የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 100: 1–3፣ ዘፍ. 1–2፣ ዘፀ. 20:8–11፣ ዘፀ. 40:33፣ ማቴ. 25:14–30፣ ማቴ. 19:7–9።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፡1)
የ
ዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ብሎም መላው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት
የሚጀምረው በእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራዎች ነው። የእኛ አፈጣጠር
የሰብዓዊውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ታሪክ ጅማሮ የሚያመላክት እንደ
መሆኑ ይህ እውነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ይህ እውነት የዘፍጥረት
መጽሐፍ የፍጥረት ታሪክ፣ ከሌሎች የሰብዓዊው ፍጡር እና የመጽሐፍ ቅዱስ
ታሪኮች ጋር ተመሳሳይ ታሪካዊ ሐቆችን እንደያዘ ያሳያል።
በዘፍጥረት ምዕ. 1 እና 2 የሚገኙት ሁለቱ የፍጥረት ሥራን የሚያመለክቱ
ጥቅሶች፣ በእግዚአብሔር እና በሰብዓዊው ፍጡር ዙሪያ ያሉ ትምርቶችን
ይዘዋል። በዚህ ሳምንት ጥናታችን ስለ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ጥልቅ ትርጉም
የተሻለ ግንዛቤ ይኖረናል። እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ፍጡር በአምሳሉ-እንዲሁም ከዐፈር ስለ መፍጠሩ ጠለቅ ብለን እንመለከታለን። መልካምና
ክፉን ስለ ምታስታውቀው ዛፍ ዓላማ እና ከሕይወት ዛፍ ጋር ስላላት ቁርኝት
ምልከታ እናደርጋለን።
ስለ መጀመሪያዎቹ ክስተቶች ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መሃል
በጣም አስፈላጊው ስለ ጸጋ የቀረበው ነው። የእኛ አፈጣጠር ሙሉ ለሙሉ የጸጋ
ብቻ ተግባር ነው። እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን የፈጠረው ከሰብዓዊው
ፍጡር ሕልውና ማግኘት አስቀድሞ ነው። መፈጠራችን የእግዚአብሔር
ስጦታ እንደሆነ ሁሉ መቤዠታችንም የእርሱ ስጦታ ነው። እነዚህ ሁለቱም
ጽንሰ ሀሳቦች ማለትም መፈጠራችን እና መቤዠታችን በሰባተኛው ቀን ሰንበት
ትእዛዝ ውስጥ መገኘታቸው የትእዛዙን ጥልቀት ያሳያል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 100፡1-3። የፍጥረት አምላክ ለሆነው ጌታ እግዚአብሔር የሰብዓዊው ፍጡር ምላሽ ምንድን ነው? ለምን?
በዘፍ. ምዕ. 1 የፍጥረት ታሪክ ቀዳሚው መልእክት “እግዚአብሔር” ነው።
ይህን ደግሞ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር” (ዘፍ. 1፡1) በሚለው መልእክት
አስቀድመን ሰምተናል። በዘፍ. 1፡1 በመጀመሪያው መስመር (ዘፍ. 1፡1) ላይ
የቀረበው “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል የጥቅሱ አማካይ እንደመሆኑ፣ ለዚህ
አምላክ ሊሰጥ የሚገባውን አጽንኦት ለማጉላት ሲባል በዕብራውያን የአምልኮ
ትውፊታዊ ዝማሬ ውስጥ በጠንካራ የሆሄያት ድምጸቶች ተመልክቷል። ይህን
የፍጥረት ሥራ አስመልክቶ የቀረበው ጽሑፍ የሚጀምረው የፍጥረት ደራሲ
ለሆነው አምላክ አጽንኦት በመስጠት ነው።
በተጨባጭ እንደምንመለከተው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ የሚጀምረው
እግዚአብሔርን በሁለት የተለያዩ አቀራረቦች በማስቀመጥ ነው። የመጀመሪያው
የፍጥረት ዘገባ (ዘፍ. 1፡1-2፣ 4) እግዚአብሔርን የሚያስቀምጠው፣ በእጅጉ
ከሰው ልጆች ርቆ የሚገኝ፣ ከተለመደው አካላዊ ሕልዎት ባሻገር ባህሪ ያለው
አድርጎ ሲሆን፣ ኤሎሂም የተሰኘ ስሙ አለቅነቱን ይናገራል። ኤሎሂም የእርሱን
ከሁሉ ልቆ መገኘት እና ኃያልነት የሚናገር ሲሆን፣ ኤሎሂም በብዙ ቁጥር
ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ ንጉሥነቱን እና ከአካላዊ ሕልዎቱ ባሻገር ያለውን
ባህሪያዊ ጽንሰ ሀሳብ ይገልጻል።
ሁለተኛው የፍጥረት ዘገባ (ዘፍ.2፡4-25) እግዚአብሔር በቅርብ ያለ፣
ግላዊ ማንነትና ሕልዎት ያለው አምላክ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ ያሕዌ-የተሰኘ ስሙ ብዙዎች እንደሚያምኑት መቀራረብንና ዝምድናን ያመለክታል።
በፍጥረት ዙሪያ የተመለከተው ጥቅስ በአጠቃላይ እግዚአብሔርን እንድናመልክ
የቀረበ የማያወላውል ተማጽኖ ነው። በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ
ታላቅነት ብሎም ኃያልነት ማወቅ እና በተመሳሳይ እኛን እንደ መፍጠሩ እርሱ
እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ማወቅ (መዝ. 100፡3) እና መተማመናችን
በእርሱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። የመዝሙር መጽሐፍ
በአመዛኙ ከፍጥረት አምልኮ ጋር የተሳሰረው ለዚህ ነው (መዝ. 95፡1-6፣ 139፡
13-14 [ከራእ. 14፡7 ጋር ያስተያዩ])
ይህ የንጉሥነቱን እና የኃያልነቱን ሁለት ገጽታ በአንድ የሚያስቀምጥ፡
ማለትም በአንድ በኩል ንጉሥ እና ኃያል--በሌላ በኩል በቅርባችን ያለ፣
አፍቃሪና ከእኛ ጋር በግንኙነት መስመር ውስጥ የሚገኝ አምላክ የመሆኑ ዕይታ፣
እንዴት በእግዚአብሔር ፊት በአምልኮ ልንቀርብ እንደሚገባ የሚያመላክት
አስፈላጊ ነጥብ ይዟል። በፍርሐት እና በአክብሮት የተሞላ አምልኮ--ከደስታ፣
ከአምላካዊው ቅርብ የመሆን ዋስትና፣ ከይቅር ባይነትና ከፍቅር ጋር አብሮ
ይሄዳል (መዝ. 2፡11)። እግዚአብሔር የቀረበባቸው ሁለት ቅደም ተከተሎች
በራሳቸው ትርጉም ያላቸው ናቸው፡ የእግዚአብሔር ቅርብ የመሆን ተሞክሮና
የሕልዎቱ አብሮነት፣ የአምላካዊውን ሊደረስበት በማይችል ርቀት የመኖር
ተሞክሮ ይከተላል። የእግዚአብሔርን ታላቅ አምላክነት ስንገነዘብ ብቻ ጸጋውን
ማድነቅ እና አስደናቂ ብሎም አፍቃሪ ስለ ሆነው ስለ እርሱ በሕይወታችን
መገኘት በመንቀጥቀጥ ሐሴት ማድረግ እንችላለን።
እርሱ በአንድ በኩል ዓለማትን ደግፎ የያዘና የማይመረመር
ግዙፍ ሥልጣንና ኃይል ባለቤት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ
ለእያንዳንዳችን እጅግ ቅርብ መሆን ይችላል። ይህ አስደናቂ
እውነት እጅግ ድንቅ የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1:4፣ 10፣ 12፣ 18፣ 21፣ 25፣ 31 እና ዘፍ. 2:1–3። እግዚአብሔር በፍጥረት ሳምንት ሥራው “መልካም እንደሆነ አየ” በሚል የቀረበው መግለጫ አንደምታ ምንድን ነው? በፍጥረት ሥራ መደምደሚያ በተዘዋዋሪ የተጠቀሰው ትምህርት ምንድን ነው (ዘፍ. 2፡1-3)?
በእያንዳንዱ የፍጥረት ዘገባ እግዚአብሔር ሥራውን “መልካም” (በዕብራይስጥ
“ቶቭ”) እያለ ይገመግማል። በአጠቃላይ ይህ ቅጽል የእግዚአብሔር የፍጥረት
ሥራ የተሳካ እንደነበር እና እርሱ “መልካም እንደሆነ አየ” ብሎ የሰጠው
አስተያየት “ሥራው ውጤታማ ነበር” የሚል ፍቺ አለው። ብርሃን ሆነ (ዘፍ. 1፡
4)። ተክሎች ፍሬ እያፈሩ ነበር (ዘፍ. 1፡12) ወዘተ።
ነገር ግን ይህ ቃል ከአንድ ተግባር ውጤታማነትም በላይ ያመለክታል።
ቶቭ የተሰኘው ይህ የዕብራይስጥ ቃል ስለ ውበት ወይም ውበትን አስመልክቶ
የሚሰጥ አድናቆትን ለመግለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ ውሏል (ዘፍ. 24፡
16)። በተጨማሪ ከሞት ጋር (ዘፍ. 2፡17) ተያይዞ የሚኖርን ክፋት (ዘፍ. 2፡9)
ለማነጻጸር ጥቅም ላይ ውሏል።
“መልካም እንደሆነ አየ” በሚል የቀረበው ሀረግ፣ የፍጥረት ሥራ ውብ፣
ፍጹም፣ አንዳችም ክፋት ያልነበረበትና በግሩም ሁኔታ እየሄደ የነበረ--የሚል
ፍቺ አለው። ምድር “ገና” እንደ ዛሬዋ፣ እንደ እኛ በኃጢአት እና በሞት
ያለመጠቃቷ ጽንሰ ሀሳብ፣ በሁለተኛው የፍጥረት ጅማሮ የሚኖረውን ሁኔታ
ያረጋገጠ ነበር (ዘፍ. 2፡5)።
ይህ ስለ ፍጥረት የቀረበ መግለጫ ከዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳቦች ጋር በእጅጉ
ይቃረናል። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳቦች ምድር በተከታታይ ገቢራዊ በሆኑ
ድንገተኛ ክስተቶች መንስዔ ደረጃ በደረጃ ራሷን በሂደት እንደምትቀርጽ በይፋ
ይናገራሉ።
በአንጻሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ደግሞ እግዚአብሔር ዓለምን ሆን ብሎና
ዐውቆ ወዲያው እንደፈጠራት ያረጋግጣል (ዘፍ. 1፡1)። ከሥነ ፍጥረት
በአጋጣሚ ወይም እንደ ዕድል የተከሰተ አንድም ነገር አልነበረም። ይህች
ዓለም በእግዚአብሔር ፈቃድ እና ቃል ብቻ እንጂ በራሷ አልመጣችም (ዘፍ.
1፡3)። በዘፍ. 1 በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን “ፈጠረ”- በዕብራይስጥ “ባራ” በሚል የቀረበው ይህ ግስ ጥቅም ላይ የሚውለው
እግዚአብሔርን ብቻ ባለቤት በማድረግ ሲሆን፣ ቅጽበታዊ ተፈጻሚነት
ማግኘትን ያመለክታል፡ እግዚአብሔር ተናገረ፣ ሆነ።
በዚያን ጊዜ “ሁሉ” ነገር ክንውን እንዳገኘ የፍጥረት ታሪክ የሚጠቁመን
ሲሆን (ዘፍ. 1፡31)፣ እንደ ራሱ እንደ ፈጣሪ አባባል ደግሞ “እጅግ መልካም
ነበረ” (ዘፍ. 1፡31)። የሰማያትንና የምድርን አፈጣጠር ራሱ ዘፍ. 1፡1 የሚገልጽልን
ሲሆን፣ ዘፍ. 2፡1 ደግሞ ሥራው ክንውን ማግኘቱን ይፋ ያደርግልናል። ሰንበትን
ጨምሮ ሁሉም በሰባት ቀናት ውስጥ ተፈጸመ።
ምድርና ሙላቷ የዛሬውን ገጽታ ለመያዝ ቢሊዮን ዓመታት
ፈጅቶባታል የሚለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳብ፣ የዘፍጥረትን
የፍጥረት ታሪክ ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርገው ለምንድን
ነው? ሁለቱ አመለካከቶች በሁሉም መንገድ የማይጣጣሙት
ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡2-3፣ ዘፀ. 20፡8-11። ሰባተኛው ቀን ሰንበት ከፍጥረት ጋር ቁርኝት የኖረው ለምንድን ነው? ይህ ግንኙነት በሰንበት አጠባበቃችን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
እግዚአብሔር የፍጥረት ሥራውን በሰባተኛው ቀን “ፈጽሞ” ሰንበትን
አቋቋመ። ስለዚህ ሰባተኛው ቀን ሰንበት እግዚአብሔር ሥራውን በዚያን ጊዜ
መጨረሱንና፣ ይህን ሥራውን “እጅግ መልካም” ሆኖ እንዳገኘው የሚያመላክት
የእምነታችን መግለጫ ነው። ሰንበትን መጠበቅ ማለት ለአምላካዊው የፍጥረት
ሥራ ዋጋና ውበት እውቅና በመስጠት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መፍጠር
ነው።
እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እኛም ከሥራችን ማረፍ እንችላለን።
ሰንበትን ማክበር ማለት እግዚአብሔር “እጅግ መልካም” ብሎ ለጠራው
የፍጥረት ሥራው አዎንታን መቸር ሲሆን፤ ይህም አካላዊ ዕረፍትን ያካትታል።
ከአንዳንድ ጥንታዊ (እንዲሁም ዘመናዊ) እምነቶች በተቃራኒ፣ ብሉይ
ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን አካልን ክፉ ብሎ አያንኳስስም። ይህ አረማዊ
እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽንሰ ሀሳብ አይደለም። ሰንበትን የሚጠብቁ ወገኖች
ግን የገዛ ሥጋቸውን ጨምሮ ለእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ አመስጋኞችና
ውለታውን የማይዘነጉ ናቸው። ስለዚህ በፍጥረት ሥራው ሐሴት ያደርጋሉ፣
ይንከባከቡታልም።
የመጀመሪያውን ሰብዓዊ ታሪክ “ፍጻሜ” የሚያመለክተው ሰንበት፣ በሥቃይ
ውስጥ ለሚገኘው ሰብዓዊ ፍጡር እና በመቃተት ላለው ዓለምም እንዲሁ
የተስፋ ምልክት ነው። ሥራውን “ፈጽሞ ነበር” የሚለው ሀረግ በዘፀ.40፡
33 የማደሪያው ድንኳን በተተከለበት ወቅት ከተነገረው ጋር ተመሳሳይ
ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፤ አሁንም በድጋሚ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ገንብቶ
ሲጨርስ (1ነገሥ. 7፡40፣ 51) ይኸው ሀረግ ተደግሞ መነገሩን እናነባለን።
እነዚህ ሁለቱም፣ የወንጌል እና የደኅንነት ትምህርት የሚሰጥባቸው ስፍራዎች
ነበሩ።
ከውድቀት በኋላ፣ በየሳምንቱ መጨረሻ የሚመጣው ሰንበት በአዲስ
ሰማያትና አዲስ ምድር የፍጥረት ሥራ (ኢሳ. 65፡17፣ ራእ. 21፡1) ታምራት ብቻ
ገቢራዊ ወደ ሚሆነው የመዳን ታምራት ያመላክተናል። በሰብዓዊ ሳምንታችን
መጨረሻ ላይ የምናገኘው ሰንበት፣ የዚህ ምድር ሥቃይና ፈተናችን መጨረሻ
እንደሚኖረው የሚያሳይ ምልክት ጭምር ነው።
የሱስ የታመሙትን ለመፈወስ ሰንበትን እጅግ ተገቢ ቀን አድርጎ የመረጠበት
ምክንያቱ ይኸው ነው (ሉቃ. 13፡13-16)። የኃይማኖት መሪዎች ከተዘፈቁበት
ማንኛውም ወግና ልማድ በተቃራኒ፣ የሱስ በሰንበት ቀናት ባደረጋቸው
ፈውሶች የመዳን ሂደት የመጨረሻ መደምደሚያ የሆነውን--ሁሉም ሥቃይ፣
ሕመም እና ሞት የሚያከትምበትን ጊዜ ለሕዝቡም ሆነ ለእኛ አመላከተ።
አሁን በየሱስ ያገኘነውን እረፍት እና ደኅንነት በሰንበት
ቀን በማረፍ እንዴት እየተለማመድነው ነው? (በመጨረሻ አዲስ
ሰማይና አዲስ ምድር ሲፈጠር ፍጻሜ የሚያገኘውን)
የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ መደምደሚያ የሰው መፈጠር መሆኑን ከዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ እንረዳለን። ለምድር መሠራት ዓላማና መንስዔ የሆኑት ሰዎች የመላው ምድራዊ የፍጥረት ሥራ መቋጫ ናቸው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1፡26-29 እና ዘፍ. 2፡7። ስለ ሰው መፈጠር አስመልክቶ በእነዚህ ሁለት የተለያዩ ሐተታዎች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
እግዚአብሔር ሰዎችን በአምሳሉ ስለ መፍጠሩ የሚናገረው ይህ መግለጫ
እጅግ አድርገው በድፍረት ከተሞሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገሮች መሃል አንዱ
ነው። በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠሩ ሰዎች ብቻ ናቸው። “እግዚአብሔር
የዱር እንስሳትን እንደ የወገናቸው” ፈጠራቸው (ዘፍ. 1፡25)። “እግዚአብሔር
ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው” (ዘፍ. 1፡27)። ይህ መሠረታዊ ደንብ
መንፈሳዊ ተፈጥሮ ላላቸው ሰብዓዊ ፍጡራን ብቻ ተወስኖ የቀረበ ሲሆን፤
“የእግዚአብሔር አምሳል” የተሰኘው አነጋገር አምላካዊውን አስተዳደራዊ
ባህሪ ለመግለጽ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር አልያም እርስ በርስ የሚኖረንን
መንፈሳዊ ግንኙነት ለማመልከት ጥቅም ላይ እንደዋለ ሆኖ ይስተዋላል።
እነዚህ ግንዛቤዎች ትክክል ቢሆኑም፣ አስፈላጊ የሆነውን የዚህን ፍጡር
ተጨባጭ አካላዊ እውነታ ግን ሳያካትቱ ቀርተዋል። ሁለቱም ገጽታዎች ይህን
ሂደት በሚገልጸው ዘፍ. 1፡26፡ “መልክ” እና “አምሳል” በሚሉ ሁለት ቃላት
መካተታቸው እሙን ነው። ጸለም ማለትም “መልክ” የተሰኘው የዕብራይስጥ
ቃል አካላዊን ቅርጽ የሚያመለክት ሲሆን፤ ዲሙት ማለትም “አምሳል” ግን
ከመለኮታዊው አካል ጋር ንጽጽርነት ያላቸውን ረቂቅ ባሕርያት ያመለክታል።
በመሆኑም “የእግዚአብሔር አምሳል” የተሰኘው የዕብራይስጥ እሳቤ፣
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ተፈጥሮ ካለው--አካላዊውንና መንፈሳዊውን ማንነት
በአንድ ያቆራኘ ዕይታ አኳያ ሊስተዋል ይገባል። የሰዎች (ወንድ እና ሴት)
አካላዊና መንፈሳዊ ማንነት በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን የመጽሐፍ
ቅዱስ ጥቅሶች ያረጋግጡልናል። “አዳም ከፈጣሪ እጅ ሲወጣ በአካል፣
በአእምሮና በመንፈሳዊ ተፈጥሮው ከፈጣሪው ጋር መመሳሰልን ተላብሶ
ነበር።”—Education, p. 15
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አካላዊና መንፈሳዊ ማንነትን በአንድ ያቆራኘው
የእግዚአብሔር አምሳል አረዳድ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍ. 2፡7)
በሚለው በሌላው የፍጥረት ዘገባ በድጋሚ ማረጋገጫ አግኝቷል። “ሕያው
ነፍስ” (በዕብራይስጥ፡ ነፍሽ) ሁለት መለኮታዊ ተግባራትን፡ ማለትም
“አበጀው” እና “እፍ አለበት” የሚሉትን ተከትሎ የሚገኝ ውጤት ነው። እዚህ
ላይ “እፍ አለበት” የተሰኘው አገላለጽ አዘውትሮ ጥቅም ላይ የሚውለው
መንፈሳዊውን ገጽታ ለማመልከት ቢሆንም፤ በተጨማሪ “ከምድር ዐፈር…
የተበጀው” ሰብዓዊ ማንነት ከሥነ ሕይወታዊው የመተንፈስ ችሎታ ጋር
በቅርብ የተሳሰረ መሆኑንም ልብ ይሏል።
እግዚአብሔር ወደፊት ሦስተኛውን ቀዶ ጥገና የሚያካሂድ ሲሆን፤ በዚህ
ወቅት ሴቲቱን ከወንዱ አካል ይፈጥራል (ዘፍ. 2፡21-22)። ይህ ሴቲቱ ከወንዱ
ጋር አንድ ዓይነት ተፈጥሮ ለመጋራቷ ጉልህ አጽንኦት የተሰጠበት መንገድ
ነው።
እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ሰው እንደፈጠረ ሦስት ስጦታዎችን ሰጠው፡
የዔደንን አትክልት ስፍራ (ዘፍ. 2፡8)፣ ምግብ (ዘፍ. 2፡16) እና ሴቲቱን
(ዘፍ. 2፡22)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡15-17። ሰው ፍጥረትንና
እግዚአብሔርን አስመልክቶ የተሰጠው ትእዛዝ ምን ነበር? የእነዚህ
ሁለት ትእዛዞች የእርስ በርስ ተዛምዶ ምን ይመስላል?
እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዝ የተቀመጠበትን ተፈጥሮ
የተመለከተ ሲሆን ይኸውም “እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት”
(ዘፍ. 2፡15) በሚል ተጠቅሷል። (የዕብራይስጡ “አቫድ”) ማለትም
“እንዲያለማት” በሚል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ሥራን ያመለክታል። ስጦታ
መቀበል ብቻውን በቂ አይደለም። ይልቁንም በተሰጠን ነገር ላይ መሥራትና
ፍሬያማ ማድረግ ይጠበቅብናል። የሱስ ንብረቱን በአደራ ሰጥቶ ወደ እሩቅ
አገር ስለ ሄደ ሰው በሰጠው ምሳሌያዊ ትምህርት ይህንኑ በድጋሚ ተናግሯል
(ማቴ. 25፡14-30)። የዕብራይስጡ “ሻማር” ወይም “እንዲጠብቃት” በሚል
የቀረበው ግሥ የተሰጠን ነገር ጠብቆ የማቆየትን ኃላፊነት ያመለክታል።
ሁለተኛው ትእዛዝ ምግቡን ይመለከታል። እግዚአብሔር ይህን ምግብ
ለሰዎች ሁሉ መስጠቱን ማስታወስ ይኖርብናል (ዘፍ. 1፡29)። በተጨማሪ
እግዚአብሔር አዳምን “ ‘ከማንኛውም… ትበላለህ’ ” (ዘፍ. 2፡16) ብሎታል።
ሰዎች ዛፎቹንም ሆነ የሚያፈሯቸውን የሚበሉ ፍሬዎች አልፈጠሩም። ስጦታ
ናቸው--የጸጋ ስጦታ!
ነገር ግን እዚህም ላይ አንድ ትእዛዝ አለ፡ የእግዚአብሔር ለጋስ ስጦታ
ከሆነው “ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ” በመመገብ ደስ መሰኘት ነበረባቸው። ይሁን
እንጂ እግዚአብሔር በዚህ የጸጋ ስጦታ ላይ ገደብ አክሎበታል። አዎ--በተለይ
የተጠቀሰውን የአንድ ዛፍ ፍሬ እንዲበሉ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ልጓም
የለሽ ደስታ ለሞት ይዳርጋል። ይህ መርኅ በኤደን የአትክልት ስፍራ ትክክል
ነበር። እናም ይኸው መርኅ በብዙ መልኩ እነሆ ዛሬም አለ።
ሦስተኛው ለሰው የተሰጠው ትእዛዝ--ሦስተኛ ስጦታ የሆነችውን ሴቲቱን
ይመለከታል፡ “ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍ. 2፡24)። ይህ ያልተለመደ አባባል ሰው
ከትዳር አጋሩ ጋር የሚገባውን ቃል ኪዳን እና “አንድ ሥጋ” ይኸውም አንድ
ሰው (ማቴ. 19፡7-9) የመሆን ዓላማን የሚያጎላ ብርቱ መግለጫ ነው።
(ሴቲቱ ሳትሆን) ወንዱ ወላጆቹን ተለይቶ የመሄዱ ምክንያት ከመጽሐፍ
ቅዱሳዊው አጠቃላይ የተባዕት ጾታ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ትእዛዙ ለሴቲቱም ሊሠራ ይችላል። ያም ሆነ ይህ የጋብቻ ትስስር
ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ቢሆንም፣ ስጦታውን አንዴ ከተቀበሉ በኋላ
ሰብዓዊውን ኃላፊነት ይጠይቃል። የትዳር ሕይወትን በታማኝነት ስኬታማ
የማድረግ ኃላፊነት በወንዱም ሆነ በሴቷ--በሁለቱም ላይ ያርፋል።
በእግዚአብሔር ስለተሰጦት ሁሉም ነገሮች አሰብ ያድርጉ።
በተሰጦት ነገሮች ላይ የእርስዎ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
Ellen G. White, “Science and the Bible,” pp. 128,
129, in Education; “The Creation,” in The Story of Redemption,
pp. 21, 22.
“የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ እና የራእይ መጽሐፍ የአንድን ምጡቅ አእምሮ
አስደናቂ ባህሪያት የያዙ እንደመሆናቸው፣ ስምሙ ለዛ ባለው ቃና ከመናገር
ባለፈ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም። በተለያዩ ዘዴዎችና በልዩ ልዩ ቋንቋዎች
ተመሳሳይ የሆኑ ታላላቅ እውነቶችን ይመሰክራሉ። ሣይንስ ከዚህ ቀደም
ያልተደረሰባቸውን አስደናቂ አዳዲስ ነገሮች እያገኘ ነው። በትክክል
እስከተስተዋሉ ድረስ ከሣይንስ ግኝቶች መሃል አንዳቸውም ከመለኮታዊው
መገለጥ ጋር አይጋጩም። ይልቁንም አንዱ በሌላው ላይ ብርሃን ይፈነጥቃል።
እርሱ በሚሠራባቸው ሕጎች ውስጥ አንድ ነገር በማስተማር ከእግዚአብሔር
ጋር እንድንተዋወቅ ያደርጉናል።
“ሆኖም በተፈጥሮ ውስጥ ከሚታዩ እውነታዎች ባፈነገጠ መንገድ የተቀመሩ
ትርጉሞች በሣይንስ እና በአምላካዊው መገለጥ መካከል ግጭት እንዲከሰት
መንስዔ ሆነዋል። በዚህም፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜዎች በአምላካዊው
ቃል ላይ ያላቸውን ጉልበት ለማመንመን እና ለማጥፋት እንዲያስችሉ ሆነው
ተቀምረዋል። የሥነ ምድር (ጂኦሎጂ) የትምህርት ዘርፍ ከሙሴ የፍጥረት ዘገባ
ቀጥተኛ ፍቺ ጋር የሚቃረን አስተምህሮ ሲሰጥ ኖሯል። ምድር በዝግመታዊ
ለውጥ ድብልቅልቅ ሁናቴ ውስጥ አልፋ የዛሬውን ገጽታ ለመላበስ በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ዓመታት ፈጅቶባታል ከሚለው የሣይንስ ግኝት ጋር መጽሐፍ
ቅዱስን ለማስማማት ሲባል--የፍጥረት ቀናት በሺዎች ብሎም በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ዓመታትን የሚሸፍኑ፣ እጅግ አድርገው የተለጠጡና ይህን ያህል
ዘመን ተብሎ ሊወሰን የማይችል ግምታዊ ስሌት አካል እንዲሆኑ ተደርጓል።
“እንዲህ ዓይነቱ መደምደሚያ ላይ መድረስ ፈጽሞ ምክንያት የለሽና ተገቢ
ያልሆነ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከራሱም ሆነ ከተፈጥሮ አስተምህሮ ጋር
ስምሙ ነው።”—Ellen G. White, Education, pp. 128, 129.
1.እኛ መንፈሳዊውን አስተምህሮ እንቀስም ዘንድ በተጨባጭ
ታስበው የተዘጋጁት የፍጥረት አጀማመር ዘገባዎች “አፈ ታሪክ”
እንደ ነበሩ አድርገን የምንቀበል ከሆነ የእምነታችን ንጽህና
የሚናጋው ለምንድን ነው? የፍጥረት አጀማመር ዘገባዎች በታሪክ
የተደገፈ ተጨባጭነት የላቸው ይሆን? እንደ ተቀሩት የመጽሐፍ
ቅዱስ ታሪኮች ሁሉ በዘፍጥረት የቀረቡትም “በታሪክ የተደገፉ”
መሆናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ያውቅ እንደ ነበር
የሚጠቁሙ ምን ዓይነት ፍንጮች ከአምላካዊው ቃል እናገኛለን?
የሱስ ዘገባዎቹ ታሪካዊ ተጨባጭነት እንዳላቸው አስመልክቶ
የሰጠው ምስክርነት ምን ነበር?
2.የዘፍጥረት ታሪክ ምድርን በመጋቢነት ስለመንከባከብ አስፈላጊነት
አስመልክቶ ምን ያስተምረናል? ከዚህ ጎን ለጎን እጅግ ከባድ
ፈተና የሆነውን፣ ከፈጣሪ በተቃራኒ ራሷን ተፈጥሮን የማምለክ
አደጋን አስወግደን የምድራችን ጥሩ መጋቢዎች መሆን የምንችለው
እንዴት ነው? (ሮሜ 1፡25)
3.ምንም እንኳ ኃጢአት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ከፍተኛ
ውድመትና ጥፋት ቢያደርስም “እጅግ መልካም” የነበረው
የቀደመው ፍጥረት ድንቅነት፣ ውበትና ሞገስ ዛሬ ድረስ
ስለ እግዚአብሔር መልካምነትና ኃያልነት በብርቱ መንገድ
የሚገልጥልንና የሚናገረን እንዴት ነው?