የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከመጋቢት 10-16

13ኛ ትምህርት

Mar 19-Mar 25




የወንድማማች መዋደድ ይኑር



ሰንበት ከሰዓት

በዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ ዕብ. 13፤ ሮሜ 12፡13፤ ኤፌ. 5፡3-5፤ 1ጴጥ. 5፡1-4፤ ዕብ. 2፡9፤ ዕብ. 4፡16፤ ገላ. 2፡20


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “የወንድማማች መዋደድ ይኑር” (ዕብ. 13፡1)

ዕ ብራውያን 13 ሐዋርያው የሚነግረንን የማጠቃለያ ምክር ይነግረናል፡ - “የወንድማማች መዋደድ ይኑር” (ዕብ. 13፡1)። በፅሁፉ ሁሉ ውስጥ ከንጉሳችንና ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ጋር ቤተሰብነት ያለን ወንድሞቹና እህቶቹ መሆናችንን አረጋግጧል። ፀሐፊው ተደራሲያኑን የሚያያቸው ለድነታቸው የሚሰሩ ግለሰቦች ብቻና ከየሱስ ጋር አንድ ለአንድ ግንኙነት እንዳላቸው ሳይሆን እንደ ቤተሰብ እና አብሮ እንደዳኑ ግለሰቦች ነው። ጳውሎስ ለኛ የሰራውን ሥራ የገለፀው “የወንድማማች መዋደድ” ብሎ ነው “ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራቸው አላፈረም” (ዕብ. 2፡11)። ስለዚህ አማኞች የሱስ ለኛ ያደረገውን በሙሉ እርስ በርሳችን ማድረግ አለብን።

በደብዳቤው ሁሉ ውስጥ የወንድማማች መዋደድ “እርስ በርስ መመካከርን” የሚያካትት ሲሆን በዚህም የተነሳ ማንም የእግዚአብሔር ፀጋ አይጎድለውም (ዕብ. 3፡13፣ ዕብ. 10፡24-25፣ ዕብ. 12፡15-17)። በምዕራፍ 13 ላይ ብዙ ሃሳቦችን አካቷል፤ እንግዶችን መቀበል (ዕብ. 13፡2) የታሰሩትን መጠየቅ እና የተጨቆኑትን መደገፍ (ዕብ 13፡3)፣ ጋብቻን ማክበር (ዕብ. 13፡4)፣ ክፉ መሻትን ማስወገድ (ዕብ. 13፡5-6)፣ ዋኖቻችን ያዘዙንን መታዘዝንና (ዕብ. 13፡7-17) ለደራሲው መጸለይንም (ዕብ. 13፡18-19) ያካትታል። የዚህን ሳምንት ትምርት አጥንተው ለመጋቢት 17 ሰንበት ይዘጋጁ።

መጋቢት 11
Mar 20

የእግዚአብሔር ህዝቦችን መንከባከብ


ዕብ. 13፡1-2፤ ሮሜ 12፡13፤ 1 ጢሞ. 3፡2፤ ቲቶ 1፡8 እና 1 ጴጥ. 4፡9ን ያንብቡ። በቀደመችው ቤተክርስቲያን እንግዳን የመቀበል ሚና ምን ነበር?



ክርስትና በየቦታው የመንቀሳቀስ ንቅናቄ ሲሆን በብዛት በክርስቲያኖችና ክርስቲያን ባልሆኑ መስተንግዶ ላይ ይመሰረት ነበር። እንግዶችን መቀበል “አትርሱ” የሚለው ትዕዛዝ አንድን ሰው እንግዳ አድርጎ ለመቀበል አለማሰብን ብቻ ሳይሆን አውቆ ችላ ማለትንም ለማመልከት ነው። ጳውሎስ እንግዶችን ስለመቀበል ሲናገር አማኞችን ብቻ አይደለም። አንዳንዶች እንግዶችን ሲቀበሉ ሳያውቁ መላእክትን እንዳስተናገዱ እያስታውሳቸው ነበር (ዕብ. 13፡2)። የሶስቱ ሰዎች አብርሃም እና ሳራን ለመጎብኘት መምጣትን እያሰበ ይሆናል (ዘፍ. 18፡2-15)። እንግዶችን ማስተናገድ ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈልን፣ ኢየሱስ ለኛ እንዳደረገውም ከሌሎች ጋር አብሮ መከራ መቀበልን ያመለክታል (ዕብ. 2፡10-18)።

በእስር ቤት ላሉ የወንድማማች ፍቅር ማሳየት ማለት ታሳሪዎችን በፀሎታችን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ እና ስሜታዊ ድጋፍን በማበርከት እረፍት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። እስረኞችን ሆን ብሎ ችላ የማለት ሁኔታ ነበረ። በማህበረሰቡ ዘንድ ለተኮነኑት ቁሳዊ እና ስሜታዊ ድጋፍ ስናበረክት ራሳችንን ከእነርሱ ጋር አብረን እንድንቆጥር እያደረግን ነው። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ከእነርሱ ጋር “አጋርነት” በመፍጠራቸው በተወሰነ መልኩ ማህበረሰባዊ ለሆነ ጥቃት(መገለል) ራሳቸውን አጋልጠዋል (ዕብ. 10፡32-34)።

ጳውሎስ እስረኞችን በተመለከተ የማበረታቻ ቃላትን ሲናገር ምስላዊ አገላለፆችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያ ፀሐፊው አንባቢያን የቀድሞ ስጋዊ ወንድሞቻቸውን እንዲያግዙ ይጠይቃቸዋል። “በነቀፋ እና በጭንቅ በገሃድ ለተጋለጡ” ከእነርሱ ጋር “ህብረት” ወይም “አጋርነት” አድርገዋል (ዕብ 10፡33)፤ ሁለተኛው “መጨቆን” የሚለው አገላለፅ የሚያስተጋባው የሙሴን ምሳሌ ነው፡- “ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በሀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ” (ዕብ. 11፡25)።

በስተመጨረሻም ጳውሎስ ስለ ወንድማማች መዋደድ ጽንሰ ሃሳብ ይናገራል። አንባቢያን “ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።” እያለ ያሳስባቸዋል (ዕብ 13፡3)። ሰው እንደመሆናቸው እነርሱም በእዛ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ማለትም በእስር ቤት ቢሆኑ ሌሎች ሊያደርጉላቸው የሚወዱትን እነርሱ እንዲያደርጉ ነገራቸው። ስለዚህም ህዝቡ እነዚህ እስረኞች እንዳልተረሱ ለማሳየት ቁሳዊ እና ስሜታዊ ድጋፍን ሊለግሷቸው ይገባቸዋል። የቤተክርስቲያን አባል ቢሆኑም ባይሆኑም በእስር ቤት ላሉ ከዚህ በላይ ልናደርግላቸው የሚገባ ሌላ ምን ነገር አለ?

መጋቢት 12
Mar 21

ሴሰኞች እና አመንዝሮች


ዕብ. 13፡4-5፤ ሉቃስ 16፡10-18፤ 1ቆሮ. 5፡1፤ ኤፌ. 5፡3-5 እና ቆላ. 3፡5ን ያንብቡ። በዚህ ክፍል ውስጥ የተዛመዱት ሁለቱ ክፋቶች ምንና ምን ናቸው?



ጳውሎስ ስለ አመንዝራነት እና ስግብግብነት ጉዳይ አንባቢያንን ያስጠነቅቃቸዋል ምክንያቱም ለወንድማማች ፍቅር ስጋት የሆኑ ሁለት መቃብሮች ናቸውና። በእርግጥም የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች እና ጥንታዊያን የግብረገብ ባለሙያዎች በነዚሁ ሁለቱ መካከል ተዛምዶ እንዳለ ተናግረዋል። ጳውሎስ ለጋብቻ ክቡርነት ጥሪውን ሲያደርግ ይህንን ጋብቻ የሚያኮስሱ ማናቸውንም ነገሮች እንዲወገዱ በማመልከት ነው። እንዲወገዱ ካላቸው ነገሮች መካከል የጋብቻ ቃል ኪዳን መጣስ እና ፍቺን ነበር (ከማቴ. 19፡9 ጋር ያነፃፅሩ)።

የጋብቻን አልጋ ንፁህ የማድረግ ምክር ከጋብቻ ውጪ የሚደረግን የግብረ ስጋ ግንኙነት ምኞትን ማስወገድን የሚገልጽ ነው።” “አመንዝራዎች” ተብሎ በአዲስ ኪዳን የተጠቀሰው አገላለፅ ማንኛውንም ወሲባዊ ግድፈት የሚናገር ነው (1ቆሮ. 5፡9-11፤ 1ቆሮ. 6፡9-10፤ ኤፌ. 5፡5፤ 1ጢሞ. 1፡9-10፤ ራዕይ 21፡8፤ ራዕይ 22፡ 15)። በተጨማሪም የግሪኮ ሮማን ማህበረሰብ ለወሲባዊና ግብረገብነት ልል የሆነ እይታ አላቸው። ወንዶቹ ጥንቁቅ እስከሆኑ ድረስ ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ ፈቃድ የሚሰጥ ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን አብሮ የያዘ መመሪያ ነበራቸው። ነገር ግን ጳውሎስ እንደሚያስጠነቅቀን እግዚአብሔር በአመንዝራዎች ላይ ይፈርዳል። አማኞች ማህበረሰባዊ ልምዶች ግብረገባዊ መመዘኛቸውን እንዲያወጡላቸው ሊፈቅዱ አይገባም።

“ገንዘብን መውደድ” በግሪኮ ሮማን ማህበረሰብ ውስጥ በዋነኝነት የሚንፀባረቅ መጥፎ ምግባር ነው። እንዲያውም ጳውሎስ በፃፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ “ገንዘብን መውደድ” የክፋት ሁሉ ስር ነው ይላል (1 ጢሞ. 6፡10)። ይህንን ክፉ ምግባር መከላከል ጳውሎስ በብዙ ሃሳቦች ላይ የሚያደፋፍረው አስተሳሰብ ነው። በመጀመሪያ ባላቸው ነገር “ረክተው” መኖር አለባቸው (2 ቆሮ. 9፡8፤ ፊሊ. 4፡11-12)። በተጨማሪም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የገባውን ቃል ኪዳን ማለትም “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” የሚለውን ሊያምኑ ይገባል (ዕብ. 13፡5)። ይህ ቃል ኪዳን በአያሌ ስፍራዎችና ሁኔታዎች ላይ ለህዝቦቹ ተጠቅሶላቸዋል። ለኛም ቢሆን ዛሬ የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው (ዘፍ. 28፡5፤ ዘዳ. 31፡6-8፤ ኢያሱ 1፡5፤ 1ዜና 28፡20)።

አማኞች የባለ መዝሙረኛውን ቃላት በመጠቀም ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ምላሽ እንዲሰጡ ተጋብዘዋል (መዝ. 118፡6) “እግዚአብሔር ረዳቴ ነው አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል”። መዝ. 118ን መጥቀሱ ያስፈለገው ባለ መዝሙሩ በማያምኑ ሰዎች የሚደርስበት ስቃይ ቢኖርም እርሱ ግን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን መታመን ስለገለፀ ነው። ዘመናዊው ማህበረሰብ ወሲባዊ ንፅህናን ለማርከስ በተመሳሳይ ጊዜ የሰው ልጅ ገንዘብን መውደድ ለማሳደግ ምን አይነት መንገዶችን ይጠቀማል? በምን አይነት ተግባራዊ መንገድ ነው ከነዚህ ሁለት አደገኛ ተግባራት ራሳችንን ለመከላከል የምንችለው?

መጋቢት 13
Mar 22

ዋኖቻችሁን አስቡ


ዕብ. 13፡7-17ን አንብቡ። ከመሪዎቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ምን መመምሰል አለበት



ዕብ. 13፡-17 የጉባኤዎቻችንን ዋኖች እንድናከብር እና እንድንታዘዝ የሚመክር ሃሳብ አለው። ባለፉት ጊዜያት የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሯችሁን ዋኖቻችሁን “አስቡ” በማለት ይጀምርና ሲደመድም ደግሞ አሁን ላይ ዋኖቻችሁን “ታዘዙ” (ዕብ. 13፡17) ይላል። የቀድሞ ዋኖቻችሁ የተባሉት ቃሉ አስቀድመው በመስበክ ጉባኤን የመሰረቱ ናቸው። “አስቡ” የሚለው ጥሪ እንዲህ በቀላሉ በአዕምሮአችን ማስታወስ ወይንም በውጫዊ ማስመሰል እነርሱን ማክበር ማለት አይደለም። ጳውሎስ “አስቡ” ብሎ ሲናገር የኑሮአቸውን ፍሬ በመመልከት በእምነታቸው እንድንመስላቸው ነው።

ለጳውሎስ የማሰብና የማመስገን ታላቁ ተግባር አብልጦ ለመስራት መሞከር ነው በዚህ መንገድ ጳውሎስ መስራች የሆኑ የጉባኤ መሪዎችን በእምነት ጀግኖች ዝርዝር ውስጥ በማስገባት አማኞችም በጥንቃቄ ነገሩን እንዲያስቡ አደረገ። በዚህ የስም ዝርዝር ውስጥ ደግሞ ዕብ. 11 ላይ ያሉት የእምነት ጀግኖች እና የሱስ በዕብ 12ላይ የተጠቀሰው የእምነታችን ጀማሪና ፈፃሚ ተካተዋል። ፀሐፊው ሲቀጥልም የሱስ “ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለም ያው ነው” (ዕብ. 13፡ 8) ይለናል። ከሐሰተኞች መምህራን ከጊዜ ጋር ትምህርታቸው የሚለዋወጥና እንግዳ ትምህርት የሚያስተምሩ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ ይቆማል (ዕብ. 13፡9)።

በዕብ. 13፡7 ላይ ዋኖቻችሁን አስቡ ብሎ በሚጣራው ክፍል መጨረሻ ላይ አስገዳጅ ቃላትን የበለጠ ሲጠቀም እናገኛን። አማኞች ዋኖቻቸውን መታዘዝ እንዳለባቸው አጥብቀው ተመክረዋል ምክንያቱም ለነፍሶቻቸው መጠንቀቅ አለባቸው። መሪዎች ተብለው እዚህ ጋ የተጠቀሱት ለጉባኤውና ለመንጋው መንፈሳዊ ጤንነትን ሀላፊነት የወሰዱ እና ለመንፈሳዊ ነገር በእግዚአብሔር ተጠያቂ ሆነው የሚቀርቡ ፓስተሮችን ነው (1ጴጥ. 5፡1-4፤ 1ቆሮ. 3፡10-15)። በእርግጥም ይህ ሀሳብ ለሁሉም የቤተክርስቲያን መሪዎች እንዲሁም ዛሬ ላይ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ ጉባኤዎች ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል።

የጥቅሱ አውድ እንደሚነግረን እነዚህ መሪዎች በየሱስ እረኝት ስር የሚያገለግሉ ናቸው “ለበጎች ትልቅ እረኛ” (ዕብ. 13፡20) የመሪዎች ጥንቃቄ እና ታማኝት ከአባላት መታዘዝ እና መታመን ጋር ሲዋሃድ ደስታን ያመጣል። ይህም ማለት መሪዎች ጉባኤያቸውን “በደስታ” ማገልገል ወይንም ጉባኤያቸውን በሃዘን ሳይሆን በደስታ ለመስጠት ይችላሉ ማለት ነው። የመሪዎችንና አባላት ጉባኤን ግንኙነት እንዲሁም በአለም ዙሪያ ካሉ መሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርና ለማሻሻል ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

መጋቢት 14
Mar 23

ከእንግዳ አስተምህሮዎች ተጠንቀቁ


ዕብራውያን 13፡9ን፣ ዕብራውያን 2፡9ን፣ ዕብራውያን 4፡16ንና ዕብራውያን 6፡19-20ን ያነፃፅሩ። ፀጋ የሚገኘው ከየት ነው? ልባችንስ የሚጠነክረው እንዴት ነው?



በዕብራውያን 13፡9 ላይ የተጠቀሰው በሀሰት ትምህርቶችና በምግቦች መካከል ያለው ግንኙነት ንፁህ በሆኑትና ባልሆኑት ምግቦች መካከል ስላለው ልዩነት የሚናገር አይመስልም። ለምን? በመጀመሪያ ጳውሎስ ንፁህና ንፁህ ስላልሆኑት ምግቦች እየተጨነቀ አልነበረም። በሐዋ. ሥራ 15 ላይ የቀደመችው ቤተክርስትያን አማኞች በፀጋ መዳናቸውንና(የሐዋ. ሥራ 15፡7-11) ከምግብ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መመሪያዎችን መከተላቸውን እንዲቀጥሉ(የሐዋ. ሥራ 15፡19-20) አሳስባለች። ንፁህ የሆኑና ያልሆኑትን የሚዳስሰውና ሌሎቹ ህግጋት ከፀጋ ጋር የተቃረኑ አይደሉም። እንደውም ጳውሎስ እንደሚሞግተው አዲሱ ኪዳን ህጉን በልባችን ውስጥ አድርጓል(ዕብ. 8፡10-12)። ሆኖም እሱ እያለ ያለው የኢየሱስ ታላቅ መስዋዕትና ካህናዊ ምልጃ በቤተመቅደሱ ሲካሄዱ ከነበሩት የእንስሳት መስዋዕቶችና የሌዋውያኑ ምልጃ የሚበልጥ መሆኑን ነው(ዕብ. 8፡4-5፣ ዕብ. 10፡1-18)።

በሁለተኛ ደረጃ ዓውዱን ስንመለከት ጳውሎስ እየወቀሳቸው ያለው አማኞች ከተወሰኑ ምግቦች መታቀባቸውን ሳይሆን ያንን የሚያደርጉት ፀጋን ለማግኘት በመሆኑ ነበር(ዕብ. 13፡9)። ምናልባትም ፀጋን ያስገኛሉ ተብለው በሚታሰቡና የቤተመቅደሱ የእንስሳት መስዋዕቶች ርዝራዥ በሆኑ የአይሁድ ልማዶችና ምግቦች እንዳይሳተፉ እያስጠነቀቃቸው ይሆናል። ሆኖም ፀጋ በነዚህ ምግቦች አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእትና ምልጃ ብቻ ነው። አማኞች ሊመገቡት የሚገባቸው መስዋእት ያም የክርስቶስ መስቀል አላቸው(ዕብ. 13፡10፣ ዮሐ. 6፡47-58)።

በዕብራውያን መልዕክት ውስጥ ፀጋ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዙፋን ነው(ዕብ. 4፡16)። በክርስቶስ በኩል የመጣው ይህ ፀጋ ከራሱ ከእግዚአብሔር ዙፋን ጋር የተሳሰረ ጠንካራ መልህቅ ነው(ዕብ. 6፡19-20ን ከዕብ. 4፡16 ጋር ያነፃፅሩ)። በክርስቶስ መስዋዕት አማካኝነት የምንቀበለው ይህ ፀጋ መፅናትንና እርግጠኝነትን ወደ ልባችን ያመጣል። ልብ በዚህ መልኩ ሲፀና በአዳዲስ ትምህርቶች አይወሰድም(ዕብ. 13፡9)፤ ከእግዚአብሔርም መንገድ አይርቅም(ዕብ. 2፡1)። በክርስቶስ ሙሉ መስዋዕት ላይ ጠለቅ ብለው ያስቡ። በዚህ መስዋዕት ላይ “ለመጨመር” እኛ የምንሠራቸው ሥራዎች በክርስቶስ ላይ ከተመሠረተው ወንጌልና ፀጋ ጋር የሚቃረነው ለምንድነው?

መጋቢት 15
Mar 24

ከሰፈሩ ውጪ ወዳለው ኢየሱስ ሂዱ


ዕብራውያን 13፡10-14ን ከማርቆስ 8፡34፣ ከማቴ. 10፡38፣ ከሉቃስ 14፡27ና ከገላ. 2፡20 ጋር ያነፃፅሩ። ከሰፈሩ ውጪ ወዳለው ኢየሱስ መሄድ ማለት ምን ማለት ነው?



ከበሩ ውጪ ያለው ቦታ ከሰፈሩ ሁሉ እጅግ የቆሸሸው ነበር። መስዋዕት የሚሆኑት እንስሳት ሆድ ዕቃዎች የሚቃጠሉት እዚያ ነው(ዘሌ. 4፡12)። ለምፃሞች ከሰፈሩ ውጪ እንዲቀመጡ ይገደዱ ነበር(ዘሌ. 13፡46)፤ እግዚአብሔርን የሚሳደቡና ሌሎች ወንጀለኞች የሚወገሩት እዚያ ነበር(ዘሌ. 24፡10-16፣ 23፣ 1 ነገ. 21፡13፣ የሐዋ. ሥራ 7፡58)። እነዚህ መመሪያዎች የሚያሳስቡት እግዚአብሔር ያለው በሰፈሩ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ነበር። ንፁህ ያልሆነ ነገር ሁሉ ወደ ውጪ ይጣል ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በውስጥ ያልነፃ ወይም ያልተቀደሰ ነገርን ማየት አይፈልግም(ዘሁ. 5፡3፣ ዘዳ. 23፡14)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቃየው ከኢየሩሳሌም ውጪ ነበር (ዮሐ. 19፡1720)። በርሱ ላይ ሆኖ የነበረውን ሀፍረት ይህ ይበልጥ ያጎላዋል(ዕብ. 12፡2)።

“የእግዚአብሔርን ስም ተሳድበሃል” ተብሎ በይፋ ጥፋተኛ ስለተባለ በእስራኤል ተገፍቶ ከግንቡ ውጪ ተገደለ (ማር. 14፡63-64፣ ዘሌ. 24፡11፣ 16)። ኢየሱስ ከሰፈሩ ውጪ እንደ ማፈሪያ ርኩስና ያልተቀደሰ ነገር ተጣለ (ዕብ. 12፡2)። ሆኖም ጳውሎስ አማኞች እርሱ የተሸከመውን ነቀፌታ በመሸከም ከሰፈሩ ውጪ እንዲከተሉት ይመክራል (ዕብ. 12፡2፣ ዕብ. 13፡13)። ከግብፅ ብዙ ሃብት ይልቅ የክርስቶስን ስድብ ለመሸከም የመረጠው ሙሴ የተከተለው ይህንን መንገድ ነበር(ዕብ. 11፡26)።

ተቃርኖ በሚመስል መልኩ የዕብራውያን መልዕክት እንደሚነግረን እግዚአብሔር ያለው ከሰፈሩ ውጪ ሆኗል። ኢየሱስን ከሰፈሩ ውጪ መከተል ስድቡን ወይም ነቀፌታውን ከመሸከም በተጨማሪ እስራኤላውያን ለወርቁ ጥጃ ከሰገዱ በኋላ ሙሴ የእግዚአብሔርን ድንኳን ከሰፈሩ ውጪ ሲያወጣው ህዝቡ “ጌታን እንደፈለገ” እርሱን መፈለግን የሚያካትት ነው(ዘፀ. 33፡7)። ይህ ታሪክ እንደሚያስታውሰን ልክ እስራኤላውያን በወርቅ ጥጃው እንዳጋጠማቸው አማኝ ያልሆኑት ኢየሱስን ከካዱ አብንም እንደሚክዱ ማሳያ ነው (ዘፀ. 32፡33)። ስለዚህ የስቃይና የሀፍረት መንገድ ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ መንገድም ነው።

ጳውሎስ አንባቢዎች የእምነታቸው ጀማሪና ፈፃሚ የሆነውን ኢየሱስን እንዲከተሉ አሁን ያሉት መከራዎች ጊዜያዊና “የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን የሚያፈሩ” እንደሆኑ እንዲያውቁ እየጋበዛቸው ነው(ዕብ. 12፡11)። የተበላሸውን ከተማ ወይም ሰፈር ወደኋላ ትተው በእግዚአብሔር የተሠራችውንና የምትመጣውን ከተማ ለመፈለግ እየወጡ ነበር (ዕብ. 13፡14፣ ዕብ. 11፡10፣16)። ለእርስዎ ኢየሱስን ከሰፈሩ ውጪ መከተል ማለት ምን ማለት ነው? በዙሪያዎ ባሉ ሰዎች መገፋትና ሀፍረትን ሊያመጡብዎ የሚችሉ የእምነት ህይወት ገፅታዎች የትኞቹ ናቸው?

መጋቢት 16
Mar 25


ተጨማሪ ሀሳብ


“መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ አማኞች ከቅዱሳን ጋር ባላቸው ህብረት ጣፋጭነት ደስታ አደረጉ። ሩህሩህ፣ ለሌላው የሚያስቡ፣ ለእውነቱ ሲሉ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ነበሩ። በየዕለቱ እርስ በእርስ በነበራቸው ጊዜ ክርስቶስ በነርሱ ላይ ያፈሰሰውን ፍቅር አሳዩ። ራስ ወዳድ ባልሆኑ ቃላትና ተግባራት ይህንን ፍቅር በሌሎች ልቦች ለመለኮስ ተጉ። . . . “ቀስ በቀስ ግን ለውጥ መጣ። አማኞቹ በሌላው አማኝ ውስጥ ስህተትን መፈለግ ጀመሩ። በስህተቶች ላይ በማተኮርና ትሁት ባልሆኑ ቃላት በመነጋገር የአዳኙና የፍቅሩ ምስል ጠፋባቸው። ከውጭ በሚታዩ ስርዓቶች፣ ከእምነት በመነጨው ተግባር ሳይሆን በመርሆቹ ላይ ብቻ አክራሪዎች ሆኑ። ሌሎችን ለመኮነን ካላቸው ትጋት የተነሳ የራሳቸው ስህተቶች አልታይ አሏቸው። ክርስቶስ የሰጣቸውን ወንድማዊ ፍቅር አጡ፤ በሚያሳዝን ሁኔታም መጥፋታቸውን እንኳን ማወቅ አቃታቸው። ደስታና ሀሴት ከህይወታቸው እየወጡ፣ ለእግዚአብሔር ፍቅር ልባቸውን ዘግተው ሲቀጥሉ በጨለማ መሄድ እንደሚጀምሩ አላስተዋሉም።

“ያ የወንድማማች ፍቅር ከቤተክርስትያን እየጠፋ መሆኑን የተረዳው ዮሐንስ ስለዚያ ፍቅር አስፈላጊነት ደጋግሞ ለመናቸው። ለቤተክርስትያናቱ የላካቸው ደብዳቤዎች በነዚህ ኃሳቦች የተሞሉ ነበሩ። “የተወደዳችሁ፣ እርስ በእርስ እንዋደድ”፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ የሚወድም ከእግዚአብሔር የተወለደና እግዚአብሔርን የሚያውቅ ነው” “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።” ብሎ ፅፏል። (1 ዮሐ. 4፡7-11)። Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 547, 548.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.የክርስትና ህይወት በአማኙና በኢየሱስ መካከል ያለ የግል ግንኙነት እንደሆነ ይታሰባል። ሆኖም ይህ የክርስትና ህይወት የተወሰነው ገፅታ ብቻ ነው። እግዚአብሔር እንደ ሕዝብ(በህብረት) እየመራን እንዳለ ማስታወስ የሚጠቅመው ለምንድነው? በህብረቱ ውስጥ የኔ ኃላፊነቶች ምንድናቸው? ከህብረቱስ ምንድነው መጠበቅ ያለብኝ?

2.በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ የወንድማማች ፍቅር ጠንካራ እንደሆነ የተሻሉት ማሳያዎች ምን ምን ናቸው? በሰንበት ትምህርት ክፍልዎ ይዘርዝሯቸው።

3.እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር ምንድነው? ባህሪያቱ፣ መንስኤዎቹና ውጤቶቹ ምንድናቸው? ከሀሰተኛ የወንድማማች ፍቅር የምንለየው በምንድነው?

የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ ማሳሰቢያ የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡ ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL