የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ሐምሌ 7- ሐምሌ 13

ሶስተኛ ትምህርት

Jul 14- 20


ህይወት በቀዳሚዋ ቤተክርስቲያን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሐዋ.2፡42-46፤ ሐዋ.4፡34-35 ፤ ሐዋ.3፡1-26፤ ሐዋ.4፡1-18፤ ሐዋ. 5፡34-39፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ፡- ‹‹በየዕለቱ በቤተመቅደስ በአንድነት እየተገናኙ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፡፡እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፡፡››(ሐዋ.2፡46-47)

የቀደምቷ ቤተክርስትያን የችኮላ ስሜት ከዚያ በላይ ሊጨምር አይችልም ነበር፡፡ የሱስ ስለ መንግስቱ መቋቋም ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ የጊዜውን ጉዳይ አለመናገሩ (ሐዋ.1፡6-8) የሚያሳየው ሁሉም የሚወሰነው በመንፈስ ቅዱስ መውረድና በሐዋሪያቱ ተልእኳቸውን መፈፀም ላይ መሆኑን ነው፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን እነዛ ቀደምት ምዕመናን ሁሉም ነገር ፍፃሜን አገኘ ብለው ነበር፡፡መንፈስ ቅዱስን ተቀብለናል ወንጌልን ለአለም አዳርሰናል ብለው አስበዋል፤ ደቀመዛሙርቱ እየሩሳሌምን ሳይለቁና ወደ አለም ሳይሄዱ አለም ወደ እነርሱ መጣች (ሐዋ.2፡5-11)፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ቤተክርስቲያን ራስዋን ከቁሳቁስ ነፃ አደረገች፡፡ ጊዜው አጭር እንደሆነ ተረድተው ያላቸውን ሁሉ ሸጠው ለመማርና ህብረት ለማድረግ ብሎም ለየሱስ ምስክር ለመሆን ራሳቸውን ሰጡ፤ከኢየሩሳሌም ግን አልወጡም፡፡ የመሠረቱት የህብረት ኑሮ ድሆችን ለመርዳት ቢጠቅማቸውም የኋላ ኋላ ችግር አመጣባቸው፤ እግዚአብሄርም የቤተክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ ሲል ጣልቃ ገባ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ከብዙ ተቃምዎች ጋር መጋፈጥ የጀመሩት፡፡ በዚህ ሁሉ ከባድ ወቅት ግን እምነታቸው አልተናወጠም፡፡

የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለ ሐምሌ 14 ሰንበት ይዘጋጁ፡፡

ሐምሌ 8
Jul 15

ማስተማርና ህብረት ማድረግ


ከጴንጤቆስጤ ቀን በኋላ ሉቃስ ትረካውን በእየሩሳሌም በምትገኘው ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ውስጣዊ ኑሮ ላይ ያነጣጥራል፡፡ ‹‹ እነርሱም በሐዋሪያት ትምህርትና በህብረት እንጀራውንም በመቁረስና በፀሎት ይተጉ ነበር፡፡›› (ሐዋ. 2፡42) እዚህ ጋ የተጠቀሱት አራት ነገሮች ሲጠቃለሉ ትምህርት እና ህብረት ማድረግ ናቸው፡፡ ቁጥር 46 እንደሚነግረን ከሆነ ትምህርቱ ይከናወን የነበረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲሆን በአንድነት የሚያሳልፉት ደግሞ በእያንዳንዳቸው ቤቶችነበር፡፡

የቤተ መቅደሱ ሸንጎ በጣሪያ የተከለለ ሲሆን ብዙውን ጊዜ መምህራን ደንቦቻቸውን የሚያስተምሩበት ስፍራ ነው፡፡ አማኞች ሁሉ ለሐዋሪያት ትምህርት የተሰጡ መሆናቸው የሚያሳየው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሀሳባዊ ወደሆነ ሀይማኖተኝነት ሳይሆን በድንቅና ተአምራት ወደ ታጀበውና ጥልቅ ወደ ሆነው የሐዋሪያት ትምህርት እንደመራቸው ነው (ሐዋ.2፡43)፡፡

መንፈሳዊ ህብረት ለቀዳሚዋ ቤተክርስቲያን ሁነኛ መገለጫዋ ነበር ፡፡ አማኞች በቤተ መቅደስ ብቻ ሳይሆን በቤቶቻቸውም ያልተቋረጠ አብሮነት ነበራቸው፡፡ አብረው ምግብ ይቆርሱ ነበር፤ የጌታን እራት ያከብሩ ነበር፤ ይፀልዩም ነበር (ሐዋ.2፡42-46)፡ ፡በየዕለቱ ይህንን በማክበር የቀድሞ ክርስትያኖች የሱስ በቅርቡ ዳግም እንደሚገለጽ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ የመሲሁ መንግስት ሲቋቋም ከእርሱ ጋር እንደገና አብረው እንደሚሆኑ ያምኑ ነበር(ማቴ.26፡29)፡፡

በቀደሞዋ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የግለሰቦች ቤት ወሳኙን ሚና ተጫውቷል፡ ፡ አማኞች በየቀኑ የቤተመቅደሱን ስርአት ይካፈላሉ(ሐዋ.3፡1)፤ በሰንበት ቀን ደግሞ ከአይሁድ ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በምኩራብ ይቀመጣሉ (ያዕ.2፡2)፡፡ ነገር ግን ልዩ የሆነው የአምልኮ ክፍል ይከናወን የነበረው በቤት ውስጥ ነበር፡፡

ሐዋ.2፡44-45፣ 4፡34-35ን ያንብቡ፡፡ ቀዳሚ የሆኑ ክርስቲያኖች ያደርጉት የነበረ ወሳኝ ነገር ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የመጨረሻው ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ስላመኑ ንብረቶቻቸውን ‹‹የየግል መጠቀሚያ እቃቸውን›› (በየቀኑ የሚጠቀሙባቸውን ነገሮች) ምንም ያህል አስፈላጊ ሆነው አልታዩዋቸውም፡፡ ስለዚህ ንብረቶቻቸውን መጋራታቸውና በጋራ መጠቀማቸው ተገቢ ነበር፡፡ መሲሁ መንግስቱን ሲያቋቁም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚሰጣቸው ስለሚያውቁ ስለነገ መጨነቅ እንደሌለባቸው አመኑ(ሉቃስ 22፡29-30)፡፡ በአብሮነት ንብረታቸውን የመጋራታቸው ሁኔታ እጅግ ታላቅ የልግስና አርአያዎች ከመሆን ባለፈ ጥልቅ የሆነ ህብረትን እንዲያጣጥሙ አደረጋቸው፡፡

ጌታ ከሰጠዎት ነገር ላይ እርስዎም ለሌላው ለመለገስ ምን ያህል ፈቃደኛ ነዎት?

ሐምሌ 9
Jul 16

የሽባው ሰው መፈወስ


በሐዋ. 3፡1 ላይ ጴጥሮስና ዮሐንስ ከቀኑ በዘጠኝ ሰአት በቤተ መቅደስ ለሚደረገው የፀሎት አገልግሎት ለመሳተፍ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡ ይህ የሚያሳየው በዚያን ወቅት የነበረው የክርስትና እምነት ውስጥ ስለነበሩ አይሁዳዊ ባህሪያት ነው፡ ፡ ይህም ማለት ሐዋሪያት ወደ ቤተ መቅደስ የሚሄዱት መመሪያ ለመስጠት ወይንም ሰዎች ልባቸው እንዲለወጥ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ጴጥሮስና ዮሐንስ አይሁዳዊ ስለነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ስርአትንም ለመፈፀም(ሐዋ.20፡16፤21፡17-26) ነበር (ቢያንስ እስከዚህኛው ክስተት ድረስ)፡፡ በዛም እጅግ አስደናቂ ተአምር ተከናወነና (ሐዋ.3፡1-10) ጴጥሮስ ሌላ ስብከት እንዲሰብክ እድል አገኘ፡፡ ሐዋ.3፡12-26ን አንብቡ፡፡ በጴጥሮስ ስብከት ውስጥ ያለው ዋነኛ ትኩረት ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በቀድሞ ክርስቲያኖች ስብከት ውስጥ የሚንፀባረቁ አምስት ወሳኝ ነጥቦች ነበሩ፡- የሱስ መከራ የተቀበለው መሲህ ነው(ሐዋ.3፡18)፤ እግዚአብሔርም ከሙታን አስነሳው(ሐዋ. 3፡15)፤ የሱስ በሰማይ ከብሯል (ሐዋ.3፡13)፤ ዳግም ተመልሶም ይመጣል(ሐዋ.3፡ 20)፤ የኃጢያትን ይቅርታ ለማግኘት ንስሃ መግባት ያስፈልጋል(ሐዋ.3፡19)፡፡ ዓውዱ ቢለወጥም ለአለም ይዘን የምንሄደው መልእክት በብዙ መንገድ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሐዋሪያት በአይሁድ ጥላ ስር ስለነበሩ ህዝቡ ሃይማኖቱን እንዲቀይር ከማድረግ ይልቅ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን ‹‹እንዲፈልሱ››አደረጉ፡፡ እንደ እግዚአብሄር ህዝብነታቸው መሲሁን መቀበልና እርሱንም በመቀበል የሚገኘውን አዲስ ልደት መለማመድ ነበረባቸው፡፡

ዛሬ ያለው ሁኔታ ከድሮው የተለየ ቢሆንም መልእክቱ ግን አሁንም አልተቀየረም፡፡ ክርስቶስ ለሐጢያታችን ሲል ሞተ፤ ከሞትም ተነሳ፤ እናም ደግሞ ተመልሶ ይመጣል ፡፡ ይህም ማለት በእርሱ አማካኝነት ድነትን እናገኛለን፡፡ በራእይ 14ላይ ከሚገኘው የሶስቱ መላእክት መልእክት አውድ አንጻር ስንቃኘው እንኳን የምናውጀው መልእክታችን ማዕከል ሊሆን የሚገባው የየሱስ መሞት፣ መነሳት እና ዳግም መመለስ ነው፡፡ ‹‹ክርስቶስን ከሚመሰክሩ ክርስትያኖች ሁሉ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሱስን ከማንም በላይ ከፍ አድርገው ለአለም ሊመስከሩ ይገባቸዋል፡፡ የሶስተኛው መልእክ መልዕክት ጥሪ የሚያመላክተን ስለ ሰንበት እውነትነት ነው፡፡ ይህ እውነትና ሌሎችም በውስጥ ያሉ መልእክቶች መታወጅ ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን የትኩረታችን ትልቁ ማዕከል የሆነው የሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በርሱ መስቀል ላይ ነው ምህረት እና እውነት የተስማሙት ጽድቅና ሰላምም የተሳሳሙት፡፡ ኃጢያተኛው ወደቀራኒዮ አይኑን እንዲያቀናልንመራው ይገባል፡፡ ይህም እንደ ትንሽ ህጻን አዳኙን በማመን ብቻ ጽድቁን መቀበል በምህረቱም መታመን ነው፡፡›› -Ellen G. White,Gospel Workers, Pp.156-157፡፡

ሐምሌ 10
Jul 17

የግጭት መነሳት


ብዙም ሳይቆይ ነበር የቤተክርስቲያኒቱን ስኬታማነት ተከትሎ በአንዳንድ የእየሩሳሌም መሪዎች አማካኝነት ግጭት ብቅ ማለት የጀመረው፡፡ የእየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሚመራው በሊቀ ካህናት እና በረዳቶቻቸው አማካኝነት ሲሆን ብዙዎቹ ደግሞ ሰዱቃውያን ነበሩ፡፡ ሊቀ ካህኑ በወቅቱ በአብዛኛው ሰዱቃውያንንና ፈሪሳውያንን ይይዝ በነበረው ሸንጎ መሪ ነበር፡፡ሰዱቃውያን በሙታን ትንሳኤ ስለማያምኑ ጴጥሮስና ዮሐንስ ስለ የሱስ ከሞት መነሳት በመስበካቸው እጅጉን ተረበሹ፡፡ ሐዋሪያቱ በቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ተይዘው በማግስቱ በሸንጎ ፊት እስኪቀርቡ ድረስ በወህኒ ቤት ቆዩ(ሐዋ.4፡1-7)፡፡

ሐዋ.4፡1-18ን ያንብቡ፡፡ ይህንን በምን ስልጣን ያደርጉ እንደነበር ሲጠየቁ ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ጴጥሮስ በመለሰላቸው መልስ ውስጥ መሪዎቹ ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጋቸው ወሳኝ መልእክት ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የአይሁድ መሪዎች ስልጣንን በተመለከተ መጠየቃቸው ኃይልን ለማግኘት ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል፡፡ ጴጥሮስ ግን ይህ ተአምር በየሱስ ስም እንደሆነ ከመናገር በተጨማሪ የድነት ምንጩ እርሱ ብቻ እንደ ሆነ አወጀ፡፡ ሐዋሪያቱ በአይሁድ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛው አካል ፊት ቢቀርቡም ከፈራጆቹ በላይ የሆነውን አምላክ ያገለግሉ ነበር፡ ፡ እነዚህ ሰዎች ተራና ያልተማሩ የገሊላ አሳ አጥማጆች ሆነው የነበራቸው ድፍረትና መተማመን በስፍራው የነበሩ ሰዎችን አስገረመ፡፡ እነዚህ መሪዎች ባያስተውሉትም ሐዋሪያት ልክ የሱስ ቀድሞ እንደተናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ስለነበር ነው (ማቴ.10፡16-20)፡፡

የተፈወሰው ሰው ሁሉም እንዲያየው በፊታቸው ስለቀረበ የሸንጎው አባላት ተዓምሩን መካድ ባይችሉም ሐዋሪያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ አስጠነቀቋቸው፡፡ የህዝቡ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሐዋሪያቱ መልእክቱ ያስፈራቸው ጀመር፡፡ ትክክለኛ ማስረጃ ማቅረብ ስለተሰናቸውና መከላከል ስለፈለጉ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ እንዲተላለፍ ፈቀዱ፡፡

ጴጥሮስ የተናገረው የመጨረሻ ቃል በሐዋሪያት ስራ መጽሀፍ ውስጥ በአስደማሚነቱ የሚታወስ ንግግር ነው፡፡ ‹‹ከእግዚብሄር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሄር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተ ፍረዱ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም፡፡››› (ሐዋ.4፡19-20)፡፡ ስለ ስልጣን ጥማት እስቲ ያስቡ፡፡ በማንኛውም ደረጃና ሁኔታ ይህ ክፉ ስሜት ምን ያህል አደገኛ መሆኑን ያስቡ፡፡አገልጋይ እንዲሆኑ እንደተጠሩ ክርስትያኖች ለስልጣን ከመማለል ፈተና መጠበቅ ያለብን ለምንድነው?

ሐምሌ 11
Jul 18

ሐናንያና ሰጲራ


ንብረትን በሙሉ ማምጣት በቀድሞ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደ ግዴታ የሚቆጠር ነገር አልነበረም፤ ይህም ማለት የቤተክርስቲያን አባል ለመሆን የሚደረግ መስፈርት አልነበረም፡፡ ነገር ግን መላውን የህብረተሰብ ክፍልን በማነቃቃት በለጋስነታቸው ትልቅ ምሳሌ የሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ምሳሌዎች አንዱ በሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ የኋለኛ ክፍል ቁልፍ ሚናን የሚጫወተው በርናባስ ነበር (ሐዋ.4፡36-37)፡፡ ሆኖም ከቤተክርስቲያን ውጪ ያሉ ጥቃት ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ባለበት ሰአት በቤተክርስቲያን ውስጥም አሉታዊ ምሳሌ በመሆን የቤተክርስትያንን ህብረት አደጋ ላይ የጣሉ ሰዎችም ነበሩ፡፡

ሐዋ.5፡1-11ን አንብቡ፡፡ ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ምንድነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምንም እንኳን ሉቃስ ዝርዝር ጉዳዩን ባይጽፍልንም መሰረታዊው ችግር ሐናኒያና ሰጲራ ገንዘቡን ለማስቀረት መሞከራቸው ሳይሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያደረጉት የማታለል ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሐጢያታቸው እንደው በጥድፊያና በድንገት የተከናወነ ሳይሆን በጥንቃቄ አቅደውና አውቀው ‹‹የጌታን መንፈስ ለመፈታተን›› (ሐዋ. ሥራ 5፡9) የሰሩት ነገር ነው፡፡ንብረቶቻቸውን ሁሉ ሸጠው ገንዘቡን ለቤተክርስቲያን የማምጣት ግዴታ አልነበረባቸውም፡፡ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ ሲወስኑ ምናልባትም ለራሳቸው ጥቅም ብቻ አስበው በለጋስነት ተግባራቸው በወንድሞች መካከል ትልቅ ተፅእኖን ለመፍጠር አስበው ሊሆን ይችላል፡፡

እግዚአብሄር በከፋ ሁኔታ እንዲቀጣቸው ያደረገው ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተክርስቲያን በሙሉ በአንድነት ሆነው መኖርን እንዲጀምሩ ያደረገው የሱስ በቅርቡ ይመጣል የሚለው እምነታቸው ቢሆንም የሐናንያና የሰጲራ ተግባር ቀዳሚ በሆነችው ቤተክርስቲያን ለእግዚአብሄር ታማኝ የመሆንን ተግባር የሚያጎድፍና በአማኞች ዘንድ መጥፎ ተጽእኖ የፈጠረ ነበር፡፡ ሐናንያ ልክ እንደ ሰጲራ(ሐዋ. ሥራ 5፡8) ንሰሃ ለመግባት እድል እንደተሰጠው ባናነብም ምናልባትም በአጭሩ ብቻ ስለተፃፈ ሊሆን ይችላል፡፡

መሰረታዊው ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ያሳዩት ተግባር በሐጢያት የተሞላ ነበር፡፡ምንም እንኳን ሁልጊዜ ወዲያውኑ ባይቀጣንም ሐጢያት በእግዚብሄር ፊት ያለው ቦታ የገዘፈ ነው (ሕዝ.18፡20፤ ሮሜ 6፡23)፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ቅጣቱ መዘግየቱ የእግዚብሄርን ፀጋብዛት ሊያስታውሰን ይገባል (2ጴጥ.3፡9)፡፡ እነዚህ ሁለት የቤተክርሰቲያን አባላት እንዳደረጉት የእግዚብሄርን የጸጋ ገደብ ላለመግፋት ምን ያህል ልንጠነቀቅ ይገባናል?

ሐምሌ 12
Jul 19

ለሁለተኛ ጊዜ መታሰር


ሐዋሪያት ልክ ሐናንያና ሰጲራ ላይ እንደሆነው የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲመጣ መጠቀሚያ ከሆኑ የእግዚአብሄር ፀጋ በሐጢያተኞች ላይ እንዲመጣም መጠቀሚያ መሆን ይችላሉ፡፡ በሐይል ተሞልቶ የነበረው የፈውስ አገልግሎታቸው (ሐዋ.5፡12-16) የእግዚአብሄር መንፈስ በእነርሱ እየሰራ እንዳለ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ የጴጥሮስ ጥላ ሳይቀር ሰዎች ላይ አርፎ እንደሚፈውሳቸው መታመኑ የሚገርም ነው፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር የሚቀራረበው ሌላ ታሪክ የየሱስን የልብሱን ጫፍ ነክታ የተፈወሰቸው ሴት ናት (ሉቃስ 8፡43-44)፡፡ ሉቃስ የጴጥሮስ ጥላ የመፈወስ ሀይል አለው እያለ ሳይሆን ሕዝቡ ግን ይህ ይሆናል ብለው አሰቡ ነው ያለን ፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ አይነት የማይመስሉ እምነቶች በስፋት ቢኖሩም እግዚአብሄር ግን ፀጋውን ያድላል፡፡

ሐዋሪያቱ በመንፈስ ቅዱስ የበለጠ በተሞሉ ቁጥር ድንቅና ተአምራት በበዙላቸው ቁጥር የሃይማኖት መሪዎች የበለጠ በቅናት ይነዱ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሐዋሪያትን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲይዟቸው አደረጋቸው(ሐዋ.5፡17-18)፡፡ በተአምር ከእስር ቤት ከወጡና (ሐዋ.5፡19-24) ጴጥሮስ‹‹ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሄር ልንታዘዝ ይገባል!›› የሚል ሌላ የድፍረት ቃል ከተናገረ (ሐዋ.5፡29) በኋላ አንዳንድ ባለ ስልጣናት ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ሀይል በስራ ላይ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ጀመሩ፡፡

ሐዋ.5፡34-39ን አንብቡ፡፡ ገማልያል እንዴት አድርጎ ነው በዛ ሸንጎ መሐል ሐዋሪያትን ከመግደል እንዲታቀቡ ያሳመናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሸንጎውን የተቆጣጠሩት ሰዱቃውያን ሲሆኑ ፊሪሳውያንም በሸንጎ መሐል አነስ ያለ ስልጣን ነበራቸው፡፡ ገማልያል ደግሞ ፈሪሳዊ ሲሆን የህግ ዶክተር ነበር፡፡ በአይሁድ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሰው ሲሆን ‹‹ረቢ›› (የኔ መምህር) ብለው ከሚጠሩት ይልቅ ‹‹ራባን›› (የኛ መምህር) ብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ ጳውሎስ ደግሞ ከሱ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር (ሐዋ.22፡3)፡፡

ገማልያልም በእስራኤል ቀደምት ታሪክ ውስጥ ተከስተው ስለነበሩ ሁለት የአመጽ እንቅስቃሴዎች በማውሳት የተፈጠረውን ግርግርና ያፈሩትን ተከታዮች ብዛት በማስታወስ ተናገረ፡፡ ቢሆንም የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች ሲገደሉ ተከታዮቻቸውም ተበታትነዋል፡፡ ከዚህ ታሪክ ላይ ማስተላለፍ የፈለገው ነገር ቢኖር የክርስትያኖች እንቅስቃሴ መነሻው ሰዋዊ ከሆነ ፈጥኖ ይከስማል፡፡ በሌላ አባባል ሐዋሪያት እንዳረጋገጡት መነሻው መለኮታዊ ከሆነ እንዴት ልትቋቋሙት ይቻላችኃል? ብሎ ነው ምክሩን የለገሳቸው፡፡ ሐዋሪያቱም ተገረፉና ዳግም በየሱስ ስም እንዳይሰብኩ ታዘዙ፡፡

ይህ ታሪክ ስለ መልካም አማካሪ አስፈላጊነትና አጋዥነት ምን ይነግረናል? ምንም ያህል ለመስማት የማንሻው ነገር ቢሆንም ምክርን ለመቀበል ክፍት መኆንን የምንማረው እንዴት ነው?

ሐምሌ 13
Jul 20
ሐምሌ 13

ተጨማሪ ጥናት፡


‹‹እኛ ጌታችን በዚህ ለማገልገል መጥቶ የነበረውን በኋላም አደራ ሰጥቶ የሄደውን የእርሱን ንብረት ለመጠበቅና መሻቱን እንድንፈጽም አምኖ የሰጠን መጋቢዎች ነን፡፡ ወደ ሰማይ ተመልሶ ሲያርግ ሐላፊነቱን የተወልን ለኛ ነው፡፡ እኛም የእርሱን መመለስ በንቃት እንድንጠብቅ ይፈልግብናል፡፡ ለተጣለብን አደራ ታማኞች እንሁን በድንገት ሲመጣ አንቀላፍተን እንዳያገኘን፡፡ ›› Ellen G.white, Testimonies for the church vol.8, P.37

‹‹ሰዎች ስለገቡት ስለት ቅዱስነትና ለእግዚአብሄር ቃል ስለገቡት ነገር ሊጨነቁ ይገባል፡፡ እንደነዚህ አይነት ቃል ኪዳኖች ሰው ከሰው ጋር እንደሚያደርጋቸው እንኳን አስገዳጅ ተደርገው አይቆጠሩም፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል የተገባው ለእግዚአብሄር ስለሆነ ቅድስናውና አስገዳጅነቱ ይቀንሳል? ክርስቲያኖች በህግ አስገዳጅነት ጥላ ስር ባለመደረጉ የገቡትን ቃል ሳያከብሩ ማለፍ አለባቸውን? ከየትኛውም ህግና ደንብ ይልቅ ለእግዚብሄር የገባነው ቃል ኪዳን የበለጠ ያስገድደናል፡፡›› Ellen G.white comments, The SDA Bible Commentry, Vol.6,1056

1.

2.

3.

4.

5.


የመወያያ ጥያቄዎች



ከብዙ ነገሮች መካከል የሱስ ሁለት ቅርሶችን ለደቀመዛመርቱ ትቶላቸው ሄደ ፡፡ የርሱን በቅርብ መገለጥ እንዲጠባበቁና አለማቀፋዊ ተልእኮአቸውን እንዲያከናውኑ፡፡ እንዴት ነው እነዚህ ሁለት ነገሮች በተልእኳችን እና ወንጌልን ለአለም ለመስበክ በተጠራነው ጥሪ ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉት?

አንድ ሰው ሲናገር ‹‹የሱስ ዛሬ እንደሚመጣ አስበን ልንዘጋጅ ነገር ግን ስራችንን ስንሰራ (የቤተክርስቲያንን ተልእኮ )ደግሞ መቶ አመት ቆይቶ እንደሚመጣ ማሰብ አለብን›› ብሏል፡፡ ከዚህ አባባል ላይ የምናገኘው ጥበብ ምንድነው?

በህይወት ጥሪያችንስ ውስጥ ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው እንዴት ነው?

የየሱስ ህይወት፣ሞት፣ትንሳኤ እና ዳግም ምጻት የስብከታችን ማዕከል መሆን ያለበት ለምንድነው?ደግሞ እንዲህ ብላችሁ እስቲ አስቡት ከዚሀ ውጪ ሌላ ምን የምስራች ልንናገር እንችላለን?

ከሐናንያና ሰጲራ ታሪክ የሰውን ልብ ማወቅ (መልካምም ይሁን ክፉ) ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ምን እንማራለን?

የዘመኑ ገማልያል ናቸው ብላችሁ የምታስቧቸው ሰዎች እነማን ናቸው?

ወይም እርስዎ ገማልያል የተጫወተውን ሚና ለመጫወት የሚያስችል ስፍራ ላይ ነዎት? በክፍል ውይይታችሁ ወቅት መልካም ምክርን መቀበልም ሆነ መስጠት ያመጣውን በጎ ነገር ምሳሌን በመጥቀስ ተነጋገሩ፡፡ ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን?