መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንተርጉም
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2020

ሚያዝያ 24-30

6ኛ ትምህርት

May 02 - May 08




ትርጉም ለምን አስፈለገ?



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ፡- ሉቃስ 24፡36-45፤ 1ቆሮ. 12፡ 10፤ 1ቆሮ. 14፡26፤ ሐዋ. 17፡16-32፤ ዮሐ.12፡42-43።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል።” (ዕብ.11፡6) ።

መ ጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ማለት መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ማለት ነው። ነገር ግን ያን እንዴት እናድርግ? ምን አይነት መርሆዎችንስ እንጠቀም? የምናገኛቸውን የተለያዩ የጽሁፍ አይነቶች በምን አይነት ሁኔታ እናስተናግዳቸው? ለምሳሌ የምናነበው ክፍል ምሳሌያዊ ንግግር፣ በህልም የተገለፀ ትንቢታዊ ምሳሌ ወይንስ ታሪክን የሚተርክ ጽሁፍ ነው? ከቃሉ አውድ በመነሳት የምናነሳቸው እንደነዚህ ያሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ራሳቸው የትርጉም ስራ ተግባራት አካል ናቸው። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መለኮት የጥበብ ቃል በመውሰድ ምሪትን እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ቃሉን እንዲሁ በዘፈቀደ ከፍተው ጥቅሶችን የሚያነቡበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን የተለያዩ ጥቅሶችን በዘፈቀደ እያገናኙ ማንበብ እንግዳ ወደሆነና ወደተሳሳተ ድምዳሜ እንድንደርስ ያደርገናል።

ለምሳሌ አንድ ባል ወደ ሌላ ሴት ሄዶ ሚስቱን ቢተዋት ሚስትየዋ የሚከተለውን ጥቅስ ስታገኝ ታላቅ ማረጋገጫ እንዳገኘች ልትቆጥር ትችላለች “በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁሁ” (ዘፍ.3፡15)። ይህን ጥቅስ መሰረት አድርጋ በመያዝ የባልዋ ጉዳይ እንደማይዘልቅ ልታምን ትችላለች! ያለ አውዱ የቀረበ ማንኛውም ጥቅስ የአንድን ሰው አጀንዳና ሃሳብ በፍጥነት ለማስረፅ ቀድሞ የቀረበ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ያክል ብቻ ሳይሆን በትክክል ለመተርጎም ማንበብ አብዝቶ ከኛ ይጠበቃል። የዚህን ሳምንት ትምርት አጥንተው ለሚያዝያ 10 ሰንበት ይዘጋጁ።

ሚያዚያ 25
May 03

አስቀድሞ የተጠየቀ ጉዳይ


ሉቃስ 24፡36-45ን አንብቡ። ከቃሉ ጋር በደንብ ይተዋወቁ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አንዳንድ ክስተቶች ተተንብየው በፊታቸው ተዘርግቶላቸው እያለ የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛ ትርጉም እንዳያዩ የጋረዳቸው ነገር ምንድነው?





ማንም በባዶ አዕምሮ ጥቅሶችን ለማንበብ አይመጣም። እያንዳንዱ አንባቢ፣ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከተለየ ታሪኩ እና ግል የህይወት ልምዱ ጋር ወደ ቃሉ ይመጣል ይህም ቃሉን የመተርጎም ሂደቱ ላይ የማይናቅ ተፅዕኖ ያመጣል። ደቀ መዛሙርቶቹ እንኳን ሳይቀር በጊዜው ይጠብቁ ከነበረው ነገር በመነሳት መሲሁን በተመለከተ የራሳቸው የተለያየ አስተሳሰብ ነበራቸው። የነበራቸው ጠንካራ እምነታቸው ስለየሱስ ህይወት፣ ሞትና፣ ትንሳኤ የመሳሰሉ ያሉ ክስተቶችን እንዲያስተውሉ የሚያደርጋቸውን ግልጽ የእግዚአብሔር ቃልን እንዳያስተውሉ ከለከላቸው።

ሁላችንም ስለዚህች አለም ሁኔታ፣ ስለ እውነት ጥግ እና ስለ እግዚአብሔር ወዘተ… በተመለከተ በውስጣችን ያዳበርናቸው ብዙ እምነቶች ስላሉን መጽሐፍ ቅዱስን ስንተረጉም አስቀድመን እንጠይቃለን ወይንም ደግሞ እንዲሁ ባለማወቅ እንቀበላለን። ማንም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በባዶ አዕምሮው የሚቀበል የለም። ለምሳሌ አንድ ሰው አለምን የሚያይበት እይታ በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ከተፈጥሮ ውጪ የሆነን ተግባር እንዳይቀበል ሊያደርገው ይችላል። ይህ ሰው በቃሉ እግዚአብሔር በታሪክ ያደረጋቸውን ነገሮች እውነተኛና ተአማኒ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ሊረዳ አይችልም። ነገር ግን ከተፈጥሮ ውጭ ያለውን ሀይል እውታ ከሚቀበሉቱ በተቃራኒ ነገሮችን በተለየ መልኩ ይተረጉማል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ከኋላ ታሪካቸው፣ ከህይወት ልምዶቻቸው፤ከሚኖሩበት አስተሳሰብ እና ቀድመው ከያዙት እምነትና እይታ ውጪ ሙሉ በሙሉ ሊነጠሉ አይችሉም። ሙሉ በሙሉ ገለልተኛና አድሎአዊነት የሌለበት ወይንም ደግሞ ፍጹም የሆነ ራሱን የቻለ ነፃ ሃሳብን ማሳካት አይቻልም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና የስነ መለኮት ነጸብራቅ ሃሳቦች ብዙ ጊዜ ከአለም ተፈጥሮ እና ከእግዚአብሔር ተፈጥሮ በተቃራኒ ቆመው ይታያሉ።

መልካሙ ዜና ግን መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በተከፈተ አዕምሮ እና ታማኝ በሆነ ልብ በምናነብበት ጊዜ ጠባብ የሆነ እይታችንንና አስቀድሞ የነበሩ ጥያቄዎቻችንን በመፍታት ግልጽ ያደርግልናል። መጽሐፍ ቅዱሳችን በተደጋጋሚ እንደሚያረጋግጥልን ከተለያየ አመጣጥና ታሪክ ቢመጡም መንፈስ ቅዱስ ስለሚመራቸው የእግዚአብሔርን ቃል ማስተዋል ችለዋል። “ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል።” (ዮሐ.16፡13)። ይህንን አለም በተመለከተ አስቀድመው የሚጠይቋቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ምንድናቸው? በምን አይነት መንገድ ነው በቃሉ ሁሉ ነገራችንን በማስረከብ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረን እውነታ ጋር እንዲጣጣምና ቃሉ ብቻ እንዲቀርፀን የምንፈቅደው?

ሚያዚያ 26
May 04

የጽሑፍ ትርጉም እና የንግግር ትርጉም


መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ጥንታዊ በሆኑት ቋንቋዎች ነው የተፃፈው፤ ብሉይ ኪዳን በአብዛኛው የተጻፈው በዕብራይስጥ ሲሆን ጥቂት ክፍሎች በአረማይክ ተፅፈዋል፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ በተለመደው የግሪክ ቋንቋ ተፃፈ። አለማችን ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ ህዝቦች ዛሬ ላይ እነዚህን ጥንታዊ ቋንቋዎች መናገርና ማንበብ አይችሉም። ስለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ወደተለያዩ ዘመናዊ ቋንቋዎች መተርጎም የነበረበት። ነገር ግን ጥሩ የሆኑ ተርጓሚዎች እንደሚረዱት ከሆነ እያንዳንዱ የጽሑፍ ትርጉም አንዳንድ የቋንቋና የንግግር ፍቺዎችን ማካተት አለበት።

በአንድ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ቃላት በሌላ ቋንቋ አቻ የሆነ ፍቺ አናገኝላቸውም። (በጥንቃቄ ጥቅሶችን የመተርጎምና በኋላም በቋንቋና ንግግሩ ይዘት የመፍታት ጥበብ “ሄርሜኔቲክስ” (hermeneutics) ይባላል።) 1ቆሮ.12፡10፤ 1ቆሮ.14፡26፤ ዮሐ.1፡41፤ 9፡7፤ ሐዋ.9፡36 እና ሉቃስ 24፡27ን አንብቡ። ከላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ የጽሁፍ ትርጉምንና የንግግር ቋንቋ ትርጉምን እሳቤ እናያለን። ሉቃስ 24፡27 ላይ የሱስ እንኳን ለደቀመዛሙርቱ የቃሉን ትርጉም መግለፅ ነበረበት። ይህ በንግግር የመተርጎምን አስፈላጊነት እንዴት አድርጎ ይነግረናል?





ሄርሜኔቲክስ `hermeneutics` (የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ) መነሻ ቃሉ የግሪክ ቃል ሄርሚኒዮ `hermeneuo` ሲሆን ቃሉ የመጣውም ከግሪክ አማልክት መካከል ሄርምስ `Hermes`ተበሎ ከሚጠራው ነው። ሄርመስ የአማልክት መልዕክተኛ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ካሉበት የሀላፊነት ጉዳዮች መካከል መለኮታዊውን መልዕክት ለሰዎች ማድረስ ይገኝበታል። ሄርሜኔቲክስን በተመለከተ የምናገኘው ወሳኝ ነጥብ ቢኖር የመነሻ ቋንቋውን ማንበብ እስካልቻልን ድረስ ጥቅሱን የምናገኘው በትርጉም ቋንቋ ነው። እንደ እድል ሆኖ አብዛኛዎቹ ትርጉሞች መሰረታዊውን ትርጉም ሳይለቁ በመተርጎም ትልቅ ስራ ሰርተዋል። በቃሉ ውስጥ የተገለፀውን ወሳኝ የሆነውን እውነት ለመረዳት የግድ የመጀመሪያውን መነሻ ቋንቋ ማወቅ አይጠበቅብንም። ይህ የቋንቋ እውቀት ቢኖረን ግን ተጠቃሚዎች ነን።

በሉቃስ 24፡27 ላይ እንደምናገኘው ጥሩ የጽሁፍ ትርጉም ትክክለኛ የሆነ የንግግር ፍቺን ይፈልጋል። የሄርሜኔቲክስ ዋነኛ ዓላማ ይሄ ነው፡- ትክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማሳየት የተማርነውን ትምህርት በህይወታችን ላይ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ከላይ በሉቃስ ላይ የተነበበው ክፍል እንደሚገልጽልን የሱስ ለተከታዮቹ ይህንን ማድረጉን ነው። የሱስ ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለእኛ ሲፈታልን ምን ሊመስል እንደሚችል ገምቱ! ብዙ ሰዎች የተለያዩ ትርጉሞችን የማግኘት እድል ቢኖራቸውም ብዙዎች ደግሞ ይህንን አላገኙም። የምትሰሩት ማንኛውም ትርጉም ቢኖር ቃሉን በጸሎት እና ትምህርቶቹን በመታዘዝ ፍላጎት የማጥናት አስፈላጊነት ምን ያክል ነው?

ሚያዚያ 27
May 05

መጽሐፍ ቅዱስ እና ልማድ


ሐዋ.17፡16-32ን አንብቡ። ጳውሎስ አዲስ በሆነ አውድ የወንጌልን መልዕክት በግሪካውያን የፍልስፍና ልማድ በኩል መስጠት ፈለገ። የተለያየ የድሮ ልማዶቻችን እንዴት አድርገው የተለያዩ ሃሳቦችን እንደምንመዝን በምን መልኩ ተፅዕኖ ይፈጥሩብናል?





ስለ ምስራቃውያን ልማድ ያለፈ እውነትን መያዝ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለመረዳት ያግዘናል። “ለምሳሌ በዕብራይስጥ ልማድ መሠረት አንድ ግለሰብ ድርጊቱን ባይፈጽም እንኳን እንዲከናወን ከፈቀደ ሙሉ ሀላፊቱን ይወስዳል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲያን በምእራባውያን አስተሳሰብ እንደሚባለው እርሱ ፈቀደ ወይንም ከመሆን አልተከለከለም በማለት በጋራ እግዚአብሔርን ይሞግቱታል ለምሳሌ ያክል የፈርኦን ልብ መደንደን። “Methods of Bible Study” section 4.p. ልማድ አተረጓጎም ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያነሳል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዛ ልማድ ጋር ግንኙነት ላላቸው ብቻ ገጣሚ እንዲሆን የተቃኘ ነውን? ወይንስ በአንድ በተለየ ልማድ ውስጥ የተሰጠ መለኮታዊ መልዕክት ነው? በዚሁ ልማድ ውስጥ አልፎ ለሰብአዊ ዘር በሙሉ መልዕክቱ ይደርሳል። የአንድ ልማድ ተሞክሮ ቃሉን ለመተርጎም መመዘኛና መሰረት በሚሆንበት ጊዜ ምን ይፈጥራል?

ሐዋ.17፡26 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ይሄንን ጥቅስ ሰዎች ሲያነቡ ካገኙት እውነታ አንጻር አስደናቂ የሆነ እይታውን ያስቀምጣል። እግዚአብሔር ከአንድ ደም እንደሰራን ይገልጽልናል። ልማዶቻችን የተለያዩ ቢሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ አነገጋገር ሁላችንንም ያስተሳሰረን የጋራ ነገር አለ። ያም ደግሞ እግዚአብሔር የሰብአዊ ዘር ሁሉ ፈጣሪ መሆኑ ነው። ሀጢያተኛነታችን እና ለድነት ያለን ፍላጎት በአንድ ልማድ ስር የተገደበ አይደለም። በክርስቶስ የሱስ ሞት እና ትንሳኤ የተሰጠ ድነት ለሁላችንም ያሻናል። ምንም እንኳን እግዚአብሔር በአንድ በተለየ ህዝብ ቢናገርም በዛ ውስጥ ያየው ወደፊት የሚመጣው ትውልድ የእግዚአብሔርን ቃል አንብቦ የሚያገኘው እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ ከነበረበት ወቅት እና ሁኔታ ያለፈና የተሻገረ እንደሚሆን ተረድቶ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ እስኪ አልጄብራ ስለሚባል በ9ኛው ክፍለ ዘመን ባግዳድ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተፈጠረ የሂሳብ ዘርፍ አስቡ። ይህ ማለት የዚህ የሂሳብ ክፍል እውነታዎች እና መርሆዎች ለዛ ጊዜና ስፍራ ብቻ ነው የሚጠቅሙት? በፍጹም። የእግዚአብሔር ቃል እውነትም መርህ ተመሳሳይ ነው። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ከአሁኑ በተለየ አለም ከረጅም አመታት በፊት በነበሩ ልማዶች ውስጥ የተጻፈ ቢሆንም እውነቱ መጀመሪያ ለነበሩ ሰዎች ገጣሚ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ለኛ ገጣሚ ነው።

ሚያዚያ 28
May 06

ሐጢያተኛ እና የወደቀ ተፈጥሮአችን


ዮሐ.9፡39-41 እና ዮሐ.12፡42-43 አንብቡ። በዚህ ጥቅስ ላይ ህዝቦቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መልዕክት እንዳይቀበሉ ምን አገዳቸው? ከዚህ ክስተት የምንወስደው የማስጠንቀቂያና የጥንቃቄ ቃላት ምንድናቸው?







ወደ ኋላ መለስ ብሎ አይቶ አሳማኝ ማስረጃ የነበራቸው የሱስን የተቃወሙ ሃይማኖታዊ መሪዎችን መናቅ ለኛ ቀላል ነገር ነው። ቃሉን በተመለከተ ተመሳሳይ አመለካከት እንዳይኖን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሐጢያት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በመቀየር ማበላሸቱ እና ማፈራረሱ ምንም ጥያቄ የለውም። ሀጢያት የሰብአዊ ዘር ህልውና ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። የሰዎች አስተሳሰብ ሂደቶች በቀላሉ ወደ ሀጢያት የቀረበ ስለሆነ ሳይሆን አስተሳሰባችንና አዕምሮአችን በሀጢያት ስለተበከለ ለእግዚአብሔር እውነት የተዘጋ በመሆኑ ነው። ከዚህ የተበላሸ አስተሳሰብ የመነጩ የሚከተሉት ባርያቶች ይገኙበታል። ኩራት፣ ራስን ማታለል፣ ጥርጣሬ፣ ርቆ መገኘት እና አለመታዘዝ። ኩራተኛ የሆነ ሰው ራሱን/ራስዋን ከእግዚአብሔር እና ከቃሉ በላይ ከፍ ያደርጋል / ታደርጋለች። የዚህ ምክንያቱ ኩራት ተርጓሚው በሰው ልጆች ምክንያታዊነት ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት እንዲያደደርግ ስለሚገፋፋው የመጨረሻውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲተው ያደርገዋል። ይህ ባህሪ ደግሞ በቃሉ ላይ ያለውን የመለኮት ስልጣን የሚያሳንስ ነው።

አንዳንድ ሰዎች ነገሩ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚቃረን ቢሆንም መስማት የሚፈልጉት ለነርሱ ማራኪ ሆኖ የሚሰማቸውን ብቻ ነው። እግዚአብሔር ራስን ስለማታለል አደገኝት አስጠንቅቆናል (ራዕ.3፡17)። ሀጢያት የእግዚአብሔርን ቃል ወደ ማመን እንዳናዘነብል በማድረግ ጥርጣሬን ያበረታታል። አንድ ሰው በጥርጣሬ ከጀመረ የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ንግግር ወደ እርግጠኝነት አይመራውም። በዚህ ፈንታ ይህ ተጠራጣሪ ሰው በፍጥነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚቀበላቸውንና የማይቀበላቸውን ነገሮች መፈረጅ በሚችልበት ስፍራ ላይ ራሱን ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ መሬት ላይ መቆም ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን በትችትና ጥርጣሬ አቀራረብ ከመቅረብ ይልቅ በእምነትና ራስን በማስረከብ አመለካከት መቅረብ አለብን። ኩራት፣ ራስን ማታለል እና ጥርጣሬ ከእግዚአብሔርና ከቃሉ የራቀ ልብ እንዲኖረን ሲያደርግ ይህም ወዳለመታዘዝና ለተገለፀው የእግዚአብሔር ፈቃድ ፈቃደኛ እንዳንሆን ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብነው ግልጽ የሆነ ቃል አንድ ነገር እንድናደርግ ሲያዘን እኛ ተቃራኒውን ለማድረግ ስንሻ ባለው የሃሳብ ትግል ውስጥ ራስዎን አግኝተውት ያውቃሉ? ከዛ ምን ሆነ፣ ከዚህ የህይወት ልምምድስ ምን ተማሩ?

ሚያዚያ 29
May 07

የንግግር ፍቺ ለምን አስፈላጊ ሆነ


ነህ.8፡1-3፣ 8ን አንብቡ። እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተክርስቲያን ቃሉን በግልጽ ማስተዋል አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?





በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው ወሳኙ ጥያቄ የድነት ጥያቄ እና እንዴት እንደዳንን ነው። ወደፊትስ ቢሆን ከዚህ ሌላ የሚያስፈልገው ነገር ምንድነው? የሱስ ራሱ እንደነገረን ሰው አለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? (ማቴ.16፡26) ። ስለ ድነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ትምህርት የተመሰረተው ትርጉም ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በስህተት ከተረጎምነው ድነትን ማስተዋል አይደለም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ማንኛውም ነገር ላይ ወደ ስህተት ድምዳሜ እንድንደርስ ያደርገናል። በሐዋርያት ጊዜ እንኳን ስነ መለኮታዊ የሆኑ ስህተቶች ቀድመው የገቡት ቃሉን በስህተት በመተርጎማቸው እንደነበረ ጥርጥር የለውም። 2ጴጥ.3፡15-16ን አንብቡ። ትክክለኛው የቃሉ አነባበብ ምን መምሰል እንዳለበት ምን ይነገረናል?





በርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መኖር የምንሻ የመጽሐፉ ሰዎች ከሆንን እንደ ባህል፣ የተለያዩ እምነቶች ወይንም የቤተክርስቲያን የመተርጎምና የማስተማር ስልጣናት በሙሉ እንደመነሻ ገዢ ሃይል ሆነው ሊቆጠሩ አይገባም። ስለዚህ ትክክኛ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ሄርሜኔቲክስ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ምን ማመን እንዳለብን እና እንዴት መኖር እንደሚገባን የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነውና።

የቃሉ አተረጓጎም ጉዳይ ለስነመለኮታዊው እና ቤተክርስቲያን ለያዘችው ተልእኮ ጤነኝነት በጣም ወሳኝ ነው። ያለ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም በአስተምህሮና በትምህርቶች መካከል አንድነት አይመጣም። ያም በቤተክርስቲያናችን እና ተልዕኮአችን ላይ አንድነትን አይፈጥርንም። መጥፎ እና የተበላሸ የስነ መለኮት ትምህርት ወደ ጎዶሎ እና የተዛባ ተልዕኮ መምራቱ አያጠራጥርም። ለአለም የምንሰጠው መልዕክት ኖሮን ነገር ግን የመልዕክቱ ትርጉም ግራ የሚያጋባ ቢሆን እንዴት አድርገን ነው ታዲያ ይህንን መስማት ለሚፈልጉ ሰዎች መልእክታችንን ማቅረብ የምንችለው።

የሶስቱን መላዕከት መልዕክት ከራዕይ 14፡6-12 ላይ አንብቡ። እዚህ ጋ ያለው የስነመለኮት ሃሳብ ምንድነው? ይህንን በትክክል መረዳት ለተልዕኮአችን አስፈላጊ የሆነው እንዴት ነው?

ሚያዚያ 30
May 08


ተጨማሪ ሐሳብ


የኤሌን ጂ ኃይት ፅሁፎችን አንብቡ `What to do with Doubt` pp. 105-113, in steps to chirst, and from the document `methods of bible study` section 1: `Bible study: pre suppostitions, principles, and methods`, section 2: `pre supposititons arising from the claims of scripture` and section 3 `prinicples for approaching the interpretation of scripture` (methods of bible study can be found at www.adventistbibleresearch.org/materials/bible-interpretaiton-hermeneutics/methods-bible-study). “በቃሉ ጥናታችን ወቅት ቀድሞ የነበራችሁን አስተሳሰብ እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ሀሳብ በመመርመሪያ ክፍል በር ላይ ጣል አድርጉት። የራሳችሁን አስተሳሰብ ለማጽደቅ ቃሉን የምታነቡ ከሆነ ወደ እውነቱ አትደርሱም። ይህንን ሀሳብ በዛ በር ላይ ጣል አድርጉና ፀፀት በተሞላበት ልብ ጌታ ለእናንተ ምን እያላችሁ እንዳለ ስሙት። እውነትን በትህትና እንደሚፈልግ ሰው በክርስቶስ እግር ስር ተቀምጣችሁ ተማሩ። ቃሉም ማስተዋልን ይሰጣችኋል። በራሳቸው እሳቤ ጠቢብ ሆነው ቃሉን ለማጥናት ለሚቀርቡ ሰዎች ክርስቶስ ሲናገር በድነት ጉዳይ ላይ ብልህ መሆን ካሻችሁ ቅንና ዝቅ ያለ ልብ ያስፈልጋችኋል ይላቸዋል።

“ቀድሞ በነበራችሁ አስተሳሰብ ቃሉን አታንብቡ። ነገር ግን ከመፈረጅ ነጸ በሆነ አዕምሮ ቃሉን በጥንቃቄ በጸሎት መርምሩ።በምታነቡበት ጊዜ አንድ የእምነት አስተሳሰብ ብቅ ሲልብዎ እና የእናንተ አስተሳሰብ ከቃሉ ጋር የማይጣጣም ሆኖ ሲገኝ ቃሉ ከእርስዎ አስተሳሰብ ጋር ገጣሚ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አታድርጉ። በቀደመው ህይወትዎ ያመኑትና ተግባራዊ ያደረጉት ነገር ማስተዋልዎን እንዲቆጣጠር አይፍቀዱለት። ከህጉ ላይ ድንቅ ነገር ማየት ይችሉ ዘንድ የልቦናዎን አይን ይክፈቱ። የተፃፈውን ነገር አግኙና ዘላለማዊ በሆነው አለት ላይ እግሮችዎ ይተከሉ።” Ellen G. white, messages to young people, p. 260.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ስለ አለም ያለን እይታ፣ ትምህርታችንና ልማዶች ቃሉን በምንተረጉም ጊዜ ተጽዕኖ የሚሳድሩብን እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስንተረጉም ያለ ጥርጥር ከውጪ ተፅዕኖ ሊፈጥሩብን የሚችሉ ነገሮችን በደንብ አድርጎ የመገንዘብ አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?

2.ሁላችንም የምንስማማው ሀጢያተኞች እና በሀጢያት ተጠቂዎች መሆናችንን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ላይ ሀጢያት ያመጣብን ተጽዕኖ ምንድው? የእግዚአብሔርን ቃል በስህተት እንድንተረጉም ሀጢያት መንስኤ የሚሆነው በምን ሁኔታ ነው? ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ የኮነነውን ድርጊት ማድረግ ስንፈልግ መጽሐፍ ቅዱስን አጣመን እንድንተረጉም መንስኤ የሚሆነን እንዴት ነው?

3.መጽሐፍ ቅዱስ የተፃፈበትን ጊዜና ልማድ የበለጠ መረዳት አንዳንድ ጥቅሶችን የበለጠ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀሱ።