የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከግንቦት 10 - 16

8ኛ ትምህርት

May 18 - May 24




ወላጅ የመሆን ጊዜ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 18:11፣ ኤር. 31:25፣ ማቴ. 11:28፣ መዝ. 127፣ ምሳ. 22:6፣ 1ሳሙ. 3:10–14፣ ፊልጵ. 3:13።


መታሰቢያ ጥቅስ:- “እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው” (መዝ. 127፡3)፡፡

ል ጅ መውለድ የተለመደ ክስተት ቢሆንም ለዚህ አስደማሚ ስጦታ ብዙውን ጊዜ ሙሉ አድናቆትና አግራሞት ስንቸር አንስተዋልም። ልጇን ቃየንን በክንዷ የታቀፈችው ሔዋን ምን ዓይነት ስሜት ውስጥ እንደነበረች በመጠኑም ቢሆን በዓይነ ህሊናዎ ለመመልከት ይሞክሩ።

በእርግዝናዋ ወራት ሰውነቷ እየከበደና ሆዷ እየገፋ መምጣቱ፣ ስትወልድ የተሰማት ብርቱ የሥቃይ ስሜት፣ ከዚያም ወላጆቹን የሚመስለውን ግን ደግሞ ራሱን መመገብም ሆነ መከላከል የማይችለውን እንቦቀቅላ መመልከታቸው--እንዴት ያለ አግራሞት ፈጥሮባቸው ይሆን! የምትገኝበት የእርጅና ዘመን ልጅ ወልዳ ለመሳም ፍጹም የማይፈቅድላት ሣራ፤ በዘጠናዎቹ የዕድሜ ክልል ሆና ልጅ ወልዳ ማሳደጓ በዓይነቱ የተለየ ተሞክሮ ነበር።

የገዛ ልጇን ይስሐቅን ዐይን ዐይኑን እያየችና እያሰላሰለች አቆላምጣ ስሙን በጠራች ቁጥር በፍጹም ፈገግታ መሞላቷን ለመገመት ብዙ አይከብድም። እግዚአብሔር ወንድ ልጅ እንዲሰጣት ባለማቋረጥ የጸለየችው ሐና ሕፃኑን ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ቤት በማምጣት “‘ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ’” (1ሳሙ. 1፡ 27) አለች። ገና በወጣትነት ዕድሜ የነበረችው ማርያም--ልጇን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ አድናቆትና ፍራቻ በተቀላቀለበት ልቦና ትንከባከብ፣ ታሳድግም ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁሉም ሰው ወላጅ ወይም አሳዳጊ ከመሆን ጋር ተያያዥነት ያለው ልዩ መብትና ኃላፊነት ሊኖረው እንደማይችል ማሰብ ተገቢ ነው።

በዚህ ሣምንት ወላጅ የመሆንን ጊዜያቶች ከተግዳሮቶቹ፣ ከአስፈሪ ሁኔታዎቹ፣ ከሚያመጣው እርካታና ደስታ አኳያ ጠለቅ አድርገን ለመመልከት እንሞክራለን።

ግንቦት 11
May 19

ጋብቻ--ያለ ልጅ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 18፡11፣ 30፡1፣ 1ሳሙ. 1፡1-8፣ ሉቃ. 1፡7። እነዚህ ሰዎች በአንድ የሚጋሩት ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የልባቸውን ምኞት እንዴት ሞላላቸው?



ልጆች የእግዚአብሔር በረከት ናቸው። ሆኖም በአንዳንድ ምክንያቶች እግዚአብሔር ሁሉንም በልጅ አይባርክም። አንዳንዶች ቤተሰብ ለመመስረት ተስፋ በማድረግ ይጸልያሉ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ የልባቸውን ሀሳብ ይሞላላቸዋል። አልፎ አልፎም እንደ ሣራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለጸሎታቸው መልስ ይሰጣቸዋል።

ሌሎች ደግሞ ከአፋቸው አንዳችም ቃል ሳይወጣ በጽኑ ጸሎት በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ይቃትታሉ። ባለ ትዳሮች ከጓደኞቻቸው ጋር በተገናኙ ቁጥር ስለ እርግዝናቸውና በሰላም ተገላግለው ስላገኙት አዲስ ልጅ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት መጠን-ጎጆአቸው ያለ ልጅ በቆዩባቸው ቀናት ገጥሟቸው ከነበረው የልብ መሰበር ጥልቀት አኳያ ሊለካ ይችላል። አንዳንዴ “ስንት ልጆች አሏችሁ?” በሚል በየዋህነት የሚጠየቁ ጥያቄዎች የትዳር ተጣማሪዎች ያለ ፍሬ መኖር የሚሹ ይመስል ልጆች ያልወለዱ ባለ ትዳሮች ራሳቸውን ከዚህ ተቋም የመነጠል ወይም ባይተዋር የማድረግ ስሜት ዘወትር ወደ አእምሮአቸው እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል።

በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ተሞክሮዎች ያለፉ ወገኖች እግዚአብሔር የልባቸውን ሐዘን እንደሚያስተውል ሊቀበሉ ይገባል። “ሰቆቃዬን መዝግብ፤ እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?” (መዝ. 56፡8) በማለት ባለ መዝሙሩ ስለ እግዚአብሔር ይናገራል። ምንም እንኳ በዝምታ ውስጥ ያለ ቢመስልም ነገር ግን “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል” (103፡ 13)።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ልጅ እንዲኖራቸው የማይፈልጉ ባለ ትዳሮች እንዳሉም ይታወቃል። እነዚህ ወገኖች በዚህ መከራ፣ ክፋትና የአደጋ ሥጋቶች ባንዣበቡበት ዓለም ተጨማሪ ፍጡር ወደዚህ ምድር ለማምጣት ለምን ከውሳኔ መድረስ እንደማይችሉ ለማስተዋል ከባድ ላይሆን ይችላል። አንዳንዶች በተለያዩ ምክንያቶች ህፃናትን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ሊመርጡ ይችላሉ። በዚህ ውሳኔያቸው በልጅ እርግዝና ብሎም ውልደት ሂደት ውስጥ ሳያልፉ፣ በወላጅ ኃላፊነት ተወስደው ለማደግ ዝግጁ የሆኑትን እንቦቀቅላዎች በጉዲፈቻ ተረክበው እንደ አብራካቸው ክፋይ ያሳድጋሉ። በዚህም፣ ብዙውን ጊዜ እንደሚስተዋለው ለእነዚህ ምስኪኖች የተሻለ የህይወት ዕድል ያጎናጽፏቸዋል።

ምድራችን ዉሉ እንደተሰወረ አስቸጋሪ ቋጠሮ ከመሆኗ አኳያ ልጅ ሊኖር ይገባል ወይም አይገባም ለተሰኘው ሙግት የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ዝብርቅርቅ ሀሳቦች ሲያስተናግዱ ይስተዋላል። በልጅ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ራሳችንን በየትኛውም ሁናቴ ውስጥ ልናገኘው ብንችል፤ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ፍቅርና ለመጨረሻችን መልካምነት ካለው ምኞት አኳያ መመላለስ እንችላለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማናቸውም ምክንያቶች ልጅ ለሌላቸው ወገኖች ስሜት በተቻለን መጠንቀቅ እንደሚኖርብን አንዘንጋ። የሱስ ከአብራኩ የወጣ ልጅ እንዳልነበረው መገንዘባችን ምን ዓይነት ትምህርት ሊሰጠን ይችላል?

ግንቦት 12
May 20

ብቸኛ ወላጅነት


የእናት ወይም የአባት ብቸኛ ወላጅነት ምድራችን እየተጋፈጠች ከምትስተዋልባቸው ክስተቶች አንዱ ነው። ከአባት ይልቅ የእናት ብቸኛ ወላጅነት ይበልጥ የተለመደ ሆኖ እናገኘዋለን።

አልፎ አልፎ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጠር ጽንስ ብቸኛ ወላጅነትን ያስከትላል። በእርግጥ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አይቆምም። ለምሳሌ አጋር ከአብርሃም ልጅ እንድትወልድ ግፊት ተደርጎባት የነበረ ቢሆንም ውሎ አድሮ ከልጇ ጋር ያንን ቤት ለቅቃ ለመውጣት ተገድዳለች (ዘፍ. 16፡3-4፣ 21፡17)። ብርቱና ገናና የነበረው ሰው በቤርሳቤህ ላይ መድረሱን ተከትሎ ይህች ሴት ለመጸነስ በቃች (2ሳሙ. 11፡4-5)።

ኤልያስ ሰራፕታ በመባል ወደ ምትታወቅ መንደር በመሄድ አንዲት መበለትን እንዲረዳ ተልኮ ነበር (1ነገሥ. 17፡9)። የሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት የጉዲፈቻ አባቱ የነበረው ዮሴፍ ማርያምን ብቸኛ ወላጅና መበለት አድርጎ በሞት ተለያት። “ሞት የሱስን ምስጢራዊ በሆነ መንገድ የመጸነሷን እውነታ ያካፈለችውን ዮሴፍ ከእርሷ ነጥሎ ወሰደባት።

አሁን ተስፋዋንና ፍርሐቷን ልታጋራው የምትችለው ሰው አልነበራትም። ያለፉት ሁለት ወራት ለማርያም ብርቱ ሐዘን የሞላባቸው ጊዜያቶች ነበሩ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 145. ያለ ትዳር አጋር ብቸኛ ወላጅ ሆኖ ልጅ ማሳደግ ምናልባት አንድ ሰው ሊገጥመው ከሚችሉ ፈታኝ ተግባራት አንዱ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ገቢያቸውን በመቆጣጠርና በመምራት ረገድ፣ ከሌሎች ወላጆች ጋር ሊኖራቸው በሚችል ጉዳይ፣ ከልጃቸው ጋር በሚውሉበት አጋጣሚ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር በሚያጠፉት ጊዜ--ከዚህ በኋላ መወደድ ይችሉ እንደሆን በአግራሞት እያሰቡ የሚያውክ ስሜት ሊመላለስባቸው ይችላል።

ብቸኛ ወላጆችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት ተስፋዎች ማግኘት ይችላል--ኤር. 31:25፣ ማቴ. 11:28፣ ኤር. 29:11፣ ኤር. 32:27፣ ምሳ. 3:5-6፣ ኢሳ. 43: 1-2።



እንደ ቤተ ክርስቲያን እኛ ሁላችን ብቸኛ ወላጆችን የመርዳትና የማገዝ ኃላፊነት አለብን። “በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ” (ያዕ. 1፡27)።

የምንሰጠው እርዳታ የግድ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ መሆን ላይኖርበት ይችላል። ይልቁንም ብቸኛዋን ወይም ብቸኛውን ወላጅ በቤት ውስጥ ሥራ፣ በዕረፍት፣ በጸሎትና የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናት ጊዜ እንዲኖራት/ እንዲኖረው ልጆችን በመጠበቅ ማገዝ ሊሆን ይችላል።

እንዲሁም ልጆችን በማስጠናት ወይም በቤት ውስጥ አንዳንድ የሚጠጋገኑ ነገሮችን በማቃናት ብቸኛ ወላጅን ማገዝ እንችላለን። ፈርጀ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ብቸኛ ወላጆችን በመርዳትና በማገዝ የእግዚአብሔር እጅ ሆነን የበኩላችንን ማበርከት እንችላለን።

ብቸኛ ወላጆች እንዴት ወደዚህ ዓይነቱ ሁናቴ እንደገቡ ሳንፈርድ፤ ይልቁንም በማበረታታትና በመርዳት ምን የተለየ ነገር ማድረግ ይችላሉ?

ግንቦት 13
May 21

ወላጅ የመሆን ደስታና ኃላፊነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 127። የዚህ አጭር መዝሙር መሰረታዊ ጭብጥ ምንድን ነው? እንዴት መኖር እንዳለብን አስመልክቶ ምን ዓይነት አስፈላጊ መርኅዎችን ለራሳችን መውሰድ ይኖርብናል?



እርስዎ የሚወዱትን ምግብ ለማብሰል ሲፈልጉ የምግብ አሠራሩ የሚጠይቀውን ያሠራር መምሪያ ይከተላሉ። ለምግቡ መሥሪያ የሚጠየቀውን እያንዳንዱን ነገር እንደ ቅደም ተከተሉ እየጨመሩና እያዋሃዱ ተስፋ ያደረጉትን ውጤት እስኪያገኙ ማብሰሎን ይቀጥላሉ። በእርግጥ ወላጅነት ምግብ እንደ ማብሰል አይደለም። አንዱ ልጅ ትክክለኛ የሌላው ግልባጭ መሆን አይችልም። ምናልባት ለአንደኛው ልጅ ያደረጉትን ነገር በተመሳሳይ ለሌላውም ቢያደርጉ እንኳ የተለያዩ ሆነው መውጣታቸው አይቀሬ ነው።

የጾታቸው ሁኔታ፣ የተወለዱበት ቅደም ተከተል፣ ጠባያቸው ወይም ሌሎች ሁናቴዎች የተለያዩ ያደርጓቸዋል። ወላጆች በአምላካዊው እቅድ መሰረት ልጆቻቸው እርሱን እንዲወዱና እንዲታዘዙ ይመራሉ፣ ያስተምራሉም (ዘዳ. 6፡4-9፣ መዝ. 78፡5-7)። “ልጅን በሚሄድበት መንገድ አስተምረው” (ምሳ. 22፡6) ሲል እግዚአብሔር ለወላጆች መመሪያ ከመስጠት ውጪ አንዳችም የተሳሳቱ ውሳኔዎችን እንዳያደርጉ ዙሪያቸውን እጠሩ አላለም።

ልጆቻችን ከእምቦቀቅላነትና ክፉና ደጉን ካለማወቅ ራሳቸውን ወደ መቻል ብሎም ወደ ስኬታማ ጎልማሳነት ሲገሰግሱ ማየት ብንፈልግም፤ ፍቅርን ወደ ማወቅና የሱስ ክርስቶስን ወደ ማገልገል መምጣታቸው የኃላፊነታችን የመጨረሻው ግብ ነው። እንደ ወላጅ--ለልጆቻችን መንፈሳዊ እድገት በዘዳግም 6 የቀረበውን ርዕሰ ጉዳይ መከተል እንችላለን፡ እርሱ “አንድ እግዚአብሔር” መሆኑን (6፡4)፣ በፍጹም ልባችን ልንወደው እንደሚገባ (6፡5)፣ ቃሉን በልባችን መያዝ እንዳለብን (6፡6) እንዲሁም ስለ እርሱ የምናውቀውን ለሌሎች ማካፈል (6፡20-23) ከእኛ ይጠበቃል።

ዘዳግም 6 ሁለት አስፈላጊ መርኅዎችን በማቅረብ ይቀጥላል። የመጀመሪያው “አስተምር-ተናገር” በመባል የሚታወቀው መርኅ ነው (ዘዳ. 6፡7)። ማስተማር መደበኛውን ትምህርት ሲወክል መናገር ደግሞ ኢመደበኛውን መምሪያ ይወክላል። እነዚህ ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነታ ተግባቦቶች በወላጅና በልጅ ግንኙነት መቼት ቀርበዋል። መደበኞቹ የማስተማሪያ ጊዜያቶች በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አምልኮ ጊዜ ገቢራዊ መሆን ይችላሉ። ምናልባት ይበልጥ አስፈላጊዎቹ በየዕለት ህይወታችን በግብታዊነት ብቅ የሚሉት ኢመደበኞቹ አስተምህሮዎች ናቸው።

የየቀኑ አጋጣሚዎች ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ተግባቦት ምቹ መሣሪያ መሆን ይችላሉ (ዘፍ. 18፡19)። ሁለተኛው ደግሞ “እሰራቸው-ጻፋቸው” የተሰኘው መርኅ ነው (ዘዳ. 6፡8-9)። መንፈሳዊ እውነት--በድርጊታችን (“እጅ”) በአመለካከታችን (“ግንባር”)፣ በግላዊው ( የ “ቤት መቃን”)፣ በውጪው ወይም በአደባባይ (“በሮች”) ህይወት መገለጽ ይኖርበታል። ከልባችን ወደ ቤታችን እንዲሁም ከቤታችን ወደ ዓለም መሰራጨት ይኖርበታል።

ግንቦት 14
May 22

ልጆችን ደቀ መዝሙር አድርጎ የማፍራት ወላጅነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 18፡18-19፣ 1ሳሙ. 3፡10-14። እነዚህን ሁለት አባቶች ያነጻጽሩ። የወላጅነታቸው ስልት ምን ዓይነት ውጤት አስከተለ?



ወላጆች ልጆቻቸውን የየሱስ ደቀ መዝሙር አድርጎ የማፍራት ኃላፊነት አለባቸው። ልጅ በአርጩሜ ሾጥ በተደረገ ቁጥር በተሻለ ይታረማል ብለው የሚያምኑ ብዙ ወላጆች አሉ (ምሳ.22:15፣ 23:13፣ 29:15)። ሆኖም በጥቅሱ የቀረቡትን ሀሳቦች በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ በልጆች ላይ ጉዳት የሚያደርሱና ተንቀጥቅጠው እንዲገዙ ለማድረግ የሚሞክሩ ወላጆች አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በተቃራኒው ልጆችን በወላጆቻቸውና በእግዚአብሔር ላይ አመጸኞች ከማድረግ በዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።

ወላጆች ልጆቻቸውን በኃላፊነት እንዲያስተዳድሩ (ኤፌ. 6:4፣ ቆለ. 3:21) እና በጽድቅ መንገድ እንዲያንጹ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (መዝ. 78:5፣ ምሳ. 22:6፣ ኢሳ. 38:19፣ ኢዮኤ. 1:3)። እንደ ወላጅ ለልጆቻችን የሚያስፈልጋቸውን ማሟላትና (2ቆሮ. 12፡14) ሊከተሉት የሚችሉት መልካም ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል (ዘፍ. 18፡19፣ ዘፀ. 13፡8፣ ቲቶ 2፡2)። የእግዚአብሔርን ፍቅር እያንጸባረቅን (ኢሳ. 66:13፣ መዝ. 103:13፣ ሉቃ. 11:11) ቤተሰባችንን በአግባቡ እንድንመራና (1ቲሞቴ. 3፡4-5፣ 12) ልጆቻችንን የጌታ ደቀ መዝሙር አድርገን እንድናሳድግ ተነግሮናል።

አምላካዊው ፈቃድ ይህ ቢሆንም በተሳሳተ መንገድ ያፈነገጡ አሳዛኝ ታሪኮችን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የይስሐቅና ርብቃን ወላጅነት አስመልክቶ ይስሐቅ ለዔሳው ርብቃ ደግሞ ለያዕቆብ የተለየ ስሜት ነበራቸው (ዘፍ. 25፡28)። ከዚያም ኋላ ላይ ያዕቆብ በዮሴፍ ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ያዘ (ዘፍ. 37፡3)። ካህኑ ኤሊ ምንም እንኳ የኃይማኖት መሪ ቢሆንም ልጆቹን ከማረምና ከመቅጣት ተሰናክሎ ነበር (1ሳሙ. 3፡10-14)።

በካህኑ ኤሊ እጅ ያደገው ሳሙዔል ራሱ በጣም ጉድለት የነበረው አባት ነበረ (1ሳሙ. 8፡1-6)። ንጉሥ ዳዊት ዝሙት በመፈጸምና በንጹህ ሰው ላይ የግድያ ትእዛዝ በመስጠት ምሳሌነቱን ለተከተሉት ልጆቹ ተወ። ንጉሥ አካዝ እንዳደረገው (2ነገሥ. 16፡2-4) ንጉሥ ምናሴ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ልጆቹን ለአጋንንት ሰዋ (2ነገሥ 21:1–9)። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የመልካም ወላጅነት ምሳሌ የሆኑ ወገኖችን ታሪክ ይነግረናል። መርዶክዮስ ሀደሳ በመባል ትጠራ ለነበረችውና ኋላ ላይ በንግሥት አስቴር ስያሜ ለምትታወቀው የጉዲፈቻ ልጁ እጅግ መልካም አባት ነበር (አስቴ. 2፡7)።

ኢዮብ ስለ ልጆቹ ዘወትር በጸሎት ይተጋ ነበር (ኢዮ. 1፡4-5)። የወላጅነት ትምህርቶችን ከእነዚህ መልካምና መጥፎ ምሳሌዎች እየነቀስን መውሰድ እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ከምንመለከታቸው የወላጅነት ምሳሌዎች ምን መማር እንችላለን? ከእነዚህ መርኅዎች አንዳንዶቹን ልጆቻችን ካልሆኑ ወገኖች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ጥቅም ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 15
May 23

የባዘነ ልጅዎን ለመለለስ የሚያደርጉት ትግል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. 22፡6። ይህን ጥቅስ የሚያስተውሉበት መንገድ ምን ይመስላል? ለመሆኑ ይህ ለወደፊቱ ዋስትና መሆን የሚችል የተስፋ ቃል ነው?



አንዳንዴ እንደ ወላጅ ማድረግ የሚኖርቦትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለልጆችዎ ትክክለኛውን ነገር ለማስተማር ብሎም በተገቢው መንገድ ለማነጽ ከእነርሱ ጋር በቂ ጊዜ ይወስዳሉ፣ እግዚአብሔርን በሚያውቁት መጠን ይመላለሳሉ፣ የተሻለ ወደ ተባለ ትምህርት ቤት ይልካሉ፣ ሳያሰልሱ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይካፈላሉ፣ እነርሱን ያካተተ የወንጌል ሥራ ይሠራሉ--ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ በስተመጨረሻ ያደጉበትን የእምነት መንገድ ይተዋሉ።

ይህን በዐይኖቹ የተመለከተ ወላጅ ሐዘኑ እጅግ የመረረ ይሆናል። ዘወትር ለልጆቹ መዳን ከማሰላሰል ውጪ ለአፍታ እንኳ ህሊናው አያርፍም። እንዲህ ያለው አሳዛኝ ክስተት የግድ በወላጅ መላከክ አይችልም። ልጆች የራሳቸው አእምሮ ስላላቸው ይህን ውሎ አድሮ በእግዚአብሔር ፊት የሚጠየቁበትን ኃላፊነት ራሳቸው ይወስዳሉ።

አንዳንዶች “በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” የሚለውን ሀረግ፤ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለውን ወላጅነት ለልጆች የደኅንነት ባለቤትነት እንደ ዋስትና ወይም የተስፋ ቃል አድርገው ይወስዳሉ። ሆኖም ሁሌም ቢሆን መጽሐፈ ምሳሌ የሚሰጠን መርኅዎችን እንጂ ገደብ የሌላቸውን ተስፋዎች አይደለም። ከዚህ ጥቅስ ልንወስድ የምንችለው--በልጅነት የተማርናቸው ትምህርቶች እስከ ዕድሜ ልክ የሚኖራቸውን ዘላቂነት ነው። እያንዳንዱ ህፃን የወላጆቹን ቅርስ እንደ ራሱ አድርጎ የሚቀበልበት ወይም የሚቃወምበት የዕድሜ ክልል ላይ አንድ ቀን ይደርሳል። የልጆቻቸው ልብ ለእግዚአብሔር ቅርብ እንዲሆን አድርገው የሚያሰለጥኑ ጥንቁቅ ወላጆች ያስተማሯቸው እውነት ሁሌም ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ማረጋገጫ አላቸው-እግሮቻቸው ማፈንገጥ ቢገጥማቸው እንኳ በልባቸው የተዘራው ዘር ዘወትር ወደ ቤት እንዲመለሱ ይማጸናቸዋልና። መልካም ወላጅ መሆን የእኛ ምርጫ ሲሆን፤ የልጆቻችን ውሳኔ ደግሞ ያው የራሳቸው ነው።

ልጅ ከቀናው መንገድ ሲያፈነግጥ የወላጅ ድርሻ ምን ሊሆን ይችላል? ልጅዎ ወደ እግዚአብሔር ይመለስ ዘንድ በጽኑ ጸሎት በፊቱ ይቅረቡ። ከሁሉም በላይ የእርስዎን ሐዘን ሊጋራ የሚችል ቢኖር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ልጆቹ ጀርባቸውን የሰጡት እግዚአብሔር አምላክ ነው። የባዘኑ ልጆችዎ ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርጉት ትግል ከጎናቸው ሳይለዩ በፍቅርና በጸሎት ሊያግዟቸው ይችላሉ።

አምላካዊውን ድጋፍና እርዳታ በጸሎት ለመጠየቅ የሐፍረት ስሜት አይሰማዎ። ለተፈጠረው ችግር ራስዎን ተወቃሽ ሊያደርጉና ሙሉ ትኩረትዎ በባዘነው ልጅ ተወስዶ የተቀረውን የቤተሰብ አባላት እንዳይረሱ ጥንቃቄ ያድርጉ። የባዘነ ልጅ ወላጅ መሆን በቤተሰብ አባላት ላይ መከፋፈል ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ ከባለቤትዎ ጋር ጥምር ግንባር ይፍጠሩ፣ በልጆች ፊትም ግልጽ ድንበር ያብጁ።

እርስዎ ልጅዎን ከሚወዱት በላይ እግዚአብሔር እንደሚወደው በማስታወስ ለባዘነው ልጅዎ ብሩህ ተስፋ ይመኙ። ልጅዎ በግስጋሴ ያለ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑንም ይቀበሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲገጥም ራስን ተወቃሽ ማድረግ ተፈጥሮአዊ ነው። እርስዎ ስህተት ሠርተው እንኳ ቢሆን ትኩረትዎን በወደፊቱና በአምላካዊው ተስፋ ላይ ማድረግ የተሻለ የሚሆነው ለምንድን ነው-ፊልጵ. 3:13?

ግንቦት 16
May 24

ተጨማሪ ሀሳብ


፡ “ከትናንሽ ልጆችዎ ጋር ለመነጋገርና ለመጸለይ ጊዜ ይኑርዎ። ይህን ከእግዚአብሔርና ከልጆችዎ ጋር የሚኖሮትን የአንድነት ጊዜ ምንም ዓይነት ነገር ጣልቃ ገብቶ እንዲያቋርጥ አይፍቀዱ። ምናልባት እንግዶች ቢፈልግዎ ‘ጌታ የሰጠኝ ሥራ ስላለ ያን መሥራት አለብኝ። ለአሉባልታና ለሐሜት ጊዜ የለኝም’ ብለው ይመልሱላቸው። ለአሁን እንዲሁም ለዘላለም የሚዘልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ይሰማዎት። ለቀዳሚው የልጆችዎ አገልግሎት ባለ ዕዳ ይሁኑ።”—Ellen G. White, The Adventist Home, pp. 266, 267. “ወላጆች ህፃናት ልጆቻችሁ ገና በእቅፍ እያሉ ሥነ ስርዓት ማስተማር ጀምሩ። ፈቃዳቸውን ለእናንተ ማስገዛት አስተምሩአቸው። ልጆች ከየትኛውም ነገር ይልቅ ፈቃዳቸውን ከወላጆች ጋር በጽኑ ማቆራኘት ይችሉ ዘንድ ወላጆች ስሜታቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠሩ፣ በእርጋታ የተሞሉና ጥብቅ ሊሆኑ ይገባል።

ህ ፃናት ገና በእንጭጩ ግልፍተኝነት ሲያሳዩ መቆጣጠር እንዲችሉ ሆነው ከወዲሁ ካልተገሩ፤ እያደር ሐሳበ ግትርና እልኸኛ ባህሪ ይዘው ያድጋሉ።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 1, p. 218.


የመወያያ ጥያቄዎች




፡ 1.የእግዚአብሔር “ልጅ” መሆን ምን ማለት ነው? እንዲህ ያለውን ሐሳብ የምናስተውለው እንዴት ነው? ከአባባሉ ምን ዓይነት መጽናናት ማግኘት እንችላለን?

2.አንድ አባት ልጆች ተወልደውለት ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ብሎ ነበር “ልጆች ካገኘሁ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ሥነ መለኮታዊ እውነቶችን ተምሬአለሁ። የመጀመሪያው የመምረጥ ነፃነት እውነታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሰብዓዊው ፍጡር ኃጢአተኛ ተፈጥሮ እውነታ ነው።” እነዚያ ታዳጊ ህፃናት እነዚህን እውነቶች እንዴት ሊያስተምሩ ቻሉ?

3.የህፃናትን የመምረጥ ነፃነት ማረቅ የሚቻልበት ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው? እንዴትስ መተግበር ይችላል? እኛ ራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ለእርሱ ሳናስገዛ ህፃናት ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያስገዙ አድርገን ልንቀርጻቸው የምንችለው እንዴት ነው?

4.በብቸኛ ወላጅችነት ዙሪያ ጠለቅ ብለው ለመመልከት ይሞክሩ። ልጆችን ያለ ትዳር አጋር በብቸኝነት ለማሳደግ ጎንበስ ቀና ለሚል/ ለምትል ብቸኛ ወላጅ ቤተ ክርስቲያንዎ እገዛ ልታደርግ የምትችልባቸው አቅጣጫዎች የትኞቹ ናቸው?

5.ልጆቻቸው ከእምነት ጎዳና የባዘኑ ወላጆችን ልናበረታታና አይዟችሁ ልንል የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?