የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ሐምሌ 28-ነሐሴ 4

ስድስተኛ ትምህርት

Aug 4- 10


የጴጥሮስ አገልግሎት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሐዋ. ሥራ 9፡32-43፣ ሐዋ.ሥራ 10፡9-16፣ ኤፌ.2፡11-19፣ ሐዋ.ሥራ 11፡1-26፣ ሐዋ. ሥራ 12፡1-18፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ፡-“ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ ፤ ”እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፣ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል፡፡” /ሐዋ. ሥራ 10፡34-35/

ጳ ውሎስ ወደ ተርሴስ በመሄዱ ጴጥሮስ ሉቃስ በፃፈው የቀደምቷ ቤተክርስቲያን ትረካ ውስጥ እንደገና ዋና ገፀ-ባህሪ ሆኗል፡፡ ጴጥሮስ በይሁዳ ውስጥና በአካባቢዋም በየቦታው እየሄደ የማገልገል ኃላፊነቱን ሲወጣ እንመለከታለን፡፡ የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍ በዚህ ቦታ የሁለት አጫጭር ተዓምራትን ታሪክ ይነግረናል፣ የኤንያ መፈወስና የጣቢታ ከሞት መነሳት፡፡ ከዚያም በምዕራፍ 10 የቆርኔሊዎስ ታሪክ ይከተላል፡፡

የአህዛብ መለወጥ በሐዋሪያት ቤተክርስቲያን ታሪክ ትልቅ ክርክርን ያስነሳ ነበር፡፡ ከቆርኔሊዎስ መጠመቅ በኋላ የተካሄዱት ውይይቶች ችግሮቹን በሙሉ ባይፈቱም የመንፈስ ቅዱስ መውረድ፣ በጴንጤቆስጤ ቀን የተገኙት ሰዎች ጴጥሮስንና በኢየሩሳሌም የነበሩትን ወንድሞች የወንጌሉ በረከት ለአይሁድ ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ ለማሳመን ጠቅመዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንፆኪያ የነበረችው ቤተክርስቲያንም ወደ አህዛብ ለመሄድ ጉዞ ጀምራ ነበር፡፡ የዚህ ሳምንት ጥናት በተጨማሪ በንጉስ ሔሮድስ ዘመን ስለተነሳና ጥቂት ጊዜ ስለቆየው የስደት ጊዜ፣ በሳኦል ከተቀጣጠለው ስደት በተረፉት በሐዋሪያት ላይ ስለፈጠረው ተፅዕኖ ይዳስሳል፡፡

ለነሐሴ 5 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡

ሐምሌ 29
Aug 05

በልዳና በኢዮጴ


ጴጥሮስ በይሁዳ የባህር ዳርቻዎች አካባቢ ያሉትን ክርስትያን ህብረተሰቦች እየጐበኘ ነበር፡፡ ምናልባትም አላማው ከቃሉ ለማስተማር /የሐዋ. ስራ 2፡42/ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በኃይል ተጠቅሞበት ልክ በኢየሱስ በራሱ እንደተፈፀሙት ዓይነት ተዓምራት እንዲያደርግ ተጠቀመበት፡፡

ሐዋ. ሥራ 9፡ 32-35ን ያንብቡ፡፡ ኢየሱስ በሉቃስ 5፡17-26 ላይ ያደረገውና በኤንያ መፈወስ ታሪክ ውስጥ ምን የሚያመሳስል ነገር እንመለከታለን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከነዚህ ባለታሪኮች የእምነት ፅናት በተጨማሪ ይህ ተዓምር በቅፍርናሆም የተፈወሰውን ሽባ ሰው ታሪክ ያስታውሰናል /ሉቃስ 5፡17-26/፡፡ ስለ አልጋውም የተነገረው ዝርዝር ተመሳሳይ ነበር፡፡

ሆኖም ዋናው ነገር የኤንያ መፈወስ በልዳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሰሮና በሚኖሩትም ዘንድ ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው፡፡ የፈውሱ ሁኔታ እውነት መሆኑን አረጋግጠው ብዙ ሰዎች ወደ ጌታ ተመለሱ፡፡

ሐዋ. ሥራ 9፡36-43ን ያንብቡ፡፡የጣቢታን (ዶርቃ) ከሞት የመነሳት ታሪክ ይመልከቱ፡ ፡ ስለ እርሷ የተለየ ነገር የሆነው ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በአረማይክ ቋንቋ “አጋዘን” የሚል ትርጉም ያለው ስም ያላት ጣቢታ (በግሪክኛ ዶርቃ) በክርስቲያናዊ በጎ-አድራጎቷ የተነሳ በጎረቤቶቿ ዘንድ ተወዳጅ የሆነች አማኝ ነበረች፡፡ የርሷ ከሞት መነሳት በኢየሱስ አማካኝነት ጴጥሮስ እያየ ከሞት ከተነሳችው የኢያኢሮስ ሴት ልጅ ከሞት መነሳት ጋር የሚመሳሰል ነው (ሉቃስ 8፡41-42፣49-56)፡፡ ልክ እንደ ኢየሱስ እርሱም ሁሉም ሰው እንዲወጣ ጠየቀ (ማርቆስ 5፡40ን ይመልከቱ)፡ ፡ ከዚያም ተንበርክኮ ፀለየና የሞተችዋን ሴት “ጣቢያ ሆይ ተነሽ ” (ሐዋ. ሥራ 9፡40) ብሎ አዘዛት፡፡

ሐዋሪያቱ ብዙ ተዓምራት እንዳደረጉ ብንናገርም በነርሱ እጅ እየሠራ የነበረው የእግዚአብሔር እጅ ነበር (ሐዋ. ሥራ 5፡12)፡፡ ከራሱ ከኢየሱስ ተዓምራት ጋር መመሳሰሉ (የሚያስተምረን) መጠቀሚያው ማንም ሆነ ማን ዋናው መለኪያ ያ ሰው ለእግዚአብሔር ያለው መሰጠት መሆኑን (ዮሐ. 14፡12) በዚያን ዘመን ለነበረችው ቤተክርስቲያንና ለእኛ ለማስታወስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ ወንጌሉ እኛን እንዲጠቀምብን ሙሉ በሙሉ ስንፈቅድለት ታላላቅ ነገሮች ይከናወናሉ፡፡ ጴጥሮስ ጣቢታን ከሞት ማስነሳቱ ሳይበቃ በዚያ ተዓምር የተነሳ በኢዮጴ የሚኖሩ ብዙዎች ወደጌታ ተመልሰዋል፡፡ (ሐዋ. ሥራ 9፡42)፡፡

አንዳንድ ሰዎች ልክ እንደዚህ አይነት ተዓምር ቢመለከቱ ኖሮ ያምኑ እንደነበር ያስባሉ፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ተዓምራት ሰዎችን ወደማመን ቢመሩም መጽሐፍ ቅዱስ ተዓምራትን አይተው ነገር ግን ባላመኑ ሰዎች ታሪክ የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ እምነታችን መመስረት ያለበት በምን ላይ ነው?

ሐምሌ 30
Aug 06

በቆርኔሌዎስ ቤት


ጴጥሮስ ስምዖን ከተባለ ከአንድ ቁርበት ፋቂ ጋር በኢዮጴ ቆየ (ሐዋ. ሥራ 9፡ 43)፡፡ ከኢዮጴ 25 ማይል (40 ኪ.ሜ.) ርቀት ላይ በምትገኘው በቂሳሪያ ቆርኔሌዎስ የሚባል የሮም መቶ አለቃ ይኖር ነበር፡፡ እርሱና ቤተሰቡ እግዚአብሔርን ከልባቸው የሚያመልኩ ነበሩ፤ ወደ አይሁድነት ግን በይፋ አልገቡም - ማለትም ቆርኔሌዎስ ያልተገረዘ አህዛብ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር በተቀበለው ራዕይ መልዕክተኞችን ወደ ኢዮጴ ልኮ ጴጥሮስን ወደቤቱ እንዲጋብዝ ተነገረው (ሐዋ. ሥራ 10፡1-8) ሐዋ. ሥራ 10፡9-16፣28፣34፣35ን ያንብቡ፡፡ ጴጥሮስ ምን ተመለከተ? እንዴትስ ተረጎመው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጴጥሮስ ራዕይ ስለ ምግብ ሳይሆን ስለ ሰዎች መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ ነው፡ ፡ አዎን እኩለ ቀን ገደማ ነበር፤ ጴጥሮስም ርቦት ነበር፤ ያ ድምፅም የሚያያቸውን አርዶ እንዲበላ ነግሮታል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ራዕይ የላከው በንፁህና ርኩስ ምግብ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥፋት ሳይሆን ወንጌል ሁሉንም የሚያቅፍ መሆኑን ለጴጥሮስ ለማስተማር ነው፡፡

ራዕዩ ጴጥሮስ አህዛብን የማግለል ልማዱን እንዲያቆም በግልፅ የተቀመጠ ነበር፡፡ ጴጥሮስ የሚያስበው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ገብቶ ከርሱ ጋር ካመለከ ራሱን እንደሚያረክስና በቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የማይገባው እንደሚሆን ነበር፡፡ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በይሁዳና አካባቢዋ የነበሩ አይሁዶች ካልተገረዙት አህዛብ ጋር አይቀላቀሉም ነበር፡፡

ችግሩ በጊዜው የነበረው ስነመለኮታዊ አስተምሮ ሲሆን አይሁዶችን ከአህዛብ ለይቶ እንደ ሀገር የመኖራቸውን ዋና ምክንያት ማለትም እውነተኛውን አምላክ ለዓለም ማሳወቅን እንዲዘነጉ አድርጎ አቅጣጫ አስቀይሯቸዋል፡፡ መገረዝ የአብርሐማዊው ቃልኪዳን ምልክት ስለነበር ያልተገረዙ አህዛብ በንቀት አይን እየታዩ ይገለሉ ነበር፡፡ ተገርዘው አይሁዳዊ ካልሆኑ በስተቀር የቃልኪዳኑ በረከቶች ተካፋይ እንደማይሆኑ ይታሰብ ነበር፡፡ ይህ ሐሳብ ቀደምት አማኞች በጊዜ ሂደት እያስተዋሉ እንደመጡት ከኢየሱስ ሞት ሁሉን አቀፍነት ጋር የማይሄድ ነበር፡፡ ቲቶ 2፡11ን ገላቲያ 3፡26-28ንና ኤፌሶን 2፡11-19ን ያንብቡ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የወንጌል መልዕክት ሁሉን አቀፍ ስለመሆኑ ምን ያስተምሩናል? ለክርስቲያኖች በዘር መከፋፈልና ጥላቻን መዝራት ስህተት ስለመሆኑ ምን ይነግሩናል?

ነሐሴ 1
Aug 07

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ


ሐዋ. ሥራ 10፡44-48 በቀደምቷ ቤተክርስቲያን ታሪክ ወሳኝ የሆነን ቅፅበት ይገልፅልናል፡፡ ከሐዋሪያቱ በአንዱ አማካኝነት ወንጌል ላልተገረዙ አህዛብ ሲሰበክ ይህ የመጀመሪያው ነበር፡፡ ከግሪክ ከመጡት አማኞች በተቃራኒ ሐዋሪያቱና ሌሎች አይሁድ አማኞች አህዛብን በቤተክርስቲያን ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም፡፡ ኢየሱስ እስራኤላዊ መሲህ ስለነበር ወንጌሉ በቅርብና በሩቅ ላሉት አይሁድ ብቻ መሰበክ አለበት ብለው ያምኑ ነበር፡፡ አህዛብ በእምነት ማህበሩ ተቀባይነት ለማግኘት በመጀመሪያ ወደ አይሁድነት ሊለወጡ ግድ ነበር፡፡ በሌላ አባባል አህዛብ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት አይሁድ መሆን ነበረባቸው፡፡ በቀደሙት አይሁዶች ዘንድ ሊለወጥ የሚገባው አስተሳሰብ ያ ነበር፡፡

ለቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የልሳን ስጦታ መሰጠቱ ያ አስተምሮ ስህተት መሆኑን በግልፅና በሚታይ ሁኔታ የሚያስረዳ ምልክት ነበር፤ ከመዳን አንፃር እግዚአብሔር በአድሎ የሚያያቸው የሉም፤ አይሁድና አህዛብ በአንድ አይነት መልኩ ይዳኛሉ፡፡ ሐዋ.ሥራ 11፡1-18ን ያንብቡ፡፡ በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተክርስቲያን አባላት ጴጥሮስ በቄሳርያ ላጋጠመው ነገር ምን ምላሽ ሰጡ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ለረጅም ዘመናት በቆየውና አይሁዶች በአሕዛብ ላይ ባላቸው የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበሩት አማኞች ጴጥሮስ ካልተገረዙት ጋር በመብላቱ ወቀሱት፡፡ ከቆርኔሌዎስና ቤተሰቦቹ መዳን በላይ የአይሁድ ስርአቶች ተጠብቆ መቆየት የበለጠ ያሳሰባቸው ይመስላል፡፡ ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ስርአቶች ጋር ከተቃረነች የእስራኤልን እምነት በመካዳቸው ምክንያት እግዚአብሔር የሚተዋቸው መስሏቸው ፈሩ፡፡ ሌሎች አይሁዶች በነርሱ ላይ በሚያቀርቡባቸው ክስና እስጢፋኖስ እንዲገደል ወደመሩት ወቀሳዎች መንገድ እንዳይሄዱ ፈሩ፡፡

“የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሙሉ ለሙሉ አዲስ ወደሆነ የስራ አቅጣጫ የምትገባበት ጊዜ መጣ፡፡ ብዙ ከአይሁድ የተመለሱ አማኞች በአህዛብ ላይ ዘግተውት የነበሩት በር በሰፊው የሚከፈትበት ጊዜ ደረሰ፡፡ ወንጌሉን የተቀበሉ አህዛብ መገረዝ ሳይኖርባቸው አይሁድ ከሆኑ ደቀመዛሙርት ጋር እኩል መታየት ቻሉ፡፡” Ellen white, The Acts of the Apostles, P.136

ልክ በጴንጤቆስጤ ቀን እንደሆነው ቀድሞ በማያውቁት ቋንቋ ተናገሩ፡፡ የአላማ ልዩነት ብቻ ነበር፡- ለሐዋሪያቱ ልሳን ሲሰጥ ለዓለም ወንጌሉን ለማዳረስ አላማ ሲሆን ለቆርኔሊዮስ ግን የእግዚአብሔር ፀጋ በአህዛብም እየሠራ እንደነበር ለማረጋገጥ ነበር የተሰጠው፡፡

ነሐሴ 2
Aug 08

የአንፆኪያዋ ቤተክርስቲያን


በቆርኔሌዎስ መለወጥ በመነሳሳት ሉቃስ የጴጥሮስን አገልግሎት ትረካ አቋርጦ ወንጌል በአህዛብ ወደፊት የሄደበትን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ሐዋ. ሥራ 11፡19-26ን ያንብቡ፡፡ አንዳንድ ከኢየሩሳሌም የመጡ ስደተኞች ወደ አንፆኪያ ሲመጡ ምን ተፈጠረ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሐዋ. ሥራ 11 ይሄኛው ክፍል ጳውሎስ ያነሳሳውን (በምዕራፍ 8 የሚገኘውን) ስደት ታሪክ የሚያወሳ ነው፡፡ ስለዚህ ቀደም ብለን ያየናቸው መስፋፋቶች በይሁዳና በሌሎች ቦታዎች እየተካሄዱ ባሉበት ሰዓት ከኢየሩሳሌም እንዲወጡ ከተገደዱት ግሪካዊያን አማኞች መካከል አንዳንዶቹ ከይሁዳ ድንበር እጅግ ርቀው ወንጌልን እያዳረሱ ነበር፡፡ ሉቃስ በሶሪያ በምትገኘው አንፆኪያ በተባለችውና ስደተኛ የሆኑት አማኞች ለአይሁድ ጓደኞቻቸውና ለግሪካዊያን ወንጌልን መስበክና ብዙ አማኞችን ማግኘት በጀመሩባት ከተማ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በሐዋ. ሥራ 1፡8 ኢየሱስ የሰጠው ተልዕኮ ግሪክ በነበሩ አይሁድ ክርስቲያኖች ጥረት አማካኝነት መስተዋል ጀመረ፡፡

በአንፆኪያ በተገኘው ስኬት የተነሳ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋሪያት ሁኔታውን እንዲገመግም በርናባስን ለመላክ ወሰኑ፡፡ እርሱም ለወንጌል ሥራ መስፋፋት ያለውን ታላቅ ዕድል በመመልከት እንዲረዳው ጳውሎስን ይዞ ወደ ተርሴስ ሄደ፡፡ በርናባስ ትክክል ነበር፡፡ እርሱና ጳውሎስ አብረው በሰሩበት ዓመት አብዛኛው አህዛብ የሆነበት ብዙ ሕዝብ ወንጌሉን መስማት ቻለ፡፡ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገሩበት የነበረው ግለት አማኞቹ ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹ክርስቲያኖች›› ተብለው እንዲጠሩ አደረጋቸው (ሐዋ. ሥራ 11፡26)፡፡ ክርስቲያኖች ‹‹ተብለው ተጠሩ›› የሚለው አባባል ከቤተክርስቲያን ውጭ ባሉ ሰዎች ምናልባትም ሊያሾፉባቸው የተሰጠ ስም መሆኑን ያሳያል፡፡ አማኞች ግን ራሳቸውን ‹‹ወንድሞች›› (ሐዋ. ሥራ 1፡ 16)፣ ደቀመዛሙርት (ሐዋ.ሥራ 6፡1) ወይም ‹‹ቅዱሳን›› (ሐዋ. ሥራ 9፡13) ብለው ይጠሩ ነበር፡፡ የሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ በተፃፈበት ወቅት ‹‹ክርስትያን›› የሚለው የተለመደ መጠሪያ ሆኖ ነበር (ሐዋ. ሥራ 26፡28) ሉቃስም ያንን እያረጋገጠ ይመስላል፡ ፡ ‹‹ክርስቲያን›› ማለት የክርስቶስ ተከታይ ማለት ነው፡፡

ለእርስዎ ‹‹ክርስቲያን›› ተብሎ መጠራት ምን አይነት ትርጉም ይሰጥዎታል? ታዲያ ህይወትዎ እውነትም ክርስቲያን ነው? ማለትም በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ክርስቲያን ካልሆኑት በተለየ እንዴት እየኖሩ ይሆን?

ነሐሴ 3
Aug 09

የሔሮድስ ማሳደድ


ወደ ይሁዳ ስንመለስ ንጉስ ሔሮድስ የዮሐንስ ወንድም የሆነውንና የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብን ማስገደሉን እንመለከታለን (ማር. 1፡19)፡፡ በጴጥሮስም ላይ ተመሳሳዩን ማድረግ ፈልጎ ነበር፡፡

ሐዋ.12፡1-4ን ያንብቡ፡፡ ቀደምቷ ቤተክርስቲያን ስላጋጠማት ተጋድሎ ይህ ምን ያስተምራል?

በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ሔሮድስ አግሪጳ የመጀመሪያው ሲሆን የታላቁ ሔሮድስ የልጅ ልጅ ነው (ማቴ. 2፡1)፡፡ በይሁዳ ከ40 እስከ 44 ዓ.ም እ.ኤ.አ ገዛ፡ ፡ ለእምነቱ ያለው ፅናት በአይሁዳዊያን በተለይም በፈሪሳዊያን ዘንድ ታዋቂነትን አስገኝቶለታል፡፡ በአይሁዶች ለመወደድ ብሎ አንዳንድ ሐዋሪያትን ማሰቃየቱን ስንመለከት በሌላ ቦታ ስለርሱ ከተፃፈው ጋር ይገጥማል፡፡

ያዕቆብ በርሱ ትዕዛዝና አላማ መሠረት ስለተገደለ ጴጥሮስንም ሊያስገድል አቀደ:: ጴጥሮስ ተያዘና በአራት ፈረቃ አራት አራት ወታደሮች እንዲጠብቁት አደረገ፡፡ ጴጥሮስ ከአራት ወታደሮች ጋር ይቆይ ነበር፤ሁለቱ ከእጁ ሠንሰለት ጋር ሲታሰሩ የቀሩት ሁለት ደግሞ በሩን ይጠብቃሉ፡፡ እንዲህ ጥብቅ የሆነ ጥበቃ የሚያስደርገው ቀደም ብሎ ጴጥሮስና ዮሐንስ ታስረው ሳሉ የተፈጠረው ነገር እንዳይደገም ለማድረግ ነበር (ሐዋ. ሥራ 5፡17-20)፡፡

ሐዋ. ሥራ 12፡5-18ን ያንብቡ፡፡ ወንድሞች ሲፀልዩ ምን መልስን አገኙ? በማግስቱ አግሪጳ ጴጥሮስን ወደ ፍርድ አስወስዶ ለማስገደል አቅዶ በዚያ ለሊት ጴጥሮስ በድጋሚ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ በመልአክ አማካኝነት ከእስር ወጣ፡፡ በመቀጠል በቄሳሪያ የአግሪጳን መሞት ታሪክ እናገኛለን/ሐዋ. ሥራ 12፡20-23/፡፡ የሞተበትን ምክንያት ለመለየት የተለያዩ መላምቶች ቢሰጡም /ጨጓራ፣ መርዝ፣ የሆድ ህመም/ ሉቃስ ግን በግልፅ ንጉሱ የሞተው በመለኮታዊ ፍርድ ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ያዕቆብ ተገደለ፣ ጴጥሮስ እንዲያመልጥ ተደረገና ሔሮድስ ደግሞ መለኮታዊ ቅጣት አገኘው፡፡ በአንዳንዶቹ ጉዳዮች ፍትህን ብናይም በሌሎቹ ደግሞ እንደዚያ አይመስልም፡፡ ላሉን ጥያቄዎች ሁሉ መልስ እንደሌለንና ባልተረዳናቸው ጉዳዮችም ቢሆን ለምን በእምነት መኖር እንዳለብን እነዚህ ጉዳዮች የሚያስተምሩን እንዴት ነው?

ነሐሴ 4
Aug 10
ነሐሴ 4

ተጨማሪ ጥናት፡


“በሐዋሪያት ሥራ 10 ላይ በሰማይ መላዕክት ተሳትፎ ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የሚለወጡበትን ምሳሌ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ምዕራፎች /8-10/ በትኩረት ይነበቡ፡፡ በነዚህ ውስጥ ነፍሳትን በማዳን ሥራ ከተጠመደ ክርስትያን ጋር ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ ሰማይ በቅርበት እንደሚሠራ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰብአዊ ዘር ግድ እንደሚለውና እያንዳንዳችንም ሌላውን የጌታን ሥራ በምድር ላይ ለመጨረስ እንደሚጠቅም የእግዚአብሐር መሣሪያ አድርገን መመልከትን መማር ይኖርብናል፡፡” Ellen G White, The SDA Bible commentary, VOl.6, P. 1059

“ቤተክርስቲያን ስትፀልይ የእግዚአብሔር አላማ ወደፊት ይራመድና ምንም እንኳን ስደትና ሞት ባይቀርም ሰይጣን ግን እየተሸነፈ ይሄዳል፡፡ ሉቃስ ስለ ወንጌል አሸናፊነት በእርግጠኝነት ሲናገር አገልጋዮቹ ቢሰቃዩና ቢታሰሩም የእግዚአብሔር ቃል ግን እንደማይታሰር ይገልፃል፡፡” I Howard Marshall, The Acts of the apostles (Grand Rapids: Eerdmans,1980), PP. 206-207


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ቆርኔሌዎስ “ከመላው ቤተሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምፅዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚፀልይ ነበር፡፡” /ሐዋ. ሥራ 10፡2/ ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስንም ከመገናኘቱ በፊት የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጡ ይሠራ እንደነበር ይህ ማስረጃ ነው፡ ፡ ያለው የአምልኮ ህይወት እግዚአብሔር ወንጌሉን እንዲያበራለት በር ከፍቶ ይሆን? በርሱ ታሪክ ውስጥ ትምህርት የሚሆነን ምን አለ?

2. ወደ ሰኞው ክፍል ይመለሱና ይህንን ጥያቄ በሰንበት ት/ት ክፍልዎ ይጠይቁ፡ ፡ እንደ ክርስቲያን መግባት በሌለብን የዘር ግጭት ውስጥ የሚያስገቡን ምን አይነት ባህላዊ፣ ማህበራዊና ፓለቲካዊ አውዶች ይሆኑ? በሌላ አባባል እንደ ክርስቲያን ከባህልና አመለካከት በላይ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

3. ምንም ጉዳት ቢደርስባቸውም ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ መልካም ነገርን አምጥቷል፡፡ ወደ አንፆክያ የመጡት ስደተኞች ለአይሁዶችና ለግሪካውያን መስበክ ጀመሩ፡፡ በክፍልዎ በግል ስላጋጠምዎና ቆይቶ ወደ በረከት ስለተቀየረ ህመምና ስቃይዎ ያካፍሉ፡፡

4. ያዕቆብ ለኢየሱስ ቅርብ ከነበሩት ደቀመዛሙርት አንዱ ነበር /ማር. 5፡37፣9፡ 2፣14፡33/፡፡ ሆኖም ከአስራ ሁለቱ የመጀመሪያው ሰማዕት ሆነ፡፡ ታማኝ የሆኑ ሰዎች የማይገባቸውን መከራ ሲቀበሉ የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጥቀሱ፡፡ ስለ ስቃይ ባለን ጥያቄ ላይ ከነዚህ ታሪኮች ምን ትምህርት መውሰድ እንችላለን?