የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከየካቲት 2 - 8

7ኛ ትምህርት

Feb 09 – Feb 15




ሰባቱ መለከቶች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 8:1– 13፣ ዘኁ. 10:8–10፣ ሕዝ. 10:2፣ ራእ. 10:1–11፣ ዳን. 12:6-7፣ ራእ. 11:1–13፣ ዘሌዋ. 16.


መታሰቢያ ጥቅስ :- “ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በነፋባቸው ቀኖች፣ ለአገልጋዮቹ ለነቢያት በተገለጠላቸው መሠረት የእግዚአብሔር ምስጢር ይፈጸማል” (ራእ. 10፡7)፡፡

በ ዘመናት በእግዚአብሔር ታማኞች ላይ የደረሰውን ሰቆቃ የሚያመለክተውን በመከራ ውስጥ ያለፉ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ልቅሶ በአምስተኛው ማኅተም ትዕይንት ተመልክተናል፡፡ እነርሱም “ ‘ጌታ ሆይ እስከ መቼ አትፈርድም?’ ” ሲሉ ከመሰዊያው ስር የእግዚአብሔርን ፍትሕ ሲማጸኑ በኖሩ ነፍሳት ሁኔታ ተገልጸዋል፡ ፡ በእነርሱ ላይ ጉዳት ያደረሱ አምላካዊውን ፍትሕ የሚቀበሉበት ጊዜ መቃረቡን የገለጸላቸው ከሰማይ የመጣ ድምፅ በጽናት እንዲጠብቁ አሳሰባቸው፡፡ የየሱስን ዳግመኛ ወደዚህ ምድር መጥቶ በታማኝ ተከታዮቹ ላይ ክፉ ያደረጉትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ራእ. 6፡15-17፡፡

የአምስተኛው ማኅተም ትዕይንት በዘመናት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የደረሰውን አስከፊ ስቃይ--ይኸውም እግዚአብሔር ከአቤል አንስቶ እስከ ምድር ታሪክ መዝጊያ “ስለ አገልጋዮቹ ደም” (ራእ. 19፡2) ጻድቅ ፍርዱን እስከሚሰጥ ያለውን ጊዜ ይወክላል፡፡ በመከራ ያሉ ወገኖች እግዚአብሔር የሕዝቦቹን ጸሎት የሚሰማ አምላክ መሆኑን ሊያምኑና በጽናት ሊቆሙ የግድ ይሆናል፡፡

እግዚአብሔር ስለ ተገፉ ሕዝቦቹ በዘመናት ጣልቃ ሲገባና በጎዷቸው ላይ ፍርድ ሲሰጥ መኖሩን የሰባቱ መለከቶች ራእይ ያሳያል፡፡ የሰባቱ መለከቶች ዓላማ ሰማይ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ሥቃይና እንግልት በግዴለሽነት የሚያልፍ ላለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት ነው፡፡

የካቲት 3
Feb 10

የቅዱሳን ጸሎት


የራእ. 8 ትዕይንት--ሰባቱን መለከቶች ለመንፋት በተዘጋጁ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ሰባት መላእክት ትዕይንት ይጀምራል፡፡ ሆኖም መለከቶቹ ከመነፋታቸው አስቀድሞ--ዓላማው የመለከቶቹን ሥነ መለኮታዊ ፍቺ መግለጽ የሆነ አንድ ሌላ ትዕይንት ይጨመራል፡፡

በራእ. 8፡3-4 የቀረቡትን ጥቅሶች በመቀጠል በየሩሳሌም መቅደስ ይከናወን ከነበረ የሠርክ መሥዋዕት የአይሁድ ሐተታ ጋር ያገናዝቡ፡፡ የእኩለ ቀን መሥዋዕት ሲቀርብ የመሥዋዕቱ ጠቦት በሚቃጠለው መሥዋዕት ማቅረቢያ ላይ ይደረግና ደሙ ከመሠዊያው ሥር ይፈሳል፡፡ ለአገልግሎት የተመደበው ካኀን የወርቁን ጥና ይዞ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገባና በወርቅ መሠዊያው ላይ የዕጣን መሥዋዕት ያቀርባል፡፡ ካኅኑ ከወጣ በኋላ ጥናውን ከእጁ ሲለቀው ከፍ ያለ ድምፅ ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ የዕለቱን የቤተ መቅደስ አገልግሎት ፍጻሜ የሚያበስሩ ሰባቱ ካኅናት መለከቶቻቸውን ይነፋሉ፡፡

የእኩለ ቀኑ አገልግሎት በራእ. 8፡3-5 ጥቅም ላይ የዋለበትን መንገድ ለማየት እምብዛም አያዳግትም፡፡ መልአኩ “በዙፋኑ ፊት ባለው የወርቅ መሠዊያ” (ራእ. 8፡3) የሚሠዋው ዕጣን መሰጠቱ ታላቅ ትርጉም አለው፡፡ ዕጣኑ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ጸሎት ይወክላል (ራእ. 5፡8)፡፡ ስለዚህ መልአኩ በእግዚአብሔር ፊት የሚያቀርበው የስደት ሥቃይ የደረሰባቸውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጸሎት ነው። አሁን ጸሎታቸው በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአል፡፡

ራእ. 8፡3-5 በመጽሐፉ ስለቀረቡት መለከቶች ጠቃሚ መረጃ ይሰጠናል፡ ሀ. ሰባቱ መለከቶች ሕዝቦቹ በዐመጸኞች ለደረሰባቸው ጭቆና ለእግዚአብሔር ላቀረቡት ጸሎት የአምላካዊው ፍርድ ምላሽ ናቸው፡፡ ለ. መለከቶቹ ከየሱስ እንደ በግ መሞት አንስተው እስከ ረጅሙ የዳግም ምጽአቱ ትዕይንት ይዘልቃሉ፡፡ (ራእ. 11፡15-18)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 8፡5፣ ሕዝ. 10፡2፡፡ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ የተወረወረው እሳት ምንጩ ምንድን ነው? በሕዝቅኤል ራእይ ክህደት የፈጸመችው የሩሳሌም ላይ የተወረወረው እሳት በራእ. 19 ስለቀረበው መለከት ተፈጥሮ ምን ያብራራል? መልአኩ ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፡፡ እዚህ ላይ እሳቱ የመጣው የቅዱሳን ጸሎት ከሚቀርብበት መሰዊያ መሆኑን ልብ ይሏል። የሰባቱ መለከት ፍርዶች የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ጸሎት በመመለስ በምድር ነዋሪዎች ላይ ማረፉን ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አልተዘነጉም፡፡ እነሆ እርሱ በራሱ ጊዜ ስለ እነርሱ ጣልቃ ሊገባ ነው፡፡

የካቲት 4
Feb 11

የመለከቶቹ ፍቺ


የራእይ መጽሐፍ እግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ጣልቃ የሚገባበትን መንገድ ለመግለጽ የብሉይ ኪዳኖቹን ምሳሌያዊ መለከቶች ጥቅም ላይ ሲያውል ይታያል፡፡ መለከት ለየቀኑ የጥንቷ እስራኤል ህይወት በእጅጉ አስፈላጊ ነበር (ዘኁ. 10፡8-10፣ 2ዜና 13፡1415)፡፡ የመለከቶች ድምፅ በቤተ አምልኮ ስግደት መኖሩን ያስታውሳል፡፡ እንዲሁም በጦርነት፣ በመኸርና በልዩ ልዩ ክብረ በዓሎች የመለከት ድምፅ ይሰማ ነበር፡፡ መለከት የመንፋቱ ተግባር ጸሎት ከማድረስ ጋር ጎን ለጎን ይከናወን ነበር፡፡ በቤተ መቅደስ ይካሄድ በነበረ የአምልኮ ጊዜ ወይም በክብረ በዐላት ወቅት የሚሰማ የመለከት ድምፅ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የገባውን ኪዳን “ያስታውስ” ነበር፡፡

እንዲሁም ሕዝቡ “ለጌታ ቀን” (ኢዮ. 2፡1) እንዲዘጋጅ ያስታውስ ነበር፡፡ በጦርነት ወቅት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲታደግ በሚደረግ ጸሎት ይታጅብና መለከት ይነፋል፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በራእይ ለቀረቡት መለከቶች መነሻ ታሪክ ነው፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 8፡13፣ 9፡4፣ 20፡፡ የሰባቱ መለከቶች ፍርድ ግባቸው ምንድን ነው?



በራእይ መጽሐፍ የቀረቡት መለከቶች መነፋት መነሾ--እግዚአብሔር ለሕዝቡ ጸሎት ምላሽ ለመስጠት በዘመናት ጣልቃ የገባባቸውን ሁናቴዎች ያመለክታሉ። የማኅተሞቹ ቀደምት ተግባር ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር የተቆራኘ ሲሆን መለከቶቹ ደግሞ በምድር ነዋሪዎች ላይ ፍርድ ያውጃሉ (ራእ. 8፡13)፡፡ በተመሳሳይ ሕዝቡ ሳይረፍድ በጊዜ ወደ ንስሐ እንዲመጣ ማስጠንቀቂያ ድምፆች ናቸው፡፡ ሰባቱ መለከቶች ከዮሐንስ ዘመን አንስቶ እስከ ምድር ታሪክ መደምደሚያ ያሉትን ጊዜአቶች ይሸፍናሉ (ራእ. 11፡15-18)፡፡ መለከቶቹ የሚነፉት በሰማይ የማማለድ ሥራ እየተሠራና (ራእ. 8፡3-6) በምድር ወንጌል እየተሰበከ ባለበት ጊዜ ነው (ራእ. 8፡ 3-6)፡፡ የመለከቶቹ ፍርድ የሚነካው ከፍጥረት አንድ ሦስተኛውን ብቻ እንደመሆኑ ሁሉንም አይጠቀልልም፡፡ ሰባተኛው መለከት የፍጥረት ሁሉ ባለ መብት የሆነው አምላክ የሚገዛበት ጊዜ መድረሱን ያመለክታል፡፡ ሰባቱ መለከቶች--ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከሚሸፍኑት የጊዜ ሠሌዳ ጋር ገጣሚነት ሊኖራቸው ይችላል፡ (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ሁለት መለከቶች ክርስቶስን በሰቀሉትና የቀደመችውን ቤተ ክርስቲያን ባሳደደዱ--በዐመጸኞቹ ኢየሩሳሌምና የሮም ግዛት ላይ ፍርድ ያውጃሉ፡፡

(ለ) ሦስተኛውና አራተኛው መለከት መካከለኛው በመባል በሚታወቀው ዘመን እና በድኅረ ተሐድሶ ተከስተው ለነበሩ ክህደቶች ሰማያዊውን ምላሽ ያስቃኛሉ፡፡ (ሐ) አምስተኛውና ስድስተኛው መለከት አምላካዊ ጥበብ የጎደለው ፍልስፍና በስፋት ከተንሰራፋበት (18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ትርምስ በኋላ ዓለምን ወደ አርማጌዶን ጦርነት የሚዘፍቃት መጠነ ሰፊ ዲያብሎሳዊ አካሄድ ጋር ቁርኝት ያለው-ከመንፈሳዊነት ያፈነገጠ ዓለም የሚገኝበትን ሁኔታ ይገልጻል፡፡ የምድር ታሪክ በደም የጨቀየና በብርቱ ሰቆቃ የተሞላ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህ አሳዛኝ ተጨባጭ ሁኔታ በየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ እንደ ተሰጠን ማስተዋል እንድንችል እንዴት ይረዳናል?

የካቲት 5
Feb 12

የተከፈተውን መጽሐፍ የያዘው መልአክ


ስድስተኛው መለከት ወደ ምድር የመጨረሻ ጊዜ ያመጣናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ምን እንዲያደርጉ ተጠርተዋል? የሰባተኛው መለከት ድምፅ ከመሰማቱ አስቀድሞ በመጨረሻው ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚኖራቸውን ኃላፊነትና ተሞክሮ የሚገልጽ የእረፍት ጊዜ መግባቱ ተመልክቶአል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 10፡1-4፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ምን ይመስላል?



የክርስቶስ ዓይነት ገጽታ የሚስተዋልበት ይህ መልአክ የተከፈተ መጽሐፍ ይዞአል። አንደኛው እግሩ በየብስ ሌላኛው ደግሞ በባህር ላይ ማረፉ በዩኒቨርስ ላይ ያለውን ገዢነትና የሚያውጀው መልእክት ዓለም አቀፍ አንደምታ እንዳለው ያሳያል፡፡ የአንበሳ ግሳት የእግዚአብሔር ድምፅ ተምሳሌት እንደመሆኑ፤ እርሱም እንደሚያገሣ አንበሳ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል (ሆሴ 11፡10)፡፡ ነጎድጓዶቹ ባስተጋቡት ድምፅ ያሉትን ዮሐንስ እንዲጽፍ አልተፈቀደለትም። የወደፊቱን አስመልክቶ እግዚአብሔር በዮሐንስ በኩል ያልገለጻቸው ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 10፡5-7፡፡ ይህን ጥቅስ ከዳን. 12፡6-7 ጋር ያስተያዩ፡፡ መልእክቶቹ በጋራ የያዙዋቸው ሀሳቦች ምንድን ናቸው?



መልአኩ “ከእንግዲህ መዘግየት አይኖርም” (ራእ. 10፡6) ብሎ ሲናገር chromos የተሰኘው የግሪክ ቃል አንድ የተወሰነ የጊዜ ሠሌዳ መጥቀሱን ያሳያል፡፡ ይህም መልአኩ በዳን. 12፡6-7 የቅዱሳን ስደት--ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመንም እኩሌታ ወይም ለ1,260 ዓመታት (538-1798 ዓ.ም.) ድረስ ይቆያል በማለት ወደ ተናገረው ይመልሰናል፡፡ ከዚህ ትንቢታዊ ጊዜ በኋላ በአንዱ ቀን መጨረሻው እውን ይሆናል፡፡ በተለይ ከዳን. 8፡14 የ2,300 ትንቢታዊ ቀናት (ከክርስቶስ ልደት በፊት 457 እስከ 1844 ዓ.ም.) በኋላ ምንም ዓይነት ትንቢታዊ የጊዜ ሠሌዳ እንደማይኖር ኤለን ኋይት ትገልጻለች፡፡

“በዚህ ወቅት መልአኩ የሚያውጀው የተከበረና የረጋ ብርቱ ቃል ከጌታችን ምጽአት አስቀድሞ ገቢራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይኸውም ሕዝቡ በዚህ ጊዜ ይመጣል የሚል ቁርጥ ያለ መልእክት የለውም ማለት ነው፡፡ ከ1842 እስከ 1844 በኋላ በዚህ ወቅት የሚል ቁርጥ ያለ ትንቢታዊ ጊዜ የሚያርፍበት ዕለት ሊኖር አይችልም፡፡ ረጅሙ ስሌት ያረፈው በ1844 መከር ላይ ነበር፡፡”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 7, p. 971. ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብሎ ጊዜ መወሰን ፍጹም ሊወገድ እንደሚገባ ከላይ የቀረበው ሃሳብ ምን ይነግረናል?

የካቲት 6
Feb 13

ጥቅልሉን መጽሐፍ መብላት


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ.10፡8-11፡፡ መብላት--ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት መቀበል፤ ከዚያ ለሕዝቡ ማወጅ በሚል አንደምታ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ ውሎአል (ሕዝ. 2:8–3:11፣ ኤር.15:16)፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መልእክት ስንቀበል መልካም የምስራች ቢሆንልንም፤ ነገር ግን ለሌሎች ስንመሰክረው አልፎ አልፎ መልእክቱን ለመቀበል ዳተኞች በሆኑ ብሎም በሚቃወሙ ዘንድ ምሬት ይፈጥራል፡፡ ዮሐንስ ጥቅልሉን መጽሐፍ ሲበላ የገጠመው መራርና ጣፋጭ ተሞክሮ ከዳንኤል የመጨረሻው ዘመን ያልተከፈቱ ትንቢቶች ጋር ዝምድና አለው፡፡ እዚህ ላይ ዮሐንስ የሚወክለው በዳንኤል ትንቢት 1,260 ቀናት መጨረሻ ወንጌልን እንድታውጅ ተልዕኮ የተቀበለችውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ በ2,300 ዓመቱ ትንቢታዊ ጊዜ መደምደሚያ ወደ ሌላ ጣፋጭና መራር ተሞክሮ እንደሚያመራ ዐውደ ሃሳቡ ያመላክተናል፡፡ የዳንኤልን ትንቢቶች መሰረት አድርገው ስሌት የሠሩት ሚለርና ተከታዮቹ፤ ክርስቶስ በ1844 ይመጣል ብለው ድምዳሜ ላይ በመድረስ ያካፈሉት መልእክት በእርግጥ ጣፋጭ ሆኖላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ስሌታቸው እንደ ታሰበው ሳይሆን ሲቀር፤ ዐውጀውት በነበረው መልእክት ብርቱ የምሬት ስሜት ተፈጠረባቸው፡፡

ዮሐንስ “እንደገና ትንቢት ልትናገር ይገባሃል” በሚል ለዓለም የተሰጠው ተልዕኮ፤ ዳግም ምጽአቱን ከዳንኤል ትንቢቶች ጋር ካለው ትስስር አኳያ እንዲያውጁ የተወከሉ ሰንበት ጠባቂ የምጽአቱን ተጠባባቂዎች ያመለክታል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11፡1-2፡፡ ዮሐንስ ምን አድርግ ተብሎ ነበር የታዘዘው?



እነዚህ ጥቅሶች በራእ. ምዕ. 10 ቀርቦ የነበረው ትዕይንት ቀጣይ ክፍል ናቸው፡፡ ዮሐንስ ቤተ መቅደሱን፣ መሠዊያውንና የሚያመልኩትን ምዕመን እንዲለካ መታዘዙን እንመለከታለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤያዊ አቀራረብ--የመለካት ጽንሰ ሃሳብ ፍርድን ያመለክታል (ማቴ. 7፡2)፡፡ በራእዩ የተለካው--የሱስ ስለ እኛ አገልግሎት የሚሰጥበት ሰማያዊው ቤተ መቅደስ ነበር፡፡ ለቤተ መቅደሱ፣ ለመሠዊያውና ለሚያመልኩት ምዕመን የቀረበው ማጣቀሻ የሥርየትን ቀን ያመላክታል (ዘሌ. 16፡16-19)፡፡ የሥርየት ቀን እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ለክቶ የሚዳኝበት ዕለት ነው፡፡ በመሆኑም ራእ. 11፡1 ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ስለሚኖረው ፍርድ ይጠቅሳል፡፡ ይህ ፍርድ በተለይ በቤተ መቅደስ ለአምልኮ የሚሰበሰቡትን ወገኖች ብቻ ይመለከታል፡፡

የሰማያዊው መቅደስ መልእክት፤ በመጨረሻው የወንጌል ዕወጃ የልብ ትርታ ላይ እንደሚያርፍ ራእ. 11፡1 ያሳየናል፡፡ አምላካዊው ባህሪ ነፃ እንደሚያወጣ በጽኑ ያሳስባል፡፡ በዚህም ወንጌል--ሰብዓዊው ፍጡር ሊድን የሚችልበት ብቸኛ መንገድ የሆነውን የክርስቶስ የሥርየት ተግባርና ጽድቅ፣ በስፋትና በሙላት ያስቃኘናል፡፡ ደም--ምን ያህል የሜዳዊው የሥርየት ቀን ማዕከላዊ ክፍል እንደሆነ በአእምሮአችን እንደያዝን (ዘሌዋ. 16)፤ የፍርድን መልካም የምስራችነት እውነታ ሁሌም ጠብቀን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው?

የካቲት 7
Feb 14

ሁለቱ ምስክሮች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11:3–6፡፡ ሁለቱ ምስክሮች በንጉሣዊና ካኅናዊ ሚናቸው ዘሩባቤልን እና ኢያሱን እንዴት ያንጸባርቃሉ? ዘካ. 4፡2-3፣ 11-14



የሁለቱ ምስክሮች ጽንሰ ሃሳብ ምንጩ የአንድን ጉዳይ እውነትነት ለማጣራት ቢያንስ ሁለት ምስክሮች ያስፈለገበት የአይሁድ ሕግ አወቃቀር ነው (ዮሐ. 8፡17)፡፡ ሁለቱ ምስክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚወክሉ ቢሆንም፤ ነገር ግን በተጨማሪ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስክር የሆኑትን የእግዚአብሔር ሕዝቦችንም ይወክላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን ለዓለም እንዲያውጁ የተጠሩ በመሆናቸው፤ ሁለቱ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡

ምስክሮቹ ለ1,260 (538 ዓ.ም.-1798) ትንቢታዊ ቀናት ማቅ ለብሰው ትንቢት እንደሚናገሩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሁኔታው ዮሐንስ ትንቢት ልትናገር ይገባሃል ወደ ተባለበት ራእ. 10፡11 ይመልሰናል። ጥሪው የእግዚአብሔርን እውነት ወደምታውጀው ቤተ ክርስቲያን ያመራ መሆኑን ይህ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ማቅ የሚለበሰው በሐዘን ወቅት ነው (ዘፍ. 37፡34)። የእግዚአብሔር ሕዝቦች “እንደ ገና ትንቢት ሊናገሩ” ከመሆኑ አኳያ፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ማለፋቸው የግድ መሆኑ ይህ በማቅ የቀረበው ምሳሌ ያመላክታል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11፡7-13፡፡ በ1,260 ትንቢታዊ ቀናት መጨረሻ በሁለቱ ምስክሮች ላይ ምን እንደተከሰተ በራስዎ ቃላት በጽሁፍ ይግለጹ፡፡





ሁለቱን ምስክሮች የሚገድለው አውሬ መነሾው ጥልቁ ሲሆን ይኸውም የሰይጣን መኖሪያ ነው፡፡ ይህ ምስክሮችን ማጥፋትና መደምሰስ--በእግዚአብሔር ላይ ክህደት ፈጽሞ በመጽሐፍ ቅዱስን ላይ ጥቃት መሰንዘርና ኃይማኖትን ከምድረ ገጽ ማጥፋት-ከፈረንሳይ አብዮት ጋር ቁርኝት አለው፡፡ ይህ ጸረ ኃይማኖት የአገዛዝ ዘይቤ ወይም ሥርዓት የዘቀጠውን የሶዶም ሥነ ምግባር፣ በእብሪት የተሞላውን የግብፅ ክህደት እና የኢየሩሳሌምን ዐመጸኝነት በአንድ አጣምሮ የያዘ ነበር፡፡ ከፈረንሳይ አብዮት ትርምስ በኋላ የምስክሮቹ ዳግም ማንሰራራት መጽሐፍ ቅዱስን ያማከለ ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት ፈጠረ፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ማሰራጨት ዓላማው አድርጎ የተነሳውን፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማኅበረሰብንና አያሌ የሚሽነሪ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ መንስዔ ሆነ፡፡

መጨረሻው ከመምጣቱ አስቀድሞ ዓለም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው መልእክት ምስክር ትሆናለች፡፡ ይህ ኃይል ከዲያብሎሳዊው እንቅስቃሴ በሚያገኘው ሥልጣን በሚያደርጋቸው ታምራቶች ዓለምን በመሳብና በማማለል ተቃዋሚዎችን በማነሳሳት ከእግዚአብሔር ታማኝ ምስክሮች ጋር ወደ መጨረሻው ውጊያ ያመራል፡፡ ስለዚህ ይህ የመጨረሻ እወጃ ጣፋጭና መራር ውጤት ይኖረዋል፡፡

የካቲት 8
Feb 15


ተጨማሪ ሀሳብ


ሰባተኛው መለከት (ራእ. 11፡15-18) ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜ ለመድረሱ ምልክት ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሔር ኃይሉንና ንጉሣዊ ገዢነቱን የሚገልጥበት እነሆ ጊዜው ደርሶአል፡፡ ይህች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የኖረች ዐመጸኛ ምድር፤ በእግዚአብሔር ግዛትና አመራር ስር የምትሆንበት ቀን ተቃርቦአል፡፡ የሥልጣን ነጠቃ ለማድረግ ያሴረው ሰይጣን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከሞተና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ለዘላለም ከሰማይ ታገደ፡፡ እነሆ የክርስቶስ የምድር ሕጋዊ ገዢነትም ታወጀ (ራእ. 12፡10)፡፡ ሰይጣን ግን ጥቂት ዘመን ብቻ እንደቀረው በመገንዘብ (ራእ. 12፡12) ቁጭቱን ለመወጣት የሚችለውን ሁሉ ጥፋት ማድረሱን ገፍቶበታል፡፡

ሰባተኛው መለከት በአምላካዊ ዙፋን ላይ የተነሱ ኃይላት ጉዳይ እልባት ማግኘቱንና በመጨረሻ ይህች ዓለም በትክክለኛው ባለቤት ስር መዋሏን ያውጃል፡፡ ሰባተኛው መለከት ከመጨረሻው ዘመን ክስተቶች ጋር ተጓዳኝነት ያላቸውን የመጽሐፉ ሁለተኛ አጋማሽ ዋና ዋና ሀሳቦች ላይ አጽንኦት ይሰጣል፡ (1) አሕዛብ ተቆጥተው ነበር፡ ራእ. 12-14 የሰይጣንን በቁጣ መሞላት ይገልጻል (ራእ. 12፡17)፡ ፡ ከሁለቱ አበሮቹ ማለትም ከባሕር የወጣው እና ከምድር የወጣው አውሬ ጋር በመሆን የምድር ነዋሪዎችን በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ለውጊያ ያዘጋጃል፡፡ (2) የእግዚአብሔር ቁጣ ፍጻሜ ያገኛል፡ እግዚአብሔር በዐመጸኞች ላይ ቁጣውን የሚገልጸው አምላካዊው ቁጣ በሚል በተገለጹት በመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሰፍቶች ነው (ራእ. 15፡1)፡፡ (3) ሙታን የሚዳኙበት ጊዜ፡ በራእ. 20፡11-15 ተብራርቶአል፡ ፡ (4) የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚቀበሉት ሽልማት፡ በራእ. 21-22 ቀርቦአል፡፡ (5) ምድርን ያጠፉ ይጠፋሉ፡ በመጨረሻ ላይ ባቢሎን ይፈረድባታል ምክንያቱም ምድርን አጥፍታለችና--ራእ. 19፡2፡፡ በሰይጣንና መላእክቱ እንዲሁም በሁለቱ አበሮቹ ላይ የሚደርሰው ውድመት የታላቁ ተቃርኖ ታሪክ መደምደሚያ ይሆናል ራእ. 19፡11-20፡15፡፡




የመወያያ ጥያቄዎች




1.አልፎ አልፎ ወንጌልን መስበክ መራራ የሚሆንበት ወቅት አለ (ራእ. 10፡10)። ከአንደበታችን የሚወጡት ቃላቶችም ሆኑ እኛ ራሳችን ሊፌዝብንና ተቃውሞ ሊገጥመን ይችላል፡፡ አንዳንዴ አምላካዊውን ቃል መስበክ ብርቱ ተቃውሞ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ከገጠሟቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባህሪያት እነማንን ያስታውሳሉ? ከእነርሱ ተሞክሮዎች ምን እንማራለን?

2.“ክርስቶስ በዚህ ዕለት ይመጣል በሚል እሳቤ ጊዜ መወሰን እንደሌለብን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የምጽአቱን ጊዜና ወቅት መሰረት ያደረገ ምንም ዓይነት መልእክት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አይሰጥም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሙላት የሚፈስበትን ጊዜም ሆነ ክርስቶስ ዳግም የሚገለጥበትን ትክክለኛ ጊዜ እንድናውቅ አልተደረግንም፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 188. ከ1844 በኋላ--ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚያሳዩ የትንቢት ስሌቶችን ነቅሶ ማውጣት ምን ዓይነት ችግር ሊያስከትል ይችላል ብለው ያምናሉ? አንድ ሰው የትንቢት ስሌቶቹ ሊያመጡ ከሚችሉት ያልተጠበቀ መሰናክል መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?