የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከታህሳስ 8 -14

13ኛ ትምህርት

Dec 17–23




የፍርዱ ሂደት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 25:31–46፣ ዳን. 7:9–14፣ 1ቆሮ. 6:2-3፣ 2ጴጥ. 2:4–6፣ ሚል. 4:1፣ ራእ. 21:8።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራን፡፡ የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናቸው ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” (2ቆሮ. 5፡10)

ቅ ዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ካስቀመጧቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የፍርድ እውነታ ነው። እግዚአብሔር በዓለም ላይ ይፈርዳል። በዚህ ዙሪያ በብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን የምናገኛቸው ጥቅሶች በርካታ ከመሆናቸው በተጨማሪ የማያሻሙ ናቸው። ዛሬ በዚህ ምድር የተጓደለው ፍትሕ አንድ ቀን ብይን ያገኛል። “ ‘በዕውቀቱ ፍጹም የሆነው’ ” (ኢዮ. 37፡16) እግዚአብሔር፣ የልባችንን ስውር ሀሳብ (መክ. 12፡14፣ ኤር. 17፡10) ጨምሮ “ሁሉን ነገር የሚያውቅ” (1ዮሐ. 3፡20) አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ማንኛውንም ነገር ከሰው ልንደብቅ ብንችልም እንኳ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ሊሰወር የሚችል አንዳችም ነገር የለም። እርሱ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወት ለራሱ ለማወቅና ውሳኔ ላይ ለመድረስ ችሎት ላይ ተቀምጦ ግራ ቀኙን ማድመጥ እንደማያስፈልገው ይህ እውነታ ያመለክታል።

የእግዚአብሔር ፍርድ በሰማይም ሆነ በምድር ስላሉት ፍጥረታቱ ሲል እርሱ የሚሰጠው መለኮታዊ ብይን ነው። ሉሲፈር የአመፃ ተግባሩን በሰማይ ከጀመረ በኋላ ወደዚህች ምድር በማሰራጨቱ ምክንያት ይህ ሂደት የራሱ የሆነ ሰማያዊ ታሪካዊ ተፈጥሮ አለው (ራእ. 12፡7-9)። በዚህ ሳምንት የመጨረሻውን ጊዜ የፍርድ ሂደት ከራሱ ሦስት ዋና ዋና ቅደም ተከተሎች ጋር እንመለከታለን፡ የቅድመ ምጽአቱ ፍርድ፣ የሺህ ዓመቱ ፍርድ እና አምላካዊው ፍርድ። አጠቃላዩ ሂደት ፍጻሜ የሚያገኘው በጻድቃን የጽድቅ ባለቤት መሆን እና የኃጥአን ሁለተኛ ሞት ነው።

ታህሳስ 9
Dec 18

የመጨረሻው ፍርድ


ለብዙዎች፣ የፍርድ ጽንሰ ሀሳብ ኩነኔ የሚል ፍቺ አለው። ምንም እንኳ ይህ የሂደቱ አካል ቢሆንም፣ በዚያው የፍርድ ሂደት የጻድቃን ጽድቅም እንዲሁ ስለሚረጋገጥ፣ የፍርድ ጽንሰ ሐሳብ አዎንታዊ ጎን እንዳለውም መዘንጋት የለብንም። እንደ እውነቱ ከሆነ የዳንኤል መጽሐፍ በመጨረሻ “ ‘ለልዑሉ ቅዱሳን’ ” (ዳን. 7፡22) እንደሚፈረድላቸው ይናገራል። እምካዊው ፍርድ ሁለቱንም በብሉይ ኪዳን የሚገኙ መርኅዎች ያካትታል፡ “ ‘ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት’ ” (1ነገሥ. 8፡32)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡31-46 እና ዮሐ. 5፡21-29። ክርስቶስ በመጨረሻው ፍርድ ወቅት ስለሚሰጡት ሁለቱ ብይኖች ማለትም ኩነኔ እና ጽድቅ ጽንሰ ሀሳቦችን ያመለከተበት መንገድ ምን ይመስላል?



አንዳንዶች “ ‘አይፈረድበትም’ ” (ዮሐ. 3፡18) እና “ ‘ወደ ፍርድ አይመጣም’ ” (ዮሐ. 5፡24) የሚሉት አገላለጾች በክርስቶስ ያሉ ጭራሹኑ አይፈረድባቸውም የሚል ፍቺ አላቸው ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አገላለጾች አማኞች በፍርድ ወቅት ኩነኔ እንደማይደርስባቸው ያመለክታሉ። ስለዚህ ጥቅሶቹ፡ “ ‘አይኮነንም’ ” እና “ ‘ወደ ኩነኔ አይመጡም’ ” በሚል ሊስተዋሉ ይገባል። በአጭሩ ለመናገር የወደፊቱ ማንነታችን በዛሬው ሕይወታችን ላይ የተወሰነ ነው። በክርስቶስ ያሉ በፍርድ ወቅት አስቀድሞ የተረጋገጠ ጽድቅ ያላቸው ሲሆን፣ በክርስቶስ ያልሆኑ ግን በዚያው በኩነኔ ውስጥ ይቆያሉ። ክርስቶስ ስለ ፍርድ ሲገልጽ (ማቴ. 25፡31-46) በዚያን ወቅት የሚገኙት ፍየሎች (ኃጥአን) ብቻ ሳይሆኑ በጎች (ጻድቃን) ጭምር እንደሆኑ ጠቅሷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ተናግሯል፡ “ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል” (2ቆሮ. 5፡10)።

ስለ ፍርዱ ስናሰላስል ሳለ በጸጋ እንደዳንን (ኢሳ. 55፡1፣ ኤፌ. 2፡8-10)፣ በእምነት እንደ ጸደቅን (ዘፍ. 15፡6፣ ሮሜ 5፡1) እና ማንኛውም ሥራ ወደ ፍርድ እንደሚመጣ (መክ. 12፡14፣ ማቴ. 25፡31-46፣ ራእ. 20፡11-13) ማስታወስ ይኖርብናል። የፍርዱ ሂደት መሠረት በዐሥርቱ ትእዛዛት በአጭሩ የተገለጸው አምላካዊ ሕግ ነው (መክ. 12፡13-14፣ ያዕ. 1፡25፣ 2፡8-17)። ሥራችን በሐቅ ላይ የተመሠረተ የመዳን ተሞክሮአችን ውጪያዊ ማስረጃ እና በፍርድ ወቅት የምንገመገምበት አላባ ነው። ያስታወሱ፡ አንዳንዶች እንዲድኑ ሌሎች ደግሞ እንዲጠፉ የሚወስን የዘፈቀደ ድንጋጌ በእግዚአብሔር ዘንድ የለም። እያንዳንዱ ሰው ለራሱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የግል ኃላፊነት አለበት።

በመጨረሻ፣ ፍርድ እግዚአብሔር እኛን ለመቀበል ወይም ለመቃወም የሚወስንበት ጊዜ ሳይሆን፤ ነገር ግን እኛ እርሱን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል አንዴ ውሳኔ አድርገን ከጨረስን በኋላ፣ ምርጫችን ከሥራችን አኳያ የሚታይበት ነው።

ታህሳስ 10
Dec 19

ቅድመ ዳግም ምጽአት ፍርድ


ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት ያለው የፍርድ ጽንሰ ሀሳብ ወይም “ቅድመ ዳግም መጽአት” ፍርድ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ይገኛል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 7፡9-14፣ ማቴ. 22፡1-14፣ ራእ. 11፡ 1፣ 18-19፣ ራእ፣ 14፡6-7። እነዚህ ጥቅሶች ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ገቢራዊ በሚሆነው ሰማያዊ የፍርድ ምርመራ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ብርሃን የሚፈነጥቁት እንዴት ነው? የዚህ ፍርድ አንደምታ ምንድን ነው?



የቅድመ ዳግም ምጽአቱ የፍርድ ምርመራ ጽንሰ ሀሳብ በሦስት መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ላይ የተመሠረተ ነው። አንደኛው--የሞቱ ሰዎች በሙሉ፣ ማለትም ጻድቃን ወይም ኃጥአን እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ ምንም ነገር ሳያውቁ በመቃብር ውስጥ ይቆያሉ (ዮሐ. 5፡25–29)። ሁለተኛው--በሁሉም ሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የሚሰጠው አጽናፈ ዓለምን ያካተተ ፍርድ (2ቆሮ. 5፡10፣ ራእ. 20፡11-13)።

ሦስተኛው--የመጀመሪያው ትንሣኤ ለጻድቃን የተባረከ ሽልማት የሚያቀዳጅ እና ዳግም ምጽአቱ በኃጥአን ላይ ዘላለማዊ ሞት የሚያስከትል ይሆናል (ዮሐ. 5:28፣ 29፣ ራእ. 20:4–6፣ 12–15)። ይህ ማለት ሰብዓዊ ፍጡራን የሚዳኙ ከሆነ፣ ከትንሣኤ በፊት መዳኘት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም በትንሣኤ ወቅት የመጨረሻውን ሽልማታቸውን ነው የሚቀበሉት።

የዳንኤል መጽሐፍ የዚያን ቅድመ ዳግም ምጽአት የፍርድ ምርመራ ጊዜ እና ባህሪ ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል። በ2,300 ትንቢታዊ ቀናት መጨረሻ--1844-ሰማያዊው ቤተ መቅደስ ይነጻና (ዳን. 8፡14፣ ዕብ. 9፡23--ያስተያዩ) ቅድመ ዳግም ምጽአቱ የፍርድ ምርመራ ይጀመራል (ዳን. 7፡9-14)። ከዚያም “ ‘ለልዑሉ ቅዱሳን’ ” ይፈርድላቸዋል (ዳን. 7፡22)። ይህ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የምሥራች ነው። በማቴ. 22፡1-14 የሱስ የሰርጉ ሥነ ስርዓት ከመጀመሩ በፊት በድግሱ ላይ ስለ ተጠሩ እንግዶች ምርመራ ተናግሯል። የቅድመ ዳግም ምጽአቱ የፍርድ ምርመራ በእግዚአብሔር ቤት “ ‘የሚያመልኩትን ቁጠር’ ” (ራእ. 11፡1) እንዲሁም “ ‘የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል’ ” በሚሉ መግለጫዎች በራእይ መጽሐፍ ቀርቧል (ጥቅሶቹን ያስተያዩ--ራእ14፡6-7፣ ራእ. 14፡14-16)። በሰማይ እየተሰጠ ስላለው ፍርድ ማወቃችን አኗኗራችን ላይ ምን ተጽእኖ ሊያሳድር ይገባል?

በምድራዊው ታህሳስ 11
Dec 20

የሺህ ዓመቱ ፍርድ


በዳግም ምጽአቱ ወቅት (1) በሕይወት ያሉ እና ከመቃብር የተነሡ ጻድቃን “ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል” (1ተሰ. 4፡16-17) ከእርሱ ጋር በደመና ይነጠቃሉ (2) ሁሉም ጻድቃን እርሱ ራሱ በሰማይ ወዳዘጋጀላቸው “ ‘ብዙ መኖሪያ’ ” (ዮሐ. 14፡1-3) ስፍራ ይኖሩ ዘንድ ይወሰዳሉ፤ (3) አዲሲቱ የሩሳሌም ወደዚህ ምድር ወርዳ ዘላለማዊ የቅዱሳን መኖሪያ የምትሆነው በሺህ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ብቻ ይሆናል (ራእ. 21፡1-3፣ 9-11)። በመሆኑም በሺህ ዓመቱ ውስጥ ይህች ምድር ባድማ ሆና ስትቀጥል--ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ይነግሣሉ (ኤር. 4፡23፣ ራእ. 20፡4)።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 6፡2-3፣ ራእ. 20፡4-6፣11-13። ቅዱሳን በሺህ ዓመቱ ፍርድ ላይ ተሳትፎ የሚኖራቸው ለምንድን ነው?



አጠቃላዩ የፍርድ ሂደት (1) እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ፍትሐዊ አምላክ እንዳልሆነ ተደርጎ በሰይጣን የተቀነባበረውን ክስ መርምሮ የእግዚአብሔርን ባህሪ ማሳየት፤ (2) ለጻድቃን የተሰጠው የጽድቅ ሽልማት አድሎ የሌለበት መሆኑን ማረጋገጥ፤ (3) በዐመጸኞች ላይ የተሰጠውን ቅጣት ፍትሐዊነት ማሳየት፤ እና (4) በዩኒቨርስ ሌላ የአመጻ ተግባር እንዳይዛመት ሊያደርጉ የሚችሉ ጥርጣሬዎችን በሙሉ ማስወገድ ናቸው። በጻድቃን ቅድመ ምጽአት የፍርድ ምርመራ ላይ ተካፋይ የሚሆኑት የሰማይ ሰራዊት ብቻ ናቸው (ዳን. 7፡ 9-10)። ነገር ግን በአንድ ሺህ ዓመቱ የዐመጸኞች እና የወደቁ መላእክት ፍርድ ላይ ራሳቸው ቅዱሳንም ተካፋዮች ይሆናሉ (1ቆሮ. 6፡3፣ ይሁዳ 6፣ ራእ. 20፡ 4-6)።

1844 ላይ “ ‘ዙፋኖች ተዘረጉ… የፍርድ ጉባዔ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ’ ”ከዚያም የቅድመ ምጽአቱ የፍርድ ምርመራ ተጀመረ (ዳን. 7፡9-10)። ሆኖም የሺህ ዓመቱ ፍርድ የሚጀምረው ቅዱሳን ወደ ሰማይ ከተወሰዱና በዙፋኖች ላይ ከተቀመጡ በኋላ ነው። ከዚያም እንደገና የሰማይ መጻሕፍት ተከፍተው “ሙታንም በመጽሐፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው ተፈረደባቸው” (ራእ. 20፡4፣12)። ይህ ሂደት ቅዱሳን የሰማይ መዝገቦችን የሚገመግሙበትንና በሁሉም ጉዳዮች የእግዚአብሔርን ፍትሐዊ አሠራር የሚያዩበትን ዕድል ይሰጣቸዋል። እርሱ መላውን ሰብዓዊ ፍጡር በየግል ውሳኔው መሠረት መክፈል ብቻ ሳይሆን ለምን ይህን አሠራር እንደሚከተል ጭምር ግልጽ አድርጎ ያስረዳቸዋል።

በመቃብር ያንቀላፉ የጠፉ ዐመጸኞች ሁለተኛውን ሞት ለመጋፈጥ ከሞት ከመነሣታቸው አስቀድሞ የዳኑት በፍርድ ሂደቱ ውስጥ ተካፋይ መሆናቸውና እኛም የእግዚአብሔርን ፍትሐዊነት ሳናይ ማንም የማይቀጣ መሆኑ፣ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን ያስተምረናል? መልስዎን በሰንበት ትምህርት ጥናት ላይ ይዘው ይቅረቡ።

፡ ታህሳስ 12
Dec 21

የመጨረሻው ፍርድ


በመካከለኛው ዘመን እግዚአብሔርን ምሕረት የለሽ፣ ቀጪ ዳኛ አድርጎ የማቅረብ ከፍተኛ ዝንባሌ ነበር። ዛሬ ደግሞ ፈጽሞ ልጆቹን የማይቀጣ አፍቃሪና ልል አባት አድርጎ የመሳል ሁኔታ ይታያል። ሆኖም ፍትሕ የጎደለው ፍቅር ወደ ብጥብጥና ሥርዓተ ዐልበኝነት የሚያመራ ሲሆን፣ ፍቅር ዐልባ ፍትሕ ደግሞ ጨቋኝና አምባ ገነን ይሆናል። የአምላካዊው ፍርድ ሂደት ፍጹም የሆነ የፍትሕና ምኅረት ዉሁድ ሲሆን፣ እነዚህ ሁለቱም ምክንያታዊ ካልሆነ ፍቅሩ ይመነጫሉ።

ይህ ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ ቅጣት፣ በሰው ልጆች ታሪክ የእግዚአብሔር የመጨረሻና የማይቀለበስ የፍርድ ርምጃ ነው። ከዚህ ቀደም ዉሱን የቅጣት ፍርዶች ተሰጥተው ነበር። ለአብነት ያህል ሰይጣንና ዐመጸኛ መላእክቱ ከሰማይ በተባረሩበት ወቅት (ራእ. 12፡7-12)፣ አዳምና ሔዋን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ሲባረሩ (ዘፍ. 3)፣ የጥፋት ውሃ (ዘፍ. 6-8)፣ የሶዶም እና ጎሞራ ውድመት (ዘፍ. 19፣ ይሁዳ 7)፣ በግብጽ የበኩር ልጆች ላይ የደረሰ መቅሰፍት (ዘፀ. 11-12) እንዲሁም የሐናንያ እና ሰጲራ ሞት (ሐዋ. 5፡1-11) ናቸው። ከዚህ አኳያ በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ በዐመጸኞች ላይ የቅጣት ፍርድ መኖሩ አያስገርምም።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 2:4–6 እና 2ጴጥ. 3:10–13። የመጨረሻውን ፍርድ ባህሪ ማስተዋል እንችል ዘንድ ጥቅሶቹ እንዴት ይረዱናል? ፍርዱ አንዴ የሚሰጥ እንጂ ለዘላለም ይቀጥላል ከሚለው የፍርድን አካሄድ ከሚያዛባ አስተሳሰብ በተቃራኒ-በጥቅሶቹ የምናገኘው ጽንሰ ሀሳብ የመጨረሻው ቅጣት ፍጻሜ እንዳለው እንዴት ያሳየናል?



“እግዚአብሔር መልካምና ታጋሽ፣ ትዕግሥተኛና ምኅረቱ የበዛ አምላክ መሆኑ--ፈቃዱን ለመታዘዝ እምቢተኛ የሆነውን ኃጢአተኛ ከመቅጣት አያግደውም። እግዚአብሔር በቅዱስ ሕጉ ላይ ዐመጻ ላደረገው ወንጀለኛ ልጁ እንዲሞት በመስጠት በከፈለው ታላቅ መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ይቅር ያለበት ምክንያት ሕጉ ሊለወጥ የማይቻል በመሆኑ ነው።”--—Ellen G. White, Manuscript Releases, vol. 12, p. 208.

እግዚአብሔር የሰው ልጆች ለዘላለም ጠፍተው እንዳይቀሩ ሊያደርግ ይችል የነበረው ነገር እርሱን ራሱን ታላቅ ዋጋ አስከፍሎታል። የጠፉት በመጨረሻ ወደዚህ አሳዛኝ ፍጻሜ የመራቸውን ምርጫ አደረጉ። በጠፉት ላይ የተሰጠው አምላካዊ የፍርድ ጽንሰ ሀሳብ--ሌላው ቀርቶ እነርሱን መደምሰሱ በራሱ (ለዘላለም እየተሠቃዩ ይኖራሉ ከሚለው በተቃራኒ) ከአፍቃሪው አምላክ ባህሪ ጋር ስለሚቃረን ሰህተት ነው። ፍትሕ የሚጠይቀው የእግዚአብሔር ፍቅርና የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው።

እግዚአብሔር የሚድኑትን ሁሉ ለማዳን እስከ ምን ድረስ ለመጓዝ ፈቃደኛ እንደነበር ራሱ መስቀሉ ምን ያስተምረናል?

፡ ታህሳስ 13
Dec 22

ሁለተኛው ሞት


እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ታሪክ ወደ መጨረሻው በጡዘት የተሞላ ዘመን እየመራ ነው። በሺህ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ዐመጸኞች ከመቃብር ተነሥተው የመጨረሻውን የቅጣት ፍርዳቸውን ይቀበላሉ (ራእ. 20፡5፣ 11–15)። ከዚያም አጠቃላይ የፍርድ ሂደቱ ከተጠናቀቀና ሌላ ምንም ነገር ሊጨመር በማይችልበት ሁኔታ ዐመጸኞች የእግዚአብሔርን ፍርድ ፍትሐዊነት ይቀበላሉ። “የታላቁ ተጋድሎ ገጽታ በተጨባጭ ወለል ብሎ እየታየ ባለበት ሁኔታ ታማኝ የሆነው እንዲሁም የወደቀው ዓለም--አጽናፈ ሰማያት በሙሉ በአንድነት፡ ‘ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ’ ሲሉ ያውጃሉ”።

እንዲሁም ሰይጣን ራሱ ‘አጎንብሶ የፍርዱን ፍትሐዊነት ይናዘዛል’ ”-- Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 670, 671. ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሚልክ. 4:1፣ ራእ. 20:14-15፣ ራእ. 21:8። “የእሳት ባሕር” እና “ሁለተኛ ሞት” ምን ያህል ፍቱን መሆን ይችላሉ?



የሰይጣንና መላእክቱ እንዲሁም የዐመጸኞች መጥፋት አጥናፈ ሰማይን ከኃጢአት እና እርሱን ተከትሎ ከሚመጣው መዘዝ ያነጻል። ይህም ሆኖ፣ በዐመጸኞች ላይ የሚደርሰው የመጨረሻ ድምሰሳ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለራሳቸው ለዐመጸኞች ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። “የሚያጠፋ እሳት” (ዕብ. 12፡29) በሆነው በእግዚአብሔር አምላክ ፊት ከመኖር ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ።

“[የጠፉት] ከዚያ ቅዱስ ስፍራ ለመሸሽ ይናፍቃሉ። እነርሱን ለመዋጀት ከሞተው ጌታ ፊት ይሸሸጉ ዘንድ በላያቸው ውድመት እንዲደርስ ይመኛሉ። የዐመጸኞች መጨረሻ በገዛ ምርጫቸው ላይ የተወሰነ ነው። እግዚአብሔር ጻድቅና በምኅረት የተሞላ አምላክ እንደመሆኑ፣ ከሰማይ የተነጠሉት በራሳቸው ምርጫ ነው።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 543. በመሆኑም፣ ኃጢአት እና ኃጢአተኞች በሲኦል ውስጥ ለዘላለም እየተሠቃዩ ይኖራሉ ከሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ንድፈ ሀሳብ በተቃራኒ የምናገኘው-የኃጢአትና ኃጢአተኞች መደምሰስ--ዐመጸኞች የቱንም ያህል እኩይ ተግባር ቢፈጽሙም ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚቀበሉ ያሳየናል። እንዲሁም ኃጢአት መጀመሪያ እንደነበረው ሁሉ መጨረሻም እንደሚኖረው ያረጋግጥልናል። ከዚያም መላው አጥናፈ ሰማይ--ምስጢራዊና ምክንያት የለሽ የሆነው ኃጢአት፣ ክፋት እና አለመታዘዝ ከመከሰቱ አስቀድሞ ወደ ነበረው የቀደመ ንጽሕናው ይመለሳል።

እርሱ የእኛ “ጻድቅ ፈራጅ” (2ጢሞቴ. 4፡8) እንደመሆኑ ለጻድቃን ዘላማዊ ሕይወት በመስጠትና ዐመጸኞችን ለዘላለም በማጥፋት ፍትሐዊ ፍርድ ይሰጣል። እግዚአብሔር በመጨረሻ ሁሉንም ያድናል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ምን ችግር አለበት? ይህ አጉል ዓይነት እሳቤ የሆነው ለምንድን ነው?

፡ ታህሳስ 14
Dec 23


ተጨማሪ ሀሳብ


፡ Read Ellen G. White, “Without a Wedding Garment,” pp. 307–319, in Christ’s Object Lessons; “Desolation of the Earth,” pp. 653–661; “The Controversy Ended,” pp. 662–673, in The Great Controversy.

“በመጨረሻው ፍርድ ጊዜ እያንዳንዱ ኃጢአተኛ እውነትን የናቀበትን ምክንያት ይረዳል። በኃጢአት የታወረ አእምሮ ሁሉ የመስቀልን ምንነት ይረዳል። በቀራንዮና በቀራኒዮ ላይ በተሰዋው አንጻር ኃጥአን ይወገዛሉ። እያንዳንዱ የሐሰት ምክንያት ይሰረዛል። የሰብዓዊ ክህደት ክፉ ባሕርይ ይገለጻል። ሰዎች ምርጫቸውን ያያሉ። ስለ እውነትና ሐሰት ለረጅም ዘመን ሲያከራክር የኖረው ጥያቄ ግልጽ ይሆናል። መለኮታዊ ሕግጋት ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሆኑም ይገለጻል። የእግዚአብሔር መንግሥት ምንም እንከን አይገኝለትም።

ለቅሬታም ምክንያት አይኖርም። የልቦች ሁሉ ሀሳብ ሲገለጥ ታማኞችና አመጸኞች በአንድ ላይ “ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው፤ የሕዝቦች ንጉሥ ሆይ መንገድህ ትክክልና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ አንተን የማይፈራና ስምህንም የማያከብር ማን ነው?... የእውነት ፍርድህ ስለተገለጠ” (ራእ. 15፡3-4) ይላሉ።” (የዘመናት ምኞት [አማርኛው ትርጉም] ገጽ 43)።


የመወያያ ጥያቄዎች



1. “ፈቃድዎን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት አሻፈረኝ በማለት ከራስዎ ጋር እየተላተሙ ከሆነ ሞትን እየመረጡ ነው። ኃጢአት በየትኛውም ስፍራ ቢገኝ፣ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ነው። እርስዎ ኃጢአትን የሚመርጡ ከሆነና ከኃጢአት ለመለየት የሚቃወሙ ከሆነ ኃጢአትን የሚበላው የእግዚአብሔር ሕልዎት እርስዎንም ያጠፋዎ ዘንድ የግድ ይሆናል።”—Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 62. ይህ ጥቅስ የመጨረሻውን ፍርድ ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል?

2. በማክሰኞ ትምህርት መጨረሻ ላይ በቀረበው--የዳኑት የፍርዱ ሂደት አካል እስኪሆኑ ድረስ ከጠፉት ውስጥ አንዳቸውም የመጨረሻውን ፍርድ አይቀበሉም በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ላይ ትኩረት ያድርጉ። ይህ ስለ እግዚአብሔር ግልጽ አምላክነት በድጋሚ ምን ያስተምረናል? ፍቅር በነገሠበት በዚያ አጥናፈ ዓለም ይህ ግልጽነት በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3. ቅዱሳን በሺሁ ዓመት ፍርድ መሳተፋቸው ከሚወዷቸው የሚጠፉ ወገኖች አኳያ እንዴት ያጽናናቸዋል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL