የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ሰኔ 23-29

አንደኛ ትምህርት

Jun 30- July 6


ምስክሮቼ ትሆናላችሁ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተለቱትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሐዋ.1፡6-8፣ሉቃስ 24፡25፣ ሉቃስ 24፡44-48፣ ዘዳ.19፡15፣ ሐዋ.1፡9-26፣ ምሳሌ 16፡33፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ፡-‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌም፤ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡›› (ሐዋ.1፡8)

በ ምድር የነበረው የየሱስ ተልዕኮ አበቃ፡፡ እግዚአብሄር ወዲያውኑ መንፈስ ቅዱሱን በመላክ የደቀ መዛሙርቱን ስራ በድንቅና ተአምራት በማጀብና በማጠናከር እስከ አለም ዳርቻ የመድረስ ጥረታቸውን ሊያግዝ ነው፡፡ የሱስ ሁልጊዜ በስጋ አብሮአቸው መሆን አይችልም፡፡ በስጋ መገለጡ ከአለም አቀፉ ተልዕኮ አንፃር በአካል ውሱን እንዲሆን ማድረጉ እንዳለ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ እንዲመጣ ደግሞ የእርሱ ወደ ላይ ማረግና በሰማይ መክበር አስፈላጊ ነበር፡፡ እስከ የሱስ ትንሳኤ ድረስ ደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ይህንን አልተረዱም፡፡ ሁሉንም ነገር ትተው ሲከተሉት እርሱ የፖለቲካ ነጻ አውጪያቸው በመሆን አንድ ቀን ሮማያውያንን ከቄያቸው ጠራርጎ በማስወጣትና የዳዊትን መንግስት በሟቋቋም እስራኤልን ወደ ቀድሞ ክብርዋ ይመልሳታል ብለው ተማምነው ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር ማሰብ ለእነርሱ ቀላል አልነበረም፡፡ የሱስ በሐዋ. ሥራ1 ላይ በስተመጨረሻ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተላለፈው መመሪያ ዋና ጉዳይ ይህ ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ የተስፋ ቃል የተሰጠው በዚህ አውድ (ወንጌልን በማዳረስ) ነው፡፡ ምእራፉ ስለ የሱስ ወደ ሰማይ መመለስና ቀዳሚዋ ቤተክርስቲያን ራስዋን እንዴት ለጴንጤቆስጤ ቀን እንደዘጋጀች ያወሳል፡፡ የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለሰኔ 30 ሰንበት ይዘጋጁ፡፡

ሰኔ 24
Jul 01

የእስራኤል መታደስ


በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መሲሁ የተነገሩ ሁለት ትንቢቶች አሉ፡- አንዱ መሲሁ ንጉስ ሆኖ ለዘላለም እንደሚገዛ የሚናገር ሲሆን (መዝ.89፡3-4፣35-37፣ኢሳ.9፡6-7 ፣ህዝ.37፡25፣ ዳን. 2፡44፣ 7፡13-14) ሌላኛው ደግሞ ለአለም ህዝቦች ኃጢያት ሲል ስለሚሞተው መሲህ የሚተርከው ነው(ኢሳ.52፡13- 53፡12፣ ዳን.9፡26)፡፡ እንደነዚህ ያሉ ትንቢቶች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም ፡፡ በመሲሁ አገልግሎት ውስጥ በቅደም ተከተል ስለሚከናወኑ ሁለት ክፍሎች ማለትም በቅድሚያ እንደሚሰቃይ በመቀጠል ግን ንጉስ እንደሚሆን አመላካች የሆኑ ትንቢቶች ናቸው (ሉቃስ 17፡2425፣24፡25-26)፡፡ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ አይሁዶች ችግር ስለ መሲሁ ይጠባበቁ የነበረው በአንዱ ገፅታ ብቻ መሆኑ ነበር፡፡ ንጉስ የሚሆነው መሲህ የፖለቲካ ነጻ አውጫቸው ሆኖ የመምጣቱ ተስፋ መጥቶ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት ያለውን ትንቢት እንዳያስተውሉ ጋርዷቸው ነበር፡፡

ደቀ መዛሙርቱም ቀድመው የተናገሩት መሲሁ ይነግስልናል የሚለውን ሀሳብ ነበር፡ ፡ የሱስ መሲህ ስለመሆኑ በሚገባ አምነው ተቀብለዋል (ማቴ.16፡16-20) ፡፡ አልፎ አልፎም የሱስ በዙፋኑ በሚቀመጥበት ጊዜ ማን በቀኙ ወይም በግራው እንደሚቀመጥ አንስተው ይከራከሩ ነበር፡፡ የሱስ ስለሚጠብቀው የወደፊት እጣ ፈንታ በማንሳት ቢያስጠነቅቃቸውም እነርሱ ግንምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ ስለዚህም በሞተ ጊዜ ግራ ተጋብተው እጅጉን ተስፋ ቆረጡ፡፡ በሌላ አባባል ያሰቡት እንዲህ ነበር ‹‹እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር›› (ሉቃስ 24፡21) ፡፡ ሐዋ. ሥራ 1፡6ን ያንብቡ፡፡ ይህ ጥያቄ እስካሁን ስላላስተዋሉት ጉዳይ ምን የሚያሳየን ነገር አለው? የሱስ በሐዋ. ሥራ 1፡7 ላይ ምን ምላሽ ሰጣቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የየሱስ ሞት የደቀ መዛሙርቱን ተስፋ ያመከነ እንደሆነ ቢያመላክትም ትንሳኤው ደግሞ ተስፋቸውን አነቃቅቶ በከፍተኛ ደረጃ ከፖለቲካ ጭቆና ነጻ የመውጣት ተስፋቸው እንዲያንሰራራ አደረገ፡፡ የየሱስ ትንሳኤ መሲሁ በስተመጨረሻ የራሱን መንግስት እንደሚያቋቁም ጠንካራ ማሳያ ነው ብሎ መደምደም ትክክለኛ አስተሳሰብ መሠለ፡፡ ነገር ግን የሱስ ለጥያቄአቸው ቀጥተኛ የሆነ ምላሽ አልሰጣቸውም፡፡ ከደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ጀርባ ስላለው ስለማይቀረው መንግስቱ መምጣት እየተቃወመ አልነበረም፣እያፀደቀውም አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር የጊዜ ውሳኔ የእርሱ ብቻ ስለሆነና ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ሊደርስበት የሚችለው እውቀት ስላልሆነ ጉዳዩን በእንጥልጥል ተወው፡፡

ሉቃስ 24፡25ን ሲያነቡ የደቀመዛሙርቱ እውነተኛ ችግር ምን ሆኖ አገኙት? መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረን በተቃራኒ እኛ ማመን የምንፈልገውን ብቻ ማመን ቀላል የሚሆንልን ለምንድን ነው? ከዚህ ወጥመድ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?



ሰኔ 25
Jul 02

የደቀ መዛሙርቱ ተልዕኮ


ሐዋ. ሥራ 1፡8ን ያንብቡ፡፡ በትንቢት የተሰጠውን ሃሳብ ለራስ ፍላጎት ከመተርጎም ይልቅ ደቀመዛሙርቱ ምን እንዲያደርጉ ነበር የታዘዙት?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በዚህ ክፍል ውስጥ ስለደቀመዛሙርቱ ተልእኮ የሚናገሩ አራት ወሳኝ ነጥቦች አሉ፡፡

1. የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ፡- መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ህዝቦች መካከል ለመስራት ሁሌም ዝግጁ ነው፡፡ ነብያትም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በልዩ ሁኔታ እንደሚፈስ ተናግረው ነበር (ኢሳ.44፡3፣ ኢዩኤል 2፡28-29) ፡፡ የሱስ ራሱ ወደ ምድራዊ አገልግሎቱ ከመግባቱ በፊት በመንፈስ ቅዱስ እንደ መቀባቱ በአገልግሎቱም መንፈስ ቅዱስ በስራ ላይ ነበር (ሉቃስ 4፡18-21) ፡፡ ነገር ግን የሱስ ወደ ሰማይ እስኪያርግ ድረስ በይፋ ስራውን አልጀመረም ነበር (ዮሐ.7፡ 39፣ ሐዋ.2፡33) ፡፡

2. የመስካሪው ሚና፡- ምስክርነት የአይን እማኝ ስራ ነው፡፡ ደቀመዛመርቱ ለዚህ ምስክርነት ሙሉ በሙሉ የበቁ ነበሩ (ሐዋ.1፡21-22፣ 4፡20ን ከ1ዮሐ.1፡ 1-3ጋር ያነፃፅሩ) ፡፡ስለዚህ ከየሱስ ጋር የነበራቸውን የህይወት ልምምድ ለአለም እንዲያጋሩ ይህ ተልእኮ ተሰጣቸው፡፡

3. የተልእኮው እቅድ፡-ደቀመዛመርቱ በቅድሚያ በየሩሳሌም ከዛም በይሁዳና በሰማርያ በስተመጨረሻም እስከ አለም ዳርቻ ድረስ መመስከር ነበረባቸው፡፡ እቅዱም እየሰፋ የሚሄድ ነበር፡፡ እየሩሳሌም ለአይሁድ እምነት ማዕከላዊ ስፍራ ነበረች፤ የሱስም የተኮነነውና የተሰቀለው በዚህ ስፍራ ነበር፡፡ ይሁዳና ሰማርያ ደግሞ የሱስ ሄዶ ያገለገለባቸው የጎረቤት ክልሎች ነበሩ፡፡ ደቀመዛመርቱ በነዚህ ስፈራዎች ብቻ እንዲወሰኑ አልተጠሩም፤የተልእኳቸው ጥግ መላው አለምን የሚያዳርስ ነውና፡፡

4. የተልእኮው አካሄድ ፡- በብሉይ ኪዳን ጊዜ ሌሎች ሕዘቦች ወደ እግዚአብሄር እንዲመጡ ይጠበቅባቸው ነበር (ኢሳ. 2፡1-5ንይመልከቱ) ፤ እስራኤላውያን አልነበሩም እግዚአብሄርን ወደ ሌሎች ህዝቦች ‹‹የሚወስዱት››፡፡ ጥቂቶች (ለምሳሌ ዮናስ) ወደ ሌሎች መሄዳቸው ይህን መሰረታዊ ህግ አይቃረንም፡፡አሁን ግን እቅዱ የተለየ ነው ፡ ፡ እየሩሳሌም ያኔም ማዕከላዊ ስፍራ ነበረች፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ብቻ ቆይተው ሥር እንዲሰዱ ሳይሆን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ተንቀሳቅሰው እንዲመሰክሩ ተጠሩ፡፡ ሉቃስ 24፡44-48ን ያንብቡ፡፡ ደቀመዛሙርቱ መስበክ የሚገባቸው መሰረታዊ መልእክት ምን ነበር?

የሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለአርባ ቀናት ከደቀመዛመርቶቹ ጋር ቆይቷል (ሐዋ.1፡ 3)፡፡ በሐዋ.1፡6 ላይ የጠየቁት ጥያቄ ብዙ መረዳት እንዳልነበራቸው ቢያመለክትም የሱስ ስለ እግዚአብሄር መንግስት ሁኔታ ብዙ እውነቶችን ይገልፅላቸው እንደነበር መገመት አይከብድም፡፡ ስለተነገሩት ትንቢቶች የሚያውቁ ቢሆንም ከመስቀሉና ባዶ ከሆነው መቃብሩ በፈነጠቀው አዲስ ብርሃን አማካኝነት ነገሮችን በግልጽ ማየት ቻሉ፡ ፡ (ሐዋ.3፡17-19ን ይመልከቱ)፡፡

ሰኔ 26
Jul 03

ዳግም ይመጣል


ሐዋ.1፡9-11ን ያንብቡ፡፡ሉቃስ የክርስቶስን እርገት እንዴት አድርጎ ነው የገለፀው? ሁለቱ መላእክት ለነርሱ የተናገሩት ንግግር አስፈላጊነት ምንድነው? (ዘዳ.19፡15ን ተመልከቱ)፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሉቃስ ስለ የሱስ ወደላይ ማረግ የገለጸው በአጭሩ ነው፡፡ የሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ እየባረካቸው አብሮአቸው ቆይቶ ነበር (ሉቃስ 24፡51)፡፡ ከዛ ወደ ሰማይ ተወሰደ፡፡ ሁኔታው የተገለጸው የሰው አይን ያየውን ሁኔታ መግለጽ በሚችለው ቋንቋ እንጂ ክስተቱ ከዚህም በላይ አስገራሚነበር፡፡ የሱስ ይህንን ምድር ለቆሲሄድበአይን እንዲታይ ወደላይ ከመውጣት ሌላ መንገድ አልነበረም፡፡ የክርስቶስ እርገት እግዚአብሄር ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ሀይሉ ካደረጋቸው ተዓምራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህ ሉቃስ በፃፈው ሀሳብ ውስጥ (‹‹ወደ ላይ ተወሰደ››ሐዋ.1፡9) በሚለው አገላለፅ ተገልጧል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ አገላለጽ እዚህ ብቻ የተጠቀሰ ቢሆንም በግሪኩ የመጽሐፍ ቅጂ በብሉይ ኪዳን ውስጥ (The Septuagint) በተደጋጋሚ ተጠቅሶዋል፡፡ ሁሉም እግዚአብሄር ራሱ ያደረጋቸውን ድርጊቶች(ተዓምራት) የሚገልፁ ሲሆኑ ይህም አብ ራሱ የሱስን ከሞት እንዳስነሳው ሁሉ ወደ ሰማይም እንደወሰደው ይነግረናል (ሐዋ.2፡24፣32፤ ሮሜ 6፡4፤10፡9)፡፡ የሱስ በደመና ከተሰወረ በኋላ ነጫጭ ልብስ ለብሰው በደቀ መዛመርቱ አጠገብ ስለ ነበሩት ሁለት ሰዎች ሉቃስ በሐዋርያት ስራ ላይ ብቻ ፅፏል፡፡ አገላለፁ በሌላ ስፍራ መላእክቱ አንጸባራቂ ልብስ ለብሰው ከመገለጣቸው ክስተት ጋር የሚመሳሰል ነው (ሐዋ.10፡30፤ዮሐ.20፡12)፡፡የመምጣታቸው ምክንያት ሲሄድ ያዩት የሱስ ወደ ላይ እንደወጣ እንደዚያው ዳግም እንደሚመለስ ለደቀ መዛመርቱ ለማረጋገጥ ነበር፡፡ የሱስ ‹‹እያዩት›› ወደ ላይ እንደወጣ የሚተርክልን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ብቻ ነው (ሐዋ.1፡9)፡፡

ስለዚህ እያዩት ወደ ላይ ማረጉ እያዩት ተመልሶ እንደሚመለስ ማረጋገጫ ሆኗቸዋል፤ይህም ‹‹በኃይልና በታላቅ ክብር›› (ሉቃስ 22፡27)በደመና ይሆናል፡፡ ‹‹አይን ሁሉ ያየዋል›› (ራዕይ 1፡7) ተብሎ ስለተፃፈ በስውር የሚከናወን ነገር የለም፡ ፡ ሲመለስም ብቻውን አይሆንም (ሉቃስ9፡26፤2ተሰ.1፡7) የዳግም ምፃቱ ክብር መጀመርያ ሲያርግ ከነበረው ክብር በብዙ ይልቃልና፡፡ የዳግም መፃቱን እውነታነትና ተስፋ እንዴት አድርገን ነው ሁልጊዜ ከአእምሯችን እንዳይጠፋ አድርገን ለመያዝ መማር የምንችለው?ይህ ታላቅ እውነታ የህይወት ክፍሎቻችንን ማለትም በገንዘባችን፤ ቅድሚያ በምንሰጠው ነገርና በግብረገብ ምርጫችን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድርብን የሚገባው እንዴት ነው?

ሰኔ 27
Jul 04

ለጴንጤቆስጤ ቀን መዘጋጀት


በሐዋ.1፡7-8 ላይ የሱስ ሲመልስ ጊዜን በተመለከተ ምንም ያለው ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከንግግሩ የምንረዳው ነገር ቢኖር መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ደቀመዛመርቱም ተልእኮአቸውን ሲፈጽሙ እርሱ ዳግም ይመለሳል (ማቴ.24፡14)፡ ፡መላእክቱም ቢሆኑ ሲናገሩ (ሐዋ.1፡11) የክርስቶስ መንግስት መቼ እንደምትመጣ በመግለጽ ጥያቄያቸውን አልመለሱም ነገር ግን ጊዜው እሩቅ እንደማይሆን መረዳት ይቻላል፡፡ ደቀመዛሙርቶቹ ከዛ በኋላ ‹‹በታላቅ ደስታ ወደ እየሩሳሌም ተመለሱ››(ሉቃስ 24፡52) የተባለው በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ተልእኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ታላቅ ብርታትን ሊሰጣቸው የሚገባውና በጊዜ ስሌት ተወስኖ ያልተነገረው የየሱስ ዳግም ምጻት ተስፋ መጨረሻው በደጅ ስለመሆኑ ያመላክተናል፡፡ በሐዋርያት ስራ ላይ ያሉ ሌሎች ማብራሪያዎች ይህንን ሀሳብ በደንብ ይገልፃሉ፡፡ ሐዋ.1፡12-14ን ያንብቡ፡፡ በላይኛው ክፍል ውስጥ ሌሎች እነማን ነበሩ? መንፈስ ቅዱስ በነርሱ ላይ እንዲወርድ ያደረጉት ዝግጅትስ ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከደብረዘይት ተራራ በተመለሱ ጊዜ ደቀመዛርቱ ሁለት ፎቅ ባለው መኖሪያ ቤት ውስጥ በላይኛው የእንግዳ ክፍል (በላቲን ሴናኩለም) ተሰበሰቡ፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች የነበሩ ሴቶች (ሉቃስ 8፡1-3፣ 23፡49፣ 24፡1-12) እንዲሁም የኢየሱስ እናትና ወንድሞች ከደቀመዛርቱ ጋር አብረው ነበሩ፡፡

የየሱስ ወንድሞች ሲባል የኢየሱስ ታናሽ የሆኑ የዮሴፍና የማሪያም ወንድ ልጆች (ማር.6፡3) ወይም ዮሴፍ ማርያምን ከማግባቱ በፊት ከመጀመርያ ጋብቻው(ከሞተችው ሚስቱ)ያገኛቸው ልጆች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ስለ የሱስ ያላቸው መረዳት በጥርጥር የተሞላ ስለነበረ በደቀመዛመርቶቹ መካከል መገኘታቸው የሚያስደንቅ ነው (ማር.3፡21፤ዮሐ.7፡5)፡፡ የሱስ ከሞት እንደተነሳ በልዩ ሁኔታ ቀድሞ ለያዕቆብ መታየቱ (1ቆሮ.15፡7)ትልቅ ልዩነትን አምጥቶ ይሆናል፡፡ በኋላም ያዕቆብ የክርስትያኑን ማህበረሰብ በመምራት ሂደት ውስጥ ጴጥሮስን ተክቶ ሲቆም እናየዋለን (ሐዋ.12፡17፣15፡13፣21፡18፣ገላ.2፡9-12)፡፡

ያለማቋረጥ ተግተው በመፀለይ (ሐዋ.1፡14) ያለሟቋረጥ በመቅደሱ ውስጥ ምስጋናን እያቀረቡ (ሉቃስ 24፡53) በመናዘዝ ንስሐ በመግባትና ኃጢያታቸውን በማስወገድ ተጠምደው ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ወደ ክርስቶስ ምፃት እንደሚመራቸው በአእምሮአቸው ቢያስቡም የፀሎት ምላሽ ሆኖ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ለሚፈጠረው ነገር መንፈሳዊ ዝግጅት አድርገው ነበር፡፡

በየቀኑ የህይወት ምርጫዎቻችን ላይ መንፈስ ቅዱስ ስራውን እንዲሰራ ጥርጊያ መንገዱን እንዴት አድርገን ነው ልናዘጋጅለት የምንችለው?

ሰኔ 28
Jul 05

አስራ ሁለተኛው ሐዋርያ


120 አባላት ላሉትቀደምት የክርስትያን ማህበር የይሁዳ ምትክ ሊሆን የሚችለውን ሰው መምረጥ የመጀመርያው አስተዳደራዊ እርምጃ ነበር (ሐዋ.1፡15)፡፡

ሐዋ.1፡21-22ን ያንብቡ፡፡ ይሁዳን ሊተካ የሚመረጠው ሰው ሊያሟላው የሚገባው መስፈርት ምን ነበር ? ይህ ወሳኝ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የተፈለገው የትንሳኤው ምስክር ሆኖ የሚቆም ሰውነበር (ከሐዋ. ሥራ 4፡33 ጋር ያነፃጽሩ)፡፡ ትንሳኤው ስለ የሱስ መሲህነት እና ስለ ክርስትና እምነት እውነታነት ሁነኛ ማረጋገጫ ስለነበረ በጣም አስፈላጊ ነበር፡፡ ምርጫው መከናወን ያለበት በየሱስ የአገልግሎት ወቅት ከሐዋሪያት ጋር አብረው ከነበሩት መካከል መሆን ነበረበት፡፡ ጳውሎስ የሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ሳይሆን ቆየት ብሎ ብቅ ያለ ስለነበር ሐዋርያ ተብሎ ወዲያው አልተጠራም፡፡በደማስቆ መንገድ ላይ የሱስን ስለተገናኘ ግን የትንሳኤው ምስክር ይሆን ዘንድ አስችሎታል(1ቆሮ. 9፡1)፡ ፡ ‹‹እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር›› ብሎ ስለራሱ ቢናገርም (1ቆሮ.15፡8) ለሐዋሪያነት ብቁ ከመሆን አንፃር ከሌሎች ሐዋርያት ራሱን ያነሰ ያደረገ አይቆጥርም (1ቆሮ. 9፡2፣ ገላ. 2፡ 6-9)፡፡ ስለዚህ ‹‹ሐዋርያ›› የሚለው ስያሜ ከቤተክስቲያን አመራርና ኃላፊነት አንጻር የሚያካትተው አስራ ሁለቱንና ጳውሎስን ብቻ ነበር ማለት ይቻላል (ሐዋ.1፡25-26)፡ ፡ ነገር ግን ጠቅለል ባለ መልኩ ቃሉ መልዕክተኛና ወኪል የሚል ትርጉም እንዳለው አድርገን ስናስብ መልእክቱን ለተሸከሙ ሌሎች የወንጌል ሰራተኞች መገለጫም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል(ሐዋ.14፡4፣14፤ገላ.1፡19)፡፡

ሐዋ.1፡23-26ን ያንብቡ፡፡ ማቲያስ የተመረጠው እንዴት ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ማቲያስን የመረጡበት መንገድ እንግዳ ቢሆንም ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ እጣ መጣል አንድን ውሳኔ ለመወሰን የሚያገለግል ሂደት ነበር(ለምሳሌ ዘሌ.16፡5-10፣ ዘሁ.26፡ 55)፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምርጫው ከሁለት እኩል በሆነ ሁኔታ መስፈርቱን ከሚያሟሉ ሰዎች መካከል እንጂ ወደማይታወቅ ውጤት ለመምራት አልነበረም፡፡ አማኞችም የሚታየው ውጤት የፈቃድ መግለጫ እንዲሆን ወደ እግዚአብሄር ፀልየዋል(ከምሳሌ16፡ 33 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ውሳኔው ስህተት ተብሎ ክርክር እንደተነሳ የሚያመላክት ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ከጴንጤቆስጤ ቀን በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ቀጥተኛ ምሪት ስለነበረ እጣ የመጣሉ ሂደት አስፈላጊነት አከተመ (ሐዋ.5፡3፤11፡15-18፤13፡2፤16፡6-9)፡፡ አንድ ሰው ወደ እርስዎ መጥቶ‹‹እግዚአብሄር ለህይወቴ ያለውን ፈቃድ እንዴት አድርጌ ማወቅ እችላለሁ?›› ብሎ ቢጠይቅዎ ምላሽዎ ምን ይሆን? ለምን?

ሰኔ 29
Jul 06

ተጨማሪ ጥናት፡-


‹‹በጴንጤቆስጤ ቀንና ፓሮሲያ (ዳግም ምፃት) መካከል ያለው ጊዜ (ይነስም ይብዛም) አለማቀፋዊቷ ቤተክርቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልታ ተልእኮዋን የምትፈጽምበት ጊዜ ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች የሱስ በመጀመርያ ምፃቱ ወቅት ምን እንዳከናወነ በመናገር ሰዎች ንስሃ ገብተው ለዳግም ምጻቱ በመዘጋጀት እንዲያምኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ “እስከ አለም ዳርቻ ድረስ” (ሐዋ. 1፡8) ‹‹እስከ ፍፃሜ ጊዜ ድረስ›› ምስክሮቹ እንዲሆኑ ተጠርተዋል፡፡ … ሁለቱን ጥጎች እስክንደርስ ሥራችንን ለማቋረጥ ነፃነት አልተሰጠንም፡፡›› - John R.W.Stott, The Message Of Acts : The Spirit, The Church And The World (Downers Grove: Interrarsity, 1990)P.44:: ‹‹ለደቀመዛመርቱ የተሰጠው የአዳኛችን ተልዕኮ ሁሉንም አማኝ የሚያካትት ነው፡ ፡ እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ በክርስቶስ የሚያምኑትን በሙሉ ያካትታል ፡፡ ነፍሳትን የመማረክ ስራ ለተቀቡ አገልጋዮች ብቻ የተተወ አገልገሎት ነው ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ሰማያዊ መነሳሳት ለመጣለት ሰው ሁሉ የወንጌል አደራ ተጥሎበታል፡ ፡የየሱስን ህይወት ለተቀበሉ ሁሉ ሰዎችን ወደ ድነት ለመጥራት ተቀብተዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ሲባል ቤተክርስቲያን ተመስርታለች፤ ይህ የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ አምነው ቃል የገቡ ሁሉ የየሱስ የስራ ባልደረቦች ሆነው ይሳተፋሉ፡፡››- ELLEN G.WHITE THE DESIRE OF AGES,P.822.




የመወያያ ጥያቄዎች



1 ሐዋ.1፡7 የሚያስታውሰን ማር.13፡32ን ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰአት ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም፡፡›› ኤለን ጂ.ኋይት ስትናገር ‹‹ከዚህ በኋላ ጊዜን በተመለከተ ለእግዚአብሔር ህዝቦች የሚመጣ መልእክት አይኖርም፡፡ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድም ሆነ ስለ ክርስቶስ ምፃት ትክክለኛ ሰአት ልናውቅ አይቻለንም፡፡›› SELECTED MESSAGES, VOL.1,P.188:: እዚሁ ላይ ስታክልም ስለ ክርስቶስ መገለጥ ሰአቲቱን በተመለከተ መልእክት አለኝ ብሎ መናገር የሚጀምር ሰው ካለ ያ ሰው በራሱ ላይ ቀንበር እንዳደረገና የሱስ ያልሰጠውን መልእክት እያወጀ እንዳለ ይቆጠራል፡፡›› ADVENT REVIEW AND SABBATH HERALD, SEPT.12,1883 :: እንዲህ አይነቱ አገላለፅ ዛሬ ለኛ ያለው ፋይዳ ምን ያህል ነው?
2. አንድ ሰው ሲናገር ‹‹እግዚአብሄር ከጠበቆች ይልቅ ምስክሮችን ይሻል›› ብሏል ስለዚህ አባባል እርስዎ ምን ይሰማዎታል?
3.ቀዳሚ በነበረችው ቤተክርስቲያን ውስጥ የፀሎት ሚና ምን ያህል ነበር? ትልቅ ውሳኔ ለሚያሻቸው ጉዳዮች በሙሉ ፀሎት ማድረጋቸው እንዲሁ የአጋጣሚ ነገር ይመስለናል? (ሐዋ.1፡24፤8፡14-17፤9፡11-12፤10፡4፣9፣30፣13፡2-3) በህይወታችን ውስጥ ፀሎት ያለው ሚና ምንድነው?