የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ነሐሴ 19-25

ዘጠነኛ ትምህርት

Aug 25- 31


የጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ፡- ሐዋ. ሥራ 16፤ ሮሜ 3፡ 28፤ ገላ. 2፡16፤ሐዋ፣ ሥራ 17፤ 1ኛቆሮ.1፡23፤ ሐዋ18፡1-10፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ፡-<<አትፍራ ተናገር ዝምም አትበል እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም በአንተ ላይ ተነስቶ ሊጎዳህ አይችልም፡፡ በዚህ ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና ፡፡>> (ሐዋ. ሥራ 18፡9-10)

ወ ደ አንጾክያ ስንመለስ ጳውሎስና በርናባስ ቤተክርስትያንን በቃሉ እያበረታቱና የበለጠ ወንጌልን እየሰበኩ እናገኛቸዋለን፡፡ ከፍተኛ የሆነ አለመስማማት ወደ መለያየት ሲመራቸው ላየ ይህ በአብሮነት የሰሩበት የመጨረሻ ጊዜያቸው ይመስለዋል፡ ፡ የጳውሎስና በርናባስ አለመስማማት ምክንያቱ ማርቆስ ነበር፤ እርሱም የበርናባስ የወንድሙ ልጅ ነበር፡፡ (ቆላ.4፡10) ጳውሎስ ቀድሞ በወንጌል ወደ ደረሱበት ስፍራ በርናባስ እንዲመጣ ሲጋብዘው በርናባስ ግን የወንድሙን ልጅ አብሮት ሊወስደው ፈለገ፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ማርቆስ በፊት የሠራውን ስህተት በማንሳት ሃሳቡን ተቃወመው (ሐዋ.ሥራ 13፡13)፡፡ የጳውሎስና በርናባስ መለያየት ግን ወደ ባርኮት ተለወጠ፡፡ ምክንያቱም በመለየየታቸው የተነሳ አስቀድመው ካቀዱት በላይ ሰፊ የሆነ ስፍራን ማካለል ችለዋልና፡፡ በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደቆጵሮስ ተመለሰ፤ ይህም ስፍራ በርናባስ ያደገበት ስፍራ ነበር (ሐዋ. ሥራ4፡36)፡፡ በዚህ ጊዜም ጳውሎስ ሲላስን ወደርሱ እንዲመጣ ጠራውና ወደ ቂሳርያ እና ወደ ኬልቂያ ሄደ በዛም ቤተክርስትያንን አጠናከረ፡፡ ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ለመጀመርያ ጊዜ ከመምጣቱ በፊት በጠርሴስ ለአያሌ አመታት ቆይቷል (ሐዋ. ሥራ9፡30፣11፡25-26)፡፡ አሁን ደግሞ የመሰረተውን ህብረት ዳግም የመጎብኘት እድል አገኘ፡፡ ያም ቢሆን ግን የእግዚአብሔር እቅድ ጳውሎስ አስቀድሞ ካቀደው እቅድ እጅጉን የላቀ ነበር ፡፡

የዚህን ሳምንት ትምህርት አንብበው ለ ነሐሴ 26 ሰንበት ይዘጋጁ::

ነሐሴ 20
Aug 26

ወደልስጥራ መመለስ


ሉቃስ መርጦ ከፃፋቸው ክስተቶች መካከል የጳውሎስ ወደ ልስጥራና ደርቤ የመመለስ ታሪክ ነው፡፡ ስለ ሶርያ እና ኬልቅያ የነገረን ነገር ቢኖር ጳውሎስ በእነዚህ ስፍራዎች ሲያልፍ ቤተክርስትያንን ያበረታታ እንደነበር ብቻ ነው (ሐዋ. ሥራ 15፡41)፡፡ ሐዋ. ሥራ 16፡1-13 ያንብቡ፡፡ ሌሎችን ለመድረስ ጳውሎስ ያለው ግለት ለኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጢሞቴዎስ አባት አህዛብ ቢሆንም እናቱ ግን አይሁዳዊ ሆና በጌታ ያመነች ነበረች፤ ስሟም ኢዩኒስ ነበር፡፡ ጢሞቴዎስ ምንም እንኳን ቢገረዝም ከልጅነቱ ጀምሮ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ያውቃል (2ኛጢሞ. 3፡15) ሃይማኖተኛ ሰውም ነበር፡፡ እንደ ክርስትያንነቱ በአካባቢው ያሉ አማኞች የሚያከብሩትና የሚያደንቁት ነበር፡፡ አይሁዶች በእናቱ በኩል አይሁዳዊ ስለሆነ አይሁዳዊ አድርገው ቆጠሩት፡፡ ስለዚህ ጢሞቴዎስ አይሁዳዊ ነው፡፡ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ግን አልተገረዘም፡፡ አባቱ ግሪካዊ ስለነበር ግርዘት ኋላ ቀር ስርአት ነው ብሎ አስቦ ነበር፡፡

ጳውሎስጢሞቴዎስ የስራ አጋሩ እንዲሆን ቢፈልግም ያልተገረዘ አይሁዳዊ በመሆኑ በምኩራብ ህግ መሠረት ወደ ምኩራብ መግባት ስለማይፈቀድለትእንዲገረዝ አደረገው፡፡ ጳውሎስ ይህንን ያደረገበት መነሻ ሃሳቡ ተግባራዊ መሆን ያለበት እንጂ ከሚሰብከው የወንጌል ስብከት ተቃራኒ እንደ ሆነ ሊታሰብ አይገባም፡፡

ጳውሎስ በመጀመርያ ጉዞው ያያቸውን ስፍራዎች ደግሞ ሲጎበኝ ሳለበደቡብ ምእራብ አቅጣጫ ወደሚገኘውና የእስያ አውራጃ ክፍል ወደሆነው ስፍራ ለመሄድ ወሰነ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ይህንን እንዳያደርግ ከለከለው፡፡ ስለዚህም ወደ ሰሜን ተጓዘና ወደቢታንያ ለመድረስ ሞከረ፡፡ ነገር ግን አሁንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ወደዛ ስፍራ እንዳይሄዱ መንፈስ ቅዱስ ከለከላቸው፡፡ በሚስያ እያለፈ ባለበት ሰዓት የጳውሎስ ብቸኛ አማራጭ የነበረው ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የመርከብ ወደብ ወደ ሆነቸው ወደ ጢሮአዳ መሄድ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ወደ ብዙ አቅጣጫዎች መሄድ ይችላል፡፡ በሌሊት ራዕይ ግን እግዚአብሄር ባህሩን አቋርጦ ወደ መቄዶንያ እንዲሄድ አሳየው፡፡ ስለ ራእዩ አብረውት ያሉ ሰዎች ሲወያዩ የደረሱበት ድምዳሜ እግዚአብሄር ወንጌልን ለመቄዶንያ ሰዎች እንዲያካፍል እንደጠራው ነው፡፡ ጳውሎስ ለምን ጢሞቴዎስን እንደገረዘው እስቲ ያስቡ፡፡ እኛ የማንስማማባቸውን አንዳንድ ነገሮች ወይም አስፈላጊ አይደሉም የምንላቸውን ነገሮች በማድረግ ትልቅ ተጽእኖ ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን መፍጠር እንደምንችል ይህ እንዴት ያስተምረናል?

ነሐሴ 21
Aug 27

ፊሊጵስዮስ


ጳውሎስና አጋሮቹ መቄዶንያ ሲደርሱ በአውሮፓ የመጀመርያውን የክርስትያን ህብረት ወደ መሰረቱበት ወደ ፊሊጵስዮስ ተጓዙ፡፡ ሐዋ.ሥራ 16፡11-24ን ያንብቡ፡፡ እነዚህ ሚሽነሪዎች በሰንበቱ ቀን ወዴት ሄዱ? ለምን? በዛ ስፍራስ ምን ሆነ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ወደ ከተማ በደረሰ ቁጥር ልምዱ በአካባቢው የሚገኘውን ምኩራብ በሰንበት ቀን በመጎብኘት ለአይሁዶች መመስከር ነበር (ሐዋ. ሥራ13፡14፣42-44፣17፡1-2፣18፡ 4)፡፡ በፊሊጲስዮስ እርሱና የእርሱ ቡድኖች(አይሁድና አህዛብ ከሆኑ ሴቶች ጋር) ለመፀለይ ወደ ወንዝ ዳርቻ ሄዱ፡፡ ምናልባትም በከተማው ምኩራብ የለም ይሆናል፡ ፡ የዚህ ኃሳብ አስፈላጊነት ጳውሎስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ የሚሄደው በወንጌል አላማ ብቻ ሳይሆን ቀኑ የአምልኮ ቀን ስለሆነ ለማምለክ ጭምር ነበር፡፡ ሐዋ. ሥራ16፡25-34ን ያንብቡ፡፡ ስለ ወህኒ ቤቱ ጠባቂ መለወጥ እያሰላሰሉ፣ ለመዳን ምን ማድረግ ይጠበቅበት እንደነበር ያስቡ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለወህኒ ቤቱ ጠባቂ ጳውሎስና ሲላስ የመለሱት ምላሽ ከወንጌል ኃሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ ነው፡፡ ምክንያቱም መዳን የሚገኘው ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በማመን ነውና (ሮሜ 3፡28፣ገላ.2፡16)፡፡ ከዚህ ክፍል በመነሳት መደምደም የማንችለው ነገር ቢኖር ለመጠመቅ ሌሎቹን መሠረታዊ አስተምህሮዎችና ተግባር ተኮር መመሪያዎች ትቶ በየሱስ ማመን ብቻ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

ስለ ወህኒ ቤቱ አለቃ ምን የምናውቀው ነገር አለ? አይሁዳዊ ነው ወይስ ከአይሁድነት የተቀየረ? የትኛውንም ቢሆን የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ኢየሱስን ጌታና አዳኝ አድርጎ ማመን ነው፡፡ አህዛብ ሆኖ ልክ አንደ ቆርኔሌዎስ፣ ሊዲያና ሌሎች እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሚያመልክ የነበረስ ቢሆን? ቀደም ብሎ በከተማው ውስጥ ጳውሎስ ያስተማረባቸው ስብሰባዎች ላይ ተገኝቶ የነበረስ ቢሆን? እርሱ ማንም ቢሆን ስለርሱ የተፃፈው ነገር ማጠሩ በደንብ ሳይማሩ በአጭር ጊዜ ለመጠመቅ ሰበብ ሊሆን አይገባውም፡፡

ሐዋ16፡31-34ን ያንብቡ፡፡ ይህ ክፍል የክርስቶስ መስዋዕትነት ምን ያህል የተሟላ እንደሆነ ምን ያስተምረናል? ቀን በቀን እንዴት አድርገን ነው የክርስቶስን ጸጋ እኛን የመሸፈኑ ተስፋ ላይ ብቻ እርግጠኛ ሆነን ልባችን ሊያርፍ የሚችለው?

ነሐሴ 22
Aug 28

ተሰሎንቄ እና ቤርያ


ጳውሎስና ሲላስ ከእስር ቤት ሲለቀቁ ከፊሊጵስዮስ ለቀው ሄዱ (ሐዋ. ሥራ16፡3540):: ጳውሎስና አጋሮቹ ከፊሊጵሲዮስ ተነስተው የመቄዶንያ ዋና ከተማ ወደ ሆነቸው ወደ ተሰሎንቄ አቀኑ፡፡ ሐዋ. ሥራ 17፡1-9ን ያንብቡ፡፡ በተሰሎንቄ የሚገኙ አይሁዶች ጳውሎስ በአህዛብ መካከል የሰበከውን ፍሬያማ ስብከት እንዴት ተቀበሉት?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አሁንም ጳውሎስ ወንጌልን የሚያካፍልበትን ምኩራብ ሲፈልግ እናገኘዋለን፡፡ ቁጥራቸው አያሌ የሆነ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ግሪኮች እና የማይናቅ ቁጥር ያላቸው እውቅ ሴቶች በጳውሎስ መልእክት አመኑ፡፡ እነዚህ የተለወጡ ሰዎች ከጳውሎስና ሲላስ ጋር ተባበሩ››(ሐዋ.17፡4)፡፡ የተለየ ቡድን መስርተው ከምኩራብ ውጪ በኢያሶን ቤት ይሰበሰቡ ነበር፡፡

የነርሱ ተቃዋሚዎችም በቅናት ተነሳስተው አመጽ ቀሰቀሱ፡፡ ፍላጎታቸውም ጳውሎስንና ሲላስን (ጢሞቲዎስ አልተጠቀሰም) በከተማው ባለስልጣናት ፊት በማቅረብ ለመክሰስ ነበር፡፡ ሚሽነሪዎቹን ግን ማግኘት ባለመቻላቸው ኢያሶንና ጥቂት በቅርቡ ያመኑ ሰዎችን ወደአካባቢው ባለስልጣናት ፊት አቅርበው የፖለቲካ አመጽ ያስነሱ ሰዎችን አስጠልለዋል በሚል ሰበብ አቆሟቸው፡፡

ሐዋ. ሥራ 17፡10-15ን ያንብቡ፡፡ በቤሪያ የሚገኙ አይሁዶች በተሰሎንቄ ከሚገኙት ይልቅ በተቃራኒው ምን አይነት ምላሽ ሰጡ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ኢዮጂንስ ‘eugenēs’ ’የሚለው ቃል (ሐዋ. 17፡11) ስርወቃሉ ‹‹በመልካም ሁኔታ መወለድ›› ወይም ‹‹የመሳፍንት ውልደት›› ማለት ሲሆን ነገር ግን በዚህ ስፍራ የሚያመላክተን ‹‹ተገቢ የሆነ አስተሳሰብ›› ወይም አመለካከት ያላቸው እንደሆነ ነው፡ ፡ በቤሪያ ያሉ አይሁዳውያን የሚመሰገኑት ከጳውሎስና ሲላስ ጋር በመስማማታቸው ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በራሳቸው ፍላጎት በየቀኑ መጽሐፍትን በመመርመር ሚሽነሪዎቹ ትክክል መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ በመጣራቸው ነው፡፡ ለወንጌል ያለን ጉጉት በእውቀት ላይ ካልታነፀ እምነታችን ጥራዝ ነጠቅና ረጅም እድሜ የሌለው ይሆናል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን በቤሪያ ስደት ስለተነሳ በጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ፍሬያማነት ላይ እክል ገጠመው፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ አቴና መሄድ ግድ አለው፡፡

እርስዎ አንዳንድ ነገሮች እንደተባሉት መሆናቸውን ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስዎን በትጋት የመረመሩበት ቅርብ ጊዜ መቼ ነበር?

ነሐሴ 23
Aug 29

ጳውሎስ በአቴና


የጥንታዊቷ ግሪክ የጥበብ ማዕከል የነበረችው አቴና በጣኦታት የተሞላች ነበረች፡፡ በሁሉም ቦታ በተለይም የከተማ ህይወት ማዕከል በነበረው በአጎራ መግቢያ(የህዝብ አደባባይ) በእብነበረድ የተሠሩ ሀውልቶችና ጣዖታት ነበሩ፡፡ ጳውሎስ በበዛው የጣዖት አምልኮ ስለተረበሸ ሁሌ እንደሚያደርገው ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኩራብ መሄዱን ትቶ ሁለት ተግባራትን በተመሳሳይ ወቅት ማከናወን ፈለገ፤ በየሳምንቱ ከአይሁዳውያንና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ አህዛብ ጋር ሲያሳልፍ በየቀኑ ደግሞ በህዝብ አደባባይ ከግሪካውያን ጋር ይወያይ ነበር (ሐዋ. ሥራ 17፡15-22)፡፡

የአቴና ሰዎች አዲስን ነገር ለመስማት ሁልጊዜ ዝግጁዎች ስለነበሩ አንዳንድ ፈላስፎች ለጳውሎስ ትምህርት ፍላጎት አሳይተው አርዮስፋጎስ ወደተባለ የከተማዋ ከፍተኛ የመማክርት ጉባኤ ጋበዙት፡፡ ጳውሎስ ንግግሩን ሲያደርግ ከአይሁድ ጋር እንደሚያደርገው ከመፅሐፍ ቅዱስ ወይም ከእስራኤል ታሪክ አልጠቀሰም(ከሐዋ. 13፡16-41 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ እንደዚያ አይነት አቀራረብ ለዚህኛው ጉባኤ ጥቅም አይኖረውም፡፡ በምትኩ እነዚያ አረማውያን ሊያስተውሉት በሚችሉት መልኩ ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ገለፀላቸው፡፡ ሐዋ. ሥራ 17፡22-31ን ያንብቡ፡፡ በአርዮስፋጎስ ባደረገው ንግግር ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ መዳን፣ ስለ ታሪክና ስለ ሰብዓዊ ዘር ምን አይነት ታላላቅ እውነቶችን ሰበከ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አብዛኛዎቹ የጳውሎስ ቃላት ስለ ሐይማኖትና ስለ እግዚአብሔር የተዛባ አመለካከት ለነበራቸው አረማውያን አድማጮቹ የሚያስቁ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ስለሚፈርደው ፍርድ ሲናገር(ሐዋ. ሥራ 17፡31) ወዲያው ያቋረጡት ስለሚመስል መልዕክቱን እንዴት ሊደመድም እንዳሰበ አናውቅም፡፡ ይህ ትምህርቱ ከቀጣዮቹ የግሪክ አስተምህሮዎች ማለትም 1. እግዚአብሔር እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ በምድር ላይ ባሉ ጉዳዮች ለየትኞቹም ግድ አይለውም ጣልቃም አይገባም እና 2. ሰው ከሞተ አይነሳም ከሚሉት ጋር የሚጋጭ ነበር፡፡ ይህ ወንጌል ለግሪካውያኑ ሞኝነት(1 ቆሮ. 1፡ 23) የሆነበትንና በአቴና የአማኞች ቁጥር ያነሰበትን ምክንያት ይገልፃል፡፡ ሆኖም አማኝ ከሆኑት መካከል የአርዮስፋጎስ ምክር ቤት አባል የነበሩና በአቴናውያን ማህበረሰብ ውስጥ እጅግ ተፅዕኖ ያሳድሩ የነበሩ እንደ ዲዮናስየስ ያሉ ሰዎች ነበሩ፡ ፡ በተጨማሪም ስሟ በመጠቀሱ የምክር ቤቱ አባል ባትሆን እንኳን ከፍ ያለ ቦታ የነበራት ደማሪስም ከአማኞቹ መካከል ነበረች(ሐዋ. ሥራ 17፡34)፡፡

ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ያቀረበበት ለየት ያለ አቀራረብ ስለ ማህበራዊና ባህላዊ ልዩነቶች ግንዛቤ እንደነበረው ያሳያል፡፡ እንደውም መልዕክቱን ግልፅ ለማድረግ ከአረማዊ ግጥም ስንኞችን ጠቅሷል(ሐዋ. ሥራ 17፡28)፡፡ ይህ የተለያዩ ሰዎችን ለመድረስ የተለያዩ መንገዶችን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ምን ይነግረናል?

ነሐሴ 24
Aug 30

ጳውሎስ በቆሮንቶስ


በሐዋ. ሥራ 18፡1-11 ላይ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ስላጋጠመው ነገርና በዚያም አንድ ዓመት ተኩል ስለመቀመጡ ይነግረናል፡፡ አቂላና ጵርስቅላ የጳውሎስ የዕድሜ ዘመን ወዳጆቹ ይሆናሉ(ሮሜ 16፡3፤ 2 ጢሞ. 4፡19)፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው ምናልባትም በንጉስ ክላውዲየስ አማካኝነት ከይሁዳውያን ከሮም ተባረው ወደ ቆሮንቶስ ከመምጣታቸው በፊትም ክርስትያኖች ነበሩ፡፡

ሮማዊው የታሪክ ፀሐፊ ሱቶኒዮስ እንደጠቀሰው ለቀው እንዲወጡ የተደረገበት ምክንያት በአካባቢው ያሉ የአይሁድ አማኞች ወንጌልን በመስበካቸው ‹‹ክርስቶስ›› በሚለው ስም አማካኝነት በአይሁድ ማህበረሰብ መካከል ግጭት ስለተነሳ (Claudius 25.4) ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አቂላና ጵርስቅላም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ይሆናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ጳውሎስና አዳዲስ ወዳጆቹ ተመሳሳይ እምነትና አይሁዳዊ መሰረትን ከመጋራት ባለፈ ተመሳሳይ መተዳደሪያንም ይጋራሉ፡፡ ሐዋ.18፡4-17ን ያንብቡ፡፡ የጳውሎስ የሚሲዮናዊ እንቅስቃሴ በቆሮንቶስ ምን ውጤትን አመጣ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሲላስና ጢሞቴዎስ መቄዶንያ እንደደረሱ በዛ ከምትገኘዋ ቤተክርስቲያን የገንዘብ ድጋፍ ይዘው ነበር የመጡት(2ኛቆሮ.11፡8-9)፡፡ ይህም ጳውሎስ ሙሉ በሙሉ በስብከቱ ብቻ እንዲጠመድ አደረገው፡፡ ‹‹ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ›› (1 ቆሮ.9፡14) ቢያስተምርም የጳውሎስ(የራሱ) መመሪያ ግን ለወንጌል አገልግሎት የሚያወጣውን ወጪ በሙሉ በራሱ መሸፈን ነበር፡፡

ምንም እንኳን የጳውሎስን መልእክት አይሁዶች በብርቱ ቢቃወሙም አንዳንድ አይሁዳውያንና አህዛብ ግን አምነው ነበር፡፡ አምነው ከተለወጡት መካከል የምኩራብ አለቃ የነበረው ቀርስጶስ ከመላ ቤተሰቡ ጋር ይገኝበታል፡፡ አያሌ የቆሮንቶስ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡ የሚቀጥለው ክፍል የሚነግረን ግን በአይሁዶች በኩል ያለው ሁኔታ የበለጠ እየከረረ መሄዱን ነው (ሐዋ.18፡12-17)፡፡ ጳውሎስም በቶሎ ቆሮንቶስን ለቆ ለመሄድ አስቦ ነገር ግን በሌሊት ራዕይ በዚያ ስፍራ እንዲቆይ የመለኮት ማበረታቻን አገኘ (ሐዋ.18፡9-11)፡፡

ወደ አንጾኪያ በሚመለስበት ጊዜ ጳውሎስ አቂላና ጵርስቅላን ወስዶ ጉዞውን ከመቀጠሉ በፊት ጥቂት ቀናት በቆየበት በኤፌሶን ተዋቸው፡፡ በዛ ቆይታውም በአካባቢው ባለው ምኩራብ ውስጥ የመስበክን እድል አገኘ፡፡ የሰዎቹን መልካም የሆነ ምላሽ እግዚአብሔር ከፈቀደ ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል እንዲገባ አስገደደው (ሐዋ.18፡18-21)፡፡ ይህ የሆነው በቀጣይ ጉዞው ውስጥ ነበር፡፡

ጥሩ ምላሽ ባለማግኘቱ ተስፋ የቆረጠው ጳውሎስ በዛ ስላሉት የነፍሳት መዳን ሁኔታ ከጌታ ማበረታቻን ማግኘት አስፈለገው፡፡ የጌታ ቃል ምን ነበር ያለው (ሐዋ.18፡10)? ከጳውሎስ ጋር ተመሳሳይ ነገር ሲገጥመን ጌታ እኛን ምን ይለናል?

ነሐሴ 25
Aug 31
ነሐሴ 25

ተጨማሪ ጥናት፡


”ዛሬ ገናና ያልሆነውን እውነት የሚያስተምሩ የሚቀበላቸው ሰው ባለመግኘታቸው፣ ክርስትያን ነን የሚሉ ሰዎች ሳይቀር ባይቀበሏቸው ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም:: ጳውሎስና የስራ አጋሮቹ በሚያገለግሏቸው ሰዎች መሃል ሆነው ከዚህ በላይ ደርሶባቸዋልና፡፡ የመስቀሉ መልእክተኞች ነቅቶ በመፀለይ፣ በእምነትና በድፍረት ወደፊት በመንቀሳቀስ በየሱስ ስም ሁልጊዜ ለመስራት መታጠቅ አለባቸው።“ Ellen G. White, The Acts of the Apostles, P.230 “በምድር ታሪክ ማጠቃለያ ላይ እውነቱ የሚሰበክላቸው የቤርያን ሰዎች ፈለግ በመከተል ቃሉን በየቀኑ የሚመረምሩና እና የእግዚብሔርን ቃል ከቀረበላቸው መልእክት ጋር የሚያነፃፅሩቢሆኑ ኖሮ በንጽጽር አሁን ካሉት ጥቂት የእግዚአብሔር ህግ ታማኞች ይልቅ ብዙዎች ይገኙ ነበር፡፡”

“ሁሉም የሚፈረድባቸው በተቀበሉት ብርሃን ልክ ነው፡፡ ጌታ አምባሳደሮቹን የድነት መልእክቱን አስታጥቆ ልኳቸዋል፤ የሚሰሙትም የአገልጋዮቹን ቃል በተቀበሉበት ልክ ሃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ በቅንነት እውነትን የሚሹ ሁሉ የቀረበላቸውን አስተምህሮ በተገለጠላቸው የእግዚአብሔር ቃል ብርሀን በጥንቃቄ ሊመረምሩ ይገባቸዋል፡፡” Page 232


የመወያያ ጥያቄዎች



1. በሰኞ ጥናታችን የመጨረሻው አንቀጽ ባጠናነው አውድ መሰረት የሚከተለው አባባል የሚያመላክተውን ነገር እስቲ በክፍሎቻችሁ ውስጥ ተወያዩ፡፡ “ለጥምቀት የሚዘጋጁ እጩዎች ከልብ የሆነ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው… የክርስትያን ህይወት መርህ ወደ እውነቱ በቅርቡ ለተቀላቀሉ ሰዎች ግልጽ መሆን ይገባዋል፡፡” Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 6, pp. 91, 92::

2. በረቡዕ የመጨረሻ ጥያቄ ላይ ትኩረትዎን ያድርጉ፡፡ ልክ ጳውሎስ የባህል ልዩነቶችን እንዳስተዋለው እኛም እንደቤተክርስቲያን ልዩነታችንን አስተውለን ወንጌሉንና የሃይማኖት አቋማችንን ድርድር ውስጥ ሳናስገባሰዎችን ባሉበት ስፍራ መድረስ የሚቻለን እንዴት ነው?

3. ሐዋ. 17፡32-34ን ያንብቡ:: ጳውሎስ በአቴና ላቀረበው መልእክት ከተሰጡት ሶስት ምላሾች ምን እንማራለን?“1) አንዳንዶቹ አሾፉበት፡፡ እንግዳ በሆነውና የተነቃቃ ስሜት በነበረው አይሁድ ተዝናኑ፡፡ በህይወት ላይ ማፌዝ ይቻላል፤ ነገር ግን ይህን በሚያደርጉ ሰዎች በቀልድ የተጀመረው ነገር በሀዘን ይጠናቀቃል፡፡ 2) አንዳንዶች መወሰን አልፈለጉም፡፡ ከሁሉም አደገኛው ቀን አንድ ሰው ስለነገ ማውራት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ የሚያስተውልበት ዕለት ነው ፡፡ 3) አንዳንዶች አመኑ። ጠቢብ የሆኑ ሰዎች ሞኞች ብቻ የእግዚአብሔርን ስጦታ እንቢ እንደሚሉ ያውቃሉ፡፡”William Barclay, The Acts of the Apostles, rev. ed. (Philadelphia: Westminster, 1976), p. 133

4. ጳውሎስ ለአቴናውያን መልእክቱን ለማጉላት ከአረማዊ ፀሐፊ ጠቅሶ (ሐዋ.17፡28) ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ያሉ ምንጮችን መጥቀስ ያለውን ጥቅም እድንማር ይህ እንዴት ያግዘናል? ይህን ማድረጉ ምን አይነት አደጋስ ሊኖረው ይችላል?