የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከኅዳር 12 – 18

9ኛ ትምህርት

Nov 21 - Nov 27




ቤተ ክርስቲያን እና ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ. 10:30– 37፣ ማቴ. 5:14–16፣ ሉቃ. 4:18–23፣ ኤር. 29:13፣ ማቴ. 7:7, 1 ተሰ. 2:6–8.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም፡፡ የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንባችሁ ነበር፤ ነገር ግን እናት ልጅዋን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን፡፡ የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ (1ተሰ. 2፡6-8)፡፡

ታ ማኞች በቤተ አምልኮ፣ በመኖሪያ ቤት እንዲሁም በየአብያተ ክርስቲያናቱ እግዚአብሔርን ለማምለክ በአንድነት ይሰበሰቡ ከነበረበት ከቀደመችው ቤተ ክርስቲያን መቆርቆር ዘመን አንስቶ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናቶቻቸው እና በአምልኮአቸው እግዚአብሔርን ለማወቅና ፈቃዱን በሕይወታቸው ለመረዳት ይናፍቁ የነበሩ ሕዝቦችን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ያሳየናል። ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ዕውቀት ይበለጽግና እርሱ ለሕይወታቸው ያለውን ፈቃድ ማየት ይችሉ ዘንድ--ቤተ ክርስቲያን ጥልቀትና አግባብነት ያላቸው ውይይቶች ሊካሄድባት የሚገባ ስፍራ መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይገልጽልናል።

አንዳንድ ጊዜ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንፈራለን። ሆኖም ጥያቄዎች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስለሚያመልኩት አምላክ ግልጽ ግንዛቤ ለማዳበር እንደሚረዳቸው በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ቀርቦ እናገኛለን። በተመሳሳይ--ሰዎች ቃል ኪዳኖቻቸውን ዳግመኛ ለማጤን ዕድል የሚፈጥሩላቸው ታሪኮች በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ጥቅም ላይ ውለዋል። በተለይ ደግሞ የሱስ ከደቀ መዛሙርቱ እና ከተከታዮቹ ጋር በእንዲህ ያለው ትምህርት ላይ ትኩረት ያደርግ ነበር።

ቤተ ክርስቲያን ለመማሪያ ስፍራነት የምትውል ከሆነ እውነተኛ ውይይት መካሄድ የሚችልበትን ምህዳር መፍጠር ይኖርባታል። “የጥያቄ መጥፎ የለውም” ተብሎ በተደጋጋሚ በትምህርት ቤት እንደተነገረን--እያንዳንዱ ሰው በጸጋ፣ እግዚአብሔርን በማስተዋል እና እርሱ ለሕይወቱ ባለው ዕቅድ ያድግ ዘንድ፤ ቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ ከባቢ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባታል።

ኅዳር 13
Nov 22

እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት


በክፍል ውስጥ እንቅልፍ የተጫጫናቸውን የተማሪዎቹን ዐይኖች የተመለከተው ረቢ፡ “አንድ ሰው ሌሊቱ አብቅቶ ቀኑ መጀመሩን ማወቅ የሚችለው መቼ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

ብዙዎቹ ተማሪዎች በእርጋታ እጆቻቸውን አወጡ። ከመሃላቸው አንዱ “ረቢ፡ በበለስ ዛፍ እና በወይራ ዛፍ መካል ያለውን ልዩነት መመልከት ሲቻል” ሲል መለሰ። “ትክክል አይደለም” ሌላ ተማሪ እጁን አወጣ፡ “ረቢ፡ በበግ እና በፍየል መካከል ያለውን ልዩነት መመልከት ሲቻል።”

“ትክክል አይደለም” መምህሩ ሌሎች ተጨማሪ መልሶችን ከሰማ በኋላ በመጨረሻ እንዲህ አላቸው፡ “ተማሪዎች፡ አንድ ሰው ሌሊቱ አልፎ ቀኑ መጀመሩን ማወቅ የሚችለው ከዚህ ቀደም አይቶት የማያውቀውን የባልንጀራውን ገጽታ እንደ ወንድሙ ወይም እህቱ ለይቶ ማወቅ ሲችል ነው። ይህ ዓይነቱ ሁናቴ ገቢራዊ እስኪሆን ድረስ ቀኑ የቱንም ያህል በብርሃን ጸዳል የተሞላ ቢሆን፤ ጨለማ ነው።”

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 10፡30-37። የሱስ በዚህ ታሪክ ሊያስተምር የፈለገው ነገር ምን ነበር? ማንኛውም እውነተኛ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ሊያካትት ስለሚገባው ነገር ከዚህ ምን እንማራለን?



እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ፤ በአያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃኖች እና እውነቶች ጌታ አተረፍርፎ ባርኮናል (ከብዙዎቹ በጥቂቱ፡ የሞቱ ሰዎች ሁኔታ፣ ሰንበት፣ 1844 እና ፍርድ፣ ታላቁ ተጋድሎ…) አብዛኛው የክርስትና ዓለም ስለ እነዚህ እውነቶች ዛሬም ግንዛቤ የለውም። ሆኖም እነዚህ እውነቶች የቱንም ያህል ወሳኝ ቢሆኑም--ለሌሎች መልካም ካልሆን፣ በጭፍን ጥላቻ ከተመለከትናቸው፣ የምንገኝበት ባህላዊና ማኅበራዊ መሰረት ሌሎችን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት መንስኤ እንዲሆን ከፈቀድን--ታዲያ ምን ይረቡናል?

እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት ሌላው ቢቀር--ክርስቶስ ለሞተላቸው፣ ኃጢአታቸውን በመስቀል ላይ ለቸነከረው፣ ህልቁ መሳፍርት የሌለውን ዋጋ የከፈለላቸውን ወገኖች በሚመለከትበት ዐይን--ማለትም ከሰብዓዊ ድካም እና ክፋት በሚልቅ ልእልና እንድናያቸው ሊያደርገን ይገባል። መስቀሉን ከፍ ከፍ የምናደርግ ከሆነ የእያንዳንዱን ሰብዓዊ ፍጡር ከፍ ያለ እና የከበረ ዋጋ እናያለን፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ የሰጠውን ዋጋ ጠብቀን በእውነት እንደሚገባቸው እንመለከታቸዋለን። ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት ይህን አስተምህሮ ማካተቱ የግድ ይሆናል። ያለበለዚያ ግን “ክርስቲያን” የሚለውን ስም ለመሸከም የተገባ አይሆንም። እንደ ክርስቲያን የ ላዕላይ (የላቀ) ትብስህት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ባህልዎ ወይም ማኅበረሰቡ በገሃድም ሆነ በስውር የሚያራምደው ምን ዓይነት ጭፍን የጥላቻ አስተምህሮ አለው?

ኅዳር 14
Nov 23

ብርሃን ሆነን እንድንኖር መጠራታችን


በማንኛውም በምንመለከተው ነገር ምድራችን በራሷ እየተዟዟረች ብርሃኑን በጨለማ እየለወጠች ያለች ትመስላለች። እኛም ብንሆን በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ዓለም ተሞክሮአችን አብልጦ ለቤታችን ከቀረበው ጨለማ ጋር እንፋለማለን። ከበሽታ ጋር በምናደርገው ግብግብ፣ የምንወደውን የቤተሰብ አባል ስንነጠቅ በሚገጥመን ሐዘንና ልብ መሰበር፣ ቤተሰብ በመለያየትና በፍቺ ሲፈርስ፣ በማኅበረሰባችንና በባህላችን እየተስተዋሉ ላሉ መጠነ ሰፊ ክፋቶች ትርጉም ለመስጠት ስንዋትት--በእርግጥም ይህ ሕይወት የሚያስከትለውን ሥቃይ እናስተውላለን።

ሆኖም በዚህ የግብረገብ ኪሳራና መንፈሳዊ ጽልመት ገጽታ፣ በዚህ ውጪያዊና ውስጣዊ ሁካታ መሃል፤ ወደ እያንዳንዳችን የሚፈሱትን የየሱስ ቃላት እንሰማለን። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። እንዲሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” (ማቴ. 5፡14-16)።

እንዴት መኖር እንዳለብንና እንደ ክርስቲያን በሌሎች ላይ በምናደርገው ተጽእኖ ወገኖች እግዚአብሔርን መመልከት እንዲችሉ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?



በዚያን ቀን፣ በሞቃታማው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ተቀምጠው የነበሩት የየሱስ አድማጮች እነዚህን ቃላት እንዴት ነበር ያስተዋሏቸው? የእርሱን ቃላት የሰሙ ሁሉ ስለ ብርሃን እና ጨለማ አንድም ሳይቀር ተገንዝበው ነበር። በእርግጠኝነት አያሌ በጨለማ የተዋጡ የሚፈሯቸው ነገሮች ነበሯቸው። የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ ሮማውያን ቅኝ ግዛት ስር ይተዳደሩ የነበሩ እነዚህ ሕዝቦች ስልክ፣ ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት ባይኖራቸውም በብዙ መንገድ ብቃት ነበራቸው-አልፎ አልፎ የዘግናኝ ድርጊት ሰለባ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ። በኮረብታ ላይ ከተሰበሰበው ሕዝብ መሃል ችግር ፈጣሪ ካለ በፍጥነት የሚቀጡ፤ አለፍ ሲልም በሮማውያን መስቀል እርቃን የሚሰቅሉ ሮማውያን በየቦታው ነበሩ። ታዲያ በዚህ ስፍራ ሕዝቡ ብርሃን ሆኖ ይመላለስ ዘንድ የሱስ ጥሪ እያቀረበ ነበር። ምሕረት እንዲያደርጉ፣ ልባቸው ንጹህ እንዲሆን እና ሰላም የሚያወርዱ እንዲሆኑ። በመሆኑም ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎቻችን ለዓለም ብርሃን የሚሆኑበትን፣ እግዚአብሔር ለሌሎች ያለውን መልካምነት ገልጦ የማሳየቱን ተጨባጭ እውነታ ምርጫቸውና ውሳኔአቸው የሚያደርጉበትን--ሥርዓተ ትምህርቱ ማካተቱ የግድ ይሆናል።

ስለ እግዚአብሔር ተጨባጭ ማንነትና መልካምነት ለሌሎች ልንጠቅስ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ኅዳር 15
Nov 24

እንደ ደቀ መዝሙር መመላለስ


ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት ጉልበት ለመሆን ቁርጠኝነቱ ካላት፤ በየሱስ ትእዛዝ መጀመራችን በጣም አስፈላጊ ይሆናል። የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጥሪ አቀረበላቸው። አብሮአቸው እየተራመደ የወንጌል ተልዕኮ የሚያካሂዱበትን ሥልጠና ሰጣቸው። እንክብካቤ የሚያደርጉላቸውና ፍቅራቸውን የሚገልጹላቸው ሕዝቦች ሕይወት አካል የሚሆኑበትን ዕድል ሰጣቸው። አንዱ ሌላውን እንደ ወንድሙና እህቱ ሲመለከት ይህ ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል እያወሳ ዘወትር ይገዳደራቸው ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 4፡18-23። እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችን ለእኛ ለሁላችን ያለው መልእክት ምንድን ነው?



ደቀ መዛሙርቱ ለሦስት ዓመታት የሱስን እንደ መምህራቸው ተመለከቱት፣ በናዝሬት ምኩራብ የመጀመሪያ ስብከቱ ይፋ ካደረገው መርኅ ጋር የሚዛመድና ለመንግሥቱ ተስማሚ የሚባል ዓይነት ሕይወት ኖሩ። ይቅርታ ማድረግ፣ ጸጋ እና ፍቅር ከብቸኝነቱ፣ ቁርጠኝነቱና መከራው ጋር እጅና ጓንት ሆነው ዘለቁ። የደቀ መዝሙርነት ኃላፊነት እንደው እንደ ዋዛ የሚታይ አለመሆኑ ከዚህ ሊወሰድ የሚገባ ትምህርት ነው። የእርስዎ ደቀ መዝሙርነት የአንድ ቀን ሳይሆን የሕይወት ዘመን ነው።

“የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ተልዕኮ መላ ምዕመናኑን ይመለከታል። ነፍሳትን የማዳን ሥራ ለቄሶች ብቻ የተሰጠ ተግባር ነው ብሎ ማሰብ ወደ ጥፋት የሚያደርስ ስሕተት ነው። በሰማያዊ መንፈስ ስሜታቸው የተነካ ሁሉ የወንጌል አደራ ተሰጥቶአቸዋል። የክርስቶስን ሕይወት የተቀበሉ ሁሉ ሌሎችን በማዳን ሥራ ተነክተዋል። ቤተ ክርስቲያንዋ የተቋቋመችው ለዚሁ ጉዳይ ስለሆነ የተቀደሰውን ቃል ኪዳን የተቀበሉ ሁሉ የክርስቶስ የሥራ አጋር ለመሆን ቃል ገብተዋል” (የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 870።)

እንደ የሱስ ደቀ መዝሙርነታችን እርሱ ሁሌም የክርስቲያናዊ ኅብረታችንና አምልኮአችን ማዕከል መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ደቀ መዝሙርነትን የፈጠረው የሱስ መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ነው። ምንም እንኳ መምህርነቱ ተከታዮችን ይስብ የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን ወንዶች እና ሴቶች ይከተሉት ዘንድ ጥሪ ያቀርብ የነበረው ራሱ የሱስ ነበር። በወቅቱ የነበሩ መምህራን ግን የየሱስን ስር ነቀል ጥሪ ተቀብሎ ከእርሱ ጋር መሆንን--ከትእዛዞቻቸው ይልቅ አስፈላጊ አድርገው ሊገምቱ አልቻሉም ነበር።

እኛ እንደ የሱስ ደቀ መዝሙርነታችን ለሁሉም ሰው አክብሮት ያለን ብቻ ሳንሆን፤ ሁሉም ሰው ማደግና መበልጸግ የሚችልበትን ሁናቴ በማመቻቸትም እንሠራለን። ስለሆነም ሁሉም ክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት ይህን ዓላማ ተኮር ተልዕኮ ማካተት የሚኖርበት ለመተዳደሪያ ሳይሆን የሱስ እንድንሠራ ጥሪ ያደረገልንን እንደ አቅማችን እንድናበረክት ይኸውም--የእርሱን ዱካ ተከትለን በእጦት ያሉትን እንድናገለግል፣ የወንጌልንም መልካም የምስራች እናካፍል ዘንድ ነው።

ኅዳር 16
Nov 25

እውነትን አጥብቆ መፈለግ


የዘመናዊው ፊዚክስ አባት ተደርጎ የሚታየው አልበርት አንስታይን የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡ “ዋናውና አስፈላጊው ነገር መጠየቅ ማቆም አይደለም። የማወቅ ጉጉት ሊኖር የቻለበት የራሱ ምክንያት አለው። ስለ ዘላለማዊነት፣ ስለ ስነ ሕይወትና እውነት ተጨባጭ አወቃቀር ምስጢር ሲያሰላስል አብልጦ ከመደነቅ መገታት የሚችል አይኖርም። አንድ ሰው ስለዚህ ምስጢር በየቀኑ በጥቂቱ ለማስተዋል ቢሞክር በቂ ነው። የማወቅ ጉጉት የማያድርበት ዓይነት ሰው--ፈጽሞ አይሁኑ።”

የምንኖረው ምስጢራዊ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው--አይደል? ዘመናዊው ሳይንስ በእያንዳንዱ የሥነ ሕይወት ዘርፍ ያለውን አስደናቂ ውስብስብ ባህሪ አሳይቶናል። ታዲያ መንፈሳዊ ያልሆኑት ነገሮች እንዲህ ከሆኑ፤ መንፈሳዊው ምን ያህል ይጠልቅ? የሚከተሉት ጥቅሶች እውነት እና መልስ ስለ መፈለግ ምን ያስተምሩናል? ኤር. 29:13፣ ማቴ. 7:7፣ ሐዋ. 17:26-27፣ መዝ. 25:5፣ ዮሐ. 16:13፣ ዮሐ. 17:17።



መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ማናችንም ዓይነት የማወቅ ጉጉት በነበራቸው ሰዎች ታሪክ የተሞላ ነው--በመንገዳቸው እውነትን የሚፈልጉ እና ለሕይወት አስቸጋሪ ጥያቄዎች መልስ የሚሹ ጥያቄዎች፣ ፍርሐት፣ ተስፋ እና ደስታ ይፈራረቁባቸው የነበሩ ወንዶችና ሴቶች!

“ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም” (መክ. 3፡11)። ለመሆኑ ሰለሞን ምን እያለ ነው? በጥቅሱ የቀረበው የዕብራይስጡ “ኦላም” የተሰኘው ቃል “ዘላለማዊነት” በሚል የተተረጎመ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ “ያለፈው እና የወደፊቱ ስሜት” የሚል ፍቺ ይሰጡታል። በመሆኑም በዚህ ጥቅስ መሰረት እግዚአብሔር በሰብዓዊው ልብ እና አእምሮ ውስጥ ራሱ ዘላለማዊ የሆነውን--ያለፈውንና የወደፊቱን ስሜት አስቀምጦአል። ይህ ደግሞ እኛ እንደ ሰብዓዊነታችን የሕይወት “ታላላቅ ጥያቄዎች” ተብለው ስለሚጠሩት ነገሮች እንዲሁም በአጠቃላይ ስለ ሕይወታችን ማሰብ እንችላለን የሚል አንደምታ አለው። ቅዱሳት መጻሕፍት እዚህ ላይ ማዕከላዊ ሚና መጫወታቸው እርግጥ ነው። ለመሆኑ እኛ ማን ነን? ለምን በዚህ ተገኘን? እንዴት መኖር አለብን? ስንሞት ምን እንሆናለን? ክፋትና ሥቃይ ለምን ኖሩ? እነዚህ እንግዲህ ታሪክ መጻፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲጠየቁ የኖሩ እውነትን የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን እውነቶች የሚሹትን መርዳት የሚችሉ አንዳንድ መልሶች መስጠት መቻላችን እንዴት ያለ ልዩ መብትና ኃላፊነት ነው! በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንደሚገኘው ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት ሰዎችን ወደ እነዚህ መልሶች ካላመላከተና ካልጠቆመ እንግዲህ ፋይዳው ምንድን ነው?

ቅዱሳን መጻሕፍት በሕይወት ውስጥ ታላላቅ ጥያቄዎችን ለመመለስ ዐበይት ሚና መጫወታቸው የግድ የሆነው ለምንድን ነው?

ኅዳር 17
Nov 26

ሕይወታችንን ማጋራት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ተሰ. 2፡6-8። በትምህርት ቤት እና በቤተ ክርስቲያን ማንጸባረቅ ስለምንችለውና ስላለብን ነገር ምን እያለ ነው?



ማኅበረሰባዊው ዘውግ እየደረሰበት ያለውን መፈራረስ እየተጋፈጥን እና ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን የተረዳችበት መንገድ ይበልጥ ትርጉም የማይሰጥ የሆነበት ዘመን ውስጥ እንገኛለን። “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና” ማቴ. 18፡20 በማለት ጥቅሱ በሚሰጠው ማሳሰቢያ መሰረት ቤተ ክርስቲያን እና ማኅበረሰብ ቀዳሚውን ቅርጽ የያዙት በአማኞች መኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑን አዲስ ኪዳን ያሳየናል። ሕብረተሰቡ አነስተኛ ቁጥር በነበራቸው ቡድኖች እየተዳበለ፣ የሚጸልየው፣ የሚዘምረው፣ የጌታ ራት ሥነ ስርዓት የሚያካሂደው፣ የሚማረው እና የየሱስን ቃል አንዱ ለሌላው የሚያጋራው በዚህ ስፍራ ነበር። እነዚህ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው በኅብረት አምልኮ ያደርጉ የነበሩ ቡድኖች የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶችም ነበሩ። አዳዲስ አባላት የሱስን መሰረት ካደረገው መጽሐፍ ቅዱስ እና አዲስ ህይወት ጋር ትውውቅ ያደርጉ የነበረው በዚሁ ስፍራ ነበር። ጳውሎስ፡ “በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ 12፡2) ሲል የጻፋቸው መልእክቶች ቤተ ክርስቲያን ለሥነ ትምህርት የሥራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቷን ይጠቁማል።

አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ቡድኖች መሃል ወንጌል ምን ያህል ምርጥ በሆነ መንገድ መሥራት እንደሚችል እነዚህ የመጀመሪያ አማኞች ብዙም ሳይቆዩ መረዳት ችለው ነበር። በማኅበረሰቡ መሀል ድምጻችንን ከፍ አድርገን ለመዘመር፣ በጸሎት ለመትጋት፣ ለሌሎች ይበልጥ ለመጠንቀቅና ርኅራኄ ለማድረግ በቂ ምክንያት አለን። ሌሎች ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ሲናገሩ ስንሰማ፣ እርሱ ለእኛም ምን ያህል በጎ እንደሆነ እንረዳለን። ሰዎች እያደረጉ ስላለው ፍልሚያ እና ስለሚደርስባቸው የጉዳት መጠን ስንሰማ ደግሞ፣ እግዚአብሔር በገዛ ሕይወታችን ውስጥ እያደረገ ያለው የፈውስ መጠን ይታወቀናል፤ የጸጋው እና የፈውስ መሣሪያዎቹ ለመሆን የሚያስችለንን መታደስ ውስጣችን ይለማመዳል።

በዛሬው ምንባብ አምላካዊው ወንጌል ሁሉም ነገር ማለትም፡ የመስቀሉ ኃይል፣ የጌታ ትንሣኤ፣ የዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል መሆኑን ጳውሎስ አጽንኦት ሰጥቶ ሲናገር እንመለከታለን። በምድር ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አንዳችም መልካም የምስራች ባልነበረበት ወቅት ጳውሎስ የየሱስን ታሪክ በብርቱ ታማኝነትና ቁርጠኝነት ያካፍል ዘንድ እነሆ መላውን ህይወቱን ለዚህ ተግዳሮት አዋለ።

የወንጌል መልእክት ምርጥ በሆነ መንገድ የሚስተዋለውም ሆነ ምርጥ ተሞክሮ መሆን የሚችለው መንፈሳዊውን ህይወት ለሌላው በማጋራት እንደሆነ ጳውሎስ ጠቆም ያደርገናል። ሕይወታችን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የጸጋውን መልእክት ማሳየት አለማሳየቱን የሚከታተሉ ሰዎች በቅርባችን መኖራቸውን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም።

ስለ መንፈሳዊው ህይወትዎ በጥልቀት አሰብ ያድርጉና፡ በዙሪያዬ ላሉ ወገኖች ምን ዓይነት ምስክር ነኝ? ብለው ራስዎን ይጠይቁ።

ኅዳር 18
Nov 27


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሕዝቡ ስለ ዓለማዊ ትልቅነት የነበራቸውን ተስፋ ክርስቶስ ቀጨው። ክርስቶስ በተራራው ላይ በሰበከው ስብከት በተሳሳተ ትምህርት ምክንያት የተፈጸመውን ድርጊት ሁሉ ለማፈራረስና አድማጮቹ ስለ እርሱ መንግሥትና ስለ ራሱ ባሕርይ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ አሰበ። ሆኖም ሕዝቡን ስለ ስህተታቸው በቀጥታ አልዘለፋቸውም። የዓለም ሰቆቃ መንስኤው ኃጢአት መሆኑን ቢያውቅም፤ የሕዝቡን ጉስቁልና አስከፊነት እንደ ሥዕል አድርጎ አላሳያቸውም። እነርሱ ከሚያውቁት እጅግ በጣም ስለ ተሻለ ነገር አስተማራቸው። ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የነበራቸውን አስተሳሰብ ሳያንቋሽሽ ስለዚህ መንግሥት ምንነት ራሳቸው አስበው እንዲደርሱበት በመተው ወደዚያ መንግሥት የሚገባበትን ሁኔታ ነገራቸው። የሱስ ያስተማረው እውነት ያን ጊዜ ይከተለው ለነበረው ሕዝብ አስፈላጊ የነበረውን ያህል ዛሬም ለእኛ አስፈላጊ ነው። እኛም እንደ እነርሱ የእግዚአብሔር መንግሥት በምን መርሖች ላይ እንደ ተመሰረተ መማር ያስፈልገናል።” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 297-298።)


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሮበርት ሉዊስ ስቲቨንሰን የተወለደው በ1850 በስኮትላንድ ኤዲበርግ ነበር። ታዲያ አንድ ምሽት ላይ ሞግዚቱ ልታስተኛው አልጋውን እያሰናዳች እያለ ልቡን የመሰጠውን ትዕይነት በመስኮት ተመለከተ። በዚያን ዘመን የዛሬው ኤሌክትሪክ ገና ባለመፈልሰፉ ምሽት ላይ ለመንገዱ ብርሃን የሚሰጡት በምሰሶዎች ላይ የተተከሉ የናፍጣ ኩራዞች ነበሩ። ለሥራው የተመደበው ባለሙያ እያንዳንዱ ምሰሶ ላይ እየወጣ ኩራዙን መለኮስ ነበረበት። ስቲቨንስ እየተመለከተ ባለው ነገር አብልጦ እየተፍነከነከ ሞግዚቱን ጠርቶ “ጨለማውን በብርሃን ጸዳል የሚለኩሰውን ያንን ሰው ተመልከቺ!” አላት። ለማኅበረሰብዎ ብርሃን እና ፍቅር ያመጡ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጦት ሚና ምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ካልሆኑ ከቤተ ክርስቲያን አባላት ጋር ቁጭ ብላችሁ ልታከናወኑ በምትችሏቸው ነገሮች ዙሪያ ተወያዩ።

2.ቤተ ክርስቲያን ወደ ዓለም ትደርስ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ጥምረት መፍጠር ካለባት፤ የየሱስን ቃላት እና አገልግሎት አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል። እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ ከእኛ ጋር በምድራችን ሊኖር፣ ሊታገል፣ ሊስቅና ሊያለቅስ የመጣበት ዋና ምክንያት--በዙሪያችን ላሉ ጥንቃቄ እንድናደርግ መጠራታችንን ያሳስበናል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ይህን ሥራ ለማገዝ ይረዳ ዘንድ የጉባዔአችሁን ወጣቶች የተልዕኮው አካል ማድረግ የምትሉት እንዴት ነው?

3.እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ሕዝብ--የተሰጡንን አስደናቂ እውነቶች ለሌሎች በማስተማር ረገድ ስላለብን ኃላፊነት አሰብ ያድርጉ። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን እውነቶች ለሌሎች በማስተማር ቁልፍ ሚና ሊኖራት የሚችለው እንዴት ነው? በተመሳሳይ በዚህ ዙሪያ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ከሚጠይቁ ጋር እውነትን ለመወያየት ቤተ ክርስቲያን ደኅንነቱ የተጠበቀ ስፍራ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ጥልቀት ያላቸው ወሳኝ ጥያቄዎች የሚነሱበት ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር ምን ማድረግ ይችላሉ? 4.በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ስለሚስተዋሉ ጭፍን ፍረጃዎች ተነጋገሩ። ሰዎች ከእንዲህ ዓይነቱ ሁናቴ ተላቅቀው መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አስተምህሮ ይከተሉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያንዎ ትምህርት የምትሰጥባቸው መንገዶች ምን ይመስላሉ?