የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሰኔ 12 - 18

13ኛ ትምህርት

Jun 19 - Jun 25




የአዲሱ ቃል ኪዳን ሕይወት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 1:4፣ ዮሐ. 5:24፣ ሮሜ 3:24-25፣ 2ቆሮ. 5:21፣ 1ዮሐ. 4:16፣ ራእ. 2:11፣ ራእ. 20:6፣ 14፣ ራእ. 21:8።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ’ ” (ዮሐ. 10:10)

እግዚአብሔር አምላክ እናንተን ከኃጢአት የማድነው በዚህ መንገድ ነው ያለበትን-ቃል ኪዳኑን እያጠናን እነሆ ይህን ሩብ ዓመት ከርመናል። ምንም እንኳ ውጤቱ፣ ማለትም የታላቁ ቃል ኪዳን ፍጻሜ በአዲሲቱ ምድር የዘላለማዊ ሕይወት ባለቤት በመሆን የሚደመደም ቢሆንም፤ ዛሬም በቃል ኪዳኑ በረከቶች ሐሴት ልናደርግ ይገባል እንጂ እስከዚያ መጠበቅ የለብንም። ጌታ ስለ አሁኑ ሕይወታችን ያስባል፣ ምርጥ የሆነውን እንድናገኝ ይፈልጋል። ቃል ኪዳኑ-ይህን፣ ይህን፣ ይህን አድርጉና ከረጅም ዕረፍት በኋላ ያን የተዘጋጀላችሁን ሽልማት ቅቀበላላችሁ የሚል አንደምታ የለውም። ይልቁንም ሽልማቶቹ፣ ስጦታዎቹ-በእምነት ወደ ቃል ኪዳኑ ግንኙነት የገቡ ሰዎች አሁን በዚህ ምድር ሊያገኙ የሚችሏቸው በረከቶች ናቸው።

ቃል ኪዳኑን አስመልክቶ በተከታታይ ስናጠናቸው የነበሩ ትምህርቶች የመጨረሻ ክፍል የሆነው የዚህ ሣምንት ጥናታችን፤ ከእነዚህ ወዲያውኑ ከሚገኙ በረከቶች መካከል በጥቂቶቹ ላይ ምልከታ ያደርጋል። ከአምላካዊው ጸጋ የሚመጡ አንዳንድ ተስፋዎች በልባችን ይፈሳሉ። ለምን--እርሱ በልባችን በራፍ ቆሞ ሲያንኳኳ ሰምተን ስለከፈትንለት። በእርግጥ በዚህ ሣምንት ልንዳስስ ከምንችለው በላይ ብዙ በረከቶች አሉ። ሆኖም ይህ ጅማሮ ነው--ፍጻሜ የሌለው ነገር ጅማሮ።

ሳምንቱን በጨረፍታ: የደስታ ስሜት ሊሰማን የሚገባው ለምንድን ነው? ያንን ተስፋ በምን መሠረት የራሳችን አድርገን መቁጠር እንችላለን? ከጥፋተኝነት ሸክም ነጻ ሊያደርገን የሚገባው ቃል ኪዳኑ--ምንድን ነው? የአዲስ ልብ ባለቤት መሆን-ምን ማለት ነው?



ሰኔ 13
Jun 20

ደስታ


“ደስታችንም ፍጹም ይሆን ዘንድ ይህን እንጽፍላችኋለን” (1ዮሐ. 1:4)። ዮሐንስ በዚህ ስፍራ የጻፈውን ልብ ብለው ይመልከቱ። እኛ እንደ ቃል ኪዳን ሕዝቦች ካገኘናቸው ታላላቅ ጥቅሞች መካከል አንዱ የደስታ ተስፋ መሆኑን በጥቂት ቀለል ያሉ ቃላት ይገልጻል።

እንደ ክርስቲያን በስሜታዊነት መሄድ እንደሌለብን ተደጋግሞ ተነግሮናል። እምነት ስሜት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ከስሜቶቻችን በሻገር እውነት የሆነውን ተከትሎ መጓዝ ግድ ይሆናል። ነገር ግን በተመሳሳይ--ስሜት የለሽ፣ ስሜት ዐልባ የአእምሮ ውቅር ባይኖረን ኖሮ ሰው ባልሆንን ነበር። ስሜቶቻችንን መካድ አንችልም። እኛ ማድረግ ያለብን እነዚህን ስሜቶች ማስተዋል፣ ተገቢውን ሚና መስጠት እና በተቻለ መጠን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። ከዚህ ውጪ እነርሱን መካድ--ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ መካድ ነው። በእርግጥ ይህ ቁጥር የሚለው ስሜት ሊኖረን ብቻ አይገባም ሳይሆን (በዚህ ጉዳይ--ደስታ) የተሟሉ መሆንም አለባቸው ነው። ስሜቶቻችን ሊካዱ ይገባል የሚል አንደምታ አይደመጥም--አይደል?

ከምዕራፉ መግቢያ ጀምሮ ከላይ የቀረበውን የቁጥሩን ዐውደ ሀሳብ ያንብቡ። ዮሐንስ የጥንት ክርስቲያኖችን ደስታ ሙሉ ያደርግላቸዋል ብሎ ተስፋ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ይህ ነገር ለምን ደስታ ሊሰጣቸው ይገባል?



ዮሐንስ ከመጀመሪያዎቹ ዐሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር። ከክርስቶስ የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎት ጀምሮ ለማለት በሚያስችል መልኩ እርሱ እዚያ ነበር። የሱስ ላደረገው እያንዳንዱ አስገራሚ ነገር ምስክር ነበር (እርሱ፡ በመስቀሉ፣ በጌቴሴማኒ እና የየሱስ መልክ በቅጽበት በተቀየረበት ወቅት በዚያ ነበር)። ስለሆነም እንደ አንድ የዓይን ምስክር ስለዚህ ጉዳይ ለመናገር በእርግጥ ብቁ ነበር። እንዲሁም ዮሐንስ አጽንኦት የሰጠው ስለ ራሱ ሳይሆን፤ ደቀ መዛሙርት እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከእራሱ ከእግዚአብሔርም ጋር ሕብረት ይፈጥሩ ዘንድ የሱስ ለእነርሱ ባደረገው ነገር ዙሪያ እንደሆነ ልብ ይሏል። እኛም ከጌታ ጋር ወደዚህ የቅርብ ወዳጅነት እንድንገባ የሱስ መንገዱን ከፍቶልናል። የዚህ ሕብረት አንዱ ውጤት-ግንኙነቱ ደስታ መሆኑ ነው። ስለ የሱስ የሰሙት ሁሉ እውነት መሆኑን እንዲያውቁ የሚፈልገው ዮሐንስ (እርሱ ያየውን፣ የነካውን፣ የተሰማውን እና ያደመጠውን) እነርሱም ከወደዳቸውና በልጁ አማካይነት ራሱን ከሰጣቸው ሰማያዊ አባታቸው ጋር ደስታ የተሞላ ግንኙነት ውስጥ እንዲገቡ ይፈልጋል።

ዮሐንስ የራሱን ምስክርነት በተወሰነ መልኩ እየሰጠ ነው። እርስዎ ከየሱስ ጋር ያሎትን ግንኙነት አስመልክቶ የግል ምስክርነትዎ ምን ይመሰላል? ዮሐንስ ለማድረግ እንደ ፈለገው ሁሉ--አንድ ሰው በጌታ ያለው ደስታ እንዲጨምር የሚያግዝ ምን ዓይነት ቃል መሰንዘር ይችላሉ?





ሰኔ 14
Jun 21

ከጥፋተኝነት ስሜት ነጻ መሆን


“ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፡1) ምክንያቱም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ይመላለሳሉና። በአንድ ወቅት አንዲት ወጣት ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን ተገድላ የተገኘች ሲሆን ገዳይዋ አልታወቀም ነበር። ፖሊስ ገዳይዋን ለመያዝ ያስችለኛል ባለው ወጥመድ መቃብሯ ላይ በስውር የድምፅ መቅረጫ አስቀመጠ። ወጣቷ ከሞተች ብዙ ወራት በኋላ አንድ ምሽት ላይ አንድ ወጣት ወደ መቃብሯ መጣ። ከዚያም ተንበርክኮ እያለቀሰ ይቅርታ እንድታደርግለት ለመናት። የግለሰቡን ንግግር በማስረጃነት ያገኘው ፖሊስ ለሠራው ወንጀል ሕግ ፊት አቀረበው። ገዳዩን ወደ ሟች መቃብር አንደርድሮ የወሰደው ምን ነበር? ከጥፋተኝነት ስሜት ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጥ ማናችንም ብንሆን ወጣቱ እንዳደረገው ዓይነት የከፋ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ ሆነን አናውቅም (ብለን ተስፋ እናደርጋለን)። ሁላችንም ጥፋተኞች ነን፣ ሁላችንም የምናፍርባቸውን ነገሮች አድርገናል፣ ምነው ባላደረኩት ኖሮ ያልናቸውን ነገሮች አድርገናል።

ለየሱስ እና ለአዲሱ ቃል ኪዳን ደም ምስጋና ይግባውና ማናችንም በጥፋተኝነት መጥፎ ስም ውስጥ መኖር የለብንም። በዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሠረት ኩነኔ የለብንም። የመጨረሻው ዳኛ እንደ ጥፋተኞች አይቆጥረንም። ይልቁንም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉ ነገሮችን እንዳላደረግናቸው አድርጎ ያስባል።

በመቀጠል የቀረቡት ጥቅሶች ሮሜ 8፡1 በተሻለ እንድናስተውል እንዴት ይረዱናል? ዮሐ. 5:24፣ ሮሜ 3:24-25፣ 2ቆሮ. 5:21።





ከጌታ ጋር በቃል ኪዳናዊ ግንኙነት ከመኖር ታላላቅ ተስፋዎች አንዱ ከእንግዲህ በኃጢአት ሸክም ውስጥ መኖራችን ማክተሙ ነው። በቃል ኪዳኑ ደም ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ወደዚያ ቃል ኪዳናዊ ግንኙነት ለመግባት--ከእምነት፣ ከንስሐና ከመታዘዝ ሁኔታዎች ላይ ለመኖር ምርጫችንን ላደረግን ለእኛ--የጥፋተኝነት ሸከም ተነስቶልናል። ሰይጣን--ክፉዎች፣ መጥፎዎች፣ እጅግ ኃጢአተኞችና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሌለን መሆናችንን በጆሮአችን ሹክ ሊለን ሲሞክር፤ የሱስን በምድረ በዳ በፈተነው ጊዜ ጌታ ከቅዱሳን መጸሕፍት እንደ ጠቀሰ--እኛም ሮሜ 8፡1 መጥቀስ እንችላለን። ይህ በሕይወታችን ያለውን የኃጢአትን እውነታ መካድ አይደለም።

ይልቁንም ከጌታ ጋር ባለን የቃል ኪዳን ግንኙነት ምክንያት ከእንግዲህ በዚያ የኃጢአት ኩነኔ ስር አንኖርም እንደ ማለት ነው። የሱስ የእኛን ቅጣት ከፍሏል። ስለዚህ አሁን በእኛ ኃጢአት ፋንታ የራሱን ጽድቅ በማቅረብ ስለ እኛ ባፈሰሰው ደሙ በአብ ፊት እየማለደልን ይገኛል።

ለማንኛውም ለሠሩት ኃጢአት ከጌታ ይቅርታ ማግኘትዎ በሕይወትዎ ውስጥ ምን ዓይነት ልዩነት ያመጣል? ያ እውነታ ሰዎች በደል ሲያደርሱብዎ ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚኖርቦት በምን መልኩ ይረዳዎታል? ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖርዎ ግንኙነት ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል?



ሰኔ 15
Jun 22

አዲስ ቃል ኪዳን እና አዲስ ልብ


“ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣ የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኃይልን እንድታገኙ ነው። እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁ ዘንድ ነው” (ኤፌ. 3፡17-19)

ቀደም ባሉት ትምህርቶች እንደተመለከትነው፤ አዲሱ ቃል ኪዳን ጌታ ሕጉን በልባችን ውስጥ የሚያኖርበት መሆኑን ይህ ሩብ ዓመት አሳይቷል (ኤር. 31፡31-33)። ሕጉ በዚያ መገኘት ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ለዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የቀረቡት ጥቅሶች ክርስቶስ እና የእርሱ ሕግ በጣም የተሳሰሩ መሆናቸውን ያሳያሉ። በመሆኑም የክርስቶስን ሕግ በልባችን ውስጥ እንደያዝን እና በዚያው ውስጥ በቋሚነት በሚኖረው ክርስቶስ አማካይነት ታላቅ ወደ ሆነው ሌላው የኪዳኑ ጥቅሞች ይኸውም--አዲስ ልብ እንመጣለን።

አዲስ ልብ ለምን ያስፈልገናል? አዲስ ልብ ባላቸው ሰዎች ላይ ምን ለውጦች ይታያሉ?



ለዛሬ ጥናት የቀረቡትን ጥቅሶች በድጋሚ ያንብቡ። ጳውሎስ የፍቅርን መሠረታዊ ነገሮች አጥብቆ በመግለጽ ሥር የሰደድንና መሠረት ያለን ልንሆን እንደሚገባ መናገሩን ልብ ይበሉ። ቃላቶቹ በፍቅር መሠረት ላይ መጽናትን፣ ጥብቅ መሆንን እና መዝለቅን ያመለክታሉ። እምነታችን ለእግዚአብሔርና ለሌሎች በሚኖረን ፍቅር ላይ ካልተመሰረተ ምንም ማለት አይደለም (ማቴ. 22፡37-39፣ 1ቆሮ. 13)። ይህ ፍቅር በባዶ አይመጣም። በተቃራኒው በክርስቶስ የተገለጠውን እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በመመልከት ይመጣል። በውጤቱም ሕይወታችንና ልባችን ስለሚቀየር--አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ምኞት እና አዲስ ግብ ያላቸው ሰዎች እንሆናለን። ልቦቻችንን የሚቀይረውና ሌሎችን መውደድ የሚያስችል ፍቅር በውስጣችን የሚቀብረው ለእግዚአብሔር ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ ነው። ምናልባት ጳውሎስ ስለ መሞላት የተናገረው ይህንኑ ነው፡ “እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ”።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 4፡16። ይህ ጽሑፍ ጳውሎስ በኤፌ. 3፡ 17-19 ከጻፈው ጋር እንዴት ይዛመዳል?



ዛሬ ያጠናናቸውን ጥቅሶች ይመልከቱ። የእነዚህ መልእክት ተስፋዎች በእርስዎ ውስጥ መፈጸም ይችሉ ዘንድ ምን ማድረግ ይችላሉ? መለወጥ የሚኖርብዎ ነገሮች አሉ? ምናልባት “እግዚአብሔርን በሙላት” (ኤፌ. 3፡19) እንዳይለማመዱ መሰናክል የሆኑቦት ነገሮች ይኖሩ ይሆን? በሕይወትዎ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ እንዳለብዎ አስመልክቶ ዝርዝር ነጥቦች ያስቀምጡ። አንዱን ኮፒ ለራስዎ ያስቀሩና ከተመቾት ሌላውን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ። አስፈላጊውን ለውጥ ማምጣት ይቻል ዘንድ አንዱ ከሌላው ጋር እንዴት ሊረዳዳ ይችላል?



፡ ሰኔ 16 ሰኔ 16
Jun 23

አዲሱ ቃል ኪዳን እና ዘላለማዊ ሕይወት


“ ‘ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም’ ” (ዮሐ. 11፡25-26)። ዘላለማዊ ሕይወት ሁለት ገጽታዎች አሉት። የአሁኑ ገጽታ ለአማኙ በዚህ ምድር የተትረፈረፈ ሕይወት ልምድ የሚያመጣ ሲሆን (ዮሐ. 10፡10)፤ ይህም አሁን ለዚህ ሕይወታችን የተሰጠንን አያሌ ተስፋዎች ያካትታል። እርግጥ ነው የወደፊቱ ገጽታ--የአካል ዳግም ትንሣኤ የተስፋ ቃል፣ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ነው (ዮሐ. 5፡28-29)። ምንም እንኳ ገና ወደፊት የሚሆን ቢሆንም፤ ማንኛውንም ነገር የከበረ የሚያደርግ ክስተት ነው፤ እንደ ክርስቲያን የተስፋዎቻችን ሁሉ ጉልላት ነው።

ለዛሬ ትምህርት የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያጥኑ። የሱስ ምን እያለ ነው? በእርሱ የሚያምኑ በሕይወት ያሉ ቢሞቱም እንኳ በሕይወት እንደሚኖሩ መናገሩን እንዴት እናስተውለዋለን? (ይመልከቷቸው፡ ራእ. 2:11፣ ራእ. 20:6፣ 14፣ ራእ. 21:8)። ሁላችንም መሞታችን እርግጥ ቢሆንም ነገር ግን የሱስ እንደሚናገረው ይህ ሞት እንቅልፍ ብቻ ነው፣ ጊዜያዊ መቋረጥ ነው። በእርሱ የሚያምኑ መጨረሻ በሕይወት ትንሣኤ ይደመደማል። ክርስቶስ ዳግም ሲገለጥ በክርስቶስ ያንቀላፉ የማይሞቱ ሆነው ይነሣሉ፣ በሕይወት ያሉት የክርስቶስ ተከታዮች ደግሞ በቅጽበተ ዐይን የማይሞቱ ሆነው ይለወጣሉ። በክርስቶስ ያሉ የሞቱም ሆኑ በሕይወት ያሉ አንድ ዓይነት የትንሣኤ አካል ይኖራቸዋል። በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አለመሞት ጅማሮ ያገኛል።

መጨረሻችን መቃብር ውስጥ በስብሶ መቅረት ሳይሆን ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚዘልቅ የአዲስ ሕይወት ባለቤት መሆናችንን ማወቃችን ምንኛ ታላቅ ደስታ ነው! “ክርስቶስ እኛን በመንፈስ ከእርሱ ጋር አንድ ለማድረግ ሲል ከእኛ ጋር በሥጋ አንድ ሆነ። ከመቃብር የምንነሣው በዚህ ውሕደት ምክንያት ሲሆን ይህም የክርስቶስ ኃይል መግለጫ ብቻ ሳይሆን በኃይማኖት የእርሱ ሕይወት የእኛ ሰለሆነ ነው። የክርስቶስን እውነተኛ ባሕርይ በመረዳት በልባቸው የሚቀበሉት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። በእምነት የእግዚአብሔርን መንፈስ በልባችን ስንቀበል የዘላለም ሕይወትን መኖር ጀመርን ማለት ነው።” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 393።

ሰኔ 17
Jun 24

አዲሱ ቃል ኪዳን እና ታላቁ ተልዕኮ


“ ‘ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ” (ማቴ. 28፡19-20)

በዓለም ዙሪያ አያሌ ሕዝቦች የደቡብ አፍሪካው ደራሲ ቫን ደር ፖስት “የትርጉም የለሽ ስብእና ሸክም” ሲል ከጠራው ጽንሰ ሀሳብ ጋር በተደጋጋሚ ይታገላሉ። ሰዎች ራሳቸውን ከሕይወት ስጦታ ጋር ቢያገኙትም--በዚህ ሕይወት ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ የስጦታው ዓላማ ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚጠቀሙበትም አያውቁም። ጉዳዩ ብርቅዬ በሆኑ መጻሕፍት የተሞላ ቤተ መጻሕፍትን ለአንድ ሰው ሰጥቶ ግለሰቡ ሲያነባቸው ሳይሆን ለእሳት ማቀጣጠያ ሲጠቀምባቸው እንደማየት ነው። እጅግ በከበሩ ነገሮች ላይ እየደረሰ ያለ አስከፊ ብክነት!

ሆኖም ለአዲሱ ቃል ኪዳን ክርስቲያኖች ይህ ችግር ያን ያህል የሚያታግላቸው ዓይነት አይደለም። በተቃራኒው፣ በየትኛውም ስፍራ ያለ ሁሉም ሰው የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ኃጢአት የተሰቀለውን፣ የሞተውንና ከሞት የተነሣውን አዳኝ አስደናቂ የምሥራች የሚያወቁ (እና የግል ተሞክሮ ያላቸው) ደስታ ምን ማለት እንደሆነ ያስተውላሉ። በማቴ. 28:19-20 የቀረበውን የማያሻማ ጥሪ ከግምት ውስጥ ስናስገባ አማኙ በእርግጠኝነት በሕይወቱ ውስጥ ተልዕኮ እና ዓላማ እንዳለው የምንረዳ ሲሆን፤ ይኸውም በክርስቶስ የሱስ በግል የተመለከተውን አስደናቂ እውነት ለዓለም ማሰራጨት ነው። እንዴት ያለ ልዩ መብትና ጥቅም ነው! አብዛኛው በዚህ ዓለም የምናደርገው ማንኛውም ነገር ይህ ዓለም ሲያበቃ ያበቃል። ወንጌልን ለሌሎች ማሰራጨት ግን ዘላለማዊ አሻራ የመተው ሥራ ነው። የታላቁን ተልዕኮ እና ዓላማ ያጋሩ!

በዛሬው ጥናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የቀረቡ ጽንሰ ሀሳቦችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለመረዳት ይሞክሩ። የሱስ በተለይ እንድናደርግ እየነገረን ያሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? በእያንዳንዳቸው ውስጥ ምን ይካተታል? ክርስቶስ ያዘዘውን እንድንፈጽም እምነትና ድፍረት የሚሰጠን ምን ተስፋ አለን?



እንደ አዲስ ኪዳን ክርስቲያንነታችን በራሱ በጌታ ግልጽ አደራ ተጥሎብናል። ማን እንሁን ማን፣ የትኛውም ዓይነት የሕይወት መስመር ላይ ብንሆን፣ ምንም ዓይነት ጉደለት ሊኖረን ቢችል--ሁላችንም ሚና መጫወት እንችላለን። አንዳች ነገር እያደረጉ ነበር? ከዚህ ይበልጥ ማድረግ ይችላሉ? በዚህ ሥራ ውስጥ የላቀ ሚና ይኖራችሁ ዘንድ የእርስዎ ሰንበት ትምህርት ጥናት ቡድን በአንድ ላይ ምን ማድረግ ይችላል?





ሰኔ 18
Jun 25


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “God’s People Delivered,” pp. 635– 645, in The Great Controversy; “Rejoicing in the Lord,” pp. 115–126, in Steps to Christ. “የእግዚአብሔር ቅዱስ ልጅ የሚሸከመው የራሱ የሆነ ኃጢአት ወይም ሐዘን አልነበረውም። ነገር ግን እርሱ የሌሎችን ሐዘን ይሸከም ነበር፣ የሁላችን በደል በእርሱ ላይ ተጭኖአልና። በመለኮታዊ ርኅራኄ ራሱን ከሰው ጋር ያገናኛል፣ የሰብዓዊው ዘር ተወካይ የሆነው እርሱ እንደ ሕግ ተላላፊ ይቆጠር ዘንድ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። በኃጢአታችን ምክንያት የተከፈተውን የዋይታ ገደል በመመልከት ሰውን ከእግዚአብሔር የለየውን ይህን ገደል ድልድይ ሆኖ ለማገናኘት ወጠነ።”— Ellen G. White, Bible Echo and Signs of the Times, Aug. 1, 1892. “ወንድሜ ሆይ ና! ከእነ ኃጢአትህ እና እርክስናህ ና። የበደለኛነት ሸክምህን ሁሉ በየሱስ ላይ ጣል እና በእምነት የእርሱን የጽድቅ ሥራ የራስህ አድርግ።

የምህረት በር ሳይዘጋ ና፤ በኑዛዜ ና፤ ነፍስህን በማዋረድ ና፤ እግዚአብሔር አብዝቶ ይቅር ይልሃል። ይህን ዕድል ለሌላ ጊዜ ለማዘግየት አትድፈር። ከሙታን ተነሥተህ ክርስቶስ ያበራልህ ዘንድ አሁን እየተማጸነህ ያለውን የምህረት ድምፅ ስማ። እያንዳንዱ ጊዜ ራሱን ከማይታየው ዓለም አጉል መጨረሻ ጋር በቀጥታ እያገናኘ ይመስላል። ኩራትና አለማመንዎ ተዘርግቶሎት ያለውን ምኅረት እንዲቃወም አያድርጉ። የሚያደርጉ ከሆነ ግን በስተ መጨረሻ ለከፍተኛ ሐዘን ይተዋሉ። ‘መከሩ ዐለፈ፤ በጋው አበቃ፤ እኛም አልዳንም።’ ”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 5, p. 353.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ታዋቂው የፖለቲካ ሣይንቲስት ፍራንሲስኮ ጆሴ ሞሬኖ እንዲህ ብለው ነበር፡ “ራሳችንን ከሕዋ ጋር ካለን ዝምድና አኳያ ስንመለከት አለማወቃችንን እና የመጨረሻ አቅመቢስነታችንን እንረዳለን። በውጤቱ ፍርሐት ይሞላናል።”—Between Faith and Reason: Basic Fear and the Human Condition (New York: Harper & Row, Publishers, 1977), p. 7. ይህንን መግለጫ በዚህ ሣምንት በኤፌ.3፡17-19 ካጠኑት ጋር ያስተያዩ። በሁለቱ ስሜቶች መካከል ባሉ ልዩነቶች ዙሪያ ተወያዩ።

2.በየሱስ በማመናችን ደስታ እንደሚሰጠን እግዚአብሔር ቃል ገብቶልናል። ሁሌም ደስተኞች መሆን አለብን? ካልሆንን--በክርስቲያናዊ ተሞክሮአችን ላይ የሆነ ችግር አለ? የእነዚህን ጥያቄዎች መልሶች መረዳት እንችል ዘንድ የየሱስ ሕይወት ምን ሊገልጥልን ይችላል?

3.“እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ” (ኤፌ. 3፡19) በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ተወያዩ። ምን ማለት ነው? ይህን በሕይወታችን እንዴት መለማመድ እንችላለን?

ማጠቃለያ፡ ቃል ኪዳኑ ጥልቅ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ጽንሰ ሀሳብ ሳይሆን፤ ይልቁንም ከክርስቶስ ጋር ያለንን የመዳን ግንኙነት ባህሪ ይገልጻል። ግንኙነቱ አሁንም ሆነ ዳግም ሲገለጥ አስደናቂ ጥቅሞችን ለማጨድ ያስችለናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL