ለአሁን
ሟች መሆናችንን እንቀጥላለን፣ እናም ለተፈጥሮ ሞት ተገዢዎች ነን። በዳግም
ምጽአቱ፣ ኢየሱስ ያስነሳናል፤ እናም በዚያ ቦታ አስቀድሞ የእኛ የነበረውን
ያለመሞት ስጦታ ይሰጠናል። ስጦታው የተረጋገጠው በተፈጥሮአዊ ነፍስ
አትሞትም ተብሎ በማሰብ ሳይሆን በእርሱ በማመን ወደ እኛ በሚመጣው
የኢየሱስ ፅድቅ ነው።
በእኔ ካመናችሁ (አሁን እንዳለን) የዘላለም ሕይወት አላችሁ
በሚለው የኢየሱስ ቃል ላይ ጊዜ ወስደው ያሰላስሉ። ይህ አስደናቂ
ተስፋ አሁን ባለንበት ጊዜያዊ የሟችነት ሕይወት ውስጥ ያለውን
አሳዛኝ እውነታ እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
የተሰሎንቄ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ በሕይወት
ለሚቆዩት ብቻ እንደሚሰጥ እርግጠኞች ነበሩ። “እንዳይሞቱ እና በጌታቸው
ምጽአት የጠበቁትን በረከት እንዳያጡ፣ የጓደኞቻቸውን ህይወት በጥንቃቄ
ሲጠብቁ ነበር። ሆኖም የሚወዷቸው ሰዎች አንድ በአንድ በሞት
ተለይተዋቸዋል፤ እናም የተሰሎንቄ ሰዎች በጭንቀት የሟቾችን ፊት ለመጨረሻ
ጊዜ ሲመለከቱ ወደፊት ከእነሱ ጋር ለመገናኘት ተስፋ ለማድረግ ድፍረት
አልነበራቸውም።”—Ellen G. White The Acts of the Apostles, p. 258
1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13–18ን ያንብቡ። ጳውሎስ ይህን የተሳሳተ
አመለካከት ያረመው እንዴት ነው?
“በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል” (1ኛ ተሰ. 4፡
14) በሚለው አገላለጽ ውስጥ ጽሑፉ ከሚናገረው በላይ የማንበብ ታሪካዊ
ዝንባሌ አለ። ነፍስ አትሞትም የሚለውን ፅንሰ-ሀሳብ የተቀበሉ ብዙዎች
ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ከእርሱ ጋር ቀድሞውኑ ከእግዚአብሔር ጋር በሰማይ
ያሉትን የጻድቃን ሙታን ነፍሳት ከሰማይ እንደሚያመጣ አድርገው ያስባሉ፤
በዚህ አተረጓጎም ስንቀጥል እነዚያ ነፍሳት ከሞት ከተነሱ አካሎቻቸው ጋር
ይገናኛሉ ማለት ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አተረጓጎም ጳውሎስ በዚህ
ጉዳይ ላይ ካስተማረው አጠቃላይ ትምህርት ጋር የሚስማማ አይደለም።
አድቬንቲስት ያልሆነው የስነ-መለኮት ምሁር የዚህን ጥቅስ ትክክለኛ ትርጉም
በሚመለከት የፃፈውን የሚከተለውን ቃል ያንብቡ:- “የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች
ለሟች የቤተ ክርስቲያን አባላት በሚያዝኑበት ጊዜ ተስፋ እንዲኖራቸው
የሚያደርገው አምላክ ‘እንደሚያመጣቸው’ ማለትም በክርስቶስ ዳግም ምጽአት
ላይ እንዲገኙና ለዘላለም ከርሱ ጋር እንዲሆኑ ከሞት እንደሚያስነሳቸው
ካመኑ ነው። ማለትም የሞቱት አማኞች በክርስቶስ ዳግም ምፃት ወቅት
ምንም የሚጎድልባቸው ነገር ሳይኖር ክብሩን ከሕያዋን አማኞች ጋር እኩል
ይካፈላሉ።”— Jeffrey A. D. Weima, 1–2 Thessalonians, Baker Exegetical Commentary on the New Testament (Grand Rapids, MI:
Baker Academic, 2014), p. 319
የጻድቃን ሙታን ነፍስ በሰማይ ከጌታ ጋር ብትሆን ኖሮ፣ ጳውሎስ
የመጨረሻውን ትንሣኤ የክርስቲያን ተስፋ አድርጎ መጥቀስ አያስፈልገውም
ነበር። ጻድቃን ከጌታ ጋር እንዳሉ ሊጠቅስ ይችል ነበር። ነገር ግን ይልቁንም
“በኢየሱስ ያንቀላፉ” (1 ተሰ. 4፡14) በዘመኑ መጨረሻ ከሞት እንደሚነሡ
ተናግሯል።
በመጨረሻው ትንሣኤ ላይ ያለው ተስፋ ሐዘን ላይ ለነበሩት የተሰሎንቄ
ክርስቲያኖችን አጽናንቷል። ይኸው ተስፋ የምንወዳቸውን ሰዎች ከእኛ
የሚወስደውን የሞት ቀዝቃዛ ወቅት የሚያጋጥሙንን አሳዛኝ ጊዜያት በልበ
ሙሉነት እንድንጋፈጥ ይረዳናል።
1 ቆሮንቶስ 15:51–55ን ያንብቡ። 1 ቆሮ. 15:51 ላይ ጳውሎስ እየገለጸ ያለው የትኛውን “ምሥጢር” ነው?
አንዳንድ ታዋቂ ሰባኪዎች ይህ “ምስጢር” (1 ቆሮ. 15፡51) የቤተ ክርስቲያን
“በስውር መነጠቅ” እንደሆነ በመጠቆም ይህም የክርስቶስ ዳግም ምጽአት
ከመከሰቱ ከሰባት ዓመታት በፊት እንደሚሆን ያስተምራሉ። በዚህ “ስውር
መነጠቅ” ታማኝ ክርስቲያኖች በድንገት፣ በጸጥታ እና በድብቅ ወደ ሰማይ
ተወስደዋል፤ ሌላው ሰው ግን ምን እንደደረሰባቸው በማሰብ እዚሁ ይቆያል።
ሰዎች በድንገት ሹፌር በሌለው መኪና ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ፣ ምክንያቱም
ሹፌሩ ወደ ሰማይ ስለተነጠቀ፣ እና የቀረው ልብሱ ብቻ ስለሚሆን ነው።
ወደ አራት ፊልሞች የተቀየረውና ወደ ኋላ መቅረት የሚል ርዕስ ያለው ባለ
16 ጥራዝ መጽሐፍ ይህንን የውሸት ትምህርት በማስተዋወቅ ሚሊዮኖችን
ለትምህርቱ አጋልጧል።
እርግጥ ነው፣ የትኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባብ በመነጠቅ እና በዳግም
ምጽአት መካከል ያለውን ሰው ሰራሽ ልዩነት አይደግፍም። ጳውሎስ የጠቀሰው
“ምስጢር” ሕያዋን ጻድቃን በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ከሞት ከተነሱት
ጻድቃን ጋር ለመቀላቀል መለወጣቸውን ብቻ ነው። “መነጠቁ” ይህ ነው።
“በስውር መነጠቅ” የለም ምክንያቱም ዳግም ምጽአቱ ለሕያዋን ሰዎች ሁሉ
ስለሚታይ (ራዕ. 1፡7)፣ የሙታንም ትንሣኤም ሆነ የሕያዋን መለወጥ ክርስቶስ
ዳግም ሲገለፅ በመለከት ድምፅ ስለሚሆኑ ነው (1ኛ ቆሮ. 15፡51-52)።
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ
ግጥምጥሞሽን ይዞ ያመጣል። ሕያዋን ጻድቃን “በቅጽበት-ዐይን” ይለወጣሉ
(1ቆሮ. 15፡52)። በእግዚአብሔር ድምፅ ይከብራሉ፤ ያኔ የማይሞቱ ስለሚሆኑ
ከተነሱት ቅዱሳን ጋር ጌታቸውን በአየር ላይ ለመገናኘት ይነጠቃሉ። መላእክት
“ከአራቱ ነፋሳት ከሰማይ ጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ ምርጦቹን ይሰበስባሉ” (ማቴ.
24:31)።
“ቅዱሳን መላእክት ትንንሽ ልጆችን ተሸክመው ወደ እናቶቻቸው እቅፍ
ይወስዷቸዋል። ለረጅም ጊዜ በሞት የተለዩ ወዳጆች ፈፅሞ ላይለያዩ አንድ
ሆነው በደስታ ዝማሬ ወደ አምላክ ከተማ አብረው ይወጣሉ።”—Ellen G.
White፣ The Great Controversy ገጽ. 645.
ይህ በጣም አስደናቂ የሆነ ተስፋ ነው፤ አጋጥመውን ከሚያውቁና
ከማይታመኑ ነገሮች በጣም የተለየ ነው። ነገር ግን ስለ ዓለማት
ስፋት፣ እንዲሁም እዚህ ስላለው አስደናቂ የህይወት ውስብስብነት
ያሰላስሉ። ፍጥረት ራሱ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ኃይል
ይመሰክራል። ይህ ሁሉ በኢየሱስ ዳግም ምጽዓት ሕያዋንን
ለመለወጥ እና ሙታንን ለማስነሳት ስላለው ኃይል ምን
ያስተምረናል?
የሐዋርያት ሥራ የሚል ርዕስ ካለው
የኤለን. ጂ. ኋይት መጽሐፍ ውስጥ “ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች
የተላኩት ደብዳቤዎች” እና “ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ
የተጠራ” የሚል ርዕስ ያላቸውን ምዕራፎች ያንብቡ።
ስትፈን ኬቭ እንደፃፈው “ክርስቲያኖች አንድ ቀን በአካል ከመቃብር
እንደሚነሱ ያላቸውን እምነት ሮማውያን ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ በዚህ
ተስፋቸው ላይ ለማሾፍ እና ለማደናቀፍ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር።
በ177 ከክ.ል. በኋላ በጉዋል ስለደረሰው ስደት የሚገልጸው ዘገባ ሰማዕታቱ
መጀመሪያ እንደተገደሉ፣ ከዚያም አስከሬናቸው ከመቃጠሉ በፊት ለስድስት
ቀናት ሳይቀበር እንደቆየ ሲሆን ከዚያም የእሳቱ አመድ ወደ ሮን ወንዝ
ይጣላል። ሮማውያኑም “እስኪ አሁን እንደሚነሱ እናያለን” ይሉ ነበር።”—
Stephen Cave, Immortality: The Quest to Live Forever and How It
Drives Civilization (New York: Crown Publishers, 2012), pp. 104,
105.
ይህ ታሪክ በአጠራጣሪው ሥነ-መለኮት ውስጥ ምንም አስደናቂ ቢሆንም
ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የትንሣኤ ተስፋ ምንም የሰጠው ማረጋገጫ የለም።
ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው ኃይል የሰውነታችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለእኛም
እንዲሁ ሊያደርግልን ይችላል። ደግሞም ያ ኃይል መላውን ዩኒቨርስ ከፈጠረ
እና ከደገፈ ፣ እሱ በእርግጥ ህያዋንን ሊለውጥ ሙታንንም ሊያስነሳ ይችላል።
“እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን ደግሞ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር
ያመጣቸዋል” (1ኛ ተሰ. 4:14] በማለት ጳውሎስ ጽፏል።
ብዙዎች ይህንን
ክፍል የሚተረጉሙት ያንቀላፉት ከክርስቶስ ጋር ከሰማይ ይመጣሉ ብለው
ነው። ጳውሎስ ግን ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እግዚአብሔር
ያንቀላፉትን ቅዱሳን ከመቃብራቸው ጠርቶ ከእርሱ ጋር ወደ መንግሥተ
ሰማያት ይወስዳቸዋል ማለቱ ነው። ይህ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ብቻ
ሳይሆን በየትም ቦታ ለሚገኙ ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠ ውድ መጽናኛ!
የከበረ ተስፋ! ነው።”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p.
259.
:
1. አንድ ሰው “ሞት የሚያጠፋ ነው። . . . ሞት የአንድን
ሰው አሻራውንና ሁሉም ነገሮቹ እንዲጠፉ በማድረግ የሕይወት
ትርጉም ማጥፋት ድረስ ይሄዳል” ብሎ ተናግሯል። እሱ ትክክል
ነው። ታዲያ በሕይወታችን ውስጥ እንዲህ ያለውን ትርጉም
የለሽነት ለማምለጥ ምን ተስፋ አለን?
2. ወደ ፍጽምና የማደግን አስፈላጊነትና (ፊልጵ. 3፡12-16)
በክርስቶስ ዳግም ምጽአት የማይበሰብስ እና ኃጢአት የሌለበት
ተፈጥሮን መቀበላችንን አብረን የምናስኬዳቸው እንዴት ነው?
(1ቆሮ. 15፡50-55)?
3. “በስውር መነጠቅ” ትምህርት ውስጥ የተጠመደን አንድ ሰው
ይህ ትምህርት የተሳሳተ ለምን እንደሆነ እንዲያውቅ መርዳት
የምንችለው እንዴት ነው?
4. እንደገና 1 ቆሮንቶስ 15፡12-19ን ያንብቡ። በእነዚህ
ጥቅሶች ውስጥ ሙታን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ከመቆየት በተቃራኒ
አንቀላፍተዋል ለሚለው ትምህርት የሚያቀርበው ጠንካራ ማስረጃ
ምንድን ነው? ጻድቃን ሙታን አሁን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ካሉ
እነዚህ ጥቅሶች ምን ትርጉም አላቸው?