የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሰኔ 19 - 25

1ኛ ትምህርት

Jun 26–Jul 2




በ24/7 ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 2:1–3፣ ኤር. 45:1–5፣ ዘፀ. 20:11፣ 2ሳሙ. 7:12፣ ማር. 6:30–32፣ ዘፍ 4:1–17።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤ እጅግም ትጓጓለታለች፤ ልቤና ሥጋዬም፣ ለሕያው አምላክ እልል በሉ።” መዝ. 84፡2)

ቲ ክ-ቶክ፣ ቲክ-ቶክ፣ ቲክ-ቶክ። ሰዓቱ ያለማቋረጥና ያለ ርኅራኄ ይገሰግሳል። ሰንበት ሊገባ የቀሩት ሁለት ሰዓታት ብቻ ናቸው። ሜሪ አነስተኛ መጠን ያለውን የአፓርታማ ቤቷን መልከት አደረገችና በረጅሙ ተነፈሰች። የልጆቿ መጫወቻዎች በሳሎኑ እንደተዝረከረኩ ነው፤ ወጥ ቤቱ በሚታጠቡ ዕቃዎች ተሞልቷል፤ ትንሽዋ ልጇ ሣራ አተኩሷት አልጋ ላይ ጋደም ብላለች። ነገ ጠኋት ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ሰዎችን--እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ ለመቀበል ስለ ተስማማች ከተለመደው ሰዓት 30 ደቂቃ ቀደም ብላ ከቤት መውጣት ይኖርባታል። ነገ የተረጋጋ ቀን ይኖረኛል ስትል ሜሪ ሰንበትን በጉጉት መጠባበቅ ጀመረች።

በተመሳሳይ ወቅት በከተማው ሌላኛው ክፍል የሚገኘው ባለቤቷ ጆሽ ሣምንታዊውን የአስቤዛ ክፍያ ለመፈጸም ተሰልፏል። የትራፊክ መጨናነቁ ደግሞ ተነስቶበታል። የመውጫ መስመሮች በረጃጅም የመኪና ሰልፎች ተሞልተዋል። ሰዉ ሁሉ ተመሳሳይ ጊዜ ጠብቆ የሚገበይ ይመስላል። የሆነ ዕረፍት ያስፈልገኛል። በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም ሲል ጆሽ ለራሱ አጉተመተመ።

ህይወታችን--በጥድፊያ ሠዓታት፣ በሥራ ሠዓታት፣ በህክምና ቀጠሮዎች፣ በስካይፕ ውይይቶች፣ በግብይት እና በትምህርት ቤት ተግባራት የተመራ ነው። የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ፣ ሚድ ባስ ወይም ሞተር ብስክሌት ተጠቅመን ወደ ቤት ስንሄድና ስንመለስ በዙሪያችን ካለው ዓለም ጋር የሚኖረን የማያቋርጥ የግንኙነት መስተጋብር በትክክል አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሸፋፍነን እንዳናልፍ ያሰጋል።

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ መሃል ዕረፍት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ሰኔ 20
Jun 27

የተዳከመ እና የዛለ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡1-3። ማንም የድካም ስሜት ባልነበረው በዚያ ወቅት እግዚአብሔር ለምን የዕረፍት ቀን ፈጠረ?



ራሳችን በራሳችን ላይ በጣልነው በጫና የተሞላ የህይወት ዘይቤ ብን ብለን ከመጥፋታችን አስቀድሞ--እነሆ እግዚአብሔር ልቦናችንን ሕያው አድርጎ የሚያፍታታ ምልክት አቋቋመ። ይህ ዕለት ቆም ብለን የሕይወትን ጸጋ በማስተዋል የምናጣጥምበትና ሐሴት የምናደርግበት ነው። የዕረፍት እንጂ የሥራ ያልሆነው ቀን--በሣሩ፣ በዱር በእንስሳቱ፣ በውሃው--ከሁሉ በላይ ደግሞ የማንኛውም መልካም ነገር ፈጣሪ በሆነው አምላክ ስጦታ ደስ የምንሰኝበት ነው።

ይህ በኤደን ግዞት ወቅት ያበቃለት የአንድ ጊዜ ብቻ ግብዣ አልነበረም። ግብዣው የጊዜን ፈተና መቋቋም እንደሚጠይቅ የሚያውቀው አምላክ፤ በቀደመ የጊዜ ቀመሩ የሰንበትን እረፍት አቋቋመ። በየሣምንቱ ሰባተኛው ቀን ላይ በሚውለው በዕረፍት የተሞላ የፍጥረት መታሰቢያ ዕለት ሐሴት እናደርግ ዘንድ እነሆ ዛሬም ተደጋጋሚ ግብዣ እያቀረበልን ይገኛል። እኛ ዛሬ የምንጠቀማቸው መሣሪያዎች ጉልበት ቆጣቢ ከመሆናቸው አኳያ-ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የነበሩት ሕዝቦች ዓይነት ድካም አያውቀንም ብሎ የሚያስብ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን የዕረፍት ዕጥረት ያለ ይመስላል። ሥራ የማንሠራባቸው ጊዜያቶች እንኳ የሚያልፉት ፍርሃትና ጭንቀት በተሞሉ እንቅስቃሴዎች ነው። የቱንም ያህል ተግባራችንን ለመከወን ብንሠራም የሚቀረን እንዳለና እንደ ተንቀራፈፍን ሆኖ ይሰማናል።

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በቂ እንቅልፍ እያገኘን አይደለም። በንቃት ለመሥራት በሚል ዛሬ ብዙዎች በከፍተኛ ደረጃ የቡና እና ሻይ ጥገኞች ናቸው። ምንም እንኳ ፈጣን ሞባይል ስልኮች፣ ኮምፒውተሮችና በይነመረብ ግንኙነቶች ቢኖሩንም አሁንም በቂ ጊዜ ያለን አይመስልም። ማረፋችን አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምራሉ? ማር. 6፡31፣ መዝ. 4፡8፣ ዘፀ. 23፡12፣ ዘዳ. 5:14፣ ማቴ. 11፡28።



የፈጠረን አምላክ አካላዊ ዕረፍት እንደሚያስፈልገን ያውቃል። እርሱ አካላዊ ዕረፍት የምናገኝበትን ዕድል ይሰጠን ዘንድ ኡደቶችን በጊዜ-በሌሊት እና በሰንበት አዋቀረ። የሱስን የሕይወታችን ጌታ አድርገን መቀበላችን፤ ጊዜን የምናርፍበት አድርገን በጽኑ የመውሰድ ኃላፊነታችንንም እንዲሁ ያካትታል። የሰንበት ዕረፍት እንደው ምክረ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ቆምጨጭ ያለ ትእዛዝ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።

በውጥረት የተሞላው የገዛ ስብዕናዎ ምን ይመስላል? እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን አካላዊ እና መንፈሳዊ ዕረፍት በተሻለ ለመለማመድ ምን ማድረግ ይችላሉ?





ሰኔ 21
Jun 28

በባዶ መባዘን


ከመጠን በላይ ልፋት ያለው ሥራ መሥራታችንን ተከትሎ የሚከሰት የዕንቅልፍ እጦት እና ድካም እወነተኛ ችግር ነው። ሆኖም “በስሜት ባዶ” ሆነን እየባዘን እንደሆነ የሚሰማን ከሆነ ግን--ይህ ይበልጥ አስጨናቂ ነው። ዕንቅልፍ ማጣት በስሜታዊ ፈተናዎች ላይ ሲደመር አብልጠን ተስፋ የቆረጥን ልንሆን እንችላለን።

በቅርቡ ባቢሎናውያን የሚያደርሱትን ውድመት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለው ሁከት፣ መከራና ጥፋት--በእነዚያ የየሩሳሌም የመጨረሻዎቹ በሁከት የተሞሉ ዓመታት፣ የነቢዩ ኤርሚያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት አዘውትሮ ሳይሰማው እንዳልቀረ ይታመናል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 45፡1-5። እንደ ሥነ ልቡና ሐኪም በባሮክ ስሜታዊ የጤና ሁናቴ ዙሪያ ያለውን የምርመራ ውጤት ይጻፉ።



እግዚአብሔር ለእርስዎ በግል መልእክት ቢልክ ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማዎ እንደሚችል መገመት ይችላሉ? ባሮክ ከእግዚአብሔር ዙፋን በቀጥታ የተላከ መልእክት ተቀበለ (ኤር. 45፡2)። ይህ የሆነው “በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት በአራተኛው ዓመት” እንደሆነ የተነገረን ሲሆን፤ ይኸውም ከክርስቶስ ልደት በፊት 605 ወይም 604 ላይ ነው። ሰዎች በስሜት ባዶ ሆነው ሲባዝኑ ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ኤር. 45፡3 ጥሩ መግለጫ ይሰጠናል። በዚህ ወቅት ስለነበረው ሁናቴ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደምናውቀው የባሮክ የልቅሶ ድምጾች መሰረተ ቢስ አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ባሮክ ተስፋ ለመቁረጥም ሆነ የተዳከመ ስሜት ውስጥ ለመግባት ማለፊያ ምክንያቶች ነበሩት። በዚያን ጊዜ ብዙ መጥፎ ነገሮች እየተከሰቱ የነበረ ሲሆን፤ ተጨማሪ ክስተቶችም እየመጡ ነበር።

እግዚአብሔር ለባሮክ ህመም እና መታወክ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? ኤር.45: 4-5።



እግዚአብሔር ለባሮክ ተጨባጭ ህመም የሰጠው ምላሽ አምላካዊው የልብ መሰበርና ህመም ከባሮክ እጅግ ሳይበልጥ እንዳልቀረ ያሳየናል። እርሱ የሩሳሌምን ቢገነባም አሁን ግን ሊያፈርሳት ነው። እስራኤልን እንደ ወይን ቢተክልም (ኢሳ. 5፡1-7) አሁን ግን ነቅሎ ወደ ግዞት ሊሰድ ነው። ይህ ሕዝቡ ላይ እንዲደርስ የጌታ ፍላጎት ባይሆንም ነገር ግን በእርሱ ላይ በማመጻቸው የተነሳ መምጣቱ የግድ ሆነ። ሆኖም ለባሮክ በዋሻው መጨረሻ ብርሃን ነበር። በአስከፊው ውድመት፣ ግዞትና እጦት መሃልም እንኳ እግዚአብሔር የባሮክን ህይወት ይታደጋል።

እግዚአብሔር ለባሮክ የተናገራቸውን ቃላት ደግመው ያንብቡ። ከቃላቱ ምን ዓይነት ጠቅለል ያለ መልእክት ለራሳችን መውሰድ እንችላለን? ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን--እግዚአብሔር በመጨረሻ ለእኛ ስለ መቆሙ ምን ይነግረናል?





ሰኔ 22
Jun 29

ዕረፍት በብሉይ ኪዳን ሲገለጽ


እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ ሁላችን ዕረፍት ያስፈልገናል። ይህ ጭብጥ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰበት ምክንያቱ ይኸው ነው። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለሥራ እና እንቅስቃሴ ቢፈጥረንም፤ እንቅስቃሴአችን በዕረፍት ሊታጀብ የግድ ነው።

ለምሳሌ የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ዕረፍት አመላካች የሆኑ በርካታ ቃላቶች ተካተውበታል። በዘፍ. 2፡2-3 እግዚአብሔር አዲስ አድርጎ በፈጠረው ሰባተኛ ቀን ማረፉን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው ሰንበት የተሰኘው ግሥ “ከመሥራት መታቀብ፣ ማረፍ፣ ዕለቱን እንደ በአል መውሰድ” የሚል ቃላዊ ፍቺ አለው። በተመሳሳይ በዘፀ. 5፡5 ምክኒያታዊ ቅርጽ ይዞ ጥቅም ላይ የዋለው ግስ “እንዳይሠሩ ማድረግ” በሚል ተተርጉሞ እናገኘዋለን። የተቆጣው ፈርኦን “እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” በማለት ሙሴን ሲከሰው ይታያል። እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሰንበት ማረፉን አስመልክቶ የቀረበው የአራተኛው ትእዛዝ ማጣቀሻ በዕብራውያኑ የቃል ቅርጽ--ኑአክ ተገልጧል (ዘፀ. 20፡11፣ ዘዳ. 5፡14)።

ይህ ግሥ በኢዮ. 3፡13 “ዕረፍት” በሚል አውድ የተተረጎመ ሲሆን፤ በሌላ ስፍራ ከቃል ኪዳኑ ታቦት ጋር በተያያዘ በዘኁ. 10፡36 ተመሳሳይ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ እንመለከታለን። በ2ኛ ነገሥ. 2፡15 የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ እንደ “ዐረፈ” ልብ ይሏል።

ሌላው አስፈላጊ የቃል ቅርጽ ሻቃት ሲሆን “ማረፍ፣ ፋታ ማግኘት፣ ጸጥ ማለት” የሚል ፍቺ አለው። ከመጀመሪያው የኢያሱ ድል በኋላ ምድሪቱ ከጦርነት ማረፏን ለመግለጽ ቃሉ በኢያሱ 11፡23 ጥቅም ላይ ውሏል። ይህ ቃል “ሰላም” አመላካች ሆኖ በኢያሱ እና መሳፍንት መጽሐፍ ቀርቦአል። ሌላው ግስ ረጋ የሚል ሲሆን ይህም በተመሳሳይ ዕረፍትን ለማመልከት ያገለግላል። አለመታዘዛቸውን አስመልክቶ በዘዳግም በተሰጠው ማስጠንቀቂያ፤ በግዞት ሕይወታቸው እርጋታ ወይም ዕረፍት እንደማያገኙ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይናገራል (ዘዳ. 28፡65)። በተመሳሳይ ይኸው ግስ በኤር. 50፡24 በያዘው ምክንያታዊ ቅርጽ እረፍት መስጠት አለመቻልን ይገልጸል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 31፡16፣ 1ሳሙ. 7፡12። ስለ ምን ዓይነት ዕረፍት እየተገረ ነው?



ሁለቱም ቁጥሮች ሻካብ የሰተሰኘውን ግሥ ተፈጥሯዊ አገላለጽ የሚጠቀሙ ሲሆን፤ “ጋደም ማለት፣ መተኛት” የሚል ፍቺ ይዘዋል። “ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ” (2ሳሙ. 7፡12) ሲል እግዚአብሔር ለዳዊት የተስፋ ቃል ሰጥቶት ነበር።

ረጅም ዕረፍትን የሚያመላክቱ (ያልተሟሉ) የተለያዩ የዕብራይስጥ ግሦች ዝርዝር--የዕረፍት ሥነ መለኮታዊ ጽንሰ ሀሳብ ከአንድ ወይም ሁለት ቃላት ጋር እንደማይገናኝ ማስተዋል እንችል ዘንድ ይረዳናል። እኛ በተናጠል እና በጋራ እናርፋለን። ዕረፍት--አካላዊ፣ ማህበራዊና ስሜታዊ በሆኑ መንገዶች የሚነካን እንጂ በሰንበት ብቻ የተገደበ አይደለም።

ሞት በእርግጥ ጠላት እንደመሆኑ አንድ ቀን ይወገዳል። በሞት ለተለዩን ወገኖች የቱንም ያህል ብናዝንና ብንናፍቃቸውም፤ ቢያንስ በአሁኑ ወቅት ማረፋቸውን ማወቃችን ለምን ያጽናናል?

ሰኔ 23
Jun 30

ዕረፍት በአዲስ ኪዳን


በአዲስ ኪዳን ብዙውን ጊዜ ዕረፍት የሚለው ቃል ቅርጽ አናፓዎ ሲሆን “ማረፍ፣ ዘና ማለት፣ መታደስ” የሚል ፍቺ አለው። የሱስ ዕረፍትን አስመልክቶ ከተናገራቸው ዝነኛ መግለጫዎች አንዱ በማቴ. 11፡28 ጥቅም ላይ ውሏል፡ “‘እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።’ ” መልእክቱ አካላዊ ዕረፍትን ሊያመላክት ይችላል (ማቴ. 26፡45)። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ባቀረበው የመጨረሻ ሰላምታ መንፈሱን ያደሱለት ሰዎች በመምጣታቸው የተሰማውን ደስታ ይገልጻል (1ቆሮ. 16፡18)። ዕረፍትን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው ሌላው ግሥ ሄሲህቻዙ ነው። የሱስ በመቃብር ባረፈ ጊዜ የነበረውን የደቀ መዛሙርቱን የሰንበት ዕረፍት ይገልጻል (ሉቃ. 23፡56)። በተጨማሪ ቃሉ በጸጥታ የተሞላ የሕይወት ዘይቤን ለመግለጽ ጥቅም ላይ (1ተሰ. 4፡11) የዋለ ሲሆን፤ የተቃውሞ አለመኖርንና ዝም ማለትን ያመለክታል (ሐዋ. 11፡18)።

እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከፍጥረት ሥራው ማረፉን አስመልክቶ ዕብ. 4፡ 4 ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው የግሪኩ ቃል--ካታፓዎ “ማቆም፣ ወደ ዕረፍት መምጣት፣ ማረፍ” በሚል ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የተተረጎመውን የብሉይ ኪዳን ቃል ያስተጋባል። የሚደንቀው፤ በአዲስ ኪዳን የዚህ ግሥ አጠቃቀም አብዛኛው ተከስቶ የሚስተዋለው በዕብ. ምዕ. 4 ላይ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 6፡30-32። በወቅቱ ከነበራቸው ሰፊ የወንጌል ተልዕኮ ዕድሎች አኳያ ደቀ መዛሙርቱ ገለል ብለው ከእርሱ ጋር እንዲያርፉ የሱስ ለምን አደረገ? ስለዚህ ጥያቄ ሲያስቡ የማር. ምዕ. 6 ዐውደ ጽሑፍን ሰፋ አድርገው ይመልከቱ።



“ ‘ እስቲ ብቻችሁን… ጥቂት ዕረፉ’ ” (ማር. 6፡31) የሚለው አነጋገር በግብዣ መልክ የቀረበ አልነበረም። ይልቁንም በትእዛዝ መልክ የተገለጸ ነው። የሱስ የደቀ መዛሙርቱ አካላዊና ስሜታዊ ደኅንነት ያሳስበዋል። እነዚህ ወገኖች የሱስ ሁለት፣ ሁለት አድርጎ ከላካቸው ሰፊ የወንጌል አገልግሎት ገና መመለሳቸው ነበር (ማር. 6፡7)። ማር. 6፡30--በደስታ መመለሳቸውን ይገልጻል። ከሁኔታቸው እንደሚታየው የልባቸው የደረሰ ይመስላል። ድሎቻቸውንም ሆነ ጉድለቶቻቸውን ለየሱስ ማካፈል ፈልገዋል። ሆኖም የሱስ አስቆማቸውና መጀመሪያ እንዲያርፉ አደረገ። በዚህ ዙሪያ ማርቆስ ማብራሪያ የታከለበት ማስታወሻ አካቷል፡ “ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ አልነበራቸውም።” (ማር. 6፡31)። ለአምላካዊው ሥራ መዛልና ያለ ዕረፍት ማገልገል የደቀ መዛሙርቱ አንዱና እውነተኛው ፈተና ነበር። የዕረፍት ጊዜያት በማቀድ ጤንነታችንና ስሜታዊ ደኅንነታችንን መጠበቅ እንዳለብን የሱስ ያስታውሰናል።

የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢዎ ወይም ሌላ የሚያውቁት አገልጋይ የጌታን ሥራ በመሥራት ዝሎ እንዳይወድቅ፣ ፋታ እንዲያገኝና እንዲያርፍ ሊረዱ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ይህ ሰው ዕረፍት ያገኝ ዘንድ አድናቆትዎን በመግለጽና በመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?





ሰኔ 24
Jul 1

ኮብላይና ተቅበዝባዥ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡1-12። ቃየንን በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ያደረገው ምን ነበር? ዘፍ. 4፡12።



እግዚአብሔር አቤልንና መሥዋዕቱን ለምን እንዳከበረ እና በቃየንና መሥዋዕቱ ግን ለምን እንዳልተደሰተ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም (ዘፍ. 4፡4-5)። ነገር ግን ይህ ለምን እንደሆነ እናውቃለን። “ቃየን ቃል በተገባው መሥዋዕት እና መሥዋዕት በማቅረብ አስፈላጊነት ዙሪያ እያጉረመረመና ጎዶሎ እምነት በልቡ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ቀረበ። የእርሱ ስጦታ ለኃጢአት መጸጸቱን ፈጽሞ አይገልጽም ነበር። እርሱ ተሰምቶት የነበረው ስሜት ዛሬ ብዙዎች የሚሰማቸው ዓይነት ስሜት ሲሆን ይኸውም ያንን ቃል የተገባውን የኃጢአት ሥርየት የሚያመጣውን በማመን ፋንታ ሙሉ ለሙሉ በራስ ደኅንነት በመተማመን በእግዚአብሔር ቁልጭ ብሎ የቀረበውን ዕቅድ ያለመከተል ድካም ነው። ቃየን በራሱ የሚታመንበትን መንገድ መረጠ። የገዛ ሥራውን ይዞ ቀረበ።” የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 71።

እግዚአብሔር “በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ” ብሎ ቃየንን ስለተናገረው ቃየን ይህን ማንነት አልወሰደም። ይልቁንም ኃጢአተኛ ድርጊቱ እና አለመታዘዙ የዚህ ውጤት ባለቤት አደረገው። በእግዚአብሔር ውስጥ ዕረፍት ማግኘት ያልቻለው ቃየን፤ እውነተኛውን ዕረፍት በሌላ በማንኛውም መንገድ ሊያገኘው እንደማይችል ተገነዘበ።

“ተመለከተ” (ዘፍ. 4፡4) በሚል የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “በቅርበት ተመለከተ፣ በጥንቃቄ አጤነ” የሚል ፍቺ አለው። አምላካዊው በጥንቃቄ የተሞላ ምልከታ አብልጦ ትኩረት ያደረገው በመሥዋዕቱ ላይ ሳይሆን፤ በአቅራቢው ባህሪና አመለካከት ላይ ነው። እግዚአብሔር የቃየንን የፍራፍሬ መሥዋዕት አለመቀበሉ በዘፈቀደ የሚሠራ አምላክ ሆኖ እንደ አጋጣሚ የሰጠው ምላሽ አልነበረም። ይልቁንም መባውን የሚያቀርበውን ሰው ባህሪ፣ አመለካከትና ተነሳሽነት በጥንቃቄ የመመርመርና የመመዘን ሂደትን ይገልጻል። ጥሩ የፍርድ ምርመራ ምሳሌ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ--ዘፍ. 4፡13-17 እና ቃየን ለአምላካዊው ፍርድ የሰጠውን ምላሽ ይግለጹ።



ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ስንሞክር ዕረፍት አልባ እንሆናለን። የአምላካዊውን ጸጋ ናፍቆታችንን በቁሳቁሶች፣ በሰብዓዊ ግንኙነቶች ወይም ራሳችንን ከመጠን በላይ በሥራ በመወጠር ለመሙላት እንሞክራለን። ቃየን ሥርወ መንግሥት እና ከተማ መገንባት ጀመረ። ሁለቱም ታላላቅ ስኬቶች እንደመሆናቸው ስለ ቆራጥነቱና ጉልበቱ ይናገራሉ። ሆኖም እግዚአብሔር የሌለበት ሥርወ መንግሥትና ዐመጸኛ ከተማ ከሆነ፤ መጨረሻው ከንቱ ነው። ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ እንደሚስተዋለው ኃጢአታችን የሚያስከትለው መዘዝ ተጋሪ ብንሆንም፤ ስለ መተላለፋችን በመስቀል ላይ የተሰጠንን ይቅርታ መቀበል እንዴት መማር እንችላለን?





ሰኔ 25
Jul 2


ተጨማሪ ሀሳብ


“እንደ አይሁድ ምሑራን አስተሳሰብ ከሆነ የኃይማኖት ፍሬ ነገሩ የአገልግሎት ሽርጉድ ነው። ከሌሎች የተሻሉ ኃይማኖተኛ መሆናቸውን ለማሳወቅ በውጫዊ አገልግሎት ተማመኑ። ስለዚህ ነፍሳቸውን ከእግዚአብሔር ለዩ፤ በራስ የመተማመን ስሜትም አደረባቸው። ይህ ዓይነት አደጋ አሁንም አለ። የሥራ ዓይነት እየጨመረ እንደ ሔደ መጠን ሰዎች በእግዚአብሔር የሚሠሩት ሥራ ሲሳካላቸው በሰብአዊ ዕቅድና ስልት የመተማመን አደጋ ይኖራል። የጸሎትና የእምነት መቀነስ አዝማሚያ ይከሰታል። እኛም እንደ ደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር መተማመናችንን የሚያሳካው የእርሱ ኃይል መሆኑን በመረዳት ሁል ጊዜ የሱስን መመልከት አለብን። ለጠፉት ነፍሳት ደኅንነት በቅንነት መሥራት ቢኖርብንም በእርጋታ ለማሰላሰል፤ ለመጸለይና የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ጊዜ ሊኖረን ይገባል። በመጨረሻ ጥሩ ውጤት ለማስገኘት ብቃት የሚኖረው በብዙ ጸሎት የተከናወነና በክርስቶስ ጸጋ የተቀደሰ ሥራ ነው።” የዘመናት ምኞት ገጽ 367።


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.በነገሮች የበላይ የመሆን የማያቋርጥ ግፊት፣ በማንኛውም ጊዜ እዚህም እዚያም አለሁ ማለትና በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት በሌላቸው መርኅዎች ወይም እርሱ ባልሰጠው መንገድ ለመኖር መሞከር--ሰዎችን በስሜት፣ በአካል እና በመንፈስ በሽተኛ ያደርጋል። ቤተ ክርስቲያንዎ የዛሉና የደከሙ ሰዎች ዕረፍት የሚያገኙባት እንግዳ መቀበያ ስፍራ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

2.ለእግዚአብሔር መልካም ነገሮችን እያደረግን ዕረፍት ዐልባዎች መሆን እንችላለን? በማር. 6፡30-32 ስለ ቀረበው የየሱስ እና የደቀ መዛሙርቱ ታሪክ ያስቡና አተገባበሩን በሰንበት ትምህርት ጥናት ላይ ተወያዩ።

3.በ1899 የመኪና ፍጥነት ክብረ ወሰን ተሰብሮ ነበር። አንድ አሽርካሪ መኪናውን በሰዓት 63 ኪሎ ሜትር በመንዳት ክብረ ወሰኑን ማሻሻል ችሎ ነበር። በእርግጥ ዛሬ ተሽከርካሪዎች ከዚህ በላቀ ፍጥነት ይከንፋሉ። በሞባይል ስልኮቻችን ውስጥ ያሉት የአቀነባባሪዎች ፍጥነት ከአንድ ትውልድ በፊት ከነበሩት እጅግ ፈጣንና ትላልቅ ኮምፒተሮች የላቀ ይፈጥናሉ። የአየር ጉዞም እንዲሁ ከቀድሞው ይልቅ ፈጣን ነው። ለማንሣት የተፈለገው ነጥብ--ዛሬ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ቀድሞ ከነበረው እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም ዛሬም በጥድፊያ ውስጥ እንደሆንና ዕረፍት እንደሌለን ይሰማናል። ይህ ስለ መሰረታዊ የሰው ተፈጥሮ ምን ሊነግረን ይገባል? እግዚአብሔር ዕረፍትን ከትእዛዛቱ አንዱ አድርጎ አጽንኦት የሰጠው ለምንድን ነው?

4.ኃጢአት ከመግባቱ አስቀድሞ በኤደን የአትክልት ስፍራ የሰንበት ዕረፍት በመቋቋሙ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ትኩረት ያድርጉ። ከዚህ እውነት አስደሳች ሥነ መለኮታዊ አንደምታ በተጨማሪ፤ ኃጢአት ዐልባ በነበረው ፍጹም ዓለም እንኳ ዕረፍት ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL