የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከጥቅምት 28 - ሕዳር 4

7ኛ ትምህርት

Nov 07 - Nov 13




አምልኮ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዳን. 3፣ ራእ. 14:6–12፣ መዝ. 78:1–17፣ ዮሐ. 4:7–26፣ 1ዜና. 16:1–36፣ ማር. 7:1–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤ በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ” (1ዜና 16፡ 29)፡፡

ሰ ው በኃጢአት ቢወድቅም አምልኮ የሰብዓዊው ማንነት ክፍል ነው፣ የሰብዓዊው ተፈጥሮ አካል ነው። እኛ እንደ ሰው ከእግዚአብሔር ከተሰጠን ነፃነት የተነሳ ጌታን እንድናመልክ መፈጠራችን ጥርጥር የለውም። እርሱን እንወደዋለን አምልኮ እንደሚገባውም እናውቃለን። እንዲህ ዓይነቱ አምልኮ ሰዎች በኃጢአት፣ በሞት እና ውድመት ባልተበከለው ተፈጥሮ መሃል እግዚአብሔርን በቀጥታ ይገናኙ በነበረበት፣ ከውድቀት አስቀድሞ በነበረው ዓለም እጅግ ቀላል እንደ ነበር ለማሰብ አያዳግትም። የወደቀውን ዓለም ብቻ ለምናውቅ ለእኛ ይህን ማሰብ ቀላል ሊሆን አይችልም። ለእኛ ተፈጥሮአዊ የሆነውና ማንነታችን የሚሻው አምልኮ ዛሬም ውስጣችን መኖሩ እሙን ቢሆንም፤ ነገር ግን በዚህ ዓለም እንደ ሆነው ማንኛውም ነገር በኃጢአት የተጠማዘዘና የተዛባ ሆኗል። ይህ ማለት እኛ እንደ አምልኮ አቅራቢነታችን መጨረሻችን ላልተገቡ ነገሮች መስገድ፤ ወይም ጌታ እንዲመለክ ካስቀመጠው መንገድ ያፈነገጠ ሊሆን ይችላል (ማር. 7፡1-13፣ ኤር. 7፡4)።

በመሆኑም አምልኮ የክርስትና ተሞክሮ ማዕከላዊ አካል እንደመሆኑ፤ ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት የዚህ ሣምንት ጥናታችን ርዕሰ ጉዳይ ከሆነው የአምልኮ ጥያቄ ጋር መጎዳኘት ይኖርበታል።

ጥቅምት 29
Nov 08

ሁላችንም አንድ የምናመልከው ነገር አለ


በመጀመሪያ በእግዚአብሔር አምላክ ተሸምኖ በውስጣችን ጓዳ የተሸሸገ አንድ ነገር ለመኖሩ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን በማንኛውም ነገር ላይ እንደሆነው፤ ይህ አምልኮ ናፋቂ ማንነት በኃጢአት ተሸፈነ። ያኔ መጀመሪያ ላይ አምልኮአችን ይቀርብ የነበረው አምልኮ ለሚገባው ጌታችንና ፈጣሪያችን ለሆነው ለእርሱ ብቻ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን ከውድቀት አንስቶ ይህ ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ ተለወጠ።

እርግጥ ነው ምንም ይሁን ምን--ሁላችንም የምናመልከው አለን። ይህ ዛሬን ጨምሮ በረጅሙ የሰብዓዊው ፍጡር ታሪክ ሰዎች አምልኮ የሚያደርጉበትን መንስኤ ለመግለጽ ይረዳል። በጥንታዊቷ ግብፅ አንዳንዶች ለፈርዖኖች አምልኮ ያቀርቡ የነበረ ሲሆን የሌሎች አገር ሕዝቦች ደግሞ በዓሣ ቅርጽ ለተሠራ ሐውልት፣ ብዙ ራሶች ለነበሩት አማልክት እና ለመሳሰሉት ይሰግዱ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን የሚያመልኩ ሕዝቦችም ነበሩ።

ዛሬ በእንቁራሪት ቅርጽ ለተሰየመ ሐውልት (የማርያምን ሳንጨምር) አጎንብሶ ለመስገድ ብዙዎች የሚገኙበት ዘመነኝነት የሚፈቅድላቸው አይመስልም። ነገር ግን ይህ ማለት ዓለማውያንን ጨምሮ ሰዎች የሚያመልኩት ነገር የላቸውም ማለት አይደለም። ገንዘብ፣ ወሲብ፣ ራሳቸውን፣ የሙዚቃ ኮከቦችን፣ የፊልም አክተሮችን፣ ፖለቲከኞችን--ያመልካሉ። ልባችንን ያነሆለለው፣ አትኩሮታችንን የገዛውና ራሳችንን አሳልፈን የሰጠነው ማንኛውም ነገር--እርሱ የምናመልከው ነው። ዓለማዊው ፀሐፊ ዴቪድ ፎስተር እንደሚሉት፡ የተሳሳተውን ነገር ካመለካችሁ “በቁማችሁ ይሰለቅጣችኋል” የዳን. 3 ታሪክ ስለ እውነተኛ አምልኮ አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል?



ሦስቱ የአይሁድ ወንዶች ልጆች ሁለተኛውን ትእዛዝ (ዘፀ. 20፡4-6) እግዚአብሔር በተናገረው መሰረት አጽንኦት ሰጥተው ተግብረውታል። ለነገሩ ግድያን፣ ስርቆትንና የመሳሰሉትን የሚከለክለው የዐሥርቱ ትእዛዛት አካል አይደል? አምልኮ--ማለትም እውተኛ አምልኮ በእጅጉ አስፈላጊ እንደመሆኑ ክርስቶስ ከመገለጡ አስቀድሞ ባሉት የመጨረሻዎቹ ቀናት የሁሉም ነገር ማዕከል የሚሆንበትን ቅርጽ እየያዘ በመምጣት ዓይነተኛ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል። ስለሆነም ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት መላውን የአምልኮ ጥያቄ ማካተቱ የግድ ይሆናል፡ አምልኮ ምንድን ነው? እንዴት እንተገብረዋለን? ለምን አስፈለገ? ማንን እናመልካለን?

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-12። ክርስቶስ ዳግም ከመገለጡ አስቀድሞ ባሉት የቀውስ ወቅቶች የአምልኮ ጥያቄ ምን ያህል ወሳኝ ሊሆን እንደሚችል አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?

ጥቅምት 30
Nov 09

እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው እንዲነግሩ ነው


የብሉይ ኪዳኑ መጽሐፈ መዝሙር ውሎ አድሮ በጥንት እስራኤል ኃይማኖታዊ ህይወት የሚጫወተው ሚና ነበረው። በአምልኮ ጊዜ፤ በተለይ እስራኤላውያን ቁልፍ የነበረውን የአንድነት አምልኮ በሚያደርጉበት ወቅት ከመጽሐፉ ክፍል ቃል በቃል ደግመው እንዲሉ ከመደረጋቸው በተጨማሪ በሙዚቃ መሣሪያ እየታጀቡ ይዘምሩትም ነበር። እስራኤል እንደ አንድ ማኅበረሰብ ይንቀሳቀስና ያመልክ ነበር። መጽሐፈ መዝሙር በመሠረቱ በሥነ ግጥም መድብሎች እና በመዝሙር ግጥሞች የተዋቀረ ሥራ ነው። የዕብራይስጥ ቃል የሆነው--ቴሂሊየም “የምስጋና መዝሙሮች” የሚል ፍቺ አለው። እግዚአብሔርን ለማመስገን ስንዘምር ምንም አደረግን ምን ጌታን እያመለክን ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 78፡1-17። በዚህ ስፍራ የምናገኘው መሰረታዊ መልእክት ምንድን ነው? ከአጠቃላዩ ሥርዓተ ትምህርትና አምልኮ ጥያቄ ጋር እንዴት ይጣጣማል?



በመዝሙር 78 ላይ በቀረበው መልእክት አንድ የሆነ ቁርጠኝነት እንመለከታለን። አሳፍ በቁ. 2 “ከጥንት የነበረን ዕንቆቅልሽ” እንዴት ለሌሎች ማካፈል እንዳለብን ይጠቅሳል። ዕንቆቅልሽ የተሰኘው ቃል “ተምሳሌት”፣ “ምስጢር” ወይም “ጣፋጭ ጥንታዊ እውነቶች” በሚል ፍቺ ጥቅም ላይ የዋለበት ሁኔታም አለ። እዚህ ላይ የምናገኘው ዋናው ነጥብ የእስራኤል ሥርዓተ ትምህርት የቱንም ዓይነት ሌሎች ነጥቦች ቢያካትትም፤ ጌታ ከተመረጠው ሕዝብ ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ለልጆች ማስተማርን ያካተተ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 78፡6-17። ልጆቻቸውን ማስተማር የነበረባቸው ዓይነተኛ ትምህርቶች ምን ነበሩ? የሥርዓተ ትምህርቱ የመጨረሻ ግብ ምን ነበር?



ልጆች በእግዚአብሔር ስለ መታመንና ትእዛዛቱን ስለ መጠበቅ መማራቸው በጥቅሶቹ ከተመለከተው የሥርዓተ ትምህርቱ ግቦች መካከል አንዱ ነው። እንደ ራእ. 14፡12 ያሉ ጥቅሶች ይህን ተመሳሳይ ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ሊያንጸባርቁልን ይችላሉ።

ኅዳር 1
Nov 10

በመንፈስ እና በእውነት


የሱስ የተሰበሩ ልቦችን ካገለገለባቸው አስደናቂ የአዲስ ኪዳን መልእክቶች አንዱ የየሱስ እና በውሃ ጉድጓዱ አጠገብ የነበረችው ሴት ታሪክ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 4፡7-26። የሱስ ስለ አምልኮ ምን አላት? እንደውም ሲጀመር፤ ወደ አምልኮ ርዕሰ ጉዳይ እንዴት ሊያመሩ ቻሉ?



ምንም እንኳ ሴቲቱ ስለ አምልኮ በማንሳት እየተነጋገሩ የነበረውን ርዕስ ለመለወጥ ብትሞክርም፤ የሱስ የእርሷን ዘዴ ተጠቅሞ ስለ አምልኮ እና አምልኮ ስለሚያካትታቸው ነገሮች አንዳንድ መሰረታዊ እውነቶችን ይሰጠናል። ምናልባት ለቀጣዩ ግባችን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ነጥብ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” (ዮሐ. 4፡24) ሲል የተናገረው ነው።

ለጌታ አምልኮ የሚቀርብበት እውነተኛ መንገድ “በመንፈስ” መሆን ያለበት ሲሆን፤ ይኸውም እግዚአብሔርን ከመውደድ እና እርሱን በግል ከማወቅ ተሞክሮ መመንጨት ይኖርበታል። “ከእግዚአብሔር የሚገኝ ኃይማኖት ብቻ ነው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ። እርሱን በትክክል ለማገልገል ከመለኮታዊ መንፈስ መወለድ አለብን። ይህም ልባችንን በማንጻትና አእምሮአችንን በማደስ እግዚአብሔርን እንድናውቅና እንድንናፈቅረው የሚያደርገን አዲስ ችሎታ ይሰጠናል፤ እርሱ ከእኛ የሚፈልግብንን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኛ ያደርገናል። እውነተኛ አምልኮ ማለት ይህ ነው። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውጤት ነው” (የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 177)

በተመሳሳይ አምልኮ “በእውነት” ሊተገበር ይገባል። እግዚአብሔር ማን እንደሆነና ከእኛ ምን እንደሚፈልግ አስመልክቶ ትክክለኛ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል። በሌላ አነጋገር ኃይማኖታዊ አስተምህሮም እዚህ ውስጥ ይካተታል። (ለምሳሌ የምናመልከው አምላክ ሰዎችን ለዘላለም በገሃነም የማያቃጥል መሆኑን ማወቃችን ተገቢ፤ ብሎም ሙሉ ስሜት የሚሰጥ ነው።)

በመሆኑም አምልኮን አስመልክቶ እዚህ ላይ ሁለት አላባዎችን እናገኛለን፡ እግዚአብሔርን በማወቅና በመታዘዝ የሚመጣ ልምድ እና ስለ እግዚአብሔር የተገለጡልን ተጨባጭ እውነቶች። መንፈስ ያለ እውነት--ከምንም ነገር በላይ ተለዋዋጭ ወደሆነ ግልብ እና ኢ-ተአማኒ ስሜት ውስጥ የሚመራ ሲሆን፤ በተቃራኒው--እውነት ያለ መንፈስ ደግሞ ወደ ህይወት ዐልባ ሥርዓታዊነት ሊመራ ይችላል። ስለዚህ ሁለቱም ያስፈልጉናል።

አንድ ሰው “በመንፈስ እና በእውነት” አምልኮ እንዲያደርግ ለማስተማር ያሎት ቀናኢነት ምን ይመስላል? ከሌላኛው ይልቅ በአንደኛው ላይ ይበልጥ አጽንኦት ሊፈልግ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ኅዳር 2
Nov 11

የቅድስና ውበት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዜና 16፡1-36። ትዕይንቱን በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ። በክብር የተሞላ እና አስፈሪ ወይስ ደስታና ሐሤት የተንጸባረቀበት ድባብ? የእነዚህ የሁለቱም ጥምረት ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው? አምልኮን እንዴት ማስተማር፤ አልፎ ተርፎም መለማመድ እንዳለብን አስመልክቶ ከዚህ ትዕይንት ምን መማር እንችላለን?



እግዚአብሔር በጥንት እስራኤላውያን መሃል ያደረበትና ለሕዝቡ የደኅንነት እቅድ የተገለጠበት የአምልኮ ስፍራ የመገናኛው ድንኳን ነበር። የአምልኮና የአምልኮ አስተምህሮ አስኳል--በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ወደፊት የሚመጣውን ያመላክት የነበረው የሱስ እና አምላካዊው የደኅንነት እቅድ መሆን ይኖርበታል። እግዚአብሔር ምስጋና እና አምልኮ እንዲገባው መንስዔ ሊሆን የሚችል ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢያደርግልንም እንኳ--የዘላለማዊ ህይወት ተስፋን ያሰነቀን በእያንዳንዳችን ምትክ መሥዋዕት ከሆነበት የመስቀል ላይ ሞቱ ውጪ ምንም ማለት አይደለም። በተጨማሪ ጥቅሶቹ የያዙትን “ወንጌላዊ” ግፊት ልብ ይሏል፡ ዓለም ሁሉ ስለ የስራኤል አምልክ መማር ነበረበት።

“ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤ በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ” (1ዜና 16፡ 29)። “በቅድስናውም ክብር” የተሰኙት ቃላት ምን ዓይነት ፍቺ ይኖራቸዋል?



ኃጢአት ምን ያህል አስቀያሚ፣ አውዳሚና አዋራጅ አንደሆነ አሰብ ያድርጉ። ደግሞም የእስራኤል አጎራባች ሕዝቦች ዛሬ እኛ ለማሰብ እንኳ የሚያዳግተንን ሁሉንም ዓይነት አጸያፊ ድርጊቶች ጨምሮ ህፃናትን መሥዋእት አድርጎ እስከ ማቅረብ የዘቀጠ ክፉ እና ዘግናኝ ድርጊት ይፈጽሙ ነበር። እነዚህ ነገሮች ድርጊቶቹን ይፈጽሙ የነበሩ ሰዎችን ማንነት በጉልህ ማንጸባረቃቸው እሙን ነው።

በተቃራኒው የጥንቷ እስራኤል ዙሪያዋን ከከበቧት ክፉ ልማዶች የተለዩ ቅዱስ ሕዝብ ያላት አገር መሆን ነበረባት። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በልባቸውም ሆነ በአእምሮአቸው ቅዱስ መሆን ነበረባቸው። ይህ ደግሞ አምልኮአቸው በእግዚአብሔር ፊት ትርጉም ያለውና ውበት የተላበሰ የመሆኑ መንስኤ ነበር። በማጭበርበርና ምልጃ የመጠየቅ ቅሌት የተዘፈቁና ልባቸው ከጌታ የራቀ ሕዝቦችን የብሉይ ኪዳን ነቢያት በተደጋጋሚ አምርረው ሲወቅሱና ሲገስጹ ኖረዋል።

ኅዳር 3
Nov 12

ጣዖት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ


የጥንት እስራኤላውያን ጽኑ አምልኮ ያደርጉ በነበሩ ሕዝቦች የተከበቡ ነበሩ። እነዚህ ሕዝቦች ለአማልክቶቻቸው ያቀርቡ የነበረው አምልኮ እጅግ የከረረ ከመሆኑ የተነሳ የገዛ ልጆቻቸውን ሳይቀር በመሥዋዕትነት ይገብሩ ነበር። ይህ ለእምነታቸው የነበራቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል--አይደል?

በመሆኑም አምልኮ፣ ማለትም ለእውነተኛው አምላክ የሚቀርብ እውነተኛ ስግደት ዕብራውያን ዙሪያቸውን ከበዋቸው ከነበሩ ከእነዚህ ጣኦቶችና ሐሰተኛ አምልኮዎች መጠበቅ የቻሉበት እጅግ አስፈላጊ ክፍል ነበር። የሚገርመው ለእስራኤላውያኑ መጠነ ሰፊ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡም እነርሱ ግን በተለይ እንዳያደርጉት በተነገራቸው የጣኦት አምልኮ ደጋግመው ይወድቁ ነበር።

ዛሬስ? እርሱ ለእኛ የዋለልንን ስፍር ቁጥር የሌለው በጎ ተግባር ዘወትር እያስታወስን ይህን እውተኛ አምላክ ማምለካችን በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው--በተለይ ከፊታችን ከተጋረጠው ዘመናዊ የጣኦት አደጋ አኳያ?

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 7፡1-13። ከዓለም እየተመዘዙ በእምነት አቋማችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ነገሮችን አስመልክቶ ከክርስትና ሥርዓተ ትምህርት ዐውድ እና ከሐሰተኛ አስተምህሮ አደጋ አኳያ ዛሬ ልንተገብራቸው የምንችላቸውን ምን ዓይነት መርኅዎች ከጥቅሶቹ ማግኘት እንችላለን?



በአሁኑ ጊዜ በዓለም ከሚስተዋሉ ታላላቅ ምሑራዊ ጽንሰ ሀሳቦች አብዛኞቹ ተፈጥሮአዊውን ዕይታ መሰረት ያደረጉ ናቸው። በየትምህርት ቤቶች የሚታየው ሥነ ሥርዓት ነክ ጉዳይ የዚህ አስተሳሰብ ውጤት ከመሆኑ አኳያ--ባብዛኛው ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ ያሉ ጽንሰ ሀሳቦችን ወደ ተማሪዎች ማስረጹ የዐደባባይ ምስጢር ነው። መሰረታዊ እውነታ ተብለው የሚታሰቡትን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የተቀመጡና በተግባር ላይ የዋሉ ጽንሰ ሀሳቦች ለማምለክ ልንፈተን እንችላለን። በተጨማሪ የእነዚህን ጽንሰ ሀሳቦች አፍላቂ ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶች እና የሒሳብ ሊቅ ጠበብት አእምሮ እንደ ጣኦት ልናመልክ እንችላለን። እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች አዘውትረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ቢላተሙም፤ ችግሩ--የትምህርት ሥርዓቱ አካል በመሆናቸውና እውነት ተብለው በመታመናቸው ሰዎች ከክርስትና ሥርዓተ ትምህርት ጋር ሊያዋህዷቸው ሲሞክሩ ይታያሉ። የሆነው ሆኖ፤ ከዚህ አኳያ ሊደረግ የሚችለው ብቸኛው መንገድ እምነትን ለድርድር ማቅረብ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው መጽሐፍ ቅዱስን ከዘመኑ ጽንሰ ሀሳብ ጋር ገጣሚ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ቃሉን መጠምዘዝና ማዛባት ይሆናል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጋጩ ከፍ ያለ ዕውቅና ከተቸራቸው እምነቶች መሃል አንዳንዶቹን መጥቀስ ይችላሉ? እንደ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች ከትምህርት ሥርዓታችን ጋር ውህደት እንዳይፈጥሩ በማድረግ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ኅዳር 4
Nov 13


ተጨማሪ ሀሳብ


“ልብ ከሁሉም ነገር በላይ እጅግ አታላይ እና ክፉ ነው። የሥነ ኃይማኖት ፕሮፌሰሮች እምነታቸውን አስመልክቶ ራሳቸውን በቅርብ ለመመርመር ፈቃደኞች አይደሉም። በመሆኑም ብዙዎች ሐሰተኛ ተስፋ ላይ መመካታቸው አስፈሪ ሐቅ ነው። አንዳንዶች ከዓመታት አስቀድሞ በነበራቸው አሮጌ ተሞክሮ ላይ ይተማመናሉ። ሁሉም የየዕለት ተሞክሮ ሊኖረው የግድ እንደመሆኑ፤ የልባቸውን ጓዳ የሚመረምሩበት ጊዜ ሲመጣ ከዛሬው የሚዛመድ አንዳች ነገር እንደሌላቸው ይመለከታሉ። የቀደመው የእውነት ኪዳን እንደሚያድናቸው አድርገው የሚያስቡ ይመስላሉ። ሆኖም እግዚአብሔር የሚጠላቸው እነዚያ ኃጢአቶች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፤ የሱስ በልብዎ ጓዳ ውስጥ ገብቶ ከእርስዎ ጋር እራት ይበላል። ይህ ሲሆን ከየሱስ መለኮታዊ ብርታት ያገኛሉ፤ በእርሱም ያድጋሉ። በጌታ የሱስ ክርስቶስ ድል የሚሰጠን እግዚአብሔር አምላክ የተባረከ ይሁን ብለው በድል አድራጊነት ይናገራሉ።

በለብታ ህይወት የሚኖሩ የሥነ ኃይማኖት ፕሮፌሰሮች ጭራሹኑ ስሙን ባያነሱ ይበልጥ ለጌታ አስደሳች በሆነ ነበር። ለየሱስ ታማኝ ተከታይ ለሚሆኑ የማያባራ ሸክም ሆነው ይቀጥላሉ። ለማያምኑ የመሰናከያ እንቅፋት በመሆናቸው ክፉ መናፍስት ይከብሩባቸዋል። በጠማማው መንገዳቸው በእግዚአብሔር መላእክት ይሳለቃሉ። እንዲህ ያለው አካሄድ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላለው አምላካዊ ሥራ መርገም ነው። በከንፈራቸው ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ ልባቸው ግን ሩቅ ነው”—Ellen G. White, Spiritual Gifts, vol. 2, p. 227.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.የሐሰተኛ አምልኮ ሥረ መሰረት የልብ ችግር መሆኑን በማር. 7፡ 1-13 ተምረናል። አምልኮአችን ከልባችን ካልፈለቀ በቀር እግዚአብሔር የከንፈራችንን አይመለከትም። ወንጌል እና የሱስ ስለ እኛ የመሞቱ ታሪክ በእውነት እግዚአብሔርን የሚወዱ ልቦችን ለመክፈት ብርቱ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው?

2.እግዚአብሔርን “በንፈስ እና በእውነት” በማምለክ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ጠለቅ ያለ ምልከታ ያድርጉ። አንዱን አድርጎ ሌላውን መተው ይቻላል? ወይስ እውነተኛ አምልኮ ሁለቱንም ይጠይቃል? እንዲያ ከሆነ--ለምን?

3.እርግጥ ነው--እግዚአብሔርን በእውነት ለማምለክ ልባችን ቀናውን ጎዳና መከተል አለበት። ግን ይህ ምን ማለት ነው? ለጌታ አምልኮ ማቅረብ ከመቻልዎ አስቀድሞ ሕይወትዎ ፍጹም በሆነ ሥርዓት ከእርሱ ጋር ሙሉ ለሙሉ እስኪተሳሰር መጠበቅ ይኖርቦታል? በሌላ በኩል አምልኮ ማለትም እውነተኛ አምልኮ ልብዎ ከእግዚአብሔር ጋር በትክክል እንዲገናኝ ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?