መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንተርጉም
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2020

ሚያዝያ 17 - ሚያዝያ 23

5ኛ ትምህርት

Apr 25 - May 01




መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ



ሰንበት ከሰዓት

የሚከተሉትን ጥቅሶች ለዚህ ሳምንት ጥናት አንብቡ፡- 1ቆሮ.4፡1-6፤ ቲቶ.1፡9፤ 2ጢሞ.1፡13፤ ማር.12፡10፣ 26 ሉቃስ 24፡27፣ 44፣ 45፤ ኢሳ.8፡20።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “የእግዚአብሔር ቃል ህያውና የሚሰራ ነውና፣ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሀሳብና ምኞት ይመረምራል።” (ዕብ.4፡12)።

“መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” (sola scripture) የሚለው የፕሮቴስታንቶች ጥያቄን ስንመለከት አስተምህሮው ብቸኛው መመዘኛና ወሳኙ መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ ከፍ እንዲል ያደርገዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ እና ባህል ላይ አፅንኦት ከምትሰጠው ከሮማ ካቶሊክ በተቃራኒ የፕሮቴስታንት እምነት “ብቻ” የሚለው ወሳኝ ቃል ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ። ይህም ማለት እምነት እና አስተምህሮን በተመለከተ የመጨረሻው ስልጣን የሚያርፈው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ላይ ነው። ለምዕተ ዓመታት ሮም ስታስተምረው የነበረውን የተሳሳተ ትምህርት በመቃወም የተነሳው አብዮትና የፕሮቴስታንቶች ተሃድሶ ወሳኙ ሀይልና ስልጣን የተቀዳው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ ንግግር ፍቺ በተቃራኒ የተለያየ ትርጓሜ ያላቸው ጥቅሶችን በማንበብ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ንቅናቄ መሪዎች ሰዋሰዋዊ የቋንቋ ይዞታቸው እና የመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ ፍቺያቸው ላይ ትኩረት አድርገዋል ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ሰዋሰዋዊ ይዘት እና የቃል በቃል ትርጓሜያቸውን መሠረት ያደረገ ነው።

በዚህ ሳምንት መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለውን ሃሳብ በዝርዝር እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር የመጽሐፍ ቅዱስ ፍቺ አንዳንድ መሠረታዊ መርሆች የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ለመረዳት የማይሻሩ መርሆች ናቸው። እንደ ፕሮቴስታንቶች ሁሉ እኛም መጽሐፍ ቅዱስ በአስተምሮአችን ላይ የመጨረሻው ባለስልጣን አድርገን መጠበቅ ይገባናል። የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለሚያዝያ 3 ሰንበት ተዘጋጁ።

ሚያዚያ 18
Apr 26

መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መሪ የማህበረሰብ ልማድ


ከጅማሬው አንስቶ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ራሳቸውን የሚቆጥሩት የመጽሐፉ ሰዎች አድርገው ነው። ይህም ማለት መጽሀፍ ቅዱስን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ መርህ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ለሚለው ሀሳብ የመጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ስልጣን እንረዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የስነ መለኮት አስተምሮአችን እና ህይወታችን ላይ የመጨራሻውን የገዢነት ስልጣን የሚወስደው። ሌሎች ምንጮች ለምሳሌ የሃይማኖት ልምምድ፣ የሰዎች ምክንያታዊነት ወይንም ባህል ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ስፍራን የሚሰጡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለው መርህ አላማው የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን በቤተክርስቲያን እና አተረጓጎምዋ ላይ ጥገኛ በመሆን ትርጓሜው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመዘኛ ውጪ እንዳይሆን ከለላ መሆን ነው። 1ቆሮ.4፡1-6ን አንብቡ። በተለይ ቁጥር 6 ላይ ጳውሎስ እንደተናገረው “ከተፃፈው አትለፍ” ይለናል። ይህ ለእምነታችን ያለው አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?





ከተፃፈው አለማለፍ የተባለው ሃሳብ ከተለያዩ የትምህርት መስኮች ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው የመሬት ቁፋሮ ጥናት መረዳት ውጪ እንድንሆን አይመክረንም። የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እይታችን ላይ የጥቅሱን የታሪክ ዳራ በመስጠት መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ እንድንረዳ ብርሃን ያፈነጥቁልናል። በትርጉም ስራችን ውስጥም ሌሎች ምንጮችን ለምሳሌ መዛግብት፣ መዝገበ ቃላት፣ ማጣቀሻ ፅኁፎችንና የማብራሪያ ጽሁፎችን መተው አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ፍቺ ጥቅሱ ራሱ ከሌሎች ነገሮች፣ ከሳይንስ እና ሁለተኛ አጋዥ ምንጮች ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ሌሎች የእይታ ሃሳቦች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እየተነሱ መፈተሸ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለውን መርህ በአዎንታዊነት ስናረጋግጥ ስለ እምነታችን ፍቺ ለመስጠት ግጭት ሲነሳ ያኔ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የቤተክርስቲያን ባህሎችን ሁሉ አልፎ ብያኔን የሚሰጠው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተፃፈው አልፈን ወይም ተቃርነን መሄድ አይገባንም። እውነተኛ ክርስቲያንነት እና አሳማኝ የወንጌል ስብከት የተመሰረተው በማይነቃነቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን ላይ ነው። “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው በምድር ላይ የሚገኙ ጽሑፎች እና አስተምህሮችን የሚገዛ እውነተኛ ጌታ `Martin Luther, Luther’s works, Vol. 32: Career of the Reformer II, ed. Jarslav Jan Pelikan, Hilton C. Osawald and Helmut T. Lehmann, vol. 32 Philadelphia: fortress Press, 1999), pp.11, 12. ሐዋ. 17፡10-11በን አንብቡ። እዚህ ጋር እያወራን ያለነው የመጽሐፍ ቅዱስን ቀዳሚነት ስለመሆኑ ይህ ጥቅስ ምን ይነግረናል?

ሚያዚያ 19
Apr 27

የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት


መጽሐፍ ቅዱስ ስለራሱ የሚነግረን “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” ብሎ ነው (2ጢሞ.3፡16)። “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና” እነዚህ ሰዎች “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” (2ጴጥ. 1፡20-21)። የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ እግዚአብሔር ከሆነ የተለያዩ ወሳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ በምንማረው ትምህርት ጥቅሶች ውስጥ መሰረታዊ የሆነ አንድነትና መጣጣም እንዳለ እንረዳለን። ቲቶ 1፡9 እና 2ጢሞ. 1፡13ን አንብቡ። ለእምነታችን የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ የመሆን አስፈላጊነት ምን ያህል ነው?





ከመለኮታዊ ትርጓሜ በፈለቀው መሠረት አንድነት እና ውስጥ ለውስጥ ባለው ህብረት ብቻ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የራሱ ተርጓሚ የሆነው። መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮው ላይ ትክክለኛ አንድነት ከሌለው ሌሎች ማናቸውም ጉዳዮች ላይ የአስተምህሮ መጣጣም ማየት አንችልም። ያለ መጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ቤተክርስቲያን እውነትን ከውሸት ለይታ ልትቃወም አትችልም። የዲሰፕሊን እርምጃ ለመውሰድና ከእግዚአብሔር ቃል ያፈነገጠውን ሃሳብ ለማረም መሰረት ታጣለች። መጽሐፍ ቅዱስም የማሳመንና ነፃ የማውጣት ሀይሉን ያጣል። የሱስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲያን የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ምንጩ መለኮት እንደሆነ ይረዳሉ። ይህንን የምናየው አያሌ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን በተመጣጠነና በተጣጣመ ደረጃ የመጥቀስ የጋራ ልምምድ ስለነበራቸው ነው። (ሮሜ.3፡10-18፤ እዚህ ጋር ጳውሎስ ከመክ.7፡20፤ መዝ.14፡2-3፤ 5፡9፤ 10፡7 እና ኢሳ.59፡7-8 የሚገኙ ጥቅሶችን ጠቅሶ እናያለን)።

የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት የሚያመለክተን ነገር ቢኖር የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ስናጠና ትምህርታችንን አንዲት የጥቅስ ሃሳብ ላይ ከመመስረት ይልቅ ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለብን። መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የሚቃረኑ የሚመስሉ ጥቅሶችና ሃሳቦችን ስናገኝ ምን ማድረግ አለብን? ምላሽ ለማግኘት ምን እንስራ?

ሚያዚያ 20
Apr 28

የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መሆን


የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትርጉም ግልጽ በማይሆንበት ጊዜ ጥቅሱ ላይ ብቻ ጥያቄ ማንሳት በተወሰነ ደረጃ ተገቢነት አለው፡ ማቴ.21፡42፤ ማቴ.12፡3፣ 5፤ ማቴ.19፡4፤ ማቴ.22፡31፤ ማር.12፡ 10፣ 26፤ ሉቃስ 6፡3፤ ማቴ.24፡15 እና ማር.13፡24ን አንብቡ። የሱስ በተደጋጋሚ ጥቅሶችን በመጥቀስ ስለመልዕክቶቹ ግልጽነት ምን አለ?







የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት የማያሻማ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ነገር በበቂ ሁኔታ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ መሰረታዊ አስተምህሮው በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ህጻናትና አዋቂዎች ያስተውሉታል። እንደውም እውቀታችንንና ማስተዋላችንን በጥልቀት በማሳደግ የማያልቅ እድሎችን ይሰጠናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜን የሚነግረን ሌላ ካህን አያሻንም። ከዚህ ይልቅ መሰረታዊ ትምህርቶቹ በሁሉም ምዕመናን ዘንድ ሊስተዋሉ የሚችሉ ናቸው። ትርጓሜውን ለጥቂት ሰዎች ለምሳሌ ለቀሳውስት ከመተው ይልቅ ሁሉም ምዕመን ካህን ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለራሳችን ልናጠና ይገባናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔርን መልዕክት ለራሳችን መረዳት ይቻለናልና።

ተገቢ በሆነ ሁኔታ እንዲህ ተገልጿል። “የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲያን ባልተቋረጠ ደረጃ በገለጹልን ምሳሌ እንዳሳዩን ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል የሰጠንን ትርጉም በቀላሉ መውሰድ ይገባል። ግልጽ የሆነውን እይታ እስካላየን ድረስ ያልተገለፀውን፣ ስውር እና የተለየ መልዕክት ልናስተውል የምንችለው ቃል በቃል ግልጽ የሆነውን ሀሳብ ከተረዳን በኋላ ነው” Hand book of seventh day Adventist Theology (Hagerist own, MD: Preview and Herald Publishing Association, 2000) p.65። ከመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋና ግልጽ ቃላት ባለፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲያን የጽሁፋቸው አላማ እውነቱ ላይ እንጂ ከግል ስሜታችን ጋር በተያያዘ ከምንሰጠው ዘርፈ ብዙና መቆጣጠር ከምንችለው በላይ ካለው ትርጉም ያለፈ መሆን አለበት።

ይህ ማለት ግን ሙሉ በሙሉ የማናስተውላቸውና የማንረዳቸው ጥቅሶች ወይም ሃሳቦች የሉም ማለት አይደለም። ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው እኛ ደግሞ የወደቅን ሰብአዊ ዘር ነን። ያም ቢሆን ግን የእግዚአብሔር ቃል በተለይ ከድነት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መረዳት የሚገባንን ለማሳወቅ በበቂ ሁኔታ ግልጽ ሆኖ ተቀምጦልናል። አንዳንድ ጥቅሶችን ለመረዳት በተቸገራችሁ ጊዜ ቆየት ብላችሁ እንደምትረዱት ያሰባችሁበትን ወቅት አስቡ። በተመሳሳይ ተግዳሮት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎችን የሚያግዝ ከሕይወትዎ ልምምድ የተማሩትን ምን ነገር አለ?

ሚያዚያ 21
Apr 29

መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲፈታ


የማያወላዳ የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ስላለ ብቻ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ የሚፈታው። ያለዚህ አንድነት መጽሐፍ ቅዱስ የራሱን ትርጉም አብርቶ የሚያሳይ አይሆንም። የመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ሌላኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይፈታል ይህም ተያያዥነት ያላቸውን ክፍሎች ለመረዳት ቁልፉ ነገር ነው። ሉቃስ 24፡27፣ 44፣ 45ን አንብቡ። የሱስ እርሱ ማን እንደሆነ ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስን መለስ ብሎ የጠቀሰው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ከዚህ ምን እንማራለን?





መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም የማድረጉ ውበት ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቅ ትርጉም ማግኘታችን ነው። ይህን በማድረጋችን የራሳችንን ሃሳብ ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥቅሶችን በአንድነት በማምጣት ማጥናት አይገባንም። ይልቁንም ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ እያንዳንዱን ጥቅስ ማየት አለብን። ከጥቅሱ በፊትና በኋላ ያሉትን ጉዳዮች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከመመርመራችን ባለፈ የመጽሐፉ የጥቅስ አውድ የተገኘበት ሁኔታን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለብን። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በቃሉ እንደተናገረው “አስቀድሞ የተፃፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” (ሮሜ.15፡ 4)። በተገለፀው ነገር ላይ ቃሉ የሚነግረንን ነገር ማጥናት አለብን።

“መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ ይገልጻል። ቃሉ ከቃሉ ጋር መነፃፀር አለበት። ተማሪዎች ቃሉን በሙላት ለመረዳት የተለያዩ የቃሉ ክፍሎች ያላቸውን መስተጋብር ማየት አለባቸው። አንድ ሰው የእውቀቶች ሁሉ ማዕከላዊ የሆነውን ፍሬ ሃሳብ ማለትም እግዚአብሔር አስቀድሞ በዚህች አለም ላይ ታላቁ ተጋድሎ ሲነሳ ያዘጋጀውን የድነት ሥራ እቅድ እውቀት ማግኘት አለበት።” Ellen G. white, Educaiton, p.190. ቃሉን ከሌላኛው የቃሉ ክፍል ጋር ስናነፃፅር መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናታችን ተገቢ ነው። ከተቻለ የመጽሐፍ ቅዱስ መነሻ ቋንቋ የሆኑትን ዕብራይስጥ ግሪክን ከትክክለኛ የመጽሀፍ ቅዱስ ትርጉም ጋር ማጥናት አለብን። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ የተፃፈበትን የመነሻ ቋንቋ ማወቅ የግድ አስፈላጊ ነው ባይባልም ከተቻለ ግን በእርግጠኝነት ትልቅ እገዛ ያደርግልናል። ካልሆነም ቃሉን በታማኝነት እና በፀሎት በትህትና እና የመሰጠት አመለካከት ማጥናት ታላቅ ፍሬን እንድናፈራ ያስችለናል።

ስለ አስተምሮአችን አስቡ ለምሳሌ ስለ ሙታን ሁኔታ፤ ጥቂት የተመረጡ ጥቅሶች ላይ ትኩረታችንን ስናደርግና ሌሎች ጥቅሶችን ስንተው ወደ ስህተት ይመራናል። መጽሀፍ ቅዱስ ስለ አንድ ርዕስ የሚያስተምረንን ነገር በትክክል በመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ስለዛ ርዕስ የሚነግረንን ጥቅሶች በሙሉ የማንበብ አስፈላጊነትን እንዴት ያስተምረናል?

ሚያዚያ 22
Apr 30

መጽሐፍ ቅዱስ እና ኤለን ጂ ኋይት


ኢሳ.8፡20ን አንብቡ። ትምህርቶቻችንና አስተምህሮዎቻችንን ለመረዳት ሁልጊዜ ወደ መጽሐፍ ቅዱሳችን ተመልሰን “ህግና ምስክርን” የማየት ልማድ አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላልተካተቱ የትንቢት አገልጋዮችስ ምን አይነት ትርጉም አለው?





መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለውን ሃሳብ ይዘን ስንጓዝ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሚጋፈጡት መሰረታዊ ጥያቄ ቢኖር በእግዚአብሔር ተመርታ ለቅሬታዋ ቤተክርስቲያ መልዕክት ለማስተላለፍ የተጠቀመባት ኤለን ኋይትስ የሚለው ጥያቄ ነው። ጽሁፎችዋ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያላቸው ግንኙነትስ ምን ይመስላል? በወፍ በረር ንባብ የኤለን ኋይትን ጽሑፎች ስናነብ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የሚያሳየን ነገር ቢኖር የሃሳቦችዋ ዋና ትምህርቶች መሰረትና ማዕከል መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ነው። እንደውም በተደጋጋሚ አስረግጣ እንደተናገረችው መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም አስተምህሮዎችዋ እምነትና ተግባራት ሁሉ ታላቁ ባለስልጣን እና ልንከተለው የሚገባ የመጨረሻው ልምዳችን ነው (Great controversy p. 595 ን ተመልከቱ) ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለውን የፕሮቴስታንቶች ሃሳብ በግልጽ ትደግፋለች። (Great controversy p. 9) ።

በኤለን ጂ ኋይት እይታ ጽሑፎችዋ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሲነፃፀር “ወንዶችና ሴቶችን ወደ ትልቁ ብርሃን የሚመራ ትንሹ ብርሃን ነው” ትላለች። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመራ ብርሃን (The Advent Review and Sabbath Herald, January 20, 1903) ። ጽኁፎችዋ አቋራጭ ሆነው ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ጥናት ተክተው አያገለግሉም። ሃሳብ የምትሰጠውም “የእግዚአብሔርን ቃል አላስተዋላችሁም። የእግዚአብሔርን ቃል ስታጠኑ ሳለ የመጽሐፍ ቅዱስ መለኪያ ጫፍ ላይ ለመድረስና የክርስትናን ፍጽምና ለማግኘት ከልብ ለመሻት ቢሆን ኖሮ እነዚህ ምክሮች ባላስፈለጉ ነበር። በሚያነቃቃው ቃሉ በኩል በቀላሉ እና ቀጥተኛ በሆነ ምክሩ የመጣልንን ቃል ለመተዋወቅ ችላ ስላልን ነው ይህ የሆነው። Ellen G. white, Testimonies for the church. Vol. 2, p.605.

ጽሁፎችዋ ሊደነቁ ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲያን የሚያነቃቁበትን የተመሳሳይ መነቃቃት ሂደት ቢጋራም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተግባር የሚለየው ነገር አለው። ጽሑፎችዋ ለእግዚአብሔር ቃል ተጨማሪ ሆነው የቀረቡ አይደሉም። እንደ ቅዱስ ጽሑፍ ግን ይታያሉ። ጽሑፎችዋ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲተኩ አትሻም ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት እና ተግባሮቻችን ብቸኛው መመዘኛችን እንደሆነ በመግለጽ ቃሉን ከፍ ታደርጋለች። በኤለን ጂ ኃይት አገልግሎት በኩል ስለተሰጠን አስደናቂ ስጦታ እስቲ አስቡ። የእግዚአብሔርን ቃል ልዕልና በመጠበቅ ከእርሷ ጽሑፍ የምንማረውን አስደናቂ ብርሃን ትልቅ ቦታ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

ሚያዚያ 23
May 01


ተጨማሪ ሐሳብ


Hand book of seventh day Aeventist theology ከሚለው መጽሐፍ ላይ ስለመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም በሚናገረው ምዕራፍ የእግዚአብሔርን ቃል ማመሳሰል በሚለው ክፍል ውስጥ “የእግዚአብሔር ቃል የራሱ ተርጓሚ ነው” የሚለውን ሀሳብ የጥቅሶቹ ተያያዥነት እና ቀጣይነት ስለቃሉ ግልጽነት ደግሞ ገጽ 64-66 ላይ ያንብቡ። “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና ጥናት” በሚል ርዕስ ምዕራፍ 20 ላይ የተገለፁት ሃሳብ ገጽ 185-192 ድረስ እንዲሁም የተመረጡ መልዕክቶች መጽሐፍ 3 ገጽ 29-33 ላይ “ስለቃሉ ቀዳሚነት” የተነገረውን አንብቡ።

“የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በተማሪነት መንፈስ እንዲቀርቡ ይመከራሉ። ገጾቹን የምንመረምረው የራሳችንን ሃሳብ ለማጠናከር ሳይሆን እግዚአብሔር የሚለውን ለማወቅ ነው። እውነተኛ የቃል እውቀት ሊገኝ የሚችለው ቃሉን ራሱን በሰጠው መንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ብቻ ነው። ይህን እውቀት ለማግኘት በቃሉ ልንኖር ይገባናል። የእግዚአብሔር ቃል የሚያዘንን በሙሉ መታዘዝ አለብን…የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የእኛን ጠንካራ ትጋትና ፅኑ አስተሳሰቦችን ይፈልጋል። ማዕድን ቆፋሪው የወርቅ ሀብትን ለማግኘት በጉጉት እና በፅናት እንደሚቆፍር ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል መዝገብንም እንዲሁ ልንፈልግ ይገባል።” Ellen G. White, Educaiton, p. 189.

“መጽሐፍ ቅዱስን ምግባችሁ፣ ስጋችሁ እና መጠጣችሁ ስታደርጉ፤ መርሆቹ ደግሞ የባህሪዎቻችሁ ግብአት ሲሆኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሻለ ሁኔታ እንዴት አድርጋችሁ ምክር መቀበል እንዳለባችሁ ትረዳላችሁ። ዛሬ የከበረውን ይህን ቃል በፊታችሁ ከፍ አደርጋለሁ። እኔ ያልኩትን እየደጋገማችሁ “እህታችን ኋይት ይህን ብላለች” “እህታችን ኋይት ያንን ብላለች” አትበሉ። የእስራኤል አምላክ የነገራችሁን አግኙ የሚያዛችሁንም ፈፅሙ” Ellen G. white, Selected messages, book 3, p. 33::


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ስለ አንድ ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸውን ጥቅሶች ሙሉ በሙሉ ከመውሰድ ይልቅ ጥቂት ጥቅሶችን በመውሰድ ሰዎች እንዴት ነው የስህተት እምነትን የሚገነቡት?

2.ማቴ.11፡11 ላይ የሱስ ስለመጥመቁ ዮሐንስ ሲናገር “እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥመቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም በመንግስተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም ስላልጻፈው ነብይ ነው የሱስ ይህንን የተናገረው። እውነተኛ ነብያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፍ ባይኖራቸው እንኳን እውነተኛ ነብይ ስለመሆናቸው ይህ ምን ይነግረናል? ከዚህ እውነታ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ሊወስዱት የሚገባው መልዕክት ምንድነው?

3.እንደ አድቬንቲስትነታችን መጽሐፍ ቅዱስን የመጨረሻ ባለስልጣን መጽሐፍ አድርገን በመያዛችን ብቻችንን አይደለንም። ሌሎች ቤተክርስቲያኖችም ይህንኑ ያደርጋሉ። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ሌሎች ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል ያሉትን የሚቃረኑ አስተምህሮዎችን በመተንተን ልንገልጽላቸው የምንችለው?