የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከመጋቢት 14-20

13ኛ ትምህርት

Mar 23 – Mar 29




“እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ”



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 19:6– 19፣ ዮሐ. 14:1–3፣ 2ተሰ. 1:8–10፣ ራእ. 21:1–21፣ ኤር. 4:23–26፣ 1ቆሮ. 6:2-3፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-“በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ‘እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ፡፡ ደግሞም ‘ይህ ቃል እውነት ስለ ሆነና ስለ ታመነ ጻፍ’ አለኝ” (ራእ. 21፡5)፡፡

ስ ለ መጨረሻው ጊዜ የተሰጠው መግለጫ ከዚህች ክህደት የፈጸመች ኃይማኖታዊ ተቋም ጋር ላበሩ መጥፎ ዜና--በተቃራኒው ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ደግሞ መልካም የምሥራች ነው (ራእ. 19፡7)፡፡ የፖለቲካ ኃይላት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ስደት እንዲያደርሱና ጉዳት እንዲያስከትሉ ቀንደኛዋ አነሳሽና ተዋናይ ባቢሎን ናት (ራእ. 18፡24)፡፡ የዚህ ታላቅ ጠላት ውድመት የቅዱሳን ደኅንነት መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡

የባቢሎንን ውድመት ይፋ የሚያደርገውን አምስተኛውን ማኅተም ተከትሎ በመጨረሻ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጸሎት ምላሽ ያገኛል፡፡ “ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም?” የተሰኘው የሥቃይ ድምፅ ከአቤል ዘመን አንስቶ እግዚአብሔር በመጨረሻ ስለ ሕዝቡ እስኪበቀል ያለውን የሕዝቦቹን ሰቆቃ ይወክላል (መዝ. 79፡ 5፣ ዕምባ. 1፡2፣ ዳን. 12፡6-7)፡፡ በመጨረሻ ክፋት፣ ጭቆና እና ሥቃይ እንደሚያከትም የራእይ መጽሐፍ ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡

ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ የሚገለጥበት ጊዜ እነሆ አሁን ነው፡፡ ቀሪዎቹ የራእይ መጽሐፍ ምዕራፎች ገለጻ የሚያደርጉት ስለ መጨረሻዋ ጊዜ ባቢሎን ውድመት ብቻ አይደለም--የክፋት ሁሉ ምንጭ ስለሆነው ቀንደኛው ሰይጣን መወገድ ጭምር እንጂ! ከዚህ በተጨማሪ ስለ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት መመስረትም በጨረፍታ ይነግሩናል፡፡

መጋቢት 15
Mar 24

የበጉ ሠርግ እራት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 19፡6-9፡፣ ዮሐ. 14፡1-3፡፡ ሠርግ የተሰኘው ቃል ለረጅም ዘመን በተስፋ ሲጠበቅ የቆየውን በክርስቶስና በሕዝቡ መካከል ገቢራዊ የሚሆን ሕብረት እንዴት ባግባቡ ይገልጸዋል?



ጌታ አምላካዊውን እውነት ለእኛ ለማስተማር የጥንት አይሁድን የጋብቻ ሁኔታ ሲጠቀም ይታያል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው እጮኛ እጮኛውን ለማጨት ወደ ቤቷ ያመራል፡፡ ከዚያም እንደ ሕጉ ተገቢውን ጥሎሽ ሲያቀርብ ጥንዶቹ በጋብቻ እንደ ተሳሰሩ ሆነው ይታያሉ፡፡ ሆኖም አብረው መኖር ግን አይችሉም፡፡ አሁን ሙሽራው በጋራ የሚኖሩበትን ስፍራ ለማዘጋጀት ወደ አባቱ ቤት ይመለሳል፡፡ ሙሽራዋም ራሷን እያዘጋጀች በአባቷ ቤት ትቆያለች፡፡ ሙሽራው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ ሙሽራዋን ለማምጣት ወደ አባቷ ቤት ያመራል። በዚህ ወቅት የሠርግ ሥነ ስርዓት ይካሄዳል፡፡

ክርስቶስ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ሰማያዊ ቤቱን ትቶ በምድር ያለችውን ሙሽራ ሊያጭ መጣ፡፡ ለሙሽራዋ መክፈል የነበረበትን ጥሎሽ አስመልክቶ፤ በቀራኒዮ ሕይወቱን ከሰጠ በኋላ ከሙሽራዋ ጋር የሚኖሩበትን “ስፍራ ለማዘጋጀት” ወደ ሰማያዊ አባቱ ቤት ተመለሰ (ዮሐ. 14፡2-3)፡፡ ሙሽራዋም ራሷን እያዘጋጀች በምድር ትቆያለች፡፡ በዘመኑ መጨረሻ ሙሽራው ተመልሶ ይመጣና ወደ አባቱ ቤት ይወስዳታል፡፡ ክርስቶስ የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ልብስ ለሙሽራዋ እንደሰጣት ራእ. 19፡8 ይጠቅሳል፡፡ ይህ ሁኔታ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሠሩትን የጽድቅ ሥራ ከራሳቸው እንደሆነ አድርገው አለመቀበላቸውን ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የለበሱት ልብስ በእነርሱ ውስጥ ከሚኖረው ከክርስቶስ ጋር የፈጠሩት ሕብረት ውጤት የሆነውን “የቅዱሳንን የጽድቅ ሥራ” ይወክላል፡፡ እነዚህ ልብሶች በበጉ ደም ታጥበው ነጽተዋል (ራእ. 7፡14)፡፡ የሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ሠርግን ምሳሌ አድርጎ ብርቱ መልእክት አስተላልፎአል፡፡ አንድ ታላቅ ሠርግ ተደገሰና በሠርጉ እንዲገኙ የታደሙ እንግዶች በሥነ ስርዓቱ ላይ ለብሰው የሚመጡት የሠርግ ልብስ በንገሡ ታደሉ፡፡ ታዲያ በሠርጉ ግብዣ ከተገኙት አንዱ በንጉሡ የተሰጠውን የሠርግ ልብስ ትቶ የራሱን ልብስ ለብሶ በመገኘቱ ከሰርጉ ግብዣ እንዲባረር ተደረገ (ማቴ. 22፡8-11)፡፡

በክርስቶስ የተሰጠው ልብስ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በእጅጉ እንደሚያሻ ራእ. 3፡18 ይነግረናል፡፡ የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ነጭ ልብስ ከእርሱ እንትድገዛ ጥሪ ሲያቀርብላት፤ ለሚሰጣት ነገር በምላሹ ከእርሷ የሚጠባበቀው መኖሩን ያሳያል፡፡ ይኸውም ራሳችንን ብቁ አድርገን ማየትና በሥራችን መመጻደቅ አቁመን የእርሱን የጽድቅ ሥራ ብቸኛው የደኅንነታችን ተስፋ አድርገን መታመን ነው፡፡ እርስዎ የዳኑት በሥራዎ ሳይሆን በክርስቶስ “የጽድቅ ሥራ” መሆኑን የዛሬ ህይወትዎ ምን ያህል ይገልጻል?

መጋቢት 16
Mar 25

የአርማጌዶን ፍጻሜ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 19፡11-16፡፡ የክርስቶስ ስም “የእግዚአብሔር ቃል” (ራእ. 19፡13) በሚል መጠራቱና ስለታም ሰይፍ ከአፉ መውጣቱ ስለ መጨረሻው ጦርነት ባህሪ ምን ይጠቁማል?



እዚህ ላይ በተለያዩ ዘመናት የኖሩ አማኞች አጥብቀው ሲናፍቁት የኖረው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፍጻሜ ሥዕል ቀርቦአል፡፡ መልእክቱ የቀረበበትን ቃና ልብ ብለው ሲያጤኑ በድል አድራጊነት መሞላቱን ያስተውላሉ፡፡ የሱስ ሰይጣንን በሰማይ፣ በምድረ በዳ እና በመስቀል ላይ ድል እንዳደረገው ሁሉ በዳግም ምጽአቱም ድል ይነሳዋል!

“ከዚያም ከሰው እጅ በግማሽ የሚያንስ የሚመስል ጥቁር ደመና በምሥራቅ በኩል ታየ፡፡ አዳኙን የከበበው ደመና ከሩቅ ሲታይ ጥቁርና ጥቅልል ገጽታ ይስተዋልበታል፡ ፡ ሁኔታው የእግዚአብሔር ልጅ መገለጥ ምልክት መሆኑን የእግዚአብሔር ሕዝቦች አውቀዋል፡፡ ከግርጌው በኩል እንደሚባላ እሳት ከአናቱ ደግሞ የኪዳኑ ቀስተ ደመና ግርማ ያለው--ነጩ ደመና እጅግ ግዙፍ እስኪሆን እያደገ፣ በብርሃን እየተሞላና የከበረ እየሆነ ወደ ምድር እየተቃረበ ሲመጣ በተረጋጋ ጸጥታ ይመለከቱታል፡፡ የሱስ እንደ ኃያል ባለ ድል ወደ ፊት ይገሰግሳል፡፡ አሁን የተገለጠበት መንገድ አሳፋሪውን የውርደትና ወዮታ ጽዋ የሚጠጣን ‘የሐዘን ሰው’ ገጽታ የተላበሰ ሳይሆን፤ በሕወት ያሉትንና የሞቱትን የሚፈርድ የሰማይና የምድር ድል አድራጊ ሆኖ ነው፡፡ ‘ታማኝና እውነተኛ’ የሆነው እርሱ ‘በጽድቅ ይፈርዳል ይዋጋልም’፡፡ ‘የሰማይ ሰራዊትም ይከተሉት ነበር’ (ራእ. 19፡11-14)፡፡ መላእክት በታላቅ ሰማያዊ ዜማ አጅበውት በብዙ ሆታና እልልታ ይገለጣል፡፡ ሰማዩ “ቁጥራቸው ሺህ ጊዜ ሺህና እልፍ ጊዜ እልፍ” በሆኑ አንጸባራቂ ቅርጾች ይሞላል፡፡ ይህን ትዕይንት ሰብዓዊው ብዕር ሊገልጸው ከቶ አይችልም፡፡ ውበቱንና ድምቀቱን ሟቹ አእምሮ መረዳት አይሆንለትም፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 641. ጳውሎስ ስለ ዳግም ምጽአቱ የመጨረሻው የክርስቶስ ድል አስመልክቶ በ 2ቆሮ 1፡ 8-10 በሚሰጠን ሌላ መግለጫ፤ በእርሱ ላይ ያሴሩ ዓለማዊና ኃይማኖታዊ ኀይላት በሙሉ ሲወገዱ ሕዝቦቹ ግን ለዘላለም እንደሚድኑ ይነግረናል፡፡

ራእ. 19 በቁ. 9 እንዲሁም 17-18 ስለ ሁለት ዓይነት እራት ይናገራል፡፡ በአንደኛው እራት ተጋባዡ ሲበላ፤ በሌላኛው ግን ራሱ ይበላል፡፡ በታላቁ ቅራኔ ውስጥ የሚኖረው እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ላይ ሊደርስ የሚችለውን በአደጋ የተሞላ ሁናቴ እያነጻጸሩ በዐይነ ህሊና ለማየት መሞከር በራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ተምሳሌታዊ አቀራረብ እምነታችንን እና እምነታችን የሚያቀርብልንን ተልዕኮ ምን ያህል አጥብቀን መያዝ እንዳለብን እንዴት ሊያስተምረን ይገባል?

መጋቢት 17
Mar 26

የሺህ ዓመቱ መንግሥት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 20፡1-3፣ ኤር. 4፡23-26፡፡ በሺህ ዓመቱ ዘመን ምድር በምን ዓይነት ሁናቴ ውስጥ ትቆያለች? ሰይጣን በሰንሰለት የሚታሰረው እንዴት ነው?



1ሺ ዓመቱ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይጀምራል፡፡ በዚህ ወቅት ሰይጣንና የወደቁ መላእክቱ በሰንሰለት ይታሰራሉ፡፡ መናፍስት በእስራት አንድ ቦታ ላይ መገደብ የማይችሉ እንደመሆናቸው የሰይጣን መታሰር ተምሳሌታዊ ነው፡፡ የሰይጣን እስራት በሁናቴዎች ላይ የተገደበ ነው፡፡ የወረዱት መቅሰፍቶች ምድርን ያለ ሰው አስቀርተው ምስቅልቅሏን በማውጣት ከፍጠረት አስቀድሞ ወደ ነበረችበት ሁናቴ መልሰዋታል (ዘፍ. 12)፡፡ ይህ ሁናቴ ምድርን በዚህ አንድ ሺ ዓመት የሰይጣን እስር ቤት ያደርጋታል፡፡ ሰይጣን ሊፈትነው ወይም ሊጎዳው የሚችል አንድም ሰብዓዊ ፍጡር ምድር ላይ አለመኖሩን ተከትሎ እርሱና ዲያብሎሳዊ ማኅበሩ ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር፤ በእግዚአብሔር ላይ የፈጸሙት ዐመጻ ያስከተለውን ውጤት ማሰላሰል ይሆናል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 20፡4-15፡፡ በተጠቀሰው 1ሺህ ዓመት ቅዱሳን ምን ያደርጋሉ?



የእግዚአብሔር ሕዝቦች በዚህ ሺህ ዓመት ክርስቶስ ባዘጋጀላቸው ሰማያዊ ስፍራ እንደሚሆኑ የራእይ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ እንደ ነገሥታትና ካህናት በዙፋኖች ላይ ተቀምጠው ዓለምን ሲዳኙ ዮሐንስ ተመልክቶአል፡፡ “በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ” (ማቴ. 19፡28) ሲል የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቶላቸዋል (ማቴ. 19፡28)፡፡ ቅዱሳን በዓለም ላይ ፍርድ እንደሚሰጡ ጳውሎስ ይናገራል (1ቆሮ. 6፡2-3)፡፡ ይህ ፍርድ የእግዚአብሔርን አሠራር ፍትሐዊነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ሰይጣን በእግዚአብሔር ባህሪና ከፍጥረታቱ ጋር ባለው መስተጋብር ዙሪያ ለረጅም ዘመናት ብርቱ ጥርጣሬ ሲያስነሳ ኖሮአል፡፡ በዚህ ሺህ ዓመት--የጠፉትን አስመልክቶ በአጠቃላይ በእርሱ ፍትሐዊነት ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች እግዚአብሔር የሰጣቸው ውሳኔዎችና በገዛ ህይወታቸው ላይ ከነበረው ምሪት አኳያ ምን ያህል ቅን እንደ ነበር--እያንዳንዷን የታሪክ መዛግብት የሚፈትሹበት ፈቃድ ከእግዚአብሔር ይቀበላሉ፡፡ በእግዚአብሔር ፍትሐዊነት ዙሪያ የሚነሱ ሁሉም ጥያቄዎች በሺህ ዓመቱ መዝጊያ ለዘላለም መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሰረተ ቢስ ከሆኑት የሰይጣን ክሶች የጥርጣሬ ጥላ ባሻገር ማየት የሚችሉ ይሆናሉ፡፡ አሁን እግዚአብሔር በመጨረሻ ላይ ለሚሰጠው ፍትሐዊ አሠራርን ለተከተለ ፍርድ ምስክር ለመሆን እነሆ ዝግጁ ናቸው፡፡ ዛሬ በዚህ ምድር መመለስ የማይችሉ ጥያቄዎች የሌሉን ስንቶቻችን ነን? ይህ--አንድ ቀን ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ስለሚሰጠን ስለ እግዚአብሔር ጸባይ ምን ይነግረናል?

መጋቢት 18
Mar 27

“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር”


ኃጢአት ከተወገደ በኋላ ምድር የዳኑት መኖሪያ ሆና ትለወጣለች፡፡ ለመሆኑ ምን ትመስል ይሆን? ዮሐንስ በራእ. 21፡1 “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማየቱን ይናገራል፡፡ አይሁዳውያን ስለ ሦስቱ ሰማዮች ማለትም፡ ሰማይ፣ ከዋክብት የሚገኙበት ዩኒቨርስ እና የእግዚአብሔር ማደሪያ ስለሆነው ስፍራ ዕውቀት ነበራቸው (2ቆሮ. 12፡2)። በራእ. 21፡1 ምድራዊው ሕዋ ተወስቶአል፡፡ በኃጢአት ብክለት የደረሰበት ይህ ምድር እና ሰማይ የእግዚአብሔርን መገኘት መቋቋም አይችልም (ራእ. 20፡11)፡፡ አዲስ የተሰኘው ቃል ፍቺ የተወሰደው ከግሪክኛው kainos ሲሆን፤ ቃሉ አዲስነትን የሚገልጸው ከዓይነት እንጂ ከሥረ መሰረት እና ከጊዜ አኳያ አይደለም፡፡ ይህች ፕላኔት ከእርኩሰቷ በእሳት ትነጻና ወደ ቀደመ ማንነቷ ትመለሳለች (2ጴጥ. 3፡10-13)፡፡ ሌላው ልዩ ትኩረት የሚያጭረው ነገር በአዲሲቱ ምድር ባሕር አለመኖሩ የተወሳበት ክፍል ነው፡፡ ዮሐንስ ባሕርን የገለጸበት መንገድ የተወሰነ ገላጭ ወይም አንድን ነገር ለይቶ አመላካች ዓይነት ዘይቤን የተከተለ እንደመሆኑ፤ ቃሉን ጥቅም ላይ ያዋለው ምናልባት የመለያየትና የሥቃይ ተምሳሌት የሆነውን፣ የፍጥሞ ደሴት ዙሪያ ገባን የከበበውን ባሕር በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ አለ፡፡ በአዲሲቱ ምድር የባሕር አለመኖር፤ ለእርሱ ያለ ህመም እና ያለ ሥቃይ እንደ መሆን ማለት ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡2-8፣ 7፡15-17፡፡ በአዲሲቱ ምድር እና በዘፍጥረት የኤደን የአትክልት ስፍራ መሃል በቀረበው መግለጫ ምን ዓይነት መመሳሰል እናገኛለን?



የእግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር መገኘት ከሥቃይና ሞት ነፃ ሆና ወደ ቀድሞ ንጽህናዋ የተመለሰችው ምድር ዋስትና የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል። አዲሲቱ የሩሳሌም እግዚአብሔር በሕዝቡ መሃል የሚያድርባት መቅደስ ሆና ቀርባለች (ራእ. 21፡3)የእግዚአብሔር በሕዝቡ መሃል ማደር ወደ ቀድሞ ንጽህናዋ የተመለሰችውን አዲሲቱን ምድር የቤተ መቅደስ ገጽታ ያጎናጽፋታል፡፡ እግዚአብሔር በዚያች አገር ማደሪያውን በማድረጉ የኃጢአት ውጤት የሆኑት፡ እንባ፣ ሞት፣ ሐዘን፣ ልቅሶ ወይም ህመም አይኖርም፡፡ የኃጢአትን መወገድ ተከትሎ “ ‘የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና’ ” (ራእ. 21፡4)፡፡

ይህ ጽንሰ ሀሳብ ግልጽ ሆኖ ከቀረበባቸው መንገዶች አንዱ ማርያምና ማርታ ወንድማቸውን አልዓዛር በሞት ያጡበት ሁናቴ ነበር፡ “‘ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር’ ” (ዮሐ. 11፡21)፡፡ ሞት ክርስቶስ ባለበት ስፍራ መኖር እንደማይችል እህትማማቾቹ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የእግዚአብሔር በአዲሲቱ ምድር መኖር ዛሬ በዚህ ህይወት እየተለማመድን ካለነው ህመምና ሥቃይ እንድንጠበቅ ያደርገናል፡፡ ይህ እንግዲህ በክርስቶስ ደም ታትሞ የተበረከተልን ታላቁ ተስፋችን ነው፡፡

ለመሆኑ ይህ የአዲሲቱ ምድር አዲስ ህይወት ባለቤትነት የአጠቃላይ እምነታችን ማዕከላዊ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? እምነታችን ያለዚህ እውነታ ምን ያህል መልካም ሊሆን ይችል ነበር?

መጋቢት 19
Mar 28

9 አዲሲቱ የሩሳሌም


አሁን ዮሐንስ የአዲሲቱን ምድር ርዕሰ መዲና--አዲሲቱ የሩሳሌም በማለት ሲገልጻት ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ ተጨባጭ ሰዎችና ተጨባጭ ስፍራዎች ቢኖሩም፤ አዲሲቱ የሩሳሌምና በዚያ የሚገኘው ሕይወት ግን ከማንኛውም ምድራዊ መግለጫ ባሻገር ነው 1ቆሮ. 2፡9)፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡9-21፡፡ ለመሆኑ የአዲሲቱ የሩሳሌም ውጪያዊ ገጽታዎች ምን ይመስላሉ?



አዲሲቱ የሩሳሌም እንደ ሙሽራ ማለትም የበጉ ሚስት ሆና ተመስላ ቀርባለች፡፡ ይህ ዘይቤአዊ አቀራረብ በተጨባጭ የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ነው። አዲሲቱ የሩሳሌም ክርስቶስ በስተመጨረሻ ከሕዝቡ ጋር ኅብረት የሚፈጥርባት ስፍራ ትሆናለች፡፡

ከተማዋ የተከበበችው ዐሥራ ሁለት በሮች ባሉት ከፍ ያለ ቅጥር ሲሆን በአራቱም ማዕዘናት ከየትኛውም አቅጣጫ ለመግባት የሚያስችሉ ሦስት፣ ሦስት በሮች አሉ። ይህ ሁኔታ የከተማዋን ዩኒቨርስ አቀፍነት ያመለክታል፡፡ በአዲሲቱ የሩሳሌም ማንኛውም አካል በእግዚአብሔር ሕልዎት ፊት የመቅረብ ያልተገደበ መብት አለው። ከዚህ ባለፈ አራት መአዘን ቅርጽ ያላት ይህች ከተማ 12,000 ምዕራፍ የሚደርስ ርዝመት፣ ስፋትና ከፍታ እንዳላት ቀርቦአል፡፡ 12 መሰረቶች የነበሯት የዚህች ከተማ ቅጥር ስፋት 144,000 ሲሆን ይህ ተምሳሌታዊ ቁጥር በዘመናት የዳኑትን የእግዚአብሔር ሕዝቦች አኻዝ ይገልጻል (ራእ. 7፡4)፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረው የቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ክፍል እኩል በእኩል የሆነ ቅርጽ ነበረው (1ነገሥ. 6፡20)፡፡ በዚህም አዲሲቱ የሩሳሌም እንደ መቅደስ ብቻ ሳይሆን እንደ ቅድስተ ቅዱሳን--አገልግሎት ትሰጣለች፡፡ በቀደመችው ምድራዊ ቤተ መቅደስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ክፍል መግባት የሚችለው ሊቀ ካኅኑ ብቻ ሲሆን፤ በአዲሲቱ የሩሳሌም ግን ይህ ልዩ መብት ለሁሉም የተዋጁ ወገኖች ተሰጥቶአል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡21-22፡5፡፡ የኤደን አትክልት ስፍራን የሚያስታውሶ የትኛው የከተማዋ ውስጣዊ ክፍል ነው? በከተማዋ ከዚህ በኋላ ርግማን እንደማይኖር የመጠቀሱ አንደምታ ምንድን ነው (ራእ. 22፡3)?



ስለ አዲሲቱ የሩሳሌም በተለይ የተገለጸው በእጅጉ ዝነኛ ትዕይንት ከእግዚአብሔር ዙፋን የሚፈልቀው ውሃ ነው (ዘፍ. 2፡10)፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሩሳሌምን እየናፈቁ በግዞተኝነት ከተቀመጡበት የባቢሎን ወንዝ በተቃራኒ (መዝ. 137) እነሆ በዘመናት ሲንከራተቱ የኖሩ ሕዝቦቹ በአዲሲቱ የሩሳሌም የሕይወት ወንዝ ዳርቻዎች መኖሪያቸውን አገኙ፡፡

በወንዙ ግራና ቀኝ የሕይወት ዛፍ የነበረ ሲሆን “የዛፉ ቅጠሎች ሕዝብ የሚፈወስባቸው ነበሩ” (ራእ. 22፡2)፡፡ በአዲሲቱ ምድር ምንም ዓይነት በሽታ እንደ ሌለ ሁሉ ይህ ፈውስ ከበሽታ ጋር ቁርኝት የለውም፡፡ በዘመናት ሰዎችን ሲነጣጥል የኖረ ማንኛውም ግድግዳ ያስከተለው ቁስል ፈውስ ማግኘቱን ይጠቁማል፡፡ ከተለያዩ ዘመናት የመጡ የዳኑ ወገኖች አሁን አንድ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ናቸው፡፡

መጋቢት 20
Mar 29


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “Desolation of the Earth,” pp. 653– 661; “The Controversy Ended,” pp. 662–678, in The Great Controversy. የራእይ መጽሐፍ የሚደመደመው በመግቢያው ላይ በቀረበው መልእክት ሲሆን ይኸውም የክርስቶስን በኃይልና በክብር ዳግም መገለጥና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግሥት መመስረት በማብሰር ነው፡፡ ክርስቶስ በመጨረሻ ከሙሽራው ጋር የሚገናኝበት ዳግም ምጽአት የመጽሐፉ ወሳኝ ክፍል ነው፡፡

ሆኖም መጽሐፉ እነዚህን ክስተቶች ተጨባጭነት ከሌለው ዐውድ አኳያ ማቅረብ አይፈልግም፡፡ ስለዚህ የየሱስ በቅርብ መገለጥ ተቀዳሚ ተጨባጭ እውነታ ነው። ሁለተኛው ተጨባጭ እውነታ ደግሞ የእርሱን መመለስ እየተጠባበቅን አሁን ድረስ በዚህ ምድር መኖራችን ነው፡፡ እርሱን እየተጠባበቅን እያለ የራእይ መጽሐፍ መልእክት ግልጽ ማስተዋል ሊኖረን የግድ ይሆናል፡፡ ይህን ማግኘት የምንችለው ደግሞ የሁሉም ነገር ፍጻሜ እስኪመጣ መጽሐፉን በተደጋጋሚ በማንበብ ነው። ዐይኖቻችን ብቸኛ ተስፋችን የሆነውን እርሱን ከመጠባበቅ ውጪ ወደ ዓለማዊ ነገሮች እንዳያማትሩ የራእይ መጽሐፍ መልእክት ያለማቋረጥ ያሳስበናል፡፡ ምንም እንኳ ሕይወት በምስጢርና እንቆቅልሽ የተሞላች ብትሆንም፤ ነገር ግን የራእይ መጽሐፉ ክርስቶስ የሁሉም ሰብዓዊ ተስፋና መናፈቅ መልስ ነው፡፡ እርሱ የዚህን ዓለም እንዲሁም የእኛን የወደፊት ሁኔታ በእጆቹ ይዞአል፡፡

እንዲሁም መጨረሻው ከመምጣቱ አስቀድሞ በቅርብ የመገለጡን መልእክት ለመላው የምድር ሕዝቦች የማወጅ ኃላፊነት እንደ ተሰጠን መጽሐፉ ያሳስበናል። የእርሱን ዳግም መገለጥ የምንጠባበቀው ተነሳሽነት በጎደለው መንፈስ ሳይሆን በንቁ እንቅስቃሴ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ መንፈስና ቤተ ክርስቲያን “ ‘ና’ ” ይላሉ (ራእ. 22፡17)፡፡ የዚህ ጥሪ አካል መሆናችን የግድ ይሆናል፡፡ ይህ መልካም የምሥራች እንደመሆኑ ለዓለም ሕዝቦች መሰበኩ የግድ ነው፡፡


የመወያያ ጥያቄዎች




1.ስለ ሺህ ዓመቱ እና ከዚያ በኋላ ብቻ ስለሚሆነው ፍርድ ያስቡ። የዳኑት አንድ ሺ ዓመት ከነገሡና ጥያቄዎቻቸው በሙሉ መልስ ካገኙ በኋላ እግዚአብሔር በጠፉት ላይ የመጨረሻውን የቅጣት ብይን መስጠቱ ስለ እርሱ ምን ያስተምረናል?

2.የራእይ መጽሐፍ ትንቢቶችን የሚሰሙ፣ የሚያነቡና የሚጠብቁ በረከት ያገኛሉ ሲል ራእ. 1፡3 ተስፋ ይሰጣል፡፡ የዚህን መጽሐፍ ጥናት ስናጠቃልል--ትኩረት ሊሰጡና ሊጠብቁአቸው እንደሚገቡ ያስተዋሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?