የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ኢሳይያስ፡ “ሕዝቤን አጽናኑ”


1ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከታህሳስ 17- 23

1ኛ ትምህርት

Dec 26 - Jan 01




የማንነት ቀውስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 1:1–9፣ ኢሳ. 1:10–17፣ ኢሳ. 1:18፣ ኢሳ. 1:19–31፣ ኢሳ. 5:1–7።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ ‘ኑና እንዋቀስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ኃጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።’ ” (ኢሳ. 1፡18)።

በ አየርላንድ፣ አንድ ሰው ከከተማ ወጣ ብሎ መኪናውን እያሽከረከረ በቀጭኑ ገጠራማ አስፋልት መንገድ ቢያልፍ፤ በግራም ሆነ በቀኝ ችምችም ብሎ በበቀለ ቁጥቋጦ እና ዛፍ መሃል--መንገዱን አቋርጠው ከተሰማሩበት ግጦሽ ወደ ቀዬአቸው የሚያመሩ የከብት መንጎች ሊገጥሙት ይችላሉ። የሚያግዳቸው እረኛ ባይኖርም እንኳ፣ ወዴት እንደሚሄዱም ሆነ የማን እንደሆኑ በሚገባ የሚያውቁት እነዚህ ከብቶች፣ ግራ ቀኝ ሳይሉ በቀጥታ አሳዳሪያቸው ወደ አበጀላቸው በረት ይገባሉ። ከእናቱ ጋር ወደ ገበያ የሄደ ታዳጊ ህፃን ድንገት ከእናቱ ቢለይ፤ እርሱ ያለበትን ወይም እናቱ ያለችበትን ስፍራ በትክክል ሊያውቅ ስለማይችል “እናቴ ጠፋችብኝ!” ብሎ እሪ ይላል። በገበያው ብዙ እናቶች ሊኖሩ ቢችሉም እንኳ፤ የትኛዋ ሴት የገዛ እናቱ እንደሆነች ለይቶ ያውቃታል።

የሚያሳዝነው ከአየርላንድ ከብቶች በተቃራኒ (ከጠፋው ታዳጊ ህፃን በጣም ባነሰ) አይሁዳውያን የጌታ መሆናቸውን ዘነጉ፤ እንደ ኪዳን ሕዝብ የነበራቸውን እውነተኛ ማንነት አጡ፡ “ልጆች ወለድሁ፣ አሰሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመፁብኝ። በሬ ጌታውን፣ አህያ የባለቤቱን ጋጥ ያውቃል፤ እስራኤል ግን አላወቀም፤ ሕዝቤም አላስተዋለም” (ኢሳ. 1፡2-3)። በዚህ ሣምንት እግዚአብሔር ሕዝቡን ዳግም ወደ ራሱ መልሶ ለማቋቋም የሠራውን ሥራ እንመለከታለን።

ታህሳስ 18
Dec 27

ሰማያት ሆይ ስሙ! (ኢሳ. 1፡1-9)


የኢሳይያስ መጽሐፍ ደራሲውን (“የአሞጽ ልጅ”)፣ የመልእክቱን ምንጭ (“ራእይ”) እና ርዕሱን (ይሁዳና ርእሰ ከተማዋ ኢየሩሳሌም በአራቱ ነገሥታት ዘመን) በመንገር በአጭሩ ራሱን ግልጽ አድርጎ ያስተዋውቀናል። የኢሳይያስ ተደራሲያን እርሱ በኖረበት ዘመን የነበሩ የገዛ አገሩ ሕዝቦች እንደ ነበሩ በተጨማሪ ርዕሱ ግልጽ ያደርግልናል። ሕዝቡ ይገኝበት ስለነበረው ሁናቴ እና ወደፊት ስለሚጠብቃቸው ነገር ነቢዩ ነግሮአቸዋል።

እርሱ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ በነበረበት በዚያን ዘመን በንግሥና ላይ የነበሩ ነገሥታትን የሚጠቅሰው ኢሳይያስ፤ የመልእክቱን አንባቢዎች አሃዝ እያጠበበ መጽሐፉን ከተወሰነ ዘመን ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ዐውድ ጋር ያስተሳስረዋል። ይህ የጊዜ ማዕቀፍ ወደ 2ነገሥ. 15-20 እና 2ዜና 26-32 እንድናቀና ያደርገናል። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡2። የመልእክቱ ፍሬ ነገር ምንድን ነው? ጌታ ምን እያለ ነው? ይኸው ጽንሰ ሀሳብ በመላው ቅዱስነት ያላቸው ታሪኮች የታየው እንዴት ነው? አባባሉ ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ላይ መዋል ይችላል? መልስዎን ለማብራራት ይሞክሩ።



የኢሳይያስ መልእክት “ሰማያት ሆይ ስሙ! ምድር፤ ሆይ አድምጪ!” ብሎ እንዴት እንደ ጀመረ ልብ ይበሉ። እስቲ ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩት፡--ዘዳ. 30፡ 19፣ 31፡28። ጌታ ሰማይና ምድር መስማትና ማስተዋል ይችላሉ እያለ አይደለም። ይልቁንም አባባሉን አጽንኦት ለመስጠት እንደ ተጠቀመበት እናያለን። ለምሳሌ እንደ ኬጢያውያን ዓይነቱ የጥንት የምሥራቅ ንጉሥ ከእርሱ ዝቅ ካለ መሪ ጋር የጦር ውል ሲዋዋል፤ ማንኛውም ውል የመጣስ አካሄድ ትኩረት ተሰጥቶት ቅጣት እንደሚያገኝ አጽንኦት ለመስጠት ሲል፤ አማልክቱ ምስክር ይሆኑ ዘንድ ልመና ያቀርብ ነበር። ሆኖም መለኮታዊው የነገሥታት ንጉሥ በሙሴ ዘመን ከእስራኤላውያን ጋር ኪዳን ሲገባ፤ ሌሎች አማልክትን በምስክርነት አልጠቀሰም።

ይልቁንም እንደ ብቸኛ እውነተኛ አምላክነቱ፤ በእርሱ በኩል ያለውን ለመፈጸም ሰማይና ምድርን በእማኝነት ጠርቶ እንደ ነበር ይታያል (በተጨማሪ፡ ዘዳ. 4፡26)። ጥቅሶቹን በጥንቃቄ ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡1-9። የይሁዳ ኃጢአት ምን እንደ ነበር በቀጣዮቹ መስመሮች ላይ አጠር አድርገው ለማቅረብ ይሞክሩ። እንዲሁም የእነዚያን ኃጢአቶች ውጤት አስመልክቶ የተወሰነ ማስታወሻ ይውሰዱ። ይሁዳን ጥፋተኛ ያደረጋት ኃጢአት ምን ነበር? ጥፋተኝነቷን ተከትሎ ምን ተከሰተ? በተመሳሳይ በቁ. 9 ምን ዓይነት ተስፋ ተሰጥቶአል?

ታህሳስ 19
Dec 28

የተበላሸ ሥርዓታዊ አምልኮ (ኢሳ. 1:10–17)


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡10። ኢሳይያስ ምናባዊውን ሰዶምና ጎሞራ ለምን የተጠቀመ ይመስሎታል? ጌታ ምን ዓይነት መልእክት እያስተላለፈ ነበር?



ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡11-15። በዚያ ስፍራ ጌታ ሕዝቡን ምን እያለ ነው? ሕዝቡ እያቀረበ የነበረውን አምልኮ ጌታ ለምን ተቃወመ?



ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ የነበሩ እና ለጸሎት ይዘረጉ የነበሩ--እነዚያው እጆች “በደም የተበከሉ” ነበሩ። ይህ ማለት በአመጻ እና ሌሎችን በመጨቆን ጥፋተኞች ነበሩ (ኢሳ. 1፡15፣ ኢሳ. 58፡4-4)። በሌሎቹ የኪዳኑ ማኅበረሰብ አባላት ላይ አጓጉል ድርጊቶች በመፈጸም የመላው እስራኤላውያን ተከላካይና ጠባቂ ላይ ንቀት እያሳዩ ነበር። በሌሎች ላይ ይደረጉ የነበሩ ኃጢአቶች፤ በጌታ ላይ እንደተፈጸሙ ይቆጠሩ እንደ ነበር ልብ ይሏል። በብሉይ ኪዳን የነበረውን ሥርዓተ አምልኮ ያቋቋመው (ዘሌዋ. 1-16) እና የየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ለስፍራው ተገቢ አድርጎ የሰየመው ጌታ ራሱ መሆኑ እሙን ነው (1ነገሥ. 8፡10-11)። ነገር ግን ሥርዓተ አምልኮዎቹ እግዚአብሔር ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ከገባው ዐውድ አኳያ እንዲሠሩ የታቀዱ ነበሩ። እግዚአብሔር በመካከላቸው በቤተ መቅደስ እንዲያድር ያስቻለው ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ኪዳን ነበር።

ስለዚህ በዚያ ይደረጉ የነበሩ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች እና ጸሎቶች ተቀባይነት የሚኖራቸው ለእርሱና ለኪዳኑ ታማኝ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ብቻ ነበር። በሌላው የኪዳኑ ማኅበረሰብ አካላት ላይ ለፈጸሙት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ንስሐ ሳይገቡ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች ሐሰተኛ ኃይማኖታዊ ሥርዓት እንደፈጸሙ ይቆጠር ነበር። ስለዚህ መሥዋዕቶቻቸው ተቀባይነት ያልነበራቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ኃጢአት ነበሩ! ኃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ታማኝነታቸውን ቢናገሩም፤ ባህሪያቸው ግን ኪዳኑን ማፍረሳቸውን ያረጋገጠ ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡16-17። ጌታ ሕዝቡን ምን አድርጉ ሲል ያዛል? በዚህ መልእክት ዐውድ የቀረቡት እነዚህ ጥቅሶች የሱስ በማቴ. 23፡23-28 ከተናገረው ጋር እንዴት ይመሳሰላሉ? ከእነዚህ ጥቅሶች እና ጥቅሶቹ ከተሰጡበት ዐውድ ምን ዓይነት መልእክት ዛሬ ለራሳችን ማግኘት እንችላለን?





ታህሳስ 20
Dec 29

ሞጋቹ የይቅርታ ጥሪ (ኢሳ. 1:18)


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡18። ጥቅሱን ደጋግመው ካነበቡ በኋላ ጌታ ምን እያለ እንደሆነ ያመኑበትን በአጭሩ ለማስፈር ይሞክሩ (የመልእክቱን አጠቃላይ ዐውድ ለማግኘት ጥቂት ቁጥሮች ጨምረው ያንብቡ)።



የይሁዳ ሕዝቦች የገቡትን ውል መጣሳቸውን የሚያሳይ በብርቱ ማስረጃ የተደገፈ ክስ በእግዚአብሔር ቀርቦባቸው ነበር (ኢሳ. 1፡2-15)። ይህን ተከትሎ ተሐድሶ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደረገላቸው (ኢሳ. 1:16, 17)። በእርግጥ ጥሪው በራሱ ተስፋ መኖሩን አመላካች ነበር። ለነገሩ ሞት የሚገባው ወንጀለኛ ከመንገዱ እንዲመለስ ለምን ጥሪ ይቀርብለታል? የሞት ፍርደኛው ወንጀለኛ--የተገፉትን የሚያጽናናው፣ አባት ለሌላቸው የሚቆመውና ለመበለቶች የሚሟገተው እንዴት ነው? ነገር ግን “ኑና እንዋቀስ” (ኢሳ. 1፡18) ብሎ እግዚአብሔር ጥሪ ሲያቀርብ፤ የቱንም ዓይነት የከፋ ሁኔታ ላይ ቢገኙ እንኳ ጌታ አሁንም ከሕዝቡ ጋር ለመነጋገርና ንስሐ ገብተው ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ የሚሻ መሆኑን መመልከት እንችላለን።

ጌታ ኃጢአታችሁ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል ብሎ ሲነግራቸው እንመለከታለን። ለመሆኑ ኃጢአት ለምን በቀይ ቀለም ተመሰለ? ለዚህ ምክንያቱ ቀይ የ “ደም” ቀለም በመሆኑና የእነዚህ ሕዝቦች እጆች በደም በመበከላቸው ነው (ኢሳ. 1፡15)። በተቃራኒው ነጭ ከደም የጥፋተኝነት ምልክት ነጻ የሆነ የንጽህና ምልክት ነው። እዚህ ላይ ይለወጡ ዘንድ እግዚአብሔር ጥሪ ሲያቀርብላቸው ይታያል። ንጉሥ ዳዊት ቤርሳቤህን ወስዶ ባሏ እንዲወገድ በማድረግ ለሠራው ኃጢአት እግዚአብሔር ይቅር እንዲለው ወደ እርሱ ሲያለቅስ የተጠቀመው ቋንቋ በተመሳሳይ በዚህ ስፍራ ጥቅም ላይ ውሏል (መዝ. 51፡7፣ 14)። በኢሳ. 1፡18 የተመለከተው የእግዚአብሔር ሞጋች ሀሳብ ሕዝቡን ይቅር ለማለት ያቀረበው ጥሪ ነው።

እግዚአብሔር ለእነዚህ ሕዝቦች ያቀረበው የይቅርታ ጥሪ ከመንገዳቸው እንዲመለሱ ሊሞግታቸው የሚችለው እንዴት ነው? ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ - ኢሳ. 1፡18 እና ኢሳ. 44፡22 እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ ስለት ያላቸውን ቃላት ጥቅም ላይ ያዋለበትን ዓላማ ከዚህ መረዳት እንችላለን። ቃላቶቹ ጥቅም ላይ የዋሉት ሕዝቡን እስከ ወዲያኛው ላለመቀበልና ለመተው ሳይሆን፤ መልሶ ወደ እርሱ ለማምጣት ነበር።

ሕዝቡ ራሱን ከእኩይ ተግባር እንዲያነጻ የቀረበው የይቅርታ ስጦታ፤ ለአምላካዊው ተማጽኖ ብርቱ ድጋፍ የሚሆን ሞጋች ሀሳብ ነው (ኢሳ. 1፡16-17)። ይቅርታው-በቀረበላቸው አምላካዊ ኃይል መለወጥ እንዲችሉ መንስኤ ሆኗቸዋል። ይቅር መባል ከእግዚአብሔር ጋር በአዲስ ልብ ግንኙነት የመፍጠር መስረት መሆኑን የሚያሳዩ የ “አዲስ ኪዳን” ዘሮች በኤር. 31፡ 31-34 በትንቢት ቀርበው እንደ ነበር እንመለከታለን። እንደ ደም የቀላው ጅማሮአችን ልንከፍል በማንችለው ዕዳ መዘፈቃችንን ያሳያል። ይቅርታ እንደሚያስፈልገን ሊያመላክት የሚችል ትሁት አቋም፤ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ያለንን ዝግጁነት ይገልጣል።

ታህሳስ 21
Dec 30

መብላት ወይም መበላት (ኢሳ. 1፡19-31)


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1፡19-31። የመላው መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች አካል የሆነ ምን ዓይነት ርዕሰ ጉዳይ በዚህ ስፍራ ቀርቦአል?



በኢሳ. 1፡19-20 የቀረበውን መልእክት አመክኖአዊ አወቃቀር ይመልከቱ፡ እነዚህ ሕዝቦች እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ከሆኑ ከምድሪቱ መልካም ፍሬ ይበላሉ (ኢሳ. 1፡19)። በተቃራኒው ወደ ቀደመው ንጽሕና በሚመልሳቸው በይቅርታ ስጦታውና በእርሱ ላይ የሚያምጹ ከሆነ ግን ሰይፍ ይበላቸዋል (ኢሳ. 1፡20)። እንግዲህ ምርጫው የነርሱ ነው። ስለዚህ ጥቅሶቹ በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ በረከቶች እና መርገሞች ይዘዋል።

“ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራለሁ” (ዘዳ. 30፡19-20) በሚል ከእስራኤላውያን ጋር የተገባው ኪዳን ሲቋቋም የቀረቡትን እነዚህን ቃላት--ኢሳይያስ በምዕ. 1 በድጋሚ ሲያቀርብና ሲተገብር ይታያል። እነዚህን በሙሴ የተነገሩ ቃላት ልብ ብለው ይመልከቱ። መሃል ሰፋሪ የሚባል ላለመኖሩም አጽንኦት ይስጡ። የቀረበው--ሕይወት ወይም ሞት፣ በረከት ወይም መርገም ነው። ከሁለቱ አንዱን ብቻ መምረጥ የሚኖርብን ለምን ይመስሎታል? አንድ የሆነ መደራደሪያ ለምን አልኖረም?



በዘዳ. 27-30 በጭሩ የቀረቡ እነዚህ ተከታታይነት ያላቸው የሙሴ-ማስጠንቀቂያዎች፣ በረከቶች እና እርግማኖች የኪዳኑን መቋቋም ይገልጻሉ (ያስተያዩ-ዘሌዋ. 26)። የኪዳኑ ባህሪያት የሚከተሉትን ነጥቦች ያካትታሉ፡ (1) እግዚአብሔር ለእነርሱ ያደረጋቸውን ነገሮች ደግመው ደጋግመው የመንገር ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ (2) ኪዳኑ በሁኔታዎችና ግዴታዎች ላይ መመስረቱ (3) የምስክሮች መጠቀስ እና (4) በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተው ኪዳን የሚያስከትለው በረከት እና እርግማን በማስጠንቀቂያነት ለሕዝቡ መሰጠቱ ነበሩ።

እነዚህ የኪዳኑ ባህሪያት እንደ ኬጥያውያን ዓይነት ከእስራኤላውያን ነገድ ውጪ የነበሩ ሕዝቦች በዘመኑ ይፈጽሟቸው የነበሩ ፖለቲካ ነክ ውሎች ጋር ተመሳሳይ አወቃቀር እንደ ነበራቸው ምሑራን ይናገራሉ። ስለዚህ አምላካዊውን ኪዳን ከእስራኤላውያን ጋር ለመመስረት--ሕዝቡ በቅርብ ሊያስተውለው እና ውስጡን ሊኮረኩር የሚችለውን ይህን ውል ጥቅም ላይ አዋለ። ሕዝቡ ለመግባት እየመረጠ የነበረው ይህ የራሱ አስገዳጅ ባህሪያት የነበሩት ውል፤ ሁለቱንም ወገን በጋራ የሚያስር ተፈጥሮ ነበረው። ኪዳኑ ሊያስገኝ የሚችላቸው ፖለቲካዊ ትሩፋቶች አስደናቂ ቢሆኑም፤ እስራኤላውያን የገቡትን ኪዳን የሚያፈርሱ ከሆነ ግን ከመቼውም የከፋ ነገር ይደርስባቸዋል። ከላይ እንደ ተመለከተው የበረከትና እርግማን መርኅዎችን በገዛ የክርስትና ጉዞዎ የተለማመዱበት መንገድ ምን ይመስላል?

ታህሳስ 22
Dec 31

አስፈሪ የፍቅር ዜማ (ኢሳ. 5፡1-7)


ከላይ በተጠቀሱት ቁጥሮች የቀረበውን ቅኔያዊ ስንኞች ያንብቡ። የዚህ ምሣሌያዊ አነጋገር ፍቺ ምንድን ነው?



እግዚአብሔር የቅኔውን ፍቺ በመጨረሻ ላይ ማለትም በቁ. 7 ያብራራል። ምሳሌያዊ አነጋገሩን ተጠቅሞ ሕዝቡ በተጨባጭ ወደ ራሱ በመመልከት የሚገኝበትን እውነተኛ ሁኔታ አምኖ እንዲቀበል ለመርዳት ሲሞክር ይታያል። እግዚአብሔር ከንጉሥ ዳዊት ጋር በነበረው አግባብ ይህን ዘዴ በሚገባ ተጠቅሞበታል (2ሳሙ. 12፡1-13)። እግዚአብሔር በዚህ--ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ቅኔ ገና ከመጀመሪያው ለሕዝቡ ያለውን ተነሳሽነት ይገልጻል። ከእነርሱ ጋር ያለው ግንኙነት ምንጭ ፍቅር የሆነው ባህሪው ነው (1ዮሐ. 4፡8)። ስለዚህ አጸፋዊ የፍቅር ምላሽ ጠበቀ። ሆኖም በ “መልካም የወይን ፍሬ” ፋንታ “ኮምጣጣ” ፍሬ አፍርቶ ያገኘበት ይህ ሁኔታ፤ በዕብራይስጥ “የሚከረፉ ነገሮች” የሚል ትርጉም አለው።

ጌታ--በኢሳ. 5፡4 “ከዚህ ካደረግኩት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር?” ሲል ምን ማለቱ ነው? እግዚአብሔር በቀጣዮቹ ቁጥሮች እንዲህ ይላል፡ “እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፤ መረጋገጫም ይሆናል። የማይኮተኮትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኩርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት አዝዛለሁ።” (ኢሳ. 5፡5-6)።

ኃጢአት ስንሠራ እግዚአብሔር እርግፍ አድርጎ ትቶን በዙሪያችን ያለውን ጥበቃ ወዲያው አስወግዶ አያጠፋንም። ይልቁንም በትዕግሥት ይቅርታውን የምንቀበልበትን ዕድል ይሰጠናል (2ጴጥ. 3፡9)። እርሱ ምላሽ የማይሰጠውን ማንኛውም ሰው ከፊቱ አያስወግድም። የምላሽ ተስፋ እስኪያገኝ ጥሪ ማድረጉን ይቀጥላል። አላዋቂዎች እና በኃጢአት የምንታለል መሆናችንን የሚያውቀው ይህ አምላክ፤ አሉታዊ ምላሻችንን የመጨረሻ ቃል አድርጎ አይወስድም። ነገር ግን በየትኛውም ሁኔታ አብሮነቱን የማንሻ ከሆነ፤ ውሎ አድሮ ምርጫችንን በመገንዘብ በመረጥነው መንገድ እንድንሆን ይፈቅዳል (ራእ. 22፡11)።

እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት የሚያቀርብልንን ልመናዎችና ጥሪዎች በመቃወም የምንጸና ከሆነ፤ በስተመጨረሻ መመለስ የምንችልበትን ነጥብ አልፈን ልንሄድ እንችላለን (ማቴ. 12፡31-32)። አንዴ ክርስቶስን ከቀመሱ በኋላ በእርሱ ላይ ክህደት መፈጸም ውጤቱ አደገኛ ነው (ዕብ. 6፡4-6)። እግዚአብሔር ነጻ የሆነውን የመምረጥ መብታችንን ከማክበር ውጪ ሌላ ምንም ማድረግ አይችልም።

“ከዚህ ካደረግኩት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር?” በሚል የቀረበውን ጽንሰ ሀሳብ ወስደው--እኛ በሕጉ ላይ ለፈጸምነው ጥሰት እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ሲል ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበትን እና በሥጋው የከፈለውን ዋጋ በመስቀሉ ብርሃን ይመልከቱ። እርሱ በዚያ ስፍራ ከከፈለው በላይ ምን የላቀ ነገር ሊደረግልን ይችል ነበር? የመስቀሉን ታሪክ በጥልቀት መመልከታችን የደኅንነት ማረጋገጫ በመስጠት--ንስሐ ገብተን ከተሳሳተው መንገድ እንድንመለስ እንዴት ሊያነሳሳን ይችላል?

ታህሳስ 23
Jan 01


ተጨማሪ ጥናት


ኤለን ኋይት በኢሳ. 1፡4 ዐውድ የሚከተለውን ጽፋለች፡ “ከእግዚአብሔር ጋር ኪዳን ገብተው የነበሩ ሕዝቦች ከእርሱ በመለየታቸው የነበራቸውን ጥበብ አጡ፤ ማስተዋላቸውም ተዛባ። አርቀው መመልከት ተሳናቸው፤ የቀደሙ ኃጢአቶቻቸው ይቅር መባላቸውንም ዘነጉ። የነጻነታቸውን ትዝታ እና የቀድሞ ግዛታቸውን ደስታ ከአእምሮአቸው ለመደምሰስ አጥብቀው ሻቱ፣ ያለ ዕረፍት ተቅበዘበዙ፣ ጽልመት ባጠላበት ያልተረጋገጠ ሁኔታ ውስጥ ወደቁ።

ይህ ቀረሽ የማይባል ግብዝነት ውስጥ ጠለሙ፣ አጉል ዓይነት እብደት ተጠናወታቸው፣ ራሳቸውን ከአምላካዊው ፈቃድ በተቃራኒ አኖሩ፣ በበደለኝነታቸውም አጥብቀው ገፉበት። ሰይጣን በመለኮታዊው ባህሪ ላይ ለሚያቀርበው ክስ ጆሮዎቻቸውን ሰጡ፣ እግዚአብሔርንም ይቅርታና ምህረት የማያውቅ አምላክ አድርገው ሳሉ።”—The SDA Bible Commentary, vol. 4, p. 1137.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ራስዎን አጥበው ንጹህ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ፊልጵ. 2፡12-13)

2.የሱስ ቅኔያዊውን የወይን ተክል ስንኝ ወስዶና አስፋፍቶ ጥቅም ላይ ያዋለው እንዴት ነበር? ማቴ. 21፡33-45፣ ማር. 12፡1-12፣ ሉቃ. 20፡9-19። እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን፤ ከላይ በቀረበው ታሪክ ምን ዓይነት ትምህርቶች እናገኛለን?

3.እግዚአብሔር በሚሰጠው ይቅርታ እና በሕይወታችን ውስጥ በሚያከናውነው እኛን የመለወጥ ሥራ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የትኛው ይቀድማል፡ በመጀመሪያ መለወጥ፣ ቀጥሎ ይቅር መባል--ወይስ በመጀመሪያ ይቅር መባል፣ ቀጥሎ መለወጥ? የቱ ቀድሞ እንደሚመጣ ማወቃችን ጥቅሙ ምንድን ነው?

4.ከላይ በምህጻረ ቃል በቀረበው ጽሑፍ፡ ሰዎች “ራሳቸውን ከአምላካዊው ፈቃድ በተቃራኒ አኖሩ” በማለት ኤለን ኋይት ትናገራለች። ምን ማለት ነው?

ማጠቃለያ፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እርሱን ዘንግተው በረከቶቹን ያለምንም ጥያቄ ወይም ተቃውሞ መቀበላቸው፤ ከእርሱ ጋር ለገቡት ኪዳን ተጠያቂነት እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል። በምህረት የተሞላው አምላክ የሚገኙበትን ሁናቴ እንዲገነዘቡ በመርዳት፤ ከእርሱ ጥበቃና ከለላ መውጣት ሊያስከትል የሚችለውን አውዳሚ መዘዝ ያስጠነቅቃቸዋል። ይፈውሳቸው እና ያነጻቸው ዘንድ እንዲፈቅዱለት አጥብቆ ያስገነዝባቸዋል።