“ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ…”
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከመስከረም 3-9

12ኛ ትምህርት

Sep 14 - Sep 20




ምህረትን መውደድ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 6:25– 33፣ ያዕ. 1:5–8፣ 2:15-16፣ ኢሳ. 52:7፣ 1ዮሐ. 3:16–18፣ ኢሳ. 58:1–10፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ:- “ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል፡፡ ለጋስና ያለ ማንገራገር የሚያበድር፣ ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል” (መዝ. 112፡ 4-5)፡፡

መ ጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለ ደኻውና የተጨቆነው ምን ያህል እንደሚቆረቆር--ሕዝቡም ስለ እነዚህ ሰብዓዊ ወገኖች እንዲሠራ የቀረቡለትን ጥሪዎች በሚያሳዩ ጥልቅ ስሜት ባላቸው መግለጫዎች የተሞላ መሆኑን ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ሲሰጥና ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አደራ አልፎ አልፎ ፍጻሜ ሲያገኝ ቢስተዋልም፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ፍጻሜ የሚያገኘው ከየሱስ ዳግም ምጽአት በኋላ ገቢራዊ በሚሆኑ ታላላቅ ክስተቶች ይሆናል፡፡

እስከዚያው ግን ክፉው ከጨለማው የዲያብሎስና መላእክቱ ተጽእኖ በሚያገኘው ጉልበት እየታገዘ በብዙ ቅርጽና መጠን መታየቱን ይቀጥላል፡፡ ይህ ክፉ አዘውትሮ የሚገለጥባቸው መንገዶች ድኽነት፣ ብጥብጥ፣ ጭቆና፣ ባርነት፣ ብዝበዛ፣ ራስ ወዳድነትና ስስት ናቸው፡፡ የቱንም ያህል ዋጋ ሊያስከፍል ቢችልም--ማኅበረሰባችን፣ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ቤተሰባችን ከእነዚህ የክፉ ተግባራት በተቃራኒ ሊቆሙ ይገባል፡፡

ለእግዚአብሔር ፍቅርና ትእዛዞች በምንሰጠው ምላሽ፣ በየሱስ አገልግሎትና የመሥዋዕትነት ብርሃን በምናደርገው መመላለስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሞላታችንና ምሪት ማግኘታችን--ፍትሕን እናደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም እንወድድ ዘንድ፣ በአምላካችን ፊት በትህትና መራመድን (ሚልክ. 6፡8) አጥብቀን በመሻት ሩኅሩኅዎች፣ ብልህዎችና ጀግኖች ልንሆን ይገባል፡፡

መስከረም 4
Sep 15

የሰማያዊው መንግሥት ቅድሚያዎች


በየሱስ አስተምህሮና በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ግልጽ ሆኖ እንደቀረበው የእግዚአብሔር መንግሥት አባል ሆነው ለመኖር የሚመርጡ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ዓለም ቅድሚያ ከምትሰጣቸው በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 6፡25-33፡፡ በጥቅሶቹ የተሰጠን መጽናኛ ምንድን ነው? ይህ መጽናኛ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ላይ እንዴት ተጽእኖ ማሳደር ይችላል?



የሱስ “ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?” በማለት በማቴ. 6፡ 25 ይናገራል፡፡ የእነዚህ ነገሮች አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ባይገባም፤ በአምላካዊው መንግሥት ብርሃን ልናያቸው ግን የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ህይወታችንን በተጨባጭ ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ ሌሎችን ስንረዳና ስናግዝ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ለቀረቡት ጥሪዎች እውቅና እንሰጣለን፡፡ የየሱስን ፈለግ ለመከተል ያለንን መሻት ስናሳይ ይህ ጥሪ ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ጥሪ በራሳችን ጉዳዮች ዙሪያ በጥቂቱ--ሌሎች ላይ ግን የላቀ ትኩረት እንድናደርግ ሊረዳን ይገባል፡፡

ይህ ለየትኛው ቅድሚያ መስጠት እንዳለብንና እንደሌለብን እገዛ የሚያደርግልን ትክክለኛ አስተሳሰባዊ አወቃቀር ከምድራዊ አለቆቻችንና ከተጨቆኑ ጋር ያለንን ግንኙነት ይቀይራል፡፡ ክርስቲያኖች በተቻላቸው መጠን መንግሥታዊ አካላትን እንዲያከብሩና እንዲታዘዙ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምር ሁሉ (ሮሜ. 13፡ 1-7) “ከሰው ሁሉ ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል” (ሐዋ. 5፡29) ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ የጻፈልንን የምናስተጋባበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም መዘንጋት የለብንም።

አንዳንዶች የሱስን በተንኮል ለማጥመድ በጠየቁት ጊዜ የሰጣቸው መልስ እነዚህን ሁለት መርኅዎች በሚዛናዊነት ያስቀመጠ ነበር “‘የቄሳርን ለቄሳር፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ’” (ማቴ. 22፡21)፡፡ የመንግሥት ይሁን ወይም ከዚያ ውጪ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች እያስፈራሩ ወይም ኃይል እየተጠቀሙ የበላይነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ፡፡ ክፉው ለተጋረጠበት ሁኔታ በታማኝነት ለመመላለስ ሁል ጊዜና በማንኛውም ሁኔታ ታዛዥ መሆን እንደማይጠበቅብን ከየሱስ ህይወት መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ስለነበረው የባሪያ አሳዳሪ ሥርዓት ኤለን ጂ. ኋይት የሚከተለውን ጽፋለች፡ “የሰው ሕጎች ከአምላካዊው ቃል እና ሕግ ጋር ሲጣረሱ ውጤቱ የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችል የአምላክን ቃል መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ ባሪያን ለባለቤቱ እንድንሰጥ የሚጠይቀንን የምድራችንን ሕግ የማንታዘዝ ከሆነ ይህን ሕግ በመጣሳችን የሚመጣውን መዘዝ መቀበል የግድ ይሆናል፡፡

ባሪያ የማንም ሰው የግል ንብረት አይደለም፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር ባለመብት ጌታ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው የባለ-እጁን ንብረት እንደ ራሱ መቁጠር አይችልም፡፡”—Testimonies for the Church, vol. 1, pp. 201, 202. ለባለሥልጣኖች በመታዘዝ እና በጨቋኝ ሥልጣን ሰለባ ሊሆኑ በሚችሉ ወገኖች በመቆም መሀል ያለው ቀጭን መስመር መገኛው የት ላይ ነው?

መስከረም 5
Sep 16

በርኅራኄ መዛል


ስለዚህ ዓለም መጨነቃችንን ተቋቁመን በሥቃይ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ህይወት ላይ ልዩነት ማምጣት የአብዛኞቻችን ፍላጎት ነው፡፡ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰብዓዊ ወገኖች አዎንታዊ ምላሽ እንድንሰጥ ሊረዱን የሚችሉ በርካታ ባህሪያትና ድርጊቶች አሉ፡፡

ርኅራኄ፡ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሁኔታ በቅጡ አጢኖ ችግራቸውን እንደ ራስ ማየት ወደ ድርጊት የሚመራን የመጀመሪያው ቅደም ተከተል ነው፡፡ በሥቃይ ለሚገኙ የምናንጸባርቀውን የመቆርቆር ስሜት ማሳደግና ጠብቀን ማቆየት አለብን፡፡ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን አሳዛኝ ታሪክ ስንሰማ ከርኅራኄ ብዛት የሚከሰት የልብ መሰበርና ሐዘን ኪሳችንን ከመዳበስ አልፎ ጭንቀት ውስጥ ሊከተን የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ዙሪያውን የከበበውን ክፋትና ሥቃይ በጥንቃቄ ያስተውል የነበረው የሱስ በርኅራኄው እንደ ጸና ሁሉ እኛም የእርሱን ፈለግ መከተል ይጠበቅብናል፡፡ ትምህርት፡ አብዛኞቹ ከፍትሕ መዛባትና ድኽነት ጋር ትስስር ያላቸው ሁናቴዎች ውስብስብ ከመሆናቸው አኳያ አንድን ጉዳይ ከስሩ ማድመጥና ምን ማድረግ እንደምንችል መማር በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ እርዳታ ለማድረግ ከመሞከር ጋር ተያይዞ አስቀድመው በተወጠኑ ተገቢ ያልሆኑ ተግባሮች በሌሎች ህይወት ላይ የተፈጸሙ በምሳሌ የሚጠቀሱ አያሌ መሰሪ ተግባራት አሉ፡፡ ይህ ሌሎችን ላለመርዳት እንደ ሰበብ መቆጠር እንደማይችል ሁሉ በቂ መረጃ ባላቸው የርኅራኄ ተግባራት ለመሳተፍ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል፡፡

ጸሎት፡ አንድ የሆነ ችግር ስንመለከት በመጀመሪያ ወደ ልባችን የሚመጣው “በተግባር የሚገለጥ” ድርጊት ነው፡፡ ሆኖም ጸሎት በተግባር የሚገለጥ ድርጊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ለድኾችና ለተጨቆኑ እንዲሁም ለበላዮቻቸው በመጸለይ በህይወታቸው ላይ ተጨባጭ ልዩነት ማምጣት እንችላለን (1ጢሞቴ. 2፡ 1-2)፡፡ በተጨማሪ ውጤታማ በሆነ አካሄድ ልንረዳቸው የምንችልበትን አምላካዊ ምሪት መሻትም እንዲሁ ከእኛ ይጠበቃል (ምሳ. 2፡7-8)፡፡

ተስፋ ማድረግ፡ በሥቃይ ውስጥ ያሉትን ሰብዓዊ ወገኖች ችግር ለማቃለል የምንሠራበት ሌላው አስፈላጊ ነጥብ ውስብስብ ለሆኑ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ግላዊ ሁናቴዎች ተገቢ ግምት መስጠት ነው፡፡ ሰዎች ሊኖራቸው ያልቻለውን ምርጫና ዕድል መስጠት ተስፋችን ሊሆን ይገባል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህን እድሎች የሚያገኙ ሰዎች አንዳንዴ ቅር ሊያሰኙን ቢችሉም እነዚያን ምርጫዎች ማክበራችን ግን የግድ ይሆናል፡፡ በሥቃይ ውስጥ ላሉ ሰዎች በየትኛውም አቅጣጫ ልንሠራ ብንሞክር የምንከተለው መርኅ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” የሚል ነው (ማቴ. 7፡12)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ያዕ. 1፡5-8፡፡ በክርስቲያን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጸሎት ምን ዓይነት ሚና ሊኖረው ይገባል? ለሌሎች የምንጸልየውን ጸሎት ምላሽ በመስጠቱ ረገድ እንዴት ራሳችን አስተዋጾ ሊኖረን እንደሚችል ያዕ. 2፡15-16 ምን ይጠቁመናል?

መስከረም 6
Sep 17

ልግስና


“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል” (2ቆሮ. 9፡7)፡፡ በልግስና መስጠት የክርስትና ህይወት መሰረታዊ ገጽታ ነው፡፡ በመስጠታችንና ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ማስቀደም ስላለብን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሞግተን መፍቀዳችን እንዳለ ሆኖ፤ ልግስና ገንዘብን ለአንድ ጉዳይ ከመወርወር የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ይልቁንም ልግስና በመዝ. 112 በተደጋጋሚ እንደ ተገለጸው “እግዚአብሔርን የሚፈሩ” አብዛኛው የሕይወታቸው አመለካከትና ቁልፍ መለያ ባህሪ ነው፡፡ “ለጋስና ያለማንገራገር የሚያበድር፣ ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል” (መዝ. 112፡5)፡፡

በችግር ላሉ ልግስና ስለ ማሳየት ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል? ዘሌዋ. 25፡35-37፣ መዝ. 119፡36፣ 2ቆሮ. 8፡12-15፣ 1ዮሐ. 3፡16-18፣ 1ጢሞቴ. 6፡17-19፡፡



ጳውሎስ በአዲስ ኪዳን መልእክቶቹ የክርስትና ተስፋ ምንጭ የሆነው የሱስ ስለ እኛ የሰጠውን ፍቅሩን በመግለጽ ስለ እግዚአብሔር ልግስና በተደጋጋሚ ጠቅሶአል፡፡ የእርሱ ለእኛ መሞት ስለ ሌሎች ለጋስ ህይወት እንድንኖር አነሳሽ ምክንያታችን ነው፡ “በክርስቶስ ስላለን መልካም ነገር ሁሉ በሚገባ ትረዳ ዘንድ፣ እምነትህን ለሌሎች በማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ” (ፊልሞ. 1፡6)፡፡

ልግስና ግዝፈት ያለው፣ በድፍረት የተሞላና አቃፊ የህይወት አመለካከት ነው፡ ፡ አብዛኛው ግላዊ፣ ማኅበረሰባዊና ባህላዊ የህይወታችን ክፍል የተቻለንን ያህል በራሳችን ዙሪያ ትኩረት እንድናደርግ ይገፋፉናል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ የአብዛኞቻችን ነባራዊ ሁኔታ ሁል ጊዜም እኔ፣ እኔ፣ እኔ--ብቻ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እምነታችን እኔነትን ገድሎ ለሌሎች እንድንኖር መንስኤ ይሆነናል፡፡ እምነታችን ዓለምንና ሕዝቦቿን እግዚአብሔር በሚያይበት ዐይን ማየት እንድንችል ይረዳናል፡፡ እርዳታ ለሚያሻቸው አቅማችን እንደ ፈቀደ የበኩላችንን እንድናበረክትም ይገፋፋናል፡፡

ምርጥ የሕይወት ዘይቤ የሆነው ለጋስነት በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዘንድ ከፍ ያለ አድናቆት ይቸረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ልግስና በመጠን የሚለካና በቀጥታ ሥራ ላይ መዋል የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ከፍ ያሉ ችሮታዎች የሰጪውን በልግስና የተሞላ ህይወት ላያንጸባርቁ ይችላሉ (ማር. 12፡41-44)፡፡ በልግስና የተሞላ ህይወት ከማንኛውም ችሮታ የላቀና የገዘፈ ነው፡፡ በምናደርጋቸው ነገሮች ለልግስና መንፈስ የተሻለ ዋጋ ልንሰጥና እንዲዳብር መፍቀድ ይጠበቅብናል፡፡ ልግስና ለብዙዎች አብሮአቸው የተፈጠረ ነገር አይደለም፡፡ ምንም እንኳ ኃጢአተኛውና ራስ ወዳዱ ሰብዓዊ ማንነት ቁልቁል ቢስበንም፤ ይህን ጸጋ በእቅድና በዝግጅት በህይወታችን ገልጠን ልናወጣ ይገባናል፡፡

በልግስና ገንዘብ ከመስጠት ጎን ለጎን በልግስና የተሞላውን መንፈስ ገልጸን የምናሳይባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

መስከረም 7
Sep 18

ሰላም ማውረድ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5፡9፡ እኛ በምንኖርበት በዚህ ዓይነቱ ዓለም የሱስ እየተናገረ ያለውን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው? ውሎ አድሮ ስኬታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ማር. 13፡7፡፡



የከረረ ግጭት ዋንኛ የሥቃይና እንግልት መንስኤ ነው፡፡ በጦርነት ምክንያት በህይወት ላይ በቀጥታ የሚደርሰው ምስቅልቅልና ሥቃይ ውጊያ የሚያስወጣው ከፍተኛ ወጪ ዋንኛ አካል ነው፡፡ ለጦር ተሸከርካሪና መሣሪያ የሚውለው ሀብት ከዘመቻ ተርፎ የተመለሰውን “አሸናፊ” ጨምሮ የሰብዓዊውን መሰረታዊ ፍላጎት ለማቅለል ቢውል እጅግ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስፍር ቁጥር የሌለውን ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ህይወት ፍርሃት ውስጥ የሚከቱ በርካታ አነስተኛ ግጭቶች አሉ፡፡ ፍትሕ እንዲሰፍን አጥብቆ የሚሻው ማንነት ሰላም እንዲያወርድ የተጣለበትን ዐደራ ችላ ብሎ ማለፍ አይችልም፡፡

ቸርና ለጋስ የሆነው መሃሪ አምላክ ታላቁ ድርጊት፤ ከኃጢአተኛው ሰብዓዊ ፍጡር ጋር ሰላም ማውረድና ከፈጣሪው ጋር ማስታረቅ ሲሆን ይኸውም የየሱስ ወንጌል አስኳል ነው (2ቆሮ. 5፡18-21)፡፡ ይህ የምንቀበለው እርቅ ለሌሎችም “አምባሳደሮቹ” እንድንሆን ያስችለናል፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 52፡7 ይህን አባባል ወደ ተግባር የሚቀይሩት እንዴት ነው?



የሰላም ወንጌል ነውጠኛዋ ዓለም ወደ ሰላም እንድንመጣ አነሳሽ፣ ተምሳሌትና በተግባር ላይ መዋል የሚችል ሰነድ ነው፡፡ “ከእግዚአብሔር ጋር ስምሙ የሆነው ልብ የሰማያዊው ሰላም ተካፋይ በመሆኑ የተባረከውን ተጽእኖ በዙሪያው ያሰራጫል፡፡ የሰላም መንፈስ በዓለማዊው ሁከት የተቸገሩ ልቦች ላይ እንደ ጤዛ ያርፋል፡፡”—Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 28. የሱስ በተረራው ላይ ስብከቱ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁአን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” (ማቴ. 5፡9) በማለት ተናግሮአል፡፡

የሱስ ይህንን ሀሳብ ወደ ላቀ ደረጃ ሲያሸጋግር አትግደል የሚለውን ትእዛዝ ማጽናት ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ወንድሙን ያለ አግባብ መቆጣት ወይም ቂም መያዝ (ማቴ. 5፡2126) እንደሌለበት ተናግሮአል፡፡ እንዲሁም ጠላቶቻችንን ልንወድና ለሚያሳድዱን ልንጸልይ እንደሚገባ (ማቴ. 5፡43-48) ማለትም የእነርሱን መልካም ነገር በመፈለግ ንቁ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚኖርብን ተናግሮአል፡፡ በተለያዩ ግጭት የሚስተዋልባቸው የዓለም ክፍሎች በመጠኑም ቢሆን የእርቅ፣ የሰላምና የፈውስ ጭላንጭል እንዲታይ በማድረግ፣ ግጭቶቹ ያስከተሏቸው መጠነ ሰፊ ሥቃይና እንግልቶች እንዲቀንሱ ያላሰለሰ ሚና የተጫወቱ ልብ የሚነኩ የብዙ ሰዎች ታሪኮች አሉ፡፡ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ በአጥቢያ ደረጃ ሰላም የማውረድ ሚና እንዲኖራት የሚያስችሉ አካሄዶች የትኞቹ ናቸው?

መስከረም 8
Sep 19

ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን


ሰለሞን “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” (መክ. 3፡7) በማለት ጽፏል። ትክክል ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ሚዛናዊ ሁኔታ ማግኘት ለማንኛችንም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ለተጨቆኑና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆንና ክፉን በመልካም ለማሸነፍ መፈለግ ረገድ እንደ ቤተ ክርስቲያን ድምጻችን ሊሰማ ሲገባው በጣም ዝምታ በሰፈነበት አቅጣጫ መዋላችን ስህተት ይሆን? ክርስቲያኖች የሱስ ሌሎችን እንድናገለግል ያቀረበልንን ጥሪ በመጥቀስ የየሱስ እጆችና እግሮች ስለ መሆን አዘውትረው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን ከትንቢታዊ ሚና አኳያ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቀረበው ከሆነ እግዚአብሔር ለወንዶችና ለሴቶች ያቀረበው የመጀመሪያ ጥሪ የእርሱ ድምጽ ሆነው--እንዲናገሩና እርሱ ሊከላከልላቸው ለሚፈልጋቸውም አንደበት ይሆኑ ዘንድ ነው (መዝ. 146፡6-10)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 58፡1-10፡፡ በዚያ የተወሰነ ጊዜ፣ ቦታ እና ዐውድ የተሰጠው ይህ መልእክት ዛሬ ለእኛ በሌላ ጊዜ፣ ስፍራና ዐውድ ለምንገኝ ምን እያለን ነው? ኢሳይያስ ይህን መልእክት በጻፈበት ጊዜና በዛሬዋ ዓለማችን መሀል ነገሮች ምን ያህል ተለውጠዋል?



ፍትሕ እንዲሰፍን ነቢዩ ያቀረበው ጥሪ ወደ ዝና የሚወስድ ልነበረም፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ተልዕኮ በመነሳሳት፣ እርሱ ለፍትሕ የነበረውን ጥልቅ ፍላጎት በማስተዋል፣ የድኾችንና የተጨቆኑትን ሐዘንና መከራ በመካፈልና ምርጥ የሆነውን ለማኅበረሰባቸው በመመኘት--ነቢያቱ ብርቱ ተቃውሞ፣ መጎሳቆልና አደጋ ቢጋረጥባቸውም እነርሱ ግን ለነበሩበት ጊዜና ስፍራ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመሆን ደፈሩ (1ጴጥ. 3፡7)፡፡

ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ስለ ወንጌል ባለን መረዳትና የሱስን ለዓለም ለማንጸባረቅ በቀረበው ጥሪ--በዓለም ከሰፈነው ክፉ ጋር በሚደረገው ግብ ግብ አያሌ ልናበረክት የምንችላቸው መልካም ነገሮች አሉ፡፡ “ድኽነትንና ተጓዳኝ ኢፍትሐዊነትን ለመቀነስ የሚደረግ እርምጃ የክርስቲያን ማኅበራዊ ሀላፊነት አስፈላጊ ክፍል ነው ብለው ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ያምናሉ። እግዚአብሔር ለድኾች ያለውን የተለየ ፍላጎት እና የእርሱ ተከታዮች ራሳቸውን መርዳት ላልቻሉት ምላሽ ሲሰጡ ለመመልከት ተስፋ እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ መላው የእግዚአብሔርን አምሳል የያዘ የሰው ዘር የአምላካዊ በረከት ተቀባይ ነው (ሉቃ. 6፡20)፡፡ እኛ ከድኾች ጋር በመሥራት የየሱስን አስተምህሮ ምሳሌ እንከተላለን (ማቴ. 25፡35-36)፡፡

ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች እንደ አንድ መንፈሳዊ ማኅበረሰብ ‘ስለ ራሳቸው መናገር ለማይችሉ በመናገር’ (ምሳ. 31፡8) እና ‘የደኻውን መብት የሚገፍፉትን’ (ኢሳ. 10፡2) በመቃወም ስለ ድኻው ፍትሕ ይቆማሉ፡፡ ‘የደኻውን ፍትሕ ከሚያስጠብቀው’ (መዝ. 140፡12) እግዚአብሔር አምላክ ጋር ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡” Seventh-day Adventist Official Statement on Global Poverty, June 24, 2010.

መስከረም 9
Sep 20


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “A Higher Experience,” pp. 503– 516, in The Ministry of Healing; “Duty to the Unfortunate” and “Man’s Duty to His Fellow Men,” pp. 511–526, in Testimonies for the Church, vol. 3; “Doing for Christ,” pp. 24–37, in Testimonies for the Church, vol. 2. “ሰማይና ምድርን ብንፈትሽ የእኛ ርኅራኄና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በምህረት ሥራዎች ከተገለጠው የላቀ በግዝፈት የተገለጠ እውነት የለም፡፡ ይህ በየሱስ የነበረ እውነት ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ የወርቃማውን ሕግ መርኅዎች በተግባር ላይ ሲያውሉ ለሐዋርያት ወንጌል የወረደው ኃይል በእነርሱም ገቢራዊ ይሆናል”—Ellen G. White, Thoughts From the Mount of Blessing, p. 137. “የከበረውን ፍቅር ለእግዚአብሔር እንድናሳይና እርስ በርሳችን ደግሞ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲኖረን የሚያስችል ምርጥ ስጦታ የሰማዩ አባታችን ሊሰጠን ይችላል፡፡ ይህ ፍቅር ስሜት ሳይሆን የማይለዋወጥ መለኮታዊ መርኅ ነው። ራሱን ለጌታ ቀድሶ ያልሰጠ ልብ ይህን ፍቅር ከየትም ሊያመጣው አይችልም፡፡ የሱስ በነገሠበት ልብ ውስጥ ብቻ ይገኛል. . . ይህ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ፍቅር ህይወትን ያጣፍጣል፣ በዙሪያችንም አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 551.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.የሱስ ስለ እኛ መጠነ ሰፊ ተግባራትን እንዳከናወነ እኛም ስለ ሌሎች እንሠራ ዘንድ ወንጌል ምሳሌያችንና መበረታቻ ምክንያታችን ሆኖ መቀጠሉን በዚህ ሣምንት ጥናታችን ተመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውንና ፍቅሩን የገለጸበትን ይህን መልካም የምሥራች ያስተውሉና ያደንቁ ዘንድ አመለካከትዎን ማስፋት የቻለው እንዴት ነው?

2.ድምጻቸው ለማይሰማ ድምጻችንን ማሰማታችን፣ ሰላም በማውረድ ተግባር ላይ መሳተፋችንና የሌሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች አካል መሆናችን ወደ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ መድረኮች እንድንሳብ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ሆኖም ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን መካከል መለያየት እንዲኖር አጥብቃ በመሥራት ትታወቃለች፡፡ አግባብ ባልሆነ መንገድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባትና ድምጽን እያሰሙ ለሰላም በመሥራት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

3.በዚህ ሣምንት ጥናታችን ከተወያየንባቸው ነጥቦች መሃል የትኛውን ለግልዎና ለማኅበረሰብዎ መተግበር ይችላሉ? ይህን እንዴት እውን ማድረግ ይችላሉ?

4.ለማኅበረሰብዎ ወይም በዓለማቀፍ ደረጃ ሊጸልዩበት የወሰኑት የክፉው ርዕሰ ጉዳይ እና ጭቆና የትኛው ነው?

ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር ስለ ደኻውና ስለ ተገፋው ያለውን ብርቱ መቆርቆር የምንቀላቀልበትን ቅንአት በውስጣችን መፍጠር ጨምሮ፤ የየሱስ ተከታይ መሆን ህይወታችንን በብዙ መንገድ ይለውጠዋል፡፡ ይህ እምብዛም ገናና ያልሆነ ነገር ፈጽሞ ቀላል ኃላፊነት አይደለም፡፡ ቅድሚያ እንሰጣቸው የነበሩ ነገሮችን ትተን በአካባቢያችን ብሎም በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የተጎዱ ሰብዓዊ ወገኖች ለመፈወስ በሚያስችሉን ቅደም ተከተሎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ይኖረን ዘንድ መነሳሳት ይፈጥርልናል፡፡