የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከታህሳስ 15 -21

14ኛ ትምህርት

Dec 24–30




ሁሉም ነገር አዲስ ይሆናል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 3:13፣ ራእ. 21:3፣ 22፣ 1ዮሐ. 3:2፣ 3፣ 1ጴጥ. 1:22፣ ኢሳ. 25:8፣ ራእ. 22:3–5።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ ‘እነሆ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ፤ ደግሞም፣ ‘ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ’ አለኝ” (ራእ. 21፡5)፡፡

መ ጽሐፍ ቅዱስ ይህን ተስፋ ይሰጠናል፡ “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” (2ኛ ጴጥ. 3፡13)። የ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” (ራእ. 21፡1) ተስፋ ቃል ለአንዳንዶች በሥልጣን ላይ ያሉ ልሒቃን ሕዝቡ ከዚህ ምድር ባሻገር ስላለው ሕይወት ብቻ እያሰላሰለ በቀላሉ እንዲገዙላቸው የፈጠሩት የቅዠት ዓለም ሊመስል ይችላል። ምንም እንኳ በዚህ ምድር ችግርና ጉስቁልና ቢገጥምህም፣ አይዞህ አንድ ቀን በሰማይ ሽልማትህን ትቀበላህ--ይሉ እንደነበረው ዓይነት።

አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የተስፋ ቃል በዚህ መንገድ አጣምመው መጠቀማቸው፣ እኛ በአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተስፋ ቃል እውነት ላይ ያለንን አመለካከት አይለውጥም። በመጨረሻዎቹ ቀናቶች ዘባቾች በተባረከው ተስፋችን ላይ ይሳለቃሉ (2ጴጥ. 3፡3-7)። ነገር ግን አስቀድሞ በትንቢት በተነገረው መሠረት የእነርሱ መዘበት መጽሐፍ ቅዱስ ለሚናገረው እውነት ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖ መታየት የሚችል ይሆናል። በዚህ ሳምንት ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔርን ሕልዎት፣ የሞት እና እንባ ፍጻሜን ጨምሮ በአስደናቂ ክብር በተሞላው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተስፋ ቃል ላይ ምልከታ እናደርጋለን። በመጨረሻም የእግዚአብሔርን ፍቅር አሸናፊነት እንቃኛለን።

በዚህ ሳምንት ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔርን ሕልዎት፣ የሞት እና እንባ ፍጻሜን ጨምሮ በአስደናቂ ክብር በተሞላው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተስፋ ቃል ላይ ምልከታ እናደርጋለን። በመጨረሻም የእግዚአብሔርን ፍቅር አሸናፊነት እንቃኛለን።

ታህሳስ 16
Dec 25

አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር


አንዳንድ የግሪክ ፍልስፍና ተከታዮች ቁስ አካላዊው ነገር በሙሉ መጥፎ ነው የሚል ጽንሰ ሀሳብ ያራምዳሉ። ይህን ተከትሎ የወደፊቱን እውነተኛ ሰማይ ተጨባጭ ከሆኑት ሰብዓዊ ፍጡራን ጋር በአንድ ማሰብ አይሆንላቸውም። በዚህ አስተሳሰብ መሠረት፣ ሰማይን መልካም አድርጎ ለመውሰድ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ ከሚገኝ ማንኛውም ጉድለት ፍጹም የጸዳና እንከን የለሽ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ አድርጎ ማሰብ ይጠይቃል። አንድ ነገር ቁስ አካላዊ ነው ከተባለ፣ መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም የሚል ጽኑ አቋም ስላላቸው፤ መንፈሳዊ ከሆነ ደግሞ ቁሳዊ መሆን አይችልም ብለው ያምናሉ። በአንጻሩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማይ በተጨባጭ የሚናገር ሲሆን፣ በኃጢአት መከሰት ምክንያት የደረሰውን ውሱንነት ግን አያካትትም።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 65፡17-25፣ ኢሳ. 66፡22-23፣ 2ጴጥ. 3፡13፣ ራእ. 21፡1-5። የእነዚህ ጥቅሶች የመጨረሻ መልእክት ምንድን ነው?



እስራኤል እንደ ሕዝብ ለእግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ቢቀጥል ኖሮ ምድር ምን መምሰል ትችል እንደ ነበር የኢሳይያስ መጽሐፍ አስደናቂ ፍንጮችን ይሰጠናል (ኢሳ. 65:17–25፣ ኢሳ. 66:22-23--ጥቅሶቹን ከዘዳ. 28 ጋር ያስተያዩ)። አጠቃላይ ከባቢያዊ ሁኔታው ከበርካታ የሕይወት መገለጫዎች አኳያ ሲታይ፣ ከኃጢአት በፊት ወደ ነበረው የቀደመ አምላካዊ ዕቅድ ይበልጥ እያደገ መሄድ የሚችል ነበረ። ይሁን እንጂ ይህ ዕቅድ እንደተጠበቀው ሊሳካ አልቻለም ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ አዲስ ዕቅድ የተወጠነ ሲሆን፣ አሁን ዕቅዱ አይሁዳውያንን እና አሕዛብን በአንድ ባቀፈችው ቤተ ክርስቲያን የተወጠነ ነበር (ማቴ. 28፡18-20፣ 1ጴጥ. 2፡ 9)። ስለዚህ የኢሳይያስ ትንቢቶች ከቤተ ክርስቲያን አኳያ እንደገና መነበብ ነበረባቸው (2ጴጥ. 3፡13፣ ራእ. 21፡1-5)።

“በመጽሐፍ ቅዱስ፣ የዳኑት የሚወርሱት--‘አገር’ ተብሎ ይጠራል (ዕብ. 11፡ 14-16)። በዚያም ሰማያዊው እረኛ መንጋውን ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራል። የሕይወት ዛፍ በየወሩ ፍሬ የሚሰጥ ሲሆን፣ የዛፉ ቅጠሎች ለሕዝቦች ፈውስ ናቸው። እንደ መስታወት የጠሩ ጅረቶች ያለማቋረጥ የሚፈሱባት ይህች ከተማ በግራና ቀኝ በጌታ ለዳኑ በተዘጋጁ መንገዶች ላይ ጥላ የሚሆኑ ዛፎች አሏት። ለጥ ካሉት መስኮችና ውበት ከተላበሱት ኮረብቶች ባሻገር፣ የግዙፎቹ ተራሮች ጫፎች ይታያሉ። ከእነዚያ ሕያው ጅረቶች ጎን ለጎን በተሰራፉ ሰላማዊ መስኮች የረጅም ዘመናት መንፈሳዊ ጉዞ መንገደኞችና ተንከራታች የእግዚአብሔር ሕዝቦች መኖሪያ ቤታቸውን ያገኛሉ።”--—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 675.

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ዘላለማዊ ተስፋ የሌላቸው በርካታ ዓለማዊ ጸሐፊያን የሰው ሕልውና ትርጉም የለሽ መሆኑን የሚያወሱ ብርቱ የሰቆቃ ድምጾች አሰምተዋል። ምንም እንኳ የወደፊቱን አስመልክቶ የተሳሳተ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ ነገር ግን ተስፋ ከሌለ ሕይወት ትርጉም የለሽ ከመሆኗ አኳያ ከሚያነሡት ነጥብ ጋር ለመግጠም አዳጋች የሚሆነው ለምንድን ነው? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ላይ ይዘው ይቅረቡ።

፡ ታህሳስ 17
Dec 26

በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ


አንዳንድ ሰዎች ሰማይ የእግዚአብሔር መቅደስ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ነገር ግን የራእይ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ዙፋንና የብርጭቆው ባሕር ስለሚገኙበት በራሷ በአዲሲቱ የሩሳሌም ቅጥር ውስጥ ስላለ መቅደስ ይጠቅሳል (ራእ. 4:2–6፣ ራእ. 7:9–15፣ ራእ. 15:5–8)። በዚያም ከሕዝብ ሁሉ፣ ከነገድ፣ ከወገንና ከቋንቋዎች የተውጣጡ እጅግ ብዙ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ለዘላለም ያመልካሉ (ራእ. 7፡9-17)። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ራእ. 7፡9-15 እና ራእ. 21፡3፣22። እነዚያ የዳኑ እጅግ ብዙ ሕዝቦች እግዚአብሔርን “ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል” (ራእ. 7፡15) በሚል የቀረበውን መግለጫ ዮሐንስ “በከተማይቱ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም” (ራእ. 21፡22) ሲል ካሰፈረው ሀሳብ ጋር እንዴት ማስማማት እንችላለን?



ሰማያዊው መቅደስ (ቤተ መቅደስ) የሰማይ ሰራዊት ሁሌም እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ስፍራ ነው። ነገር ግን ኃጢአት መከሰቱን ተከትሎ ያ መቅደስ ለሰው ልጆች መዳን አገልግሎት የሚሰጥበት ስፍራም ሆነ። “የኃጢአት ችግር ሲያከትም፣ ሰማያዊው መቅደስ እንደገና ወደ መጀመሪያ ሥራው ይመለሳል። ባለ ራእዩ ዮሐንስ ከእንግዲህ የከተማዋ መቅደስ ሁሉን ቻይ አምላክና በጉ በመሆኑ በከተማዋ ቤተ መቅደስ አለማየቱን በራእ. 21፡22 ይነግረናል።

ነገር ግን ይህ አነጋገር ፍጥረታቱ በፊቱ ቀርበው ከእርሱ ጋር የተለየ አምልኮ የሚያደርጉበት ጊዜ አያስፈልጋቸውም ማለት ይሆን? በፍጹም!”—Richard M. Davidson, “The Sanctuary: ‘To Behold the Beauty of the Lord,’” in Artur Stele, ed., The Word: Searching, Living, Teaching, vol. 1 (Silver Spring, MD: Biblical Research Institute, 2015), p. 31. የራእይ መጽሐፍ ለሚመለከው አምላክና እርሱን ለሚያመልኩት ፍጥረታት ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ይህ ሰማያዊ አምልኮ እግዚአብሔርንና በጉን ያማከለ ነው (ራእ. 5፡13፣ ራእ. 7፡10)። እንደ ሁልጊዜ እና መሆንም እንዳለበት፣ ክርስቶስ የአምልኮ ማዕከል ነው።

እግአብሔርን የሚያመልኩት ወገኖች “ ‘ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል’ ” (ራእ. 7፡14)። እነርሱ የመዋጀትና የመለወጥ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ኃይል ሕያው ምስክሮች ናቸው። ስለ ማንነቱና ስላደረገላቸው ነገር የምስጋና ዝማሬ ያሰማሉ። “‘እነሆ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል’ ” (ራእ. 21፡

3)። እነዚህ ጥቅሶች አያሌ ሌሎች ጥቅሶችን ያንጸባርቃሉ (ኤር. 32:38፣ ሕዝ. 37:27፣ ዘካ. 8:8፣ ዕብ. 8:10)። እግዚአብሔር አምላካችን እኛም ሕዝቦቹ አንሆናለን የሚለው ይህ መልእክት ለእኛ አሁንም በዚህ ምድር ላለነው ምን ትርጉም አለው? ይህን አስደናቂ እውነት በተግባር ላይ የምናውለው እንዴት ነው?

፡ ታህሳስ 18
Dec 27

በእግዚአብሔር ሕልዎት ፊት


መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር “ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል” (1ጢሞቴ. 6፡16) “እርሱን ያየ ማንም የለም” (ዮሐ. 1:18፣ 1ዮሐ. 4:12)። ይህ ማለት--በሰማይ ቅዳሳን እግዚአብሔር አብን ፈጽሞ አያዩትም ማለት ነው? በጭራሽ! በሰማይ ያሉ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ያዩታል። እግዚአብሔርን ማየት አለመቻል የሚያያዘው ከውድቀት በኋላ ካለው ሰብዓዊ ፍጡር ጋር መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በማስረጃነት መቅረብ ይችላሉ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5፡8፣ 1ዮሐ. 3፡2-3፣ ራእ. 22፡ 3-4። እግዚአብሔርን ማየት ስለሚያስገኘው ከፍተኛ መብትና ጥቅም ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



“እርሱን ያየ ማንም የለም” ብሎ የጻፈልን ራሱ ዮሐንስ (ዮሐ. 1፡18፣ 1ዮሐ. 4፡ 12) “እናየዋለን” (1ዮሐ. 3፡2-3) “ፊቱን” እናያለን (ራእ. 22፡3-4) ሲል በይፋ ይነግረናል። እነዚህ ጥቅሶች የሚናሩት ስለ እግዚአብሔር አብ ነው ወይስ ስለ ክርስቶስ የሚሉ ሞጋች ሀሳቦች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ከራሱ ከክርስቶስ መግለጫ አንጻር ጥርጣሬዎች ሁሉ ይቀረፋሉ። “ ‘ልባቸው ንጹህ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና’ ” (ማቴ. 5፡8)። የተዋጁት እግዚአብሔርን በቤተ በመቅደሱ ማምለካቸው እንዴት ያለ መብትና ጥቅም ያስገኝላቸዋል! ነገር ግን ከሁሉ የላቀው መብትና ጥቅም ፊቱን ማየታቸው ይሆናል። “የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከአብ እና ወልድ ጋር ግልጽ የሆነ ኅብረት የመፍጠር ዕድል አላቸው። “አሁን የምናየው በመስታወት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው’ (1ቆሮ. 13፡12)። የእግዚአብሔርን ገጽታ የምናየው እንደ መስተዋት ውስጥ ነጸብራቅ ሲሆን፣ ይኸውም በተፈጥሮ ውስጥ እና ከሰዎች ጋር ካለው መስተጋብር አኳያ ነው። ያን ጊዜ ግን ካለ መጋረጃ፣ ፊት ለፊት እናየዋለን። በእርሱ ፊት ቆመን የፊቱን ክብር እናያለን።”-Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 676, 677.

በዛሬው ጥናት በቀረቡ አንዳንድ ጥቅሶች በንጽህና እና እግዚአብሔርን በማየት መካከል ያለውን ትስስር ያስተውሉ። “ ‘ልባቸው ንጹህ የሆነ’ ” እግዚአብሔርን ያዩታል፤ “እርሱ ንጹሕ እንደሆነ ራሱን ያነጻል” (1ዮሐ. 3፡3)። እኛ ለሰማይ እንድንዘጋጅ የሚረዳንን ሥራ እግዚአብሔር አሁን በእኛ ውስጥ መሥራት እንዳለበት እነዚህ ጥቅሶች ይገልጻሉ።

ምንም እንኳ በስተመጨረሻ የመንግሥተ ሰማይ ወራሾች መሆናችን በየሱስ ሞት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ እኛን ለዘላማዊው ቤታችን እንድንዘጋጅ ሊረዳን በሚችለው የመንጻት ሂደት ውስጥ አሁን በዚህ ምድር እናልፋን። ለመንጻት ሂደት ዋንኛው ነጥብ ቃሉን መታዘዝ ነው። ጥቅሱን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 1፡22። ጥቅሱ በመታዘዝ እና በመንጻት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ያሳየናል? እኛን ሊያነጻ የሚችለው መታዘዝ ምንድን ነው? በተለይ ጴጥሮስ መታዛችን ተገልጦ ስለሚታይበት ሁኔታ ምን ይላል?

፡ ታህሳስ 19
Dec 28

ከእንግዲህ ሞት እና እንባ የለም


ነፍስ ለዘላለም በገሐነም እሳት እየተቃጠለች ትኖራለች እንጂ አትሞትም የሚለው ንድፈ ሀሳብ፣ አዲስ በሆነው ሰማይ እንዲሁም በአዲሲቱ ምድር “ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም’ ” (ራእ. 21፡4) ከሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ጋር ይጣረሳል። ለዘላለም የሚነደው የገሐነም እሳት ንድፈ ሀሳብ እውነት ቢሆን ኖሮ “ሁለተኛው ሞት” ኃጢአትንና ኃጢአተኞችን በዘላለማዊ የሐዘን እና ልቅሶ ሲኦል ውስጥ አጉሮ ከማስቀመጥ ውጪ ኃጢአትን ከዩኒቨርስ ማስወገድ አይችልም ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ አጥናፈ ሰማይ ወይም ዩኒቨርስ ፈጽሞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀደመ ንጽህናው አይመለስም ማለት ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ፍጹም የተለየ ሥዕል ስለሚሰጠን ለጌታ ምስጋና ይግባው! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 25፡8፣ ራእ. 7፡17፣ ራእ. 21፡4።

በዚህ ዓለም ፈተና እና መከራ ቢደርስብንም ጥቅሶቹ ምን ዓይነት መጽናናትና ተስፋ ሊሰጡን ይችላሉ?



ሕይወት በጣም ከባድ፣ ኢፍትሐዊና ጨካኝ ልትሆን ትችላለች። አንዳንድ በጣም የምንወዳቸውን ወገኖች በጨካኙ ሞት ተነጥቀናል። ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በስውር ወደ ሕይወታችን ዘልቀው ገብተው ስሜታችንን ከጎዱ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ ከፊታችን ገሸሽ ይላሉ። በምንወደውና በምንተማመንበት ሰው መከዳት ምንኛ አስፈሪ ነው! በሐዘን በተደቆሰ ልብ ውስጥ ሆነን ሕይወት ምን ዋጋ አለው--ብለን ልንጠይቅ የምንችልባቸው በርካታ ጊዜያቶች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ሐዘናችን ምንም ይሁን ምን--እግዚአብሔር አምላክ በተቻለ መጠን በርካታ እንባዎችን ከጉንጮቻችን ለማበስ ምንጊዜም ጉጉ ነው። ነገር ግን ሞት፣ ሐዘን እና ልቅሶ እስከሚያከትሙበት እስከዚያች በክብር የተሞላች ዕለት ድረስ አልፎ አልፎ ሊገጥመን የሚችል ልብ ሰባሪ እንባ መውረዱን ይቀጥላል (ራዕ. 21፡1-5)።

በመጨረሻው ፍርድ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው በፍትሕ እና በፍቅር ይዳኛል። በክርስቶስ የሞቱ የምንወዳቸው ሰዎች ሁሉ ለዘላለም ከእኛ ጋር ለመኖር ከሞት ይነሣሉ። ለዘላለማዊው ሕይወት ያልተገቡ፣ ደስ ሊሰኙበት በማይችሉት ሰማይ ወይም ለዘላለም በሚቃጠሉበት የገሐነም እሳት ውስጥ አይኖሩም፤ ይልቁንም በመጨረሻ መኖር ያቆማሉ። እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው ፍትሐዊ አምላክ መሆኑ ከሁሉ የላቀው መጽናኛችን ነው። በመጨረሻ ሞት ሲሸነፍና ሕልውናው ሲያከትም የተዋጁት “ ‘ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ?’ ” (1ቆሮ. 15:54-55) ሲሉ በደስታ ድምፆቻቸውን ከፍ አድርገው ያሰማሉ።

ጌታ በሚፈጥረው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም’ ” (ኢሳ. 65:17) ሲል ቃል ገብቶልናል። ይህ ማለት በመንግሥተ ሰማይ የማስታወስ ኃይላችን ደካማ ይሆናል ሳይሆን--ይልቁንም ያለፈው ጊዜ፣ ፍጻሜ በሌለው ሰማያዊ ደስታ ላይ ተግዳሮት አይሆንም እንደ ማለት ነው። በዚህ ምድር በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ባለው ኢፍትሐዊ ጥፋት ያልተሰማው ማን ነው? በተለይ ዕኩይ ጊዚያቶች ሲገጥሙን፣ በእግዚአብሔር ስለ መታመን መማር ብሎም በአምላካዊው በጎነትና ፍቅር ሐሴት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

፡ ታህሳስ 20
Dec 29

ስሙ በግንባራቸው ይጻፋል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 22፡3-5። የእግዚአብሔር ስም በግምባራቸው ላይ ከሚጻፍባቸው ሰዎች መካከል እንደምንሆን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?



ከሉሲፈር አመጽ እንዲሁም ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ እግዚአብሔር ሁለቱን ኃጢአተኞች ማጥፋት ይችል ነበር። እርሱ ለፍጥረታቱ ምክንያታዊ ያልሆነ ፍቅሩን እንደ መግለጹ፣ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ሁሉ የሚቀበሉትን ለማዳን በምኅረት የተሞላ ዕቅድ አዘጋጀ። ይህ “የደኅንነት ዕቅድ” በመባል የሚታወቅና ምድር ከመፈጠሯ አስቀድሞ የነበረ (ኤፌ. 1:3-4፣ 2ጢሞቴ. 1:9፣ ቲቶ 1:2፣ ራእ. 13:8) አምላካዊ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤደን ለሰው የተሰጠው-ሰው በኃጢአት እንደወደቀ ነበር። ከዚያም በዕብራውያኑ የቤተ መቅደስ አገልግሎት ምሳሌዎችና ጥላዎች ይበልጥ ተገልጦአል (ዘፀ. 25)። በመጨረሻም በየሱስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ በሙላት መገለጽ ቻለ (ሮሜ 5)።

የሱስ በሠራቸው ሥራዎች ላይ የተመረኮዘውን በመስቀል ላይ የሰጠውን ታላቁን ስጦታ በእምነት ለሚቀበሉ ሁሉ--የደኅንነት ዕቅድ አስኳል የዘላለም ሕይወት የተስፋ ቃል ነው። መዳን ከመስቀል በፊትም ሆነ በኋላ ሁሌም በእምነት እንጂ በሥራ ሆኖ አያውቅም። ሆኖም አብልጠን በጎ ሥራ መሥራታችን የመዳናችን መገለጫ ነው።

ጳውሎስ ክርስቶስ ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ አስቀድሞ ስለነበረው አብርሃም እንዲህ ሲል ጽፏል፡ “አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ፣ የሚመካበት ነበረው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት በመመካት አይችልም። መጽሐፍስ ምን ይላል? ‘አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት’ ” (ሮሜ. 4:2-3)። ጽድቅ የሚገኘው በእምነት መሆኑን እናስተውል ዘንድ እነዚህ ጥቅሶች እንዴት ይረዱናል?



የሱስን እንደ ግል አዳኛችን ከተቀበልን፣ ራሳችንን ለእርሱ ካስገዛን፣ ዛሬ በእርሱ ያለንን አዲስ ሕይወት ጨምሮ የተስፋ ቃሉን የግላችን ካደረግንና በሌላ በማንም ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ሥራ ላይ ከተደገፍን--ለመዳናችን ማረጋገጫ አለን ማለት እንችላለን። አብርሃም ማመኑ፣ ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት ሁሉ በተመሳሳይ ለእኛም እንዲሁ ነው። እንግዲህ ስሙ በግንባራችን ላይ ይጻፋል ማለት ፍቺው ይኸው ነው። አሁን ስሙ ግንባራችን ላይ ከተጻፈልንና ፊታችንን ከእርሱ የማንመልስ ከሆነ፣ በአዲሶቹ ሰማያት እና በአዲሲቱ ምድርም እንዲሁ ይጻፋል።





፡ ታህሳስ 21
Dec 30


ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Read Ellen G. White, “The Controversy Ended,” pp. 674–678, in The Great Controversy; “The Earth Made New,” pp. 133–145; “Heaven Is a School,” pp. 146–158; “It Will Not Be Long,” pp. 159–166; “Heaven Can Begin Now,” pp. 167–176; “The Music of Heaven,” pp. 177–184; “A Call for Us to Be There,” pp. 185–192, in Heaven.

የክርስቶስ መስቀል የተዋጁት ወገኖች ለዘላለም የሚያጠኑት ሳይንስ እና የሚያዜሙት መዝሙር ይሆናል። በዚያ በከበረ ክርስቶስ ውስጥ ያን የተሰቀለ ክርስቶስ ያዩታል። ሕልቁ መሳፍርት ዓለማትን የፈጠረውና ግዙፉን የጠፈር ግዛት ደግፎ የያዘው የእጹብ ድንቅ ኃይል ባለቤት፣ ተወዳጁ አምላክ፣ የሰማይ ንጉሥ፣ ኪሩቤል እና አንጸባራቂው ሱራፌል ደስ የሚሰኙበትና የሚወዱት እርሱ--የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር ለማቅናት ራሱን ትሑት ያደረገው፣ የኃጢአትን በደለኝነትና ውርደት የተሸከመው፣ የአባቱ ፊት ከእርሱ የተሸሸገበት፣ የጠፋው ዓለም ዋይታ ልቡን የሰበረውና ሕይወቱን በቀራኒዮ መስቀል የቀጠፈው ጌታ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይችልም። ያ የሁሉም ዓለማት ፈጣሪ እና ዳኛ ለሰው ባለው ፍቅር የተነሣ ክብሩን ትቶ ራሱን ማዋረዱ ዩኒቨርስ ለዘላለም እንዲደነቅበት ብሎም ሲወደው እንዲኖር ያደርጋል።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 651.

“ታላቁ ተጋድሎ ተጠናቅቆአል። ኃጢአትና ኃጢአተኞች ከዚህ በኋላ የሉም። መላው አጥናፈ ሰማይ ከኃጢአት እርክስና ነጽቶአል። አንድ ወጥ ስምሙ የደስታ ጸዳል በግዙፉ የፍጥረታት የልብ ትርታ ውስጥ ይደመጣል። ሁሉን ከፈጠረው ከእርሱ በመላው አጥናፈ ሰማይ ግዛት--ሕይወት፣ ብርሃን እና ደስታ ይፈሳል። ከኢምንቱ አቶም እስከ ታላቁ ዓለም ያሉ ሕይወት ያላቸው እና የሌላቸው ፍጥረታት አንዳችም ጥላ ባላጠላ ውበታቸው እና ፍጹም ደስታቸው እግዚአብሔር ፍቅር ነው ሲሉ ያውጃሉ።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 678.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1. በርካታ ዓለማዊ ክርስቲያኖች ይህ ዓለም ለዘላለም እንደሚኖር የሚመስል ሕይወት ይኖራሉ (ሉቃ. 12፡16-21)። ምድራዊ አስተሳሰባችንን ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ሰማያዊ ነገሮች ጋር ሚዛናዊ አድርገን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው? የሱስ በሉቃ. 12 ካስጠነቀቀን ነገር መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

2. ሰማይ የሚጀምረው እዚሁ ከሆነ፣ ቤታችን እና የግል ሕይወታችን ሰማያዊው መርኅ በጥቂቱ የሚገለጽት አድርገን ለመለወጥ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

3. በእሁድ ትምህርት መጨረሻ ላይ በተጠየቀው ጥያቄ ላይ ትኩረት ያድርጉ። በዘላለም ሕይወት የማያምኑ ሰዎች አፍራሽ አመለካከት በስተጀርባ ያለው አመክንዮ ምንድን ነው? በሌላ በኩል፣ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ ባይገለጥባቸውም “ደስተኛ” ሕይወት የሚመሩ ይመስላሉ። ይህን እንዴት የሚያደርጉ ይመስሎታል? ማለትም ከዚህ ሕይወት ባሻገር አንዳች የሚጨበጥ ተስፋ ሳይኖራቸው?



በትምህርቱ ውስጥ የተጠቀሰ አዲስ ቃል --> መንጽሔ፦ (Purgatory)




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL