የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከየካቲት 30 - መጋቢት 6

11ኛ ትምህርት

Mar 09 – Mar 15




ሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 15:1፣ 7:1–3፣ 14:9-10፣ 16:1–12፣ 17:1፣ ዳን. 5፣ ራእ. 16:16፣ 2ተሰ. 2:9–12፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-“ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ ስምህን የማያከብርስ ማነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፡፡ የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ’ ” ራእ. 15፡ 4)

“አሕዛብ ተቆጥተው ነበር” በሚል ዓይነት--በእግዚአብሔር ትሩፋን ላይ የመጨረሻውን ጦርነት ለመክፈት የሚደረገውን ዝግጅት ራእ. 11፡18 በአጭሩ ያጠቃልላል፡፡ እግዚአብሔር ንስሐ ባልገቡ ዐመጸኞች ላይ በሰባቱ መቅሰፍቶች አማካይነት በቁጣው ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ እነሆ አሁን ደረሰ፡፡ ራእ. 15 በዚህ መለኮታዊ ቁጣ የተሞሉ ሰባት መቅሰፍቶችን በያዙ ሰባቱ መላእክት ትዕይንት ይጀምራል፡፡ ሆኖም መቅሰፍቶቹ ከመውረዳቸው አስቀድሞ የእግዚአብሔር ታማኞች የትዕይንቱ አካል ሆነው እንመለከታለን (ራእ. 15፡1-4)፡፡ እነዚህ በአውሬውና በምስሉ ላይ ባለ ድል የሆኑ ወገኖች የብርጭቆ በሚመስል ባሕር አጥገብ ቆመው የሙሴንና የበጉን መዝሙር ይዘምሩ ነበር፡፡

ትዕይንቶቹ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ለሰጣቸው ድል በቀይ በሕር ዳርቻ ተሰብስበው የነበራቸውን የደስታና የፍስሐ ጊዜ የሚያስታውስ ዓይነት ነበር (ዘፀ. 15)፡፡ እነዚህ ባለ ድል ቅዱሳን 144,000 በሚል በራእ. 14፡1-5 ከተጠቀሱት ወገኖች ጋር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ የአውሬውን ምልክት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው አውዳሚ ውጤት ካላቸው ሰባት መቅሰፍቶች ተጠብቀው ማለፍ ችለዋል፡፡ የሱስ በኃይልና በክብር ሲገለጥ (1ተሰ. 4፡17) አንቀላፍተው የነበሩ ጻድቃን የማይበሰብሰውን አካል ለብሰው ሲነሱ፣ እነሱም የማይጠፋውን በመልበስ ይለወጣሉ (1ቆሮ. 15፡5154)፡፡

መጋቢት 1
Mar 10

የሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች ፍቺ


በዚህ ወቅት ሰዎች በግል ምርጫና ውሳኔአቸው መሰረት በእግዚአብሔር ወይም በባቢሎን በኩል ቆመዋል፡፡ አሁን ክርስቶስ ዳግም ሊገለጥ ዝግጅቱን ጨርሶአል። ሆኖም ከዚያ አስቀድሞ በመላእክት ተይዘው የነበሩት (ራእ. 7፡1-3) አውዳሚ ነፋሳት አሁን ይለቀቃሉ፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 15፡1፣ ራእ. 7፡1-3፣ ራእ፣ 14፡9-10፡፡ በግብፃውያን ላይ የወረዱት መቅሰፍቶች ከዓላማና ትርጉማቸው አኳያ ለእነዚህኞቹ እንደ መነሻ መታየት ይችላሉ?



ሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች ከሰባቱ የመለከት ድምፅ መቅሰፍቶች በኋላ ስለሚመጡ “የመጨረሻዎቹ” በሚል ይታወቃሉ፡፡ መለከቶቹ መላውን የክርስትና ዘመናት አጠቃልለው የሚሸፍኑ ሲሆን የያዙት ዓላማና ጽንሰ ሃሳብም ውሱን ነው። በሥራ ላይ እንዲውሉ የሆኑት ወንጌል እየተሰበከና (ራእ. 10፡8፣ 11፡14) የማማለድ ሥራም እየተሠራ ባለበት ወቅት ነው (ራእ. 8፡2-5)፡፡ ከምኅረት ጋር የተቀላቀሉ በመሆናቸው ዓላማቸው ለእግዚአብሔር ጠላት የሆኑ ሕዝቦችን ወደ ንስሐ ማምጣት ነው፡፡

በሌላ በኩል የመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሰፍቶች የሚወርዱት ከዳግም ምጽአቱ ጥቂት ጊዜያት ብቻ ቀደም ብለው ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹ ዓለማቀፋዊ ስርጭት ስለሚኖራቸው ምድርን በሙሉ ይመታሉ፡፡ ልቦቻቸውን እንደ ፈርዖን አደንድነው ወደ ንስሐ ለመምጣት አሻፈረኝ ባሉ ላይ ይወርዳሉ (ራእ. 16፡11)፡፡ የሰዎችን ምርጫ ትከትሎ መለኮታዊው ቁጣ ሲወርድ (ሮሜ 1፡26-28)፤ የጠፉትም የገዛ ምርጫቸው ያስከተለውን ውጤት ለማጨድ ይገደዳሉ፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 15፡5-8፣ ዘፀ. 40፡34-35፣ 1ገሥ. 8፡10-11፡፡ “ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም” የሚለው ሃረግ ስለ መጨረሻዎቹ ሰባት መቅሰፍቶች ምን ይናገራል?



“ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም” (ራእ. 15፡8) በሚል የቀረበው አገላለጽ የምኅረትን በር መዘጋት ያመለክታል፡፡ የክርስቶስ ሰማያዊ የምልጃ አገልግሎት ወደ ፍጻሜ ሲመጣ፤ ወደ ንስሐ መግቢያው ምቹ ጊዜ ያበቃና የምኅረት ደጃፍ ይዘጋል፡፡ የመጨረሻዎቹ መቅሰፍቶች ማንንም ወደ ንስሐ አያመጡም፡፡ ይልቁንም ከባቢሎን ጎን ለመቆም የመረጡትን ልብ እያደነደኑ ከቀድሞው በበለጠ እግዚአብሔርን እንዲጠሉ ይገፋፋሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰባት ያለችውን የዛሬዋን ዓለም ይመልከቱ፡፡ ዛሬ ድረስ የዘገዩት መቅሰፍቶች ስለ አምላካዊው ምኅረትና ትዕግሥት ምን ያስተምሩናል?

መጋቢት 2
Mar 11

የመጨረሻዎቹ መቅሰፍቶች መውረድ


ክርስቶስ በሰማያዊው መቅደስ የሚሰጠውን የምልጃ አገልግሎት ሲያቋርጥ የእያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታ ባለበት ለዘላለም ተወስኖ ይቀራል፡፡ ወንጌልን በጥላቻ ያሽቀነጠሩ ሁሉ አምላካዊውን ቁጣ በሙላት የሚቀምሱበት እነሆ ጊዜው ደረሰ፡፡ ሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች በግብፃውያን ላይ ወርደው የነበሩትን መቅሰፍቶች የሚያሳዩ መስታወት ናቸው (ዘፀ. 7-11)፡፡ መቅሰፍቶቹ እስራኤላውያንን ሳይነኩ በግብፃውያን ላይ ግዙፍ ጉዳት እንዳደረሱ ሁሉ፤ ከእነዚህ የመጨረሻ መቅሰፍቶች መሃል የመጀመሪያዎቹ አራቱ--እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ወገኖችን ዘልለው ለአውሬው የሚሰግዱት ላይ ጉዳት ማድረስ ተቀዳሚ ተግባራቸው ይሆናል፡፡ በግብፅ ላይ የወረዱት መቅሰፍቶች የፈርዖንን ልበ ደንዳናነትና ግብፃውያን ያመልኳቸው የነበሩ አማልክትን ከንቱነት ገልጠው ያሳዩ ነበሩ፡፡

በተመሳሳይ የመጨረሻዎቹም መቅሰፍቶች ለአውሬው የሚሰግዱ ሕዝቦችን ልብ ይበልጥ እንዲደነድን ከማድረጉ በተጨማሪ ባቢሎን ከመለኮታዊው ፍርድ ልትከላከልላቸው የሚያስችል አቅም እንደሌላት የሚገልጥ ይሆናል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡1-11፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው? ክስተቱ የቀረበበት ትዕይንት ምን ይመስላል?



የመጀመሪያዎቹ አራት አምላካዊ ቁጣዎች ወይም መቅሰፍቶች መላውን የምድር ሕዝብ ይመታሉ፡፡ የመጀመሪያው መቅሰፍት የአውሬውን ምልክት በተቀበሉና ለምስሉም በሰገዱ ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚያሠቃይ ቁስል እንዲወጣባቸው መንስኤ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው እና ሦስተኛው መቅሰፍቶች ደግሞ ባሕሩን፣ ወንዞችንና ምንጮችን ወደ ደም በመቀየር ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የሚጠጣ ውሃ በሌለበት ሁኔታ ዐመጸኛው ሰብዓዊ ዘር መኖር አይችልም፡፡ አራተኛው መቅሰፍት በፀሐይ ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ሰዎች ሊቋቋሙት በማይችሉት ንዳድ ይመታሉ፡፡ በመቅሰፍቶቹ የተነሳ የሚደርሱ ክፉኛ የሚያሠቃዩ ህመሞች፤ ከዐመጻ አስተሳሰባቸው ይመለሱ ዘንድ የሰዎችን ልብ አያለሳልሱም፡፡ ይልቁንም መቅሰፍቶቹን ያወረደውን እግዚአብሔር ይሳደባሉ፣ ይራገማሉም፡፡ አንዳቸውም ቢሆኑ ወደ ንስሐ አልመጡም፡፡

አምስተኛው መቅሰፍት--ራእ. 16፡10-11 (ዘፀ. 10፡21-23) የአውሬውን ዙፋን መምታቱን መመልከት እንችላለን፡፡ እዚህ ላይ ሰይጣን የራሱን ዙፋን ለአውሬው ሰጥቶት እንደ ነበር ልብ ይሏል (ራእ. 13፡2)፡፡ አሁን ሰይጣን በኃይል የሚቀመጥበት ዙፋን ሳይቀር እነዚያን የሚወርዱ መቅሰፍቶች መቋቋም አልተቻለውም፡፡ ሰዎች ብርቱ ህመም የሚያስከትል ሥቃይ ሲደርስባቸው ባቢሎንን እንደ ጥላ ከለላ ተመልክተው ነበር፡፡ ሆኖም በእግዚአብሔር ላይ ክፉኛ በመታበያቸው እነዚያ የሚወርዱ አሰቃቂ መቅሰፍቶችም እንኳ ልቦቻቸውን መለወጥ አልቻሉም፡፡ አሳዛኝ ክስተት ደርሶ በሥቃይ ውስጥ የምንወድቅበት አጋጣሚ ሊፈጠር ቢችል እንኳ--ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እርግጠኞች ሆነንና በእርሱ ታምነን ከጌታ ጋር ያለን ቅርበት እንደ ተጠበቀ መራመድ የምንችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 3
Mar 12

የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡12፣ 17፡1፣ 15፡፡ ኤፍራጥስ የምን ተምሳሌት ነው? የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ ከሰባቱ የመጨረሻ መቅሰፍቶች ዐውድ ምን ያመለክታል?



በብሉይ ኪዳን ዘመን የኤፍራጥስ ወንዝ የእስራኤል ጠላቶች ለነበሩት ባቢሎን እና አሦር ወሳኝ ጉልበት ነበር (ኢሳ. 7፡20፣ ኤር. 46፡10)፡፡ ባቢሎንን አቋርጦ የሚፈሰው የባቢሎን ወንዝ የተዘራውን የሚያጠጣና ለሕዝቡም ዋንኛ የውሃ አቅርቦት ምንጭ ሆኖ በማገልገሉ ለከተማዋ በእጅጉ መሰረታዊ ነበር፡፡

በዘመኑ መጨረሻ ላይ የምትገኘውን ባቢሎን ራእ. 17፡1 በብዙ ውሆች ላይ እንደተቀመጠች አድርጎ የሚገልጻት ምናልባት ኤፍራጥስን እንደ ማመሳከሪያ በማቅረብ ሊሆን ይችላል (ኤር. 51፡13)፡፡ የመጨረሻው ዘመኗ ባቢሎን መኖሪያዋ የሆነው ብዙ ውሃ--አቅፎና ደግፎ የያዛትን ሕዝብ፤ ይኸውም የተቋሟ ደጀን የሆነውን በዓለም ዙሪያ የሚገኝ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ኃይል ይወክላል፡፡ የሆነው ሆኖ እነዚህ ኃይላት ኋላ ላይ የቀድሞ ድጋፋቸውን ያቋርጣሉ፡፡ የስድስተኛው መቅሰፍት ትዕይንት የጥንታዊው ባቢሎንን በሜዶንና ፋርስ ምርኮ ስር መውደቅ ያንጸባርቃል (ዳን. 5)፡፡ እንደ የጥንቱ የታሪክ ጸሐፊ ሔሮዱተስ ዘገባ ከሆነ፡ ንጉሥ ቤልሻጽር ለሺህ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ ባደረገበት በዚያ የፈንጠዝያ ምሽት የፋርስ ሰዎች የኤፍራጥስ ወንዝ የሚፈስበትን ሸለቆ ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት ሳይታሰብ ከመዳፋቸው አስገቧት፡፡

በራእ. 16፡12 የቀረበው የተምሳሌታዊው ኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ በመጨረሻ ዕውን የሚሆነውን የባቢሎን ውድቀት ያስከትላል፡፡ በራእይ መጽሐፍ የቀረበው የኤፍራጥስ ወንዝ የዓለም መንግሥታትና ፖለቲካዊ ኃይላት ለባቢሎን የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚወክል ሁሉ፤ የወንዙ መድረቅ የድጋፋቸው መቋረጥና የተቋሟ መገርሰስ ተምሳሌት ነው፡፡ በተፈጥሮአዊው ምስቅልቅል ሥቃይ ውስጥ የወደቁት የዓለም ሕዝቦች (ራእ. 16፡10-11) ከለላ ፍለጋ ፊታቸውን ባቢሎን ላይ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም አምስተኛው መቅሰፍት የባቢሎንን ዙፋን እንደ መታ ሲገነዘቡ እቅዳቸው ከንቱ መሆኑን ይገነዘባሉ፡፡ በባቢሎን መታለላቸው የተሰማቸው እነዚህ ሕዝቦች በእርሷ ላይ ይነሱባታል (ራእ. 17፡16)፡፡ ይህም ቢሆን ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው ልባቸው በእግዚአብሔር ላይ እንደ ደነደነ ይቀራል፡፡ ይህ ሁኔታ ዓለምን ከእግዚአብሔር ጋር ለፍልሚያ ለሚያነሳሳው ለመጨረሻው የሰይጣን ማታለያ ምቹ አድርጎ ያዘጋጃቸዋል፡፡

መታመናችንን በሰዎችና በሰብዓዊ ተቋማት ላይ ማድረጋችን ምን ያህል አደጋ እንዳለው አስመልክቶ ያገኙት ትምህርት ምን ይመስላል?

መጋቢት 4
Mar 13

ታላቁና የመጨረሻው የሰይጣን ማሳቻ


የኤፍራጥስን ወንዝ የደረቀበት ምክንያት “ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው” መሆኑን ራእ. 16፡12 ይነግረናል፡፡ በብሉይ ኪዳን “የምሥራቅ ነገሥታት” ከምሥራቅ በኩል በባቢሎን ላይ የሚመጡ የቂሮስና የእርሱ ኃይሎች ናቸው (ኢሳ. 41፡25)፡፡ የእነርሱ ባቢሎንን በቁጥጥር ስር ማዋል የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲገቡ አስችሎአቸዋል (ኢሳ. 44፡27-28)፡፡ በተመሳሳይ የተምሳሌታዊው ኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ዘመን ሕዝቦች ለመታደግ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገዱን የሚጠርግ ይሆናል፡፡

በራእ. 16፡12 የቀረቡት ከምሥራቅ የሚመጡ ነገሥታት፤ ክርስቶስ እና የእርሱ ታማኝ ሰራዊት ናቸው፡፡ የሱስ በሰማይ መላእክት ታጅቦ ዳግም በሚገለጥበት ጊዜ የመጨረሻው ውጊያ በክርስቶስ ታማኝ ትሩፋንና በሰይጣን መካከል እንደሚደረግ ራእ. 17፡14 ያሳየናል፡፡ በራእ. 19፡14 እንደ ቀረበው የበጉ ልብስ የሆነውን (ራእ. 19፡8) “ነጭ፣ ንጹህና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ” የለበሱ የሰማይ ሰራዊትን የሱስ ይመራል፡፡ በራእ. 7 በተጓዳኝ በምድር የሚገኘው 144,000 ሰራዊት ለመጨረሻው ውጊያ መዘጋጀቱ ተመልክቶአል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡13-14፡፡ ለመጨረሻው ውጊያ በሚደረገው ዝግጅት የሦስቱ እንቁራሪት መሳይ እርኩሳን መናፍስት ሚና ምንድን ነው? በራእ. 14 ለቀረበው የሦስቱ መልእክት መለእክት ሐሳዊ የአጸፋ ምላሽ የሚሆኑት እንዴት ነው?



የኤፍራጥስ መድረቅ በሰይጣናዊው ሦስትዮሽ አካል ላይ መናወጥ ይፈጥራል። በዚህ ወቅት እንቁራሪት የሚመስሉ ሦስት እርኩሳን መናፍስት ከአፉ እንደ ወጡ ዮሐንስ ተመልክቶአል፡፡ በግብፃውያን ላይ ወርደው በነበሩት መቅሰፍቶች፤ እንቁራሪት የፈርዖን አስማተኞች አስመስለው ማድረግ የቻሉት የመጨረሻው ሙከራቸው ነበር (ዘፀ. 8፡1-15)፡፡ በተመሳሳይ እነዚህ ሦስት እርኩሳን መናፍስት ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ አስመስሎ የሚሠራበት መጨረሻ ሙከራው ይሆናል፡፡ ከሰይጣናዊው ሦስትዮሽ አካላት “አፍ” የሚወጡት ሦስቱ እርኩሳን መናፍስት የሰይጣንን የመጨረሻ ስልት ይወክላል፡፡ ሰይጣን የሙታን መንፈስ እንጠራለን የሚሉን አካትቶ ማንኛውንም ትኩረት በግ ወደሚመስለው አውሬ (ራእ. 13፡1314) የሚስብ ታምራዊ ምልክቶችን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል፡፡ ዓለም በእውነተኛው አምላክ ምትክ እርሱን እንዲያምንና እንዲከተል ከሚጠቀማቸው የመጨረሻው ዘመን ስልቶች አንዱ ታምራዊ ምልክቶች ይሆናሉ (2ተሰ. 2፡9-12)፡፡ እንቁራሪት የሚመስሉት እርኩሳን መናፍስት የተላኩት ከሐሰተኛው ወንጌል ሲሆን ይኸውም በእግዚአብሔር ላይ ለሚደረገው ውጊያ ዓለምን ለማነሳሳት ነው፡፡ ምንም እንኳ ሁኔታው የዓለም መሪዎችን ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ውስጥ ቢከትም ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ጀርባቸውን ሰጥተው ከሰይጣን ጋር ግንባር ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ ወቅት ይህንን ምድር ወደ ፍጻሜ ለሚያመጣው የመጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነት መድረኩ ይመቻቻል፡፡

መጋቢት 5
Mar 14

ለመጨረሻው ጦርነት መሰብሰብ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 16፡16፡፡ ሰይጣን የዓለምን ሕዝቦች አስቶ ለውጊያ በአርማጌዶን በመሰብሰቡ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል?



አሳቾቹ የክፉ መናፍስት ታምራቶች ዓለማቀፋዊ ስኬት ያስገኛሉ፡፡ ሰዎች እውነተኛውን ወንጌል እየጠሉ በሐሰተኛ ታምራቶች የተደገፈውን ሽንገላ ያምናሉ። በዕብራውያን ቋንቋ አርማጌዶን ወይም የመጊዶ ተራራ በመባል በሚታወቀው ተምሳሌታዊ ስፍራ በአንድነት ይሰበሰባሉ፡፡ በኢይዝራኤል ሸለቆ በቀርሜሎስ ተራራ ግርጌ ጉብታ ላይ ይገኝ የነበረው የምሽግ ከተማ--መጊዶ አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ገዢ ስፍራ ነበር፡፡ በእስራኤላውያን ታሪክ ይህ ስፍራ አያሌ ወሳኝ ውጊያዎች ተካሂደውበታል (መሳ. 5፡19፣ 6፡33፣ 2ነገሥ. 9፡27፣ 23፡29-30) የራእይ መጽሐፍ አርማጌዶን በመባል የሚታወቀውን ይህን በእግዚአብሔርና በክፉ ኃይላት መካከል የሚደረገውን የመጨረሻ ታላቅ ፍልሚያ ለማሳየት ይህን ጭብጥ ጥቅም ላይ ሲያውል ይስተዋላል፡፡ የዓለም ሕዝብ በሰይጣን ሕብረት መሪነት ስር ውህደት የፈጠረ ሰራዊት ሆኖ ቀርቦአል፡፡

ቀርሜሎስ ተራራ የሚል አንደምታ ሊኖረው የሚችለው መጊዶ ተራራ መገኛ ከከተማዋ አጠገብ ነበር፡፡ ስፍራው የነቢዩ ኤልያስንና ስንና በዓልን ተግዳሮት ጨምሮ (1ነገሥ. 18) በእሰራኤል ታሪክ እጅግ ወሳኝ ውጊያዎች ከተካሄዱባቸው ዐውደ ግንባሮች አንዱ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ጉዳዩ የሚያጠነጥነው በእውነተኛው አምላክ ማንነት ጥያቄ ዙሪያ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከሰማይ የወረደው እሳት ጌታ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑንና እርሱ ብቻ በብቸኝነት መመለክ እንዳለበት ያሳየ ነበር፡፡

ከምድር የወጣው አውሬ የእግዚአብሔርን ሥራ አስመስሎ እሳት ከሰማይ በማውረድ መላውን የዓለም ሕዝብ እንደሚያስት ራእ.13፡13-14 ግልጽ አድርጎ ያስቀምጥልናል፡፡ አርማጌዶን በአንድ የሆነ የመካከለኛው ምሥራቅ ግምባር የሚደረግ ወታደራዊ ውጊያ ሳይሆን በክርስቶስና በጨለማ ኃይላት መካከል ተግባራዊ የሚሆን መንፈሳዊ ውጊያ ነው (2ቆሮ. 10፡4)፡፡ በዚህ የመጨረሻ ውጊያ በዩኒቨርስ ሕጋዊ ገዢነት ዙሪያ የሚነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ያገኛል፡፡ የመጨረሻውን ውጊያ ተከትሎ የሚመጣው ውጤት በቀርሜሎስ እንደሆነው--ውሎ አድሮ እግዚአብሔር በጨለማ ኃይላት ላይ አሸናፊነቱ የሚረጋገጥበት ይሆናል፡፡

ብዙዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚስተዋለውን የማያባራ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውጥንቅጥ የመጨረሻው ብሎም የአርማጌዶን ፍጻሜ ምልክት አድርገው ሲመለከቱ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ በአርማጌዶን ዙሪያ ብዛት ያላቸው ትንቢቶች ቢነገሩም፣ ቀናት ቢቆረጡም ነገር ግን አንዱም አልሰመረም፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን አንድን አካባቢ ያማከሉ ክስተቶች እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት ፍጻሜ አድርጎ ፍቺ ከመስጠት ተመሳሳይ ስህተት እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

መጋቢት 6
Mar 15


ተጨማሪ ሀሳብ


“አስደናቂ ታምራቶችን በሚያደርጉ ክፉ መናፍስት ፊታዉራሪነት አውራሪነት ልዕለ ተፈጥሮ ባህሪ ያላቸው አስፈሪ ክስተቶች በቅርቡ በሰማያት ይገለጣሉ፡፡ የዲያብሎስ መናፍስት በአሳች ማማለያ ሊተበትቧቸው ወደ ምድር ነገሥታት ብሎም መላው የዓለም ሕዝብ በማምራት፤ ሰይጣን በሰማይ መንግሥት ላይ ለሚያደርገው የመጨረሻ ትንቅንቅ ከእርሱ ጋር እንዲያብሩ ይገፋፏቸዋል። ገዢዎችም ሆኑ ተገዢዎች በእነዚህ ወኪሎች ተመሳሳይ መታለልው ውስጥ ይወድቃሉ. . .

“ታላቁ ሕዝቦችን የማሳት ድራማ የመጨረሻው ከፍታ ሰይጣን ክርስቶስን ተመስሎ መምጣቱ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተስፋዋ ፍጻሜ የሆነውን የአዳኙን ዳግም ምጽአት ለረጅም ዘመናት ስትጠባበቅ ኖራለች፡፡ አሁን ታላቁ አሳች ክርስቶስ ዳግም እንደ ተገለጠ አድርጎ ምድራዊ ድራማውን ያቀናብራል፡፡ ሰይጣን በዮሐንስ ራእይ በቀረበው የእግዚአብሔር ልጅ መግለጫ መሰረት በድምቀት የሚያበራ የፀሐይ ገጽታን ተላብሶ በተለያዩ የምድር ክፍሎች ይገለጣል፡፡ ዙሪያውን የሚከብበው ክብርና ውበት ሟቹ ሰብዓዊ ዐይን ከተመለከተው ሁሉ በእጅጉ የላቀ ይሆናል፡፡ የሰማዩ አድማስ “እነሆ ክርስቶስ መጣ! ክርስቶስ መጣ!” በሚል በድል አድራጊነት የተሞላ እልልታ ዳር እስከ ዳር ያስተጋባል፡፡ ሰዎች ለእርሱ አክብሮት በመስጠት ከፊቱ ይነጠፋሉ. . . በተረጋጋና ርኅራኄ በተሞላው ድምፀት አዳኙ ተናግሮአቸው የነበሩ ደርባባ ሰማያዊ እውነቶችን ይናገራል፡፡

የታመሙትን ይፈውሳል፣ እንዲሁም የክርስቶስን ባህሪ የተላበሰ በሚመስል ሁኔታ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ወደ እሁድ መለወጡን ይናገራል፡፡ እርሱ የባረከውን ይህን ቀን ሰው ሁሉ እንዲቀድሰውም ያዛል፡፡ ሰባተኛውን የሰንበት ቀን በቅድስና በመጠበቅ የሚጸኑ በብርሃንና በእውነት ወደ እነርሱ የተላኩ መላእክቱን ለመስማት በመቃወም የእርሱን ስም እንደሚሳደቡ ይፋ ያደርጋል፡፡ ይህ እጅግ የበረታና በብርቱ ኃይል አእምሮን መቆጣጠር የሚችል ማታለያ ነው፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 624.


የመወያያ ጥያቄዎች




1.የሱስ ለአርማጌዶን ውጊያ ስለሚደረግ ዝግጅት በራእ. 16፡15 የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ያንብቡ፡፡ ክርስቶስ ቀደም ሲል ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ተማጽኖ በጥንቃቄ ይመልከቱ (ራእ. 3፡18)፡፡ ለመጨረሻው ውጊያ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ለሚኖሩ ማለትም ለሎዶቅያ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይህ መልእክት ያለው አንደምታ እንዴት ይታያል? መልእክቱ ከእርስዎ የግል ሁኔታ ጋር መገናዘብ የሚችለው እንዴት ነው?

2.በራእይ መጽሐፍ ነጭ ልብስ የክርስቶስን ጽድቅ ያመለክታል (ራእ. 3፡ 4-5፣ 19፡7-9)፡፡ በመጨረሻው አሰቃቂ ወቅት ጸንተው መቆም የሚችሉ የክርስቶስን ጽድቅ የሚለብሱ ብቻ ይሆናሉ፡፡ አንድ ሰው በበጉ ደም ልብሱን ማንጻት የሚችለው እንዴት ነው (ራእ. 7፡14)?